ገና ዓለማዊ በዓል ወይስ ሃይማኖታዊ በዓል?
በቻይና የገና ሽማግሌ ተብሎ ይጠራል። በዩናይትድ ኪንግደም የገና አባት ተብሎ ይታወቃል። በሩሲያ የሚኖሩ ሰዎች በረዶው አያታችን ሲሉት በዩናይትድ ስቴትስ ደግሞ ሳንታ ክሎዝ ብለው ሰይመውታል።
በርካታ ሰዎች ይህን ቦርጫም የሚያስመስል ነገር ያደረገና እንደ በረዶ የነጣ ጢም ያንዠረገገ ፍልቅልቅ ሽማግሌ የገና ምልክት አድርገው ይወስዱታል። ይሁን እንጂ ሳንታ ክሎዝ በአራተኛው መቶ ዘመን ይኖር ከነበረ የሙራ (የዘመናዊቷ ቱርክ ከተማ) ጳጳስ ጋር ግንኙነት ባለው ወግና ልማድ ላይ የተመሠረተ አፈ ታሪክ መሆኑም በሰፊው ይታወቃል።
ወግና ባህል ከፍተኛ ተጽዕኖ ካሳደሩባቸው በርካታ በዓላት መካከል አንዱ ገና ነው። የሳንታ አፈ ታሪክ ብዙዎች ከሚያከብሩት አንድ በዓል ጋር ከተያያዙት ጥንታዊ ተረቶች መካከል በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው። አንዳንድ ሰዎች የገና በዓል ልማዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው በሚገኙ ክንውኖች ላይ የተመሠረቱ ናቸው ቢሉም እውነታው እንደሚያሳየው ግን አብዛኞቹ ወጎች አረማዊ ሥረ መሠረት ያላቸው ናቸው።
ለዚህ ተጨማሪ ማስረጃ የሚሆነን የገና ዛፍ ነው። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔድያ ብሪታኒካ እንዲህ ብሏል:- “አረማውያን በሆኑ አውሮፓውያን ዘንድ የተለመደ የነበረው የዛፍ አምልኮ ወደ ክርስትና ከተለወጡም በኋላ እንዳለ ቀጥሏል፤ በመሆኑም ስካንዲኔቪያውያን በአዲስ ዓመት ላይ ዲያብሎስን ለማራቅ ቤታቸውንና መጋዘናቸውን ከዓመት ዓመት ቅጠላቸው በማይረግፍ ዛፎች የሚያሸበርቁ ሲሆን በገና በዓል ወቅት ወፎች የሚያርፉበት ዛፍ ያቆማሉ።”
ሆሊ በተባለው ዛፍ ወይም ከዓመት ዓመት ቅጠላቸው በማይረግፍ ሌሎች ዛፎች የአበባ ጉንጉን መሥራት ሌላው ተወዳጅ የገና በዓል ልማድ ነው። ይህም ራሱ ከአረማዊ አምልኮ ጋር በጥብቅ የተሳሰረ ነው። የጥንቶቹ ሮማውያን የእርሻ አምላክ ለሆነው ለሳተርን በክረምት ወራት አጋማሽ ላይ በሚያከብሩት ሳተርናሊያ በተባለው የሰባት ቀን በዓል ቤተ መቅደሶቻቸውን ሆሊ በተባለው ዛፍ ቅርንጫፎች ያስጌጡ ነበር። ይህ አረማዊ በዓል በተለይ ገደብ በሌለው ፈንጠዝያና ርኩሰት የታወቀ ነበር።
በገና ጊዜ ሚስልቶ (ሥዕሉ ላይ የሚታየው) በተባለው ተቀጥላ ተክል ቀንበጥ ሥር መሳሳምን አንዳንዶች የፍቅር መግለጫ አድርገው ይወስዱት ይሆናል፤ ነገር ግን ታሪካዊ አመጣጡ ወደ መካከለኛው ዘመን መልሶ ይወስደናል። በጥንቷ ብሪታንያ ይኖሩ የነበሩ ድሩድስ የሚባሉ ቀሳውስት ሚስልቶ አስማታዊ ኃይል አለው ብለው ያምኑ ስለነበር ከአጋንንት፣ ከድግምትና ከሌሎች ክፉ ነገሮች መከላከያ አድርገው ይጠቀሙበት ነበር። ከጊዜ በኋላ ደግሞ በሚስልቶ ሥር ሆኖ መሳሳም ለጋብቻ ያበቃል የሚል አጉል እምነት ብቅ አለ። ይህ ልማድ በገና ጊዜ በአንዳንድ ሰዎች ዘንድ አሁንም ድረስ ይሠራበታል።
እነዚህ ነገሮች የአረማዊ ትምህርቶች ተጽዕኖ ካደረገባቸው ወይም በቀጥታ ከእነሱ ከመነጩት የዘመናዊው የገና በዓል ልማዶች ጥቂቶቹ ናቸው። ይሁንና ይህ ሁሉ እንዴት እንዲህ ሊሆን ቻለ ብለህ ትገረም ይሆናል። የክርስቶስን ልደት ለማሰብ የሚከበር በዓል ክርስቲያናዊ ባልሆኑ ልማዶች እንዲህ ሊጠላለፍ የቻለው እንዴት ነው? ከሁሉ በላይ ደግሞ አምላክ ጉዳዩን እንዴት ይመለከተዋል?
[ምንጭ]
ገጽ 3:- ሳንታ ክሎዝ:- Thomas Nast/Dover Publications, Inc., 1978; በገጽ 3 ላይ የሚገኘው ሚስልቶና በገጽ 4 ላይ ያለው ሥዕል:- Discovering Christmas Customs and Folklore by Margaret Baker, published by Shire Publications, 1994