ማማረር ፈጽሞ ስህተት ነውን?
የሚደርስብንን በደል አፍኖ ከመያዝ የከፋ ስሜትን የሚያቆስል ምን ነገር ይኖራል?—ማርኪ ደ ኩስቲን፣ 1790-1857
አብሯት የሚሠራ አንድ ሰው በጾታ ስሜት እየተዳፈራት ለሁለት ዓመታት ችላ ኖራለች። ድርጊቱን መቃወሟ ያተረፈላት ነገር ቢኖር ስድብና ኩርፊያ ነበር። አምቃ የያዘችው ጭንቀት ጤንነቷን እየጎዳው ሄደ። ነገር ግን ምን ማድረግ ትችላለች? ከክፍሉ አንደኛ የወጣ አንድ ተማሪ ደግሞ ትምህርት ቤቱ የሚፈልግበትን ራስን የመከላከያ ዘዴዎችን ለመለማመድ ሕሊናው እንደማይፈቅድለት በመናገሩ ከትምህርት ቤቱ ተባሯል። ሁለቱም እንደተበደሉ ተሰምቷቸዋል። ይሁን እንጂ ቅሬታቸውን መግለጽ ይኖርባቸው ይሆን? ቅሬታቸውን ቢገልጹ መፍትሔ ያገኙ ይሆን ወይስ ነገሩን ይበልጥ ያባብሰዋል?
በዚህ ፍጽምና በሌለውና አስቸጋሪ በሆነ ዓለም ውስጥ እንደነዚህ የመሳሰሉም ሆኑ ሌሎች የሚያማርሩ ነገሮች የተለመዱ ናቸው። ማማረር ሲባል ሐዘንን፣ ሥቃይን ወይም ተቃውሞን በሰላማዊ መንገድ መግለጽ ብቻ ሳይሆን በደል ፈጽሞብኛል በማለት በአንድ ግለሰብ ላይ ክስ መመሥረትንም ይጨምራል። ብዙ ሰዎች ከማማረርና ግጭት ከመፍጠር መሸሽ ይፈልጋሉ። ይሁንና አንድ ሰው ሁልጊዜ ዝም ማለት አለበትን? የመጽሐፍ ቅዱስ አመለካከት ምንድን ነው?
በራስና በሌሎች ላይ የሚያስከትለው ጉዳት
ሥር የሰደደ የማማረር መንፈስ ጎጂ መሆኑ የተረጋገጠ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስም የተወገዘ ነው። የሚያማርር ሰው በራሱ ላይ አካላዊና መንፈሳዊ ጉዳትን ከማምጣቱም በላይ የሚያማርርባቸውንም ሰዎች ለብስጭት ይዳርጋል። በትንሽ በትልቁ ማማረር የሚቀናትን ሚስት አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ “በዝናብ ቀን የሚያንጠባጥብ ቤትና ጠበኛ [“ነዝናዛ፣” NW] ሴት አንድ ናቸው” ይላል። (ምሳሌ 27:15) በተለይ ደግሞ በይሖዋ ወይም በዝግጅቶቹ ላይ ማማረር ስህተት ነው። የእስራኤል ብሔር በ40 ዓመት የምድረ በዳ ጉዞ ወቅት በተዓምራዊ መንገድ የቀረበለትን መና “ቀላል እንጀራ” በማለት ባማረረ ጊዜ ይሖዋ መርዛማ እባቦችን በመላክ እነዚያን አክብሮት የጎደላቸው አጉረምራሚ ሰዎች እንዲነደፉ አድርጓል፤ ብዙዎችም ሞተዋል።—ዘኁልቁ 21:5, 6
በተጨማሪም ኢየሱስ ተከታዮቹ ሌሎች ሰዎች በሚፈጽሟቸው እንደ “ጉድፍ” በሚቆጠሩ ስህተቶች ከማማረር ይልቅ እንደ “ምሰሶ” ሊቆጠሩ የሚችሉትን የራሳችንን ጉድለቶች በሚገባ ማስተዋል እንደሚኖርብን መክሯል። (ማቴዎስ 7:1-5) በተመሳሳይ ሁኔታ ጳውሎስ “የምታመካኘው የለህም፤ . . . አንተው ፈራጁ እነዚያን ታደርጋለህና” በማለት መፍረድን (የማማረርን አንዱ ገጽታ) አውግዟል። ማማረርን አስመልክቶ የተሰጡት እነዚህ ማሳሰቢያዎች አላስፈላጊ ትችት ከማቅረብና የማማረር መንፈስ ከማዳበር እንድንቆጠብ ሊገፋፉን ይገባል።—ሮሜ 2:1
ማማረር ጨርሶ የተወገዘ ነገር ነውን?
ታዲያ በምንም ነገር ይሁን ማማረር ጨርሶ የተወገዘ ነገር እንደሆነ አድርገን መደምደም ይኖርብናልን? እንዲህ ብለን ልንደመድም አይገባንም። በምንኖርበት በዚህ ጎደሎ ዓለም ውስጥ መታረም የሚያስፈልጋቸው በርካታ የግፍ ሥራዎች መኖራቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ይገልጻል። ኢየሱስ በተናገረው አንድ ምሳሌ ላይ ‘ሁልጊዜ እየመጣች እንዳታውከው’ ሲል በደል ለደረሰባት አንዲት መበለት ሳይፈልግ ስለፈረደላት አንድ ዓመፀኛ ዳኛ ይናገራል። (ሉቃስ 18:1-8) እኛም በአንዳንድ ሁኔታዎች ስህተት የሆኑ ነገሮች እስኪታረሙ ድረስ ቅሬታችንን በማሰማት መቀጠል ይኖርብን ይሆናል።
ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት እንድትመጣ እንድንጸልይ በማበረታታት በጊዜያችን የሚገኘው ዓለም ጉድለቶች ያሉት መሆኑን እንድንገነዘብና መፍትሔ እንዲያመጣልን ወደ አምላክ ‘እንድንጮኽ’ አላሳሰበንምን? (ማቴዎስ 6:10) በጥንቶቹ ሰዶምና ጎሞራ ስለሚፈጸመው ክፋት ይሰማ የነበረው “ጩኸት” ወደ ጆሮው በደረሰ ጊዜ ይሖዋ “እንደ ጩኸትዋ አድርገው እንደ ሆነ ወርጄ አያለሁ” በማለት መፍትሔ ለማምጣት ማሰቡን በመግለጽ መልእክተኞቹን ልኳል። (ዘፍጥረት 18:20, 21) ይሖዋ ወደ እሱ በምሬት ለጮኹት ሰዎች እፎይታ ሲል ሁለቱን ከተማዎች በሥነ ምግባር ብልሹ ከነበሩት ነዋሪዎቻቸው ጋር በማጥፋት ሁኔታውን ወዲያውኑ አስተካክሏል።
የክርስቲያን ጉባኤ
ማማረር በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ በሚገኙ ወንድሞች ዘንድ ከዚህ የተለየ ሊሆን ይገባዋልን? ክርስቲያኖች ፍጽምና የሌላቸው ወንዶችና ሴቶች ቢሆኑም አምላክን በሰላምና በአንድነት ለማገልገል ከልባቸው ይጥራሉ። ይሁንና በተወሰነ ደረጃ ወደ ማማረር የሚያደርሱና መፍትሔ የሚሹ ነገሮች በመካከላቸው ሊነሱ ይችላሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ከጰንጠቆስጤ በዓል ጥቂት ጊዜ በኋላ በመንፈስ በተቀቡት ወንድሞች ጉባኤ ውስጥ አንድ ሁኔታ ተከስቶ ነበር። ወደ ክርስትና የተለወጡ በርካታ አዳዲስ ሰዎች ተጨማሪ መመሪያና ማበረታቻ ለማግኘት በኢየሩሳሌም ቆይታ አድርገው ነበር። የሚቀርብላቸውን ምግብ ተከፋፍለው ይመገቡ ነበር። ይሁን እንጂ “ከግሪክ አገር መጥተው የነበሩት አይሁድ በይሁዳ ኖረው በነበሩት አይሁድ አንጐራጐሩባቸው፣ በየቀኑ በተሠራው አገልግሎት መበለቶቻቸውን ችላ ይሉባቸው ነበርና።” ሐዋርያት እነዚህን ሰዎች ችግር ፈጣሪዎች ብለው ከማውገዝ ይልቅ ሁኔታውን ለማስተካከል እርምጃ ወስደዋል። አዎን፣ በአክብሮትና በትክክለኛ መንፈስ የሚቀርቡ ምክንያታዊ የሆኑ ቅሬታዎች ጉባኤውን በበላይነት በሚቆጣጠሩ ወንድሞች አማካኝነት ተገቢውን ምላሽ ያገኛሉ።—ሥራ 6:1-6፤ 1 ጴጥሮስ 5:3
ለተገቢው ባለ ሥልጣን
ከላይ በተጠቀሰው ምሳሌ መሠረት ቅሬታ ሊገለጽ የሚገባው በትክክለኛ መንፈስና ለተገቢው ባለሥልጣን መሆኑን አስተዋላችሁን? ለምሳሌ ያህል ለአንድ ፖሊስ ስለተጣለብን ከፍተኛ ቀረጥ መናገር ወይም ለአንድ ዳኛ ስለሚሰማን አካላዊ ሕመም መግለጽ ትርጉም የሌለው ነገር ነው። በተመሳሳይም በጉባኤ ውስጥም ሆነ ከጉባኤ ውጪ ስለ አንዳንድ ሁኔታዎች እርዳታ ለመስጠት ሥልጣኑም ሆነ ችሎታው ለሌለው ሰው ቅሬታችንን ማሰማት ትክክል አይሆንም።
ዛሬ በብዙ አገሮች የተወሰነ እፎይታ ለማግኘት ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች አቤቱታዎቻቸውን የሚያቀርቡባቸው ፍርድ ቤቶችና ተገቢ ባለ ሥልጣናት አሉ። በመግቢያችን ላይ የተጠቀሰው ተማሪ አቤቱታውን ለፍርድ ቤት አቀረበ። ዳኞቹ ለእሱ የፈረዱለት ሲሆን ትምህርት ቤቱም ተማሪውን ከይቅርታ ጋር ወደ ትምህርት ገበታው መልሶታል። የሥራ ባልደረባዋ በጾታ ስሜት ይዳፈራት የነበረችው ሴትም በሠራተኛ ሴቶች አንድነት ማኅበር አማካኝነት እፎይታ ልታገኝ ችላለች። የትምህርት ቤቶች ቦርድም ይቅርታ ጠይቋታል። አሠሪዎቿ የጾታ ጥቃትን ለማስቆም እርምጃ ወስደዋል።
ይሁን እንጂ ስለሚደርስብን በደል የምናሰማው አቤቱታ ሁሉ ተመሳሳይ የሆነ መልካም ውጤት ይኖረዋል ብሎ መጠበቅ አይቻልም። ጠቢቡ ንጉሥ ሰሎሞን “ጠማማ ይቀና ዘንድ አይችልም” በማለት እውነታውን ገልጿል። (መክብብ 1:15) አንዳንድ ጉዳዮችን አምላክ ራሱ በወሰነው ጊዜ እስኪያስተካክላቸው ድረስ ዝም ብለን መጠበቅ እንደሚያስፈልገን መገንዘብ ይኖርብናል።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ሽማግሌዎች ትክክለኛ ቅሬታዎችን ይሰማሉ እንዲሁም ተገቢውን እርምጃ ይወስዳሉ