‘ይሖዋ ሕዝቡን አይጥልም’
“የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፣ እግዚአብሔርም ከሁሉ ያድናቸዋል።”— መዝሙር 34:19
1, 2. (ሀ) ዛሬ ይሖዋ ሕዝቡን እየባረከ ያለው እንዴት ነው? (ለ) ብዙ ክርስቲያኖች ምን ዓይነት ሁኔታዎች ይገጥሟቸዋል? ምን ጥያቄዎችስ ይነሣሉ?
በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ መሠረት የይሖዋ አገልጋዮች የሚኖሩት በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው። (2 ቆሮንቶስ 12:1-4) የይሖዋ ምሥክሮች በፍቅሩና በአንድነቱ ተለይቶ የሚታወቅ ዓለም አቀፍ የወንድማማች ኅብረት ክፍል ናቸው። (ዮሐንስ 13:35) ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነት ስፋትና ጥልቀት ያለው እውቀት አግኝተዋል። (ኢሳይያስ 54:13) በይሖዋ መንፈሳዊ ድንኳን ውስጥ የማደር መብት በማግኘታቸው ምንኛ አመስጋኞች ናቸው!— መዝሙር 15:1
2 በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ያሉ ሁሉ ከመንፈሳዊ ብልጽግናው ተካፋይ ናቸው፤ ይሁን እንጂ አንዳንዶች አንፃራዊ የሆነ ሰላምና እርጋታ አግኝተው ሲኖሩ ሌሎቹ ደግሞ በአንድ ወይም በሌላ መልኩ መከራ ይደርስባቸዋል። ብዙ ክርስቲያኖች ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅና ምንም የተስፋ ጭላንጭል በሌለው አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ሲፈጠሩ ተስፋ መቁረጣችን አይቀርም። (ምሳሌ 13:12) የደረሰብን ችግር የአምላክ ሞገስ እንደሌለን የሚያሳይ ማስረጃ ነውን? ይሖዋ ለአንዳንዶቹ ክርስቲያኖች ልዩ ከለላ እየሆነ ሌሎቹን ችላ ብሏቸዋል ማለት ነውን?
3. (ሀ) ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ ለሚደርሱት መከራዎች ተጠያቂ ነውን? (ለ) የታመኑ የይሖዋ አገልጋዮች እንኳ ሳይቀሩ መከራዎች የሚደርሱባቸው ለምንድን ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ በማለት መልሱን ይሰጣል:- “ማንም ሲፈተን:- በእግዚአብሔር እፈተናለሁ አይበል፤ እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) ይሖዋ የሕዝቦቹ ጠባቂና ተንከባካቢ ነው። (መዝሙር 91:2-6) “እግዚአብሔር ሕዝቡን አይጥልም።” (መዝሙር 94:14) ይህ ማለት ግን የታመኑ አገልጋዮቹ መከራ አይደርስባቸውም ማለት አይደለም። ያለንበት ዓለም የነገሮች ሥርዓት የሚተዳደረው ፍጽምና በሌላቸው ግለሰቦች ነው። ብዙዎቹ ምግባረ ብልሹዎች ሲሆኑ ጥቂቶቹ ደግሞ ጭራሽ ክፉዎች ናቸው። አንዳቸውም ቢሆኑ ጥበብ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ዞር አይሉም። ይህም በሰው ልጅ ላይ ብዙ መከራ እንዲደርስ ምክንያት ሆኗል። የይሖዋ ሕዝቦች የሰው ልጅ አለፍጽምናና ክፋት የሚያስከትለው መዘዝ ሳይነካቸው መኖር እንደማይችሉ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።— ሥራ 14:22
ታማኝ ክርስቲያኖች መከራ እንደሚደርስባቸው ያውቃሉ
4. ሁሉም ክርስቲያኖች በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እስከኖሩ ድረስ ምን ነገር ሊጠብቁ ይችላሉ? ለምንስ?
4 የኢየሱስ ተከታዮች የዓለም ክፍል ባይሆኑም የሚኖሩት በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ነው። (ዮሐንስ 17:15, 16) መጽሐፍ ቅዱስ ከዚህ ዓለም በስተጀርባ ያለው ኃይል ሰይጣን ዲያብሎስ መሆኑን ይገልጻል። (1 ዮሐንስ 5:19) በመሆኑም መቼም ይሁን መቼ ሁሉም ክርስቲያኖች ከበድ ያለ ችግር እንደሚገጥማቸው ሊጠብቁ ይችላሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ይህንን በአእምሮው በመያዝ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በመጠን ኑሩ ንቁም፣ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና፤ በዓለም ያሉት ወንድሞቻችሁ ያን መከራ በሙሉ እንዲቀበሉ እያወቃችሁ በእምነት ጸንታችሁ ተቃወሙት።” (1 ጴጥሮስ 5:8, 9) አዎን፣ መላው የክርስቲያኖች ወንድማማች ማኅበር መከራ እንደሚደርስ ሊጠብቅ ይችላል።
5. ኢየሱስ የታመኑ ክርስቲያኖችም በሕይወታቸው ውስጥ አሳዛኝ ነገሮች እንደሚገጥማቸው የገለጸው እንዴት ነው?
5 ይሖዋን በጥልቅ የምናፈቅርና ለመሠረታዊ ሥርዓቶቹ ታማኞች ብንሆንም እንኳ በሕይወታችን ውስጥ አሳዛኝ ነገሮች ይገጥሙናል። ኢየሱስ ቃሉን የሚታዘዙትንና የማይታዘዙትን ሰዎች እያነጻጸረ በተናገረበት፣ በማቴዎስ 7:24-27 ላይ ተመዝግቦ በሚገኘው ምሳሌው ውስጥ ይህንን ነገር በግልጽ አስቀምጦታል። ታዛዥ የሆኑ ደቀ መዛሙርቱን ቤቱን በዓለት ላይ ከሠራ ልባም ሰው ጋር አመሳስሏቸዋል። ቃሉን የማይታዘዙትን ደግሞ ቤቱን በአሸዋ ላይ ከሠራ ሞኝ ሰው ጋር አመሳስሏቸዋል። ከባድ ዝናብና ዓውሎ ነፋስ በመጣ ጊዜ የተረፈው በዓለት ላይ የተመሠረተው ቤት ብቻ ነበር። የልባሙም ሰው ቤት ‘ዝናብ እንደወረደበት፣ ጎርፍና ነፋስም እንደገፋው ነገር ግን እንዳልወደቀ አስተውል።’ ኢየሱስ ይህ ልባም ሰው ሁል ጊዜ ሰላምና እርጋታ አግኝቶ ይቀመጣል የሚል ዋስትና አልሰጠም። ከዚህ ይልቅ ግን ሰውዬው ልባም መሆኑ ከባዱን ዝናብና ዓውሎ ነፋስ ለመቋቋም አስችሎታል። በዘሪው ምሳሌ ውስጥም ተመሳሳይ መልእክት ተንጸባርቋል። ኢየሱስ በዚህ ምሳሌ ውስጥ ‘መልካምና በጎ ልብ’ ያላቸው ታዛዥ አገልጋዮቹ እንኳ ‘ፍሬ የሚያፈሩት በመጽናት’ እንደሆነ ተናግሯል።— ሉቃስ 8:4-15
6. ጳውሎስ እሳትን መቋቋም የሚችሉ ነገሮችን በተመለከተ በሰጠው ምሳሌ ውስጥ እንደ እሳት ባለው ፈተና ውስጥ የሚያልፉት እነማን ናቸው?
6 ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ሲጽፍ ፈተናን ለመቋቋም ስለሚያስችሉን ዘላቂ ባሕርያት ለማስረዳት በምሳሌያዊ አነጋገር ተጠቅሟል። እንደ ወርቅ፣ ብርና ክቡር ድንጋይ ያሉት እሳትን መቋቋም የሚችሉ ነገሮች አምላካዊ ባሕርያትን ያመለክታሉ። (ከምሳሌ 3:13-15 እና ከ1 ጴጥሮስ 1:6, 7 ጋር አወዳድር።) በአንጻሩ ደግሞ ሥጋዊ የሆኑት ባሕርያት በእሳት ከሚጠፉ ነገሮች ጋር ተመሳስለዋል። ከዚያም ጳውሎስ በመቀጠል እንዲህ ብሏል:- “የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል፤ በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፣ የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል።” (1 ቆሮንቶስ 3:10-14) እዚህም ላይ ቢሆን መጽሐፍ ቅዱስ ሁላችንም በሆነ መንገድ ፈታኝ ሁኔታ እንደሚደርስብን መናገሩ ነው።
7. በሮሜ 15:4 መሠረት ቅዱሳን ጽሑፎች በፈተናዎች ለመጽናት የሚረዱን እንዴት ነው?
7 መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መከራ ስለደረሰባቸውና አንዳንዴም ለረጅም ጊዜ መጽናት ስላስፈለጋቸው የአምላክ ታማኝ አገልጋዮች የሚገልጹ በርካታ ዘገባዎች ይገኛሉ። ይሁን እንጂ ይሖዋ አልጣላቸውም። ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ሐሳብ የተናገረው እንዲህ ዓይነት ምሳሌዎችን በአእምሮው ይዞ ሳይሆን አይቀርም:- “በመጽናትና መጻሕፍት በሚሰጡት መጽናናት ተስፋ ይሆንልን ዘንድ አስቀድሞ የተጻፈው ሁሉ ለትምህርታችን ተጽፎአልና።” (ሮሜ 15:4) እስቲ ከአምላክ ጋር የቀረበ ግንኙነት እያላቸው ብዙ መከራ የደረሰባቸውን የሦስት ሰዎች ምሳሌ ተመልከት።
ከመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች የምናገኘው ትምህርት
8. ይሖዋ በዮሴፍ ላይ ምን እንዲደርስ ፈቅዷል? ለምን ያህል ጊዜስ?
8 የያዕቆብ ልጅ ዮሴፍ ከልጅነቱ አንስቶ የይሖዋን ሞገስ ያገኘ ሰው ነበር። ያም ሆኖ ግን ያለጥፋቱ ብዙ መከራዎች ተፈራርቀውበታል። የገዛ ወንድሞቹ አፍነው በመውሰድ የጭካኔ ድርጊት ፈጽመውበታል። ወደማያውቀው አገር በባርነት ተሸጧል፤ እዚያም በሐሰት ተከሶ “በግዞት” እንዲቀመጥ ተደርጓል። (ዘፍጥረት 40:15) “እግሮቹም በእግር ብረት ደከሙ፣ እርሱም በብረት ውስጥ ገባ።” (መዝሙር 105:17, 18) ዮሴፍ በባርነትና በእስር በነበረባቸው ጊዜያት ይሖዋ ነፃ እንዲያወጣው ደጋግሞ እንደጠየቀ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሖዋ በተለያዩ መንገዶች ያበረታው የነበረ ቢሆንም ለ13 ዓመታት ባሪያ ወይም እስረኛ ሆኖ ኖሯል።— ዘፍጥረት 37:2፤ 41:46
9. ዳዊት ለበርካታ ዓመታት ምን ነገር በጽናት መቋቋም አስፈልጎታል?
9 የዳዊትም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ እስራኤልን የሚያስተዳድር ብቃት ያለው ሰው በመረጠበት ጊዜ “እንደ ልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ” ሲል ተናግሯል። (ሥራ 13:22) ዳዊት በይሖዋ ዓይን ሞገስ ያገኘ ሰው ቢሆንም ብዙ መከራ ደርሶበታል። ለበርካታ ዓመታት በምድረ በዳ፣ በዋሻ፣ በጉድጓድ ውስጥና በባዕድ አገር ተደብቆ ሲኖር ሕይወቱ አደጋ ላይ ነበር። እንደ አውሬ እየታደነ በተስፋ መቁረጥና በፍርሃት ተሰቃይቷል። የሆነ ሆኖ ከይሖዋ ባገኘው ኃይል ጸንቷል። ዳዊት ከራሱ ተሞክሮ በመነሣት:- “የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው፤ እግዚአብሔር ከሁሉ ያድናቸዋል” በማለት በትክክል መናገር ችሏል።— መዝሙር 34:19
10. በናቡቴና በቤተሰቡ ላይ ምን ከባድ መከራ ደርሶባቸዋል?
10 በነቢዩ በኤልያስ ዘመን በእስራኤል ውስጥ የሐሰት አምላክ ለሆነው ለበኣል ጉልበታቸውን ያላንበረከኩት 7,000 ሰዎች ብቻ ነበሩ። (1 ነገሥት 19:18፤ ሮሜ 11:4) ከእነዚህ ሰዎች አንዱ ናቡቴ ሳይሆን አይቀርም። ይህ ሰው የሚዘገንን ግፍ ተፈጽሞበታል። ንጉሡንና አምላክን ሰድቧል ተብሎ ተዋርዷል። ጥፋተኛ ነህ ተብሎ በንጉሣዊው ቤተሰብ ትእዛዝ መሠረት በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ተፈረደበት፤ ደሙንም ውሾች ላሱት። ልጆቹ ሳይቀሩ ተገደሉ! ይሁን እንጂ ናቡቴ ከዚህ ሁሉ ክስ ነፃ ነበር። በእርሱ ላይ የመሰከሩትም ሰዎች ሐሰተኞች ነበሩ። ይህ ሁሉ ነገር ንጉሡ የናቡቴን የወይን እርሻ በእጁ እንዲያስገባ ስትል ንግሥቲቷ ኤልዛቤል የሸረበችው ሴራ ነበር።— 1 ነገሥት 20:1-19፤ 2 ነገሥት 9:26
11. ሐዋርያው ጳውሎስ በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ ስለተጠቀሱት የታመኑ ወንዶችና ሴቶች ምን ይነግረናል?
11 ዮሴፍ፣ ዳዊትና ናቡቴ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት መከራ የደረሰባቸው ብዙ የታመኑ ወንዶችና ሴቶች መካከል ሦስቱ ብቻ ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ በተለያዩ ዘመናት ስለነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች ጠቅለል አድርጎ ጽፏል። እንዲህ አለ:- “መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ፤ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ፣ ተፈተኑ፣ በመጋዝ ተሰነጠቁ፣ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ፣ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ፤ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ፣ በዋሻና በምድር ጒድጓድ ተቅበዘበዙ።” (ዕብራውያን 11:36-38) ይሁን እንጂ ይሖዋ አልጣላቸውም።
ይሖዋ መከራ ለሚደርስባቸው ሰዎች ያስባል
12. ዛሬ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ ከሚደርሱት መከራዎች መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው?
12 ዛሬ ስላሉት የይሖዋ ሕዝቦችስ ምን ማለት ይቻላል? በድርጅት ደረጃ መለኮታዊ ጥበቃ እንደምናገኝና እነዚህን የመጨረሻ ቀናትም ሆነ ታላቁን መከራ ያለ ችግር እንደምናልፍ ልንጠብቅ እንችላለን። (ኢሳይያስ 54:17፤ ራእይ 7:9-17) ይሁን እንጂ በግለሰብ ደረጃ ሁሉም ሰው “ጊዜና አጋጣሚ” የሚያመጣው ነገር እንደሚያገኘው እንገነዘባለን። (መክብብ 9:11 NW) በዛሬው ጊዜ መከራ እየደረሰባቸው ያሉ ብዙ የታመኑ ክርስቲያኖች አሉ። አንዳንዶች የከፋ ድህነት ይገጥማቸዋል። መጽሐፍ ቅዱስ በመከራ ላይ ስላሉ ‘ወላጆች የሌሏቸው ክርስቲያን ልጆችና መበለቶች’ ይናገራል። (ያዕቆብ 1:27) ሌሎች ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ፣ በጦርነት፣ በወንጀል፣ በሥልጣን ብልግና፣ በሕመም ወይም በሞት ምክንያት መከራ ይደርስባቸዋል።
13. በቅርቡ ምን አሳዛኝ ተሞክሮዎች ሪፖርት ተደርገዋል?
13 ለምሳሌ ያህል የይሖዋ ምሥክሮች የመጠበቂያ ግንብ ቅርንጫፍ ቢሮዎች በ1996 ለአስተዳደር አካሉ በላኩት ሪፖርታቸው ላይ አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች የሙጥኝ በማለታቸው ምክንያት በአሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ በእስር ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል። በደቡብ አሜሪካ በሚገኝ አገር ውስጥ የሽምቅ ተዋጊዎች በአንድ አካባቢ የሚገኙ በመቶዎች የሚቆጠሩ ምሥክሮች አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ በማስገደዳቸው ምክንያት በዚያ የነበሩት ሦስት ጉባኤዎች ፈርሰዋል። በምዕራብ አፍሪካ በሚገኝ አንድ አገር አንዳንድ ምሥክሮች በዙሪያቸው በተነሣ ቀላል ግጭት ምክንያት ተገድለዋል። በመካከለኛው አሜሪካ በምትገኝ አንድ አገር የደረሰው ዓውሎ ነፋስ ያስከተለው ከባድ ጥፋት በዚያ የሚገኙትን ወንድሞች አስቸጋሪ የኢኮኖሚ ሁኔታ ይበልጥ የከፋ እንዲሆን አድርጎታል። የድህነትና የምግብ እጥረት ችግር በሌለባቸው አካባቢዎች ደግሞ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሌሎች ነገሮች የአንዳንዶችን ደስታ ይቀንሱባቸው ይሆናል። ብዙዎች ደግሞ በዛሬው ጊዜ ያለው የኑሮ ተጽዕኖ እንዲዝሉ አድርጓቸዋል። ሌሎች እንዲሁ የመንግሥቱን ምሥራች በሚሰብኩበት ጊዜ ሰዎች በሚያሳዩት ግዴለሽነት የተስፋ መቁረጥ ስሜት ሊያድርባቸው ይችላል።
14. (ሀ) ከኢዮብ ምሳሌ ምን እንማራለን? (ለ) የሚያስጨንቅ ነገር በሚገጥመን ጊዜ አፍራሽ አስተሳሰብ ከመያዝ ይልቅ ምን ማድረግ ይገባናል?
14 እነዚህ ነገሮች የአምላክን ሞገስ እንዳጣን የሚያረጋግጡ ምልክቶች እንደሆኑ ተደርገው ሊታዩ አይገባም። የኢዮብን ሁኔታና የደረሱበትን የተለያዩ መከራዎች አስታውስ። “እንከን የሌለበትና ቅን” ሰው ነበር። (ኢዮብ 1:8 NW) ኤልፋዝ ኃጢአት ሠርተሃል ብሎ ሲወነጅለው ኢዮብ ምንኛ አዝኖ ይሆን! (ኢዮብ ምዕራፍ 4, 5, 22) መከራ የሚደርስብን በሆነ መንገድ ይሖዋን ስላሳዘንነው ወይም ደግሞ ከእኛ ላይ በረከቱን ስለወሰደ ነው ብለን ለመደምደም መቸኮል አይገባንም። መከራ በሚደርስብን ጊዜ አፍራሽ አስተሳሰብ መያዝ እምነታችንን ሊያዳክመው ይችላል። (1 ተሰሎንቄ 3:1-3, 5) የሚያስጨንቅ ነገር ሲገጥመን ምንም ዓይነት ሁኔታ ቢከሰት ይሖዋና ኢየሱስ ከጻድቁ ጎን እንደሚቆሙ ማሰላሰላችን ከሁሉ የተሻለ ይሆናል።
15. ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ ስለሚደርሰው መከራ በጥልቅ እንደሚያስብ እንዴት እናውቃለን?
15 ሐዋርያው ጳውሎስ እንደሚከተለው በማለት ማረጋገጫ ሰጥቶናል:- “ከክርስቶስ ፍቅር ማን ይለየናል? መከራ፣ ወይስ ጭንቀት፣ ወይስ ስደት፣ ወይስ ራብ፣ ወይስ ራቁትነት፣ ወይስ ፍርሃት፣ ወይስ ሰይፍ ነውን? . . . ሞት ቢሆን፣ ሕይወትም ቢሆን፣ መላእክትም ቢሆኑ፣ ግዛትም ቢሆን፣ ያለውም ቢሆን፣ የሚመጣውም ቢሆን፣ ኃይላትም ቢሆኑ፣ ከፍታም ቢሆን፣ ዝቅታም ቢሆን፣ ልዩ ፍጥረትም ቢሆን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን ካለ ከእግዚአብሔር ፍቅር ሊለየን እንዳይችል ተረድቼአለሁ።” (ሮሜ 8:35, 38, 39) ይሖዋ ስለ እኛ በጥልቅ የሚያስብ ከመሆኑም ሌላ ስለሚደርስብን መከራ ሁሉ ያውቃል። ዳዊት በስደት ላይ እያለ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና። እግዚአብሔር ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው።” (መዝሙር 34:15, 18፤ ማቴዎስ 18:6, 14) ሰማያዊ አባታችን ስለ እኛ ያስባል፤ መከራ ለሚደርስባቸውም ያዝናል። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) የደረሰብን መከራ ምንም ዓይነት ቢሆን ለመጽናት የሚያስፈልገንን ነገር ይሰጠናል።
የይሖዋ ስጦታዎች ይደግፉናል
16. ይሖዋ እንድንጸና የሚረዳንን ምን ዝግጅት አድርጎልናል? ለመጽናት የሚረዳንስ እንዴት ነው?
16 በዚህ አሮጌ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ ከመከራ ነፃ የሆነ ሕይወት እናገኛለን ብለን መጠበቅ ባንችልም ‘የተጣልን አንሆንም።’ (2 ቆሮንቶስ 4:8, 9) ኢየሱስ ለተከታዮቹ ረዳት እንደሚልክላቸው ቃል ገብቷል። እንዲህ አለ:- “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ [“ረዳት፣” NW] ይሰጣችኋል፤ እርሱም . . . የእውነት መንፈስ ነው።” (ዮሐንስ 14:15-17) ሐዋርያው ጴጥሮስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት አድማጮቹ ‘ነፃ ስጦታ የሆነውን መንፈስ ቅዱስ’ መቀበል እንደሚችሉ ተናግሯል። (ሥራ 2:38) ዛሬ መንፈስ ቅዱስ እየረዳን ነውን? አዎን! የይሖዋ አንቀሳቃሽ ኃይል እንደ “ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ እምነት፣ የውሃት፣ ራስን መግዛት” ያሉትን ድንቅ ፍሬዎች እንድናፈራ ይረዳናል። (ገላትያ 5:22, 23) እነዚህ ሁሉ በዋጋ ሊገመት የማይችል ጠቀሜታ ያላቸው ለመጽናት የሚረዱን ባሕርያት ናቸው።
17. እምነታችንንና ይሖዋን በትዕግሥት ለመጠባበቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ የሚያጠናክሩልን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች የትኞቹ ናቸው?
17 በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ አሁን የሚደርስብን መከራ ከዘላለም ሕይወት ሽልማታችን ጋር ሲወዳደር ‘ቀላልና ጊዜያዊ’ መሆኑን እንድናስተውል ይረዳናል። (2 ቆሮንቶስ 4:16-18) አምላክ ያከናወንነውን ሥራና ለእርሱ ያሳየነውን ፍቅር እንደማይረሳ እርግጠኞች ነን። (ዕብራውያን 6:9-12) በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉትን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት ስናነብ ብዙ መከራዎችን በጽናት አሳልፈው ደስተኞች እንደሆኑ የተነገረላቸው የጥንቶቹ የታመኑ አገልጋዮች ምሳሌ ያጽናናናል። ያዕቆብ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ወንድሞች ሆይ፣ የመከራና የትዕግሥት ምሳሌ የሆኑትን በጌታ ስም የተናገሩትን ነቢያትን ተመልከቱ። እነሆ፣ በትዕግሥት የጸኑትን ብፁዓን እንላቸዋለን።” (ያዕቆብ 5:10, 11) መጽሐፍ ቅዱስ በፈተናዎች ለመጽናት የሚረዳንን ‘ከወትሮው የላቀ ኃይል’ እንደምናገኝ ተስፋ ይሰጠናል። በተጨማሪም ይሖዋ በትንሣኤ ተስፋ ይባርከናል። (2 ቆሮንቶስ 1:8-10፤ 4:7) መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብና በእነዚህ ተስፋዎች ላይ በማሰላሰል እምነታችንንና አምላክን በትዕግሥት ለመጠባበቅ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ እናጠናክራለን።— መዝሙር 42:5
18. (ሀ) በ2 ቆሮንቶስ 1:3, 4 ላይ ምን እንድናደርግ ማበረታቻ ተሰጥቶናል? (ለ) ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች የመጽናናትና የብርታት ምንጭ ሊሆኑ የሚችሉት እንዴት ነው?
18 ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የክርስቲያን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እውነተኛ ፍቅር ማግኘት የምንችልበትን መንፈሳዊ ገነት አዘጋጅቶልናል። እርስ በርሳችን ለመጽናናት እያንዳንዳችን የምናበረክተው ድርሻ ይኖራል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) በተለይ ክርስቲያን የበላይ ተመልካቾች ትልቅ የመጽናኛና የብርታት ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ። (ኢሳይያስ 32:2) እነዚህ ‘የወንድ ስጦታዎች’ መከራ የደረሰባቸውን የማነጽ፣ ‘የተጨነቁትን ነፍሳት የማጽናናትና ደካሞችን የመደገፍ’ ተልእኮ ተሰጥቷቸዋል። (ኤፌሶን 4:8, 11, 12፤ 1 ተሰሎንቄ 5:14) ሽማግሌዎች የመጠበቂያ ግንብ እና ንቁ! መጽሔቶችን እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሚያወጣቸውን ሌሎች ጽሑፎች በሚገባ ሊጠቀሙባቸው ይገባል። (ማቴዎስ 24:45-47) እነዚህ ጽሑፎች የሚያስጨንቁንን ችግሮች ለመፍታት ብሎም ለመከላከል ሊረዱን የሚችሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ብዙ ምክሮችን ይዘዋል። በአስቸጋሪ ወቅቶች ጊዜ አንዳችን ሌላውን በማጽናናትና በማበረታታት ይሖዋን የምንመስል እንሁን!
19. (ሀ) አንዳንድ መከራዎችን ለማስቀረት የሚረዳን ምንድን ነው? (ለ) ከፍተኛ ትምክህት መጣል የሚገባን በማን ላይ ነው? ፈተናዎችንስ ለመቋቋም የሚረዳን ምንድን ነው?
19 ክርስቲያኖች ወደ መጨረሻዎቹ ቀናት ይበልጥ እየገባንና በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ያሉት ሁኔታዎችም እየከፉ በሄዱ መጠን ችግሮችን ለማስወገድ የተቻላቸውን ሁሉ ያደርጋሉ። (ምሳሌ 22:3) ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ፣ ጤናማ አስተሳሰብና የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ማወቅ የጥበብ እርምጃዎችን እንድንወስድ ሊረዱን ይችላሉ። (ምሳሌ 3:21, 22) አላስፈላጊ ስህተቶችን ከመሥራት ለመቆጠብ የይሖዋን ቃል እናዳምጣለን እንዲሁም እንታዘዛለን። (መዝሙር 38:4) የሆነ ሆኖ በግላችን ምንም ያህል ጥረት ብናደርግ ጨርሶ መከራ እንዳይደርስብን መከላከል እንደማንችል እናውቃለን። በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ብዙ ጻድቅ ሰዎች ከባድ መከራዎች ይደርሱባቸዋል። ይሁን እንጂ ‘ይሖዋ ሕዝቡን እንደማይጥል’ ሙሉ ትምክህት ኖሮን የሚደርሱብንን ፈተናዎች ልንቋቋም እንችላለን። (መዝሙር 94:14) በቅርቡ ይህ የነገሮች ሥርዓትም ሆነ በሥርዓቱ ውስጥ ያሉት መከራዎች እንደሚያልፉ እናውቃለን። እንግዲያውስ “ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት” እንዳንታክት ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።— ገላትያ 6:9
ምን ትምህርት አግኝተናል?
◻ መላው የክርስቲያኖች ወንድማማች ማኅበር ምን ፈተናዎች ይገጥሙታል?
◻ መከራዎች በእኛ ላይ መድረሳቸው የይሖዋን ሞገስ እንዳጣን የሚያረጋግጥ አለመሆኑን የሚያሳዩት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
◻ ይሖዋ በሕዝቦቹ ላይ ስለሚደርሰው መከራ ምን ይሰማዋል?
◻ በፈተና ለመጽናት የሚያስችሉን አንዳንዶቹ የይሖዋ ስጦታዎች ምንድን ናቸው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ዳዊት፣ ናቡቴና ዮሴፍ መከራ የደረሰባቸው ሰዎች ናቸው