የሥጋ ደዌ በሽተኛ ብሆንም ሕይወቴ አስደሳችና መንፈሳዊ በረከት የሞላበት ነው
አይዛያ አዳግቦና እንደተናገረው
ያደኩት በናይጄርያ፣ አኩሬ በተባለ ቦታ ነው። ቤተሰቦቼ የስኳር ድንች፣ የሙዝ፣ የካሳቫና የኮኮዋ እርሻ ነበራቸው። አባቴ ወደ ትምህርት ቤት ሄጄ እንድማር አይፈልግም ነበር። “አንተ ገበሬ ነህ። ስኳር ድንች ለማምረት ደግሞ ማንበብ አያስፈልግም” ይለኝ ነበር።
ቢሆንም ማንበብ ለመማር እፈልግ ነበር። የግል አስተማሪ ተቀጥሮላቸው የሚማሩ ልጆች ወደነበሩበት አንድ ቤት ማታ ማታ እየሄድኩኝ በመስኮት በኩል ቆሜ የሚማሩትን አዳምጥ ነበር። ይህ የሆነው በ1940 ሲሆን በዚያን ጊዜ 12 ዓመት ይሆነኛል። የልጆቹ አባት ሲያየኝ እየጮኸ ያባርረኝ ነበር። ይሁን እንጂ መሄዴን አላቆምኩም። አንዳንድ ጊዜ አስተማሪው ሲቀር ተደብቄ እገባና ከልጆቹ ጋር ሆኜ መጽሐፋቸውን እመለከት ነበር። አልፎ አልፎ ልጆቹ መጽሐፋቸውን ያውሱኝ ነበር። ማንበብ የተማርኩት በዚህ መንገድ ነው።
ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ተገናኘሁ
ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ስላገኘሁ ወደ መኝታዬ ከመሄዴ በፊት ሁልጊዜ አነበው ጀመር። አንድ ቀን ምሽት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በሰዎች እንደሚጠሉና እንደሚሰደዱ የሚገልጸውን ማቴዎስ ምዕራፍ 10ን አነበብኩ።
የይሖዋ ምሥክሮች ወደ ቤታችን መጥተው በነበረበት ጊዜ ተቃውሞ እንዳጋጠማቸው አስታውሳለሁ። ኢየሱስ የተናገረላቸው ሰዎች እነዚህ መሆን አለባቸው አልኩ። በሚቀጥለው ጊዜ ምሥክሮቹ ቤታችን ሲመጡ አንድ መጽሔት ወሰድኩ። ከእነርሱ ጋር መሰብሰብ ስጀምር ሰዎች መሳለቂያ አደረጉኝ። ሆኖም ሰዎች ተስፋ ሊያስቆርጡኝ በሞከሩ መጠን እውነተኛውን ሃይማኖት ማግኘቴን ይበልጥ እንዳምን ስላደረገኝ በይበልጥ አስደስቶኛል።
ምሥክሮቹ በሰፈሬ እንዳሉት እንደ ሌሎቹ ሃይማኖታዊ ቡድኖች በአካባቢው የሚገኙትን አረማዊ ሃይማኖታዊ ወጎችንና ልማዶችን በአምልኮታቸው ውስጥ አለመቀላቀላቸው በጣም ነክቶኝ ነበር። ለምሳሌ ያህል ቤተሰቤ ወደ አንግሊካን ቤተ ክርስቲያን የሚሄድ ቢሆንም አባቴ ግን ለዮሩባ አምላክ ለኦጉን አምልኮ የሚያቀርብበት የተወሰነ ቦታ ነበረው።
አባቴ ከሞተ በኋላ ያንን ቦታ እንድወርስ ይጠበቅብኝ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ጣዖት አምልኮን እንደሚያወግዝ ስለማውቅ ቦታውን ለመውረስ አልፈለግሁም። ይሖዋ በመንፈሳዊ እንዳድግ ስለረዳኝ በታኅሣሥ 1954 ተጠመቅሁ።
የሥጋ ደዌ በሽታ ያዘኝ
በዚያ ዓመት መጀመሪያ ላይ እግሮቼ እያበጡና ስሜት አልባ እየሆኑ እንደመጡ ተመለከትሁ። በፍም ከሰል ላይ ብራመድም ምንም አይሰማኝም ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ በግንባሬና በከንፈሮቼ ላይ ቀያይ ቁስሎች ወጡብኝ። እኔም ሆንኩ ቤተሰቦቼ ችግሩ ምን እንደሆነ ስላላወቅን ችፌ ይሆናል ብለን አስበን ነበር። ፈውስ ፍለጋ 12 የባህል መድኃኒት ቀማሚዎች ጋ ሄጄ ነበር። በመጨረሻ ከመካከላቸው አንዱ የሥጋ ደዌ መሆኑን ነገረን።
ምንኛ አስደንጋጭ ነበር! በጣም ስለተረበሽኩ በደንብ አልተኛም ነበር። ያቃዠኝ ነበር። ይሁን እንጂ የነበረኝ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት እንዲሁም በይሖዋ መታመኔ የወደፊቱን ጊዜ በትምክህት እንድመለከት ረድቶኛል።
መሥዋዕት ለማቅረብ ወደ አንድ አዋቂ ቢሄድ በሽታው ይሻለዋል በማለት ሰዎች ለእናቴ ይነግሯት ነበር። እንዲህ ያለው ድርጊት ይሖዋን እንደማያስደስተው ስለማውቅ ለመሄድ ፈቃደኛ አልሆንኩም። የእናቴ ጓደኞች ላለመሄድ መወሰኔን ሲገነዘቡ እናቴ በኮላ ፍሬ ግንባሬን እንድታስነካ ነገሯት። ከዚያም ያንን የኮላ ፍሬ በእኔ ስም ለአዋቂው መሥዋዕት አድርጋ ታቀርበዋለች። እንዲህ እንድታደርግ እንደማልፈልግ ነገርኳት። በመጨረሻም በአረማዊ ሃይማኖት ተካፋይ እንድሆን የምታደርገውን ጥረት አቆመች።
ወደ ሆስፒታል የሄድኩት የሥጋ ደዌ በሽታው በሰውነቴ ውስጥ ከተሰራጨ በኋላ ነበር። ሰውነቴ በሙሉ በቁስል ተወርሶ ነበር። በሆስፒታሉ ሕክምና ከተደረገልኝ በኋላ ቆዳዬ ቀደም ሲል ወደነበረው ጤናማ ሁኔታ ተመለሰ።
ሞቷል ብለው አስበው ነበር
ይሁን እንጂ ገና ብዙ ችግሮች ነበሩብኝ። የቀኝ እግሬ በጣም ተመርዞ ስለነበር በ1962 መቆረጥ ነበረበት። ከቀዶ ሕክምናው በኋላ ውስብስብ የጤና እክሎች ነበሩብኝ። ሐኪሞቹ ይሞታል ብለው ደምድመው ነበር። አንድ ነጭ ሚስዮናዊ ቄስ ሥጋወ ደሙን ሊያቀምሰኝ መጣ። መናገር እስኪያቅተኝ ድረስ በጣም ደክሜ ነበር። ይሁን እንጂ አንዲት ነርስ የይሖዋ ምሥክር መሆኔን ነገረችው።
ቄሱ “ወደ ሰማይ መሄድ እንድትችል ወደ ካቶሊክነት ለመለወጥ ትፈልጋለህን?” ሲል ጠየቀኝ። አነጋገሩ በሆዴ እንድስቅ አድርጎኝ ነበር። መልስ ለመስጠት የሚያስችል ጥንካሬ እንዲሰጠኝ ወደ ይሖዋ ጸለይኩ። በስንት ትግል “አልፈልግም!” ብዬ ተናገርኩ። ቄሱ ትቶኝ ሄደ።
የሆስፒታሉ ሠራተኞች ሞቷል ብለው እስኪደመድሙ ድረስ ሁኔታዬ ተባባሰ። ፊቴን በጨርቅ ሸፈኑት። ቢሆንም አንድ ሐኪም ወይም አንዲት ነርስ መሞቴን ማረጋገጥ ስለነበረባቸው ወደ ሬሳ ክፍል አልወሰዱኝም። ተረኛ ሐኪም አልነበረም፤ እንዲሁም ሁሉም ነርሶች ወደ ግብዣ ሄደው ነበር። ስለዚህ ሌሊቱን በበሽተኞች ክፍል ውስጥ አሳለፍኩ። በማግስቱ ጠዋት ሐኪሙ በሽተኞችን እየዞረ ሲጠይቅ በጨርቅ ተሸፍኜ ስለነበርና ሞቷል ብለው ስላሰቡ ወደ እኔ አልጋ የመጣ ማንም አልነበረም። በመጨረሻ አንድ ሰው በጨርቅ የተሸፈነው “ሬሳ” የሚንቀሳቀስ መሆኑን ተመለከተ!
ከበሽታዬ ካገገምኩ በኋላ በታኅሣሥ 1963 በደቡብ ምዕራብ ናይጄሪያ በአቢዎኩታ ወደሚገኘው የሥጋ ደዌ በሽተኞች መንከባከቢያ ተቋም ተዛወርኩ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የምንኖረው በዚያ ነው።
የስብከት ሥራዬ ተቃውሞ ገጠመው
መንከባከቢያ ተቋሙ ስደርስ ወደ 400 የሚጠጉ የሥጋ ደዌ በሽተኞች የነበሩ ሲሆን ከእኔ በስተቀር አንድም የይሖዋ ምሥክር አልነበረም። ለማኅበሩ ጻፍኩ፤ እነሱም የአኮሞጄ ጉባኤ ከእኔ ጋር እንዲገናኙ በማድረግ ወዲያውኑ ምላሽ ሰጡ። ስለዚህ ከወንድሞች ጋር ያለኝን ግንኙነት አቋርጬ አላውቅም።
በመንከባከቢያ ተቋሙ እንደ ደረስኩ መስበክ ጀመርኩ። በዚያ የሚገኙት ፓስተር በመስበኬ ስላልተደሰቱ የመንከባከቢያ ተቋሙ አስተዳዳሪ ለሆኑት ለእርዳታ ሹሙ ነገሯቸው። የእርዳታ ሹሙ ከጀርመን የመጡ ጠና ያሉ ሰው ነበሩ። ትምህርትም ሆነ የምስክር ወረቀት ስለሌለኝ መጽሐፍ ቅዱስን የማስተማር መብት እንደሌለኝ ነገሩኝ። የማስተማር ብቃቱ ስለሌለህ ሰዎችን የተሳሳተ ነገር ታስተምራቸዋለህ አሉ። በአቋሜ ከቀጠልኩ ከመንከባከቢያ ተቋሙ ልባረርና ሕክምናም ልከለከል እንደምችል ነገሩኝ። መልስ እንድሰጣቸው አልፈቀዱልኝም።
ቀጥሎ ማንም ሰው ከእኔ ጋር መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያጠና የሚከለክል ማዘዣ አወጡ። በዚህ ምክንያት ፍላጎት የነበራቸው ሰዎች ወደ እኔ መምጣታቸውን አቆሙ።
ጥበብና መመሪያ እንዲሰጠኝ ስለ ጉዳዩ ለይሖዋ በጸሎት ነገርኩት። በሚቀጥለው እሁድ በሃይማኖታዊ ሥርዓቱ ተካፋይ ባልሆንም ወደ መጥምቃውያን ቤተ ክርስቲያን ሄድኩ። በፕሮግራሙ መካከል በቦታው የተገኙ ሰዎች ጥያቄዎችን የሚጠይቁበት ክፍለ ጊዜ ነበር። እጄን አውጥቼ እንዲህ ስል ጠየቅሁ:- “ጥሩ ሰዎች ሁሉ ወደ ሰማይ፣ መጥፎ ሰዎች ደግሞ ወደ አንድ ሌላ ቦታ የሚሄዱ ከሆነ፣ ኢሳይያስ 45:18 አምላክ ምድርን የፈጠራት ለመኖሪያነት መሆኑን የሚናገረው ለምንድን ነው?”
በጉባኤው መካከል ብዙዎች ሲያንሾካሽኩ ነበር። በመጨረሻ ሚስዮናዊው ፓስተር የአምላክን መንገዶች ልንገነዘባቸው አንችልም በማለት ተናገሩ። ከዚያም 144,000 ሰዎች ወደ ሰማይ እንደሚሄዱ፣ ክፉዎች እንደሚጠፉ እንዲሁም ጻድቅ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንደሚኖሩ የሚናገሩ ጥቅሶችን እያወጣሁ በማንበብ የራሴን ጥያቄ መለስኩ።—መዝሙር 37:10, 11፤ ራእይ 14:1, 4
በሰጠሁት መልስ በመደነቅ ሁሉም አጨበጨቡ። ከዚያም ፓስተሩ “ይህ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ስለሚያውቅ በድጋሚ አጨብጭቡለት” ሲሉ ተናገሩ። ፕሮግራሙ ካበቃ በኋላ አንዳንዶች ወደ እኔ መጥተው “ከፓስተሩ የሚበልጥ እውቀት አለህ!” ብለውኛል።
እኔን ለማባረር የሚደረገው ጥረት ቀጠለ
ይህ ሁኔታ የሚደርስብኝን ስደት በእጅጉ ስለቀነሰው ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት ወደ እኔ መምጣት ጀመሩ። ይሁን እንጂ የእርዳታ ሹሙ እንዲያባርሩኝ ግፊት የሚያደርጉ ተቃዋሚዎች አሁንም ነበሩ። በቤተ ክርስቲያኑ ሥርዓት ላይ ከተገኘሁ ከአንድ ወር በኋላ ጠሩኝና እንዲህ አሉኝ:- “መስበክህን የቀጠልከው ለምንድን ነው? የአገሬ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን አይወዷቸውም፤ እዚህም ያው ነው። ለምን ችግር ትፈጥርብኛለህ? ላባርርህ እንደምችል አታውቅም?”
እንዲህ ስል መለስኩላቸው:- “አባባ፣ በሦስት ምክንያቶች አከብርዎታለሁ። በመጀመሪያ ደረጃ በዕድሜ ይበልጡኛል። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ አረጋውያንን አክብር ይላል። እኛን ለመርዳት ሲሉ አገርዎን ትተው መምጣትዎ እንዳከብርዎት የሚያደርገኝ ሁለተኛ ምክንያት ነው። በሦስተኛ ደረጃ ደግና ለጋስ ነዎት፤ እንዲሁም የተጨነቁ ሰዎችን ይረዳሉ። ይሁን እንጂ እኔን ለማባረር ምን መብት አለዎት? የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የይሖዋ ምሥክሮችን አላባረሩም። የአካባቢው የጎሣ መሪ አያባርሩንም። ከዚህ መንከባከቢያ ተቋም ቢያባርሩኝ እንኳ ይሖዋ ይንከባከበኛል።”
እንዲህ ፍርጥርጥ አድርጌ ተናግሬ ስለማላውቅ ምን ያህል እንደተገረሙ ለማየት ችያለሁ። ምንም ቃል ሳይተነፍሱ ሄዱ። ከጊዜ በኋላ አንድ ሰው ስለ እኔ አቤቱታ ሲያቀርብላቸው በጣም ተበሳጭተው “ከእንግዲህ ወዲህ በዚህ ጉዳይ ውስጥ እጄን አላስገባም። ለምን ይሰብካል የምትል ከሆነ ራሱን ልታነጋግረው ትችላለህ!” ብለው መለሱለት።
የጐልማሶች ትምህርት ቤት
በመጠለያው ውስጥ የሚገኘው የመጥምቃውያን ቤተ ክርስቲያን አባላት የስብከት ሥራዬን መቃወማቸውን ቀጠሉ። ከዚያም ይሖዋ አንድ ሐሳብ እንዳፈልቅ ረዳኝ። ወደ እርዳታ ሹሙ ሄጄ የጎልማሶች ትምህርት ቤት መክፈት እችል እንደሆነ ጠየቅኋቸው። ምን ያህል እንዲከፈለኝ እንደምፈልግ ሲጠይቁኝ ምንም ክፍያ እንደማልፈልግ ነገርኳቸው።
የመማሪያ ክፍል፣ ጥቁር ሰሌዳና ጠመኔ ካቀረቡልኝ በኋላ አብረውኝ ያሉ አንዳንድ ሰዎችን ንባብ ማስተማር ጀመርኩ። ትምህርቱ የሚሰጠው በየቀኑ ነበር። ለመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች ንባብ አስተምራለሁ፤ ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ አንድ ታሪክ እነግራቸውና ታሪኩን አብራራላቸዋለሁ። ከዚያ በኋላ ታሪኩን ከመጽሐፍ ቅዱስ እናነባለን።
ኒሞታ የምትባል አንዲት ሴት ተማሪ ነበረች። ለመንፈሳዊ ነገሮች ጥልቅ ፍላጎት ስለነበራት ወደ ቤተ ክርስቲያንም ሆነ ወደ መስጊድ እየሄደች ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን ትጠይቅ ነበር። በእነዚህ ቦታዎች ለጥያቄዎቿ መልስ ለማግኘት ባለመቻሏ እኔን ለመጠየቅ ትመጣ ነበር። ውሎ አድሮ ሕይወቷን ለይሖዋ ወስና ተጠመቀች። ከዚያም በ1966 ተጋባን።
ዛሬ በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ ወንድሞች ማንበብና መጻፍ የተማሩት በዚያ የጎልማሶች ትምህርት ቤት ነው። ይህ ትምህርት ቤት እንዲከፈት ሐሳቡን የማቅረብ ጥበቡ አልነበረኝም። የይሖዋ በረከት ማረጋገጫ ነበር። ከዚያ በኋላ የስብከት ሥራዬን ለማስቆም ሙከራ ያደረገ አንድም ሰው አልነበረም።
በመጠለያው ውስጥ የሚገኝ የመንግሥት አዳራሽ
ከኒሞታ ጋር በተጋባን ጊዜ የመጠበቂያ ግንብ ጥናት ለማድረግ አራት ሆነን እንሰበሰብ ነበር። ለአንድ ዓመት ያህል የሥጋ ደዌ በሽተኞች ቁስላቸውን በሚታጠቡበት ክፍል ውስጥ ተሰብስበናል። ከዚያም አሁን ወዳጄ የሆኑት የእርዳታ ሹሙ “በአንድ የሕክምና መስጫ ክፍል ውስጥ ሆናችሁ አምላካችሁን ማምለካችሁ ጥሩ አይደለም” አሉኝ።
የአናጢው መጋዘን ባዶ ስለሆነ እዚያ ልንሰበሰብ እንደምንችል ነገሩን። ከጊዜ በኋላ ይህ መጋዘን ወደ መንግሥት አዳራሽነት ተለውጧል። በ1992 በከተማው ውስጥ በሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ አዳራሹን ሠርተን ጨረስን። በገጽ 24 ላይ ካለው ሥዕል ለማየት እንደምትችሉት አዳራሻችን የተለሰነና ቀለም የተቀባ እንዲሁም መሬቱ ሊሾ የሆነና በደንብ የተሠራ ጣሪያ ያለው ግሩም ሕንጻ ነው።
የሥጋ ደዌ በሽታ ላለባቸው ሰዎች መመስከር
ይህ የሥጋ ደዌ በሽተኞች መንከባከቢያ ተቋም ላለፉት 33 ዓመታት የአገልግሎት ክልሌ ሆኖ ቆይቷል። የሥጋ ደዌ በሽታ ላለባቸው ሰዎች መመስከር ምን ይመስላል? በዚህ በአፍሪካ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ሁሉም ነገር የሚመጣው ከአምላክ ነው የሚል እምነት አላቸው። ስለዚህ የሥጋ ደዌ ሲይዛቸው የአምላክ እጅ አለበት ብለው ያምናሉ። አንዳንዶች ስለ ሁኔታቸው በጣም ይጨነቃሉ። ሌሎች በመናደድ “አምላክ አፍቃሪና ርኅሩኅ መሆኑን አትንገረን። አምላክ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ይህ በሽታ ይተወን ነበር!” ይላሉ። ከዚያም በያዕቆብ 1:13 ላይ የሚገኘውን ‘አምላክ ማንንም በክፉ አይፈትንም’ የሚለውን ጥቅስ አውጥተን እናነብላቸዋለን። የጥቅሱን ሐሳብም እንወያይበታለን። ቀጥሎ ሰዎች በሽታ እንዲይዛቸው ይሖዋ ለምን እንደፈቀደ እናስረዳቸውና ሰው በሽተኛ ስለማይሆንበት ስለ ገነቲቷ ምድር ተስፋ የሚናገሩትን ጥቅሶች እናነብላቸዋለን።—ኢሳይያስ 33:24
ብዙዎች ለምሥራቹ አዎንታዊ ምላሽ ሰጥተዋል። ወደዚህ መጠለያ ከመጣሁበት ጊዜ አንስቶ የሥጋ ደዌ በሽተኞች የሆኑ 30 ሰዎች ራሳቸውን ወስነው እንዲጠመቁ ለመርዳት ይሖዋ ተጠቅሞብኛል። ብዙዎቹ ከበሽታው ከዳኑ በኋላ ወደየመጡበት አካባቢ የተመለሱ ሲሆን ጥቂቶች ደግሞ ሞተዋል። አሁን 18 የመንግሥቱ አስፋፊዎች ሲኖሩን 25 ሰዎች በስብሰባዎቻችን ላይ አዘውትረው ይገኛሉ። በሽምግልና የምናገለግለው ሁለት ስንሆን አንድ የጉባኤ አገልጋይና አንድ የዘወትር አቅኚ አሉን። ዛሬ በዚህ መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ብዙ ሰዎች ይሖዋን በታማኝነት በማገልገል ላይ መሆናቸውን ስመለከት ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል! እዚህ ስመጣ ብቸኛ እሆናለሁ ብዬ ሰግቼ ነበር፤ ይሁን እንጂ ይሖዋ በሚያስደንቅ መንገድ ባርኮኛል።
ወንድሞቼን በማገልገል የማገኘው ደስታ
ከ1960 ጀምሮ ለሥጋ ደዌ በሽታ እወስድ የነበረውን መድኃኒት ከአምስት ዓመት በፊት አቁሜአለሁ። አሁን እኔም ሆንኩ ሌሎች በጉባኤያችን ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች ከበሽታችን ሙሉ በሙሉ ድነናል። በሥጋ ደዌው ምክንያት አንዱን እግሬን ከጉልበቴ በታች ያጣሁና እጆቼን መዘርጋት የማልችል ብሆንም በሽታው ለቅቆኛል።
ከበሽታው ስለዳንኩ መጠለያውን ለቅቄ ለምን ወደ መጣሁበት ተመልሼ እንደማልሄድ አንዳንዶች ይጠይቁኛል። በመጠለያው ውስጥ የምቆይበት በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ዋነኛው ግን እዚህ ያሉትን ወንድሞች ለመርዳት ያለኝ ፍላጎት ነው። የይሖዋን በጎች መንከባከብ የሚሰጠኝ ደስታ ወደ ቤተሰቤ ብመለስ እነሱ ሊሰጡኝ ከሚችሉት ማንኛውም ነገር ይበልጥብኛል።
የሥጋ ደዌ በሽታ እንዳለብኝ ከማወቄ በፊት ይሖዋን በማወቄ በጣም አመስጋኝ ነኝ። እንደዚያ ባይሆን ኖሮ ሕይወቴን አጠፋ ነበር። ባለፉት ዓመታት ብዙ መከራና ችግር ተፈራርቆብኛል። ይሁን እንጂ ደግፎ ያቆመኝ መድኃኒቱ ሳይሆን ይሖዋ ነበር። ወደኋላ መለስ ብዬ ሳስብ በደስታ እዋጣለሁ፤ ወደፊት በአምላክ መንግሥት ሥር ስለሚፈጸሙ ነገሮች ሳስብ ደግሞ ከዚያ ይበልጥ ደስ ይለኛል።
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
የሥጋ ደዌ በሽታ አጭር መግለጫ
የሥጋ ደዌ በሽታ ምንድን ነው?
በጊዜያችን የሚገኘው የሥጋ ደዌ በሽታ ባሲለስ በሚባል ባክቴሪያ ሳቢያ የሚከሰት ነው። ይህን በሽታ የሚያመጣውን ባክቴሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በ1873 ለይቶ ያወቀው አርሞር ሃንሰን ነው። ሐኪሞች ለሥራው እውቅና ለመስጠት ሲሉ ሥጋ ደዌን የሃንሰን በሽታ ብለውም ይጠሩታል።
ይህ ባሲለስ ነርቭን፣ አጥንትን፣ ዓይንንና አንዳንድ የአካል ክፍሎችን ይጎዳል። አብዛኛውን ጊዜ እጅና እግር ስሜት አልባ እንዲሆኑ ያደርጋል። በቶሎ ካልታከሙ በሽታው ፊትን፣ እጅንና እግርን ክፉኛ ይቆራርጣል። በበሽታው ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም አናሳ ነው።
ፈውስ አለውን?
ቀለል ያለው ዓይነት የሥጋ ደዌ በሽታ ያለባቸው ሰዎች ያለ ምንም ሕክምና ይድናሉ። ይበልጥ ከባድ የሆኑት ደግሞ መድኃኒት በመውሰድ ሊድኑ ይችላሉ።
በ1950ዎቹ የተቀመመው የመጀመሪያው ፀረ ሥጋ ደዌ መድኃኒት የመፈወስ አቅሙ አዝጋሚ የነበረ ከመሆኑም በላይ ሥጋ ደዌ አምጪ የሆነው ባሲለስ የተባለው ባክቴሪያ የመድኃኒቱን የመፈወስ ኃይል ስለተቋቋመው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ ሄዷል። አዳዲስ መድኃኒቶች የተቀመሙ ሲሆን ከ1980ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ መልቲ ድራግ ቴራፒ የሚባለው የሕክምና ዘዴ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሥራ ላይ ውሏል። ይህ የሕክምና ዘዴ ዳፕሶን፣ ሪፋምፒሲን እና ክሎፋዚሚን የተባሉት ሦስት መድኃኒቶች ጥምረት ነው። የተለያዩ መድኃኒቶችን አንድ ላይ አጣምሮ መስጠቱ ባሲለሱን ቢያጠፋውም ይህ ባክቴሪያ ቀደም ሲል ያደረሰውን ጉዳት ግን አይፈውስም።
የተለያዩ መድኃኒቶችን አጣምሮ በመስጠት የሚካሄደው ሕክምና ከፍተኛ የመፈወስ አቅም ያለው ነው። በመሆኑም በ1985 የሥጋ ደዌ በሽተኞች ቁጥር 12 ሚልዮን የነበረ ሲሆን በ1996 አጋማሽ ላይ ወደ 1.3 ሚልዮን ዝቅ ብሏል።
ምን ያህል ተላላፊ ነው?
የሥጋ ደዌ በሽታ እጅግም ተላላፊ አይደለም። ብዙ ሰዎች በሽታውን ለመቋቋም የሚያስችል በቂ የተፈጥሮ መከላከያ በሰውነታቸው ውስጥ አላቸው። በሽታው በአብዛኛው የሚከሰተው በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር ለረዥም ጊዜ በመነካካት ነው።
ሐኪሞች ባሲለስ ወደ ሰውነት እንዴት እንደሚገባ በእርግጠኝነት የሚያውቁት ነገር የለም። ይሁን እንጂ በቆዳ ወይም በአፍንጫ በኩል ወደ ሰውነት ይገባል የሚል ግምት አላቸው።
የበሽታው የወደፊት ሁኔታ
የሥጋ ደዌ በሽታ “እንደ አንድ ሕዝባዊ የጤና እክል” ተቆጥሮ በ2000 ዓመት ከምድረ ገጽ ለማጥፋት በእቅድ ተይዟል። ይህ ማለት በየትኛውም ማኅበረሰብ ውስጥ ከሚኖሩ ሰዎች መካከል በሥጋ ደዌ በሽታ የሚለከፉት ብዛት ከ10,000 ሰው ከ1 አይበልጥም ማለት ነው። በአምላክ መንግሥት ግዛት ሥር ግን ሙሉ በሙሉ ተጠራርጎ ይጠፋል።—ኢሳይያስ 33:24
ምንጭ:- የዓለም የጤና ድርጅት፤ ኢንተርናሽናል ፌዴሬሽን ኦቭ አንቲ ሌፕረሲ አሶሲዬሽንስ፤ እንዲሁም ማንሰንስ ትሮፒካል ዲዚዝስ፤ የ1996 እትም።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
በጊዜያችን ያለው የሥጋ ደዌ በሽታ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ከነበረው ጋር ተመሳሳይ ነውን?
ዛሬ የሕክምና ማስተማሪያ መጻሕፍት ለሥጋ ደዌ በሽታ ትክክለኛውን ትርጉም ይሰጣሉ። በበሽታው ውስጥ የሚገኘው ሚክሮብ ሳይንሳዊ ስሙ ማይኮባክቴሪየም ሌፕሬ ነው። እርግጥ ነው መጽሐፍ ቅዱስ የሕክምና ማስተማሪያ መጽሐፍ አይደለም። በበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ላይ “ሥጋ ደዌ” ተብለው የተተረጎሙት የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት ይበልጥ ሰፊ የሆነ ትርጉም ያዘሉ ናቸው። ለምሳሌ ያህል የመጽሐፍ ቅዱሱ ሥጋ ደዌ (ለምጽ) በሰዎች ላይ ብቻ ሳይሆን በልብሶችና በእቃዎች ላይ ጭምር የሚታይ ምልክት ያወጣል። ባሲለስ ግን ይህን አያደርግም።—ዘሌዋውያን 13:2, 47፤ 14:34
ከዚህም በላይ ዛሬ ሥጋ ደዌ በያዛቸው ሰዎች ላይ የሚታዩ ምልክቶች በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን ለነበረው ሥጋ ደዌ ከተሰጠው መግለጫ ጋር እምብዛም ተመሳሳይነት የላቸውም። አንዳንዶች ይህ የሆነበት ምክንያት ጊዜ እያለፈ በሄደ ቁጥር የበሽታዎች ባሕርይም የሚለዋወጥ በመሆኑ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው የሥጋ ደዌ ኤም ሌፕሬ በተባለው ሚክሮብ የሚከሰተውን ጨምሮም ይሁን ሳይጨምር ብዛት ያላቸውን የበሽታ ዓይነቶች የሚያመለክት ነው ብለው ያምናሉ።
ዘ ቲኦሎጂካል ዲክሽነሪ ኦቭ ዘ ኒው ቴስታመንት እንደሚለው በአብዛኛው ሥጋ ደዌ ተብለው የተተረጎሙት ሁለቱም የዕብራይስጥና የግሪክኛ ቃላት “የሚያመለክቱት ተመሳሳይ የሆነን በሽታ ወይም የበሽታዎች ስብስብን ነው። . . . ይህ በሽታ ዛሬ ሥጋ ደዌ ብለን የምንጠራው መሆኑ አጠያያቂ ነው። ይሁን እንጂ ለበሽታው የተሰጠው ትክክለኛ የሕክምና ማብራሪያ [ኢየሱስና የእርሱ ደቀ መዛሙርት ሥጋ ደዌ በሽተኞችን] ስለመፈወሳቸው ለሚናገረው ዘገባ ያለንን ግምት አይቀንሰውም።”
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጉባኤው በሥጋ ደዌ በሽተኞች መጠለያ ውስጥ ከሚገኘው የመንግሥት አዳራሽ ውጪ ተሰብስቦ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አይዛያ አዳግቦና እና ባለቤቱ ኒሞታ