ታስታውሳለህን?
በቅርብ ጊዜ ከወጡት የመጠበቂያ ግንብ እትሞች ተግባራዊ ጠቀሜታ አግኝተህባቸዋልን? እንግዲያው ምን ያህል እንደምታስታውስ በሚከተሉት ጥያቄዎች ለምን ራስህን አትፈትንም?
◻ ‘በጌታ ቀን’ እና ‘በይሖዋ ቀን’ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? (ራእይ 1:10፤ ኢዩኤል 2:11)
‘የጌታ ቀን’ ከራእይ ምዕራፍ 1 እስከ 22 ድረስ ያሉትን የ16ቱን ራእዮች ፍጻሜ የሚያጠቃልልና ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ስለ መገኘቱ ምልክት ላቀረቡት ጥያቄ መልስ በሰጠበት ወቅት የተነበያቸው ነገሮች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ ይጨምራል። የጌታ ቀን የመጨረሻ ከፍተኛ ደረጃው ላይ በሚደርስበት ጊዜ ብልሹ በሆነው የሰይጣን ዓለም ላይ የጥፋት ፍርድ የሚያስፈጽምበት አስፈሪው የይሖዋ ቀን ይፈነዳል። (ማቴዎስ 24:3-11፤ ሉቃስ 21:11)—12/15፣ ገጽ 11
◻ የማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ አንዳንድ ልዩ ገጽታዎች ምንድን ናቸው?
በማካሪዮስ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይሖዋ የሚለው ስም ከ3,500 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ ይገኛል። አንድ የሩሲያ ሃይማኖታዊ ጽሑፎች ምሁር “ትርጉሙ የዕብራይስጡን ጽሑፍ በጥብቅ የተከተለ ሲሆን የተጠቀመበትም ቋንቋ ለርዕሰ ጉዳዩ የሚስማማ ነው” ብለዋል።—12/15፣ ገጽ 27
◻ ኢየሱስ ነፃ ያወጣችኋል ያለው “እውነት” ምንድን ነው? (ዮሐንስ 8:32)
ኢየሱስ “እውነት” ሲል አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት የሰጠውን መረጃ፣ በተለይም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾ የሚገኘውን ስለ አምላክ ፈቃድ የሚናገረውን መረጃ ማለቱ ነው።—1/1፣ ገጽ 3
◻ የዘመናችን ኢዩና ኢዮናዳብ እነማን ናቸው?
ኢዩ በምድር ላይ ‘የአምላክ እስራኤል’ በሆኑት ቅቡዓን ክርስቲያኖች የሚወከለውን ኢየሱስ ክርስቶስን ያመለክታል። (ገላትያ 6:16፤ ራእይ 12:17) ኢዮናዳብ ኢዩን ሊገናኘው እንደወጣ ሁሉ ከብሔራት የተውጣጡ “እጅግ ብዙ ሰዎች” የኢየሱስን ምድራዊ ወኪሎች ለመደገፍ መጥተዋል። (ራእይ 7:9, 10፤ 2 ነገሥት 10:15)—1/1፣ ገጽ 13
◻ ‘አካሄድን ከአምላክ ጋር ማድረግ’ ማለት ምን ማለት ነው? (ዘፍጥረት 5:24፤ 6:9)
ሄኖክንና ኖኅን የመሳሰሉ ይህን የሚያደርጉ ሁሉ በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት እንዳላቸው በሚያሳይ መንገድ ተመላልሰዋል ማለት ነው። ይሖዋ ያዘዛቸውን ከማድረጋቸውም ሌላ እርሱ ከሰው ልጆች ጋር ካደረጋቸው ግንኙነቶች በመማር ከዚያ ጋር በሚስማማ መንገድ ሕይወታቸውን መርተዋል።—1/15፣ ገጽ 13
◻ አንድ ሰው ልሞት እችል ይሆናል ብሎ በማሰብ ቅድመ ዝግጅት የሚያደርገው ለምንድን ነው?
ይህን ዝግጅት ማድረግ ለአንድ ሰው ቤተሰብ ስጦታ ነው ለማለት ይቻላል። ፍቅሩን ያሳያል። አንድ ሰው ከቤተሰቡ ጋር አንድ ላይ በሕይወት ያለ እንኳ ባይሆን ‘ስለ ቤተሰቡ እንደሚያስብ’ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (1 ጢሞቴዎስ 5:8)—1/15፣ ገጽ 22
◻ ‘አሮጌው ሕግ’ ምን ነገር አከናውኗል? (2 ቆሮንቶስ 3:14)
አዲሱን ቃል ኪዳን ያመላከተ ሲሆን በተደጋጋሚ ጊዜ መሥዋዕት ማቅረብን የሚጠይቅ መሆኑ የሰው ልጅ የግድ ከኃጢአትና ከሞት የሚቤዠው እንደሚያስፈልገው የሚያሳይ ነበር። ‘ወደ ክርስቶስ የሚያደርስ ሞግዚት ነበር።’ (ገላትያ 3:24)—2/1፣ ገጽ 14
◻ አዲሱ ቃል ኪዳን ዘላለማዊ የሆነው በምን መንገዶች ነው? (ዕብራውያን 13:20)
በመጀመሪያ ደረጃ እንደ ሕጉ ቃል ኪዳን በሌላ አይተካም። በሁለተኛ ደረጃ የሚያስገኘው ውጤት ዘላቂ ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ምድራዊ ተገዢዎች በሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ከአዲሱ ኪዳን ዝግጅት መጠቀማቸውን ይቀጥላሉ።—2/1፣ ገጽ 22
◻ አመስጋኝ ከመሆን ምን ጠቃሚ ውጤቶች ይገኛሉ?
አመስጋኝ የሆነ ሰው ምስጋና በማቅረቡ የሚሰማው ሞቅ ያለ ስሜት ለደስታውና ለሰላሙ አስተዋጽኦ ያደርጋል። (ከምሳሌ 15:13, 15 ጋር አወዳድር።) አመስጋኝነት አዎንታዊ ባሕርይ ስለሆነ እንደ ቁጣ፣ ቅናትና ብስጭት ከመሳሰሉት አፍራሽ አስተሳሰቦች አንድን ሰው ይጠብቃል።—2/15፣ ገጽ 4
◻ በመንፈስ የተወለዱት ክርስቲያኖች በየትኞቹ ቃል ኪዳኖች ውስጥ ታቅፈዋል?
በይሖዋና በመንፈሳዊ እስራኤል መካከል በተደረገው በአዲሱ ቃል ኪዳንና ኢየሱስ ዱካውን ከሚከተሉት የተቀቡ ተከታዮቹ ጋር ባደረገው የመንግሥት ቃል ኪዳን ውስጥ ታቅፈዋል። (ሉቃስ 22:20, 28-30)—2/15፣ ገጽ 16
◻ እስራኤላውያን እንዲያከብሯቸው የታዘዙት ሦስቱ ታላላቅ በዓላት የትኞቹ ናቸው?
ኒሳን 14 ቀን ከሚከበረው የማለፍ በዓል ቀጥሎ የሚከበረው የቂጣ በዓል፤ ከኒሳን 16 አንስቶ 50ኛው ቀን ላይ የሚከበረው የሳምንታት በዓል፤ በሰባተኛው ወር ላይ የሚከበረው የመሰብሰቢያ በዓል ወይም የዳስ በዓል። (ዘዳግም 16:1-15)—3/1፣ ገጽ 8, 9
◻ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መገኘት መብት የሆነው ለምንድን ነው?
ኢየሱስ “ሁለት ወይም ሦስት በስሜ በሚሰበሰቡበት በዚያ በመካከላቸው እሆናለሁና” ብሏል። (ማቴዎስ 18:20፤ 28:20) በተጨማሪም መንፈሳዊ ምግብ ከሚቀርብበት ዋነኛ መንገዶች መካከል የጉባኤ ስብሰባዎችና ታላላቅ ስብሰባዎች ይገኛሉ። (ማቴዎስ 24:45)—3/1፣ ገጽ 14
◻ ናምሩድ የሚለው ስም ከምን የመጣ ነው?
ብዙ ሊቃውንት ናምሩድ የሚለው ስም ሲወለድ የወጣለት እንዳልሆነ ይስማማሉ። ከዚህ ይልቅ ዓመፀኛ ባሕሪው ከታወቀ በኋላ ከሥራው ጋር የሚስማማ ስም እንደተሰጠው አስተውለዋል።—3/15፣ ገጽ 25
◻ የቤተሰብ ሕይወት ለሰብዓዊ ኅብረተሰብ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
ቤተሰብ ለሰው ልጅ የግድ አስፈላጊ ነው። ታሪክ እንደሚያሳየው የቤተሰብ ዝግጅት ሲቆረቁዝ የማኅበረሰቦችና የመንግሥታት ጥንካሬ ይዳከማል። ስለዚህ የቤተሰብ ሕይወት የኅብረተሰብን መረጋጋት፣ የልጆችን ደህንነት እንዲሁም የወደፊቱን ትውልድ በቀጥታ ይነካል።—4/1፣ ገጽ 6
◻ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል መሆኑን የሚያረጋግጡት ሦስቱ ማስረጃዎች የትኞቹ ናቸው?
(1) ሳይንሳዊ ትክክለኛነት ተንጸባርቆበታል፤ (2) ለዘመናዊው ኑሮ ተግባራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ጊዜ የማይሽራቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች ይዟል፤ (3) ፍጻሜያቸውን አግኝተው በታሪክ ሐቅነት የተመዘገቡ ትንቢቶችን ይዟል።—4/1፣ ገጽ 15