ይሖዋ በሙሉ ነፍስ የምታቀርቡትን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል
“ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት [“በሙሉ ነፍስ፣” NW] አድርጉት።”—ቆላስይስ 3:23
1, 2. (ሀ) ልናገኘው ከምንችለው መብት ሁሉ እጅግ የላቀው መብት የትኛው ነው? (ለ) አንዳንድ ጊዜ በአምላክ አገልግሎት መሥራት የምንፈልገውን ያህል መሥራት ሳንችል የምንቀረው ለምን ሊሆን ይችላል?
ይሖዋን ማገልገል ልናገኛቸው ከምንችላቸው መብቶች ሁሉ እጅግ የላቀ መብት ነው። ይህ መጽሔት ከረጅም ጊዜ አንስቶ ክርስቲያኖች በአገልግሎቱ ሥራ እንዲካፈሉና አልፎ ተርፎም የሚቻል ከሆነ “የበለጠ ሙሉ በሙሉ” እንዲያገለግሉ ሲያበረታታ መቆየቱ ተገቢ ነው። (1 ተሰሎንቄ 4:1 NW) ይሁን እንጂ በአምላክ አገልግሎት ሁልጊዜ የፈለግነውን ያህል ለመሥራት ይሳካልናል ማለት አይደለም። ከተጠመቀች 40 ዓመት ገደማ የሆናት አንዲት ነጠላ እህት እንዲህ ብላለች:- “እንደ ሁኔታዬ ቢሆን ኖሮ ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት መግባት ነበረብኝ። ተቀጥሬ ለመሥራት የተገደድኩት የሕክምና ወጪዎቼን ጨምሮ የግድ የሚያስፈልጉኝን ነገሮች ለማሟላት እንጂ ውድና የፋሽን ልብሶችን ለመግዛት ወይም እረፍት ወስጄ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ ሽርሽር ለማድረግ አይደለም። ለይሖዋ ትራፊዬን እየሰጠሁት እንዳለ ሆኖ ይሰማኛል።”
2 ለአምላክ ያለን ፍቅር በስብከቱ ሥራ የተቻለንን ያክል እንድንሠራ ይገፋፋናል። ይሁን እንጂ ብዙውን ጊዜ በሕይወታችን ውስጥ ያሉት ሁኔታዎች አቅማችንን ይገድቡብናል። የቤተሰብ ኃላፊነቶችን ጨምሮ ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎችን መወጣት አብዛኛውን ጊዜያችንንና ጉልበታችንን የሚጠይቅ ይሆናል። (1 ጢሞቴዎስ 5:4, 8) በእነዚህ ‘አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት’ ውስጥ ሕይወት ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ተፈታታኝ ሆኗል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1) በአገልግሎቱ የምንፈልገውን ያክል መሥራት ሳንችል ስንቀር እንጨነቅ ይሆናል። አምላክ በምናቀርበው አገልግሎት ስለመደሰቱም ጥርጣሬ ይገባን ይሆናል።
በሙሉ ነፍስ የሚቀርብ አገልግሎት ያለው ውበት
3. ይሖዋ ከሁላችንም የሚጠብቀው ምንድን ነው?
3 መጽሐፍ ቅዱስ በመዝሙር 103:14 ላይ ይሖዋ ‘ፍጥረታችንን ያውቃልና፤ አፈር መሆናችንን ያስባል’ በማለት የሚያጽናና ማረጋገጫ ይሰጠናል። እርሱ ያሉብንን የአቅም ገደቦች ከማንም በላይ ያውቃል። ከአቅማችን በላይ አይጠይቅብንም። ይሖዋ ከእኛ የሚጠብቀው ነገር ምንድን ነው? እያንዳንዱ ሰው ሁኔታው ምንም ይሁን ምን ሊያደርገው የሚችለውን ነገር ነው። ይህም እንደሚከተለው ተብሎ ተገልጿል:- “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ፣ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት [“በሙሉ ነፍስ፣” NW] አድርጉት።” (ቆላስይስ 3:23) አዎን፣ ይሖዋ ሁላችንም በሙሉ ነፍስ እንድናገለግለው ይጠብቅብናል።
4. ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ማለት ምን ማለት ነው?
4 ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ማለት ምን ማለት ነው? “በሙሉ ነፍስ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል ጥሬ ፍቺ “ከነፍስ” ማለት ነው። “ነፍስ” አካላዊና አእምሯዊ ችሎታን ጨምሮ የአንድ ሰው ሁለንተና ማለት ነው። በመሆኑም በሙሉ ነፍስ ማገልገል ማለት ለአምላክ አገልግሎት ራሳችንን ማቅረብ፣ ችሎታችንን ሙሉ በሙሉ መጠቀም፣ የመጨረሻ ኃይላችንን ተጠቅመን ማገልገል ማለት ነው። በአጭር አነጋገር ነፍሳችን ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ማድረግ ማለት ነው።—ማርቆስ 12:29, 30
5. የሐዋርያቱ ምሳሌ ሁሉም ሰው በአገልግሎት እኩል መጠን ያለው ነገር እንደማያከናውን የሚያሳየው እንዴት ነው?
5 በሙሉ ነፍስ ማገልገል ማለት ሁላችንም በአገልግሎት የምናከናውነው መጠን እኩል መሆን አለበት ማለት ነውን? የእያንዳንዱ ሰው ሁኔታና ችሎታ ስለሚለያይ በፍጹም እንደዚያ ማለት አይደለም። የታመኑትን የኢየሱስ ሐዋርያት ምሳሌ ተመልከት። ሁሉም እኩል መጠን ያለው አገልግሎት ማከናወን አልቻሉም ነበር። ለምሳሌ ያህል ስለ ቀነናዊው ስምዖንና ስለ እልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ እምብዛም የምናውቀው ነገር የለም። ምናልባትም በሐዋርያነት ያደረጉት እንቅስቃሴ ውስን ይሆናል። (ማቴዎስ 10:2-4) በአንጻሩ ደግሞ ጴጥሮስ ብዙ ከባድ ኃላፊነቶችን መቀበል ችሎ ነበር፤ ኢየሱስም ‘የመንግሥተ ሰማያትን መክፈቻ’ ሰጥቶታል። (ማቴዎስ 16:19) ይሁንና ጴጥሮስ ከሌሎች ልቆ ይታይ ነበር ማለት አይደለም። ዮሐንስ ስለ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በተገለጠለት ራእይ ውስጥ (በ96 እዘአ) ‘የአሥራ ሁለቱም ሐዋርያት ስም የተጻፈባቸው’ አሥራ ሁለት የመሠረት ድንጋዮች ተመልክቷል።a (ራእይ 21:14) አንዳንዶቹ የበለጠ መሥራት ችለው የነበረ ቢሆንም ሁሉም ሐዋርያት ያከናወኑት አገልግሎት በይሖዋ ፊት ትልቅ ዋጋ ነበረው።
6. ኢየሱስ ስለ ዘሪው በሰጠው ምሳሌ ውስጥ “በመልካም መሬት” ላይ የወደቀው ዘር ምን ውጤት ነበረው? ምን ጥያቄዎችስ ይነሣሉ?
6 በተመሳሳይም ይሖዋ ሁላችንም እኩል መጠን ያለው የስብከት ሥራ እንድንሠራ አይጠብቅብንም። ኢየሱስ ስለ ዘሪው በተናገረው ምሳሌ ላይ ይህን ጉዳይ ጠቅሷል፤ በዚህ ምሳሌ ውስጥ የስብከቱ ሥራ ዘርን ከመዝራት ጋር ተመሳስሎ ተገልጿል። ዘሩ የወደቀው በተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ላይ ሲሆን ይህም መልእክቱን የሚሰሙ ሰዎች የሚያሳዩትን የተለያየ የልብ ዝንባሌ ያመለክታል። ኢየሱስ እንዲህ በማለት አስረድቷል:- “በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤ እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል።” (ማቴዎስ 13:3-8, 18-23) ይህ ፍሬ ምንድን ነው? መጠኑ የተለያየውስ ለምንድን ነው?
7. የተዘራው ዘር ፍሬ ምንድን ነው? የፍሬውስ መጠን የተለያየው ለምንድን ነው?
7 የተዘራው ዘር “የመንግሥቱ ቃል” በመሆኑ ፍሬ ማፍራቱ የቃሉን ስርጭት ማለትም ለሌሎች መነገሩን ያመለክታል። (ማቴዎስ 13:19) ፍሬው ከሠላሳ አንስቶ እስከ መቶ ድረስ የተለያየ የሆነው የእያንዳንዱ ሰው ሁኔታም ሆነ ችሎታ ስለሚለያይ ነው። ጥሩ ጤናና አካላዊ ሁኔታ ያለው ሰው ሥር በሰደደ የጤና ችግር ወይም በዕድሜ መግፋት ምክንያት አቅሙ ከተመናመነ ሰው የበለጠ ብዙ ጊዜ በስብከቱ ሥራ ማሳለፍ ይችል ይሆናል። ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሙሉ ቀን መሥራት ከሚጠበቅበት ሰው ይልቅ ከቤተሰብ ኃላፊነት ነፃ የሆነ ነጠላ ወጣት የበለጠ ሊሠራ ይችል ይሆናል።—ከምሳሌ 20:29 ጋር አወዳድር።
8. ይሖዋ ነፍሳቸው የሚፈቅድላቸውን ምርጣቸውን የሚሰጡትን ሰዎች እንዴት ይመለከታቸዋል?
8 በአምላክ ዓይን ሲታይ በሙሉ ነፍስ በማገልገል ሠላሳ ፍሬ ያፈራው ሰው መቶ ፍሬ ያፈራውን ሰው ያህል የታመነ አይደለም ማለት ነውን? በፍጹም! የፍሬው መጠን ሊለያይ ቢችልም ነፍሳችን የቻለውን ያክል በማገልገል ምርጣችንን ከሰጠነው ይሖዋ ይደሰታል። የተለያየ መጠን ያላቸው ፍሬዎች የተገኙት ‘በመልካም መሬት’ ከተመሰሉት ልቦች እንደሆነ አትዘንጋ። “መልካም” ተብሎ የተተረጎመው (ካሎስ የሚለው) የግሪክኛ ቃል “ልብን የሚማርክና ለማየት ደስ የሚል” “ውብ” ነገርን ያመለክታል። የተቻለንን ሁሉ ስናደርግ ልባችን በአምላክ ዓይን ውብ ሆኖ እንደሚታይ ማወቅ እንዴት የሚያጽናና ነው!
አንዳችንን ከሌላው ጋር አያወዳድረንም
9, 10. (ሀ) ልባችን ወደ ምን አሉታዊ አስተሳሰብ ሊመራን ይችላል? (ለ) በ1 ቆሮንቶስ 12:14-26 ላይ ያለው ምሳሌ ይሖዋ የምናደርገውን ነገር በመመልከት ከሌሎች ጋር እንደማያወዳድረን የሚያሳየው እንዴት ነው?
9 ይሁን እንጂ ፍጹም ያልሆነው ልባችን ነገሮችን የሚመዝንበት መንገድ የተለየ ሊሆን ይችላል። አገልግሎታችንን ከሌሎች ጋር ያወዳድር ይሆናል። ‘ሌሎች ከእኔ ይበልጥ በአገልግሎቱ ብዙ እየሠሩ ነው። ታዲያ ይሖዋ በእኔ አገልግሎት እንዴት ሊደሰት ይችላል?’ ብለን እንድናስብ ያደርገን ይሆናል።—ከ1 ዮሐንስ 3:19, 20 ጋር አወዳድር።
10 የይሖዋ ሐሳቦችና መንገዶች ከእኛ እጅግ ከፍ ያሉ ናቸው። (ኢሳይያስ 55:9) ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የምናደርገውን ጥረት እንዴት እንደሚመለከተው ከ1 ቆሮንቶስ 12:14-26 አንዳንድ ነገሮችን ጠለቅ ብለን ማስተዋል እንችላለን፤ በዚህ ጥቅስ ላይ ጉባኤው እንደ ዓይን፣ እጅ፣ እግር፣ ጆሮ የመሳሰሉት ብዙ ብልቶች ካሉት አካል ጋር ተነጻጽሯል። እስቲ ጥቂት ቆም ብለህ ስለ ሰብዓዊ አካል አስብ። ዓይንህን ከእጅህ ወይም ደግሞ እግርህን ከጆሮዎችህ ጋር ማወዳደር እንዴት ያለ ቀልድ ይሆናል! እያንዳንዱ ብልት የየራሱ ተግባር አለው፤ ይሁንና ሁሉም ብልቶች ጠቃሚና ትልቅ ግምት የሚሰጣቸው ናቸው። በተመሳሳይም ሌሎች የበለጠ ሠሩም ያነሰ ይሖዋ አንተ በሙሉ ነፍስህ የምታቀርበውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ገላትያ 6:4
11, 12. (ሀ) አንዳንዶች “ደካሞች” ወይም “ያልከበሩ” እንደሆኑ የሚሰማቸው ለምን ሊሆን ይችላል? (ለ) ይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት የሚመለከተው እንዴት ነው?
11 አንዳንድ ጊዜ በጤና ችግር፣ በዕድሜ መግፋት ወይም በሌሎች ሁኔታዎች አቅማችን በመገደቡ ምክንያት “ደካሞች” ወይም ‘ያልከበርን’ እንደሆንን ይሰማን ይሆናል። ይሁን እንጂ የይሖዋ አመለካከት ከዚህ የተለየ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይለናል:- “ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ . . . ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፣ . . . ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፣ ለጐደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው።” (1 ቆሮንቶስ 12:22-24) በመሆኑም እያንዳንዱ ግለሰብ በይሖዋ ዘንድ የተወደደ መሆን ይችላል። ያሉብንን የአቅም ገደቦች ግምት ውስጥ በማስገባት የምናቀርበውን አገልግሎት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። የሰው ችግር የሚገባውንና አፍቃሪ የሆነውን እንዲህ ዓይነቱን አምላክ ለማገልገል የቻልከውን ሁሉ እንድታደርግ ልብህ አይገፋፋህምን?
12 በመሆኑም ይሖዋ የሚፈልገው ሌሎች የሚያደርጉትን ያህል ማድረግህን ሳይሆን አንተ በግልህ ማለትም ነፍስህ ማድረግ የሚችለውን ያህል ማድረግህን ነው። ኢየሱስ በምድራዊ ሕይወቱ የመጨረሻ ቀናት ፈጽሞ ተቃራኒ ሁኔታ ለነበራቸው ሁለት ሴቶች የነበረው አመለካከት ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ የምናደርገውን ጥረት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከት ልብ በሚነካ መንገድ የሚያሳይ ነው።
የአንዲት አድናቂ ሴት “ዋጋው እጅግ የከበረ” ስጦታ
13. (ሀ) ማርያም ግሩም መዓዛ ያለውን ሽቱ በኢየሱስ ራስና እግር ላይ ባፈሰሰች ጊዜ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል ነበር? (ለ) የማርያም ሽቱ ዋጋው ምን ያህል ነበር?
13 ኢየሱስ ዓርብ ዕለት ምሽት ኒሳን 8 ከኢየሩሳሌም ሦስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከደብረ ዘይት ተራራ በስተ ምሥራቅ ወደምትገኘው ትንሽ መንደር፣ ወደ ቢታንያ መጣ። ኢየሱስ በዚህች ትንሽ ከተማ ውስጥ እንደ ማርያም፣ ማርታና እንደ ወንድማቸው አልዓዛር የመሳሰሉ የቅርብ ወዳጆች አሉት። ኢየሱስ በእንግድነት (ምናልባትም በተደጋጋሚ ጊዜ) ወደ ቤታቸው ይሄድ ነበር። ቅዳሜ ዕለት ምሽት ግን ኢየሱስና ወዳጆቹ የተስተናገዱት ስምዖን በሚባል ሰው ቤት ውስጥ ነበር፤ ይህ ሰው ቀደም ሲል የሥጋ ደዌ ሕመም የነበረበት ሲሆን የፈወሰው ኢየሱስ ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ በማዕድ ተቀምጦ ሳለ ማርያም ወንድሟን ከሞት ላስነሳላት ሰው ያላትን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ትሕትና የተሞላበት ነገር አደረገች። “ዋጋው እጅግ የከበረ” ጥሩ መዓዛ ያለው ዘይት የያዘ ብልቃጥ አምጥታ ከፈተችው። በእርግጥም ይህ ሽቱ ዋጋው እጅግ ውድ ነበር! ቢሸጥ 300 ዲናር ያወጣ የነበረ ሲሆን ይህም የአንድ ሰው የዓመት ገቢ ነው። ይህንን ጣፋጭ መዓዛ ያለው ዘይት በኢየሱስ ራስና እግር ላይ አፈሰሰች። ከዚህም በላይ እግሩን በፀጉሯ አበሰች።—ማርቆስ 14:3፤ ሉቃስ 10:38-42፤ ዮሐንስ 11:38-44፤ 12:1-3
14. (ሀ) ደቀ መዛሙርቱ ማርያም ያደረገችውን ነገር እንዴት ተመለከቱት? (ለ) ኢየሱስ ማርያም ያደረገችውን ነገር የደገፈው እንዴት ነበር?
14 ደቀ መዛሙርቱ በዚህ ነገር እጅግ ተቆጡ! ‘ገንዘቡ ለምን ይባክናል?’ ሲሉ ጠይቀዋል። ይሁዳ ስውር የስርቆት ምኞቱን በልቡ ይዞ ለችግረኞች ችሮታ እንዲውል የፈለገ ይመስል “ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው?” አለ። ማርያም ምንም አልተነፈሰችም። ይሁን እንጂ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ:- “ተውአት ስለ ምን ታደክሙአታላችሁ? መልካም [ካሎስ ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተወሰደ ነው] ሥራ ሠርታልኛለች። . . . የተቻላትን አደረገች፤ አስቀድማ ለመቃብሬ ሥጋዬን ቀባችው። እውነት እላችኋለሁ፣ ይህ ወንጌል በዓለሙ ሁሉ በሚሰበክበት በማናቸውም ስፍራ፣ እርስዋ ያደረገችው ደግሞ ለእርስዋ መታሰቢያ ሊሆን ይነገራል።” እነዚህ የሚያጽናኑ የኢየሱስ ቃላት የማርያምን ልብ ምንኛ አረጋግተውላት ይሆን!—ማርቆስ 14:4-9፤ ዮሐንስ 12:4-8
15. ኢየሱስ ማርያም ባደረገችው ነገር ልቡ በጣም የተነካው ለምን ነበር? እኛስ በሙሉ ነፍስ የሚቀርብን አገልግሎት በሚመለከት ከዚህ ምን እንማራለን?
15 ኢየሱስ ማርያም ባደረገችው ነገር ልቡ በጥልቅ ተነክቶ ነበር። በእርሱ አመለካከት ያደረገችው ነገር የሚያስመሰግን ነበር። ኢየሱስ ያተኮረው በስጦታው ውድነት ላይ ሳይሆን ‘የተቻላትን በማድረጓ’ ላይ ነው። አጋጣሚውን ተጠቅማ መስጠት የምትችለውን ነገር ሰጥታለች። ሌሎች ትርጉሞች እነዚህን ቃላት “የምትችለውን ሁሉ አድርጋለች” ወይም “አቅሟ የሚፈቅድላትን አድርጋለች” በማለት አስቀምጠዋቸዋል። (አን አሜሪካን ትራንስሌሽን፤ ዘ ጀሩሳሌም ባይብል) ማርያም የሰጠችው ምርጧን ስለነበር በሙሉ ነፍሷ ያደረገችው ነገር ነበር። በሙሉ ነፍስ የሚቀርብ አገልግሎትም ትርጉሙ ከዚህ የተለየ አይደለም።
የመበለቲቱ ‘ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች’
16. (ሀ) ኢየሱስ አንዲት ድሃ መበለት ያኖረችውን መዋጮ ሊያስተውል የቻለው እንዴት ነው? (ለ) የመበለቲቱ ሳንቲሞች ዋጋቸው ምን ያህል ነበር?
16 ከጥቂት ቀናት በኋላ ማለትም በኒሳን 11፣ ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ብዙ ሰዓታት አሳለፈ፤ በዚሁ ጊዜም በምን ሥልጣን ነገሮችን እንደሚያደርግ እንዲሁም ቀረጥን፣ ትንሣኤንና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት ለቀረቡለት አስቸጋሪና ድንገተኛ ጥያቄዎች መልስ ሲሰጥ ቆየ። ጻፎችንና ፈሪሳውያንንም ከሚያደርጓቸው ሌሎች ነገሮች በተጨማሪ ‘የመበለቶችን ቤት ስለሚበሉ’ አወገዛቸው። (ማርቆስ 12:40) ከዚያም ኢየሱስ ከሁኔታዎች ለመረዳት እንደሚቻለው ወደ ሴቶች ሸንጎ ገብቶ አረፍ አለ፤ በዚህ ቦታ በአይሁዳውያን ወግ መሠረት 13 የገንዘብ ማስቀመጫ ዕቃዎች ተቀምጠው ነበር። ኢየሱስ ለጥቂት ጊዜ ተቀምጦ ሰዎች መዋጮአቸውን ሲያኖሩ በጥንቃቄ ይመለከት ነበር። ብዙ ሃብታሞች መዋጮ ለማድረግ የመጡ ሲሆን ምናልባትም የአንዳንዶቹ ሁኔታ ራስን የማመጻደቅ አልፎ ተርፎም የይታይልኝ ዓይነት መንፈስ የሚያንጸባርቅ ሳይሆን አይቀርም። (ከማቴዎስ 6:2 ጋር አወዳድር።) የኢየሱስ ትኩረት አንዲት ሴት ላይ አረፈ። ሌላ ሰው ቢሆን ስለ እርሷም ሆነ ስላኖረችው ስጦታ የተለየ ነገር ላያስተውል ይችላል። ይሁን እንጂ የሌሎችን ልብ የማወቅ ችሎታ የነበረው ኢየሱስ “ድሃ መበለት” መሆኗን አውቋል። ምን ያህል ስጦታ እንዳስቀመጠችም በትክክል ያውቅ ነበር፤ “እጅግ አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች” ነበሩ።b—ማርቆስ 12:41, 42 NW
17. ኢየሱስ መበለቲቱ ያደረገችውን መዋጮ እንዴት ተመልክቶታል? ለአምላክ መስጠትን በሚመለከት ከዚህ ምን እንማራለን?
17 ኢየሱስ ሊያስተምራቸው የፈለገውን ነገር በዓይናቸው እንዲያዩ ሲል ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠራቸው። ኢየሱስ ይህች መበለት “በመዝገብ ውስጥ . . . ከሁሉ አብልጣ ጣለች” ሲል ተናገረ። በእርሱ አመለካከት ሌሎች የጣሉት በአንድ ላይ ቢደመር እንኳ ከእርሷ ጋር አይተካከልም። “የነበራትን ሁሉ” ማለትም እጅዋ ላይ የቀረቻትን ጥቂት ገንዘብ ሰጠች። ይህ፣ ይሖዋ እንደሚንከባከባት ተማምና እንደነበር ያሳያል። በመሆኑም ለአምላክ በመስጠት እንደ ምሳሌ ተደርጋ የተጠቀሰችው ከቁሳዊ ጠቀሜታ አንጻር እምብዛም ዋጋ ያልነበረው ስጦታ ያመጣችው ሴት ናት። ይሁን እንጂ ስጦታዋ በአምላክ ፊት በገንዘብ የማይተመን ዋጋ ነበረው!—ማርቆስ 12:43, 44፤ ያዕቆብ 1:27
ይሖዋ በሙሉ ነፍስ ለሚቀርብ አገልግሎት ካለው አመለካከት መማር
18. ኢየሱስ ሁለቱን ሴቶች በሚመለከት ከተናገረው ነገር ምን እንማራለን?
18 ኢየሱስ እነዚህን ሁለት ሴቶች በሚመለከት ከተናገረው ነገር ይሖዋ በሙሉ ነፍስ ለሚቀርብ አገልግሎት ምን አመለካከት እንዳለው ልብ የሚነካ ትምህርት እናገኛለን። (ዮሐንስ 5:19) ኢየሱስ መበለቲቱን ከማርያም ጋር አላወዳደራትም። የመበለቲቱን ሁለት ሳንቲሞች ማርያም ካመጣችው “ዋጋው እጅግ የከበረ” ሽቱ ባላነሰ መንገድ ከፍ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። ሁለቱም ሴቶች የሰጡት ምርጣቸውን በመሆኑ በአምላክ ዘንድ የሁለቱም ስጦታ ትልቅ ግምት የሚሰጠው ነበር። እንግዲያስ በአምላክ አገልግሎት የምትፈልገውን ያክል መሥራት ባለመቻልህ ምክንያት ዋጋ ቢስ እንደሆንክ ቢሰማህ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ መስጠት የቻልከውን ምርጥህን ለመቀበል ደስተኛ ነው። ይሖዋ ‘የሚያየው ልብን እንደሆነ’ አትዘንጋ፤ በመሆኑም የልብህን ፍላጎት በሚገባ ያውቃል።—1 ሳሙኤል 16:7
19. ሌሎች በአምላክ አገልግሎት የሚያከናውኑትን ነገር በሚመለከት ፈራጆች መሆን የሌለብን ለምንድን ነው?
19 ይሖዋ በሙሉ ነፍስ ለሚቀርብ አገልግሎት ያለው አመለካከት አንዳችን ለሌላው የሚኖረንን አመለካከትና አያያዝ ሊነካው ይገባል። የሌሎችን ጥረት ማንኳሰስ ወይም የአንድን ሰው አገልግሎት ከሌላው ጋር ማወዳደር ምንኛ ፍቅር የጎደለው ድርጊት ይሆናል! የሚያሳዝነው አንዲት ክርስቲያን እንዲህ ስትል ጽፋለች:- “አንዳንድ ጊዜ አንዳንዶች አቅኚ ካልሆናችሁ ዋጋ የላችሁም የሚሉ ይመስላሉ። አዘውታሪ የመንግሥቱ አስፋፊ ‘እንኳ’ ለመሆን የሚንገታገተው እንደ እኛ ያለውም ቢሆን አድናቆት ይሻል።” ሌላው መሰል ክርስቲያን የሚያከናውነው አገልግሎት የሙሉ ነፍስ ነው አይደለም ብለን የመፍረድ ሥልጣን እንዳልተሰጠን አንዘንጋ። (ሮሜ 14:10-12) ይሖዋ በሚልዮን የሚቆጠሩት የታመኑ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የሚያከናውኑትን የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው ሁሉ እኛም እንዲሁ ልናደርግ ይገባናል።
20. ብዙውን ጊዜ መሰል አምላኪዎችን በተመለከተ ምን ብሎ ማሰቡ ከሁሉ የተሻለ ይሆናል?
20 ይሁን እንጂ አንዳንዶች በአገልግሎት ሊያደርጉት ከሚችሉት ያነሰ ነገር እያከናወኑ ቢሆንስ? አንድ ክርስቲያን የሚያደርገው እንቅስቃሴ መቀነሱ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ሽማግሌዎች ይህ አስፋፊ እርዳታ ወይም ማበረታቻ እንደሚያስፈልገው የሚጠቁም ነው። በአንጻሩ ደግሞ የአንዳንዶች የሙሉ ነፍስ አገልግሎት እንደ ማርያም ውድ ሽቱ ሳይሆን ከመበለቲቱ ትንንሽ ሳንቲሞች እምብዛም የማይበልጥ እንደሚሆን ልንዘነጋ አይገባንም። ብዙውን ጊዜ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሖዋን እንደሚያፈቅሩና በእንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ተገፋፍተው የሚችሉትን ያህል (ትንሽ ሳይሆን) ብዙ ለመሥራት እንደሚጥሩ ማሰብ ከሁሉ የተሻለ ይሆናል። የትኛውም ንቁ የይሖዋ አገልጋይ በአምላክ አገልግሎት ከሚችለው በታች ለመሥራት እንደማይመርጥ የተረጋገጠ ነው!—1 ቆሮንቶስ 13:4, 7
21. ብዙዎች በምን የሚክስ መስክ ተሠማርተዋል? ምን ጥያቄዎችስ ይነሣሉ?
21 ይሁን እንጂ ለብዙዎቹ የአምላክ ሕዝቦች የሙሉ ነፍስ አገልግሎት ማለት እጅግ የሚክስ በሆነው የአቅኚነት አገልግሎት መሠማራት ማለት ሆኗል። እነዚህ አቅኚዎች የሚያገኟቸው በረከቶች ምንድን ናቸው? አቅኚ መሆን የማንችለውስ የአቅኚነትን መንፈስ ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ ውስጥ መልስ ያገኛሉ።
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a በይሁዳ ፋንታ የተተካው ሐዋርያ ማትያስ ስለሆነ በአሥራ ሁለቱ የመሠረት ድንጋይ ላይ ከሰፈሩት ስሞች መካከል አንዱ የእርሱ እንጂ የጳውሎስ አይሆንም። ጳውሎስ ሐዋርያ ቢሆንም ከአሥራ ሁለቱ አንዱ አልነበረም።
b እነዚህ ሳንቲሞች እያንዳንዳቸው አንድ አንድ ሌፕተን ሲሆኑ በወቅቱ ይሠራባቸው ከነበሩት የአይሁዳውያን ሳንቲሞች ሁሉ የመጨረሻዎቹ ትንንሽ ሳንቲሞች ናቸው። የሁለት ሌፕታ ዋጋ የአንድ ቀን ምንዳ 1/64ኛ ነው። እንደ ማቴዎስ 10:29 ገለጻ አንድ ሰው በአንድ አሳሪዮን ሳንቲም (ይህ ከስምንት ሌፕታ ጋር የሚተካከል ነው) ሁለት ድንቢጦች መግዛት ይችል ነበር፤ እነዚህ፣ ድሃ የሆኑ ሰዎች ለመብል የሚጠቀሙባቸው በጣም ርካሽ ወፎች ናቸው። ይህቺ መበለት ግን የነበራት ገንዘብ ለአንድ ጊዜ ምግብ እንኳ የማትበቃውን አንዲት ድንቢጥ ለመግዛት ከሚያስችለው ዋጋ ግማሽ ያህል ብቻ ነበር። በእርግጥም ይህች ሴት ድሃ ነበረች።
ምን ብለህ ትመልሳለህ?
◻ ይሖዋን በሙሉ ነፍስ ማገልገል ማለት ምን ማለት ነው?
◻ በ1 ቆሮንቶስ 12:14-26 ላይ የሚገኘው ምሳሌ ይሖዋ ከሌሎች ጋር እንደማያወዳድረን የሚያሳየው እንዴት ነው?
◻ ኢየሱስ የማርያምን ውድ የሆነ ሽቱና የመበለቲቱን ሁለት ሳንቲሞች በሚመለከት ከተናገረው ነገር፣ በሙሉ ነፍስ ስለሚቀርብ አገልግሎት ምን እንማራለን?
◻ ይሖዋ በሙሉ ነፍስ ስለሚቀርብ አገልግሎት ያለው አመለካከት አንዳችን ለሌላው ያለንን አመለካከት ሊነካው የሚገባው እንዴት ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ማርያም በኢየሱስ ሰውነት ላይ ‘ዋጋው እጅግ የከበረ’ ሽቱ በማርከፍከፍ ምርጧን ሰጥታለች
[በገጽ 16 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከቁሳዊ ጠቀሜታ አንጻር ሲታዩ ኢምንት የሆኑት የመበለቲቱ ሳንቲሞች በይሖዋ ፊት በገንዘብ የማይተመን ዋጋ ነበራቸው