የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 10/15 ገጽ 4-7
  • መጽሐፍ ቅዱስን ልታምንበት ትችላለህ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መጽሐፍ ቅዱስን ልታምንበት ትችላለህ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • መጽሐፍ ቅዱስ ወይስ ወግ?
  • የቅዱሳን ጽሑፎች አስፈላጊነት
  • በመጽሐፍ ቅዱስ መመራት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
  • በትንሣኤ ላይ ያለህ እምነት ምን ያህል ጠንካራ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • በመለወጥ ላይ ያለው “የክርስትና እምነት” ገጽታ—በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አለውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 10/15 ገጽ 4-7

መጽሐፍ ቅዱስን ልታምንበት ትችላለህ?

በዚህ ዘመናዊ ዓለምም እንኳ መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ይታመንበታል። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ጋለፕ በሚባለው ጥናት አማካኝነት ከአሜሪካውያን የተሰበሰበ የሕዝብ አስተያየት እንዳመለከተው 80 በመቶ የሚሆኑት መጽሐፍ ቅዱስ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈ የአምላክ ቃል መሆኑን እንደሚያምኑ ገልጸዋል። በአካባቢህ ያለው አኃዝ ከዚህ ይብዛም ይነስም ይህ እምነት ያላቸው ሰዎች በቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስን እንማራለን ብለው እንደሚጠብቁ መረዳት አያዳግትህም። ይሁን እንጂ አብዛኛውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስን አይማሩም። ለምሳሌ ያህል ከሞት በኋላ ነፍስ ትቀጣለች የሚለውን መሠረተ ትምህርት ተመልከት።

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለ መንጽሔ ወይም ስለ እሳታማ ሲኦል የሚገልጽ ትምህርት ይገኛልን? ዛሬ በሕዝበ ክርስትና ውስጥ ያሉ ብዙ ሃይማኖታዊ ምሁራን አይገኝም የሚል መልስ ይሰጣሉ። ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ እንዲህ በማለት ይገልጻል:- “መንጽሔን በተመለከተ ካቶሊክ የምትከተለው መሠረተ ትምህርት በቅዱስ ጽሑፍ ላይ ሳይሆን በወግ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ ውሎ አድሮ ታውቋል።” ኤ ዲክሽነሪ ኦቭ ክርስቲያን ቲኦሎጂ ሲኦልን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “አዲስ ኪዳን ውስጥ እሳታማ ሲኦል የቀድሞው ክርስትና ትምህርት አንዱ ክፍል ሆኖ አናገኘውም።”

እንዲያውም የእንግሊዝ ቤተ ክርስቲያን የመሠረተ ትምህርት አርቃቂ ኮሚቴ የእሳታማ ሲኦል ትምህርትን ፈጽሞ ለመሻር ሐሳብ ማቅረቡን በቅርቡ ይፋ አድርጎ ነበር። የሊችፊልድ ካቴድራል ዲን የሆኑት ክቡር ዶክተር ቶም ራይት ቀድሞ የነበረው ምናባዊ ሲኦል “አምላክን የለየለት ጭራቅ አድርጎ ከማቅረቡም በላይ በብዙዎች ላይ የማይሽር የአእምሮ ጠባሳ ትቶባቸዋል” ሲሉ ገልጸዋል። ሲኖዶሱ ባቀረበው ሪፖርት ላይ ሲኦልን “ፈጽሞ የሌለ ነገር” ሲል ገልጾታል።a በተመሳሳይም ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ ካቶሊክ ያላትን አመለካከት እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ዛሬ ያለው መንፈሳዊ ትምህርት ሲኦልን በተመለከተ ያለውን አስተሳሰብ ከአምላክ እንደሚያራርቅ አድርጎ ይቆጥረዋል።”

እንደ እውነቱ ከሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ነፍስ የሚያስተምረው ከመንጽሔም ሆነ ከእሳታማ ሲኦል ትምህርት ጋር ይቃረናል። መጽሐፍ ቅዱስ ነፍስ ሟች መሆኗን ደጋግሞ ይናገራል። “ኃጢአት የምትሠራ ነፍስ እርስዋ ትሞታለች።” (ሕዝቅኤል 18:​4) መጽሐፍ ቅዱስ በሚገልጸው መሠረት ሙታን ጨርሶ ስለማይሰሙ ስለማይለሙ ሊሰቃዩ አይችሉም። “ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም።” (መክብብ 9:​5) መጽሐፍ ቅዱስ ሙታን ወደፊት ትንሣኤ እንደሚያገኙ ተስፋ ይሰጣል። የኢየሱስ ወዳጅ የሆነው አልዓዛር በሞተበት ጊዜ ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ ጋር አመሳስሎታል። የአልዓዛር እህት ማርታ መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ተስፋ እንዲህ በማለት ገልጻለች:- “በመጨረሻው ቀን በትንሣኤ እንዲነሣ አውቃለሁ።” ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት በማስነሳት ይህን ተስፋ ለሰው ልጆች አረጋግጧል።​—⁠ዮሐንስ 5:​28, 29፤ 11:​11–14, 24, 44

የታሪክ ምሁራን ሰው ተለይታው የምትሄድ የማትሞት ነፍስ አለችው የሚለው ትምህርት ከመጽሐፍ ቅዱስ ሳይሆን ከግሪካውያን ፍልስፍና የመነጨ መሆኑን ይገልጻሉ። የጥንት ዕብራውያን ሰው የሥጋዊ አካልና የማትጨበጥ ነፍስ ውኅደት ነው ብለው አለማመናቸውን ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ ጠቅሷል። የዕብራውያኑን እምነት በተመለከተ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “አምላክ ከአፈር ያበጀው የመጀመሪያው ሰው ውስጥ የሕይወት እስትንፋስ ሲገባ ሰውየው ‘ሕያው ፍጡር’ ሆነ። (ዘፍጥረት 2.​7) የግሪካውያን ፍልስፍና እንደሚለው ሞት በሰው ውስጥ ያሉ የሁለት የተለያዩ ነገሮች መነጣጠል ተደርጎ አይታይም ነበር። የሕይወት እስትንፋሱ ሲወጣ ሰው ‘የሞተ ፍጡር’ ይሆናል። (ዘሌዋውያን 21.​11፤ ዘኁልቁ 6.​6፤ 19.​13) በሁለቱም አገባቦች ‘ፍጡር’ የሚለው ቃል አብዛኛውን ጊዜ ‘ነፍስ’ ተብሎ የተተረጎመው [ነፈሽ] የሚለው የዕብራይስጥ ቃል መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከሰውዬውም ጋር አንድ እንደሆነ ተገልጿል።”

ይኸው ኢንሳይክለፒዲያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የካቶሊክ ምሁራን “አዲስ ኪዳን የነፍስን አለመሞት በሔለናውያን [በግሪካውያን] መንፈስ አያስተምርም የሚል አመለካከት ይዘዋል” ሲል ገልጿል። “የችግሩ መሠረታዊ መፍትሔ ያለው በፍልስፍና ግምታዊ አስተሳሰብ ላይ ሳይሆን ከሰው ችሎታ በላይ በሆነው የትንሣኤ ስጦታ ላይ ነው” በማለት ደምድሟል።

መጽሐፍ ቅዱስ ወይስ ወግ?

ሆኖም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆኑ አስተሳሰቦች የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ክፍል ሊሆኑ የቻሉት እንዴት ነው? ብዙ አብያተ ክርስቲያናት መጽሐፍ ቅዱስ ዋነኛው መመሪያቸው መሆኑን ይናገራሉ። ለምሳሌ ያህል በቅርቡ ሊቃነ ጳጳሳት ዮሐንስ ጳውሎስ ዳግማዊ ቅዱሳን ጽሑፎች “ሙሉ በሙሉ እውነትና የእምነታችን ዋነኛ መመዘኛ ተደርገው በካቶሊኮች ዘንድ ተቀባይነት ማግኘት” እንደሚያስፈልጋቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ያለው የሕዝበ ክርስትና ትምህርት ከመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ትምህርት ጋር ተመሳሳይ አለመሆኑ በሰፊው የታወቀ ነው። አብዛኞቹ አብያተ ክርስቲያናት የተደረጉትን ለውጦች የቤተ ክርስቲያን መሠረተ ትምህርቶች ቀስ በቀስ ያደረጉት መሻሻል ክፍል አድርገው ይቆጥሩታል። ከዚህም በላይ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ የቤተ ክርስቲያን ወግ ከቅዱሳን ጽሑፎች የማይተናነስ ተቀባይነት አለው የሚል አቋም አላት። ኒው ካተሊክ ኢንሳክለፒዲያ ቤተ ክርስቲያኒቷ “የቤተ ክርስቲያን ወጎችን ገሸሽ አድርጋ አንድን መሠረተ ትምህርት በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ ብቻ ተመሥርታ አትቀበልም ወይም ቅዱሳን ጽሑፎችን ገሸሽ አድርጋ ማንኛውንም መሠረተ ትምህርት በወግ ላይ ብቻ ተመሥርታ አትቀበልም” ሲል ገልጿል።

ባለፉት የታሪክ ዘመናት አብያተ ክርስቲያናት ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርቶችን በወግ ላይ ብቻ በተመሠረቱ ትምህርቶች ተክተዋል። እንዲያውም ባሁኑ ጊዜ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ስህተት ናቸው ብለው ያምናሉ። ለምሳሌ ያህል ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ “አብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርቶች በዘመናዊ የሳይንስና የታሪክ እውቀት መለኪያ ሲመዘኑ እውነት ሆነው እንደማይገኙ ግልጽ ነው” ሲል ተናግሯል። ሙታን ምንም እንደማያውቁ ስለሚገልጸው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ሲናገር “ብሉይ ኪዳን ሃይማኖታዊ በሆኑ ጉዳዮች እንኳ ሳይቀር . . . ከሞት በኋላ ስላለ ሕይወት የተሟላ እውቀት አለመያዙን ያሳያል” ሲል አክሏል። ኢንሳይክለፒዲያው ለዚህ ማስረጃ በማድረግ “በሞት የሚያስብህ የለምና፣ በሲኦልም [ወይም በሔድስም] የሚያመሰግንህ ማን ነው?” የሚለውን መዝሙር 6:​5ን (በአንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሶች ቁጥር 6) ይጠቅሳል። አንዳንድ የፕሮቴስታንት መንፈሳዊ ትምህርት ቤቶችና ኮሌጆች መጽሐፍ ቅዱስ አይሳሳትም ብለው ማስተማራቸውን ትተዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መጽሐፍ ቅዱስ የያዘውን ትምህርት ለመተርጎም የሚያስችል የማስተማር ሥልጣን እንዳላት ታምናለች። ይሁን እንጂ ‘እነዚህ ትርጉሞች ከቅዱሳን ጽሑፎች ጋር ቢቃረኑስ?’ ብለህ ትጠይቅ ይሆናል።

የቅዱሳን ጽሑፎች አስፈላጊነት

ኢየሱስ ቅዱሳን ጽሑፎችን እንደ ባለሥልጣን አድርጎ ደጋግሞ ጠቅሷል። አብዛኛውን ጊዜ የተናገራቸውን ነገሮች “ተብሎ ተጽፎአል” በማለት ደምድሟል። (ማቴዎስ 4:​4, 7, 10፤ ሉቃስ 19:​46) በእርግጥም ኢየሱስ ስለ ጋብቻ ጉዳይ ጠቅሶ የተናገረው ከዘፍጥረት መጽሐፍ የፍጥረት ታሪክ እንጂ በግምት ላይ ከተመሠረተው የግሪካውያን ፍልስፍና አልነበረም። (ዘፍጥረት 1:​27፤ 2:​24፤ ማቴዎስ 19:​3–9) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ ቅዱሳን ጽሑፎች በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፉና እውነትን ያዘሉ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። ለአምላክ ባቀረበው ጸሎት ላይ “ቃልህ እውነት ነው” ብሎ ተናግሯል።​—⁠ዮሐንስ 17:​17b

ኢየሱስ በዘመኑ በነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ላይ የሰነዘረውን ወቀሳ መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቅሳል። “ወጋችሁን ትጠብቁ ዘንድ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ እጅግ ንቃችኋል። . . . ባስተላለፋችሁትም ወግ የእግዚአብሔርን ቃል ትሽራላችሁ።” (ማርቆስ 7:​6-13) በተመሳሳይ መንገድ ሐዋርያው ጳውሎስ የግሪካውያን ፍልስፍናንም ሆነ የተሳሳቱ ወጎችን ትምህርቶቹ ውስጥ እንዲያካትት የደረሰበትን ግፊት ተቋቁሟል። “እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” ሲል አስጠንቅቋል። (ቆላስይስ 2:​8፤ 1 ቆሮንቶስ 1:​22, 23፤ 2:​1–13) ጳውሎስ ክርስቲያኖች እንዲከተሏቸው ያሳሰባቸው አንዳንድ ወጎች ወይም ትምህርቶች ነበሩ። ሆኖም እነዚህ ወጎች በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የተመሠረቱና ከእነሱ ጋር ሙሉ በሙሉ የሚስማሙ ናቸው። (2 ተሰሎንቄ 2:​13–15) ጳውሎስ ‘የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ . . . ጠቃሚ ነው’ ሲል ጽፏል።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​16, 17፣ በሰያፍ የጻፍነው እኛ ነን።

ጳውሎስ ሰዎች ከቅዱሳን ጽሑፎች ፈቀቅ እንደሚሉ አስቀድሞ ተገንዝቧል። ጢሞቴዎስን “ሰዎች ንጹሑን ቃል ለመስማት የማይፈልጉበት ጊዜ ይመጣል፤ . . . እውነትን መስማት ትተው ተረትን መስማት ይወዳሉ” ሲል ካስጠነቀቀው በኋላ “አንተ ግን በሁሉ ነገር ራስን ተቆጣጠር” በማለት አጥብቆ መክሮታል። (2 ጢሞቴዎስ 4:​3-5 የ1980 ትርጉም) ሆኖም ይህን ማድረግ የሚቻለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ “ልበ ሰፊ” በመሆን ነው። አንድ የግሪክኛ መዝገበ ቃላት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል “ለመማርና አንድን ነገር ባልተዛባ መንገድ ለመመዘን ፈቃደኛ መሆን” ሲል ይፈታዋል። ሉቃስ ይህን ቃል የተጠቀመው በመጀመሪያው መቶ ዘመን ጳውሎስን ያዳምጡ ስለነበሩት የቤርያ ሰዎች ሲገልጽ ነው። የጳውሎስ ትምህርት ለእነሱ እንግዳ ከመሆኑም በላይ በተሳሳተ አቅጣጫ መሄድ አልፈለጉም። ሉቃስ እነሱን አመስግኖ ሲጽፍ “እነዚህም በተሰሎንቄ ከሚኖሩት ይልቅ ልበ ሰፊዎች ነበሩና:- ነገሩ እንደዚሁ ይሆንን? ብለው ዕለት ዕለት መጻሕፍትን እየመረመሩ ቃሉን በሙሉ ፈቃድ ተቀበሉ” ብሏል። የቤርያ ሰዎች ልበ ሰፊዎች መሆናቸው ማንኛውንም ነገር አምነው ለመቀበል ፍላጎት የሌላቸው ተጠራጣሪዎች አላደረጋቸውም። ከዚህ ይልቅ ‘ጥቂት ያይደሉ ማመናቸው’ በቅን ልቦና የተደረገ ምርምር ያስገኘው ውጤት ነው።​—⁠ሥራ 17:​11, 12

በመጽሐፍ ቅዱስ መመራት የሚያስገኛቸው ጥቅሞች

የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች መጽሐፍ ቅዱስን በጥብቅ በመከተላቸውና የራስን ጥቅም መሥዋዕት በሚያደርገው ፍቅራቸው ይታወቁ ነበር። ይሁን እንጂ ዛሬ ያሉት አብዛኞቹ ሰዎች ‘የአምልኮት መልክ ያላቸው ኃይሉን ግን የካዱ ናቸው።’ (2 ጢሞቴዎስ 3:​5) በዛሬው ጊዜ ያለ ከቀድሞው ክርስትና ጋር የማይስማማ ማንኛውም ዓይነት ክርስትና በሰዎች ሕይወት ላይ በጎ ተጽእኖ የሚያሳድር እውነተኛ ግፊት ሊኖረው አይችልም። በአብዛኛው የሕዝበ ክርስትና ክፍል ውስጥ እየጨመረ የሚሄድ ዓመፅ፣ ብልግና፣ የቤተሰብ መፈራረስና ፍቅረ ነዋይ የምናየው በዚህ ምክንያት ይሆን? በአንዳንድ “ክርስቲያን” አገሮች ተመሳሳይ ሃይማኖት በሚከተሉ ሰዎች መካከል እንኳ ሳይቀር አሰቃቂ የጎሳ ጦርነቶች ይካሄዳሉ።

የቤርያ ሰዎች የነበራቸው የልበ ሰፊነት መንፈስ ጠፍቷል? በዛሬው ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚያምኑና በሕይወታቸው የሚመሩበትን ሰዎች ብቻ ያቀፈ ቡድን ይገኛል?

ኢንሳይክለፒዲያ ካናዲያና እንዲህ ይላል:- “የይሖዋ ምሥክሮች ሥራ በአንደኛውና በሁለተኛው መቶ ዘመን ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ይከተሉት የነበረው የጥንቱ ክርስትና ማንሰራራትና ዳግም መቋቋም ውጤት ነው።” ኒው ካተሊክ ኢንሳይክለፒዲያ ስለ ምሥክሮቹ ሲናገር “መጽሐፍ ቅዱስን የእምነታቸው ብቸኛ ምንጭና የሕይወታቸው መመሪያ አድርገው ይመለከቱታል” ብሏል።

የይሖዋ ምሥክሮች በዓለም ዙሪያ በመንፈሳዊ ብልጽግናቸው፣ ሰላማቸውና ደስታቸው እንዲታወቁ ያስቻላቸው ዓብይ ምክንያት ይህ መሆኑ አያጠራጥርም። ይህም በመሆኑ አንባቢዎቻችን የመጽሐፍ ቅዱስን ጤናማ መንፈሳዊ ትምህርቶች ይበልጥ እንዲማሩ እናበረታታቸዋለን። ሰፊ እውቀት ማግኘት በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከፍተኛ ትምክህትና በአምላክ ላይ ጠንካራ እምነት ወደ ማሳደር ሊያመራ ይችላል። ይህ ዓይነቱ እምነት የሚያስገኛቸው ዘላለማዊ በረከቶች ቢደከምላቸው የሚያስቆጩ አይደሉም።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ናሽናል ፐብሊክ ራዲዮ​—⁠“ሞርኒንግ ኤዲሽን”

b መጽሐፍ ቅዱስ እምነት የሚጣልበት ስለመሆኑ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ለሰው ሁሉ የሚሆን መጽሐፍ የተባለውን ብሮሹር አንብብ።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ሐዋርያው ጳውሎስም ሆነ ሌሎች በገበያ ቦታ ሰብከዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የይሖዋ ምሥክሮች “መጽሐፍ ቅዱስን የእምነታቸው ብቸኛ ምንጭና የሕይወታቸው መመሪያ አድርገው ይመለከቱታል”

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ