ተሰውሮ የነበረው ውድ ሀብት ይፋ ሆነ
የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ
በ1993 አንድ ተመራማሪ በሴንት ፒተርስበርግ በሚገኘው የሩሲያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ መልካቸው የወየበ፣ ኦርቶዶክስ ሪቪው የተባለው መጽሔት የቆዩ ቅጂዎች ተከምረው አገኙ። ከ1860 እስከ 1867 ድረስ የታተሙት እነዚሁ መጽሔቶች በገጾቻቸው ላይ ከአንድ መቶ ዓመት ለሚበልጥ ጊዜ ከሩሲያ ሕዝብ ተሠውሮ የኖረ ውድ ሀብት ይዘው ተገኝተዋል። ይህ ውድ ሃብት በሩሲያ ቋንቋ የተዘጋጀ መላው የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም “የብሉይ ኪዳን” የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ነው!
የቅዱሳን ጽሑፎቹ ተርጓሚዎች አቡኑ ማካሪዮስ በመባል የሚታወቀው ሚኬል ያኮቭሊቪች ግሉካሬፍ እና ጊራሲም ፔትሮቪች ፓቭስኪ ናቸው። ሁለቱም ሰዎች በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጉልህ ቦታ ያላቸው አባላትና የቋንቋ ምሁራን ነበሩ። እነዚህ ሰዎች ባለፈው መቶ ዘመን መባቻ ላይ ሥራቸውን ሲጀምሩ ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሩሲያኛ አልተተረጎመም ነበር።
እርግጥ ነው፣ ለዛሬው የሩሲያ ቋንቋ መቅድም በነበረው በስላቮን ቋንቋ የተዘጋጀ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። ይሁን እንጂ የስላቮን ቋንቋ ከ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽም በፊት ለሃይማኖታዊ ሥርዓት ካልሆነ በስተቀር የሕዝብ መገልገያ ቋንቋ መሆኑ አክትሞለት ነበር። በዚህ ጊዜም ቢሆን የሚጠቀሙበት ቀሳውስቱ ነበሩ። የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ላቲን ሙት ቋንቋ ከሆነ ከረጅም ጊዜ በኋላም እንኳ ሳይቀር መጽሐፍ ቅዱስ በላቲን ቋንቋ ብቻ ተወስኖ እንዲቀር ለማድረግ ትጥር በነበረበት በምዕራቡ ዓለምም ተመሳሳይ ሁኔታ ነበር።
ማካሪዮስና ፓቭስኪ መጽሐፍ ቅዱስ በተራው ሰው እጅ እንዲገባ ለማድረግ ሞክረዋል። ለረጅም ዘመን ተረስቶ የቆየው ሥራቸው መገኘቱ በሩሲያ ሥነ ጽሑፋዊና ሃይማኖታዊ ቅርስ ታሪክ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነገር ሆኗል።
ይሁን እንጂ ማካሪዮስና ፓቭስኪ እነማን ነበሩ? መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ተራው ሕዝብ ቋንቋ ለመተርጎም ያደረጉትስ ጥረት ይህን ያህል ተቃውሞ የገጠመው ለምንድን ነው? የእነዚህ ሰዎች ታሪክ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያፈቅሩ ሰዎችን ሁሉ የሚያስደንቅና እምነት የሚያጠነክር ነው።
በሩሲያ ቋንቋ መጽሐፍ ቅዱስ ማዘጋጀት ያስፈለገበት ምክንያት
መጽሐፍ ቅዱስን በተራው ሕዝብ ቋንቋ የማዘጋጀቱን አስፈላጊነት የተገነዘቡ የመጀመሪያዎቹ ሰዎች ማካሪዮስና ፓቭስኪ አልነበሩም። ከአንድ መቶ ዓመት ቀደም ብሎ የሩሲያው ዛር ቀዳማዊ ፒተር ወይም ታላቁ ፒተር የዚህን ጉዳይ አስፈላጊነት ተገንዝቦ ነበር። ለቅዱሳን ጽሑፎች አክብሮት የነበረው ሲሆን እንደሚከተለው ብሎ እንደነበር ይነገርለታል:- “መጽሐፍ ቅዱስ ከሌሎች መጻሕፍት ሁሉ የላቀ መጽሐፍ ነው፤ ሰው ለአምላክና ለጎረቤቶቹ ሊያደርጋቸው የሚገቡትን ነገሮች ሁሉ በዝርዝር ይዟል።”
በመሆኑም ፒተር በ1716 በራሱ ወጪ በአምስተርዳም አንድ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲታተም ለቤተ መንግሥቱ ትእዛዝ አስተላለፈ። በእያንዳንዱ ገጽ ላይ አንደኛው ዓምድ የሩሲያ ቋንቋ ሌላኛው ደግሞ የደች ቋንቋ የያዘ ሆኖ እንዲዘጋጅ ታቀደ። ልክ ከአንድ ዓመት በኋላ ማለትም በ1717 የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም “የአዲስ ኪዳን” ክፍል ተጠናቀቀ።
በ1721 በአንድ ዓምድ ብቻ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን የዳች ትርጉም የያዘ ባለ አራት ጥራዝ ትርጉም ታተመ። ሌላኛው ዓምድ በኋላ የሩሲያኛው ትርጉም እንዲቀመጥበት ሲባል ክፍት ተተወ። ፒተር የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ ሃይማኖታዊ የሥልጣን አካል የሆነው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን “ቅዱስ ሲኖዶስ” የኅትመቱን ሥራ እንዲያስፈጽምና ሥርጭቱን እንዲያካሂድ ሲል መጽሐፍ ቅዱሱን ወደዚያ መራው። ይሁን እንጂ ሲኖዶሱ ይህን ጉዳይ ከዳር ሳያደርሰው ቀረ።
ፒተር ከዚያ በኋላ አራት ዓመት እንኳ ሳይቆይ ሞተ። መጽሐፍ ቅዱሶቹስ ምን ደረሱ? የሩሲያው ትርጉም እንዲሠፍርበት ተብሎ ክፍት የተተወው ዓምድ ሳይሞላ ቀረ። መጽሐፍ ቅዱሶቹ ምድር ቤት ውስጥ አንድ ላይ ተቆልለው በመቀመጣቸው በሰበሱ፤ ከጊዜ በኋላ አንድ እንኳ ደህና ቅጂ ማግኘት አልተቻለም! ሲኖዶሱ “የቀረው ሁሉ ለነጋዴዎች እንዲሸጥ” ወሰነ።
የትርጉም ሥራ ለመሥራት ጥረት ተጀመረ
በ1812 የብሪታንያና የባሕር ማዶ አገራት የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር አባል የሆነው ጆን ፓተርሰን ወደ ሩሲያ መጣ። ፓተርሰን በሴንት ፒተርስበርግ የነበሩ ምሁራን የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር የማቋቋም ፍላጎት እንዲያድርባቸው አድርጓል። የሩሲያ ሠራዊት የቀዳማዊ ናፖሊዮንን ወራሪ ኃይል ባባረረበት ዓመት በ1812 ታኅሣሥ 6 ቀን ዛር አሌክሳንደር ቀዳማዊ የሩሲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበርን መቋቋሚያ ቻርተር አጸደቀ። በ1815 ንጉሠ ነገሥቱ፣ የማኅበሩ ሊቀ መንበር የነበረው ልዑል አሌክሳንደር ግለየትሲን ለሲኖዶሱ አስተዳደር እንደሚከተለው የሚል ሐሳብ እንዲያቀርብ አዘዙ:- “የሩሲያም ሕዝብ የአምላክን ቃል በትውልድ አገር ቋንቋው በሩሲያኛ ማንበብ የሚችልበት አጋጣሚ ሊያገኝ ይገባል።”
የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መጀመሪያ ከተጻፈበት የዕብራይስጥ ቋንቋ በቀጥታ ወደ ሩሲያኛ እንዲተረጎም መፈቀዱ የሚያስደስት ነበር። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ስላቮን ቋንቋ ለመተርጎም መነሻ ሆኖ ያገለገለው የጥንቱ የሰፕቱጀንት ትርጉም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ ለመተርጎም የተዘጋጁት ሰዎች የትርጉም ሥራው ተቀዳሚ መርኆ ትክክለኛ፣ ግልጽ እና ያልተበከለ ትርጉም ማዘጋጀት የሚል እንደሆነ ተነግሯቸው ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን በሩሲያ ቋንቋ ለማዘጋጀት የተደረጉት የእነዚህ ውጥኖች ውጤት ምን ነበር?
የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራ አከተመለት ማለት ነበርን?
በቤተ ክርስቲያንና በመንግሥት መካከል የነበሩ አንዳንድ ወግ አጥባቂ ወገኖች የባሕር ማዶውን ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ ተጽዕኖ በጥርጣሬ ዓይን ማየት ጀመሩ። ይባስ ብለው አንዳንድ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ከሩሲያኛ ይልቅ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በተሻለ መንገድ የሚያስተላልፈው የቤተ ክርስቲያን መገልገያ የሆነው የስላቮን ቋንቋ ነው ማለት ጀመሩ።
ስለዚህ በ1826 የሩሲያ የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ፈረሰ። የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበሩ ያዘጋጃቸው በርካታ ሺህ የትርጉም ቅጂዎች ተቃጠሉ። ከዚህ የተነሣ መጽሐፍ ቅዱስ ከሃይማኖታዊ ሥርዓትና ወግ ኋላ እንዲሠለፍ ተደረገ። ሲኖዶሱ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያንን ፈለግ በመከተል በ1836 እንደሚከተለው ሲል ደነገገ:- “ማንኛውም ለአምላክ ያደረ ሰው ቅዱሳን ጽሑፎችን ማዳመጥ ይፈቀድለታል፤ ይሁን እንጂ ያለ መመሪያ አንዳንድ የቅዱሳን ጽሑፎችን ክፍሎች በተለይ ደግሞ ብሉይ ኪዳንን ማንበብ ለማንኛውም ሰው የተከለከለ ነው።” የመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ ያከተመለት ይመስል ነበር።
የፓቭስኪ የትርጉም ሥራ
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዕብራይስጥ ቋንቋ ፕሮፌሰር የሆነው ጊራሲም ፓቭስኪ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ሩሲያኛ መተርጎሙን ተያያዘው። በ1821 የመዝሙር መጻሕፍትን ትርጉም አጠናቀቀ። የዛር አስተዳደር ወዲያው ስላጸደቀለት በጥር 1822 የመዝሙር መጽሐፉ ለሕዝብ ይፋ ሆነ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት በማግኘቱ መጽሐፉን 12 ጊዜ በተከታታይ ማሳተም አስፈልጎ የነበረ ሲሆን በድምሩ 100,000 ቅጂዎች ታትመዋል!
ፓቭስኪ ያደረገው ምሁራዊ ጥረት በብዙ የቋንቋና የሃይማኖት ምሁራን ዘንድ አክብሮት አትርፎለታል። የተሸረቡበትን ሴራዎች ሁሉ ያሸነፈ ግልጽና ሐቀኛ ሰው የሚል ስም አትርፏል። ቤተ ክርስቲያኒቱ የሩሲያን የመጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር ትቃወም የነበረና አንዳንዶች ደግሞ ማኅበሩ የባሕር ማዶ ሰዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ እንደቆመ አድርገው ይመለከቱት የነበረ ቢሆንም ፕሮፌሰር ፓቭስኪ በሚሰጣቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ወቅት ጥቅሶችን ወደ ሩሲያኛ መተርጎሙን ቀጥሎ ነበር። ሥራውን የሚያደንቁለት ተማሪዎቹም የሚናገራቸውን የጥቅስ ትርጉሞች በጽሑፍ በማስፈር ከጊዜ በኋላ ሥራውን አንድ ላይ ማጠናቀር ችለው ነበር። በ1839 ሳንሱር የሚያደርጉትን ወገኖች ፈቃድ ሳይጠይቁ እንደምንም ጨክነው በአካዳሚው ማተሚያ 150 ቅጂዎችን ማዘጋጀት ችለዋል።
የፓቭስኪ የትርጉም ሥራ በአንባቢዎቹ ላይ የነበረው ተጽዕኖ ቀላል ስላልነበር ሥራዎቹን ለማግኘት የሚቀርበው ጥያቄ እያደገ መጣ። ይሁን እንጂ በ1841 ይህ የትርጉም ሥራ የኦርቶዶክስን ቀኖና የተከተለ ባለመሆኑ “አደገኛ” ነው የሚል አቤቱታ ካልታወቀ ወገን ለሲኖዶሱ ደረሰው። ከዚያም ከሁለት ዓመታት በኋላ ሲኖዶሱ “በጂ ፓቭስኪ የተዘጋጀው የብሉይ ኪዳን ትርጉም የእጅ ግልባጭም ሆነ የኅትመት ቅጂ በሙሉ እየተለቀመ እንዲቃጠል” የሚል ድንጋጌ አወጣ።
የአምላክን ስም ከፍ ከፍ ማድረግ
የሆነ ሆኖ ፓቭስኪ በመጽሐፍ ቅዱስ የትርጉም ሥራ መስክ የሌሎችን ፍላጎት አቀጣጥሏል። በሌላም አንገብጋቢ ጉዳይ ረገድ ይኸውም የአምላክን ስም በሚመለከት ከኋላው ለሚመጡት ተርጓሚዎች ግሩም ምሳሌ ትቷል።
ሩሲያዊው ተመራማሪ ኮርሰንስኪ እንዲህ ሲሉ ተናግረዋል:- ‘ከስሞቹ ሁሉ ይበልጥ ቅዱስ የሆነው ትክክለኛው የአምላክ ስም ከአራት ዕብራይስጥ ፊደላት יהוה የተውጣጣ ሲሆን በዛሬው ጊዜ ጅሆቫ ተብሎ ይነበባል።’ በጥንቶቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ውስጥ ይህ የአምላክ መለያ ስም በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ብቻ በሺህ ለሚቆጠሩ ጊዜያት ተጠቅሶ ይገኝ ነበር። ይሁን እንጂ አይሁዳውያኑ ይህ መለኮታዊ ስም እጅግ ቅዱስ ከመሆኑ የተነሣ ሊጻፍም ሆነ ሊጠራ አይገባም የሚል የተሳሳተ እምነት አመጡ። ይህን በሚመለከት ኮርሰንስኪ አስተያየታቸውን ሲሰጡ ‘በንግግርም ሆነ በጽሑፍ በአብዛኛው ቦታ አዶናይ በሚለው ቃል ተተካ፤ ይህም ብዙውን ጊዜ የሚተረጎመው “ጌታ” ተብሎ ነው’ ብለዋል።
በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው መለኮታዊውን ስም መጠቀም ያቆሙት ከአጉል እምነት በመነጨ ፍርሃት እንጂ ለአምላክ በነበራቸው አክብሮታዊ ፍርሃት አልነበረም። መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ስም ከመጠቀም ወደኋላ እንድንል የሚያበረታታበት አንድም ቦታ የለም። አምላክ ለሙሴ እንዲህ ሲል ነግሮታል:- “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ትላለህ የአባቶቻችሁ አምላክ . . . እግዚአብሔር [“ይሖዋ፣” NW] ወደ እናንተ ላከኝ፤ ይህ ለዘላለሙ ስሜ ነው፣ እስከ ልጅ ልጅ ድረስም መታሰቢያዬ ነው።” (ዘጸአት 3:15) ቅዱሳን ጽሑፎች አምላኪዎችን በተደጋጋሚ “እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ስሙንም ጥሩ” በማለት አጥብቀው ያሳስባሉ። (ኢሳይያስ 12:4) ሆኖም ግን አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች የአይሁዳውያኑን ወግ መከተል መርጠው በመለኮታዊው ስም ሳይጠቀሙ ቀርተዋል።
ይሁን እንጂ ፓቭስኪ ይህንን ወግ አልተከተለም። በመዝሙር መጽሐፍ ትርጉሙ ውስጥ ብቻ ይሖዋ የሚለው ስም 35 ጊዜ ተጠቅሷል። የፓቭስኪ ልበ ሙሉነት በዘመኑ ከነበሩት መካከል በአንዱ ላይ ጉልህ ተጽዕኖ ነበረው።
አቡኑ ማካሪዮስ
በፓቭስኪ ዘመን የነበረው ይህ ሰው አቡኑ ማካሪዮስ ሲሆን እጅግ ከፍተኛ የቋንቋ ችሎታ የነበረው የሩሲያ ኦርቶዶክስ ሚስዮናዊ ነበር። የሰባት ዓመት ልጅ በነበረበት ገና በለጋ ዕድሜው በሩሲያ ቋንቋ ያሉ አጫጭር ሐሳቦችን ወደ ላቲን መተርጎም ይችል ነበር። ዕድሜው 20 ዓመት ሲሆን የዕብራይስጥ፣ የጀርመንኛና የፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን ያውቅ ነበር። ይሁን እንጂ የነበረው የትሕትና መንፈስና በአምላክ ፊት ያለበትን ኃላፊነት በቅን ልቦና መገንዘቡ በራሱ ከልክ በላይ በመተማመን ወጥመድ ውስጥ እንዳይወድቅ ጠብቆታል። በተደጋጋሚ ጊዜያት ሌሎች የቋንቋ ሊቃውንትንና ምሁራንን ያማክር ነበር።
ማካሪዮስ በሩሲያ የነበረውን የሚስዮናዊነት እንቅስቃሴ የማሻሻል ፍላጎት ነበረው። ክርስትና በሩሲያ በሚገኙ ሙስሊሞችና አይሁዶች ከመወሰዱ በፊት ቤተ ክርስቲያኒቱ “ትምህርት ቤቶችን በማቋቋምና መጽሐፍ ቅዱስን በሩሲያ ቋንቋ በማሰራጨት ብዙሐኑን ማንቃት” ይጠበቅባታል የሚል አቋም ነበረው። ማካሪዮስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ሩሲያኛ ለመተርጎም ፈቃድ እንዲሰጠው መጋቢት 1839 ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሄደ።
ማካሪዮስ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሆኑትን የኢሳይያስንና የኢዮብ መጻሕፍት ተርጉሞ ነበር። ይሁን እንጂ ሲኖዶሱ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ሩሲያ ቋንቋ ለመተርጎም ፈቃድ ከለከለው። እንዲያውም ማካሪዮስ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን ወደ ሩሲያ ቋንቋ እተረጉማለሁ የሚለውን ሕልምህን ብትረሳው ይሻላል ተባለ። ሲኖዶሱ ሚያዝያ 11 ቀን 1841 “ቶምስክ ውስጥ በሚገኝ የአንድ ጳጳስ ቤት ውስጥ ከሦስት እስከ ስድስት ሳምንት ለሚያክል ጊዜ ሱባኤ ገብቶ በጸሎትና ተንበርክኮ በመለመን ሕሊናውን እንዲያነጻ” የሚል ውሳኔ በማካሪዮስ ላይ አስተላለፈ።
ማካሪዮስ የወሰደው የድፍረት አቋም
ማካሪዮስ ከታኅሣሥ 1841 እስከ ጥር 1842 ድረስ ባለው ጊዜ ሱባኤውን ፈጸመ። ይሁን እንጂ ይህን እንደፈጸመ ወዲያው የቀረውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል መተርጎሙን ተያያዘው። የፓቭስኪን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም አንድ ቅጂ አግኝቶ ስለነበር የራሱን ትርጉም ለማስተያየት ተጠቅሞበታል። ልክ እንደ ፓቭስኪ እርሱም መለኮታዊውን ስም ለመሰወር ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል። እንዲያውም ይሖዋ የሚለው ስም በማካሪዮስ ትርጉም ውስጥ ከ3,500 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል!
ማካሪዮስ የትርጉም ቅጂዎች ሥራውን ለሚደግፉለት ወዳጆቹ ላከላቸው። በጊዜው አንዳንድ በእጅ የተገለበጡ ቅጂዎች ተሠራጭተው የነበረ ቢሆንም ቤተ ክርስቲያኒቱ ሥራው እንዳይታተም መከላከሏን ቀጠለች። ማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱሱን በባሕር ማዶ ለማሠራጨት ዕቅድ አወጣ። ይሁን እንጂ በሚሄድበት ዕለት ዋዜማ ታመመና ብዙም ሳይቆይ በ1847 ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ። የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ሥራው በእርሱ የሕይወት ዘመን ሳይታተም ቀረ።
በመጨረሻ ለኅትመት በቃ!
የኋላ ኋላ ፖለቲካዊና ሃይማኖታዊ ሁኔታዎቹ ተቀየሩ። በአገሪቱ ለዘብ ያለ አዲስ ሁኔታ በመስፈኑ በ1856 ሲኖዶሱ መጽሐፍ ቅዱስ በሩሲያ ቋንቋ እንዲተረጎም እንደገና ፈቃድ ሰጠ። በዚህ ለውጥ ምክንያት የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ ከ1860 እስከ 1867 በተከታታይ በወጡት ኦርቶዶክስ ሪቪው በተባለው መጽሔት እትሞች ላይ ወደ ሩሲያ ቋንቋ ለመተርጎም የተደረገ ሙከራ በሚል አምድ ሥር እየታተመ ወጣ።
የሩሲያ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ምሁር የሆኑት የቼርኒጎቩ ሊቀ ጳጳስ ፌላራ ስለ ማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል:- “ትርጉሙ የዕብራይስጡን ጽሑፍ በጥብቅ የተከተለ ሲሆን የተጠቀመበትም ቋንቋ ያልተበረዘና ለርዕሰ ጉዳዩ የሚስማማ ነው።”
ይሁን እንጂ የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ ለሕዝቡ ይፋ ሳይሆን ቀረ። እንዲያውም ጨርሶ ተረስቶ ነበር ማለት ይቻላል። በ1876 የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎችን ያካተተው መላው መጽሐፍ ቅዱስ በሲኖዶሱ ፈቃድ ወደ ሩሲያ ቋንቋ ተተረጎመ። ይህ ሙሉ መጽሐፍ ቅዱስ ብዙውን ጊዜ የሲኖዶስ ትርጉም በመባል ይታወቃል። የሲኖዶስ ትርጉም ይባል እንጂ ለዚህ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን “ኦፊሴላዊ” ትርጉም ዋነኛ ምንጭ ሆነው ያገለገሉት የማካሪዮስና የፓቭስኪ የትርጉም ሥራዎች ናቸው። ነገር ግን መለኮታዊውን ስም የተጠቀሙት በዕብራይስጡ ቅጂ ላይ ከሚገኝባቸው ቦታዎች መካከል በጥቂቶቹ ላይ ብቻ ነው።
የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ
የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ እስከ 1993 ድረስ ተሠውሮ ኖሯል። በመግቢያው ላይ እንደተጠቀሰው በዚህ ዓመት በሩሲያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ ከብርቅዬ መጻሕፍት መደዳ በተመደቡት የኦርቶዶክስ ሪቪው መጽሔቶች ላይ ሠፍሮ ተገኘ። የይሖዋ ምሥክሮች ይህን መጽሐፍ ቅዱስ ለሕዝቡ የማዳረሱን አስፈላጊነት ተገንዝበው ነበር። ይህ መጽሐፍ ታትሞ ይሠራጭ ዘንድ ቤተ መጻሕፍቱ በሩሲያ ለሚገኘው የይሖዋ ምሥክሮች ሃይማኖታዊ ድርጅት የማካሪዮስን መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ቅጂ ለማግኘት የሚያስችል ፈቃድ ሰጠ።
ከዚያም የይሖዋ ምሥክሮች ወደ 300,000 በሚጠጉ የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች በኢጣሊያ ታትመው በመላዋ ሩሲያና የሩሲያ ቋንቋ በሚነገርባቸው ሌሎች ብዙ አገሮች እንዲሠራጭ ዝግጅት አደረጉ። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ኅትመት አብዛኛውን የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ክፍል ከያዘው የማካሪዮስ ትርጉም በተጨማሪ የፓቭስኪን የመዝሙር መጻሕፍት ትርጉም እንዲሁም በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ ፈቃድ የተዘጋጀውን የግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ትርጉም ያካተተ ነው።
በዚህ ዓመት ጥር ወር ላይ በሩሲያ ሴንት ፒተርስበርግ በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህ መጽሐፍ ቅዱስ መውጣቱ ተገልጿል። (ገጽ 26ን ተመልከት።) ይህ አዲስ መጽሐፍ ቅዱስ በመውጣቱ የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ አንባቢዎች ተጨማሪ የእውቀት ብርሃን እንደሚያገኙና እንደሚነቃቁ ምንም ጥርጥር የለውም።
የዚህ መጽሐፍ ቅዱስ መታተም ሃይማኖታዊም ሥነ ጽሑፋዊም ድል ነው! ከዚህም በተጨማሪ በኢሳይያስ 40:8 ላይ የሚገኙትን ቃላት እውነተኛነት በሚመለከት እምነታችንን የሚያጠነክር ክስተት ነው:- “ሣሩ ይደርቃል አበባውም ይረግፋል፣ የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንታ ትኖራለች።”
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሣጥን/ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ከተቺዎች አድናቆት አተረፈ
“ይሁንና ሌላ የሥነ ጽሑፍ ቅርስ ተገኝቷል፤ ይኸውም የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ ነው።” ኮምሶሞለስኪ ፕራቭዳ የተባለው ጋዜጣ በመግቢያው ላይ ከላይ እንደተጠቀሰው በማለት የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ መታተሙን አስታውቋል።
ይህ ጋዜጣ፣ እስከ ዛሬ “120 ዓመታት” ገደማ ድረስ መጽሐፍ ቅዱስ በሩሲያ ቋንቋ እንዳልነበር ካሰፈረ በኋላ እንዲህ በማለት ቅሬታውን ገልጿል:- “ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ በቀላሉ በሚገባ ቋንቋ እንዳይተረጎም ለብዙ ዓመታት ስትከላከል ኖራለች። ቤተ ክርስቲያኒቱ በርካታ ትርጉሞችን ለመቀበል አሻፈረኝ ስትል ኖራ በመጨረሻ 1876 አንዱን ተቀብላለች፤ ይህም የሲኖዶስ ትርጉም የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል። ይሁን እንጂ ይህም ቢሆን ወደ ቤተ ክርስቲያን እንዲገባ አልተፈቀደም ነበር። እስከ ዛሬም ድረስ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እውቅና ያገኘው በስላቮን ቋንቋ የተዘጋጀው መጽሐፍ ቅዱስ ነው።”
ሴንት ፒተርስበርግ ኤኮ የተባለውም ጋዜጣ የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ መታተሙ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “በሴንት ፒተርስበርግ መንግሥታዊ ዩኒቨርሲቲ፣ በኸርዘን ፔዳጎጂካል ዩኒቨርሲቲና በሃይማኖታዊ ታሪክ መንግሥታዊ ቤተ መዘክር ያሉ በሙያው የተሠማሩ ምሁራን የዚህን መጽሐፍ ቅዱስ ኅትመት በእጅጉ አወድሰዋል።” ጋዜጣው በመቀጠልም ባለፈው መቶ ዘመን የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ ማካሪዮስና ፓቭስኪ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ ሩሲያ ቋንቋ መተርጎማቸውን ከዘገበ በኋላ እንዲህ ብሏል:- “እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሩሲያ ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ የሚቻለው በስላቮን ቋንቋ ብቻ ነበር፤ ይህንንም ቢሆን የሚረዱት ቀሳውስቱ ብቻ ናቸው።”
የይሖዋ ምሥክሮች የማካሪዮስን መጽሐፍ ቅዱስ አሳትመው ማውጣታቸው በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በተካሄደ አንድ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተዘግቧል። ኔፍስኮይ ቨሬምያ የተባለው የአካባቢው ዕለታዊ ጋዜጣ እንዲህ ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል:- “በሙያው የተሠማሩት ምሁራን . . . ይህ ኅትመት በሩሲያና በሴንት ፒትስበርግ የባህላዊ ቅርስ ታሪክ ውስጥ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ነገር መሆኑን አስምረውበታል። አንድ ሰው ስለዚህ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንቅስቃሴ ምንም ያስብ ምን ከአሁን በፊት የማይታወቅ የነበረው ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም መታተሙ ታላቅ ጥቅም እንዳለው አይካድም።”
በጽሑፍ የሠፈረው የአምላክ ቃል ተራው ሕዝብ አንብቦ ሊረዳው በሚችለው ቋንቋ በመዘጋጀቱ አምላክን የሚያፈቅሩ ሁሉ ደስ እንዳላቸው ምንም ጥርጥር የለውም። በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያፈቅሩ ሰዎች በሙሉ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት በሚልዮን የሚቆጠሩ ሩሲያኛ ተናጋሪዎች ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ማግኘት በመቻላቸው ተደስተዋል።
[ሥዕል]
የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ እንደወጣ የተገለጸው በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት ነበር
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተሰውሮ የኖረ ውድ ሃብት የተገኘበት የሩሲያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍት
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ታላቁ ፒተር መጽሐፍ ቅዱስ በሩሲያ ቋንቋ እንዲታተም ለማድረግ ሞክሯል
[ምንጭ]
Corbis-Bettmann
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
መጽሐፍ ቅዱስ ወደ ሩሲያ ቋንቋ እንዲተረጎም አስተዋጽኦ ያበረከተው ጊራሲም ፓቭስኪ
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አዲሱ የሩሲያ መጽሐፍ ቅዱስ በስሙ የተሰየመለት አቡኑ ማካሪዮስ