ሄኔሲፎሩ ደፋር አጽናኝ
“ከእነርሱ ጋር እንደ ታሰረ ሆናችሁ እስሮችን አስቡ፣ የተጨነቁትንም ራሳችሁ ደግሞ በሥጋ እንዳለ ሆናችሁ አስቡ።” (ዕብራውያን 13:3) ሐዋርያው ጳውሎስ በ61 እዘአ ገደማ ይህን ሲጽፍ ከአንድ ጊዜ በላይ ታስሮ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ሰማዕት ሆኖ ከመሞቱ በፊት እንደገና የሚታሰርበት ጊዜ ቀርቦ ነበር። (ሥራ 16:23, 24፤ 22:24፤ 23:35፤ 24:27፤ 2 ቆሮንቶስ 6:5፤ 2 ጢሞቴዎስ 2:9፤ ፊልሞና 1) ጉባኤዎች እምነታቸው እየተፈተነ ያሉትን መሰል አማኞች መርዳታቸው በዚያን ጊዜም ቢሆን እንደዛሬው አጣዳፊ ጉዳይ ነበር።
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረ ሄኔሲፎሩ የሚባል አንድ ደቀ መዝሙር ለዚህ አስፈላጊ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ነበር። ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ በሮም በታሰረበት ወቅት ሄኔሲፎሩ ሄዶ ጠይቆት ነበር። ሐዋርያው እሱን አስመልክቶ ሲጽፍ እንዲህ ብሏል:- “ጌታ ለሄኔሲፎሩ ቤተ ሰዎች ምሕረትን ይስጥ፣ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛልና፤ በሰንሰለቴም አላፈረበትም፣ ነገር ግን በሮሜ ባደረ ጊዜ ፈልጎ ፈልጎ አገኘኝ።” (2 ጢሞቴዎስ 1:16, 17) እነዚህ ጥቂት ቃላት የያዙትን ትርጉም ለመረዳት ጊዜ ወስደህ አሰላስለህባቸው ታውቃለህን? እንዲህ ማድረግህ ለሄኔሲፎሩ ያለህን አድናቆት ከፍ ያደርግልሃል። ሄኔሲፎሩ ደፋር አጽናኝ እንደነበረ ለመመልከት ትችላለህ።
ጳውሎስ ለሁለተኛ ጊዜ በታሰረበት ወቅት
ጳውሎስ ለመጀመሪያ ጊዜ ታስሮ ከተፈታ በኋላ እንደገና በሮም በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ ሲታሰር፣ የነበረበት ሁኔታ ከቀድሞው የተለየ ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ታስሮ በነበረበት ወቅት ጓደኞቹ በተከራየው ቤት ውስጥ አግኝተው ሊያነጋግሩት ይችሉ ነበር። እንዲሁም ጳውሎስ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊፈታ እንደሚችል ትምክህት የነበረው ይመስላል። አሁን ግን ብዙዎቹ ስለተዉት የሰማዕትነት ሞት ጥላ አጥልቶበታል።—ሥራ 28:30፤ 2 ጢሞቴዎስ 4:6-8, 16፤ ፊልሞና 22
ጳውሎስ በዚህ ሁኔታ በእስር ላይ ይገኝ የነበረው በ65 እዘአ ገደማ ነበር። ከአንድ ዓመት ገደማ በፊት በሐምሌ 64 እዘአ በሮም ከተማ ይገኙ ከነበሩት 14 ቀበሌዎች ውስጥ በአሥሩ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ የእሳት ቃጠሎ ተነስቶ ነበር። ሮማዊው ታሪክ ጸሐፊ ታሲተስ እንደገለጸው ንጉሠ ነገሥት ኔሮ “ለእሳት ቃጠሎው ምክንያት የሆነው አገዛዙ ነው የሚለውን፣ አደገኛ ሁኔታ ሊያስከትል የሚችል እምነት ለማስቀረት አልቻለም ነበር። ኔሮ ይህን አመለካከት ለማስወገድ ሲል ጥፋቱን ሕዝቡ ክርስቲያኖች ብሎ በሚጠራቸው ላይ በማላከክ አስከፊ የሆነ ተግባር በፈጸመ ወገን ላይ የሚወሰድ ጭካኔ የተሞላበት የቅጣት እርምጃ እንዲፈጸምባቸው አድርጓል። . . . የውርደት ሞት እንዲሞቱ ተደርጓል። በአውሬዎች ቆዳ ተሸፍነው በውሻዎች ተቦጫጭቀው እንዲሞቱ ወይም በመስቀል ላይ እንዲሰቀሉ፣ ወይም ደግሞ ሲመሽ ብርሃን ሰጪ ሆነው እንዲያገለግሉ እሳት ውስጥ ተወርውረው ይቃጠሉ ነበር።”
ጳውሎስ እንደገና ወደ እስር ቤት የገባው ይህንና ይህን የመሳሰሉ ሁኔታዎች በነበሩበት ጊዜ ነበር። ጓደኛው የነበረው ሄኔሲፎሩ ሊጠይቀው በሄደ ጊዜ በጣም መደሰቱ ምንም አያስደንቅም! ይሁን እንጂ እስቲ ይህን ሁኔታ በሄኔሲፎሩ ቦታ ሆነን እንመልከተው።
እስረኛውን ጳውሎስ መጠየቅ
የሄኔሲፎሩ ቤተሰብ ይኖር የነበረው በኤፌሶን ሳይሆን አይቀርም። (2 ጢሞቴዎስ 1:18፤ 4:19) ሄኔሲፎሩ ወደ ግዛቱ ዋና ከተማ የመጣው ለራሱ ጉዳይ ይሁን ወይም ጳውሎስን ለመጠየቅ በግልጽ የሰፈረ ነገር የለም። ያም ሆነ ይህ ሐዋርያው ‘ሄኔሲፎሩ ወደ ሮሜ መጥቶ ሳለ ብዙ ጊዜ አሳርፎኛል’ በማለት ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 1:16, 17) ይህ ምን ዓይነት እረፍት ነው? ምንም እንኳ የሄኔሲፎሩ እርዳታ ቁሳዊ ነገሮችን ሊጨምር ቢችልም የእሱ በዚያ መገኘት ለጳውሎስ የሚያጠነክርና የሚያበረታታ ማነቃቂያ እንደሚሆንለት የተረጋገጠ ነው። እንዲያውም አንዳንድ ትርጉሞች “ብዙ ጊዜ መንፈሴን አነቃቅቶታል” ወይም “ብዙ ጊዜ አጽናንቶኛል” ይላሉ።
በዚያን ወቅት በሮም የሚገኝን አንድን ክርስቲያን እስረኛ ለመጠየቅ የሚፈልግ ሰው ብዙ ችግሮችን መጋፈጥ ነበረበት። በሮም የሚገኙ ክርስቲያኖች ጳውሎስ በመጀመሪያ ታስሮ የነበረበትን ቦታ ያውቁ የነበረ ቢሆንም በዚህኛው ጊዜ ግን የት እንዳለ አላወቁም ነበር። እንደ ሮም ባለ ትልቅ ከተማ ውስጥ በተለያዩ ጥፋቶች ከታሰሩ በርካታ እስረኞች መካከል አንድን የት እንዳለ የማይታወቅ እስረኛ ፈልጎ ማግኘት ቀላል አልነበረም። በመሆኑም ትጋት የተሞላበት ፍለጋ ማካሄድ አስፈላጊ ነበር። ጆቫኒ ሮስታኒዮ የተባሉት ምሁር ጉዳዩን እንደሚከተለው በማለት ይገልጹታል:- “ችግሮቹ የተለያየ መልክ ሳይኖራቸው አይቀርም። ከሁሉም በላይ ደግሞ ፍለጋውን ለማካሄድ ከወትሮው ለየት ያለ ጥንቃቄ ማድረግ አስፈላጊ ነበር። መረጃዎችን ከዚህም ከዚያም ማሰባሰብና በበርካታ ወንጀሎች የተከሰሰና አክራሪ የሆነን አንድ አረጋዊ እስረኛ ያለበትን እስር ቤት ለማግኘት አጥብቆ መፈለግ የማያስፈልግ ጥርጣሬ ሊቀሰቅስ ይችል ነበር።”
ደራሲው ፒ ኤን ሃሪሰን ይህንኑ ሁኔታ ጉልህ በሆነ መንገድ ሲገልጹት እንዲህ ብለዋል:- “በብዙ መንገደኞች መካከል በዓላማ የሚጓዝ አንድ ሰው ብቅ ሲል እናያለን። ከኤጅያን የባህር ዳርቻ የመጣው ይህ እንግዳ ሰው የሚያደርገው ነገር ሊያስከትልበት የሚችለውን አደገኛ ሁኔታ ቢረዳም ፍለጋውን በመቀጠል በአንድ በማይታወቅ እስር ቤት ውስጥ አንድ የሚያውቀው ሰው ድምፅ እስኪቀበለውና ጳውሎስን ከአንድ ሮማዊ ወታደር ጋር በሰንሰለት ታስሮ እስኪያገኘው ድረስ በማያውቃቸው መንገዶች ላይ ሲንከራተት፣ በርካታ በሮችን ሲያንኳኳና ያገኘውን እያንዳንዱን ፍንጭ ሲከታተል በጉጉት እንመለከተዋለን።” ይህ እስር ቤት እንደሌሎቹ የሮም እስር ቤቶች ከሆነ ቀዝቃዛ፣ ጨለማና ሁሉም ዓይነት መከራና ስቃይ የሞላበት አሰቃቂ ቦታ ይሆናል።
አንድ ሰው ጳውሎስን ከመሰለ እስረኛ ጋር ጓደኝነት እንዳለው ከታወቀ በጣም አደገኛ ነበር። ጳውሎስን አዘውትሮ መጠየቅ ደግሞ የበለጠ አደገኛ ነበር። አንድ ሰው ክርስቲያን መሆኑን በግልጽ ማሳወቁ እንዲያዝና ተሠቃይቶ እንዲሞት ሊያደርገው ስለሚችል በራስ ላይ አደጋ መጋበዝ ነበር። ይሁን እንጂ ሄኔሲፎሩ ጳውሎስን አልፎ አልፎ በመጠየቅ ብቻ አልረካም። ጳውሎስን “ብዙ ጊዜ” መጠየቅ አላሳፈረውም ወይም አላስፈራውም። ሄኔሲፎሩ የሚለው ስም ትርጉም “እርዳታ የሚያበረክት” ማለት ሲሆን በአደገኛ ሁኔታዎች ሥር ድፍረት የሞላበት ፍቅራዊ እርዳታ በማበርከት ከስሙ ትርጉም ጋር የሚስማማ ሥራ ፈጽሟል።
ሄኔሲፎሩ ይህን ሁሉ ያደረገው ለምንድን ነው? ብራያን ራፕስኪ እንዲህ ብለዋል:- “እስር ቤት በእስረኛው ላይ አካላዊ ሥቃይ የሚያደርስ ቦታ ብቻ ሳይሆን ጭንቀት በመፍጠር ሥር የሰደደ ስጋት የሚያስከትል ቦታ ነው። እንዲህ ባለ ሁኔታ እርዳታ የሚያበረክቱ ሰዎች በአካል መገኘታቸውና የሚያበረታቱ ቃላት መናገራቸው የእስረኛውን ስሜት በከፍተኛ ሁኔታ ሊያነቃቃው ይችላል።” ሄኔሲፎሩ ይህን በሚገባ ተረድቶ ስለነበር ከጓደኛው ጋር በድፍረት ተጣብቋል። ጳውሎስ ይህን የመሰለውን እርዳታ በከፍተኛ አድናቆት ተመልክቶት መሆን አለበት!
ሄኔሲፎሩ ምን አጋጥሞት ይሆን?
ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ በላከው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ ለሄኔሲፎሩ ቤተሰቦች ሰላምታ የላከ ሲሆን ሄኔሲፎሩን በተመለከተም እንዲህ ብሎ ነበር:- “በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው።” (2 ጢሞቴዎስ 1:18፤ 4:19) ብዙ ሰዎች “በዚያን ቀን” የሚሉት ቃላት የአምላክን የፍርድ ቀን ስለሚያመለክቱ ሄኔሲፎሩ ሞቷል ወደሚለው መደምደሚያ ደርሰዋል። ጉዳዩ እንዲህ ከሆነ ፒ ኤን ሃሪሰን እንደተናገሩት “ሄኔሲፎሩ ወደዚህ አደገኛ አካባቢ ደጋግሞ መመላለሱ . . . ሕይወቱን አሳጥቶት” ሊሆን ይችላል። እርግጥ ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት ሄኔሲፎሩ ከቤት ርቆ ሄዶ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ ጳውሎስ ለቤተሰቦቹ በላከው ሰላምታ ውስጥ እሱንም ጨምሮት ሊሆን ይችላል።
አንዳንዶች “በዚያን ቀን ከጌታ ምሕረትን እንዲያገኝ ጌታ ይስጠው” የሚሉት ቃላት ልዩ ትርጉም እንዳላቸው ያምናሉ። እነዚህ ሰዎች በመንፈሳዊው ዓለም ውስጥ ለሚኖሩና ምናልባትም በመሰቃየት ላይ ለሚገኙ የሞቱ ሰዎች ነፍሳት የሚቀርብ የምልጃ ጸሎት መሆኑን ቃላቶቹ ያረጋግጣሉ በማለት ይናገራሉ። ይሁን እንጂ ይህ ሐሳብ ሙታን አንዳች ነገር አያውቁም ከሚለው ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት ጋር ይጋጫል። (መክብብ 9:5, 10) ሄኔሲፎሩ በወቅቱ ሞቶ የነበረ ቢሆን እንኳ ጳውሎስ ጓደኛው ከአምላክ ምሕረት እንዲያገኝ የነበረውን ምኞት መግለጹ ብቻ ነበር። አር ኤፍ ሃርተን “ይህ ለሰዎች ሁሉ የምንመኘው ዓይነት ምኞት ነው። ይሁን እንጂ ስለ ሙታን መጸለይና የቅዳሴ ሥርዓት ማካሄድ [በሐዋርያው] አእምሮ ውስጥ ፍጹም የሌሉ ነገሮች ናቸው” ብለዋል።
ታማኝ አጽናኞች እንሁን
ሄኔሲፎሩ ሕይወቱን ያጣው ጳውሎስን በመርዳት ላይ እያለም ይሁን አይሁን ሐዋርያው የታሰረበትን እስር ቤት ለመፈለግና እሱንም ለመጠየቅ ሲል ሕይወቱን አደጋ ላይ መጣሉ የተረጋገጠ ነው። ጳውሎስ ከሄኔሲፎሩ ያገኘውን እጅግ አስፈላጊ የሆነ ድጋፍና ማበረታቻ በአድናቆት ተመልክቶት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም።
መሰል ክርስቲያኖች ፈተናና ስደት ሲደርስባቸው ወይም ሲታሰሩ እነሱን ለማጽናናትና ለማበረታታት በምንችልበት ሁኔታ ላይ እንገኝ ይሆናል። እንግዲያው ስለ እነሱ እንጸልይ፤ እንዲሁም በፍቅር ተነሳስተን እነሱን ለመርዳት የምንችለውን ሁሉ እናድርግ። (ዮሐንስ 13:35፤ 1 ተሰሎንቄ 5:25) እኛም እንደ ሄኔሲፎሩ ደፋር አጽናኞች እንሁን።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሐዋርያው ጳውሎስ በእስር ላይ በነበረበት ጊዜ ሄኔሲፎሩ በድፍረት አጽናንቶታል