የጊልያድ የ104ኛው ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት አስደሳች ወቅት ነበር
“ይህ አስደሳች ቀን ነው። ሁላችንም ደስ ብሎናል።” የይሖዋ ምሥክሮች አስተዳደር አካል አባል የሆነው ኬሪ ባርበር መጋቢት 14, 1998 የተካሄደውን የጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት 104ኛ ክፍል የምረቃ ሥነ ሥርዓት የከፈተው በእነዚህ ቃላት ነበር። በአዳራሹ የነበሩት 4,945 ተሰብሳቢዎች የሥነ ሥርዓቱ መክፈቻ የሆነውንና “የደስታ መዝሙር” የሚል ጭብጥ ያለውን የመንግሥት መዝሙር ቁጥር 208 እንዲዘምሩ ተጋበዙ።
ደስተኛ ሆኖ ለመቀጠል የሚረዳ ተግባራዊ ምክር
በፕሮግራሙ መግቢያ ላይ በተከታታይ የቀረቡት አምስት አጫጭር ቅዱስ ጽሑፋዊ ንግግሮች በምረቃው ዕለት ሰፍኖ የታየውን የደስታ መንፈስ ጠብቆ ለማቆየት የሚረዱ አንዳንድ ተግባራዊ ምክሮችን ለግሰዋል።
የመጀመሪያውን ንግግር ያቀረበው በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ የሚሠራው ጆሴፍ ኢምስ ነበር። የንግግሩ ጭብጥ “ታማኝ የሆኑ ሰዎች የነበራቸውን መንፈስ ኮርጁ” የሚል ሲሆን 2 ሳሙኤል ምዕራፍ 15 እና 17 ላይ በሚገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ላይ የተመሠረተ ነበር። በዚህ ምዕራፍ ውስጥ የዳዊት ልጅ አቤሴሎም ዓመፅ በማነሳሳት አባቱ ከአምላክ የተቀበለውን መንግሥት ለመንጠቅ እንዳሤረ ተገልጿል። ይሁን እንጂ በይሖዋ ለተቀባው ለንጉሥ ዳዊት ታማኝነታቸውን ያሳዩ ሰዎችም ነበሩ። አዲሶቹ ሚስዮናውያን ከእነዚህ ታሪኮች ምን ትምህርት ይቀስማሉ? ወንድም ኢምስ ንግግሩን እንዲህ በማለት ደምድሟል:- “ሚስዮናዊ ሆናችሁ በየትኛውም ቦታ ብትመደቡ ታማኞች በመሆን ከቲኦክራሲያዊ ሥልጣን ጋር የመተባበርና እንዲህ ላለው ሥልጣን አክብሮት የማሳየት መንፈስ እንዲሰፍን ለማድረግ ጣሩ። ሌሎችም እንዲሁ እንዲያደርጉ እርዷቸው።”
ቀጣዩን ንግግር ያቀረበው ወንድም ዴቪድ ሲንክሌር ሲሆን በመዝሙር 15 ላይ የተገለጹትን ‘በይሖዋ ድንኳን’ በእንግድነት ለመቀመጥ የሚያስፈልጉ አሥር መሥፈርቶች ዘርዝሯል። “በሚስዮናዊ ድንኳናችሁ ውስጥ በእንግድነታችሁ ቀጥሉ” የሚል ጭብጥ ያለው ንግግሩ ተመራቂ ተማሪዎቹ እንግዶች ሆነው በሚቀመጡባቸው የሚስዮናዊ ምድቦቻቸው ይህን መዝሙር ተግባራዊ እንዲያደርጉ አበረታቷቸዋል። ወንድም ሲንክሌር በማንኛውም ጊዜ አምላካዊ የአቋም ደረጃዎችን ጠብቆ የመኖርን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። ይህስ ምን ውጤት ይኖረዋል? መዝሙር 15:5 እንደሚለው “እንዲህ የሚያደርግ ለዘላለም አይታወክም።”
ቀጥሎ የቀረበው ተናጋሪ የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ጆን ባር በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ መዘመር የሚያበረታታ መሆኑን ገልጿል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ በመዘመር ላይ ያለው ከሁሉ የሚበልጠው አስደሳች መዝሙር የትኛው ነው? ስለ መሲሐዊው የአምላክ መንግሥት የሚናገረው ምሥራች ነው። ይህ ሁሉ ዝማሬ ወይም ስለ አምላክ መንግሥት የሚናገረው ስብከት ምን ውጤት አስገኝቷል? የመዝሙር ቁጥር 208 ሁለተኛው ስንኝ ቅልብጭ ባለ አነጋገር እንደሚከተለው ሲል ያስቀምጠዋል:- “በመንግሥቱ ስብከት በክርስቲያን ትምህርት፣ ከይሖዋ ጎን ቆመዋል ብዞች። ይዘምራሉ የደስታ መዝሙር፣ ድምፃቸው ይሰማል በመላው ምድር!” አዎን፣ በየቀኑ 1,000 የሚያክሉ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በመጠመቅ ላይ ናቸው። ወንድም ባር “ወንድሞች፣ የውዳሴ መዝሙራችሁን ለመስማት የሚፈልጉ ሰዎች ወዳሉባቸው ክልሎች እንደምትላኩ ማወቃችሁ አያስደስታችሁም?” በማለት ንግግሩን ደምድሟል።
“ተሞክሮ ያላቸውን አዳምጡ” የሚል ርዕስ ያለውን ቀጣዩን ንግግር ያቀረበው በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል የሚሠራው ጄምስ ማንትስ ነበር። አንዳንድ ነገሮችን መማር የምንችለው ከግል ተሞክሯችን ብቻ እንደሆነ አመልክቷል። (ዕብራውያን 5:8) የሆኖ ሆኖ ምሳሌ 22:17 ‘ጆሮዎቻችንን አዘንብለን የጠቢባንን ወይም ተሞክሮ ያካበቱ ሰዎችን ቃላት እንድንሰማ’ ያበረታታናል። ተመራቂዎቹ ተማሪዎች ከእነሱ በፊት ከነበሩት ሚስዮናውያን ብዙ ነገር ሊማሩ ይችላሉ። “የቆዩት ሚስዮናውያን በአካባቢው ከሚገኙ ሱቆች ተከራክረው ዕቃ መግዛትን ያውቁበታል። በከተማው ውስጥ ለደህንነታቸውም ሆነ ለሥነ ምግባር ንጽሕናቸው አስጊ የሆኑት ቦታዎች የትኞቹ እንደሆኑ ያውቃሉ። የአገሬውን ሕዝብ ስሜት የሚጎዱ ነገሮች ምን እንደሆኑ ያውቃሉ። በሚስዮናዊነት ረዥም ጊዜ ያሳለፉት ወንድሞች በምድባችሁ ደስተኛና ስኬታማ እንድትሆኑ ምን ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ ያውቃሉ” ሲል ወንድም ማንትስ ተናግሯል።
የጊልያድ ትምህርት ቤት ሬጂስትራር የሆነው ዋላስ ሊቨረንስ “ቲኦክራሲያዊ ምድባችሁን አድንቁ” በሚል ጭብጥ በሰጠው ንግግር ላይ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስና በርናባስ ያሉ አንዳንድ ሚስዮናውያን የአገልግሎት ምድባቸውን ከአምላክ የተቀበሉት በመንፈስ ቅዱስ ወይም በአንዳንድ ተዓምራዊ መግለጫዎች አማካኝነት ነው። በጊልያድ የሰለጠኑ ሚስዮናውያን ግን በዓለም አቀፉ መስክ ውስጥ በአንድ ቦታ እንዲያገለግሉ የሚመደቡት በ“ታማኝና ልባም ባሪያ” መሆኑን ገልጿል። (ማቴዎስ 24:45-47) ሚስዮናውያኑ የተመደቡባቸውን ቦታዎች ጌዴዎን ምድያማውያንን ለመውጋት የተዘጋጁትን ወታደሮቹን ከመደበባቸው ቦታዎች ጋር አመሳስሏቸዋል። (መሳፍንት 7:16-21) “ቲኦክራሲያዊ የሚስዮናዊ ምድባችሁን አድንቁ። የጌዴዎን ወታደሮች ‘ሁሉም በየቦታቸው እንደቆሙ’ ሁሉ እናንተም የአገልግሎት ምድባችሁን ቦታችሁ አድርጋችሁ ተመልከቱት። ይሖዋ የጌዴዎንን ሦስት መቶ ወታደሮች እንደተጠቀመ ሁሉ በእናንተም እንደሚጠቀም እምነት ይኑራችሁ” ሲል ወንድም ሊቨረንስ አሳስቧል።
ሰዎችን በመርዳት ላይ ማተኮር ደስታ ያስገኛል
በአንድ ወቅት መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ፍላጎታችንንና ሕይወታችንን ቀጣይነታቸው በማያስተማምነው የዚህ ዓለም ምርቶችና የቅንጦት ዕቃዎች ላይ እንዲያተኩር ከማድረግ ይልቅ ሰዎችን በመርዳት ላይ ብናተኩርና ለሌሎች መልካም በማድረግ እውነተኛ ደስታ ማግኘትን ብንማር ምንኛ የተሻለና ጥበባዊ እርምጃ ይሆናል።” ከዚህ ጋር በመስማማት የጊልያድ ትምህርት ቤት አስተማሪ የሆነው ወንድም ማርክ ኑሜር ከአንድ የተማሪዎች ቡድን ጋር በመስክ አገልግሎት ስላጋጠሟቸው ተሞክሮዎች ከተወያየ በኋላ “ጥሩ ሚስዮናውያን የሚያደርጋችሁ በግል ለሌሎች አሳቢነት ማሳየታችሁ ነው” ብሏል።
በባሕር ማዶው መስክ ደስታ ለማግኘት የሚረዱ ቁልፍ ነገሮች
በሚስዮናዊነት ሥራ ስኬታማና ደስተኛ ለመሆን የሚረዱ አንዳንድ ቁልፍ ነገሮች ምንድን ናቸው? በአገልግሎት ክፍል የሚሠራው ወንድም ቻርለስ ዉዲ እንዲሁም ቀደም ሲል በላቲን አሜሪካ ሚስዮናዊ የነበረውና የትምህርት ኮሚቴ ረዳት ሆኖ የሚያገለግለው ሃረልድ ጃክሰን በቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዘጠነኛ ክፍል በመካፈል ላይ ከሚገኙ የተለያዩ የቅርንጫፍ ቢሮ ኮሚቴ አባላት ጋር ቃለ ምልልስ አድርገዋል። እነዚህ ወንድሞች ከለገሷቸው ምክሮች መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል:-
ከዛምቢያ የመጣው አልበርት ሙሶንዳ እንደሚከተለው ብሏል:- “አንድ ሚስዮናዊ በራሱ ተነሳስቶ ወንድሞችን ሰላም ሲል ጥሩ መንፈስ እንዲዳብር ያደርጋል። ምክንያቱም ወንድሞች ይቀርቡታል እርሱም ከወንድሞች ጋር ይቀራረባል።”
ከጓቲማላ የመጣው ሮላንዶ ሞራሌስ አዳዲስ ሚስዮናውያን በአካባቢው የሚዘጋጁ መጠጦችን እንዲጠጡ ወዳጃዊ በሆኑ ሰዎች ሲጋበዙ በደግነትና በዘዴ እንዲህ ብለው ሊመልሱ ይችላሉ ብሏል:- “ለዚህ አገር እንግዳ ነኝ። ብጠጣ ደስ ይለኝ ነበር። ይሁን እንጂ ሰውነቴ እንደናንተ ሰውነት ያለ ተፈጥሯዊ የመከላከያ ኃይል ገና አላዳበረም። ወደፊት ልጠጣው እንደምችል ተስፋ አደርጋለሁ። ያኔ ግብዣችሁን ለመቀበል ፈቃደኛ ነኝ።” ይህን የመሰለው ምላሽ ምን ጥቅም አለው? “ሰዎቹም አይቀየሙም፤ ሚስዮናውያኑም አሳቢነታቸውን የሚያሳዩበት አጋጣሚ ይሆናል።”
ሚስዮናውያኑ በአገልግሎት ምድባቸው እንዲጸኑ ሊረዳቸው የሚችለው ምንድን ነው? ከጊልያድ 79ኛ ክፍል የተመረቀውና ላለፉት 12 ዓመታት በላይቤርያ ሲያገለግል የቆየው ወንድም ፖል ክሩደስ የሚከተለውን ተናግሯል:- “ወላጆች ልጆቻቸውን እንደሚናፍቁ አውቃለሁ። ይሁን እንጂ ሚስዮናዊው ከተመደበበት አገር፣ አካባቢ፣ ባሕልና ሕዝብ ጋር ለመላመድ ጥረት እያደረገ ይሆናል። ምናልባትም ሚስዮናዊ ምድቡን ለቅቆ ለመሄድ እያቅማማ ይሆናል። በዚህ ላይ ‘በጣም ናፍቀንሃል። አንተ በሌለህበት ምን እንደምናደርግ አናውቅም’ የሚል ደብዳቤ ከቤተሰቡ ከደረሰው ጓዜን ጠቅልዬ ወደ አገሬ ልመለስ እንዲል ሊያደርገው ይችላል። ዛሬ በዚህ የተገኙ ዘመዶች ይህን ጉዳይ ማስታወሳቸው በጣም አስፈላጊ ነው።”
ከቃለ ምልልሶቹ በኋላ የፕሮግራሙን የመጨረሻ ንግግር ያቀረበው የአስተዳደር አካል አባል የሆነው ቴዎዶር ጃራዝ ነበር። ጭብጡ “በሕይወታችሁ ውስጥ ለመንግሥቱ ቀዳሚውን ቦታ ስጡት” የሚል ነበር። ሚስዮናውያኑ ሳይባክኑ በሥራቸው ላይ እንዳተኮሩ ሊቀጥሉ የሚችሉት እንዴት ነው? በሕይወታቸው ውስጥ ለመንግሥቱ ቀዳሚውን ቦታ መስጠታቸውን እንዲቀጥሉ ስለሚረዳቸው የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚያደርጉበት ፕሮግራም እንዲኖራቸው አበረታቷቸዋል። ከዚያም የሚከተለውን ወቅታዊ ማሳሰቢያ አቅርቧል:- “አንዳንድ ሚስዮናውያን በአዳዲስ የኤሌክትሮኒካዊ ነገሮች፣ በኤሌክትሮኒክስ መልእክት ልውውጥና በኮምፒዩተር ራሳቸውን ስለሚያስጠምዱ የግል ጥናታቸውን ችላ ብለዋል። ማንኛውንም መገልገያ በመጠቀም ረገድ ሚዛናዊ ልንሆን ይገባናል። የአምላክን ቃል እንዳናጠና እንቅፋት በሚሆንብን ነገር ላይ ከልክ ያለፈ ጊዜ ማጥፋት አይኖርብንም።”
ከወንድም ጃራዝ ንግግር በኋላ ለተመራቂዎቹ ዲፕሎማ የመስጠቱ ሥነ ሥርዓት ቀጠለ። ከዚያም የክፍሉ ተማሪዎች አድናቆታቸውን የገለጹበት ደብዳቤ ተነበበ። የክፍሉ ተወካይ የሁሉንም ስሜት በሚከተለው መንገድ ገልጾታል:- “ኢየሱስ ተከታዮቹ ተለይተው እንደሚታወቁበት የገለጸውን ፍቅር በጉልህ ተመልክተናል። ይህ ደግሞ የትም ብንሆን የት የሚደግፈን አፍቃሪና እንደ እናት የሚንከባከብ ድርጅት እንዳለ አረጋግጦልናል። እንዲህ ከመሰለው ድጋፍ ጋር እስከ ምድር ዳር ድረስ ለመሄድ ተዘጋጅተናል።” ለጊልያድ የ104ኛው ክፍል አስደሳች የምረቃ ቀን ይህ ስሜት ቀስቃሽ የሆነ መደምደሚያ ነበር።
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ስለ ተማሪዎቹ የቀረበ አኃዛዊ መረጃ
ሚስዮናውያኑ የተውጣጡባቸው አገሮች:- 9
የተመደቡባቸው አገሮች ብዛት:- 16
የተማሪዎቹ ብዛት:- 48
ባልና ሚስት የሆኑ:- 24
አማካይ ዕድሜ:- 33
በእውነት ውስጥ የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 16
በሙሉ ጊዜ አገልግሎት የቆዩባቸው ዓመታት በአማካይ:- 12
[በገጽ 25 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ከጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት የተመረቁ የ104ኛው ክፍል ተማሪዎች
ከዚህ በታች ባለው ዝርዝር ለእያንዳንዱ ረድፍ ተራ ቁጥር የተሰጠው ከፊት ወደ ኋላ ሲሆን ስሞቹ የሰፈሩት ከግራ ወደ ቀኝ ነው
(1) ሮሜሮ ኤም፣ ሆዋርዝ ጄ፣ ብላክበርን-ኬን ዲ፣ ሆሄንጋሰር ኢ፣ ዌስት ኤስ፣ ቶም ኤስ (2) ኮሎን ደብልዩ፣ ግላንሲ ጄ፣ ኮኖ ዋይ፣ ድሩስ ፒ፣ ታም ኤስ፣ ኮኖ ቲ፣ (3) ታም ዲ፣ ዜሽማይስተር ኤስ፣ ገርዴል ኤስ፣ ኤልዌል ጄ፣ ደኔክ ፒ፣ ቲበዶ ኤች (4) ቴይለር ኢ፣ ሂልድረድ ኤል፣ ሳንቼስ ኤም፣ አንደርሰን ሲ፣ በክኖር ቲ፣ ሆሄንጋሰር ኢ (5) ሆዋርዝ ዲ፣ ዋርድ ሲ፣ ሂንች ፒ፣ መክዶነልድ ዋይ፣ ሳንቼስ ቲ፣ ቶም ኦ (6) ድሩስ ቲ፣ ቲበዶ ኢ፣ ኤልዌል ዲ፣ ደኔክ ደብልዩ፣ ብላክበርን-ኬን ዲ፣ ዋርድ ደብልዩ (7) አንደርሰን ኤም፣ ዜሽማይስተር አር፣ መክዶነልድ አር፣ በክኖር አር፣ ግላንሲ ኤስ፣ ገርዴል ጂ (8) ሮሜሮ ዲ፣ ሂንች አር፣ ሂልድረድ ኤስ፣ ቴይለር ጄ፣ ኮሎን ኤ፣ ዌስት ደብልዩ
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የጊልያድን 104ኛ ክፍል በማስተማሩ ሥራ የተካፈሉ ወንድሞች:- (ከግራ ወደ ቀኝ) ደብልዩ ሊቨረንስ፣ ዩ ግላስ፣ ኬ አዳምስ፣ ኤም ኑሜር