የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w19 ሐምሌ ገጽ 25-29
  • ይሖዋ ከጠበቅኩት በላይ አትረፍርፎ ባርኮኛል

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ይሖዋ ከጠበቅኩት በላይ አትረፍርፎ ባርኮኛል
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ዓይናፋርነትን ማሸነፍ
  • በጊልያድ ያገኘሁት በጣም ጠቃሚ ትምህርት
  • ሚስዮናውያን ሆነን ስናገለግል ያገኘነው ግሩም ሥልጠና
  • በኬንያ ማገልገል
  • በኢትዮጵያ ስናገለግል ያገኘነው በረከት
  • ይሖዋ አሳድጎታል
  • በይሖዋ አገልግሎት ያገኘኋቸው ያልተጠበቁ በረከቶችና ትምህርቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2023
  • አምላክ ኃይል ስለሚሰጠን ወደኋላ አናፈገፍግም
    የይሖዋ ምሥክሮች የሕይወት ታሪኮች
  • በመላው ሕይወታችን ከታላቁ አስተማሪያችን ያገኘናቸው ትምህርቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • ይሖዋ ታማኝ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2019
w19 ሐምሌ ገጽ 25-29
ማንፍሬድ እና ጌይል ቶናክ በሠርጋቸው ዕለት

የሕይወት ታሪክ

ይሖዋ ከጠበቅኩት በላይ አትረፍርፎ ባርኮኛል

ማንፍሬድ ቶናክ እንደተናገረው

‘አቅኚ መሆን አለብኝ። ግን አቅኚነት ያን ያህል የሚያስደስት ነገር ነው?’ ብዬ አስብ ነበር። ጀርመን ሳለሁ የነበረኝን ሥራ እወደው ነበር፤ ሥራዬ እንደ ዳሬ ሰላም፣ ኢሊዛቤትቪል እና አስመራ ወዳሉ በአፍሪካ የሚገኙ ከተሞች የምግብ ሸቀጦችን ከመላክ ጋር የተያያዘ ነበር። ከበርካታ ዓመታት በኋላ በእነዚህና በሌሎች በርካታ የአፍሪካ ከተሞች ይሖዋን በሙሉ ጊዜዬ እንደማገለግል ጨርሶ አላሰብኩም ነበር!

በመጨረሻም ራሴን አሳምኜ አቅኚ ሆኜ ማገልገል ስጀምር ከጠበቅኩት ሁሉ የላቀ በረከት የሚያስገኝ በር ተከፈተልኝ። (ኤፌ. 3:20) ‘እንዴት?’ ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። እስቲ ታሪኬን ከመጀመሪያው ልንገራችሁ።

በ1939 ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ ከጥቂት ወራት በኋላ በርሊን፣ ጀርመን ውስጥ ተወለድኩ። በ1945 ጦርነቱ ሊገባደድ ሲቃረብ በርሊን ላይ ከባድ የአየር ጥቃት ይሰነዘር ጀመር። አንድ ቀን ሰፈራችን በቦምብ ስለተደበደበ እኔና ቤተሰቤ ወደ አየር ጥቃት መከለያ ሸሸን። በኋላ ላይ ግን ለደህንነታችን ስለሰጋን የእናቴ የትውልድ ቦታ ወደሆነው ወደ ኤርፈርት ሄድን።

ማንፍሬድ ቶናክ ከወላጆቹና ከእህቱ ጋር ጀርመን ውስጥ፣ በ1950 ገደማ

ከወላጆቼና ከእህቴ ጋር ጀርመን ውስጥ፣ በ1950 ገደማ

እናቴ እውነትን አጥብቃ ትፈልግ ነበር። የፈላስፎችን የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ታነብ እንዲሁም የተለያዩ ሃይማኖቶችን ትመረምር የነበረ ቢሆንም የሚያረካ ነገር አላገኘችም። በ1948 አካባቢ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ቤታችን መጡ። እናቴ ወደ ቤት እንዲገቡ ከጋበዘቻቸው በኋላ ብዙ ጥያቄዎችን ጠየቀቻቸው። ውይይት በጀመሩ አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ፣ እናቴ እኔንና ታናሽ እህቴን “እውነትን አገኘሁ!” አለችን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ እኔ፣ እናቴና እህቴ ኤርፈርት ውስጥ በሚደረጉ ስብሰባዎች ላይ መገኘት ጀመርን።

በ1950 ወደ በርሊን ተመለስን፤ በዚያም በርሊን ክሮይጽበርግ ወደሚባለው ጉባኤ መሄድ ጀመርን። በርሊን ውስጥ ወደ ሌላ አካባቢ ከተዛወርን በኋላ ደግሞ በርሊን ተምፕልሆፍ ወደሚባለው ጉባኤ ሄድን። ከጊዜ በኋላ እናቴ ተጠመቀች፤ እኔ ግን ውሳኔ ለማድረግ እያመነታሁ ነበር። ለምን?

ዓይናፋርነትን ማሸነፍ

በጣም ዓይናፋር ስለነበርኩ ብዙም መንፈሳዊ እድገት ማድረግ አልቻልኩም። ከሌሎች ጋር አገልግሎት ብወጣም ለሁለት ዓመት ያህል ለአንድም ሰው መሥክሬ አላውቅም። ለአምላክ ካደሩና ደፋር ከሆኑ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረብ ስጀምር ግን ሁኔታዎች ተለወጡ። አንዳንዶቹ በናዚ የማጎሪያ ካምፖች ወይም በምሥራቅ ጀርመን ወህኒ ቤቶች ታስረው የነበሩ ናቸው። ሌሎቹ ደግሞ ተይዘው ሊታሰሩ እንደሚችሉ እያወቁም እንኳ ጽሑፎችን ወደ ምሥራቅ ጀርመን በድብቅ ያስገቡ ነበር። የእነሱ ምሳሌ በጥልቅ ነካኝ። እነዚህ ወንድሞች ሊታሰሩ ወይም ሊገደሉ እንደሚችሉ እያወቁም እንኳ ይሖዋንና ወንድሞቻቸውን ለማገልገል ራሳቸውን ካቀረቡ እኔም ቢያንስ ዓይናፋርነቴን ለማሸነፍ ጥረት ማድረግ እንዳለብኝ ተሰማኝ።

በ1955 በተደረገ ልዩ የስብከት ዘመቻ መካፈሌ ዓይናፋርነቴን በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለማሸነፍ ረድቶኛል። ወንድም ናታን ኖር ኢንፎርማንትa ላይ በወጣ ደብዳቤ ላይ ይህ ዘመቻ፣ ድርጅቱ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ካዘጋጃቸው ትላልቅ ዘመቻዎች አንዱ እንደሚሆን ገልጾ ነበር። ሁሉም አስፋፊዎች በዘመቻው ከተካፈሉ “እስከ ዛሬ በምድር ላይ ታይቶ የማያውቅ በጣም ግሩም የምሥክርነት ወር” እንደምናሳልፍ ተናግሮ ነበር። ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል! ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ራሴን ለይሖዋ ወሰንኩ፤ ከዚያም በ1956 ከአባቴና ከእህቴ ጋር ተጠመቅን። ብዙም ሳይቆይ ግን ሌላ ከባድ ውሳኔ ተደቀነብኝ።

አቅኚነት በሕይወቴ ውስጥ ላከናውነው የምችለው ከሁሉ የተሻለ ሥራ እንደሆነ ባውቅም ውሳኔ ማድረግ ከብዶኝ የተወሰኑ ዓመታት አሳልፌያለሁ። በቅድሚያ በርሊን ውስጥ በጅምላ ንግድ እንዲሁም በአስመጪና ላኪ የሥራ ዘርፍ ሥልጠና ለማግኘት ወሰንኩ። ከዚያ በኋላ ደግሞ በሙያዬ ልምድ ማግኘት እንድችል የተወሰነ ጊዜ ለመሥራት አሰብኩ። ስለዚህ በ1961 የጀርመን ትልቋ የወደብ ከተማ በሆነችው በሃምበርግ ሥራ አግኝቼ ተቀጠርኩ። በሥራው እየተጠመድኩ ስሄድ ደግሞ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመጀመር ያሰብኩበትን ጊዜ ማራዘም ፈለግኩ። ታዲያ ውሳኔ ለማድረግ የረዳኝ ምንድን ነው?

ይሖዋ አፍቃሪ በሆኑ ወንድሞች ተጠቅሞ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ እንድሰጥ ስለረዳኝ አመስጋኝ ነኝ። አንዳንድ ጓደኞቼ በአቅኚነት ማገልገል ጀምረው ስለነበር ጥሩ ምሳሌ ሆነውኛል። በተጨማሪም በማጎሪያ ካምፕ ታስሮ የነበረ ኤርሽ ሙንት የተባለ ወንድም በይሖዋ እንድታመን አበረታታኝ። በማጎሪያ ካምፕ ውስጥ በራሳቸው የታመኑ ወንድሞች በኋላ ላይ እንደደከሙ ነገረኝ። በይሖዋ ሙሉ በሙሉ የታመኑት ግን በታማኝነት መጽናትና ለጉባኤው ዓምድ መሆን ችለዋል።

ማንፍሬድ ቶናክ በ1963

አቅኚነት በጀመርኩበት ወቅት፣ 1963

ከጊዜ በኋላ የበላይ አካል አባል ሆኖ ያገለገለው ወንድም ማርቲን ፖትጺንገርም “ከሁሉ የላቀ ሀብታችሁ ድፍረት ነው!” በማለት ወንድሞችን ያበረታታ ነበር። በእነዚህ ሐሳቦች ላይ ካሰላሰልኩ በኋላ ሥራዬን አቆምኩና ሰኔ 1963 አቅኚነት ጀመርኩ። በወቅቱ ላደርገው የምችለው ከሁሉ የተሻለው ውሳኔ ይህ ነበር! አቅኚ ከሆንኩ ከሁለት ወር በኋላ ልዩ አቅኚ ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ ይህ ግብዣ ሲቀርብልኝ ሌላ ሥራ መፈለግ እንኳ አልጀመርኩም ነበር። ከጥቂት ዓመታት በኋላ ደግሞ ይሖዋ ፈጽሞ ያልጠበቅኩትን ነገር አደረገልኝ። በጊልያድ ትምህርት ቤት 44ኛው ክፍል ገብቼ እንድማር ተጋበዝኩ።

በጊልያድ ያገኘሁት በጣም ጠቃሚ ትምህርት

በጊልያድ ካገኘኋቸው በጣም ጠቃሚ ትምህርቶች አንዱ “የአገልግሎት ምድባችሁን ለመተው አትቸኩሉ” የሚለው ነው፤ በተለይ ወንድም ናታን ኖር እና ወንድም ላይመን ስዊንግል ይህን ነጥብ አጉልተውታል። የተመደብንበት ቦታ አስቸጋሪ ቢሆንም በአገልግሎታችን እንድንጸና አሳስበውናል። ወንድም ኖር እንዲህ አለን፦ “ትኩረት የምታደርጉት በምን ላይ ነው? በተመደባችሁበት ቦታ ባለው አቧራ፣ ተባይና ድህነት ላይ ነው? ወይስ በዛፎቹ፣ በአበቦቹና ደስተኛ በሆኑት ሰዎች ላይ ታተኩራላችሁ? ለሰዎቹ ፍቅር አዳብሩ!” አንድ ቀን ወንድም ስዊንግል፣ አንዳንድ ወንድሞች በአገልግሎት ምድባቸው ቶሎ ተስፋ የሚቆርጡት ለምን እንደሆነ እያብራራ ሳለ እንባ ተናነቀው። ራሱን ለማረጋጋት ንግግሩን ማቋረጥ አስፈልጎት ነበር። ይህ በጣም ስለነካኝ ክርስቶስንም ሆነ ታማኝ ወንድሞቹን የሚያሳዝን ነገር ላለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አደረግኩ።—ማቴ. 25:40

ማንፍሬድ ቶናክ፣ ክሎድ ልንዚ እና ሃይንርሽ ዴንቦስተል በሚስዮናዊነት እንዲያገለግሉ በተመደቡበት በሉቡምባሺ፣ ኮንጎ፣ 1967

እኔ፣ ክሎድና ሃይንርሽ በሚስዮናዊነት እንድናገለግል በተመደብንበት በሉቡምባሺ፣ ኮንጎ፣ 1967

ምድባችን ሲነገረን አንዳንድ ቤቴላውያን የተመደብነው የት እንደሆነ ጠየቁን። አንዳንዶቹ ተማሪዎች ምድባቸውን ሲነግሯቸው ቤቴላውያኑ የሚያበረታታ ሐሳብ ይሰነዝሩ ነበር። እኔ የተመደብኩት “ኮንጎ (ኪንሻሳ)” መሆኑን ስነግራቸው ግን ሁሉም ጸጥ አሉ፤ ከዚያም “ኮንጎ? ይሖዋ ከአንተ ጋር ይሁን!” አሉኝ። በዚያ ወቅት ኮንጎ (ኪንሻሳ) ውስጥ ስለሚካሄደው ጦርነትና የእርስ በርስ ውጊያ በዜና ብዙ ይወራ ነበር። እኔ ግን ትኩረት ያደረግኩት በጊልያድ ባገኘኋቸው ትምህርቶች ላይ ነበር። መስከረም 1967 ከተመረቅን ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔ፣ ሃይንርሽ ዴንቦስተል እና ክሎድ ልንዚ ወደ ኮንጎ ዋና ከተማ ወደ ኪንሻሳ አቀናን።

ሚስዮናውያን ሆነን ስናገለግል ያገኘነው ግሩም ሥልጠና

ኪንሻሳ ከደረስን በኋላ ለሦስት ወር ያህል ፈረንሳይኛ ተማርን። ከዚያም በኮንጎ ደቡባዊ ክፍል፣ በዛምቢያ ድንበር አቅራቢያ ወደምትገኘው ወደ ሉቡምባሺ (ቀደም ሲል ኢሊዛቤትቪል ትባል ነበር) በረርን። በዚያም በከተማዋ መሃል በሚገኝ የሚስዮናውያን ቤት መኖር ጀመርን።

በሉቡምባሺ በሚገኙት በብዙዎቹ አካባቢዎች ምሥራቹ ስላልተሰበከ ለአብዛኞቹ ነዋሪዎች እውነትን ለመጀመሪያ ጊዜ መናገር መቻላችን አስደስቶን ነበር። ብዙም ሳይቆይ ልናስጠናቸው ከምንችለው በላይ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች አገኘን። በተጨማሪም ለመንግሥት ባለሥልጣናት እና ለፖሊሶች እንሰብክ ነበር። ብዙዎቹ ለአምላክ ቃልና ለስብከቱ ሥራችን ጥልቅ አክብሮት ነበራቸው። ሕዝቡ በዋነኝነት የሚናገረው ስዋሂሊ ስለነበር እኔና ክሎድ ልንዚ ይህን ቋንቋም ተማርን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ በስዋሂሊ ቋንቋ በሚመራ ጉባኤ እንድናገለግል ተመደብን።

ብዙ አስደሳች ጊዜያት ብናሳልፍም ተፈታታኝ ሁኔታዎችም አጋጥመውናል። መሣሪያ የታጠቁ የሰከሩ ወታደሮችና ጠብ የሚፈልጉ ፖሊሶች በሐሰት በመወንጀል ብዙ ጊዜ ያንገላቱን ነበር። አንድ ቀን በሚስዮናውያን ቤት የጉባኤ ስብሰባ እያደረግን ሳለ የታጠቁ ፖሊሶች በድንገት ገቡና ወደ ማዕከላዊው ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን፤ በዚያም መሬት ላይ እንድንቀመጥ ያደረጉን ሲሆን የለቀቁን ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ ነበር።

በ1969 ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሆኜ እንዳገለግል ተመደብኩ። በወረዳዬ ውስጥ ወደ አንዳንድ አካባቢዎች ለመሄድ በረጃጅም ሣሮች የተሸፈኑ መስኮችን ማቋረጥና በጭቃ መንገዶች ላይ ረጅም ርቀት መጓዝ ነበረብኝ። ከምጎበኛቸው መንደሮች በአንዱ ውስጥ አንዲት ዶሮ ከነጫጩቶቿ የምታድረው አልጋዬ ሥር ነበር። ዶሮዋ ገና ጀምበር ሳይወጣ የምታሰማው ኃይለኛ ጩኸት ይቀሰቅሰኝ እንደነበር ትዝ ይለኛል። ምሽት ላይ እሳት ካነደድን በኋላ ዙሪያውን ከብበን ከወንድሞች ጋር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የምናደርገውን አስደሳች ጭውውት አልረሳውም።

በዚያ ካጋጠሙኝ እጅግ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አንዱ ኪታዋላb የተባለውን ንቅናቄ የሚደግፉ ሐሰተኛ ወንድሞችን መጋፈጥ ነበር። ከዚህ ንቅናቄ አባላት አንዳንዶቹ ወደ ጉባኤዎቹ ሰርገው በመግባት የኃላፊነት ቦታ ይዘው ነበር። “እንደተደበቀ ዓለት” ከሆኑት ከእነዚህ ሰዎች ብዙዎቹ፣ እውነተኛ ወንድሞችና እህቶች ባደረጉት ጥረት ተጋልጠዋል። (ይሁዳ 12) ውሎ አድሮ ይሖዋ ጉባኤዎችን ያነጻ ሲሆን ይህም አስደናቂ እድገት እንዲኖር መንገድ ከፍቷል።

በ1971 በኪንሻሳ በሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ እንዳገለግል ተመደብኩ፤ በዚያም በተለያዩ ክፍሎች ውስጥ እሠራ ነበር፤ ለምሳሌ ከደብዳቤ ልውውጥ፣ ከጽሑፍ ትእዛዝ እንዲሁም ከአገልግሎት ዘርፍ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን አከናውን ነበር። መሠረተ ልማት ብዙም ባልተስፋፋበት ትልቅ አገር ውስጥ ሥራውን ማደራጀት የምችልበትን መንገድ በቤቴል ተምሬያለሁ። በአየር የምንልካቸው መልእክቶች አንዳንድ ጊዜ ወደ ጉባኤዎች ለመድረስ ወራት ይወስድባቸዋል። መልእክቶቹ ከአውሮፕላን ወርደው ጀልባ ላይ ከተጫኑ በኋላ ጀልባዎቹ የሚያደርጉት ጉዞ ሳምንታት ሊፈጅ ይችላል፤ ምክንያቱም ውኃው በእምቦጭ አረም በመሸፈኑ ጀልባዎቹ ለመጓዝ ይቸገራሉ። እነዚህና ሌሎች ችግሮች ቢኖሩም ሥራው መከናወን ችሏል።

ወንድሞች በጥቂት ገንዘብ ትላልቅ ስብሰባዎችን እንዴት እንደሚያደራጁ መመልከቴ አስገርሞኛል። በምስጥ ኩይሳ መድረክ ይሠራሉ፤ ረጃጅም ሣሮችን ደግሞ እንደ ግድግዳ ይጠቀሙባቸዋል፤ እንዲሁም እነዚህን ሣሮች ጠቅልለው በማሰር መቀመጫ ያዘጋጃሉ። ቀርከሃን እንደ ቋሚ አድርገው ይጠቀሙ እንዲሁም በሸምበቆ ጣሪያ እና ጠረጴዛ ይሠሩ ነበር። በሚስማር ምትክ ደግሞ የዛፍ ልጥ ይጠቀማሉ፤ ልጡን በቀጫጭኑ በመሰንጠቅ ለማያያዣነት ይጠቀሙበታል። እነዚያ ወንድሞችና እህቶች አስቸጋሪ ሁኔታዎችን እንዴት በብልሃት ይወጡ እንደነበር ሳስብ በጣም ያስደንቀኛል። ለእነሱ ልዩ ፍቅር አለኝ። በሌላ ቦታ እንዳገለግል ስመደብ ከእነሱ መለየት በጣም ከብዶኝ ነበር!

በኬንያ ማገልገል

በ1974 በናይሮቢ፣ ኬንያ ወደሚገኘው ቅርንጫፍ ቢሮ ተዛወርኩ። የኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ በአቅራቢያው ባሉ አሥር አገሮች የሚከናወነውን የስብከት እንቅስቃሴ ይከታተል ስለነበር ብዙ ሥራ ነበረን፤ ከእነዚህ አገሮች በአንዳንዶቹ ሥራችን ታግዶ ነበር። እነዚህን አገሮች በተለይ ደግሞ ኢትዮጵያን እንድጎበኝ በተደጋጋሚ እላክ ነበር። በኢትዮጵያ ያሉት ወንድሞቻችን በዚያ ወቅት ስደትና ከባድ ፈተናዎች ያጋጥሟቸው ነበር። ብዙዎቹ ጭካኔ የተሞላበት እንግልት ደርሶባቸዋል እንዲሁም ወህኒ ወርደዋል፤ የተገደሉም አሉ። ይሁን እንጂ ወንድሞች ከይሖዋ ጋር ያላቸው ወዳጅነት እንዲሁም እርስ በርሳቸው የነበራቸው ጥሩ ግንኙነት በታማኝነት እንዲጸኑ ረድቷቸዋል።

በ1980 በሕይወቴ ውስጥ አስደሳች ለውጥ አጋጠመኝ፤ በዚህ ዓመት ከጌይል ማተሰን ጋር ትዳር መሠረትኩ። ካናዳዊት ከሆነችው ከጌይል ጋር በጊልያድ አብረን ተምረናል። ከተመረቅን በኋላም ደብዳቤ እንጻጻፍ ነበር። ጌይል በቦሊቪያ ሚስዮናዊ ሆና ታገለግል ነበር። ከ12 ዓመታት በኋላ ኒው ዮርክ ውስጥ በድጋሚ ተገናኘን። ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኬንያ ውስጥ ተጋባን። ጌይልን በጠንካራ መንፈሳዊነቷ እንዲሁም ባሏት ነገሮች የምትረካ በመሆኗ በጣም አደንቃታለሁ። አሁንም ድረስ የምትደግፈኝ ውድና አፍቃሪ አጋሬ ናት።

የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባል ሆኜ ከማከናውነው ሥራ በተጨማሪ በ1986 በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንዳገለግል ተመደብኩ። እኔና ጌይል በዚህ ሥራ ስንካፈል በኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር ያሉ በርካታ አገሮችን ጎብኝተናል።

ማንፍሬድ ቶናክ በአስመራ (ኤርትራ) በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ንግግር ሲሰጥ፣ 1992

በአስመራ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ንግግር ስሰጥ፣ 1992

በ1992 በአስመራ (ኤርትራ) ትልቅ ስብሰባ ለማካሄድ ዝግጅት ስናደርግ ያሳለፍነውን ጊዜ አልረሳውም፤ በወቅቱ በዚያ አካባቢ ሥራችን አልታገደም ነበር። የሚያሳዝነው ለስብሰባው ማግኘት የቻልነው ቦታ፣ ከውጭ ሲያዩት የማያምር ውስጡ ደግሞ የባሰ የሚያስጠላ መጋዘን ነበር። የስብሰባው ቀን ሲደርስ፣ ወንድሞች ይህን መጋዘን ይሖዋን ለማምለክ የሚመጥን ዓይነት ቦታ እንዲሆን ለማድረግ እንዴት እንዳስዋቡት ስመለከት ገረመኝ። ብዙ ቤተሰቦች የሚያማምሩ ጨርቆች በማምጣት ደስ የማይሉትን ነገሮች በሙሉ ሸፍነዋቸው ነበር። በዚህ መንገድ፣ 1,279 ተሰብሳቢዎች የተገኙበት በጣም አስደሳች ስብሰባ አደረግን።

በጉብኝት ሥራ ላይ በነበርንበት ወቅት በየሳምንቱ በተለያዩ ቦታዎች ስለምናርፍ ሁኔታውን መልመድ ተፈታታኝ ነበር። አንድ ሳምንት በባሕር ዳርቻ ላይ በሚገኝ የሚያምር ቪላ ውስጥ አርፈን ነበር፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ የሠራተኞች ካምፕ ውስጥ ባለ የቆርቆሮ ቤት ውስጥ አርፈናል፤ በዚህ ቦታ መጸዳጃ ቤቱ የሚገኘው ከ100 ሜትር በላይ ርቆ ነበር። ሆኖም ያገለገልነው የትም ይሁን የት ከሁሉ በላይ የምናስታውሰው ቀናተኛ ከሆኑ አቅኚዎችና አስፋፊዎች ጋር በአገልግሎት ተጠምደን ያሳለፍናቸውን አስደሳች ቀናት ነው። ቀጣዩ ምድባችን ሲነገረን በጣም የምንወዳቸውን ብዙ ወዳጆቻችንን ትተን መሄድ ከብዶን ነበር።

በኢትዮጵያ ስናገለግል ያገኘነው በረከት

በ1980ዎቹ መገባደጃ እና በ1990ዎቹ መጀመሪያ አካባቢ፣ በኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር በነበሩ አንዳንድ አገሮች ውስጥ ሥራችን ሕጋዊ እውቅና አገኘ። በዚህም የተነሳ በእነዚህ አገሮች ውስጥ ቅርንጫፍ ቢሮዎችና የአገር ቢሮዎች ተቋቋሙ። በ1993 በአዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ በሚገኘው ቢሮ እንድናገለግል ተመደብን፤ በዚህ አገር ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ሥራችን በድብቅ ሲከናወን ከቆየ በኋላ ሕጋዊ እውቅና ማግኘታችን ነበር።

ማንፍሬድ እና ጌይል ቶናክ በኢትዮጵያ፣ በ1996

በኢትዮጵያ ገጠራማ አካባቢዎች በጉብኝት ሥራ ላይ ሆነን፣ 1996

ይሖዋ በኢትዮጵያ ያለውን ሥራ ባርኮታል። በርካታ ወንድሞችና እህቶች በአቅኚነት አገልግሎት ተሰማርተዋል። ከ2012 ወዲህ በየዓመቱ፣ ከ20 በመቶ በላይ የሚሆኑት አስፋፊዎች የዘወትር አቅኚዎች ሆነው አገልግለዋል። በተጨማሪም በቲኦክራሲያዊ ትምህርት ቤቶች አማካኝነት አስፈላጊው ሥልጠና እየተሰጠ ሲሆን ከ120 የሚበልጡ የስብሰባ አዳራሾች ተገንብተዋል። በ2004 የቤቴል ቤተሰብ አዲስ ወደተገነባ ሕንፃ ተዛወረ፤ በዚያው ግቢ ውስጥ የሚገኘው የትላልቅ ስብሰባዎች አዳራሽም ለወንድሞች በረከት ሆኗል።

ባለፉት ዓመታት እኔና ጌይል በኢትዮጵያ ካሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር የቅርብ ወዳጅነት መሥርተናል። ፍቅራቸውና ደግነታቸው በጣም እንድንወዳቸው አድርጎናል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንዳንድ የጤና እክሎች ስላጋጠሙን ወደ ማዕከላዊ አውሮፓ ቅርንጫፍ ቢሮ መዛወር አስፈልጎናል። በዚህ ያሉት ወንድሞች ፍቅራዊ እንክብካቤ የሚያደርጉልን ቢሆንም በኢትዮጵያ ያሉት ውድ ወዳጆቻችን በጣም ይናፍቁናል።

ይሖዋ አሳድጎታል

ይሖዋ ሥራውን እንዴት እንደሚያሳድገው ተመልክተናል። (1 ቆሮ. 3:6, 9) ለምሳሌ ያህል፣ በኮንጎ መዳብ ማውጫ ውስጥ ለሚሠሩ ሩዋንዳውያን ለመጀመሪያ ጊዜ በመሠከርኩበት ወቅት በሩዋንዳ አንድም አስፋፊ አልነበረም። አሁን ግን በሩዋንዳ ከ30,000 በላይ የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች አሉ። በ1967 በኮንጎ (ኪንሻሳ) 6,000 ገደማ አስፋፊዎች ነበሩ። አሁን 230,000 ገደማ የይሖዋ ምሥክሮች የሚገኙ ሲሆን በ2018 በመታሰቢያው በዓል ላይ ከአንድ ሚሊዮን የሚበልጡ ሰዎች ተገኝተዋል። በአንድ ወቅት በኬንያ ቅርንጫፍ ቢሮ ሥር በነበሩት አገሮች ውስጥ ያሉት አስፋፊዎች አጠቃላይ ቁጥር ደግሞ ከ100,000 በላይ ሆኗል።

ማንፍሬድ እና ጌይል ቶናክ በአሁኑ ወቅት

ከ50 ከሚበልጡ ዓመታት በፊት ይሖዋ በተለያዩ ወንድሞች ተጠቅሞ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንድገባ ረድቶኛል። አሁንም ቢሆን ከዓይናፋርነት ጋር የምታገል ቢሆንም በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመንን ተምሬያለሁ። በአፍሪካ ያሳለፍኩት ሕይወት ትዕግሥት እና ባለኝ መርካትን አስተምሮኛል። እኔና ጌይል፣ ግሩም የእንግዳ ተቀባይነት መንፈስ ያላቸውን፣ ከባድ ችግሮችን በጽናት የተወጡትንና በይሖዋ የሚታመኑትን ውድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እናደንቃቸዋለን። ይሖዋ ላሳየኝ ጸጋ በጣም አመስጋኝ ነኝ። በእርግጥም ይሖዋ ከጠበቅኩት ሁሉ በላቀ መንገድ ባርኮኛል።—መዝ. 37:4

a ከጊዜ በኋላ የመንግሥት አገልግሎታችን ተብሏል፤ አሁን ደግሞ ክርስቲያናዊ ሕይወታችንና አገልግሎታችን—የስብሰባው አስተዋጽኦ በተባለው ጽሑፍ ተተክቷል።

b “ኪታዋላ” የሚለው መጠሪያ የመጣው “መቆጣጠር፣ መምራት ወይም መግዛት” የሚል ትርጉም ካለው የስዋሂሊ ቃል ነው። ኪታዋላ፣ ከቤልጅየም ቅኝ ግዛት ነፃ ለመውጣት የሚደረግ ፖለቲካዊ ንቅናቄ ነበር። የኪታዋላ ቡድኖች የይሖዋ ምሥክሮች ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች ይወስዱ፣ ያጠኑና ያሰራጩ ነበር፤ በተጨማሪም ፖለቲካዊ አመለካከታቸውን፣ በአጉል እምነት ላይ የተመሠረቱ ልማዶቻቸውን እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደለው አኗኗራቸውን ትክክል ለማስመሰል የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን አጣምመው ያቀርቡ ነበር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ