ጤርጥዮስ የታመነው የጳውሎስ ጸሐፊ
ጤርጥዮስ ከባድ ሥራ ይጠብቀዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለሚገኙት መሰል ክርስቲያኖች ረጅም ደብዳቤ ለመጻፍ እርሱን እንደ ጸሐፊው አድርጎ ሊጠቀምበት ፈልጓል። ይህ ከባድ ሥራ ነበር።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ ጸሐፊ ሆኖ ማገልገል ይህን ያክል አስቸጋሪ የነበረው ለምንድን ነው? እንዲህ ዓይነቱ ሥራ የሚሠራው እንዴት ነበር? በዚያን ጊዜ ይገለገሉባቸው የነበሩት የጽሕፈት መሣሪያዎች ምንድን ናቸው?
የጥንቶቹ ጸሐፊዎች
በጥንቱ የግሪካውያንና የሮማውያን ኅብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ ዓይነት ጸሐፊዎች ነበሩ። አንዳንዶቹ በቻንስለሩ ቢሮ የሚቀመጡ የሕዝብ ባለ ሥልጣናት ሆነው በመንግሥት ጸሐፊነት ያገለግሉ ነበር። በገበያ ቦታዎች ተቀምጠው ለሕዝቡ አገልግሎት የሚሰጡ ጸሐፊዎችም ነበሩ። ባለጠጋ የሆኑት ሰዎች ደግሞ የግል ጸሐፊዎች (ብዙውን ጊዜ ባሪያዎች ናቸው) ነበሯቸው። ከዚህም ሌላ ደብዳቤ መጻፍ የፈለጉ ወዳጆቻቸውን በፈቃደኛነት የሚረዱ ሰዎች ነበሩ። ምሁሩ ኢ ራንዶልፍ ሪቻርድ እንዳሉት ከሆነ ሥራቸው ኦፊሲየላዊ ያልሆነው የእነዚህ ጸሐፊዎች ችሎታ የተለያየ ሲሆን “ስለ ቋንቋው እና/ወይም ስለ ጽሑፍ ሥርዓት ውስን እውቀት ብቻ ያላቸው አሉ፤ የዚያኑ ያህል ደግሞ ትክክለኛ፣ የተሟላና ማራኪ ደብዳቤ በአጭር ጊዜ ውስጥ የሚያዘጋጁ በሙያው የተካኑ ጸሐፊዎች አሉ።”
በጸሐፊዎች የሚጠቀሙት እነማን ነበሩ? በመጀመሪያ ደረጃ ማንበብና መጻፍ የማይችሉት ሰዎች ነበሩ። ጥንት ይጻፉ የነበሩት ብዙዎቹ የውልና የንግድ ደብዳቤዎች የሚደመደሙት ለጸሐፊው ሥራውን የሰጠው ሰው የጽሑፍ ችሎታ ስለ ሌለው እርሱ እንደጻፈለት በሚገልጽ ሐሳብ ነበር። ከግብጽ ቲቤስ የተገኘ አንድ የጥንት ደብዳቤ ጸሐፊዎች የሚቀጠሩበትን ሁለተኛ ምክንያት ይጠቁማል። አስክሊፒያደስ ለተባለ ሰው የተጻፈው ይህ ደብዳቤ በመደምደሚያው ላይ እንዲህ ይላል:- “እርሱ ሲጽፍ ዝግተኛ በመሆኑ . . . የጻፈለት የኤርማ ልጅ ኤቭሜለስ ነው።”
ሆኖም በጸሐፊዎች መጠቀም አለመጠቀማቸውን የሚወስነው የማንበብና የመጻፍ ችሎታቸው አልነበረም። የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኝ የሆኑት ጆን ኤል ማክኬንዚ እንደገለጹት ሰዎች ጸሐፊዎችን የሚጠቀሙት “የሰነዱ ሕጋዊነት እንዲጠበቅ ተጨንቀው አይመስልም፤ ከዚህ ይልቅ ውበቱን ለመጠበቅ ሲሉና ቢያንስ ቁልጭ ያለ እንዲሆን በማሰብ ነበር።” ለተማሩት ሰዎች እንኳ ሳይቀር መጻፍ አድካሚ ሥራ ነበር፤ በተለይ ደግሞ በጣም ረጅምና ዝርዝር ደብዳቤ መጻፍ በሚያስፈልግበት ጊዜ ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ምሁሩ ጄ ኤ ኤሽሊማን በጸሐፊ መጠቀም የሚችል ማንኛውም ሰው “ይህን ሥራ የጽሕፈት ሙያ ላለው ባሪያው ሰጥቶ መገላገል ያስደስተው ነበር” ብለዋል። ከዚህም በተጨማሪ የሚጠቀሙበትን የጽሕፈት መሣሪያና የሚጽፉበትን ሁኔታ ስንመለከት ሰዎች የራሳቸውን ደብዳቤ እንኳ መጻፍ ለምን እንደሚያስጠላቸው ለመረዳት ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በሰፊው ይሠራበት የነበረው መጻፊያ ደንገል ነበር። ከዚህ ተክል ግንድ ላይ እንደ ስፖንጅ ያለው የመሀለኛው ክፍል በቁመቱ በስሱ ይተለተላል። ከዚያም ትልታዩ በቁመቱ ይረበረባል። በዚህ መልክ የተሠራው ሌላው ርብራብ በመጀመሪያው ርብራብ ላይ በአግድሞሽ ቀጥ ብሎ ይደረባል። ከዚያም ሁለቱን ርብራቦች በኃይል በመጫን እርስ በርሳቸው እንዲጣበቁ ስለሚደረግ አንድ ገጽ “ወረቀት” ይወጣዋል።
በዚህ ገጽ ላይ መጻፍ ቀላል አልነበረም። በጣም ሻካራና ጭራ የበዛበት ነው። እንደ ምሁሩ አንጄሎ ፔና አባባል ከሆነ “የስፖንጅነት ባሕርይ ያላቸው የደንገሉ ክሮች ቀለሙ እንዲቅባባ በተለይ ደግሞ በቀጫጭኖቹ ትልታዮች መካከል ባሉት ጠባብ ክፍተቶች መካከል እንዲገባ ያደርጋሉ።” ጸሐፊው ሥራውን የሚሠራው እግሮቹን አጥፎ በመሬት ላይ በመቀመጥ ወረቀቱን አንድ ሰሌዳ ላይ አድርጎና በአንድ እጁ ደግፎ ሊሆን ይችላል። ተሞክሮ ከሌለው ወይም የሚጽፍበት የደንገል ወረቀት ጥራቱ ዝቅተኛ ከሆነ የላባ ወይም የመቃ ብዕሩ ደንገሉን ሊነጭበትና ወረቀቱ ሊቀደድ ወይም ጽሑፉ ተቀባይነት ሊያጣ ይችላል።
ቀለሙ የሚሠራው ጥቀርሻን ከዕጽዋት ከሚገኝ ፈሳሽ ጋር በማቀላቀል ነው። በጥፍጥፍ መልክ የሚሸጠው ቀለም ለጽሑፍ ከመዋሉ በፊት በቀለም መበጥበጫ ዕቃ ውስጥ ሆኖ በውኃ መበጥበጥ ይኖርበታል። እንደ ጤርጥዮስ ያለ ጸሐፊ ሊጠቀምባቸው ከሚችላቸው የጽሕፈት መሣሪያዎች መካከል የመቃ ብዕሩን የሚያሾልበት ቢለዋ እና የተሳሳተውን ፊደል ለማጥፋት የሚያገለግል ውኃ የተነከረ ስፖንጅ ይገኙበታል። እያንዳንዱ ሆሄ በጥንቃቄ መጻፍ ነበረበት። በመሆኑም የጽሕፈት ሥራው የሚከናወነው በዝግታ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ ችግሮች አሉት።
‘እኔ ጤርጥዮስ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ’
ለሮሜ ሰዎች ከተጻፈው ደብዳቤ መጨረሻ ላይ ከተጠቀሱት ሰላምታዎች መካከል “ይህን መልእክት የጻፍሁ እኔ ጤርጥዮስ በጌታ ሰላምታ አቀርብላችኋለሁ” ሲል የገለጸው የጳውሎስ ጸሐፊ የላከው ሰላምታ ይገኝበታል። (ሮሜ 16:22) ከዚህ ሌላ በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ ስለ ጸሐፊዎቹ በግልጽ የተጠቀሰበት ቦታ የለም።
ስለ ጤርጥዮስ ብዙም የምናውቀው ነገር የለም። ‘በጌታ’ ካቀረበው ሰላምታ ግን የታመነ ክርስቲያን ነበር ብለን መደምደም እንችላለን። ምናልባት በሮም ከነበሩት ብዙ ክርስቲያኖች የሚተዋወቅ የቆሮንቶስ ጉባኤ አባል ሳይሆን አይቀርም። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ጁሴፔ ባርባሊዮ ጤርጥዮስ ባርያ ወይም ከባርነት ነፃ የወጣ ሰው ሊሆን እንደሚችል አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል። ለምን? በመጀመሪያ ደረጃ “ጻፎች ባብዛኛው ከዚህ መደብ የሚገኙ ሲሆኑ ሌላው ምክንያት ደግሞ የላቲን ስሙ . . . በባሪያዎች ዘንድ ወይም ከባርነት ነፃ በወጡት ሰዎች ዘንድ በእጅጉ የሚዘወተር በመሆኑ ነው።” “በመሆኑም” ይላሉ ባርባግሊዮ “ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ ረጅምና አንድ ወጥ የሆነውን ደብዳቤውን በማጠናቀር ጳውሎስን ረዳው እንጂ ‘ሌላ ሥራ ያልነበረው’ ሙያተኛ ጸሐፊ አልነበረም፤ ጳውሎስን ብዙ ጊዜ ከማጥፋትና ከድካም ያዳነውን ድንቅ አገልግሎት አከናውኗል።”
በእርግጥም ጤርጥዮስ ያከናወነው ሥራ በጣም የሚደነቅ ነው። ባሮክ ኤርምያስን ስልዋኖስ ደግሞ ጴጥሮስን በተመሳሳይ ሥራ ረድተዋቸዋል። (ኤርምያስ 36:4፤ 1 ጴጥሮስ 5:12) እነዚህ ረዳቶቻቸው እንዴት ያለ ታላቅ መብት አግኝተዋል!
ለሮሜ ሰዎች መጻፍ
ለሮሜ ሰዎች የተላከው ደብዳቤ የተጻፈው ጳውሎስ በቆሮንቶስ በጋይዮስ ዘንድ በእንግድነት ተቀምጦ ሳለ ሳይሆን አይቀርም። ይህም በሐዋርያው ሦስተኛ የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት በ56 እዘአ ገደማ ነበር። (ሮሜ 16:23) ጳውሎስ ደብዳቤውን ለመጻፍ ጤርጥዮስን እንደ ጸሐፊው አድርጎ እንደተጠቀመበት እርግጠኞች ብንሆንም እንዴት እንደተጠቀመበት ግን በትክክል የምናውቀው ነገር የለም። የተጠቀመበት ዘዴ ምንም ይሁን ምን ሥራው በቀላሉ ሊሠራ የሚችል ዓይነት አልነበረም። ስለ አንድ ነገር ግን እርግጠኞች መሆን እንችላለን፤ ይኸውም እንደ ቀረው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ሁሉ ለሮሜ ሰዎች የተጻፈው ደብዳቤም “በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት” የተጻፈ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17
ይህ ደብዳቤ ተጽፎ ሲጠናቀቅ ጤርጥዮስና ጳውሎስ ከደንገል የተሠሩ በርካታ ገጾችን በመጠቀም በሺህ የሚቆጠሩ ቃላትን ጽፈው ነበር። እነዚህ ገጾች በኅዳጋቸው በኩል እርስ በርስ ተያይዘው አንድ ጥቅልል ወጥቷቸዋል። ምናልባትም ከ3-4 ሜትር ርዝማኔ ያለው ሳይሆን አይቀርም። ከዚያም ደብዳቤው በጥንቃቄ ተጠቅልሎ ታሸገ። ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ ወደ ሮም ለመሄድ ተዘጋጅታ ለነበረችው በክንክራኦስ ላለችው እህት ፌበን በአደራ ሳይሰጣት አይቀርም።—ሮሜ 16:1, 2
ከአንደኛው መቶ ዘመን ወዲህ የጽሑፍ ዝግጅት ዘዴዎች በእጅጉ ተለውጠዋል። ይሁንና አምላክ ለሮሜ ክርስቲያኖች የተጻፈው ደብዳቤ ባለፉት መቶ ዘመናት ሁሉ ተጠብቆ እንዲቆይ አድርጓል። የታመነና ታታሪ በነበረው የጳውሎስ ጸሐፊ በጤርጥዮስ ረዳትነት ለተጻፈው ለዚህ የይሖዋ ቃል ክፍል ምንኛ አመስጋኞች ልንሆን ይገባናል!