መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ዘመናችን የደረሰው እንዴት ነው? ክፍል ሁለት
በሚንቀለቀለው እሳት ውስጥ ማገዶው እየተጋዘ ሲጨመር ነበልባሉ ወደ ሰማይ ይጎናል። ይሁን እንጂ ይህ ተራ እሳት አልነበረም። ቀሳውስትና አቡኖች ቆመው እያዩ በሚንበለበለው እሳት ውስጥ ይማገድ የነበረው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። ይሁን እንጂ የለንደኑ ሊቀ ጳጳስ መጽሐፍ ቅዱሶችን ለማጥፋት በማሰብ ሲሸምቱ፣ ሳያውቁት ተርጓሚው ዊልያም ቲንደል ተጨማሪ እትሞችን ማዘጋጀት የሚችልበት የገንዘብ ምንጭ እንዲያገኝ እየረዱት ነበር!
በፍልሚያው ግንባር የተሰለፉት ሁለቱም ወገኖች እንዲህ እንዲጨክኑ ያደረጋቸው ነገር ምንድን ነበር? ከዚህ ቀደም በወጣው እትም ላይ በመካከለኛው ዘመን መገባደጃ ላይ የተከናወነውን የመጽሐፍ ቅዱስ የኀትመት ሥራ ታሪክ ዳስሰን ነበር። አሁን ደግሞ የአምላክ ቃል መልእክት በኅብረተሰቡ ዘንድ ጉልህ ስፍራ ሊያገኝ የተቃረበበትን የአዲስ ዘመን መባቻ እንመለከታለን።
አንድ አቅኚ ብቅ አለ
የተከበረው የኦክስፎርድ ምሁር ጆን ዊክሊፍ በ‘አምላክ ሕግ’ ማለትም በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተመርኩዞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን የምታከናውናቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ ድርጊቶች በጥብቅ በማውገዝ ሰብኳል እንዲሁም ጽፏል። ሎላርድ በመባል የሚታወቁት ተማሪዎቹ በእንግሊዝ የገጠር ክፍሎች በሙሉ እየተዘዋወሩ ለሚሰማቸው ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በእንግሊዝኛ እንዲሰብኩ ልኳቸዋል። በ1384 ከመሞቱ በፊት መጽሐፍ ቅዱስን ከላቲን ቋንቋ በዘመኑ ይነገር ወደ ነበረው የእንግሊዝኛ ቋንቋ ለመተርጎሙ ሥራ ፈር ቀድዷል።
ቤተ ክርስቲያን ዊክሊፍን የምታጣጥልባቸው ብዙ ምክንያቶች ነበሯት። በመጀመሪያ ደረጃ ቀሳውስቱ በሚፈጽሙት የማን አለብኝነት ተግባርና በብልግና አኗኗራቸው ምክንያት ያወግዛቸው ነበር። ከዚህ በተጨማሪ ብዙዎቹ የዊክሊፍ አድናቂዎች የሚያካሂዱትን የራሳቸውን የትጥቅ ትግል ተቀባይነት እንዳለው አስመስለው ለማቅረብ የእርሱን ትምህርቶች አላግባብ ተጠቅመው ነበር። ዊክሊፍ የዓመፅ ንቅናቄዎችን የሚያራምድ ሰው ባይሆንም ቀሳውስቱ ከሞተም በኋላ እንኳ ሳይቀር ይነቅፉት ነበር።
አቡኑ አርንደል በ1412 ለሊቀ ጳጳስ ጆን 23ኛ በጻፉት ደብዳቤ ላይ “ያ መርዘኛ ጭንጋፍ ጆን ዊክሊፍ፣ በእኩይ ተግባሩ የሚታወስ የቀድሞው እባብ ልጅ፣ የክፋት ተምሳሌትና የክርስቶስ ተቃዋሚ ውላጅ” ሲሉ ጠርተውታል። አርንደል ውግዘታቸውን ሲያጠቃልሉ “የተንኮል ጽዋውን ይሞላ ዘንድ በአፍ መፍቻ ቋንቋው አዲስ የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ለማዘጋጀት ታጥቆ ተነሣ” ብለዋል። በእርግጥም የቤተ ክርስቲያን መሪዎቹን እጅግ ያንገበገባቸው ዊክሊፍ ለሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን በቋንቋቸው ለማዘጋጀት መነሳቱ ነበር።
የሆነ ሆኖ ከፍተኛ ቦታ የነበራቸው ጥቂት ግለሰቦች በአገሬው ቋንቋ የተዘጋጀውን ቅዱስ ጽሑፍ የሚያገኙበት አጋጣሚ ነበራቸው። ከእነዚህ መካከል አንዷ የወደፊቱን የእንግሊዝ ንጉሥ ሪቻርድ ዳግማዊን በ1382 ያገባችው የቦሔሚያ ተወላጅ የሆነችው አን ነበረች። ዊክሊፍ ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የተረጎማቸው የወንጌሎች ቅጂ የነበራት ሲሆን ይህንኑ ሌት ተቀን ታጠናው ነበር። አስቀድሞ በጎ አመለካከት ስለነበራት ንግሥት በሆነች ጊዜ ይህ አመለካከቷ ከእንግሊዝ ውጭ ሳይቀር ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚደረገው ትግል እመርታ እንዲያሳይ እገዛ አድርጓል። አን በቦሔሚያ በፕራግ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ወደ ኦክስፎርድ እንዲመጡ አበረታታቸዋለች። እዚያም በዊክሊፍ ሥራዎች ላይ ጥልቅ ጥናት አካሂደው አንዳንዶቹን ሥራዎቹን ይዘው ወደ ፕራግ ተመልሰዋል። የዊክሊፍ ትምህርቶች በፕራግ ዩኒቨርሲቲ ገናናነት ማግኘታቸው በዚህ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ተከታትሎ እዚያው አስተማሪ ለሆነው ለያን ሁስ ድጋፍ ሆኖታል። ሁስ ከጥንቱ የስላቮን ትርጉም በቼክ ቋንቋ ለማንበብ የሚጋብዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አዘጋጅቷል። ሁስ ያደረገው ጥረት መጽሐፍ ቅዱስ በቦሔሚያና በአካባቢው አገሮች በሰፊው ጥቅም ላይ እንዲውል አስችሏል።
ቤተ ክርስቲያን የብቀላ እርምጃ ወሰደች
ዊክሊፍና ሁስ ቤተ ክርስቲያኒቱ በተቀበለቻቸው መጽሐፍ ቅዱሶች ሕዳግ ላይ ከተሰጠው አሰልቺና ልማዳዊ የሆነ ማብራሪያ የበለጠ ኃይል ያለውን “ሌጣ ጥቅስ” ማለትም ምንም ያልተጨመረበትን በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቅዱስ ጽሑፍ እንዳለ በማስተማራቸው ቀሳውስቱ ቆሽታቸው አርሮ ነበር። እነዚህ ሰባኪዎች የተጋደሉት ይህ ያልተበረዘ የአምላክ ቃል መልእክት ለተራው ሕዝብ እንዲደርስ ነበር።
ሁስ በ1414 ጀርመን በሚገኘው የካቶሊክ ኮንስታንስ ምክር ቤት ፊት ቀርበህ አቋምህን አስረዳ፤ ለደህንነትህ ዋስትና እንሰጥሃለን በሚለው የሐሰት ቃል ተታለለ። ምክር ቤቱ 2,933 ቀሳውስት፣ ጳጳሳትና ካርዲናሎችን ያቀፈ ነበር። ሁስ ከቅዱሳን ጽሑፎች ማስረጃ በማቅረብ የእርሱ ትምህርቶች ሐሰት መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ከሆነ አሜን ብሎ እንደሚቀበል ተስማማ። ምክር ቤቱን ያሳሰበው ነገር ግን ይህ አልነበረም። የምክር ቤቱን ሥልጣን ተዳፍሯል በሚል ምክንያት ብቻ በ1415 በእንጨት ላይ ሰቅለው በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት አደረጉት፤ ሁስ ሲገደል ጮክ ብሎ ይጸልይ ነበር።
ይኸው ምክር ቤት የጆን ዊክሊፍ አጽም እንግሊዝ ውስጥ ተቆፍሮ እንዲወጣና እንዲቃጠል በመደንገግ እርሱን ማውገዙንና ለእርሱ ያለውን ንቀት አሳይቷል። ይህ መመሪያ በጣም የሚዘገንን ከመሆኑ የተነሣ በሊቀ ጳጳሱ ትእዛዝ ተግባራዊ እስከሆነበት እስከ 1428 ድረስ ሳይፈጸም ቆይቷል። ይሁን እንጂ እንደ ወትሮው ሁሉ ይህ ጭካኔ የተሞላበት የተቃውሞ እርምጃ የሌሎችን እውነት አፍቃሪዎች ቅንዓት አላዳፈነውም። ይልቁንም የአምላክን ቃል ለማሳተም ያላቸውን ቁጥር ውሳኔ አጠናክሮላቸዋል።
የኅትመት ሥራ ያመጣው ውጤት
ሁስ ከሞተ በኋላ 35 ዓመታት እንዳለፉ ማለትም በ1450 ዮሐንስ ጉተንበርግ ጀርመን ውስጥ በተንቀሳቃሽ የጽሕፈት መሣሪያ ማተም ጀመረ። የመጀመሪያው ታላቅ ሥራው በ1455 ገደማ የተጠናቀቀው የላቲኑ ቩልጌት ትርጉም ነው። እስከ 1495 ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ ሙሉ በሙሉም ይሁን በከፊል በጀርመንኛ፣ በጣልያንኛ፣ በፈረንሳይኛ፣ በቼክ፣ በዳች፣ በዕብራይስጥ፣ በካታላን፣ በግሪክኛ፣ በስፓንኛ፣ በስላቮን፣ በፖርቱጋል እና በሰርቢያ ቋንቋዎች በቅደም ተከተላቸው ተዘጋጅተዋል።
የደቹ ምሁር ዴሲዴሪየስ ኤራዝመስ በ1516 የመጀመሪያውን የተሟላ የግሪክኛ እትም አዘጋጅቷል። ኤራዝመስ ቅዱሳን ጽሑፎች “ወደ ሁሉም ሕዝብ ቋንቋዎች ቢተረጎሙ” ደስ ባለው ነበር። ይሁን እንጂ ራሱ እንዳይተረጉም የነበረውን ከፍተኛ የከበሬታ ቦታ አጣለሁ የሚል ስጋት አደረበት። ሆኖም የተሻለ ድፍረት የነበራቸው ሌሎች ሰዎች ብቅ ብለዋል። ከእነዚህ ሰዎች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ዊልያም ቲንደል ነው።
ዊልያም ቲንደል እና የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ
በ1521 በኦክስፎርድ የተማረው ቲንደል የሰር ጆን ዎልሽ ልጆች አስተማሪ ሆኖ ወደ ቤታቸው ይገባል። ወጣቱ ቲንደል ብዙውን ጊዜ በዎልሽ ቤት የተትረፈረፈ ማዕድ ዙሪያ ቁጭ ብሎ ከአካባቢው ቀሳውስት ጋር የቃላት ውጊያ ይከፍት ነበር። ቲንደል መጽሐፍ ቅዱስ ገልጦ ከቅዱሳን ጽሑፎች ማስረጃ በማቅረብ ሐሳባቸውን ይቃወም ነበር። ውሎ አድሮ የዎልሽ ቤተሰቦች ቲንደል በሚናገረው ነገር እያመኑ ስለመጡ ቀሳውስቱ አሁንም አሁንም መጋበዛቸው ቀረና ፊት ይነሷቸው ጀመር። ይህም ቀሳውስቱ በቲንደልና በትምህርቶቹ ይበልጥ እንዲመረሩ አድርጓቸዋል።
በአንድ ወቅት እንዲሁ ሲከራከሩ አንዱ የቲንደል ተቀናቃኝ “የሊቀ ጳጳሱ ሕግ ከሚቀርብን የአምላክ ሕግ ቢቀርብን ይሻላል” ሲሉ ተናገሩ። ቲንደል እንደሚከተለው ብሎ መመለሱ ምን ዓይነት ጽኑ እምነት እንደነበረው ይጠቁማል:- “ሊቀ ጳጳሱም ሆኑ የእርሳቸው ሕግ ለእኔ ምኔም አይደለም፤ አምላክ ረጅም ዘመን እንድኖር ቢፈቅድልኝ ኖሮ እርፍ ጨብጦ የሚያርሰውን ወጣት አንተ ከምታውቀው የበለጠ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንዲያውቅ አደርገው ነበር።” ቲንደል ቆርጦ ተነስቶ ነበር። ከጊዜ በኋላም እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ተራው ሕዝብ የመጽሐፉ ፍሬ ነገር፣ መልእክትና ትርጉም እንዲገባው ሲባል በአፍ መፍቻ ቋንቋው የቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ተዘጋጅቶ ካልቀረበለት በስተቀር የትኛውንም እውነት እንዲገነዘብ ለመርዳት ማሰብ ዘበት እንደሆነ ከተሞክሮ ተረድቻለሁ።”
በወቅቱ በእንግሊዝኛ የታተመ መጽሐፍ ቅዱስ አልነበረም። በመሆኑም በ1523 ቲንደል የትርጉም ሥራ ለመጀመር የሚያስችለውን ፈቃድ ከሊቀ ጳጳስ ተንስተል ለማግኘት ሲል ወደ ለንደን ተጓዘ። ቲንደል ፊት ስለነሱት ዓላማውን ከግብ ለማድረስ ሲል ዳግም ላይመለስ እንግሊዝን ለቆ ሄደ። ቲንደል በጀርመን ኮሎኝ ውስጥ የነበረችው የመጀመሪያ ማተሚያ ቢሮው በመከበቧ ያልተጠረዙትን ገጾች አፋፍሶ ሕይወቱን ለማዳን ሸሽቶ አመለጠ። ይሁን እንጂ በዎርምስ ጀርመን ቢያንስ 3,000ዎቹ የእንግሊዝኛ “አዲስ ኪዳን” ቅጂዎቹ ተጠናቅቀው ነበር። እነዚህ ቅጂዎች ወደ እንግሊዝ ተልከው በ1526 መጀመሪያ ላይ መሠራጨት ጀመሩ። ሊቀ ጳጳስ ታንስተል እየገዙ ያቃጥሉ የነበረው እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ሲሆን ሳያውቁት ቲንደል ሥራውን እንዲቀጥል እገዛ አድርገዋል!
ምርምር ይበልጥ የጠራ ግንዛቤ ያስገኛል
ቲንደል ሥራውን ይወደው እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም። ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል እንዲህ ሲል ገልጾታል:- “ቅዱሳን ጽሑፎች ያስደስቱት ነበር፤ ይህ ደስታው ሕያው በሆነውና በሚንቆረቆረው የጽሑፍ ሥራው ውስጥ ተንጸባርቆአል።” የቲንደል ግብ ለተራው ሕዝብ በተቻለ መጠን ትክክለኛና ቀላል የሆነ ትርጉም ማቅረብ ነበር። ያካሄዳቸው ጥናቶች ለብዙ መቶ ዘመናት በቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርት ተድበስብሰው የነበሩትን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃላት ትርጉም እንዲረዳ አስችሎታል። ቲንደል የሞት ፍርሃትም ሆነ የቀንደኛ ባላንጣው የሰር ቶማስ ሞር የብዕር ጦር ሳያርደው የምርምሩን ውጤት በትርጉም ሥራው ውስጥ አካትቷል።
ቲንደል ለትርጉም ሥራው የላቲኑን ቅጂ ከመጠቀም ይልቅ የኤራዝመስን የግሪክኛ ቅጂ በመጠቀሙ አጋፔ የሚለውን የግሪክኛ ቃል ይበልጥ በተሟላ መንገድ ለመግለጽ ሲል “ችሮታ” ከሚለው ቃል ይልቅ “ፍቅር” በሚለው ቃል ለመጠቀም መርጧል። በተጨማሪም “ቤተ ክርስቲያን” በሚለው ፋንታ “ጉባኤ”፣ “ሱባኤ መግባት” ከማለት ይልቅ “ንስሐ መግባት” እንዲሁም “ቀሳውስት” ከማለት ይልቅ “ሽማግሌዎች” እያለ መጠቀምን መርጧል። (1 ቆሮንቶስ 13:1-3፤ ቆላስይስ 4:15, 16፤ ሉቃስ 13:3, 5፤ 1 ጢሞቴዎስ 5:17 የቲንደል ትርጉም።) እነዚህ ማስተካከያዎች ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሥልጣን እንዲሁም ለቀሳውስት መናዘዝን ለመሳሰሉት በወግ ላይ ለተመሠረቱት ሃይማኖታዊ ልማዶች ጠንቅ ነበሩ።
በተመሳሳይም ቲንደል የመንጽሔ ትምህርትና ከሞት በኋላ በሕይወት የሚቀጥል ነገር አለ የሚለው ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑን በመግለጽ “ትንሣኤ” የሚለውን ቃል የሙጢኝ ብሏል። ሙታንን በሚመለከት “ሙታን በሰማይ፣ በሲኦልና በመንጽሔ ይገኛሉ እያልክ ስትናገር ክርስቶስና ጳውሎስ ያቀረቡትን የትንሣኤ ማስረጃ መርገጥህ ነው” ሲል ለሞር ጽፎለታል። ቲንደል ማቴዎስ 22:30-32ን እና 1 ቆሮንቶስ 15:12-19ን መጥቀሱ ነበር። ሙታን ወደ ፊት ትንሣኤ እስከሚያገኙ ድረስ ሕይወት አልባ ሆነው ይቆያሉ ብሎ በትክክል ያምን ነበር። (መዝሙር 146:4፤ መክብብ 9:5፤ ዮሐንስ 11:11, 24, 25) ይህም ወደ ማርያም እና “ቅዱሳን” ጸሎት ለማቅረብ የተደረገውን ዝግጅት ሁሉ ትርጉም የሚያሳጣ ነበር፤ ምክንያቱም ሕይወት አልባ ከሆኑ ሊሰሙም ሆነ ሊያማልዱ አይችሉም።
ቲንደል የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ተረጎመ
ቲንደል በ1530 ፔንታቱችን ማለትም የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን የመጀመሪያ አምስት መጻሕፍት የያዘ እትም አዘጋጀ። በዚህ መንገድ መጽሐፍ ቅዱስን ከዕብራይስጥ በቀጥታ ወደ እንግሊዝኛ ለመተርጎም የመጀመሪያው ሰው ሆኗል። በተጨማሪም ጅሆቫ የሚለውን ስም በመጠቀም ረገድ ቲንደል የመጀመሪያው የእንግሊዝኛ ተርጓሚ ሆኗል። የለንደኑ ምሁር ዴቪድ ዳንኤል እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የአምላክ ስም እንደ አዲስ መገለጡ የቲንደልን አንባቢዎች ስሜት የሚኮረኩር እንደነበር ምንም ጥርጥር የለውም።”
የቲንደል ጥረት ግልጽ የሆነ ትርጉም ለማዘጋጀት ስለነበር ለአንድ የዕብራይስጥ ቃል የተለያዩ የእንግሊዝኛ ቃላት ተጠቅሟል። ይሁን እንጂ የዕብራይስጡን አቀማመጥ በጥብቅ ተከትሏል። ከዚህ የተነሣ የዕብራይስጡ ጽሑፍ ያለውን ኃይል እንዳለ ማስተላለፍ ችሏል። እርሱ ራሱ እንዲህ ብሏል:- “የዕብራይስጡ ቋንቋ ከላቲኑ ይልቅ ከእንግሊዝኛው ጋር ሺህ ጊዜ እጥፍ ይስማማል። የቋንቋዎቹ የንግግር ዘይቤ ተመሳሳይ ነው፤ በመሆኑም በአብዛኛዎቹ ቦታዎች የሚያስፈልገው ከዕብራይስጡ ወደ እንግሊዝኛ ቃል በቃል መተርጎም ብቻ ነው።”
በጥቅሉ ሲታይ ቲንደል በትርጉሙ ውስጥ ቃል በቃል ፍቺ መስጠቱ የዕብራይስጡን የአገላለጽ ለዛ እንዲጠብቅ አስችሎታል። አንዳንዶቹ አገላለጾች ምናልባት ለመጀመሪያ ጊዜ ለሚያነባቸው ሰው እንግዳ መስለው ይታዩ ይሆናል። ይሁን እንጂ የኋላ ኋላ ሰዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በሰፊው እየተዋወቁ በመሄዳቸው ዛሬ ከእነዚህ መግለጫዎች መካከል ብዙዎቹ የእንግሊዝኛ ቋንቋ ክፍል ሆነዋል። ከእነዚህም መካከል “ኤ ማን አፍተር ሂስ ኦውን ኻርት” [“እንደ ልቡ የሆነ ሰው”] (በ1 ሳሙኤል 13:14 ላይ) “ፓስኦቨር” [“የማለፍ በዓል”] እንዲሁም “ስኬፕጎት” [“የሚለቀቅ ፍየል”] የሚሉት ይገኙበታል። ከዚህም በላይ የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ቅዱስ አንባቢዎች ከዕብራይስጡ ሐሳብ ጋር ሊተዋወቁ በመቻላቸው በመንፈስ አነሳሽነት ስለተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች የበለጠ ጥልቅ የሆነ ማስተዋል እንዲያገኙ ረድቷቸዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ እና ቲንደል በእገዳ ሥር
መጽሐፍ ቅዱስን በትውልድ አገር ቋንቋ የማንበብ አጋጣሚ ማግኘት እጅግ ያስደስታል። የእንግሊዝ ሕዝብ በጣቃ ጨርቆች ወይም በሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች እየተሸፈኑ ወደ አገር ውስጥ በድብቅ የሚገቡትን መጽሐፍ ቅዱሶች በሙሉ በመግዛት መደሰቱን አሳይቷል። በዚህ መሐል ቀሳውስቱ መጽሐፍ ቅዱስ እንደ ከፍተኛው ባለሥልጣን መታየት ከጀመረ እነርሱ ቦታቸውን ማጣታቸው አይቀሬ መሆኑ ያብሰለስላቸው ጀመር። በመሆኑም ሁኔታው ለተርጓሚውና ለደጋፊዎቹ እያደር የሞትና የሕይወት ጉዳይ እየሆነ መጣ።
ቤተ ክርስቲያኒቱና መንግሥት ያለማቋረጥ የሚያድኑት ቲንደል በቤልጂየም አንትወርፕ ተደብቆ ሥራውን ቀጠለ። ያም ሆኖ ጊዜ ማሳለፊያዬ ለሚለው ሌሎች የእንግሊዝ ስደተኞችን፣ ድኾችንና ሕሙማንን ለማገልገሉ ሥራው በሳምንት ሁለት ቀናት መድቦ ነበር። አብዛኛውን ገንዘቡን የሚያውለው ለዚህ ሥራው ነበር። ቲንደል የቀረውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ከማዘጋጀቱ በፊት ወዳጅ መስሎ የቀረበ አንድ እንግሊዛዊ ሰው ለገንዘብ ሲል አሳልፎ ሰጠው። በ1536 በቪልቮርዴ ቤልጂየም የሞት ፍርድ ሲፈጸምበት ያሰማቸው ከውስጡ ፈንቅለው የወጡት የመጨረሻዎቹ ቃላት “ጌታ ሆይ! የእንግሊዝን ንጉሥ ዓይን ክፈት” የሚሉት ነበሩ።
በ1538 ንጉሥ ሄንሪ ስምንተኛ በራሱ የግል ምክንያቶች መጽሐፍ ቅዱስ በእንግሊዝ ባሉ ቤተ ክርስቲያናት በሙሉ እንዲቀመጥ አዘዘ። ቲንደል ለሥራው ምስጋናን ባያገኝበትም በአብያተ ክርስቲያናቱ እንዲቀመጥ በአንደኛ ደረጃ የተመረጠው የእርሱ ትርጉም ነበር። ይህም የቲንደል ሥራ እጅግ ታዋቂና ተወዳጅ እንዲሆን ከማድረጉም ሌላ “ከዚያ በኋላ የተሠሩት አብዛኛዎቹ [የእንግሊዝኛ] ትርጉሞች ላላቸው ይዘት መሠረት ጥሏል።” (ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ዘ ባይብል) በ1611 የተዘጋጀው የኪንግ ጀምስ ቨርሽን 90 በመቶ የሚያክለው ክፍል በቀጥታ ከቲንደል ትርጉም የተወሰደ ነው።
በእንግሊዝ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ለማግኘት መቻል ታላቅ ለውጥ ነበር። በቤተ ክርስቲያናቱ ውስጥ በመጽሐፍ ቅዱስ ዙሪያ የሚካሄዱ ውይይቶች ሞቅ ያሉ ከመሆናቸው የተነሣ አንዳንድ ጊዜ የቤተ ክርስቲያኑን የቅዳሴ አገልግሎት ሳይቀር ይረብሹ ነበር! “አረጋውያን ራሳቸው የአምላክን ቃል አንብበው ለመረዳት ሲሉ ማንበብን ተምረዋል፤ ልጆችም ትላልቆቹ ሰዎች ሲያነቡ ያዳምጡ ነበር።” (ኤ ኮንሳይስ ሂስትሪ ኦቭ ዚ ኢንግሊሽ ባይብል) በዚህ ዘመን በሌሎች የአውሮፓ አገሮችና ቋንቋዎችም ጭምር በመጽሐፍ ቅዱስ ሥርጭት ረገድ ከፍተኛ እመርታ ታይቷል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን በሚመለከት በእንግሊዝ የተጀመረው ንቅናቄ ዓለም አቀፋዊ ተጽዕኖም ነበረው። ይህ የሆነው እንዴት ነው? እንዲሁም ተጨማሪ ግኝቶችና ምርምሮች ዛሬ በእጃችን ባለው መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ምን ለውጥ አምጥተዋል? በሚቀጥለው እትም ላይ በሚወጣው ተመሳሳይ ርዕስ ዘገባችንን እናጠናቅቃለን።
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በ1526 የተዘጋጀው የቲንደል “አዲስ ኪዳን” —ከእሳቱ እንደተረፈ የሚታወቀው ብቸኛው የተሟላ ቅጂ
[ምንጭ]
©The British Library Board
[በገጽ 26, 27 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ/ሥዕሎች]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት
ቁልፍ የሆኑ ዘመናት በመጽሐፍ ቅዱስ የሥርጭት ታሪክ
እንደ ዘመናችን አቆጣጠር
የዊክሊፍ መጽሐፍ ቅዱስ ተጀመረ (ከ1384 በፊት)
1400
ሁስ የተገደለበት 1415
ጉተንበርግ—በመጀመሪያ የታተመው መጽሐፍ ቅዱስ በ1455 ገደማ
1500
በአገሬው ቋንቋ የተዘጋጁ የመጀመሪያዎቹ ቅጂዎች
የኤራዝመስ ግሪክኛ እትም 1516
የቲንደል “አዲስ ኪዳን” 1526
ቲንደል የተገደለበት 1536
ሄንሪ ስምንተኛ መጽሐፍ ቅዱስ በቤተ ክርስቲያናት እንዲቀመጥ ያዘዘበት 1538
1600
ኪንግ ጄምስ ቨርሽን 1611
[ሥዕሎች]
ዊክሊፍ
ሁስ
ቲንደል
ሄንሪ ስምንተኛ