ኢየሩሳሌም —‘ለደስታችሁ ምክንያት ከሚሆኑት ነገሮች ሁሉ በላይ’ ናትን?
“ምላሴ በጉሮሮዬ ይጣበቅ፤ ከደስታዬ ሁሉ በላይ ኢየሩሳሌምን ባልወድድ።”—መዝሙር 137:6
1. በርካታ የአይሁድ ግዞተኞች በአምላክ ስለ ተመረጠችው ከተማ ምን አመለካከት ነበራቸው?
የመጀመሪያዎቹ አይሁዳውያን ግዞተኞች በ537 ከዘአበ ወደ ኢየሩሳሌም ከተመለሱ ወደ ሰባት የሚጠጉ አሥርተ ዓመታት አልፈዋል። የአምላክ ቤተ መቅደስ ተመልሶ ቢገነባም ከተማዋ ግን አሁንም እንደ ፈራረሰች ናት። ይህ በእንዲህ እንዳለ በዚያው በግዞት አንድ አዲስ ትውልድ አደገ። ብዙዎቹ እንደሚከተለው ብሎ ከዘመረው መዝሙራዊ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ስሜት እንደተሰማቸው ምንም አያጠራጥርም:- “ኢየሩሳሌም ሆይ፣ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ።” (መዝሙር 137:5) አንዳንዶች ኢየሩሳሌምን እንዲሁ ከማስታወስ የበለጠ ነገር አድርገዋል፤ ‘ለደስታቸው ምክንያት ከሚሆኑት ነገሮች ሁሉ በላይ መሆኗን’ በተግባራቸው አሳይተዋል።—መዝሙር 137:6
2. ዕዝራ ማን ነበር? የተባረከውስ እንዴት ነበር?
2 ለምሳሌ ያህል ካህኑን ዕዝራን ተመልከቱ። ወደ አገሩ ከመመለሱ በፊት እንኳ በኢየሩሳሌም የሚከናወነውን ንጹሕ አምልኮ ለመደገፍ ሲል በቅንዓት ሠርቷል። (ዕዝራ 7:6, 10) ዕዝራ ይህን በማድረጉ በእጅጉ ተባርኳል። ዕዝራ ሁለተኛ የግዞተኞች ቡድን በመምራት ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ መብት እንዲሰጠው ይሖዋ አምላክ የፋርሱን ንጉሥ ልብ አነሳስቷል። ከዚህም በላይ ንጉሡ ‘ለእግዚአብሔር ቤት ማሳመሪያ’ ከፍተኛ መጠን ያለው ወርቅና ብር ሰጥቷቸዋል።—ዕዝራ 7:21–27
3. ነህምያ ከምንም ነገር በላይ የሚያሳስበው የኢየሩሳሌም ጉዳይ መሆኑን ያሳየው እንዴት ነው?
3 ወደ አሥራ ሁለት ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ወሳኝ እርምጃ የወሰደ ነህምያ የሚባል አንድ ሌላ አይሁዳዊ ነበር። ሱሳ በሚገኘው የፋርስ ቤተ መንግሥት ውስጥ ያገለግል ነበር። ለንጉሥ አርጤክስስ የወይን ጠጅ አሳላፊ የመሆን ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ሲሆን ይህ ግን ለነህምያ ‘ደስታ ዋነኛ ምክንያት’ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ነህምያ ወደ ኢየሩሳሌም የሚሄድበትንና መልሶ የሚገነባበትን ጊዜ ይናፍቅ ነበር። ነህምያ ስለዚህ ጉዳይ ለወራት ሲጸልይ ነበር፤ እንዲህ በማድረጉ ይሖዋ አምላክም ባርኮታል። የፋርሱ ንጉሥ ነህምያ ያሳሰበውን ነገር በተረዳ ጊዜ ወታደራዊ ኃይልና ኢየሩሳሌምን መልሶ ለመገንባት ፈቃድ ያለው መሆኑን የሚገልጹ ደብዳቤዎች ሰጠው።—ነህምያ 1:1—2:9
4. የይሖዋ አምልኮ ሊያስደስተን ከሚችል ከማንኛውም ነገር የሚበልጥ መሆኑን እንዴት ልናሳይ እንችላለን?
4 ዕዝራ፣ ነህምያና ከእነሱ ጋር የተባበሩ ብዙ አይሁዳውያን ኢየሩሳሌምን ማዕከል ያደረገው የይሖዋ አምልኮ ከማንኛውም ነገር በላይ አስፈላጊ መሆኑን፣ ‘የደስታቸው ዋነኛ ምክንያት’ ማለትም ሊደሰቱበት ከሚችሉበት ከማንኛውም ነገር የሚበልጥ መሆኑን ያለ ምንም ጥርጥር አረጋግጠዋል። እነዚህን የመሳሰሉ ግለሰቦች ይሖዋን፣ አምልኮውንና በመንፈስ የሚመራ ድርጅቱን በተመሳሳይ መንገድ ለሚመለከቱ በዛሬው ጊዜ ለሚገኙ ሁሉ እንዴት ያሉ ማበረታቻዎች ናቸው! አንተስ እንዲህ ይሰማሃል? በአምላካዊ ሥራዎች በመጽናት ለደስታህ ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች ሁሉ የሚበልጠው ራሳቸውን ለይሖዋ ከወሰኑ ሰዎች ጋር በመሆን እሱን የማገልገል መብት ማግኘት መሆኑን ታሳያለህን? (2 ጴጥሮስ 3:11) በዚህ ረገድ ተጨማሪ ማበረታቻ ለማግኘት ዕዝራ ወደ ኢየሩሳሌም ያደረገው ጉዞ ያስገኘውን መልካም ውጤት እንመልከት።
በረከቶችና ኃላፊነቶች
5. የይሁዳ ነዋሪዎች በዕዝራ ዘመን ምን የተትረፈረፉ በረከቶች አግኝተው ነበር?
5 በዕዝራ ሥር የነበሩት ወደ 6,000 የሚጠጉ ከግዞት የሚመለሱ ሰዎች ለይሖዋ ቤተ መቅደስ የሚሆን የወርቅና የብር መዋጮዎችን አምጥተዋል። እነዚህ መዋጮዎች በአሁኑ የዋጋ ተመን ወደ 35 ሚልዮን ዶላር ይጠጋሉ። ይህ ደግሞ የመጀመሪያዎቹ ግዞተኞች ይዘው ከተመለሱት ወርቅና ብር ወደ ሰባት እጥፍ ገደማ ይበልጥ ነበር። የኢየሩሳሌምና የይሁዳ ነዋሪዎች ይህን ሁሉ የሰውና የቁሳቁስ ድጋፍ በማግኘታቸው ይሖዋን ምንኛ አመስግነውት ይሆን! ሆኖም ከአምላክ የሚገኙ የተትረፈረፉ በረከቶች ኃላፊነትም ያስከትላሉ።—ሉቃስ 12:48
6. ዕዝራ አገሩ በደረሰ ጊዜ ምን ነገር ተመለከተ? እንዴትስ ተሰማው?
6 ብዙም ሳይቆይ ዕዝራ አንዳንድ ካህናትንና ሽማግሌዎችን ጨምሮ ብዙ አይሁዳውያን አረማዊ ሚስቶችን በማግባት የአምላክን ሕግ መተላለፋቸውን ተመለከተ። (ዘዳግም 7:3, 4) የአምላክ ሕግ ቃል ኪዳን በመጣሱ ምክንያት ማዘኑ የተገባ ነበር። “ይህንም ነገር በሰማሁ ጊዜ ልብሴንና መጎናጸፊያዬን ቀደድሁ፣ . . . ደንግጬም ተቀመጥሁ።” (ዕዝራ 9:3) ከዚያም የተጨነቁት እስራኤላውያን በተገኙበት ዕዝራ ከልቡ ወደ ይሖዋ ጸለየ። ሁሉም እየሰሙ ዕዝራ እስራኤላውያን ባለፉት ጊዜያት የሠሯቸውን በደሎችና አምላክ የምድሪቱን አረማዊ ነዋሪዎች ካገቡ ምን እንደሚደርስባቸው የሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ ከለሰ። እንዲህ ሲል ደመደመ:- “አቤቱ የእስራኤል አምላክ ሆይ፣ አንተ ጻድቅ ነህ፤ ዛሬም እንደ ሆነው እኛ አምልጠን ቀርተናል፤ እነሆ በፊትህ በበደላችን አለን፤ ስለዚህ በፊትህ ሊቆም የሚችል ማንም የለም።”—ዕዝራ 9:14, 15
7. (ሀ) ዕዝራ መጥፎ ድርጊትን በተመለከተ የወሰደው እርምጃ ግሩም ምሳሌ የሚሆነው እንዴት ነው? (ለ) በዕዝራ ዘመን የነበሩ ጥፋተኞች እንዴት ያለ ምላሽ ሰጡ?
7 ዕዝራ “እኛ” የሚለውን መግለጫ ተጠቅሟል። አዎን፣ ምንም እንኳ እሱ በግል ጥፋተኛ ባይሆንም ራሱን ጨምሮ ተናግሯል። ዕዝራ የተሰማው ጥልቅ ሐዘንና ያቀረበው ልባዊ ጸሎት የሕዝቡን ልብ በመንካቱ ለንስሐ የሚገቡ ሥራዎችን እንዲሠሩ አነሳስቷቸዋል። ምንም እንኳ ለእነሱ ቀላል ባይሆንም የአምላክን ሕግ የጣሱ በሙሉ ከባዕድ አገር ያመጧቸውን ሚስቶቻቸውን ከወለዱላቸው ልጆቻቸው ጋር ወደ አገራቸው መልሰው በመስደድ የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ተስማሙ። ዕዝራ ይህን የመፍትሔ ሐሳብ የተቀበለው ሲሆን ጥፋተኞቹም ባሉት መሠረት እርምጃ እንዲወስዱ አበረታታቸው። ዕዝራ ከፋርስ ንጉሥ ባገኘው ሥልጣን አማካኝነት ሕግ ተላላፊዎችን በሙሉ የመግደል አሊያም ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ የማባረር መብት ነበረው። (ዕዝራ 7:12, 26) ይሁን እንጂ እንዲህ ያለውን እርምጃ መውሰድ ያስፈለገው አይመስልም። “ጉባኤውም ሁሉ” እንዲህ አለ:- “እንደ ተናገርኸን እናደርግ ዘንድ ይገባናል።” ከዚህም በላይ “በዚህም ነገር እጅግ በድለናልና” ሲሉ ተናዘዙ። (ዕዝራ 10:11–13) ዕዝራ ምዕራፍ 10 የባዕድ አገር ሚስቶቻቸውንና የወለዱላቸውን ልጆች በመላክ ውሳኔውን ተግባራዊ ያደረጉትን የ111 ወንዶች ስም ይዘረዝራል።
8. የባዕድ አገር ሚስቶችን ወዲያው የማሰናበት እርምጃ መወሰዱ ለመላው የሰው ዘር ጠቃሚ የሆነው በምን መንገድ ነው?
8 ይህ እርምጃ ለእስራኤላውያን ብቻ ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር ጭምር ጠቃሚ ነበር። ጉዳዩን ለማስተካከል ምንም እርምጃ ባይወሰድ ኖሮ እስራኤላውያን በዙሪያቸው ካሉ ብሔራት ጋር ይቀላቀሉ ነበር። ይህ ደግሞ የሰው ልጆችን ለመባረክ ተስፋ የተሰጠበት ዘር መገኛ መስመር እንዲበረዝ ያደርግ ነበር። (ዘፍጥረት 3:15፤ 22:18) ተስፋ የተሰጠበት ዘር ከይሁዳ ነገድ የመጣ የንጉሥ ዳዊት ዝርያ መሆኑን መለየት አስቸጋሪ ይሆን ነበር። አሥራ ሁለት ከሚሆኑ ዓመታት በኋላ ይህ አሳሳቢ ጉዳይ እንደገና ትኩረት ተሰጥቶት “የእስራኤልም ዘር ከእንግዶች ሁሉ ራሳቸውን ለዩ።”—ነህምያ 9:1, 2፤ 10:29, 30
9. መጽሐፍ ቅዱስ የማያምን የትዳር ጓደኛ ላላቸው ክርስቲያኖች ምን ጥሩ ምክር ይሰጣል?
9 በዚህ ዘመን የሚገኙት የይሖዋ አገልጋዮች ከዚህ ታሪክ ምን ሊማሩ ይችላሉ? እርግጥ ክርስቲያኖች በሕጉ ቃል ኪዳን ሥር አይደሉም። (2 ቆሮንቶስ 3:14) ከዚህ ይልቅ “የክርስቶስን ሕግ” ይታዘዛሉ። (ገላትያ 6:2) ስለዚህ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያለው ክርስቲያን ከሚከተለው የጳውሎስ ምክር ጋር ይስማማል:- “ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ፣ አይተዋት።” (1 ቆሮንቶስ 7:12) ከዚህም በላይ የማያምን የትዳር ጓደኛ ያላቸው ክርስቲያኖች ጋብቻቸው የሰመረ እንዲሆን ጠንክሮ የመሥራት ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታ አለባቸው። (1 ጴጥሮስ 3:1, 2) ይህን ግሩም ምክር መታዘዙ አብዛኛውን ጊዜ የማያምኑ የትዳር ጓደኞች ልባቸውን ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲያዘነብሉ አድርጓቸዋል። እንዲያውም አንዳንዶች የተጠመቁ ታማኝ ምሥክሮች ሆነዋል።—1 ቆሮንቶስ 7:16
10. ከባዕድ አገር ያገቧቸውን ሚስቶቻቸውን ወደ አገራቸው መልሰው ካሰናበቱት 111 እስራኤላውያን ወንዶች ክርስቲያኖች ምን ትምህርት ሊቀስሙ ይችላሉ?
10 ሆኖም ባዕድ ሚስቶቻቸውን ያሰናበቱት እስራኤላውያን ጉዳይ ለነጠላ ክርስቲያኖች በጣም ጥሩ ትምህርት ይሰጣል። ከማያምኑ ሰዎች ጋር ለጋብቻ መጠናናት መጀመር የለባቸውም። እንዲህ ካለው ግንኙነት መራቅ አዳጋች አልፎ ተርፎም የሚያሰቃይ ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም የአምላክን በረከት በቀጣይነት ለማግኘት የሚፈልግ ሰው ሊወስደው የሚገባ ከሁሉ የተሻለ እርምጃ ነው። ክርስቲያኖች “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ” ተብለው ታዝዘዋል። (2 ቆሮንቶስ 6:14) ማግባት የሚፈልግ ማንኛውም ነጠላ ክርስቲያን እውነተኛ የእምነት ጓደኛውን የማግባት እቅድ ሊኖረው ይገባል።—1 ቆሮንቶስ 7:39
11. እንደ እስራኤላውያን ወንዶች ለደስታችን ምክንያት በሚሆነው ነገር ረገድ ልንፈተን የምንችለው እንዴት ነው?
11 በሌሎች ብዙ መንገዶች ጭምር ክርስቲያኖች ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆነ አቅጣጫ እየተጓዙ እንዳሉ ሲነገራቸው ማስተካከያዎችን አድርገዋል። (ገላትያ 6:1) ይህ መጽሔት አንድ ሰው የአምላክ ድርጅት አባል ሆኖ እንዳይቀጥል የሚያደርጉት ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆኑ ድርጊቶች ምን እንደሆኑ የሚገልጽ ትምህርት በየጊዜው ሲያወጣ ቆይቷል። ለምሳሌ ያህል በ1973 የይሖዋ ሕዝቦች አደገኛ ዕፆችን መውሰድና ትምባሆ ማጨስ ከባድ ኃጢአቶች መሆናቸውን ተገነዘቡ። አምላካዊ አካሄድን ለመከተል “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ሁሉ ራሳችንን” ማንጻት አለብን። (2 ቆሮንቶስ 7:1) ብዙዎች ይህን ምክር በመቀበል እርምጃ ወስደዋል፤ ከአምላክ ንጹሕ ሕዝቦች ጋር ለመቆየት ሲሉ ከእነዚህ ነገሮች መላቀቅ የሚያስከትልባቸውን ሥቃይ ለመቀበል ፈቃደኞች ሆነዋል። በተጨማሪም የፆታ ጉዳዮችን፣ አለባበስን፣ አጋጌጥን እንዲሁም ዓለማዊ ሥራን፣ መዝናኛንና ሙዚቃን በጥበብ መምረጥን የሚመለከቱ ግልጽ የሆኑ ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያዎች ተሰጥተዋል። ማንኛውም ቅዱስ ጽሑፋዊ መመሪያ ሲሰጠን 111ዱ እስራኤላውያን ወንዶች እንዳደረጉት “ለመስተካከል” ዝግጁ መሆናችንን እናሳይ። (2 ቆሮንቶስ 13:11 NW) እንዲህ ማድረጋችን ይሖዋን ከቅዱስ ሕዝቡ ጋር በኅብረት ሆኖ የማምለክ መብት ማግኘታችን ‘ለደስታ ምክንያት ከሚሆነን ነገር ሁሉ የሚበልጥ’ መሆኑን ያሳያል።
12. በ455 ከዘአበ ምን ነገር ተከናወነ?
12 መጽሐፍ ቅዱስ ከባዕድ አገር ስለመጡ ሚስቶች የሚናገረውን ታሪክ ከተረከ በኋላ በሚቀጥሉት 12 ዓመታት ውስጥ በኢየሩሳሌም ስለተከናወነው ነገር ምንም አይነግረንም። ብዙ የጋብቻ ውሎች መፍረሳቸው የእስራኤላውያን ጎረቤቶች ለእስራኤላውያን የነበራቸው ጠላትነት ይበልጥ እንዳባባሰው አያጠራጥርም። በ455 ከዘአበ ነህምያ በወታደር ታጅቦ ኢየሩሳሌም ደረሰ። የይሁዳ ገዥ እንዲሆን ተሹሞ የነበረ ሲሆን ከተማዋን እንደገና ለመገንባት ከፋርስ ንጉሥ ሥልጣን ማግኘቱን የሚገልጹ ደብዳቤዎች አምጥቷል።—ነህምያ 2:9, 10፤ 5:14
ምቀኛ ከነበሩ ጎረቤቶቻቸው የደረሰባቸው ተቃውሞ
13. የሐሰት ሃይማኖት የሚከተሉ የአይሁዳውያን ጎረቤቶች ምን ዝንባሌ አሳይተዋል? ነህምያስ ምን እርምጃ ወሰደ?
13 የሐሰት ሃይማኖት ተከታይ የሆኑ ጎረቤቶች ነህምያ የመጣበትን ዓላማ ተቃወሙ። መሪዎቻቸው እንዲህ ብለው በመጠየቅ አስፈራሩት:- “በውኑ በንጉሡ ላይ ትሸፍቱ ዘንድ ትወድዳላችሁን?” ነህምያም በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለው በማሳየት እንዲህ ሲል መለሰ:- “የሰማይ አምላክ ያከናውንልናል፣ እኛም ባሪያዎቹ ተነሥተን እንሠራለን፤ እናንተ ግን በኢየሩሳሌም እድል ፈንታና መብት መታሰቢያም የላችሁም።” (ነህምያ 2:19, 20) የቅጥሩ እድሳት በተጀመረ ጊዜ እነዚያው ጠላቶች እንዲህ ሲሉ አሾፉ:- ‘እነዚህ ደካሞች አይሁድ የሚሠሩት ምንድን ነው? ድንጋዩን ከፍርስራሹ መልሰው ያድኑታልን? በድንጋይ በሚሠሩት ቅጥራቸው ላይ ቀበሮ ቢመጣበት ያፈርሰዋል።’ ለእነዚህ አስተያየቶች መልስ ከመስጠት ይልቅ ነህምያ እንዲህ ሲል ጸለየ:- “አምላካችን ሆይ፣ ተንቀናልና ስማ፤ ስድባቸውን በራሳቸው ላይ መልስባቸው።” (ነህምያ 4:2–4) ነህምያ ምንጊዜም በይሖዋ ላይ በመታመን ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል!—ነህምያ 6:14፤ 13:14
14, 15. (ሀ) ነህምያ ለጠላት የዓመፅ ዛቻ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች ጠንካራ ተቃውሞ እያለም መንፈሳዊ የግንባታ ሥራቸውን ለመቀጠል የቻሉት እንዴት ነው?
14 በዛሬው ጊዜም የይሖዋ ምሥክሮች አስፈላጊውን የስብከት ተልዕኳቸውን ለመፈጸም በአምላክ ይታመናሉ። ተቃዋሚዎች በማሾፍ ይህን ሥራ ለማሰናከል ይሞክራሉ። አንዳንድ ጊዜ ለመንግሥቱ መልእክት ፍላጎት ያሳዩ ግለሰቦች የሚደርስባቸውን ፌዝ መቋቋም ስለማይችሉ ይሸነፋሉ። ተቃዋሚዎች ፌዛቸው ምንም ተጽእኖ ሳያሳድር ከቀረ ሊናደዱና የኃይል እርምጃ ለመውሰድ ሊዝቱ ይችላሉ። የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች ይገነቡ በነበሩ ሰዎች ላይ የደረሰው ይኸው ነበር። ሆኖም ነህምያ ጨርሶ በፍርሃት አልተዋጠም። ከዚያ ይልቅ ሠራተኞቹ ከጠላት የሚመጣባቸውን ጥቃት ለመመከት የሚያስችላቸውን መሣሪያ አስታጠቃቸውና እንዲህ በማለት እምነታቸውን አጠነከረላቸው:- “አትፍሩአቸው፤ ታላቁንና የተፈራውን ጌታ አስቡ፣ ስለ ወንድሞቻችሁም ስለ ወንዶችና ስለ ሴቶች ልጆቻችሁም ስለ ሚስቶቻችሁም ስለ ቤቶቻችሁም ተዋጉ።”—ነህምያ 4:13, 14
15 በነህምያ ዘመን እንደሆነው ሁሉ የይሖዋ ምሥክሮች ጠንካራ ተቃውሞ ቢኖርም መንፈሳዊ የግንባታ ሥራቸውን በማከናወን ለመቀጠል እንዲችሉ በሚገባ ታጥቀዋል። “ታማኝና ልባም ባሪያ” እገዳ ባለባቸው ቦታዎች እንኳን ሳይቀር የአምላክ ሕዝቦች ፍሬያማ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን እምነት የሚያጠነክር መንፈሳዊ ምግብ ሲያቀርብ ቆይቷል። (ማቴዎስ 24:45) በዚህም ምክንያት ይሖዋ በምድር ዙሪያ ጭማሪ እንዲያገኙ በማድረግ ሕዝቦቹን መባረኩን ቀጥሏል።—ኢሳይያስ 60:22
የውስጥ ችግሮች
16. የኢየሩሳሌምን ቅጥር የሚገነቡ ሰዎችን መንፈስ የሚያዳክሙ ምን የውስጥ ችግሮች ነበሩ?
16 የኢየሩሳሌምን ቅጥር የመገንባቱ ሥራ እየተፋጠነና የቅጥሩ ቁመት እያደገ ሲሄድ ሥራው ይበልጥ አስቸጋሪ እየሆነ መጣ። ቅጥሩን ለመገንባት ደፋ ቀና ይሉ የነበሩትን ሰዎች መንፈስ የሚያዳክም ችግር ብቅ ያለው በዚህ ጊዜ ነበር። የምግብ እጥረት በመከሰቱ ምክንያት አንዳንድ አይሁዶች ለቤተሰቦቻቸው ምግብ ማቅረብና ለፋርሱ ንጉሥ ቀረጥ መክፈል ተስኗቸው ነበር። ባለጠጋ የነበሩ አይሁዳውያን ምግብና ገንዘብ አበደሯቸው። ይሁን እንጂ ከአምላክ ሕግ ጋር በሚጻረር ሁኔታ ድሃ የነበሩት እስራኤላውያን የተበደሩትን ገንዘብ እስከነወለዱ እስኪከፍሉ ድረስ መሬታቸውንና ልጆቻቸውን በመያዣነት ሰጥተው ነበር። (ዘጸአት 22:25፤ ዘሌዋውያን 25:35–37፤ ነህምያ 4:6, 10፤ 5:1–5) አሁን እነዚህ አበዳሪዎቻቸው መሬታቸውን ለመውሰድና ልጆቻቸውን ባሪያዎች አድርገው እንዲሸጡላቸው በማስገደድ እያስፈራሯቸው ነበር። ነህምያ በዚህ ፍቅር በጎደለው የፍቅረ ንዋይ ዝንባሌ በጣም ተናደደ። የኢየሩሳሌምን ቅጥር መልሶ የመገንባቱን ሥራ ይሖዋ መባረኩን እንዲቀጥል ሲል ፈጣን እርምጃ ወስዷል።
17. ይሖዋ የግንባታ ሥራውን መባረኩን እንዲቀጥል ነህምያ ምን አደረገ? ከምንስ ውጤት ጋር?
17 ‘ትልቅ ጉባኤ’ ተዘጋጀና ነህምያ ባለጠጋ የነበሩት እስራኤላውያን የሠሩት ሥራ ይሖዋን እንዳላስደሰተው በግልጽ አስረዳቸው። ከዚያም አንዳንድ ካህናትን ጨምሮ ጥፋተኛ ለነበሩት ሰዎች፣ የወሰዱትን ወለድ እንዲሁም ወለድ የመክፈል አቅም ከሌላቸው ላይ በሕገ ወጥ መንገድ የወሰዱትን መሬት እንዲመልሱ ጠየቀ። ጥፋተኞቹ በሚያስመሰግን ሁኔታ እንዲህ አሉ:- “እንመልስላቸዋለን፣ ከእነርሱም ምንም አንሻም እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን።” እነዚህ እንዲሁ ለይምሰል ብቻ የተነገሩ ቃላት አልነበሩም፤ መጽሐፍ ቅዱስ “ሕዝቡም እንደዚህ ነገር [እንደ ነህምያ ቃል] አደረጉ” በማለት ይናገራል። እንዲሁም መላው ጉባኤ ይሖዋን አወደሰ።—ነህምያ 5:7–13
18. የይሖዋ ምሥክሮች በየትኛው ባህርያቸው የታወቁ ሆነዋል?
18 ስለ ዘመናችንስ ምን ለማለት ይቻላል? የይሖዋ ምሥክሮች በበዝባዥነታቸው ሳይሆን ለእምነት አጋሮቻቸውና በችግር ላይ ለወደቁ ለሌሎች ሰዎች ጭምር በሚሰጡት ልግስና በሰፊው ይታወቃሉ። ይህ፣ በነህምያ ዘመን እንደሆነው ሁሉ ይሖዋ በእጅጉ እንዲወደስ አድርጓል። ያም ሆኖ ግን “ታማኝና ልባም ባሪያ” ንግድ ነክ የሆኑ ጉዳዮችንና ሌሎችን በስግብግብነት ከመበዝበዝ የመቆጠብ አስፈላጊነትን አስመልክቶ ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር መስጠት አስፈላጊ ሆኖ አግኝቶታል። በአንዳንድ አገሮች በጣም ውድ የሆነ ጥሎሽ መጠየቅ የተለመደ ቢሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ስስታሞችና ነጣቂዎች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ በግልጽ ያስጠነቅቃል። (1 ቆሮንቶስ 6:9, 10) አብዛኞቹ ክርስቲያኖች እንዲህ ላለው ምክር የሰጡት መልካም ምላሽ ድሃ ወንድሞቻቸውን መበዝበዝ ኃጢአት መሆኑን የተገነዘቡትን አይሁዶች የሚያስታውስ ነው።
የኢየሩሳሌም ቅጥር ተጠናቀቀ
19, 20. (ሀ) የኢየሩሳሌም ቅጥር ተገንብቶ ማለቁ በሃይማኖታዊ ተቃዋሚዎች ላይ ምን ስሜት ፈጠረ? (ለ) የይሖዋ ምሥክሮች በብዙ አገሮች ምን ድል ተቀዳጅተዋል?
19 ያ ሁሉ ተቃውሞ ቢኖርም የኢየሩሳሌም ቅጥር በ52 ቀናት ውስጥ ተሠርቶ ተጠናቀቀ። ይህ በተቃዋሚዎቹ ላይ ምን ስሜት ፈጠረ? ነህምያ እንዲህ ብሏል:- “ጠላቶቻችንም ሁሉ ይህን በሰሙ ጊዜ በዙሪያችን የነበሩ አሕዛብ ሁሉ ፈሩ፣ በራሳቸውም አሳብ እጅግ ተዋረዱ፣ ይህም ሥራ በእግዚአብሔር እንደ ተደረገ አወቁ።”—ነህምያ 6:16
20 ዛሬ ጠላት በአምላክ ሥራ ላይ የሚያመጣው ተቃውሞ በተለያዩ መንገዶችና ቦታዎች ቀጥሏል። ይሁን እንጂ በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የይሖዋ ምሥክሮችን መቃወም ከንቱ መሆኑን ተገንዝበዋል። ለምሳሌ ያህል በናዚ ጀርመን፣ በምሥራቅ አውሮፓና በብዙ የአፍሪካ አገሮች የሚከናወነውን የስብከት ሥራ ለማስቆም የተደረጉ ሙከራዎችን ተመልከቱ። እነዚህ ሙከራዎች በሙሉ ከሽፈዋል፤ እንዲሁም በአሁኑ ጊዜ ብዙ ሰዎች ‘ሥራችን በአምላክ እየተደረገ እንዳለ’ አምነው ተቀብለዋል። በእነዚህ አገሮች የነበሩ ለብዙ ጊዜያት በታማኝነት ያገለገሉ ሁሉ የይሖዋ አምልኮ ‘ለደስታቸው ምክንያት ከሚሆኑ ነገሮች በላይ’ እንዲሆን በማድረጋቸው በእጅጉ ተክሰዋል!
21. በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ የጎላ ትርጉም ያላቸው የትኞቹን ነገሮች እንመረምራለን?
21 በሚቀጥለው ርዕሰ ትምህርት ላይ መልሶ የተገነባው የኢየሩሳሌም ቅጥር ለመመረቅ ወደ ተደረገው አስደሳች በዓል የመሩ አስፈላጊ ክንውኖችን እንከልሳለን። በተጨማሪም ለመላው የሰው ልጅ ጥቅም ሲባል ከዚያ ይበልጥ ትልቅ የሆነች የአንዲት ከተማ ግንባታ እንዴት ሊጠናቀቅ እንደቀረበ እንመለከታለን።
[ታስታውሳለህን?]
◻ ዕዝራም ሆነ ሌሎች በኢየሩሳሌም እንደሚደሰቱ ያሳዩት እንዴት ነበር?
◻ ዕዝራና ነህምያ ብዙ አይሁዳውያን የሠሯቸውን የትኞቹን ስህተቶች እንዲያርሙ ረድተዋቸዋል?
◻ ስለ ዕዝራና ነህምያ ከሚናገሩት ታሪኮች ምን ትምህርት ለመቅሰም ትችላላችሁ?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነህምያን ይበልጥ ያሳሰበው በሱሳ የነበረው ከፍተኛ ክብር ያለው ሥራው ሳይሆን የኢየሩሳሌም ጉዳይ ነበር
[በገጽ 16, 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ነህምያ እንዳደረገው እጅግ አስፈላጊ በሆነው የስብከት ተልእኳችን ለመቀጠል እንድንችል የይሖዋን አመራርና ጥንካሬ ለማግኘት መጸለይ አለብን