የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
“ባልተጠበቁ ሰዎች ምድር” ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ማሸነፍ
ሐዋርያው ጳውሎስ በቆሮንቶስ የነበሩትን የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች “ደግሞም መለከት የማይገለጥን ድምፅ ቢሰጥ ለጦርነት ማን ይዘጋጃል? እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል?” ብሎ ጠይቋቸው ነበር።—1 ቆሮንቶስ 14:8, 9
አንዳንድ ጊዜ፣ ያልተጠበቁ ሰዎች ምድር እየተባለች በምትጠራው በፓፑዋ ኒው ጊኒ የሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ግልጽ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት በሚሰብኩበት ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ዕንቅፋቶች ያጋሟቸዋል። ከ700 በላይ የሚሆኑ የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚናገሩና በጣም ብዙ ባሕሎች ላሏቸው ሰዎች ይሰብካሉ። ከዚህም በተጨማሪ ምሥክሮቹ ተራራማው መልክአ ምድር፣ የመንገዶች አለመኖርና እየጨመረ የሚሄደው ወንጀል የሚያስከትሉትን ችግር መቋቋም አስፈልጓቸዋል። ከእነዚህ አስቸጋሪ ሁኔታዎች በተጨማሪ ከአንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖችና አልፎ አልፎ ደግሞ ከትምህርት ቤት ባለሥልጣኖች ጭምር ተቃውሞ ይገጥማቸዋል።
የሆነው ሆኖ ያገኙት ጥሩ መንፈሳዊ መመሪያና መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ በአገሩ ቋንቋዎች የተዘጋጁ በዓይነት እያደጉ ያሉ መጻሕፍት፣ ምሥክሮቹ ምሥራቹን ልዩ እንደሆነ የመለከት ድምፅ እንዲያሰሙ አስታጥቀዋቸዋል። ቀጥሎ ያሉት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት ብዙውን ጊዜ ምላሹ አዎንታዊ ነው:-
• አዲሱ የትምህርት ዓመት በጀመረ ጊዜ፣ አንድ አስተማሪ የይሖዋ ምሥክሮች ልጆች ለባንዲራ ለምን ሰላምታ እንደማይሰጡ ወይም ብሔራዊ መዝሙሩን ለምን እንደማይዘምሩ ለማወቅ ፈለገ። ጥያቄውን የተጠመቀች ምሥክር ለሆነችው ማዮላ ለተባለች የ13 ዓመት ተማሪ አቀረበ። ማዮላ በቅዱስ ጽሑፉ ላይ የተመሰረተ ግልጽ ማብራሪያ ሰጠች። ለጥያቄው መልስ የሰጠችው ከመጽሐፍ ቅዱስ ስለነበር አስተማሪው ያቀረበችውን ማብራሪያ ተቀበለ። የሰጠችው መግለጫ ለተቀሩት የትምህርት ቤቱ መምህራንም ተዳረሰ።
በሌላ ጊዜ ተማሪዎቹ ድርሰት እንዲጽፉ የቤት ሥራ ሲሰጣቸው ማዮላ የሥላሴን ርዕስ መረጠች። ከክፍሉ ውስጥ የእርሷ ድርሰት ከፍተኛውን ነጥብ አገኘ፣ አስተማሪውም መረጃውን ከየት እንዳገኘችው ጠየቃት። በምድር ላይ በገነት ለዘላለም መኖር ትችላለህ የተባለውን መጽሐፍ የእንግሊዝኛውን ቅጂ አሳየችው። አስተማሪው መጽሐፉን ለክፍሉ ተማሪዎች በሙሉ ባስተዋወቃቸው ጊዜ ብዙዎቹ የራሳቸው የግል ቅጂ ለማግኘት ፈለጉ። በሚቀጥለው ቀን ማዮላ 14 መጻሕፍትና 7 መጽሔቶች ለትምህርት ቤት ጓደኞቿ አበረከተችላቸው፤ ከሦስቱ ጓደኞቿ ጋር ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጀመረች። ማዮላ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ የመሆን ግብ አላት።
• ፖርት ሞረስባይ አቅራቢያ በባሕር ዳር ባለች መንደር ውስጥ የሚገኝ አንድ ገለልተኛ የይሖዋ ምሥክሮች ቡድን ከ1970ዎቹ መጀመሪያ አንስቶ ተቃውሞ ገጥሞታል። በቅርቡ ግን ካልጠበቁት ምንጭ እርዳታ አገኙ። በመንደሩ የዩናይትድ ቸርች ጳጳስ የሆኑና ውጭ አገር የተማሩ አንድ የፓፑዋ ኒው ጊኒ ተወላጅ አንድ ቀን በቤተ ክርስቲያን የተሰበሰቡትን አድማጮች ጥያቄ እንዲጠይቁ አበረታቷቸው። ከተሰብሳቢዎቹ አንዱ “በመንደራችን ውስጥ ያሉት ሃይማኖቶች የዩናይትድ ቸርችና የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው። ምሥክሮቹ ቤታችን በሚመጡበት ጊዜ ምን እናድርግ?” ብሎ ጠየቀ። ከረዥም ዝምታ በኋላ፣ ጳጳሱ እንዲህ ሲሉ መለሱ:- “ምን ብዬ እንደምመልስላችሁ አላውቅም። በቅርቡ ሁለት ወጣት ምሥክሮች ቤቴ መጡ። አንድ ጥያቄ ጠየቁኝ፣ ከፍተኛ የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የተከታተልኩ ብሆንም መልሱን አላወቅሁትም። እነርሱ ግን ያለ አንዳች ችግር መልሱን ከመጽሐፍ ቅዱስ አሳዩኝ። ስለዚህ ምን ማድረግ እንዳለባችሁ እኔ አልነግራችሁም፤ ይህን ለእናንተ እተወዋለሁ። ካልፈለጋችሁ እነርሱን የማዳመጥ ግዴታ የለባችሁም፤ ነገር ግን በእነርሱ ላይ ጠብ አታንሱ።”
አንድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ተጓዥ ተወካይ ከጊዜ በኋላ ይህን የምሥክሮች ቡድን ጎብኝቶ የሚከተለውን ሪፖርት አቅርቧል:- “በመንደሩ ውስጥ ያሉት ሰዎች በአጠቃላይ ማለት ይቻላል ምሥክሮቹ በሚሰብኩበት ጊዜ ያዳምጧቸዋል። ሌላው ቀርቶ አንዳንዶች ቤታቸው እንዲገቡ ይጋብዟቸው ነበር። ባሁኑ ጊዜ ቦታው ለስብከት ምቹ ሆኗል።”