የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 10/15 ገጽ 19-24
  • ከስሟ ትርጉም ጋር የምትስማማዋ ኢየሩሳሌም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ከስሟ ትርጉም ጋር የምትስማማዋ ኢየሩሳሌም
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • አስደሳች የስብሰባ ቀን
  • ሌላ አስደሳች ስብሰባ
  • የአምላክን ቤት ችላ ልንል አይገባም
  • አስደሳች ምረቃ
  • ለዘላለማዊ ደስታ የሚሆን ምክንያት
  • ኢየሩሳሌም —‘ለደስታችሁ ምክንያት ከሚሆኑት ነገሮች ሁሉ በላይ’ ናትን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • የነህምያ መጽሐፍ ጎላ ያሉ ነጥቦች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2006
  • የኢየሩሳሌም ግንብ
    ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ምን ትማራለህ?
  • የኢየሩሳሌም ግንብ
    የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች መማሪያ መጽሐፌ
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 10/15 ገጽ 19-24

ከስሟ ትርጉም ጋር የምትስማማዋ ኢየሩሳሌም

“በፈጠርሁት ደስ ይበላችሁ ለዘላለምም ሐሴት አድርጉ፤ እነሆ፣ ኢየሩሳሌምን ለሐሤት . . . እፈጥራለሁና።”​—⁠ኢሳይያስ 65:​18

1. ዕዝራ በአምላክ ስለ ተመረጠችው ከተማ እንዴት ተሰምቶት ነበር?

አይሁዳዊው ካህን ዕዝራ የአምላክ ቃል ትጉህ ተማሪ ስለነበረ በአንድ ወቅት ኢየሩሳሌም ከይሖዋ ንጹሕ አምልኮ ጋር የነበራትን ግንኙነት ከፍ አድርጎ ተመልክቶታል። (ዘዳግም 12:​5፤ ዕዝራ 7:​27) ለአምላክ ከተማ የነበረው ፍቅር በመንፈስ አነሣሽነት ከጻፋቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ማለትም ከአንደኛና ከሁለተኛ ዜና እንዲሁም ከዕዝራ መጻሕፍት ለመመልከት ይቻላል። ኢየሩሳሌም የሚለው ስም በጠቅላላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ800 ጊዜ በላይ ተጠቅሶ የሚገኝ ሲሆን ከዚህ ውስጥ ወደ አንድ አራተኛ የሚጠጋው የሚገኘው በእነዚህ ታሪካዊ ዘገባዎች ውስጥ ነው።

2. ዕዝራ አንዳንድ ጊዜ ኢየሩሳሌም የሚለውን ስም በምን መልኩ ጽፎታል? የዚህስ ትርጉም ምንድን ነው?

2 መጽሐፍ ቅዱስ በተጻፈበት ዕብራይስጥ “ኢየሩሳሌም” የሚለው ቃል ድርብ መልእክት በሚያስተላልፍ የዕብራይስጥ ቋንቋ የአጻጻፍ ስልት የተቀመጠ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህ ድርብ መልእክት የሚያስተላልፍ የአጻጻፍ ስልት አብዛኛውን ጊዜ የሚሠራበት እንደ ዓይን፣ ጆሮ፣ እጅና እግር ለመሳሰሉት ጥንድ ሆነው ለሚገኙ ነገሮች ነው። ኢየሩሳሌም የሚለው ስም ጥንድ መልእክት በሚያስተላልፍ በዚህ የአጻጻፍ ስልት ሲጻፍ የአምላክ ሕዝቦች እጥፍ በሆነ መልኩ ማለትም በመንፈሳዊና በሥጋዊ የሚያገኙትን ሰላም የሚያመለክት ትንቢት ሊሆን ይችላል። ዕዝራ ይህን ሙሉ በሙሉ ይረዳው አይረዳው ቅዱሳን ጽሑፎች ምንም የሚገልጹት ነገር የለም። ይሁንና ካህን እንደመሆኑ መጠን አይሁዳውያኑ ከአምላክ ጋር ሰላም እንዲኖራቸው የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። እንዲሁም ኢየሩሳሌም “የእጥፍ ሰላም ባለቤት [ወይም፣ መሠረት]” ከሚለው የስሟ ትርጉም ጋር የምትስማማ ከተማ እንድትሆን ጠንክሮ ሠርቷል።​—⁠ዕዝራ 7:​6

3. ስለ ዕዝራ እንቅስቃሴዎች እንደገና የምንሰማው ከስንት ዓመታት በኋላ ነው? የምናገኘውስ በምን ሁኔታ ላይ ነው?

3 ዕዝራ ኢየሩሳሌምን በጎበኘበትና ነህምያ ወደ ከተማዋ በመጣበት ጊዜ መካከል በነበሩት 12 ዓመታት ውስጥ ዕዝራ የት እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ አይናገርም። በዚያን ወቅት ሕዝቡ የነበረበት ደካማ መንፈሳዊ ሁኔታ ዕዝራ በአካባቢው እንዳልነበረ ይጠቁማል። ሆኖም ዕዝራ የከተማዋ ቅጥር መልሶ ከተገነባ ከጥቂት ጊዜ በኋላ በኢየሩሳሌም እንደገና ካህን ሆኖ በታማኝነት ሲያገለግል እናገኘዋለን።

አስደሳች የስብሰባ ቀን

4. የእስራኤልን ሰባተኛ ወር የመጀመሪያ ቀን ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው?

4 የኢየሩሳሌም ቅጥር ተሠርቶ ያለቀው ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው በዓላት በሚከበሩበት በእስራኤል ሃይማኖታዊ የቀን መቁጠሪያ መሠረት ቲሽሪ በሚባለው ሰባተኛ ወር ውስጥ ነበር። በቲሽሪ ወር የመጀመሪያ ቀን ላይ የመለከት መንፋት በዓል ተብሎ የሚጠራው ልዩ የሆነ የአዲስ ጨረቃ በዓል ይከበር ነበር። በዚያ ቀን ለይሖዋ መሥዋዕቶች በሚቀርቡበት ጊዜ ካህናት መለከቶችን ይነፉ ነበር። (ዘኁልቁ 10:​10፤ 29:​1) ይህ ቀን በቲሽሪ ወር 10ኛ ቀን ላይ ለሚከበረው ዓመታዊው የስርየት ቀንና በዚሁ ወር ከ15ኛው ቀን አንስቶ እስከ 21ኛው ቀን ለሚከበረው የመከር በዓል እስራኤላውያንን ያዘጋጃቸው ነበር።

5. (ሀ) ዕዝራና ነህምያ ‘የሰባተኛውን ወር የመጀመሪያ ቀን’ ጥሩ አድርገው የተጠቀሙበት እንዴት ነበር? (ለ) እስራኤላውያን ያለቀሱት ለምን ነበር?

5 “በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን” በነህምያና በዕዝራ ቀስቃሽነት ሳይሆን አይቀርም ‘ሕዝቡ ሁሉ’ ተሰበሰቡ። ወንዶች፣ ሴቶችና ‘አስተውለውም የሚሰሙ ሁሉ’ ተገኝተው ነበር። ይህም ትንንሽ ልጆች በስብሰባው ላይ መገኘታቸውን የሚያመለክት ሲሆን ዕዝራ በመድረክ ላይ ቆሞ “ከማለዳ ጀምሮ እስከ ቀትር ድረስ” ሕጉን ሲያነብ በትኩረት ይከታተሉ ነበር። (ነህምያ 8:​1–4) ሕዝቡ እየተነበበ ያለውን እንዲያስተውሉ ሲባል የተወሰነ ነገር ከተነበበ በኋላ ሌዋውያኑ ያብራሩላቸው ነበር። በዚህ ወቅት እነሱም ሆኑ አባቶቻቸው የአምላክን ሕግ ከመታዘዝ ምን ያህል እንደራቁ ሲገነዘቡ አለቀሱ።​—⁠ነህምያ 8:​5–9

6, 7. ነህምያ አይሁዶች ማልቀሳቸውን እንዲያቆሙ ለማድረግ ከወሰደው እርምጃ ክርስቲያኖች ምን ሊማሩ ይችላሉ?

6 ሆኖም ጊዜው የሐዘን እንባ የሚፈስበት ወቅት አልነበረም። የበዓል ቀን ሲሆን ሕዝቡም የኢየሩሳሌምን ቅጥር መልሶ የመገንባቱን ሥራ ገና ማጠናቀቃቸው ነበር። ስለዚህ ነህምያ ትክክለኛ አስተሳሰብ እንዲይዙ ለመርዳት ሲል እንዲህ አላቸው:- “ሂዱ፣ የሰባውንም ብሉ፣ ጣፋጩንም ጠጡ፣ ለእነዚያም ላልተዘጋጀላቸው እድል ፈንታቸውን ስደዱ፤ ዛሬ ለጌታችን የተቀደሰ ቀን ነው፤ የእግዚአብሔርም ደስታ ኃይላችሁ ነውና አትዘኑ።” በታዛዥነት “ሕዝቡም ሁሉ የተነገረላቸውን ቃል አስተውለዋልና ሊበሉና ሊጠጡ እድል ፈንታም ሊሰድዱ ደስታም ሊያደርጉ ሄዱ።”​—⁠ነህምያ 8:​10–12

7 ዛሬ የአምላክ ሕዝቦች ከዚህ ታሪክ ብዙ ነገር ለመማር ይችላሉ። በጉባኤና በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ክፍል የማቅረብ መብት ያላቸው ወንድሞች ከላይ የተጠቀሰውን ማስታወስ ይኖርባቸዋል። እነዚህ ወቅቶች አንዳንድ ጊዜ አስፈላጊ የሆነው የእርምት ምክር የሚሰጥባቸው ብቻ ሳይሆኑ አምላክ የሚፈልግብንን ብቃቶች ማሟላት የሚያስገኛቸው ጥቅሞችና በረከቶች የሚጎላባቸውም ናቸው። ለተሠሩ መልካም ሥራዎች ምስጋና ይቀርባል፤ እንዲሁም ለመጽናት የሚያስችል ማበረታቻ ይሰጣል። የአምላክ ሕዝቦች በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ከአምላክ ቃል ገንቢ ትምህርት በማግኘት ከልብ ተደስተው መመለስ አለባቸው።​—⁠ዕብራውያን 10:​24, 25

ሌላ አስደሳች ስብሰባ

8, 9. በሰባተኛው ወር ሁለተኛ ቀን ላይ ምን ልዩ ስብሰባ ተደርጎ ነበር? ለአምላክ ሕዝቦችስ ምን አስገኝቶላቸዋል?

8 በዚያ ልዩ ወር ሁለተኛ ቀን ላይ “ከሕዝቡ ሁሉ የአባቶች ቤቶች አለቆች ካህናቱም ሌዋውያኑም የሕጉን ቃል ይተረጉምላቸው ዘንድ ወደ ጸሐፊው ወደ ዕዝራ ተሰበሰቡ።” (ነህምያ 8:​13) ዕዝራ “የእግዚአብሔርን ሕግ ይፈልግና ያደርግ ዘንድ፣ ለእስራኤልም ሥርዓትንና ፍርድን ያስተምር ዘንድ ልቡን አዘጋጅቶ” ስለነበር ይህን ስብሰባ ለመምራት ሙሉ ብቃት ነበረው። (ዕዝራ 7:​10) ይህ ስብሰባ የአምላክ ሕዝቦች ወደ ሕጉ ቃል ኪዳን ይበልጥ መጠጋት በሚያስፈልጋቸው ነጥቦች ላይ ትኩረት እንዳደረገ አያጠራጥርም። በተለይ አፋጣኝ ትኩረት ይሻ የነበረው ጉዳይ መጪውን የዳስ በዓል ለማክበር ተገቢውን ዝግጅት ማድረግ ነበር።

9 ይህ ሳምንት የሚፈጅ በዓል በትክክለኛው መንገድ የተከበረ ሲሆን ሕዝቡ በሙሉ ከተለያዩ ዛፎች በተቆረጡ ቅርንጫፎችና ቅጠሎች በተሠሩ ጊዜያዊ መጠለያዎች ውስጥ ተቀምጦ ነበር። ሕዝቡ እነዚህን ዳሶች ዝርግ በሆነው ጣሪያቸው ላይ፣ በግቢያቸው፣ በቤተ መቅደሱ አጥር ግቢ ውስጥና በኢየሩሳሌም የሕዝብ አደባባዮች ላይ ሠርተው ነበር። (ነህምያ 8:​15, 16) ይህ ወቅት ሕዝቡን ለመሰብሰብና የአምላክ ሕግ ሲነበብ እንዲያዳምጥ ለማድረግ እንዴት ያለ ጥሩ አጋጣሚ ነበር! (ከዘዳግም 31:​10–13 ጋር አወዳድር።) ይህም ይደረግ የነበረው ከበዓሉ “ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ እስከ መጨረሻው ቀን ድረስ” በየቀኑ ሲሆን የአምላክ ሕዝቦችም “እጅግ ታላቅ ደስታ” ተሰምቷቸው ነበር።​—⁠ነህምያ 8:​17, 18

የአምላክን ቤት ችላ ልንል አይገባም

10. በሰባተኛው ወር በ24ኛው ቀን ላይ ልዩ ስብሰባ የተዘጋጀው ለምን ነበር?

10 በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያሉት ከባድ ድክመቶች የሚታረሙበት ተገቢ ጊዜና ቦታ አለ። ዕዝራና ነህምያ ይህ ጊዜ እንዲህ ለማድረግ አመቺ መሆኑን በመገንዘብ ይመስላል በቲሽሪ ወር በ24ኛው ቀን ላይ የጾም ቀን እንዲሆን ዝግጅት አደረጉ። የአምላክ ሕግ በድጋሚ ተነበበ፤ ሕዝቡም ኃጢአታቸውን ተናዘዙ። ከዚያም አምላክ ዓመፀኛ ሕዝቦቹን በምሕረት ስለያዘበት መንገድ ሌዋውያን አብራሩ፤ ውብ በሆኑ ቃላት ይሖዋን አወደሱ፤ እንዲሁም በአለቆቻቸው፣ በሌዋውያንና በካህናቶቻቸው ማኅተም ትክክለኛነቱ የተረጋገጠ ‘የታመነ ቃል ኪዳን’ ተፈራረሙ።​—⁠ነህምያ 9:​1–38

11. አይሁዳውያን ከየትኛው ‘የታመነ ቃል ኪዳን’ ጋር ራሳቸውን አስተሳስረው ነበር?

11 ሕዝቡ በጠቅላላ የተጻፈውን ‘የታመነ ቃል ኪዳን’ እንደሚፈጽሙ በመሐላ አረጋገጡ። ‘በእውነተኛው አምላክ ሕግ ለመሄድ’ ተስማሙ። እንዲሁም ‘ከምድር አሕዛብ’ ጋር በጋብቻ ላለመተሳሰር ተስማሙ። (ነህምያ 10:​28–30) ከዚህም በላይ አይሁዳውያን ሰንበትን ለመጠበቅ፣ እውነተኛውን አምልኮ የሚደግፍ ዓመታዊ መዋጮ ለማድረግ፣ በመሠዊያው ላይ ለሚቀርበው መሥዋዕት የሚሆን እንጨት ለማቅረብ፣ የመንጎቻቸውን በኩራት መሥዋዕት እንዲሆኑ ለመስጠት እንዲሁም የመሬታቸውን ፍሬ በኩራት ወደ ቤተ መቅደሱ ጓዳዎች ለማምጣት ወሰኑ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ‘የአምላካቸውን ቤት ችላ ላለማለት’ ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር።​—⁠ነህምያ 10:​32–39

12. በዛሬው ጊዜ የአምላክን ቤት ችላ አለማለት ምን ነገርን ይጨምራል?

12 ዛሬ የይሖዋ ሕዝቦች በታላቁ የይሖዋ መንፈሳዊ ቤተ መቅደስ አደባባዮች ‘ቅዱስ አገልግሎት የማቅረብ’ መብታቸውን ችላ እንዳይሉ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። (ራእይ 7:​15 NW) ይህም የይሖዋ አምልኮ እንዲስፋፋ አዘውትሮ ልባዊ ጸሎት ማቅረብን ይጨምራል። ከዚህ ዓይነቱ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ መኖር ደግሞ ለክርስቲያናዊ ስብሰባዎች መዘጋጀትና ተሳትፎ ማድረግ፣ ምሥራቹን ለመስበክ በሚወጡ ዝግጅቶች መካፈል እንዲሁም ፍላጎት ያሳዩትን ለመርዳት ተመልሶ መጠየቅና የሚቻል ከሆነም መጽሐፍ ቅዱስን ማስጠናት ይጠይቃል። የአምላክን ቤት ችላ ማለት የማይፈልጉ ብዙዎች ለስብከቱ ሥራና እውነተኛው አምልኮ ለሚካሄድባቸው ሥፍራዎች እደሳ የሚውል የገንዘብ መዋጮ ያደርጋሉ። በተጨማሪም በአስቸኳይ የሚያስፈልጉ የመሰብሰቢያ ቦታዎች በሚገነቡበት ጊዜም ሆነ የተገነቡትን በንጽሕና በመያዝ ድጋፋችንን ልንሰጥ እንችላለን። ለአምላክ መንፈሳዊ ቤት ፍቅር እንዳለን የምናሳይበት አንዱ አቢይ መንገድ በመሰል አማኞች መካከል ሰላም እንዲሰፍን መጣርና በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ የተቸገሩትን መርዳት ነው።​—⁠ማቴዎስ 24:​14፤ 28:​19, 20፤ ዕብራውያን 13:​15, 16

አስደሳች ምረቃ

13. የኢየሩሳሌም ቅጥር ከመመረቁ በፊት የትኛው አጣዳፊ ጉዳይ ትኩረት ያሻው ነበር? ብዙዎችስ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ትተዋል?

13 በነህምያ ዘመን የታተመው ‘የታመነው ቃል ኪዳን’ የጥንቶቹን የአምላክ ሕዝቦች የኢየሩሳሌም ቅጥር ለሚመረቅበት ቀን አዘጋጅቷቸዋል። ሆኖም ትኩረት የሚያሻው ሌላ አስቸኳይ ጉዳይ ነበር። አሥራ ሁለት በሮች ባሉት ትልቅ ቅጥር የታጠረችው ኢየሩሳሌም ብዙ ነዋሪ ሕዝብ ያስፈልጋት ነበር። አንዳንድ እስራኤላውያን በዚያ ይኖሩ የነበረ ቢሆንም ‘ከተማይቱ ሰፊና ትልቅ ነበረች፤ በውስጥዋ የነበረው ሕዝብ ግን ጥቂት ነበር።’ (ነህምያ 7:​4) ይህን ችግር ለመፍታት ሕዝቡ ‘ከአሥሩ ክፍል አንዱ በቅድስቲቱ ከተማ በኢየሩሳሌም ይቀመጡ ዘንድ ዕጣ ተጣጣሉ።’ ለዚህ ዝግጅት የተሰጠው የፈቃደኝነት ምላሽ ሕዝቡ “በፈቃዳቸው በኢየሩሳሌም ለመቀመጥ የወደዱትን ሰዎች” እንዲባርኩ አነሳስቷቸዋል። (ነህምያ 11:​1, 2) የጎለመሰ ክርስቲያን እርዳታ ይበልጥ ወደሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ለመዛወር ሁኔታቸው ለሚፈቅድላቸው በጊዜያችን ለሚገኙ እውነተኛ አምላኪዎች ይህ እንዴት ያለ ግሩም ምሳሌ ነው!

14. የኢየሩሳሌም ቅጥር በተመረቀበት ቀን ምን ነገር ተከስቶ ነበር?

14 የኢየሩሳሌም ቅጥር ለሚመረቅበት ታላቅ ቀን አስፈላጊው ዝግጅት መደረግ ጀመረ። ሙዚቀኞችና መዘምራን በይሁዳ አካባቢ ከሚገኙ ከተሞች ተሰበሰቡ። እነዚህ ሰዎች ለአምላክ ምስጋና በሚያቀርቡ ሁለት ትላልቅ የመዘምራን ቡድኖች የተከፈሉ ሲሆን ሁለቱንም ቡድኖች ሕዝቡ በሰልፍ ይከተላቸው ነበር። (ነህምያ 12:​27–31, 36, 38) መዘምራኑና ሰልፈኞቹ ከቤተ መቅደሱ ርቆ ከሚገኘው ቅጥር ላይ ምናልባትም ከሸለቆው በር ተነስተው በተቃራኒ አቅጣጫ በሰልፍ በመጓዝ ወደ አምላክ ቤት ሲደርሱ ተገናኙ። “እግዚአብሔርም በታላቅ ደስታ ደስ አሰኝቶአቸዋልና፤ በዚያ ቀን ትልቅ መሥዋዕት አቀረቡ፣ ደስም አላቸው፤ ሴቶቹና ልጆቹም ደግሞ ደስ አላቸው፤ የኢየሩሳሌምም ደስታ ከሩቅ ተሰማ።”​—⁠ነህምያ 12:​43

15. የኢየሩሳሌም ቅጥር መመረቅ ለዘላቂ ደስታ ምክንያት ያልሆነው ለምንድን ነው?

15 መጽሐፍ ቅዱስ ይህ አስደሳች በዓል በምን ቀን እንደዋለ አይገልጽም። ሆኖም በኢየሩሳሌም የመልሶ ግንባታ ሥራ ጉልህ ስፍራ የሚሰጠው ምናልባትም የመጨረሻውን ከፍተኛ ደረጃ የያዘ ሊሆን እንደሚችል ምንም አያጠራጥርም። እርግጥ በከተማዋ ውስጥ መሠራት የሚገባው ብዙ የግንባታ ሥራ ነበረ። ከጊዜ በኋላ የኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ግሩም የነበረውን መንፈሳዊ አቋማቸውን አጡ። ለምሳሌ ያህል ነህምያ ከተማዋን ለሁለተኛ ጊዜ ሲጎበኝ የአምላክ ቤት ተትቶ እንደነበረና እስራኤላውያን ወንዶች አረማውያን ሴቶችን እንደገና ማግባት ጀምረው እንደነበር ተመልክቷል። (ነህምያ 13:​6–11, 15, 23) እነዚህ መጥፎ ሁኔታዎች ተከስተው እንደነበር ነቢዩ ሚልክያስ የጻፈው ትንቢት ያረጋግጥልናል። (ሚልክያስ 1:​6–8፤ 2:​11፤ 3:​8) ስለዚህ የኢየሩሳሌም ቅጥር መመረቅ ለዘላቂ ደስታ ምክንያት አልሆነም።

ለዘላለማዊ ደስታ የሚሆን ምክንያት

16. የአምላክ ሕዝቦች በጉጉት የሚጠባበቋቸው የትኞቹን ላቅ ያለ ግምት የሚሰጣቸው ክንውኖች ነው?

16 ዛሬ የይሖዋ ሕዝቦች፣ አምላክ በጠላቶቹ ሁሉ ላይ ድል የሚቀዳጅበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። ይህ ጊዜ በ“ታላቂቱ ባቢሎን” ማለትም ሁሉንም ዓይነት የሐሰት ሃይማኖት ጠቅልላ በያዘችው ምሳሌያዊት ከተማ ጥፋት ይጀምራል። (ራእይ 18:​2, 8) የሐሰት ሃይማኖት መጥፋት የመጪውን ታላቅ መከራ የመጀመሪያ ምዕራፍ የሚያመለክት ይሆናል። (ማቴዎስ 24:​21, 22) እንዲሁም ከፊታችን አንድ ታላቅ ክንውን አለ፤ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስና ሙሽራይቱ ማለትም የ“አዲሲቱ ኢየሩሳሌም” ዜጎች የሆኑት የ144,000ዎቹ ሰማያዊ ጋብቻ ይከናወናል። (ራእይ 19:​7፤ 21:​2) ይህ የላቀ ግምት የሚሰጠው ጋብቻ መቼ እንደሚጠናቀቅ በትክክል ማወቅ ባንችልም አስደሳች ጊዜ እንደሚሆን ግን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።​—⁠መጠበቂያ ግንብ 16–111 ገጽ 30–1 ተመልከት።

17. ስለ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ግንባታ መጠናቀቅ ምን የምናውቀው ነገር አለ?

17 የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም ግንባታ የሚጠናቀቅበት ጊዜ በጣም ቅርብ እንደሆነ እናውቃለን። (ማቴዎስ 24:​3, 7–14፤ ራእይ 12:​12) እንደ ምድራዊቷ የኢየሩሳሌም ከተማ የሐዘን ምክንያት አትሆንም። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ዜጎቿ በሙሉ በመንፈስ የተወለዱ፣ የተፈተኑና የጠሩ የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች በመሆናቸው ነው። እስከ ሞት ድረስ የታመኑ ሆነው በመገኘት ለአጽናፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዥ ለይሖዋ አምላክ ለዘላለም ታማኝ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። ይህ ለተቀረው የሰው ዘር፣ በሕይወት ላሉትም ሆነ ለሞቱት ከፍተኛ ትርጉም አለው!

18. ‘ደስ ሊለንና ለዘላለም ሐሤት ልናደርግ’ የሚገባን ለምንድን ነው?

18 አዲሲቱ ኢየሩሳሌም በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት በሚያምኑ ሰዎች ላይ ትኩረቷን ስታደርግ ምን እንደሚሆን ተመልከት። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና።” (ራእይ 21:​2–4) ከዚህም በላይ አምላክ ይህን ከተማ መሰል ዝግጅት የሰው ልጆችን ሰብዓዊ ፍጽምና ለማላበስ ይጠቀምበታል። (ራእይ 22:​1, 2) እነዚህ ነገሮች ‘አምላክ አሁን በመፍጠር ላይ ባለው ነገር ለዘላለም እንድንደሰት’ የሚያደርጉን ምንኛ አስደናቂ ምክንያቶች ናቸው!​—⁠ኢሳይያስ 65:​18

19. ክርስቲያኖች የተሰባሰቡበት መንፈሳዊ ገነት ምንድን ነው?

19 ይሁን እንጂ ንስሐ የገቡ ሰዎች ከአምላክ እርዳታ ለማግኘት እስከዚያ ጊዜ ድረስ መቆየት አያስፈልጋቸውም። ይሖዋ የ144,000ዎቹን የመጨረሻ አባላት ፍቅር፣ ደስታና ሰላም የመሳሰሉ የአምላክ መንፈስ ፍሬዎች ተትረፍርፈው ወደሚገኙበት መንፈሳዊው ገነት የመሰብሰቡን ሥራ በ1919 ጀምሯል። (ገላትያ 5:​22, 23) የአምላክ መንግሥት ምሥራችን በምድር ዙሪያ የመስበኩን ሥራ በግንባር ቀደምትነት በመምራት በሚያስደንቅ ሁኔታ ፍሬያማ የነበሩት የቅቡዓን ነዋሪዎቹ እምነት የዚህ መንፈሳዊ ገነት አንዱ ጉልህ ገጽታ ነው። (ማቴዎስ 21:​43፤ 24:​14) በዚህም ምክንያት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ወደ ስድስት ሚልዮን የሚጠጉ “ሌሎች በጎች” ወደ መንፈሳዊው ገነት ለመግባትና ውጤታማ በሆነው ሥራ ተካፋዮች ለመሆን ችለዋል። (ዮሐንስ 10:​16) ለዚህ ብቁ የሆኑት በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ ያላቸውን እምነት መሠረት በማድረግ ራሳቸውን ለይሖዋ አምላክ በመወሰን ነው። ወደፊት የአዲሲቱ ኢየሩሳሌም አባላት ከሚሆኑት ጋር መተባበራቸው በረከት መሆኑ ተረጋግጧል። ስለዚህ ይሖዋ ከቅቡዓን ክርስቲያኖች ጋር ባለው ግንኙነት ለ“አዲስ ምድር” ማለትም የሰማያዊውን መንግሥት ምድራዊ ክፍል ለሚወርሱ ፈሪሃ አምላክ ላላቸው ሰዎች የሚሆን ጽኑ መሠረት ጥሏል።​—⁠ኢሳይያስ 65:​17፤ 2 ጴጥሮስ 3:​13

20. አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ከስሟ ትርጉም ጋር የምትስማማ ከተማ የምትሆነው እንዴት ነው?

20 የይሖዋ ሕዝቦች በአሁኑ ጊዜ በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ እያገኙት ያለው ሰላማዊ ሁኔታ በቅርቡ በምድራዊ ገነት ላይ ተፈጻሚነት ይኖረዋል። ይህ የሚሆነው አዲሲቱ ኢየሩሳሌም የሰው ልጆችን ለመባረክ ከሰማይ በምትወርድበት ጊዜ ነው። ድርብ በሆነ መንገድ የአምላክ ሕዝቦች በኢሳይያስ 65:​21–25 ላይ ቃል የተገባላቸውን ሰላማዊ ሁኔታ ይጎናጸፋሉ። በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ይሖዋን በአንድነት በማምለክ ላይ የሚገኙ እንደመሆናቸው መጠን በሰማያዊቷ አዲሲቱ ኢየሩሳሌም ውስጥ ቦታቸውን ለመያዝ የሚጠባበቁት ቅቡዓኑና “ሌሎች በጎች” በአሁኑ ጊዜ የአምላክን ሰላም አግኝተዋል። እንዲሁም ‘በሰማይ የሆነው የአምላክ ፈቃድ በምድርም በሚሆንበት’ ጊዜ እንዲህ የመሰለው ሰላም በምድራዊ ገነት ውስጥ ይሰፍናል። (ማቴዎስ 6:​10) አዎን፣ የአምላክ ክብራማ ሰማያዊት ከተማ ከስሟ ትርጉም ጋር በሚስማማ መንገድ ‘የእጥፍ ሰላም’ ጽኑ መሠረት ትሆናለች። ለታላቁ ፈጣሪዋ ለይሖዋ አምላክና ሙሽራዋ ለሆነው ንጉሥ ለኢየሱስ ክርስቶስ ምስጋና የምታመጣ በረከት በመሆን ለዘላለም ትኖራለች።

[ታስታውሳለህን?]

◻ ነህምያ ሕዝቡን በኢየሩሳሌም በሰበሰበበት ወቅት ምን ተከናውኖ ነበር?

◻ የጥንቶቹ አይሁዶች የአምላክን ቤት ችላ እንዳይሉ ምን ማድረግ ነበረባቸው? እኛስ ምን እንድናደርግ ተጠርተናል?

◻ “ኢየሩሳሌም” ዘላቂ ደስታና ሰላም በማምጣት ረገድ ድርሻ ያላት እንዴት ነው?

[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ካርታ]

(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)

የኢየሩሳሌም በሮች

ቁጥሮቹ የሚያመለክቱት በአሁኑ ጊዜ የበሮቹ ቁመት በሜትር ስንት እንደሆነ ነው

የዓሣ በር

የአሮጌዋ ከተማ በር

የኤፍሬም በር

የማዕዘን በር

ሰፊ ቅጥር

አደባባይ

የሸለቆ በር

ሁለተኛ ክፍል

የቀድሞው ሰሜናዊ ቅጥር

የዳዊት ከተማ

የጉድፍ መጣያ በር

የሄኖም ሸለቆ

ግንብ

የበጎች በር

የዘበኞች በር

የቤተ መቅደሱ አካባቢ

የሐሚፍቃድ (መቆጣጠሪያ) በር

የፈረስ በር

ዖፌል

አደባባይ

የውኃ በር

የግዮን ፏፏቴ

የምንጭ በር

የንጉሡ አትክልት

ዓይን ሮጌል

ታይሮፖየን (መካከለኛ)ሸለቆ

የቄድሮን ጅረት ፈፋ

740

730

730

750

770

770

750

730

710

690

670

620

640

660

680

700

720

740

730

710

690

670

የኢየሩሳሌም ከተማ በጠፋችበት ጊዜና ነህምያ የመሪነቱን ቦታ በመያዝ ቅጥሩን መልሶ መገንባት በጀመረበት ጊዜ የኢየሩሳሌም ቅጥር ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰበው ስፋት

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ