የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w97 9/15 ገጽ 29-31
  • አርስጥሮኮስ ታማኝ ጓደኛ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • አርስጥሮኮስ ታማኝ ጓደኛ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም
  • ወደ ሮም ያደረጉት ጉዞ
  • ከጳውሎስ ጋር ‘አብሮ የታሰረ’
  • ‘ብርታት የሚሰጥ እርዳታ’
  • ሌሎችን ‘በእጅጉ ማጽናናት’ ትችላለህ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • በይሖዋ መንገድ ሂድ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2008
  • አትፍራ፣ ይሖዋ ረዳትህ ነው
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2020
  • የጳውሎስ የሥራ ባልደረቦች እነማን ነበሩ?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1997
w97 9/15 ገጽ 29-31

አርስጥሮኮስ ታማኝ ጓደኛ

አርስጥሮኮስ ከብዙዎቹ የሐዋርያው ጳውሎስ ታማኝ የሥራ ጓደኞች መካከል አንዱ ነበር። ስሙን ስትሰሙ ምን ትዝ ይላችኋል? ወደ አእምሯችሁ የሚመጣ ነገር አለ? በጥንት የክርስትና ታሪክ ውስጥ የተጫወተው ሚና ምን እንደሆነ ለመናገር ትችላላችሁ? አርስጥሮኮስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተጠቀሱት በደንብ ከምናውቃቸው ሰዎች መካከል ባይሆንም በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በሚገኙ በተለያዩ ታሪኮች ላይ ተጠቅሷል።

ታዲያ አርስጥሮኮስ ማን ነበር? ከጳውሎስ ጋር ምን ግንኙነት ነበረው? አርስጥሮኮስ ታማኝ ጓደኛ ነበር ሊባል የሚቻለው ለምንድን ነው? የእርሱን ምሳሌ በመመርመርስ ምን ትምህርት ልናገኝ እንችላለን?

አርስጥሮኮስ በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ በሚገኘው ታሪክ ላይ በአስገራሚ ሁኔታ ተጠቅሶ የምናገኘው በኤፌሶን ከተማ በተነሳው ረብሻ ምክንያት በነበረው ጩኸትና ረብሻ መካከል ነው። (ሥራ 19:​23-41) የውሸት አምላክ የሆነችውን የአርጤምስን ቤተ መቅደስ ምስሎች ከብር እየሠሩ መሸጥ ለድሜጥሮስና ለሌሎች የኤፌሶን አንጥረኞች ከፍተኛ ትርፍ የሚያስገኝ ሥራ ነበረ። ስለዚህ የጳውሎስ የስብከት ዘመቻ በከተማዋ ውስጥ የነበሩ ብዙ ሰዎች ለዚህች እንስት ጣዖት የሚያቀርቡትን የረከሰ አምልኮ እንዲተዉ ባደረጋቸው ጊዜ ድሜጥሮስ ሌሎች አንጥረኞችን ቀሰቀሰ። የጳውሎስ ስብከት ገቢያቸውን ማሳጣት ብቻ ሳይሆን የአርጤምስን አምልኮ እስከነጭራሹ ከንቱ እንደሚያደርግ ነገራቸው።

እነዚያ በቁጣ የገነፈሉ ረብሸኞች ጳውሎስን ለማግኘት ባለመቻላቸው የእሱ ጓደኞች የሆኑትን አርስጥሮኮስንና ጋይዮስን እያዳፉ ወደ ጨዋታ ስፍራ ወሰዷቸው። የሁለቱ ሕይወት በአደገኛ ሁኔታ ላይ ይገኝ ስለነበር የጳውሎስ ወዳጆች “ወደ ጨዋታ ስፍራ ራሱን እንዳይሰጥ ለመኑት።”

እስቲ ራሳችሁን በዚያ ሁኔታ ሥር እንደሆናችሁ አድርጋችሁ አስቡ። ረብሸኞቹ “የኤፌሶን አርጤምስ ታላቅ ናት” እያሉ ለሁለት ሰዓታት ያህል ጮኹ። አርስጥሮኮስና ጋይዮስ ራሳቸውን ለመከላከል መናገር እንኳ በማይችሉበት ሁኔታ ጭፍን አቋም በነበራቸው ሰዎች ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ስር መሆን በጣም የሚያስፈራ ሆኖባቸው እንደነበር ምንም አያጠራጥርም። ከዚያ ሁኔታ በሕይወት የመትረፋቸው ጉዳይ በጣም አጠራጥሯቸው መሆን አለበት። ደግነቱ በሕይወት ሊተርፉ ችለዋል። አንዳንድ የሃይማኖት ምሁራን ሉቃስ ታሪኩን ቁልጭ አድርጎ ሊጽፍ የቻለው የዓይን ምሥክር ከሆኑ ሰዎች ምናልባትም ከራሳቸው ከአርስጥሮኮስና ከጋይዮስ ካገኘው የምሥክርነት ቃል ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አድሮባቸዋል።

በመጨረሻም የከተማይቱ ጸሐፊ ጩኸቱን ጸጥ አሰኘ። የከተማው ጸሐፊ አርስጥሮኮስና ጋይዮስ ጥፋተኞች አለመሆናቸውን በማስተባበል ሲናገር ሲሰሙትና ከብቧቸው የነበረው ሁካታ የሚያሰማ ሕዝብ ሲበተን ሲመለከቱ ትልቅ እፎይታ ተሰምቷቸው መሆን አለበት።

ይህን ከመሰለ ገጠመኝ በኋላ እንዴት ይሰማህ ነበር? የጳውሎስ ሚስዮናዊ ጓደኛ መሆን በጣም አደገኛ ከመሆኑ የተነሳ ለአንተ ስለማይስማማህ የተረጋጋ ሕይወት ለመምራት ትፈልግ ነበርን? አርስጥሮኮስ እንዲህ አላደረገም! የተሰሎንቄ ሰው ስለነበረ ምሥራቹን ማወጅ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን ቀደም ሲል ሳይገነዘብ አይቀርም። ጳውሎስ ከሁለት ዓመታት በፊት፣ አርስጥሮኮስ ይኖርበት በነበረው ከተማ በሚሰብክበት ጊዜ እዚያም ረብሻ ተነስቶ ነበር። (ሥራ 17:​1-9፤ 20:​4) አርስጥሮኮስ ከጳውሎስ ጋር በታማኝነት ተጣብቋል።

ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም

አንጥረኞቹ ያስነሱት ረብሻ ካለፈ ከጥቂት ወራት በኋላ ጳውሎስ ወደ ግሪክ ሄደ። ከግሪክ በመነሳት በሶሪያ በኩል አድርጎ ወደ ኢየሩሳሌም በመርከብ ለመጓዝ አስቦ የነበረ ቢሆንም ‘አይሁዳውያን አሲረውበት’ ነበር። (ሥራ 20:​2, 3) በእነዚህ ቀውጢ ቀናት ከጳውሎስ ጋር የምናገኘው ማንን ይሆን? አርስጥሮኮስን ነው!

ይህ አዲስ ዛቻ ጳውሎስ፣ አርስጥሮኮስና ሌሎች ጓደኞቻቸው እቅዳቸውን እንዲለውጡ ስላደረጋቸው በመጀመሪያ በመቄዶንያ በኩል ተጓዙ፤ ከዚያም በትንሿ እስያ ድንበር የሚገኙ ቦታዎችን አልፈው ጳጥራ ሲደርሱ በመርከብ ተሳፍረው ወደ ፊንቄ ሄዱ። (ሥራ 20:​4, 5, 13-15፤ 21:​1-3) የዚህ ጉዞ ዓላማ በመቄዶንያና በአካይያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በኢየሩሳሌም ለሚኖሩ ችግረኛ ወንድሞቻቸው ያሰባሰቡትን መዋጮ ለማድረስ እንደነበር ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። (ሥራ 24:​17፤ ሮሜ 15:​25, 26) ከተለያዩ ጉባኤዎች ተወክለው ስለመጡ ሳይሆን አይቀርም ብዙ ቁጥር ያላቸው ወንድሞች አንድ ላይ ተጉዘዋል። በተጨማሪም እንደዚህ ያለው ሰፊ የሰዎች ቡድን አንድ ላይ መጓዙ የበለጠ ደህንነት እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑ አያጠራጥርም።

አርስጥሮኮስ ከጳውሎስ ጋር በመሆን ከግሪክ ወደ ኢየሩሳሌም የመጓዝ ትልቅ መብት አግኝቷል። ይሁን እንጂ የሚቀጥለው ጉዟቸው ከይሁዳ መልሶ ወደ ሮም የሚወስዳቸው ነበር።

ወደ ሮም ያደረጉት ጉዞ

በዚህ ጊዜ ሁኔታዎቹ ፍጹም የተለዩ ነበሩ። ጳውሎስ በቂሣርያ ለሁለት ዓመታት ታስሮ እንዲቆይ የተደረገ ሲሆን ለቄሣር ይግባኝ በማለቱ በሰንሰለት እንደታሰረ ወደ ሮም ሊላክ ነበር። (ሥራ 24:​27፤ 25:​11, 12) የጳውሎስ ጓደኞች ምን ተሰምቷቸው እንደነበር ለመገመት ሞክሩ። ከቂሣርያ ወደ ሮም የሚደረገው ጉዞ ረጅምና ስሜትን ውጥረት ውስጥ የሚከት ሲሆን የመጨረሻ ውጤቱ ምን እንደሚሆን አይታወቅም ነበር። ከጳውሎስ ጋር አብሮ በመሄድ ድጋፍና እርዳታ ማን ሊያበረክትለት ይችል ይሆን? ፈቃደኞች የነበሩ ሁለት ሰዎች ተመረጡ። እነሱም አርስጥሮኮስና የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍን የጻፈው ሉቃስ ነበሩ።​—⁠ሥራ 27:​1, 2

ሉቃስና አርስጥሮኮስ ወደ ሮም በተደረገው የመጀመሪያ ጉዞ ላይ ከጳውሎስ ጋር በአንድ መርከብ ተሳፍረው ሊጓዙ የቻሉት እንዴት ነው? ታሪክ ጸሐፊው ጁዜፔ ሪቾቲ:- “እነዚህ ሁለት ሰዎች የግል ተጓዦች ሆነው ተሳፍረው ይሆናል . . . ወይም አንድ የሮማ ዜጋ ሁለት ባሪያዎች እንዲኖረው ሕጉ ስለሚፈቅድለት የጦር አዛዡ ሁለቱ ሰዎች የጳውሎስ ባሪያዎች መስለውት በደግነት እንዲሳፈሩ የፈቀደላቸው ይመስላል” ሲሉ ሐሳባቸውን ሰጥተዋል። ጳውሎስ እዚያ በመገኘታቸውና በማበረታቻቸው ልቡ እንዴት ተነክቶ ይሆን!

ሉቃስና አርስጥሮኮስ ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ለጳውሎስ የነበራቸውን ፍቅር አሳይተዋል። እንደ እውነቱ ከሆነ በመላጥያ ደሴት ላይ መርከባቸው ተሰብሮ የእነሱንም ሆነ የእስረኛ ጓደኛቸውን ሕይወት የሚያሳጣ አደጋ አጋጥሟቸው ነበር።​—⁠ሥራ 27:​13–28:​1

ከጳውሎስ ጋር ‘አብሮ የታሰረ’

ጳውሎስ ለቆላስይስ ሰዎችና ለፊልሞና በ60-61 እዘአ ደብዳቤ ሲጽፍ አርስጥሮኮስና ሉቃስ ከእርሱ ጋር አብረው በሮም ይገኙ ነበር። አርስጥሮኮስና ኤጳፍራ ከጳውሎስ ጋር ‘አብረው የታሰሩ’ እንደሆኑ ተደርገው ተገልጸዋል። (ቆላስይስ 4:​10, 14፤ ፊልሞና 23, 24) ስለዚህ ለጊዜውም ቢሆን አርስጥሮኮስ ከጳውሎስ ጋር ታስሯል።

ጳውሎስ ቢያንስ ለሁለት ዓመታት ያህል በሮም እስረኛ ሆኖ ቢቆይም በጥበቃ ሥር ሆኖ ራሱ በተከራየው ቤት ውስጥ እንዲኖር ተፈቅዶለት ስለነበር ወደ ቤቱ ለሚመጡ እንግዶች ምሥራቹን ሊያውጅ ይችል ነበር። (ሥራ 28:​16, 30) በዚያን ጊዜ አርስጥሮኮስ፣ ኤጳፍራ፣ ሉቃስና ሌሎችም ጳውሎስን በመርዳትና በማጽናናት አገልግለውታል።

‘ብርታት የሚሰጥ እርዳታ’

በመንፈስ በተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ውስጥ አርስጥሮኮስ የተጠቀሰባቸውን የተለያዩ ታሪኮች ከመረመርን በኋላ ስለ አርስጥሮኮስ ምን እንማራለን? ደራሲው ደብልዩ ዲ ቶማስ፣ አርስጥሮኮስ “ተቃውሞን መጋፈጥ የሚችል እንዲሁም እምነቱን ሳያጎድልና የማገልገል ውሳኔውን ሳይቀይር መቀጠል የሚችል ሰው ነበር። አምላክን የሚወድ ሰው መሆኑን ያስመሰከረው በደህና ቀን ብቻ ሳይሆን በአስቸጋሪ ጊዜ ጭምር ነው” በማለት ተናግረዋል።

ጳውሎስ አርስጥሮኮስና ሌሎችም ሰዎች ‘ብርታት የሚሰጥ እርዳታ’ (በግሪክኛ ፓሬጎሪያ) ማለትም የመጽናናት ምንጭ ሆነውለት እንደነበር ገልጿል። (ቆላስይስ 4:​10, 11) ስለዚህ ጳውሎስን በማጽናናትና በማበረታታት በኩል አርስጥሮኮስ በተፈላጊው ጊዜ የተገኘ እውነተኛ ጓደኛ ነበር። ከሐዋርያት ጋር ለብዙ ዓመታት ጓደኛና ወዳጅ መሆን በጣም የሚያረካና በመንፈሳዊም የሚያበለጽግ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም።

የአርስጥሮኮስን በመሰሉ አስደናቂ ገጠመኞች ውስጥ አናልፍ ይሆናል። ይሁን እንጂ ዛሬ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ሁሉ ለክርስቶስ መንፈሳዊ ወንድሞችና ለይሖዋ ድርጅት ተመሳሳይ የሆነ ታማኝነት ማሳየት ያስፈልጋቸዋል። (ከማቴዎስ 25:​34-40 ጋር አወዳድር።) ፈጥኖም ይሁን ዘግይቶ መሰል አምላኪዎች ምናልባት በዘመድ ሞት፣ በሕመም ወይም በሌሎች ፈተናዎች ምክንያት መከራ ወይም ሥቃይ እንደሚደርስባቸው እናውቃለን። ከእነርሱ ጋር በመጣበቅና እርዳታ፣ ማጽናኛና ማበረታቻ በመስጠት ደስታ ልናገኝ እንዲሁም ታማኝ ጓደኞች መሆናችንን ልናስመሰክር እንችላለን።​—⁠ከምሳሌ 17:​17 እና ከሥራ 20:​35 ጋር አወዳድር።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ