የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ሪፖርት
በትምህርት ቤት ውስጥ መንፈሳዊ ረሐብተኞችን ማጥገብ
ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ “ለሚያስፈልጓቸው መንፈሳዊ ነገሮች ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሎ ነበር። (ማቴዎስ 5:3 አዓት) በትምህርት ቤት የሚገኙ ብዙ ልጆች ስለ አምላክና ስለ አስደናቂ ዓላማዎቹ የማወቅ ጥማት አላቸው። ስለ ሕይወት ለሚጠይቋቸው ጥያቄዎች አጥጋቢ መልስ ይፈልጋሉ፤ በተጨማሪም አምላክ የሚቀበላቸውና ደስተኞች ለመሆን እንዴት ሆነው መኖር እንዳለባቸው ለማወቅ ይፈልጋሉ። ይህ ዓይነቱ መንፈሳዊ ጥማት በብሪቲሽ ቨርጅን ደሴት ታይቶአል። በዚያ የሚኖር እንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ በማለት ይተርካል።
◻ “በአንድ ትምህርት ቤት በተደረገ የወላጆችና የመምህራን ስብሰባ ላይ ተገኘሁ። ስለ አደንዛዥ መድኃኒቶች፣ ስለ ስካር፣ ከተቃራኒ ጾታ ጋር ስለ መቀጣጠር፣ ቴሌቪዥን ስለ መመልከት፣ ስለ ተማሪዎች ማርክና ስለ ሌሎች ጉዳዮች ሰፋ ያለ ውይይት ተደርጎ ስለነበረ የወጣቶች ጥያቄዎችና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባለው መጽሐፍ ለትምህርት ቤቱ ዲሬክተር ለመስጠት ወሰንኩ። እርስዋም መጽሐፉን ከመረመረች በኋላ እንዲህ ያለው መጽሐፍ በጣም እንደሚያስፈልጋቸውና 120 ለሚያክሉት ተማሪዎች አንዳንድ ቅጂ ለማግኘት ይቻል እንደሆነ ጠየቀችኝ። ስለጉዳዩ ከጉባኤ ሽማግሌዎች ጋር ተወያየንና መጽሐፎቹን ለትምህርት ቤቱ በስጦታ መልክ ለማበርከት ተወሰነ። ይህን በነገርናቸው ጊዜ መምህራኑ ለመላው ተማሪ ስለ መጽሐፉ ገለጻ እንድናደርግ ጠየቁን። ሁለት ምሥክሮች ተላኩ። ተማሪዎቹ አንዱን ክፍል ሞልተው ይጠብቁአቸው ነበር። ወንድሞች የግማሽ ሰዓት ንግግር አደረጉ። መጽሐፉ እንዴት ወጣቶችንም ሆነ ትላልቅ ሰዎችን እንደረዳ የሚገልጹ ተሞክሮዎች ከመጠበቂያ ግንብ መጽሔቶች ተነበቡ። ከዚያ በኋላ መጽሐፎቹ በጉጉት ይጠባበቁ ለነበሩት ተማሪዎች ታደሉ።”
ትምህርት ቤቱ ለአራተኛና ለአምስተኛ ክፍል በሚሰጠው መደበኛ ትምህርት በዚህ መጽሐፍ ለመጠቀም መወሰኑን ማወቅ በጣም ያስደስታል። በእርግጥም እነዚህ ተማሪዎች ስለ ሕይወትና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ለሚጠይቁአቸው ብዙ ጥያቄዎች መልስ እንዲያገኙ ይረዳቸዋል።
በፓፑዋ ኒው ጊኒ መንፈሳዊ ረሐብተኞችን ማጥገብ
የሚከተለው ተሞክሮ ከአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ደርሶናል። በዚያ አገር የሚኖሩ ሰዎች እንዴት ያለ መንፈሳዊ ረሐብ እንዳላቸውና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሰረቱት ጽሑፎቻችን ረሐባቸውን ለማስታገስ ምን ያህል ውጤታማ እንደሆኑ የሚያሳይ ተሞክሮ ነው።
◻ የበላይ ተመልካቹ እንዲህ ይላል:- “ወደ ካምበራቶሮ መንደር ለመሄድ ስላልቻልኩ በቫኒሞ ከሚገኘው አነስተኛ ጉባዔ ጋር ሳገለግል ሰነበትኩ። በዚህ ቦታ ብዙ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አሉ። ብዙ የበዋኒ ሰዎች ጽሑፎቻችንን ወሰዱ። አንድ ሰው ወደ መንደሩ እንድሄድ በመጠየቅ በዚያም ተቀብሎ እንደሚያሰተናግደኝ ነገረኝ። ብዙ ሰዎች ጽሑፎቻችንን ያውቁአቸዋል። ወደ ቫኒሞ ከተማ በሄድን ቁጥር ሶስት ካርቶን መጽሐፍ ይዘን ብንሄድም ጽሑፎቻችን አልቀውብን እንመለስ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮችን የያዘው መጽሐፌ የተባለው መጽሐፍ የወርቅ ያህል ተፈላጊነት አለው። ሁሉም ሰዎች ይህን መጽሐፍ አጥብቀው ይፈልጋሉ። የወሰድኳቸው መጻሕፍት በፍጥነት ተበርክተው አለቁ። ጽሑፎቻችንን ለሰዎች ስናሳይ አንዳንዶች ‘ቢጫው መጽሐፍ የታለ?’ ብለው ይጠይቁናል። አንድ ሰው ስድስት መጻሕፍት አዘዘ። ስሙንና አድራሻውን ከሰጠኝ በኋላ መጽሐፎቹን እንዳገኘሁ በሬዲዮ ማስታወቂያ እንዳስነግርና ወዲያው እንደሰማ ከመንደሩ መጥቶ እንደሚወስድ ነገረኝ።” ተጓዥ የበላይ ተመልካቹ በመቀጠል “በቫኒሞ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች የሰው ልጅ አምላክን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ እና የወጣቶች ጥያቄና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው የተባሉትን መጻሕፍት እንደሚወስዱ ተገንዝቤአለሁ” ብሎአል።
ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ እና ይሖዋ “በታማኝና ልባም ባሪያ” አማካኝነት በሚያዘጋጃቸው ጽሑፎች ውስጥ ለሚገኙት መንፈሳዊ ምግቦች እንዴት ያለ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ተሞክሮ ነው። (ማቴዎስ 24:45–47) የይሖዋ ምሥክሮች እነዚህን መንፈሳዊ ረሐብተኞች ለመርዳት በመቻላቸው ምንኛ ደስተኞች ናቸው!
[በገጽ 19 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በፓፑዋ ኒው ጊኒ ምሥክርነት ሲሰጥ