በይሖዋ አገልግሎት ረጅም ዘመን በማሳለፌ ደስተኛ ነኝ
ኦቲሊ ሚድለን እንደተናገረችው
በ19ኛው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ በንፋስ ግፊት የሚንቀሳቀሱ መርከቦች በምዕራባዊ ኖርዌይ በምትገኘው በኮፐርቪክ ወደብ ተደርድረው ይቆሙ ነበር። በዚያ ዘመን በየመንገዱ በሰዎች ወይም በፈረሶች የሚጎተቱ ጋሪዎች ይታዩ ነበር። ሰዎች ለመብራትነት ይጠቀሙ የነበረው በፓራፊን መብራቶች ሲሆን ነጭ ቀለም የተቀቡ የእንጨት ቤቶቻቸውን የሚያሞቁት ደግሞ በእንጨትና በከሰል እሳት ነበር። በዚህ አካባቢ ሰኔ 1898 ተወለድኩ፤ በቤታችን ካሉት አምስት ልጆች እኔ ሁለተኛ ነኝ።
በ1905 አባታችን ከሥራ በመውጣቱ ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄዶ ነበር። ከሦስት ዓመታት በኋላ ሲመለስ አንድ ሻንጣ ሙሉ ለእኛ የሚያስደስቱ ስጦታዎችንና ለእናታችን ደግሞ የሐር ጨርቆችና ሌሎች ዕቃዎች ይዞ መጣ። ለአባቴ ግን ከሁሉ የበለጡ ውድ ንብረቶቹ ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ በሚል ርዕስ በቻርልስ ቴዝ ራስል የተጻፉት ጥራዞች ነበሩ።
አባቴ ከእነዚህ መጻሕፍት የተማራቸውን ነገሮች ለወዳጆቹና ለዘመዶቹ መናገር ጀመረ። በአካባቢው የጸሎት ቤቶች ስብሰባ በሚደረግበት ወቅት ሲኦል የሚባል ማቃጠያ ነገር እንደሌለ መጽሐፍ ቅዱስ እያወጣ ያሳያቸው ነበር። (መክብብ 9:5, 10) በ1909፣ አባቴ ከዩናይትድ ስቴትስ ከተመለሰ ከአንድ ዓመት በኋላ ወንድም ራስል ወደ ኖርዌይ መጥቶ በበርገንና ዛሬ ኦስሎ በምትባለው በክሪስቲያኒያ ንግግር አቀረበ። አባቴ የእርሱን ንግግር ለመስማት ወደ በርገን ሄዶ ነበር።
አብዛኞቹ ሰዎች የሐሰት ትምህርቶችን ያስፋፋል በማለት አባቴን ይከሱት ነበር። ስላዘንኩለት ለጎረቤቶቻችን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትራክቶችን በማሰራጨት እረዳው ጀመር። በ1912 ለአንዲት የቄስ ልጅ ስለ ሲኦል የሚናገር ትራክት ሰጠኋት። እኔንም አባቴንም ሙልጭ አድርጋ ሰደበችን። ከአንዲት የቄስ ልጅ አፍ ይህን የመሰለ አጸያፊ ንግግር ይወጣል ብዬ ስላልገመትኩ በጣም ደነገጥሁ!
በዚያን ጊዜ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመባል ከሚታወቁት የይሖዋ ምሥክሮች መካከል ጥሩ ተናጋሪ የነበረውን ቴዎዶር ሲመንሰንን ጨምሮ ሌሎችም ወደ ኮፐርቪክ እየመጡ አልፎ አልፎ ይጎበኙን ነበር። ወንድም ቴዎዶር እቤታችን ንግግር በሚሰጥበት ጊዜ ሌሎች ሰዎች እንዲገኙ እጋብዝ ነበር። ከንግግሩ በፊት በዚዘር የሙዚቃ መሣሪያ እየተጫወተ ይዘምርና ከንግግሩም በኋላ የመሰነባበቻ አንድ መዝሙር ይዘምርልን ነበር። ለእርሱ ጥልቅ አክብሮት ነበረን።
ሌላዋ ቤታችን እየመጣች ትጎበኘን የነበረችው ኮልፖርተር ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ደግሞ አና አንደርሰን ነበረች። ለሰዎች መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን እያበረከተች ከከተማ ወደ ከተማ በመዘዋወር መላዋን ኖርዌይ ታዳርስ ነበር፤ አብዛኛውን ጊዜ የምትጓዘው በብስክሌት ነበር። በአንድ ወቅት የአዳኝ ሠራዊት (ሳልቬሽን አርሚ) መኮንን ስለነበረች በኮፐርቪክ ከሚገኙት አንዳንድ የአዳኝ ሠራዊት መኮንኖች ጋር ትተዋወቅ ነበር። በስብሰባ ቦታቸው ተገኝታ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንግግር እንድትሰጥ ፈቀዱላት፤ እኔም ሌሎች ሰዎች በዚያ ተገኝተው ንግግሩን እንዲያዳምጡ ጋበዝኩ።
ኮፐርቪክ እየመጣ ይጎበኘን የነበረው ሌላው ኮልፖርተር ደግሞ ካርል ገንበር ነው። ይህ ትሑት፣ ረጋ ያለና ተጫዋች ሰው በኦስሎ በሚገኘው የቅርንጫፍ ቢሮ ውስጥ አልፎ አልፎ በተርጓሚነት ያገለግል ነበር። ከዓመታት በኋላ በቤቴል አብረን አገልግለናል።
ሃይማኖታዊ አመለካከቶች ያሳደሩብኝ ተጽዕኖ
በወቅቱ ብዙዎቹ ሰዎች በአምላክና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ጽኑ እምነት የነበራቸው ከመሆኑም ሌላ እንደ እሳታማ ሲኦልና ሥላሴ ባሉት እምነቶች ተጠላልፈው ነበር። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹ እነዚህ መሠረተ ትምህርቶች ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አይስማሙም እያሉ ማስተማራቸው ቁጣ አስነስቶ ነበር። ጎረቤቶቻችን አባቴ መናፍቅ እንደሆነ በመግለጽ የሚሰነዝሩት ጠንካራ ነቀፋ ተጽእኖ አሳድሮብኝ ነበር። እንዲያውም አንድ ቀን “አንተ የምታስተምረው ነገር እውነት አይደለም። ኑፋቄ ነው!” አልኩት።
“ኦቲሊ፣ ነይ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ተመልከቺ” በማለት አበረታታኝ። ከዚያ በኋላ በእርሱና በሚያስተምራቸው ትምህርቶች ላይ ያለኝ ትምክህት ጨመረ። ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ የተባለውን መጽሐፍ እንዳነብ ስላበረታታኝ በ1914 የበጋ ወራት ብዙውን ጊዜ ቁልቁል ከተማዋን ማየት ከሚቻልበት አንድ ጉብታ ላይ ቁጭ ብዬ አነብብ ነበር።
በነሐሴ 1914 ሰዎች በአካባቢያችን በሚገኘው ጋዜጣ በሚዘጋጅበት ሕንፃ አጠገብ ተሰብስበው አንደኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳቱን የሚገልጸውን ዜና ያነባሉ። አባቴ ጉዳዩ ምን እንደሆነ ለማጣራት ወደዚያ መጣ። “ተመስገን አምላኬ!” ሲል በደስታ ተናገረ። የጦርነቱ መፈንዳት እርሱ ሲሰብካቸው የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ መሆኑን ተገንዝቦ ነበር። (ማቴዎስ 24:7) በዚያ ጊዜ ብዙዎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቅርቡ ወደ ሰማይ እንወሰዳለን ብለው ይጠብቁ ነበር። ይህ ነገር ሳይሆን በመቅረቱ አንዳንዶች ተስፋ ቆርጠዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት በመደገፍ የወሰድኩት አቋም
በ1915 በአሥራ ሰባት ዓመቴ የመለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን አጠናቀኩና በአንድ ቢሮ ውስጥ ተቀጥሬ መሥራት ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ መጠበቂያ ግንብ አዘውትሬ ማንበብ ጀመርሁ። ይሁን እንጂ እስከ 1918 ድረስ በኮፐርቪክ ቋሚ ስብሰባዎች ማድረግ አልተጀመረም ነበር። መጀመሪያ አካባቢ የምንሰበሰበው አምስት ብቻ ነበርን። ስተዲስ ኢን ዘ ስክሪፕቸርስ የተባለውን ዓይነት የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ጽሑፎች እናነብና በጥያቄና መልስ ትምህርቱን እንወያይበት ነበር። እናቴ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎቹን እያሞገሰች ትናገር የነበረ ቢሆንም እንደ እኛ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ሳትሆን ቀርታለች።
ከ1918 ጀምሮ እሠራበት በነበረው ቢሮ ውስጥ የተዋወቅሁትን አንቶን ሳልትነስን የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ እንዲሆን ረድቼዋለሁ። በዚህ ወቅት አዘውታሪ አስፋፊ ሆኜ በ1921 በበርገን በተካሄደው ስብሰባ ላይ ተጠመቅሁ።
በግንቦት 1925 የስካንዲኔቪያ አገሮችን በጠቅላላ የሚያቅፍ ስብሰባ በስዊድን ኦሬብሮ ተዘጋጀ። የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረውን ወንድም ጄ ኤፍ ራዘርፎርድን ጨምሮ ከ500 የሚበልጡ ሰዎች በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር። ሠላሳ የምንሆነው ከኦስሎ አንድ ፉርጎ ሞልተን በባቡር ሄድን።
በዚህ ስብሰባ ላይ በስካንዲኔቪያ በጠቅላላና በቦልቲክ አገሮች የሚካሄደውን የስብከት ሥራ የሚመራ አንድ የሰሜን አውሮፓ ቢሮ በዴንማርክ ኮፐንሃገን ውስጥ እንደሚከፈት ማስታወቂያ ተነገረ። ዊልያም ዴይ የስብከቱን ሥራ በበላይነት እንዲከታተል ከስኮትላንድ ተመደበ። ዊልያም በአጭር ጊዜ ከፍተኛ ተወዳጅነት በማትረፉ ትልቁ የስኮትላንድ ሰው ተብሎ ይጠራ ነበር። መጀመሪያ አካባቢ ወንድም ዴይ የትኛውንም የስካንዲኔቪያ አገሮች ቋንቋ ስለማያውቅ በጉባኤና በትላልቅ ስብሰባዎች ወቅት ከኋላ ተቀምጦ ወላጆች ከመድረክ የሚሰጠውን ትምህርት በትኩረት መከታተል እንዲችሉ ልጆቻቸውን ይጠብቅላቸው ነበር።
የመጋቢት 1, 1925 መጠበቂያ ግንብ ራእይ ምዕራፍ 12ን በመጥቀስ ምዕራፉ የአምላክ መንግሥት በሰማይ ስለመወለዱ እንደሚገልጽና ይህም የተከናወነው በ1914 በሰማይ እንደሆነ አብራርቶ ነበር። መጠበቂያ ግንቡ ይህ ነገር በ1914 እንደተፈጸመ ገልጿል። ይህንን ነገር መረዳት ከብዶኝ ስለ ነበር ርዕሱን ደግሜ ደጋግሜ አነበብኩት። በመጨረሻ ነጥቡ ሲገባኝ በጣም ተደሰትኩ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በነበረን ግንዛቤ ላይ ማስተካከያዎች ሲደረጉ አንዳንዶች ተደናቅፈው ከአምላክ ሕዝቦች መካከል ወጥተዋል። ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን ማስተካከያ ለመረዳት ከባድ ሆኖ ሳገኘው ትምህርቱን ደግሜ ደጋግሜ በማንበብ ሐሳቡን ለመረዳት እሞክራለሁ። ይህንንም አድርጌ የተሰጠው አዲስ ማብራሪያ ካልገባኝ ይበልጥ ግልጽ የሆነ ማብራሪያ እስኪሰጥ ድረስ እጠብቅ ነበር። እንዲህ የመሰለውን ትዕግሥት ማሳየቴ ብዙ ጊዜ ጠቅሞኛል።
የቤቴል አገልግሎት
ለተወሰኑ ዓመታት በሒሳብ ያዥነት፣ በጸሐፊነትና በኦዲተርነት ሠርቻለሁ። በ1928 የማኅበሩን የገንዘብ ሒሳብ ይይዝ የነበረው ወንድም ታምሞ ከቤቴል ወጣ። እኔ በዚህ ሥራ ተሞክሮ ስለነበረኝ እርሱን እንድተካው ጥያቄ ቀረበልኝ። በሰኔ 1928 የቤቴል አገልግሎት ጀመርሁ። አልፎ አልፎ ወንድም ዴይ እየመጣ የሠራሁትን ሒሳብ ይመረምር ነበር። የቤቴል ቤተሰባችን በኦስሎ በሚካሄደው የስብከት ሥራም በግንባር ቀደምትነት ይካፈል ነበር፤ በወቅቱ በዚያ የነበረው ጉባኤ አንድ ብቻ ነበር።
አንዳንዶቻችን በቤቴል የዕቃ መላኪያ ክፍል ውስጥ ያገለግል የነበረውን ወንድም ሳክሸመርን ወርቃማው ዘመን (አሁን ንቁ!) የሚባለውን መጽሔት በማሸጉና በመላኩ ሥራ እናግዘው ነበር። ከሚረዱን ወንድሞች መካከል ወንድም ሲመንሰን እና ጋንበር ይገኙበት ነበር። እነዚህ ወንድሞች ብዙውን ጊዜ እየሠራን መዝሙር ይዘምሩ ስለነበር አብረን ደስ የሚል ጊዜ አሳልፈናል።
በመንግሥቱ ተስፋ ላይ የነበረኝ ትምክህት
በ1935 “እጅግ ብዙ ሰዎች” ሁለተኛ ደረጃ ያላቸው የሰማያዊ ውርሻ ተካፋዮች አለመሆናቸውን ተረዳን። ከዚህ ይልቅ ግን ከታላቁ መከራ በሕይወት የሚያልፉትንና ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ተስፋ ያላቸውን ሰዎች እንደሚያመለክቱ ተገነዘብን። (ራእይ 7:9-14) በዚህ አዲስ ግንዛቤ መሠረት ከመታሰቢያው በዓል ምሳሌያዊ ወይንና ቂጣ ይካፈሉ የነበሩት አንዳንዶች ጥሪያቸው ምድራዊ እንደሆነ ስለተገነዘቡ መካፈላቸውን አቆሙ።
የሰማያዊ ተስፋ ተካፋይ ስለመሆኔ ጥርጣሬ ገብቶኝ ባያውቅም ብዙውን ጊዜ ‘አምላክ እኔን የመረጠኝ ለምንድን ነው?’ እያልኩ አስባለሁ። እንዲህ ለመሰለው ትልቅ መብት የምገባ ሰው እንደሆንኩ አይሰማኝም ነበር። ዓይናፋርና ተራ ሴት ሆኜ ሳለ ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመንገሥ መብት ማግኘቴን ሳስበው በጣም ያስገርመኛል። (2 ጢሞቴዎስ 2:11, 12፤ ራእይ 5:10) ይሁን እንጂ “ኀያላን የሆኑ ብዙዎች” አልተጠሩም፤ ከዚህ ይልቅ “ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ” የሚሉትን የጳውሎስ ቃላት አሰላስላለሁ።—1 ቆሮንቶስ 1:26, 27
በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የነበረው እንቅስቃሴ
ሚያዝያ 9, 1940 ኖርዌይ በጀርመን ሠራዊት ተወርራ ብዙም ሳይቆይ አገሪቷ ተያዘች። ጦርነቱ ብዙ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት ምላሽ እንዲሰጡ አደረጋቸው። ከጥቅምት 1940 እስከ ሰኔ 1941 ድረስ ከ272,000 በላይ መጻሕፍትና ቡክሌቶች አበርክተናል። ይህም ማለት በወቅቱ በኖርዌይ የነበሩት ከ470 የሚበልጡ ምሥክሮች እያንዳንዳቸው በእነዚህ ዘጠኝ ወራት ውስጥ በአማካይ ከ570 በላይ መጻሕፍትና ቡክሌቶች አበርክተው ነበር ማለት ነው!
በሐምሌ 8, 1941 የጌስታፖ ፖሊሶች ወደ ሁሉም ሰብሳቢ የበላይ ተመልካቾች ሄደው የስብከቱ ሥራ ካላቆመ ወደ ማጎሪያ ካምፖች እንደሚላኩ ነገሯቸው። አምስት የጀርመን ፖሊስ መኮንኖች ወደ ቤቴል መጥተው አብዛኛውን የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ንብረቶች ወረሱ። የቤቴል ቤተሰብ አባላት በሙሉ ተወስደን ቃላችንን ሰጠን፤ ይሁን እንጂ ከመካከላችን የታሰረ ማንም አልነበረም። በመጨረሻም ሐምሌ 21, 1941 በኢንኮግኒቶጋተን 28 ቢ የሚገኘው የማኅበሩ ሕንፃ ተወረሰ፤ የስብከት ሥራችንም ታገደ። ከዚያም ወደ ኮፐርቪክ ተመልሼ ራሴን ለማስተዳደር የሚያስችል ሥራ አገኘሁ።
በዚህ ጊዜ አባቴ አቅኚ ሆኖ ያገለግል ነበር። አንድ ቀን ናዚዎች መጥተው የአባቴን ቤት ፈተሹ። መጽሐፍ ቅዱሱንና የመጽሐፍ ቅዱስ ኮንኮርዳንሶቹን ጨምሮ ጽሑፎቹን ሁሉ ወሰዱበት። በዚህ ወቅት የምናገኘው መንፈሳዊ ምግብ እጅግ ጥቂት ነበር። በመንፈሳዊ ጠንክረን ለመቀጠል ገቨርንመንት እንደሚለው ያሉትን መጻሕፍት ደግመን ደጋግመን እናጠና ነበር፤ ስብከታችንንም አላቋረጥንም።
የሚያሳዝነው ግን በብዙ አካባቢዎች ወንድሞች ተከፋፍለው ነበር። አንዳንዶቹ በግልጽ መስበክና ከቤት ወደ ቤት መሄድ አለብን ሲሉ ሌሎች ደግሞ ሰዎችን በሌሎች መንገዶች በማነጋገር በምሥጢር መሥራት አለብን ይሉ ነበር። ከዚህ የተነሣ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ቀደም ሲል በሚገባ ተባብረው ይሠሩ የነበሩ እጅግ የምንወዳቸው ወንድሞች እርስ በርሳቸው መነጋገር አቁመው ነበር። የይሖዋ ምሥክር ሆኜ ባሳለፍኳቸው ዓመታት በእነርሱ መካከል ያየሁትን መለያየት ያክል ስሜቴን ያቆሰለ ነገር አላጋጠመኝም።
ከጦርነቱ በኋላ አዲስ እንቅስቃሴ ተጀመረ
ከጦርነቱ በኋላ በ1945 የበጋ ወራት ወንድም ዴይ ወደ ኖርዌይ መጥቶ በኦስሎ፣ በሻንና በበርገን ስብሰባዎችን አደረገ። ወንድሞች ቅሬታዎቻቸውን እንዲያስወግዱ ካግባባቸው በኋላ እንዲህ ማድረግ የሚፈልጉ ተነሥተው እንዲቆሙ ጠየቀ። ሁሉም ተነሥተው ቆሙ! ውዝግቡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የተፈታው በወቅቱ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ፕሬዚዳንት የነበረው ወንድም ናታን ኤች ኖር በታኅሣሥ 1945 ካደረገው ጉብኝት በኋላ ነው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሐምሌ 17, 1945 ከቅርንጫፍ አገልጋዩ ከወንድም ኤኖክ ኦማን ‘ወደ ቤቴል መቼ ልትመለሽ ትችያለሽ?’ የሚል የቴሌግራም መልእክት ደረሰኝ። አንዳንዶች ቤት ሆኜ ከ70 ዓመት በላይ የሆነውን አባቴን መጦር እንደሚገባኝ ይነግሩኝ ነበር። ይሁን እንጂ አባቴ የቤቴል አገልግሎቴን እንድቀጥል ስለ አበረታታኝ እንደገና አገልግሎቴን ጀመርኩ። በ1946 ከዩናይትድ ስቴትስ ወንድም ማርቨን ኤፍ አንደርሰን የቅርንጫፍ ቢሮው የበላይ ተመልካች ሆኖ ተሾመ፤ የስብከቱ ሥራም እንደ አዲስ ተደራጀ።
በበጋው የእረፍት ጊዜዬ ወደ ኮፐርቪክ እየሄድኩ ቤተሰቦቼን እጠይቃቸው ነበር። ሁለቱ ወንድሞቼና ሁለቱ እህቶቼ የይሖዋ ምሥክር ባይሆኑም አባቴንም ሆነ እኔን አይቃወሙንም ነበር። አንደኛው ወንድሜ የወደብ ኃላፊ ሲሆን ሌላው ደግሞ አስተማሪ ነበር። እኔ በቁሳዊ ሁኔታ ያለኝ ነገር ከእነርሱ ያነሰ ቢሆንም አባቴ “ኦቲሊ ከእናንተ ይልቅ ሃብታም ነች” ይላቸው ነበር። ደግሞም እውነቱን ነበር! እነርሱ ያካበቱት ነገር እኔ ካገኘሁት መንፈሳዊ ብልጽግና ጋር ፈጽሞ ሊወዳደር አይችልም! አባቴ በ78 ዓመቱ በ1951 በሞት ተለየን። እናቴ የሞተችው በ1928 ነበር።
በ1953 በኒው ዮርክ ከተማ በተካሄደው የይሖዋ ሕዝቦች ዓለም አቀፍ ስብሰባ ላይ መገኘት መቻሌ በሕይወቴ ውስጥ እጅግ ካስደሰቱኝ ነገሮች አንዱ ነው። የዓለም አቀፉ የአስፋፊዎች ቁጥር ከ500,000 ያለፈው በዚያው ዓመት ሲሆን ከ165,000 በላይ በስብሰባው ላይ ተገኝተው ነበር! በ1953 ከተካሄደው ስብሰባ በፊት በይሖዋ ምድራዊ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ማለትም በብሩክሊን ቤቴል ለአንድ ሳምንት ያክል ሠርቻለሁ።
የአቅሜን ያህል ማከናወን
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ካታራክት በተባለ በሽታ ምክንያት ዓይኔ ደክሟል። አሁንም ቢሆን በትላልቁ የተጻፉ ፊደላትን ከፍተኛ ኃይል ባለው መነፅርና የማጉያ መስተዋት በመጠቀም ትንሽ ትንሽ አነባለሁ። በሳምንት ሁለት ጊዜም ክርስቲያን እህቶች እየመጡ ያነቡልኛል፤ ለዚህም በጣም አመስጋኝ ነኝ።
የስብከት እንቅስቃሴዬም ቢሆን የተወሰነ ነው። አልፎ አልፎ በበጋ ወራት ክርስቲያን እህቶች በተሽከርካሪ ወንበሬ ላይ ሆኜ ጥቂት የስብከት ሥራ ማከናወን ወደምችልበት ቦታ ይዘውኝ ይሄዳሉ። እንዲሁም አንድ መቶ ከሚጠጋ ዓመት በፊት የተማርኩበትን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመሳሰሉት በኮፐርቪክ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መጽሔቶችንና ብሮሹሮችን በፖስታ እልካለሁ። አሁንም አዘውታሪ አስፋፊ መሆን መቻሌ ያስደስተኛል።
ደግነቱ የእኔ ማደሪያ ያለው ከኦስሎ ውጭ በምትገኘው በኢትሬ ኤኔባክ በ1983 በተገነባው ቤቴል የምግብ መመገቢያውና የመንግሥት አዳራሹ በሚገኙበት ሕንጻ ላይ ነው። በመሆኑም ለጠዋት አምልኮ፣ ለምግብና ለስብሰባዎች በምርኩዝ ተደግፌ መሄድ እችላለሁ። አሁንም ቢሆን ወደ አውራጃ ስብሰባዎችና ሌሎች ትላልቅ ስብሰባዎች ለመሄድ በመቻሌ ደስ ይለኛል። ለረጅም ዓመታት የማውቃቸውን ወዳጆቼን፣ አዳዲስ ወንድሞችና እህቶችን እንዲሁም ብዙ ደስ የሚሉ ሕፃናትን ሳገኝ ደስ ይለኛል።
እምነትን እስከ መጨረሻው መጠበቅ
እዚህ ቤቴል ውስጥ ንቁ፣ አስደሳችና መንፈሳዊ በሆኑ ሰዎች ተከብቦ መኖር በረከት ነው። የቤቴል አገልግሎቴን በጀመርኩበት ጊዜ ሁሉም የቤቴል አባላት ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ነበሩ። (ፊልጵስዩስ 3:14) ዛሬ ግን ከእኔ በቀር ቤቴል ያሉት ሁሉም በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ናቸው።
እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ቀደም ብሎ እርምጃ ይወስዳል ብለን ጠብቀን ነበር። ይሁንና እጅግ ብዙ ሰዎች በቁጥር እየጨመሩ መሄዳቸውን ሳይ እጅግ ደስ ይለኛል። በሕይወት ዘመኔ ያየሁት ጭማሪ እንዴት አስገራሚ ነው! ለመጀመሪያ ጊዜ በአገልግሎት ስካፈል በዓለም ዙሪያ የነበሩት አስፋፊዎች ቁጥር 5,000 ያህል ብቻ ነበር። ዛሬ ግን ከ5,400,000 የሚበልጡ አስፋፊዎች አሉ! በእርግጥም ‘ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሽ ለብዙ ሕዝብ ሲሆን’ ተመልክቻለሁ። (ኢሳይያስ 60:22) ነቢዩ ዕንባቆም “ቢዘገይም በእርግጥ ይመጣልና ታገሠው፤ እርሱም አይዘገይም” ሲል እንደጻፈው ይሖዋን በጉጉት እየተጠባበቅን መኖር ይገባናል።—ዕንባቆም 2:3