‘የሁሉም ታናሽ ብርቱ ሕዝብ’ ሲሆን ተመልክቻለሁ
ዊልያም ዲንመን እንደተናገረው
በ1936 በዩ ኤስ ኤ ኦሪገን፣ በሴለም ከተማ በአንድ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ተገኝቼ ነበር። “የታላቁ ሕዝብ ክፍል እነማን ናቸው?” የሚል ጥያቄ በስብሰባው ላይ ቀረበ። (ራእይ 7:9፣ “ኪንግ ጄምስ ቨርሽን”) በዚያ የተገኘሁት አዲስ ሰው እኔ ብቻ ስለነበርኩ ሁሉም ወደ እኔ እያመለከቱ “አንዱ እሱ ነው!” አሉ።
በ1930ዎቹ አጋማሽ በምድር ላይ በገነት ለዘላለም የመኖር መጽሐፍ ቅዱሳዊ ተስፋ የነበራቸው የይሖዋ ምሥክሮች ቁጥር በአንፃራዊ ሁኔታ ሲታይ ጥቂት ነበር። (መዝሙር 37:29፤ ሉቃስ 23:43) ከዚያ በኋላ ነገሮች በሚያስደንቅ ሁኔታ ተለውጠዋል። በመጀመሪያ ግን በኦሪገን፣ በሴለም ከተማ የይሖዋ ምሥክሮች ስብሰባ ላይ ለመገኘት ያስቻሉኝ ሁኔታዎች ምን እንደሆኑ ልናገር።
አባቴ ቀደም ሲል ወርቃማው ዘመን ተብሎ የሚጠራው የንቁ! መጽሔት ኮንትራት ነበረው። በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ መጽሔቱን ማንበብ ያስደስተኝ ነበር፤ እንዲሁም መጽሔቱ አስፈላጊ የሆኑ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነቶችን የያዘ መሆኑን ተረድቼ ነበር። ስለዚህ በወርቃማው ዘመን የመጨረሻ ገጽ ላይ የሚወጣውን ኩፖን አንድ ቀን ሞልቼ ላክሁ። ይህ ኩፖን 20 ቡክሌቶች፣ አንድ መጽሐፍና በቅርብ የሚገኝ የይሖዋ ምሥክሮችን የጉባኤ ስም ለማግኘት የሚያስችል ነበር። ጽሑፎቹ ልክ እንደደረሱኝ ከቤት ወደ ቤት በመሄድ ቡክሌቶቹንና መጽሐፉን በጠቅላላ አበረከትኩ።
በዚያን ወቅት መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠናኝ ሰው አልነበረም። እንዲያውም ከአንድም የይሖዋ ምሥክር ጋር ተነጋግሬ አላውቅም ነበር። ይሁን እንጂ በአቅራቢያዬ የሚገኘውን የመንግሥት አዳራሽ አድራሻ ይዤ ስብሰባ ለመካፈል ወደ ኦሪገን ሴለም 40 ኪሎ ሜትር ያህል ተጓዝኩ። “የታላቁ ሕዝብ ክፍል” ተብዬ የተጠራሁት በዚያን ዕለት ሲሆን ዕድሜዬ ገና 18 ነበር።
ለአገልግሎት ምንም ዝግጅት ያላደረግሁ ቢሆንም ከሴለም ጉባኤ ጋር ማገልገል ጀመርኩ። ምሥክርነት ስሰጥ ሦስት መሠረታዊ ነገሮችን እንድጠቅስ ማበረታቻ ተሰጥቶኝ ነበር። በመጀመሪያ ይሖዋ አምላክ መሆኑን፣ ሁለተኛ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሾመ ንጉሥ መሆኑንና ሦስተኛ ደግሞ የዓለም ብቸኛው ተስፋ መንግሥቱ መሆኑን መጥቀስ ነበረ። ይህን መልእክት በየቤቱ ለማገኛቸው ሰዎች ሁሉ ለመናገር ጥረት አድርጌያለሁ።
በሴለም ከሚገኙ የይሖዋ ምሥክሮች ጋር ለሁለት ዓመታት ያህል ከተሰበሰብኩ በኋላ በሚያዝያ 3, 1938 ተጠመቅሁ። በሴለም ይገኙ የነበሩ ወንድሞች “የታላቁ ሕዝብ ክፍል” ከሆንነው መካከል ብዙዎቻችን ስንጠመቅ በማየታቸው ተደስተዋል። በየካቲት 1939 አቅኚ ወይም የሙሉ ጊዜ አገልጋይ ሆንኩ። በዚያው ዓመት በታኅሣሥ ወር የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ወደ አሪዞና እንድዛወር ግብዣ ቀረበልኝ።
አቅኚነት በአሪዞና
በአሪዞና የሚከናወነው የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ አዲስ ስለነበረና እኛን በተመለከተ ብዙ የተሳሳቱ አመለካከቶች ስለነበሩ ዩናይትድ ስቴትስ ወደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በገባችበት ወቅት ብዙ ስደቶች ደርሰውብናል። ለምሳሌ በ1942 በአሪዞና ስታፎርድ ከተማ በማገለግልበት ጊዜ የሞርሞን እምነት ተከታዮች እኛን በመቃወም ረብሻ ለማስነሳት ማሰባቸው ይወራ ነበር። እንደ አጋጣሚ ደግሞ እኔና አብረውኝ የሚያገለግሉት አቅኚዎች የምንኖረው አንድ የሞርሞን ጳጳስ የሚኖርበት አካባቢ ነበር። ይህ ሰው ለእኛ አክብሮት የነበረው ከመሆኑም በላይ “የሞርሞን ሚስዮናውያን እንደ ምሥክሮቹ ተግተው ቢሠሩ ኖሮ የሞርሞን ቤተ ክርስቲያን የት በደረሰ ነበር” ሲል ተናግሯል። ስለዚህ በቤተ ክርስቲያኑ እንዲህ በማለት በይፋ ተናግሯል:- “ምሥክሮቹን በመቃወም ረብሻ ለማስነሳት እንደታቀደ ሰምቻለሁ። የእኔ ቤትና የእነዚህ ልጆች ቤት አጠገብ ለአጠገብ ነው። ስለዚህ ረብሻ የሚነሳ ከሆነ ጠመንጃዬ ከአጥሩ ባሻገር ያነጣጥራል። ይሁን እንጂ የምተኩሰው በምሥክሮቹ ላይ አይሆንም። ከዚህ ይልቅ የምተኩሰው በረብሸኞቹ ላይ ይሆናል። ስለዚህ ረብሻ ለማስነሳት ካሰባችሁ ምን እንደሚከተል እወቁት።” የታሰበው ረብሻ ሳይነሳ ቀረ።
በአሪዞና በቆየሁባቸው ሦስት ዓመታት በርካታ ጊዜያት ተይዤ ታስሬአለሁ። አንድ ጊዜ ለ30 ቀናት ታሰርኩ። ፖሊሶች በአገልግሎታችን ላይ ችግር እንዳይፈጥሩብን ለማድረግ ስንል በራሪ ጓድ ተብሎ የሚጠራ አንድ ቡድን መሠረትን። የቡድኑ አስተባባሪ የነበረው ወንድም “እንግዲህ የምናከናውነው ነገር ልክ ስማችን እንደሚያመለክተው ነው። ጠዋት በአሥራ አንድ ሰዓት ወይም በአሥራ ሁለት ሰዓት እንነሳና በፍጥነት በየቤቱ በራፍ ላይ አንድ ትራክት ወይም ቡክሌት እያስቀመጥን እንሄዳለን” ብሎ ነገረን። የእኛ “በራሪ ጓድ” የአሪዞናን ግዛት የተወሰነ ክፍል ሸፍኗል። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ አሠራር ፍላጎት ያሳዩ ሰዎችን ለመርዳት ስላላስቻለን ተውነው።
የጊልያድ ትምህርት ቤትና ልዩ አገልግሎት
በታኅሣሥ 1942 በይሖዋ ምሥክሮች በተቋቋመው አዲስ የሚስዮናውያን ትምህርት ቤት እንዲካፈሉ በደብዳቤ ግብዣ ከቀረበላቸው በአሪዞና ከሚገኙ በርካታ አቅኚዎች መካከል አንዱ እኔ ነበርኩ። በመጀመሪያ ትምህርት ቤቱ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ኮሌጅ ይባል ነበር። ከጊዜ በኋላ ግን ስሙ ተቀይሮ የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ የጊልያድ ትምህርት ቤት ተባለ። ትምህርት ቤቱ 4,800 ኪሎ ሜትሮች ርቆ በኒው ዮርክ ሰሜናዊ ክፍል በኢታካ ከተማ አቅራቢያ ይገኝ ነበር።
በጥር 1943 በኦሪገን ጥቂት ቆይታ ካደረግን በኋላ አቅኚዎች የሆንን አብዛኞቻችን በግሬይሃውንድ አውቶቡስ ተሳፍረን የአሪዞናን በረሃ ለቀን ሄድን። ከበርካታ ቀናት ጉዞ በኋላ ኒው ዮርክ ደረስን፤ እዚያ ደግሞ የአሪዞና ሙቀት ተቃራኒ የክረምቱ በረዶ ጠበቀን። ትምህርት ቤቱ የካቲት 1, 1943 የተከፈተ ሲሆን የትምህርት ቤቱ ፕሬዚዳንት የነበረው ናታን ኤች ኖር አንድ መቶ ለሚሆኑት ተማሪዎች ባደረገው የምረቃ ንግግር እንዲህ ብሎ ነበር:- “የዚህ ኮሌጅ ዓላማ የተሾማችሁ አገልጋዮች እንድትሆኑ እናንተን ማስታጠቅ አይደለም። ቀድሞውኑም ቢሆን እናንተ የተሾማችሁ አገልጋዮች በመሆን ለዓመታት በትጋት ስታገለግሉ ነበር። . . . በኮሌጁ የሚሰጠው ኮርስ ዋነኛ ዓላማ በምትሄዱባቸው የአገልግሎት ክልሎች ይበልጥ ብቁ አገልጋዮች እንድትሆኑ እናንተን ማዘጋጀት ነው።”
በሰብዓዊ ትምህርት ብዙም ስላልገፋሁ መጀመሪያ አካባቢ በጊልያድ የሚሰጠው ትምህርት ከብዶኝ ነበር። ይሁን እንጂ አስተማሪዎቹ ችግሬን ተረድተውልኝ ስለነበር በትምህርቱ በጣም እየተደስትሁ መጣሁ። ከአምስት ወራት ከፍተኛ ሥልጠና በኋላ ተመረቅን። ከዚያ በኋላ ጥቂቶቻችን በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወደሚገኘው ዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ተልከን የወረዳ የበላይ ተመልካች በመሆን በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት እንድናገለግል የሚያስችለንን ተጨማሪ ሥልጠና አገኘን። መጀመሪያ የተመደብኩት በሰሜንና በደቡብ ካሮላይና ነበር።
ቀደም ባሉት በእነዚያ ጊዜያት የወረዳ የበላይ ተመልካቾች ሁልጊዜ እንደተጓዙ ነበር። አነስተኛ ከሆነ ጉባኤ ጋር ለአንድ ቀን፣ ትልቅ ጉባኤ ከሆነ ደግሞ ለሁለት ቀናት ያህል እንቆይ ነበር። በዚያን ጊዜ የነበሩት ብዙዎቹ ጉባኤዎች ትናንሽ ነበሩ። ስለዚህ ሙሉ ቀን እንዲሁም ብዙውን ጊዜ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በመጎብኘትና ጥያቄዎችን በመመለስ ካሳለፍኩ በኋላ ወደሚቀጥለው ጉባኤ ለመጓዝ በማግሥቱ ጠዋት በአሥራ አንድ ሰዓት እነሳ ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካች በመሆን ለአንድ ዓመት ያህል ካገለገልሁ በኋላ ለጥቂት ጊዜ ደግሞ በቴንሲ እና በኒው ዮርክ አቅኚ ሆኜ አገልግያለሁ።
ወደ ኩባ ከዚያም ወደ ፖርቶ ሪኮ
በግንቦት 1945 ከሌሎች ወንድሞች ጋር በመሆን ወደ መጀመሪያው የውጪ አገር ሚስዮናዊ ምድቤ ወደ ኩባ ተላክሁ! በኩባ ዋና ከተማ ሃቫና በደረስንበት በዚያው ምሽት መጽሔት በማበርከቱ ሥራ ለመካፈል ወደ መስክ ወጣን። በሳንታ ክላራ ከተማ ቤት እስክናገኝ ድረስ በሃቫና ቆየን። ምግብንና የቤት ኪራይን ጨምሮ አስፈላጊ ነገሮች ለመግዛት በየወሩ የሚሰጠን የወጪ መሸፈኛ 25 ዶላር ብቻ ነበር። አልጋችንንና ሌሎች ቁሳቁሶችን ከምናገኛቸው ዕቃዎች እንሰራ የነበረ ሲሆን የፍራፍሬ መያዣ ሣጥኖችን ደግሞ ለልብሳችንና ለተለያዩ ነገሮች ማስቀመጫ አድርገን እንጠቀምባቸው ነበር።
በቀጣዩ ዓመት የወረዳ ሥራ እንድሠራ ተመደብኩ። በዚያን ጊዜ በመላው ኩባ አንድ ወረዳ ነበር። ከእኔ በፊት የነበረው የወረዳ የበላይ ተመልካች እግሮቹ ረጃጅም ስለነበሩና የእግር ጉዞም ይወድ ስለነበር ሌሎች ወንድሞችና እህቶች ከእሱ ጋር እኩል ለመራመድ ቃል በቃል መሮጥ ነበረባቸው። እኔም ልክ እንደእርሱ የምሆን ስለመሰላቸው ልጎበኛቸው ስሄድ ሁሉን ነገር አዘጋጅተው ጠበቁኝ። ሁሉም በአንድ ቀን ወደ አገልግሎት ከመውጣት ይልቅ በቡድን በመከፋፈል ከእኔ ጋር በየተራ ሠሩ። በመጀመሪያው ቀን አንድ ቡድን ራቅ ወዳለ የአገልግሎት ክልል ወሰደኝ፤ በሚቀጥለው ቀን ሌላ ቡድን እንደዚሁ ሩቅ ወደሆነ ሌላ የአገልግሎት ክልል ይዞኝ ሄደ። እንዲህ እያለ ቀጠለ። በጉብኝቱ ማብቂያ ላይ በድካም ብዝልም ደስታ አግኝቼበታለሁ። ከዚያ ጉባኤ የማይረሱ ትዝታዎች አሉኝ።
በ1950 በኩባ ከ7,000 የሚበልጡ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የነበሩ ሲሆን ይህ ቁጥር በወቅቱ ሜክሲኮ ከነበራት የአስፋፊ ቁጥር ጋር የሚቀራረብ ነበር። በዚያው ዓመት በሐምሌ ወር በኒው ዮርክ ከተማ በያንኪ ስታዲየም ተደርጎ የነበረውን የቲኦክራሲው ጭማሪ የተባለውን ዓለም አቀፍ የአውራጃ ስብሰባ ተካፈልኩ። ከዚያ በኋላ አዲስ የሚስዮናዊ ምድብ በመቀበል ወደ ፖርቶ ሪኮ ሄድኩ። ወደ ፖርቶ ሪኮ አብረውኝ ከተጓዙት የ12ኛው ክፍል አዳዲስ ሚስዮናውያን መካከል ኤስቴልና ቴልማ ዊክሊ ይገኙበት ነበር።
ከስምንት ዓመት በኋላ እኔና ኤስቴል በቤያሞን ፖርቶ ሪኮ የወረዳ ስብሰባ ባደረግንበት ቀን በእረፍት ሰዓት፣ በመድረኩ ላይ ቀለል ያለ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በማድረግ ተጋባን። ከመጋባታችን በፊትም ሆነ በኋላ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ አገልግያለሁ። እኔና ኤስቴል ፖርቶ ሪኮ በቆየንባቸው አሥር ዓመታት 500 የነበረው የአስፋፊዎች ቁጥር ከ2,000 በላይ በመሆን ከፍተኛ ጭማሪ ሲገኝ ለመመልከት ችለናል። ብዙዎች ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ በመርዳትና በርካታ አዳዲስ ጉባኤዎች በማቋቋም የበኩላችንን አድርገናል።
በታኅሣሥ 1960 ኒው ዮርክ ከሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ሚልተን ሄንሸል ፖርቶ ሪኮን ለመጎብኘትና ከሚስዮናውያኑ ጋር ለመነጋገር መጥቶ ነበር። ሌላ አገር ተመድቦ ለማገልገል ፈቃደኛ የሚሆን ካለ የሚል ጥያቄ አቅርቦ ነበር። እኔና ኤስቴል ፈቃደኛ ከሆኑት መካከል ነበርን።
በዶሚኒካን ሪፑብሊክ የሚገኘው ቤታችን
አዲሱ ምድባችን ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ሲሆን በሰኔ 1, 1961 ወደዚያ ለመዛወር ወሰንን። በግንቦት 30 የዶሚኒካን ሪፑብሊክ አምባገነን መሪ ራፋኤል ትሩጂሎ በመገደሉ ምክንያት ወደ አገሪቱ የሚደረጉ በረራዎች በሙሉ ተሠረዙ። ይሁን እንጂ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በረራዎቹ በመቀጠላቸው በእቅዳችን መሠረት በሰኔ 1 ወደ ዶሚኒካን ሪፑብሊክ ለመብረር ቻልን።
እዚያ በምንደርስበት ጊዜ አገሩ በረብሻ ላይ የነበረ ሲሆን መጠነኛ የሆነ ወታደራዊ እንቅስቃሴም ነበር። ዓመፅ እንዳይነሳ ፍርሃት ስለነበረ ወታደሮች ማንንም ሰው በመንገድ ላይ አስቁመው ይፈትሹ ነበር። በርካታ የፍተሻ ጣቢያዎች ላይ እየቆምን ሻንጣችን አንድ በአንድ ተፈትሿል። ጥቃቅን የሆኑ ነገሮች እንኳ ሳይቀሩ ሁሉንም ነገር ከሻንጣችን ውስጥ ያወጡ ነበር። ዶሚኒካን ሪፑብሊክን የተዋወቅነው በዚህ ሁኔታ ነበር።
የመጀመሪያው ምድባችን ወደሆነው ወደ ላ ሮማና ከተማ ከመሄዳችን በፊት በዋና ከተማው በሳንቶ ዶሚንጎ በርከት ላሉ ሳምንታት ተቀመጥን። በአምባገነኑ የትሩጂሎ አገዛዝ ዘመን የይሖዋ ምሥክሮች ኮሙኒስቶችና የመጨረሻ መጥፎ ሰዎች እንደሆኑ ለሕዝቡ ተነግሯቸው ነበር። በዚህ ምክንያት ምሥክሮቹ በከፍተኛ ሁኔታ ስደት ደርሶባቸዋል። ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ ይህን መሠረተ ቢስ ጥላቻ ለማስቀረት ችለናል።
በላ ሮማና ከተማ ለጥቂት ጊዜ ከሰራን በኋላ የወረዳ የበላይ ተመልካች በመሆን እንደገና ማገልገል ጀመርን። ከዚያም በ1964 በሳንቲያጎ ከተማ ሚስዮናውያን ሆነን እንድናገለግል ተመደብን። በቀጣዩ ዓመት በዶሚኒካን ሪፑብሊክ ሌላ አብዮት በመፈንዳቱ አገሪቱ እንደገና በብጥብጥ ታመሰች። በግጭቱ ወቅት በፖለቲካ ቀስቃሽነቱ ወደሚታወቀው መንደር ወደ ሳን ፍራንሲስኮ ደ ማኮሪስ ተዛወርን። ዳሩ ግን ያለ ምንም መሰናክል ሰበክን። የፖለቲካ አለመረጋጋት ቢኖርም እንኳ አንድ አዲስ ጉባኤ ለማቋቋም ችለናል። ሳንቲያጎ በሚገኘው በአሁኑ መኖሪያችን እንደገና ከመመደባችን በፊት በተከታዮቹ ዓመታት ምድባችን በየጊዜው ሲለዋወጥ ቆይቷል።
በዚህ በዶሚኒካን ሪፑብሊክ በሚካሄደው ሥራ የይሖዋን በረከት በእርግጥ ልንመለከት ችለናል። በ1961 እዚያ ስንደርስ 600 የሚሆኑ ምሥክሮችና 20 ጉባኤዎች ይገኙ ነበር። አሁን ከ300 በሚበልጡ ጉባኤዎች ውስጥ የሚገኙ 20,000 የሚሆኑ አስፋፊዎች ስለ አምላክ መንግሥት ምሥራች በመስበክ ላይ ናቸው። በ1997 የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ 81,277 ተሰብሳቢዎች መገኘታቸው ወደፊት ከፍተኛ ጭማሪ ሊኖር እንደሚችል ማረጋገጫ ይሰጣል። ይህ የአስፋፊዎቹን ቁጥር በሦስት ተኩል የሚያጥፍ ነው!
አሁን ብርቱ የሆነ ሕዝብ
የዚህ ዓለም መልክ በየጊዜው መለዋወጡን ቢቀጥልም የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰብኩት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ምንጊዜም አንድ ዓይነት ነው። (1 ቆሮንቶስ 7:31) ይሖዋ አሁንም አምላክ ነው፣ ክርስቶስ አሁንም ንጉሥ ነው፣ መንግሥቱ ደግሞ ከምንጊዜውም ይልቅ ዛሬ ብቸኛው የዓለም ተስፋ መሆኑ ግልጽ ነው።
ከ60 ዓመት በፊት በኦሪገን ግዛት በሴለም ከተማ ያንን ስብሰባ ከተካፈልኩ ወዲህ በይሖዋ ሕዝቦች ውስጥ አስደናቂ የሆኑ ለውጦች ተደርገዋል። ዛሬ ታላቁ ሕዝብ ወይም እጅግ ብዙ ሰዎች ከአምስት ሚልዮን በላይ በመሆናቸው ታላቅ ሆነዋል። አስቀድሞ ይሖዋ ስለ ሕዝቡ “ታናሹ ለሺህ የሁሉም ታናሹ ለብርቱ ሕዝብ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር በዘመኑ ይህን አፋጥነዋለሁ” በማለት የተናገረው ተፈጽሟል።—ኢሳይያስ 60:22
ከ60 ዓመታት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት በኋላ በሚስዮናዊ አገልግሎት በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ለመቀጠል በመቻሌ በጣም ደስተኛ ነኝ። በዚያ ሥራ ተካፋይ በመሆን ‘የሁሉም ታናሹ ብርቱ ሕዝብ’ ሲሆን ለመመልከት መቻል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!
[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከባለቤቴ ጋር በዶሚኒካን ሪፑብሊክ