ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው የቅዱስ አገልግሎት መብቶች
የቅዱስ አገልግሎት ሥራዎችን አቅልሎ መመልከት ተገቢ አይደለም። በጥንቷ ይሁዳ የነበሩ ካህናት በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ለተሰጧቸው የአገልግሎት መብቶች የግዴለሽነት ዝንባሌ ባሳዩ ጊዜ ይሖዋ በጥብቅ ወቅሷቸዋል። (ሚልክያስ 1:6-14) ከዚህም በተጨማሪ በእስራኤል የነበሩ አንዳንድ ሰዎች ናዝራውያን ከቅዱስ አገልግሎት ጋር በተያያዘ የተቀበሏቸውን ኃላፊነቶች አቅልለው እንዲመለከቱ ሲገፋፏቸው ይሖዋ እነዚህን ኃጢአተኛ እስራኤላውያን ገሥጿቸዋል። (አሞጽ 2:11-16) እውነተኛ ክርስቲያኖችም ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ፤ በቁም ነገርም ይመለከቱታል። (ሮሜ 12:1) ይህ ቅዱስ አገልግሎት አስፈላጊ የሆኑ በርካታ ዘርፎች አሉት።
ኢየሱስ ከተከታዮቹ ጋር ምድር ላይ በነበረበት ወቅት የአምላክ መንግሥት አዋጅ ነጋሪዎች እንዲሆኑ አሰልጥኗቸዋል። ከጊዜ በኋላ የሚያሰራጩት መልእክት በመላው ምድር ላይ ይዳረሳል። (ማቴዎስ 28:19, 20፤ ሥራ 1:8) ይህ የስብከት ሥራ በአሁኑ የነገሮች ሥርዓት የመጨረሻ ቀኖች ውስጥ ይበልጥ አጣዳፊ ሆኗል።
ሁሉም የይሖዋ ምሥክሮች በዚህ ሥራ ይሳተፋሉ። በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ አቅኚ ሆነው በሥራው መሳተፍ በመቻላቸው ደስታ አግኝተዋል። በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚካሄደው ሥራ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ለማከናወን ሲሉ በሺህዎች የሚቆጠሩ በቤቴል፣ በወረዳና በአውራጃ የበላይ ተመልካችነት ወይም በሚስዮናዊነት በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል ራሳቸውን አቅርበዋል። ይህን በመሰለው ልዩ አገልግሎት ለመቀጠል የሚፈልጉ ምን ማድረግ ሊጠይቅባቸው ይችላል?
ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ አጣዳፊ ጉዳዮች ሲከሰቱ
አንድ ሰው በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ከመጀመሩ በፊት አብዛኛውን ጊዜ በሕይወቱ ላይ አንዳንድ ማስተካከያዎች ማድረግ ይኖርበታል። ሁሉም ሰው ይህን ማድረግ ይችላል ማለት አይቻልም። አንድ ሰው አስቀድሞ የተሸከማቸው ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዳይካፈል ያግዱት ይሆናል። ሆኖም በልዩ አገልግሎት እየተካፈሉ ያሉ ወንድሞች ከቤተሰብ ጋር የተያያዙ አጣዳፊ ጉዳዮች ምናልባትም አረጋውያን ወላጆቻቸውን የሚመለከት ነገር ሲያጋጥማቸው ምን ማድረግ ይችላሉ? ቀጥሎ የቀረቡት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችና ምክሮች አስፈላጊውን መመሪያ ይሰጣሉ።
መላ ሕይወታችን ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና ላይ ማተኮር አለበት። (መክብብ 12:13፤ ማርቆስ 12:28-30) በአደራ የተሰጡንን ቅዱስ ነገሮች ከፍ አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። (ሉቃስ 1:74, 75፤ ዕብራውያን 12:16) በአንድ ወቅት ኢየሱስ ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገቡ ነገሮች ረገድ ማስተካከያ ማድረግ የነበረበትን አንድ ሰው የአምላክን መንግሥት በማወጁ ሥራ ሙሉ በሙሉ መጠመድ እንዳለበት ነግሮታል። ከሁኔታው ለመረዳት እንደሚቻለው ሰውየው ይህን ሥራ አባቱ እስከሚሞትበት ጊዜ ድረስ ለማቆየት አስቦ ነበር። (ሉቃስ 9:59, 60) በአንጻሩ ደግሞ ኢየሱስ ያለኝን ንብረት ሁሉ ለአምላክ ሰጥቻለሁ በሚል ሰበብ ‘ለአባቱና ለእናቱ ማንኛውንም ነገር ከማድረግ’ የሚታቀብ ሰው ትክክል እንዳልሆነ ተናግሯል። (ማርቆስ 7:9-13) ሐዋርያው ጳውሎስም አንድ ሰው ወላጆቹና አያቶቹን ጨምሮ ‘የእርሱ ለሆኑት ሰዎች’ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማሟላት ከባድ ኃላፊነት እንዳለበት ገልጿል።—1 ጢሞቴዎስ 5:3-8
ታዲያ እንዲህ ሲባል አጣዳፊ ጉዳዮች በሚከሰቱበት ጊዜ በልዩ አገልግሎት ውስጥ የሚገኙ አገልጋዮች ችግር ላይ የወደቁትን የቤተሰባቸው አባላት ለመንከባከብ ምድብ ሥራቸውን መተው አለባቸው ማለት ነውን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ በጉዳዩ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ በርካታ ነገሮችን ማየት ያስፈልጋል። ውሳኔው ለግለሰቡ የተተወ ነው። (ገላትያ 6:5) ብዙዎች ወላጆቻቸው ጋር ሆነው አስፈላጊውን ድጋፍ መስጠቱ የተሻለ ሆኖ ስለታያቸው ከፍ አድርገው የሚመለከቱትን ምድብ ሥራቸውን ለመተው ወስነዋል። ለምን? ጉዳዩ በጣም አንገብጋቢ ሆኖ ሊሆን ይችላል። ሊረዳቸው የሚችል ሌላ የቤተሰብ አባል ላይኖር ይችላል። ወይም ደግሞ በአካባቢው ያለው ጉባኤ አስፈላጊውን ነገር ማድረግ አልቻለ ይሆናል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ይህን የመሰለውን ድጋፍ እየሰጡም አቅኚ ሆነው መቀጠል ችለዋል። ሌሎች ደግሞ የተከሰተው አሳሳቢ ጉዳይ እልባት ካገኘ በኋላ እንደገና በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መካፈል ችለዋል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ የተከሰተውን ሁኔታ በሌሎች መንገዶች መያዝ ተችሏል።
የራሳቸውን ኃላፊነት መሸከም
በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ያሉ አንዳንዶች አጣዳፊ የሆኑ ጉዳዮች በሚከሰቱበት ጊዜ ምድብ ሥራቸውን ሳይተዉ ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት ችለዋል። ከብዙዎቹ ምሳሌዎች ውስጥ ጥቂቶቹን ተመልከት።
በዓለም አቀፉ የይሖዋ ምሥክሮች ዋና መሥሪያ ቤት ውስጥ በማገልገል ላይ ያሉ አንድ ባልና ሚስት ወረዳዎችንና አውራጃዎችን ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ በ1978 የቤቴል አገልግሎት ጀመሩ። ወንድም በቲኦክራሲያዊው ድርጅት ውስጥ ተመድቦ የሚሠራበት ቦታ ከፍተኛ ኃላፊነት የሚጠይቅ ነው። ሆኖም ወላጆቹ የሚረዳቸው ሰው ያስፈልግ ነበር። እነዚህ ቤቴላውያን ባልና ሚስት በየዓመቱ ሦስት ወይም አራት ጊዜ ወደ 3,500 ኪሎ ሜትር የሚጠጋ የደርሶ መልስ ጉዞ በማድረግ ወላጆቹን ይጠይቋቸዋል። የወላጆቹን ፍላጎት ለማሟላት በራሳቸው ወጪ ቤት የሠሩላቸው ሲሆን ድንገት በሚታመሙበት ጊዜም እነሱን ለማሳከም ወደዚያ ይጓዙ ነበር። ወደ 20 ለሚጠጉ ዓመታት የእረፍት ጊዜያቸውን በሙሉ የተጠቀሙበት ይህን ኃላፊነት ለመወጣት ነው ማለት ይቻላል። ወላጆቹን ከማፍቀራቸውና ከማክበራቸውም በተጨማሪ የቅዱስ አገልግሎት መብታቸውን ከፍ አድርገው ተመልክተውታል።
አንድ ሌላ ወንድም ደግሞ ለ36 ዓመታት በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ካገለገለ በኋላ እጅግ ፈታኝ ሁኔታ እንደገጠመው ተናግሯል። ይሖዋን በታማኝነት የሚያገለግሉት የ85 ዓመት አዛውንት የሆኑት አማቹ ሊረዳቸው ከሚችል ሰው ጋር መኖር ነበረባቸው። በዚህ ወቅት ከልጆቻቸው መካከል አብዛኞቹ እሳቸውን ማስጠጋት እንደማይችሉ ሆኖ ተሰምቷቸው ነበር። ከዘመዶቻቸው መካከል አንዱ ተጓዥ የበላይ ተመልካቹና ሚስቱ ለቤተሰቡ ሲሉ አገልግሎታቸውን አቋርጠው እናትየውን መንከባከብ እንዳለባቸው ለተጓዥ የበላይ ተመልካቹ ነገረው። ይሁን እንጂ እነዚህ ባልና ሚስት ውድ አገልግሎታቸውን አላቋረጡም፣ የእናትየውንም ችግር አቅልለው አልተመለከቱም። እናትየው ለሚቀጥሉት ዘጠኝ ዓመታት አብዛኛውን ጊዜ የኖሩት ከእነሱ ጋር ነው። መጀመሪያ ላይ በተንቀሳቃሽ ቤት ውስጥ ከዚያም ወረዳዎቹ በሚያዘጋጁላቸው የተለያዩ አፓርታማዎች ውስጥ ኖረዋል። በወቅቱ የአውራጃ የበላይ ተመልካች የነበረው ይህ ወንድም ምድብ ሥራውን ለማከናወን ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር ሚስቱ ከእናቷ ሳትለይ ፍቅራዊ እንክብካቤ ታደርግላቸው ነበር። በዚህ ሁኔታ ረጅም ጊዜ አሳልፈዋል። ባልየው በየሳምንቱ እሁድ እሁድ ስብሰባው እንዳበቃ ረጅም ጉዞ በማድረግ እነሱን ለመርዳት ተመልሶ ይመጣ ነበር። ስለሁኔታው ያውቁ የነበሩ ብዙዎች እነዚህ ባልና ሚስት እያከናወኑ ለነበሩት ሥራ ያላቸውን ጥልቅ አድናቆት አሳይተዋል። ከጊዜ በኋላ ሌሎች የቤተሰቡ አባሎችም ድጋፍ መስጠት እንደሚኖርባቸው ተሰማቸው። እነዚህ የራሳቸውን ጥቅም የሰዉ ባልና ሚስት ይህን ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መብት የሙጥኝ ብለው በመያዛቸው በሺህዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ ሕዝቦች እነሱ በሚያከናውኑት አገልግሎት መጠቀማቸውን ሊቀጥሉ ችለዋል።
ከቤተሰብ በሚገኝ ድጋፍ
አብዛኞቹ የቤተሰብ አባሎች ልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ያለውን ጠቀሜታ የሚገነዘቡ ከሆነ ከእነሱ መካከል ቢያንስ አንዳንዶቹ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሳተፍ እንዲችሉ ትብብር ያደርጋሉ።
ይህን የመሰለው የቤተሰብ ትብብር በምዕራብ አፍሪካ በሚስዮናዊነት የሚያገለግሉትን ካናዳውያን ባልና ሚስት ረድቷቸዋል። ምንም ዓይነት ችግር አይፈጠርም የሚል አጉል ተስፋ በመያዝ ድንገተኛ ነገር እስኪከሰት ድረስ ቁጭ ብለው አልጠበቁም። ከአገራቸው ውጪ ለሚያከናውኑት አገልግሎት ስልጠና ለማግኘት ወደ ጊልያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከመሄዳቸው በፊት ባልየው እናታቸው ከታመሙ ወይም የአካል ጉዳተኛ ከሆኑ ማን ሊንከባከባቸው እንደሚችል ከታናሽ ወንድሙ ጋር ተወያየ። ታናሽ ወንድምየው ለእናታቸው ባለው ፍቅር በመገፋፋት እንዲሁም የሚስዮናዊነት ሥራ ያለውን ዋጋማነት በመገንዘብ “እኔ ቤተሰብና ልጆች ስላሉኝ ራቅ ያለ ቦታ ሄጄ አንተ የምትሠራውን ሥራ ለመሥራት ሁኔታዎቼ አይፈቅዱልኝም። ስለዚህ እናታችን አንድ ነገር ቢገጥማት እኔ እንከባከባታለሁ” አለው።
ደቡብ አሜሪካ ውስጥ በሚስዮናዊነት የሚያገለግሉ አንድ ባልና ሚስት የሚስትየዋ ቤተሰቦች በዕድሜ የገፉትን እናቷን በመጦር ባሳዩት የትብብር መንፈስ በእጅጉ ተጠቅመዋል። ከእህቶችዋ መካከል አንዷ ከባልዋ ጋር በመሆን፣ እሷ ራሷ ቀሳፊ በሆነ በሽታ እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ እናትየውን ይንከባከቡ ነበር። ከዚያ በኋላስ? ባልየው ጉዳዩ ፈጽሞ እንዳያስጨንቃቸው በማሰብ እንዲህ ሲል ጻፈላቸው:- “እኔና ልጆቼ በሕይወት እስካለን ድረስ የሚስዮናዊነት አገልግሎታችሁን ማቆም አያስፈልጋችሁም።” ከዚህም በተጨማሪ ታናሽ እህቷና ባሏ እናትየውን ለመርዳት ሲሉ ቤታቸውን ቀይረው እሳቸው ወደሚኖሩበት አካባቢ በመምጣት እስከሞቱበት ቀን ድረስ ስለተንከባከቧቸው ተጨማሪ የቤተሰብ ድጋፍ አግኝተዋል። እንዴት ያለ ግሩም የትብብር መንፈስ ነው! የሚስዮናዊነት አገልግሎቱን ለመደገፍ ሁሉም አስተዋጽኦ አበርክተዋል።
ለይሖዋ በነፃ የሚሰጡ ወላጆች
ብዙውን ጊዜ ወላጆች ለቅዱስ አገልግሎት ከፍተኛ አድናቆት እንዳላቸው ያሳያሉ። ይሖዋን ለማክበር ከሚችሉባቸው ውድ ንብረቶቻቸው መካከል ልጆቻቸው ይገኙበታል። (ምሳሌ 3:9) ብዙ ክርስቲያን ወላጆች ልጆቻቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲካፈሉ ያበረታቱዋቸዋል። አንዳንዶቹ ልጅዋን ሳሙኤልን “ለዘላለም” ማለትም “ዕድሜውን ሁሉ” ይሖዋን እንዲያገለግል እንደሰጠችው እንደ ሐና ዓይነት ስሜት ይሰማቸዋል።—1 ሳሙኤል 1:22, 28
እንዲህ ዓይነት ስሜት ያላት አንዲት እናት በአፍሪካ ለምትገኘው ልጅዋ እንዲህ ስትል ጽፋላታለች:- “ላገኘሽው ግሩም መብት ይሖዋን እናመሰግነዋለን። የልባችንን ምኞት አድርሰሽልናል።” በሌላ ጊዜ ደግሞ እንዲህ ስትል ጽፋላታለች:- “እርግጥ ተራርቆ መኖር የሚጠይቀውን መሥዋዕትነት ለመክፈል ተገደናል፤ ሆኖም ይሖዋ እንዴት እየተንከባከበሽ እንዳለ ማየቱ በጣም የሚያስደስት ነው!”
በኢኳዶር የሚገኝ አንድ ሚስዮናዊ ለአረጋውያን ወላጆቹ አስፈላጊውን እንክብካቤ በማድረግ በኩል ተፈጥረው የነበሩትን ሁኔታዎች ከገለጸ በኋላ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አባቴ እኛን በመጥቀስ ያቀርባቸው የነበሩት ጸሎቶች እኔና ባለቤቴን በጣም እንደጠቀሙን ይሰማኛል። እሱ ከሞተ በኋላ እናቴ ‘አባትህ ሁለታችሁም በምድብ ሥራችሁ መቀጠል እንድትችሉ በየዕለቱ ወደ ይሖዋ ይጸልይ ነበር’ ብላ ነግራናለች።”
በዩ ኤስ ኤ፣ ካሊፎርኒያ የሚኖሩ አንድ አረጋውያን ባልና ሚስት ከወንዶች ልጆቻቸው አንዱ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት በመካፈሉ በጣም ተደስተዋል። እናትየው በሞቱበት ወቅት ልጅየውና ባለቤቱ በስፔይን ነበሩ። ሌሎቹ የቤተሰቡ አባላት አባትየውን ለመንከባከብ አንዳንድ ዝግጅቶች መደረግ እንደሚኖርባቸው ተሰማቸው። ይሁን እንጂ ሰብዓዊ ሥራ ስለሚበዛባቸውና የሚያሳድጓቸውም ልጆች ስላሉዋቸው ይህን ኃላፊነት መወጣት እንደማይችሉ ሆኖ ተሰማቸው። ስለዚህ በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ ያሉትን ባልና ሚስት ወደ አገራቸው ተመልሰው አባትየውን እንዲንከባከቡ በጥብቅ አሳሰቧቸው። ምንም እንኳ አባትየው የ79 ዓመት አዛውንት የነበሩ ቢሆንም ጥሩ ጤንነትና የጠራ መንፈሳዊ አመለካከት ነበራቸው። በአንድ የቤተሰብ ስብሰባ ላይ አብዛኞቹ ሐሳባቸውን ተናግረው ከጨረሱ በኋላ አባትየው በተራቸው ተነሱና “ወደ ስፔይን ተመልሰው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ እፈልጋለሁ” በማለት አስረግጠው ተናገሩ። እነዚህ ባልና ሚስት ተመልሰው ወደ ስፔይን የሄዱ ሲሆን አባትየውንም ተጨባጭ በሆኑ መንገዶች ረድተዋቸዋል። በአሁኑ ጊዜ ስፔይን ውስጥ በወረዳ የበላይ ተመልካችነት ሥራ እያገለገሉ ነው። ይህ የቤተሰብ ስብሰባ ከተደረገ በኋላ ሌሎች የቤተሰቡ አባላት እነዚህ ባልና ሚስት ከአገራቸው ውጪ እያከናወኑ ላሉት አገልግሎት አድናቆት አሳይተዋል። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ከወንዶች ልጆቹ መካከል አንደኛው አባትየው ከእሱ ጋር እንዲኖሩ በማድረግ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ ጦሯቸዋል።
በዩ ኤስ ኤ፣ ፔንሲልቬንያ የሚኖሩ ለ40 ዓመታት ያህል በአቅኚነት ያገለገሉ አንድ ቅቡዕ ወንድም ባለቤታቸው በጠና ታመው ሲሞቱ ከ90 ዓመት በላይ ሆኗቸው ነበር። አንድ ወንድ ልጅና ሦስት ሴቶች ልጆች የነበሯቸው ከመሆኑም በላይ በርካታ መንፈሳዊ ልጆችም ነበሯቸው። ከሴቶች ልጆቻቸው አንዷ ከባለቤቷ ጋር በሚስዮናዊነት፣ በተጓዥ የበላይ ተመልካችነት ሥራና በቤቴል በማገልገል በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ከ40 ዓመታት በላይ አሳልፋለች። አባቷ ጥሩ እንክብካቤ ማግኘት የሚችሉባቸውን አንዳንድ ዝግጅቶች በማድረግ አስተዋጽኦ አበረከተች። በአካባቢው ያሉ ወንድሞችም እሳቸውን ለስብሰባ ወደ መንግሥት አዳራሹ በማመላለስ በኩል እርዳታ አደረጉ። ከጊዜ በኋላ ባሏ ሲሞት እሳቸውን ለመንከባከብ የቤቴል አገልግሎቷን አቋርጣ እንድትመጣ ይፈልጉ እንደሆነ አባቷን ጠየቀቻቸው። አባትየው ቅዱስ ነገሮችን ከፍ አድርገው ከመመልከታቸውም በላይ የሚያስፈልጓቸው ነገሮች በሌሎች መንገዶች ሊሟሉላቸው እንደሚችሉ ስለተሰማቸው እንዲህ የሚል መልስ ሰጧት:- “ይህን ማድረግ በጣም እንደሚከብድሽ ምንም ጥርጥር የለውም፤ እኔም ብሆን ይህን እንድታደርጊ ፈጽሞ አልፈቅድልሽም።”
ድጋፍ የሚሰጡ ጉባኤዎች
አንዳንድ ጉባኤዎች በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እየተካፈሉ ያሉ ወንድሞችን ለመርዳት ብለው በዕድሜ የገፉ ወላጆችን በመንከባከብ ረገድ ከፍተኛ ትብብር ያደርጋሉ። በተለይ ደግሞ በዚህ አገልግሎት በርካታ ዓመታት ያሳለፉትን ወንድሞች ያደንቃሉ። ምንም እንኳ ከቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶቻቸው ሙሉ በሙሉ ነፃ ሊያደርጓቸው ባይችሉም፣ ሸክማቸውን በማቅለል ልጆቹ የተመደቡበትን ልዩ የአገልግሎት መስክ ለመተው እንዳይገደዱ በእጅጉ ሊረዷቸው ይችላሉ።
ከጀርመን የሄዱ አንድ ባልና ሚስት ውጭ አገር ተመድበው በአመዛኙ ጉባኤዎችን በመጎብኘት ወደ 17 ዓመት አካባቢ ካገለገሉ በኋላ አረጋዊ እናቱ ያለባቸው ችግር እየተባባሰ ሄደ። የእረፍት ጊዜያቸውን በየዓመቱ እናትየውን ለመርዳት ተጠቀሙበት። በአቅራቢያው ያሉ ምሥክሮችም ፍቅራዊ ድጋፍ ሰጥተዋል። ከዚያም እናትየው አሳሳቢ ሁኔታ ላይ በነበሩበት በአንድ ወቅት በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ላይ የነበሩት እነዚህ ባልና ሚስት አብረዋቸው ነበሩ። በዚህ ጊዜ የጉባኤው ሽማግሌዎች ከእነሱ ጋር ለመገናኘት ዝግጅት አደረጉ። ሽማግሌዎቹ እነዚህ ባልና ሚስት ለእናትየው ያልተቋረጠ ድጋፍ መስጠታቸውን አሳምረው ያውቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ ባልና ሚስቱ እያከናወኑ ያሉት ልዩ አገልግሎት ያለውን ጠቀሜታ ይገነዘባሉ። ስለዚህ ሽማግሌዎቹ እናትየው እንክብካቤ የሚያገኙበትን ፕሮግራም ካዘጋጁ በኋላ ባልና ሚስቱን እንዲህ በማለት አነጋገሯቸው:- “አሁን እያደረጋችሁት ካለው በበለጠ እሳቸውን ለመርዳት አቅማችሁ አይፈቅድም። በተመደባችሁበት ቦታ በስፔይን ሥራችሁን መቀጠል እንድትችሉ እኛ እንረዳችኋለን።” እነዚህ ሽማግሌዎች ላለፉት ሰባት ዓመታት ይህን እርዳታ ሲያበረክቱ ቆይተዋል።
በተመሳሳይ ሁኔታ ከ1967 ጀምሮ በሴኔጋል በማገልገል ላይ ያለ አንድ ወንድም አባቱ ያሉበት ጉባኤ ከፍተኛ ፍቅራዊ ድጋፍ አድርጎለታል። አፍቃሪ የሆነችው ሚስቱ አሳሳቢ ሁኔታ በተፈጠረበት ወቅት ባለቤቷ ለብቻው ወደ ዩናይትድ ስቴትስ ሄዶ ወላጆቹን እንዲረዳ በፈቃደኝነት ተባብራዋለች። ለበርካታ ወራት እዚያው መቆየት ግድ ሆነበት። ሁኔታው አስቸጋሪ ነበር፤ ሆኖም አቅሙ የሚፈቅድለትን ያህል ካደረገ በኋላ በሚስዮናዊነት አገልግሎቱ መቀጠል እንዲችል በዚያ ያለው ጉባኤ በጉዳዩ ጣልቃ በመግባት ድጋፍ ሰጠው። ጉባኤው ለ18 ዓመታት ያህል መጀመሪያ ለአባትየው (ምንም እንኳ አሁን የብዙዎቹን ማንነት መለየት ባይችሉም) ከዚያም ለእናትየው በተለያዩ መንገዶች ፍቅራዊ እርዳታ አድርገውላቸዋል። ይህ ዝግጅት ልጁን ከኃላፊነት ነፃ አድርጎታልን? በጭራሽ፤ ብዙውን ጊዜ ከሴኔጋል ድረስ እየመጣ የእረፍት ጊዜውን እነርሱን ለመርዳት ይጠቀምበት ነበር። ሆኖም ጉባኤው ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ወንድሞች እነዚህ ትጉ ባልና ሚስት በሴኔጋል ውስጥ በልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት እንዲቀጥሉ ለማስቻል የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በማበርከታቸው ተደስተዋል።
ኢየሱስ ለምሥራቹ ሲሉ ሁሉን ነገር የተዉ ሰዎች መቶ እጥፍ ወንድሞች፣ እህቶች፣ እናቶችና ልጆች እንደሚያገኙ ተናግሯል። (ማርቆስ 10:29, 30) ይህ ቃል በቃል በይሖዋ አገልጋዮች ላይ ተፈጽሟል። በምዕራብ አፍሪካ በምትገኘው በቤኒን የሚያገለግሉ አንድ ባልና ሚስት ወላጆቻቸው በሚገኙበት ጉባኤ ውስጥ ያሉ ሁለት ምሥክሮች ስለ ወላጆቻቸው መጨነቅ እንደሌለባቸው በነገሯቸው ጊዜ ኢየሱስ የተናገረው ቃል በራሳቸው ላይ ልዩ በሆነ መንገድ ሲፈጸም ተመልክተዋል። “የእናንተ ወላጆች የእኛም ወላጆች ናቸው” ብለዋቸዋል።
አዎን፣ የቅዱስ አገልግሎት መብቶችን ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ይህን ይበልጥ በተሟላ መልኩ ማድረግ የምትችልባቸው መንገዶች ይኖሩ ይሆን?
[በገጽ 26 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
ራሳቸውን ለልዩ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት አቅርበዋል