የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 8/1 ገጽ 4-6
  • ሕሊናህን ማሰልጠን የምትችልበት መንገድ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሕሊናህን ማሰልጠን የምትችልበት መንገድ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አእምሮ፣ ልብና ሕሊናህ
  • ስህተት ስንሠራ
  • “በጎ ሕሊና ይኑራችሁ”
  • ጥሩ ሕሊና ይዘህ መኖር የምትችለው እንዴት ነው?
    ‘ከአምላክ ፍቅር አትውጡ’
  • በአምላክ ፊት ጥሩ ሕሊና መያዝ
    ከአምላክ ፍቅር ሳትወጡ ኑሩ
  • ሕሊናህ በሚገባ ሠልጥኗል?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2005
  • ሕሊናችሁ አስተማማኝ መሪ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2015
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 8/1 ገጽ 4-6

ሕሊናህን ማሰልጠን የምትችልበት መንገድ

“ንጹሕ ሕሊና ምቹ ትራስ ነው።” ይህ ጥንታዊ አባባል የሚከተለውን ትልቅ ትርጉም ያለው እውነታ ጎላ አድርጎ ይገልጻል:- ሕሊናችንን ስንታዘዝ ውስጣዊ ሰላምና የሐሳብ አንድነት ይኖረናል።

ይሁን እንጂ ይህን ማድረግ የሚፈልጉት ሁሉም ሰዎች አይደሉም። አዶልፍ ሂትለር የሰውን ልጅ ሕሊና ከሚባለው ተራ ቅዠት ወይም የተሳሳተ እምነት ለማላቀቅ ቆርጦ እንደተነሳ ገልጾ ነበር። ሽብር ነግሦበት የነበረው የግዛት ዘመኑ ሰዎች ሕሊናቸውን አሽቀንጥረው ሲጥሉ ምን ያህል ጨካኝ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስፈሪ በሆነ መንገድ አመላክቷል። ያላንዳች ርኅራኄ ሰዎችን እያስገደዱ የሚያስነውሩትና የሚገድሉት በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙዎቹ ወንጀለኞችም ጭካኔያቸው ከዚህ የሚተናነስ አይደለም። ከእነዚህ ወንጀለኞች መካከል ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣ ገና ያልበሰሉ በርካታ ወጣቶችም ይገኙበታል። በዚህ አዲስ ክስተት ላይ የተካሄደውን ጥናት ይዞ የወጣ አንድ መጽሐፍ ሕሊና የሌላቸው ልጆች የሚል ንዑስ ርዕስ አውጥቷል።

አብዛኞቹ ሰዎች አረመኔያዊ ወንጀል የመፈጸም ሐሳብ ወደ አእምሯቸው ባይመጣም እንኳ ብዙዎቹ የጾታ ብልግና ሲፈጽሙ፣ ሲዋሹ ወይም ደግሞ ሲያጭበረብሩ ሕሊናቸው አይቆረቁራቸውም። ግብረ ገብነት በዓለም አቀፍ ደረጃ እያሽቆለቆለ በመሄድ ላይ ይገኛል። ሐዋርያው ጳውሎስ በእውነተኛው አምልኮ ላይ የተፈጸመውን ታላቅ ክህደት በመጥቀስ አንዳንድ ክርስቲያኖች ለዓለም ተጽዕኖ በመሸነፍ ‘ሕሊናቸው በጋለ ብረት እንደተተኮሰ ያህል ሆኖ እንደደነዘዘ’ በመግለጽ ጽፏል። (1 ጢሞቴዎስ 4:​2 የ1980 ትርጉም) በእነዚህ ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት’ ምግባረ ብልሹነት ይበልጥ አስጊ እየሆነ ሄዷል። (2 ጢሞቴዎስ 3:​1) ስለዚህ ክርስቲያኖች ሕሊናቸውን ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባቸው። ይህን ማድረግ የምንችለው ሕሊናችንን በማሰልጠንና በማጎልበት ነው።

አእምሮ፣ ልብና ሕሊናህ

ሐዋርያው ጳውሎስ “በክርስቶስ ሆኜ እውነትን እናገራለሁ፤ አልዋሽምም፤ ሕሊናዬም በመንፈስ ቅዱስ ይመሰክርልኛል” ብሏል። (ሮሜ 9:​1) ስለዚህ ሕሊና ምሥክር ሊሆን ይችላል ማለት ነው። አንድን የአኗኗር ጎዳና በመመርመር ሊቀበለው አለዚያም ደግሞ ሊያወግዘው ይችላል። ትክክል የሆነውንና ስህተት የሆነውን ነገር የመለየት ችሎታ በውስጣችን ያስቀመጠው ፈጣሪያችን ነው። ያም ሆኖ ግን ሕሊናችን ሊቀረጽና ሊሰለጥን ይችላል። ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? ትክክለኛውን የአምላክ ቃል እውቀት በመቅሰም ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “መልካሙንና ደስ የሚያሰኘውን ፍጹም የሆነውንም የእግዚአብሔርን ፈቃድ ማወቅ እንድትችሉ፣ አእምሮአችሁ ታድሶ ሕይወታችሁ ይለወጥ” ብሏል። (ሮሜ 12:​2 የ1980 ትርጉም) የአምላክ ሐሳብና ፈቃድ በአእምሮህ ውስጥ እንዲተከል ስታደርግ ሕሊናህ ይበልጥ አምላካዊ በሆነ መንገድ መሥራት ይጀምራል።

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ‘ይሖዋ አምላክንና ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲያውቁ’ ረድተዋቸዋል። (ዮሐንስ 17:​3) ያለ ክፍያ በሚያካሂዱት የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ፕሮግራማቸው አማካኝነት ይሖዋ አምላክ ጾታን፣ የአልኮል መጠጦችን፣ ጋብቻን፣ የንግድ ግንኙነቶችንና ሌሎች ብዙ ርዕሰ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለውን መሥፈርት ቅን ልብ ላላቸው ሰዎች ያስተምራሉ።a (ምሳሌ 11:​1፤ ማርቆስ 10:​6-12፤ 1 ቆሮንቶስ 6:​9, 10፤ ኤፌሶን 5:​28-33) ይህን ‘ትክክለኛ እውቀት’ መቅሰም አምላካዊ ሕሊና ለማዳበር አንድ ትልቅ እርምጃ ነው። (ፊልጵስዩስ 1:​9) እርግጥ አንድ ክርስቲያን ሕሊናው ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለገ በቂ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ካገኘ በኋላም ቢሆን ዘወትር አእምሮው የአምላክን ቃል እንዲመገብ ማድረግ አለበት።​—⁠መዝሙር 1:​1-3

ከዚህም በተጨማሪ መጽሐፍ ቅዱስ ሕሊናን ውስጣዊ ስሜቶቻችንንና መንፈሳችንን አካቶ ከያዘው ከምሳሌያዊው ልብ ጋር ያያይዘዋል። (ሮሜ 2:​15) ሕሊናችን በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ከተፈለገ አእምሮና ልብ በአንድነት ተስማምተው መሥራት አለባቸው። ይህም እንዲሁ አእምሮን በእውቀት ከመሙላት የበለጠ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። ልብህን ማለትም ውስጣዊ ስሜቶችህን፣ ፍላጎቶችህንና ምኞትህንም መቅረጽ አለብህ። ይህም በመሆኑ የምሳሌ መጽሐፍ ‘ልብህን አዘንብል፣’ ‘ልብህን አኑር’ እና ‘ልብህን ምራ’ የሚሉትን አባባሎች ይጠቀማል። (ምሳሌ 2:​2፤ 23:​19፤ 27:​23) ልብን መቅረጽ የሚቻልበት አንዱ መንገድ ቅዱሳን ጽሑፎችን በማሰብና በማሰላሰል በማብሰልሰል ነው። መዝሙር 77:​12 (የ1980 ትርጉም) “ስላደረግኸው ነገር ሁሉ አስባለሁ፤ ስለ ታላላቅ ሥራዎችህም በማሰላሰል አስታውሳለሁ” ይላል። ማሰላሰል ውስጣዊ ስሜቶቻችንንና ፍላጎቶቻችንን ለመንካት ይረዳናል።

ለምሳሌ እንደ ትምባሆ ሱስ ያለ ንጹሕ ያልሆነ ልማድ አለብህ እንበል። እንደ አብዛኞቹ ሰዎች ሁሉ አንተም በጤና ላይ ስለሚያስከትለው ጉዳት በሚገባ እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። ወዳጆችህና ቤተሰቦችህ አጥብቀው ቢወተውቱህም እንኳ ከዚህ ሱስ መላቀቅ አልቻልክም። በመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ላይ ማሰላሰልህ በዚህ ረገድ አእምሮህን ሊያጠነክርልህ የሚችለው እንዴት ነው?

ለምሳሌ ያህል በ2 ቆሮንቶስ 7:​1 ላይ በሚገኙት በሚከተሉት የጳውሎስ ቃላት ላይ ለማሰላሰል ሞክር:- “እንግዲህ፣ ወዳጆች ሆይ፣ የዚህ ተስፋ ቃል ካለን፣ በእግዚአብሔር ፍርሃት ቅድስናን ፍጹም እያደረግን ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን እናንጻ።” የእነዚህን ቃላት ትርጉም ለመረዳት ሞክር። ‘ጳውሎስ “የዚህ ተስፋ ቃል” ብሎ የገለጸው ነገር ምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። በጥቅሱ ዙሪያ ያለውን ሐሳብ ስታነብ ከላይ ከፍ ብለው ያሉት ቁጥሮች የሚከተለውን ሐሳብ እንደያዙ ትገነዘባለህ:- “ጌታ:- ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ:- እኔም እቀበላችኋለሁ፣ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ ይላል።”​—⁠2 ቆሮንቶስ 6:​17, 18

ጳውሎስ ‘ራሳችንን ከሚያረክስ ነገር እንድናነጻ’ የሰጠው ትእዛዝ አሁን የበለጠ ኃይል ያገኛል! አምላክ ‘እንደሚቀበለን’ ማለትም በእርሱ ጥበቃ ሥር እንድንሆን እንደሚያደርገን ቃል የገባልን መሆኑ ይህን ትእዛዝ እንድንፈጽም ይበልጥ ያነሳሳናል። ‘ከአምላክ ጋር ያለኝ ዝምድና በአባትና በልጅ መካከል ያለውን ዝምድና ያህል የተቀራረበ ነውን?’ ብለህ ራስህን ልትጠይቅ ትችላለህ። ጥበበኛና አፍቃሪ በሆነ አምላክ ‘ተቀባይነት ማግኘት’ ወይም መወደድ በጣም የሚያስደስት ነገር አይደለምን? በአባትና በልጅ መካከል ያለው ዝምድና ከአንተ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ መስሎ ካልታየህ አፍቃሪ አባቶች ለልጆቻቸው ያላቸውን ፍቅርና የመውደድ ስሜት የሚገልጹበትን መንገድ ተመልከት። ከዚያ በኋላ በአንተና በይሖዋ መካከል እንዲህ ዓይነት ግንኙነት እንዳለ አድርገህ አስብ! ይበልጥ በጉዳዩ ላይ ባሰላሰልክ መጠን ለእንዲህ ዓይነቱ ዝምድና ያለህ ፍላጎት እያደገ ይሄዳል።

ሆኖም የሚከተለውን ልብ በል:- ከአምላክ ጋር መቀራረብ የምትችለው ‘ርኩስ የሆነውን ነገር የማትነካ’ እስከሆነ ድረስ ብቻ ነው። የሚከተሉትን ጥያቄዎች ራስህን ጠይቅ:- ‘የትምባሆ ሱስ አምላክ ከሚያወግዛቸው “ርኩስ ነገሮች” መካከል አይደለምን? ትምባሆ ሳጨስ ራሴን ለብዙ ዓይነት የጤና ችግሮች በማጋለጥ ‘ሥጋዬን ማርከሴ’ አይደለምን? ይሖዋ ንጹሕ ወይም “ቅዱስ” አምላክ እንደመሆኑ መጠን እያወቅኩ ይህን በማድረግ ራሴን ማርከሴ በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ሊኖረው ይችላልን?’ (1 ጴጥሮስ 1:​15, 16) በተጨማሪም ጳውሎስ “መንፈስን” ወይም የአእምሮ ዝንባሌን ከሚያረክስ ነገር እንድንጠበቅ ማሳሰቡን ልብ በል። እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ:- ‘ይህ ሱስ በአስተሳሰቤ ላይ ተጽእኖ ያደርጋልን? ፍላጎቴን ለማርካት ስል ትልቅ መሥዋዕትነት እስከ መክፈል ምናልባትም ጤናዬን፣ ቤተሰቤን አልፎ ተርፎም በአምላክ ዘንድ ያለኝን አቋም አደጋ ላይ እስከ መጣል እደርሳለሁን? ለትምባሆ ያለኝ ሱስ ሕይወቴን ምን ያህል እንዲጎዳው ፈቅጄለታለሁ?’ እነዚህን ሕሊና የሚረብሹ ጥያቄዎች ራስህን መጠየቅህ ልማዱን ለመተው የሚያስችል ቆራጥነት እንደሚሰጥህ የታመነ ነው!

እርግጥ የትምባሆን ሱስ ድል ማድረግ እንድትችል የሌሎች ሰዎች እርዳታና ድጋፍ ሊያስፈልግህ ይችላል። ያም ሆኖ ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ማሰላሰልህ ሕሊናህን በማሰልጠንና በማጠንከር ራስህን ከሱስ ለማላቀቅ እንድትችል ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክትልሃል።

ስህተት ስንሠራ

ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ከፍተኛ ጥረት የምናደርግ ቢሆንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ አለፍጽምናችን ያሸንፈንና ስህተት እንሠራለን። በዚህ ጊዜ ሕሊናችን ይረብሸናል፤ ሆኖም ሕሊናችንን ችላ ለማለት እንፈተን ይሆናል። ወይም ደግሞ በጣም ተስፋ እንቆርጥና አምላክን ለማገልገል የምናደርገውን ጥረት ሁሉ እርግፍ አድርገን ለመተው እንነሳሳ ይሆናል። ይሁን እንጂ የንጉሥ ዳዊትን ሁኔታ አስታውስ። ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ከፈጸመ በኋላ ሕሊናው መታው። የተሰማውን የሕሊና ሥቃይ እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “በቀንና በሌሊት እጅህ ከብዳብኛለችና፣ እርጥበቴም ለበጋ ትኩሳት ተለወጠ።” (መዝሙር 32:​4) ዳዊት በጣም ተረብሾ ነበር! ሆኖም ይህ አምላካዊ ሐዘን ደርሶበት የነበረ መሆኑ ንስሐ እንዲገባና ከአምላክ ጋር እንዲታረቅ ገፋፍቶታል። (ከ2 ቆሮንቶስ 7:​10 ጋር አወዳድር።) ዳዊት በጣም ተጨንቆ ይቅርታ ለማግኘት ያቀረበው ልመና ከልቡ ንስሐ እንደገባ የሚያሳይ በቂ ማስረጃ ነው። ዳዊት ሕሊናውን በመታዘዙ መለወጥና በመጨረሻም ደስታውን መልሶ ማግኘት ችሏል።​—⁠መዝሙር 51

ዛሬም ተመሳሳይ ሁኔታ ሊደርስ ይችላል። አንዳንዶች ቀደም ባሉት ጊዜያት መጽሐፍ ቅዱስን ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር ያጠኑ ነበር፤ ሆኖም አኗኗራቸው ከአምላክ ከፍተኛ የአቋም ደረጃዎች ጋር እንደማይጣጣም ሲረዱ ጥናታቸውን አቁመዋል። እነዚህ ሰዎች ምናልባት ሳይጋቡ ከተቃራኒ ጾታ ጋር አንድ ላይ የሚኖሩ ወይም ደግሞ በአንዳንድ ርኩስ ልማዶች ተጠፍረው የተያዙ ሊሆኑ ይችላሉ። ሕሊናቸው በጣም ረብሿቸዋል!

አንተም በእንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምትገኝ ከሆነ ሐዋርያው ጴጥሮስ በጰንጠቆስጤ ዕለት የተናገረውን ቃል ልብ በል። የአገሩ ሰዎች የሆኑት አይሁዶች የፈጸሙትን ኃጢአት ባጋለጠ ጊዜ “ልባቸው ተነካ።” ተስፋ ቆርጠው ወደ ኋላ አላሉም፤ ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስ ንስሐ እንዲገቡ የሰጣቸውን ምክር ተቀብለው በሥራ በማዋላቸው የአምላክን ሞገስ ሊያገኙ ችለዋል። (ሥራ 2:​37-41) አንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላለህ! ሕሊናህ ሲረብሽህ እውነትን ከመተው ይልቅ ሕሊናህ ‘ንስሐ እንድትገባና እንድትመለስ’ እንዲገፋፋህ ማድረግ ይኖርብሃል። (ሥራ 3:​19) ቆራጥ ውሳኔ በመውሰድና ጥረት በማድረግ የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የሚያስችልህን ለውጥ ልታደርግ ትችላለህ።

“በጎ ሕሊና ይኑራችሁ”

“በጎ ሕሊና ይኑራችሁ” የሚለው የጴጥሮስ ምክር ስለ ይሖዋ መንገዶች ገና በመማር ላይ ላሉም ሆነ የብዙ ዓመታት ተሞክሮ ላላቸው የጎለመሱ ክርስቲያኖች ይሠራል። (1 ጴጥሮስ 3:​16) ሕሊና ፀጋ እንጂ ሸክም አይደለም። አእምሮህንና ልብህን የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ በመመገብ ሕሊናህን አሰልጥነው። ሕሊናህ ለሚሰጥህ ማስጠንቀቂያ ተገዥ ሁን። ሕሊናህን በመታዘዝ ውስጣዊ የአእምሮ ሰላም አግኝተህ ልትደሰት ትችላለህ።

ሕሊናን ማሰልጠንና መቅረጽ ቀላል ሥራ እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ይሖዋ አምላክ እንዲረዳህ መጸለይ ትችላለህ። በእሱ እርዳታ በመታገዝ አምላክን ‘በበጎ ሕሊናና ግብዝነት በሌለበት እምነት’ ማገልገል ትችላለህ።​—⁠1 ጢሞቴዎስ 1:​5

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ያለ ክፍያ የቤት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት እንዲደረግልህ የምትፈልግ ከሆነ በአካባቢህ ካለው የይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤ ጋር መገናኘት ወይም ደግሞ ለዚህ መጽሔት አዘጋጆች መጻፍ ትችላለህ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የአምላክን ቃል ማንበብና ማሰላሰል ሕሊናችንን ለማሰልጠን እንድንችል ይረዳናል

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ