ሰዎች ኃይል የሚጠቀሙት ለምንድን ነው?
በዩ ኤስ ኤ፣ ኮሎራዶ፣ ዴንቨር ከተማ ውስጥ አንድ የ27 ሳምንት ሕፃን አለጊዜው ተወለደ። ሕፃኑ ከመሞት ተረፈና በሆስፒታሉ ውስጥ ለሦስት ወራት ያህል ከቆየ በኋላ ወደቤቱ ወላጆቹ ጋር ተመለሰ። ከሦስት ሳምንታት በኋላ ሕፃኑ እንደገና ሆስፒታል ገባ። ለምን? አባትየው በንዴት ጭንቅላቱን በኃይል ከመነቅነቁ የተነሳ በአንጎሉ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ስለደረሰበት ነው። አባትየው ይህን እርምጃ የወሰደው ሕፃኑ በጣም ያለቅስ ስለነበረ መቋቋም አቅቶት ነው። ሕፃኑ ዓይነ ስውርና የአካል ጉዳተኛ ሆኖ ቀረ። ዘመናዊ ሕክምና ሲወለድ ከደረሰበት ጉዳት ሊያድነው ቢችልም ከአባቱ የኃይል እርምጃ ሊያድነው ግን አልቻለም።
ቁጥር ስፍር የሌላቸው ልጆች በምድር ላይ ካሉት ከፍተኛ የጠበኝነት ባሕርይ ከሚታይባቸው ቦታዎች በአንዱ ማለትም በቤታቸው ውስጥ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፣ ይደበደባሉ ወይም ይገደላሉ! አንዳንዶች በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ብቻ በየዓመቱ 5,000 የሚያክሉ ልጆች በወላጆቻቸው እጅ እንደሚገደሉ ይገምታሉ! ሆኖም የጥቃቱ ሰለባ የሆኑት ልጆች ብቻ አይደሉም። ዎርልድ ሄልዝ የተባለው መጽሔት እንደዘገበው ከሆነ በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ “በመውለጃ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ ሴቶች ላይ አካላዊ ጉዳት የሚያደርስባቸው ዋነኛው ነገር በሚስቶች ላይ የሚፈጸም የኃይል እርምጃ ነው።” በሌሎች አገሮችስ? በታዳጊ አገሮች ውስጥ በሚኖሩ “ሴቶች ላይ በተደረገ ጥናት አንድ ሦስተኛ ወይም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶች የትዳር ጓደኞቻቸው እንደሚደበድቧቸው ተናግረዋል።” አዎን፤ የኃይል እርምጃ በተለይ በቤት ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት በማስከተል ላይ ነው።
ብዙ ባልና ሚስቶች ኃይል በመጠቀም አለመግባባቶቻቸውን ለመፍታት ይሞክራሉ። በአንዳንድ አገሮች ወላጆችና መምህራን ንዴታቸውን በልጆች ላይ ለመወጣት ኃይል ይጠቀማሉ። ጉልበት ያላቸው ትምክህተኞች እንዲሁ በሰው ስቃይ ለመደሰት ብለው አቅም የሌላቸውን እየደበደቡ ያስጨንቋቸዋል። ሰዎች ይህን ያህል ኃይል መጠቀም የሚቀናቸው ለምንድን ነው?
ሰዎች ኃይል ለመጠቀም የሚገፋፉበት ምክንያት
የሰው ልጆች በተፈጥሯቸው ኃይል መጠቀም የሚወዱ ናቸው የሚሉ ሰዎች አሉ። ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በጥቅሉ ሲታይ ወንጀል የቀነሰ ቢሆንም እንኳ በወጣቶች ዘንድ ግን ጨምሯል። እንዲሁም ሰዎች ለዓመፅ ያላቸው ፍላጎት ከፍ ብሏል። ሦስት ታላላቅ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የሚያስተላልፏቸውን የወንጀል ታሪኮች በሁለት እጥፍ ሲያሳድጉ ስለ ግድያ የሚያቀርቡትን ደግሞ በሦስት እጥፍ ከፍ አድርገዋል። አዎን ወንጀል ከፍተኛ ገንዘብ ማስገኛ ሆኗል! የሥነ አእምሮ ሐኪም የሆኑት ካርል ሜኒንገር “ለዓመፅ ደንዳኖች መሆናችን ሳያንሰን በጋዜጦቻችን ላይ የመጀመሪያውን ገጽ እንዲይዝ አድርገናል። ከቴሌቪዥን ፕሮግራሞቻችን መካከል አንድ ሦስተኛ ወይም አንድ አራተኛ የሚሆኑት ልጆቻችንን ለማዝናናት ዓመፅ ያቀርባሉ። ዓመፅን ችላ ብለን በማለፍ ብቻ አላበቃንም፤ ይባስ ብሎም ያስደስተናል!”
በቅርቡ የተካሄዱ ሳይንሳዊ ጥናቶች የአንጎላችን አሠራርም ሆነ አካባቢያችን ሰዎች ከሚያሳዩት የጠበኝነት ባሕርይ ጋር ከፍተኛ ዝምድና እንዳላቸው ጠቁመዋል። “ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ልጆች የሚያድጉበት ጎጂ አካባቢ በእርግጥም የዓመፅ ወረርሽኝ በማስከተል ላይ መሆኑን መደምደም ጀምረናል” ሲሉ በኢሊኖይ ዩኒቨርሲቲ በወጣቶች ላይ ጥናት በሚያካሂድ ተቋም ውስጥ የሚሠሩት ዶክተር ማርከስ ጄ ክሩሲ ተናግረዋል። “በአካባቢያችን የሚፈጸሙ ክስተቶች በአንጎል ውስጥ የሞለኪላዊ ለውጦች ስለሚያስከትሉ ሰዎች ይበልጥ ግልፍተኞች እየሆኑ ነው።” “የቤተሰብ መዋቅር መፈራረስ፣ የነጠላ ወላጆች ቁጥር መጨመር፣ ሥር የሰደደ ድህነትና አደገኛ ዕፆችን እንደመውሰድ” የመሳሰሉ ነገሮች “የአንጎል አሠራር ወደ ጠበኛነት እንዲያዘነብል ሊያደርጉ ይችላሉ። ከዚህ በፊት እነዚህ ነገሮች ይህ ዓይነት ተጽእኖ ሊኖራቸው ይችላል ተብሎ አይታሰብም ነበር” በማለት ኢንሳይድ ዘ ብሬይን የተባለው መጽሐፍ ገልጿል።
በአንጎል ውስጥ የሚካሄዱ ለውጦች የኃይለኝነት ባሕርይን በቁጥጥር ሥር ያውላል ተብሎ የሚታሰበውን ሴሮቶኒን የተባለ አንጎል ውስጥ የሚገኝ ኬሚካል መጠንም እንደሚቀንሱ ይገመታል። የአልኮል መጠጥ በአንጎል ውስጥ ያለውን የሴሮቶኒን መጠን ሊቀንስ እንደሚችል ጥናቶች ጠቁመዋል። ይህ ደግሞ ከረጅም ጊዜ በፊት የሚታወቀውን በጠበኝነትና አልኮልን ያለ አግባብ በመጠጣት መካከል ላለው ግንኙነት በመጠኑም ቢሆን ሳይንሳዊ መረጃ አስገኝቷል።
በዛሬው ጊዜ እየጨመረ ላለው የጠበኝነት አዝማሚያ አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሌላም ምክንያት አለ። እምነት የሚጣልበት የትንቢት መጽሐፍ የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ይህን ማስጠንቀቂያ ይሰጣል:- “ነገር ግን በመጨረሻው ቀን የሚያስጨንቅ ዘመን እንዲመጣ ይህን እወቅ። ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱ ይሆናሉና፣ ገንዘብን የሚወዱ፣ ትምክህተኞች፣ ትዕቢተኞች፣ . . . ዕርቅን የማይሰሙ፣ ሐሜተኞች፣ ራሳቸውን የማይገዙ፣ ጨካኞች፣ መልካም የሆነውን የማይወዱ፣ ከዳተኞች፣ ችኩሎች፣ በትዕቢት የተነፉ፣ . . . ከእነዚህ ደግሞ ራቅ።” (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) አዎን፣ በዛሬው ጊዜ የምናየው የጠበኝነት መንፈስ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ “መጨረሻው ቀን” የተናገረው ትንቢት ፍጻሜ ነው።
ያለንበትን ጊዜ ይበልጥ አደገኛ የሚያደርገው ሌላ ተጨማሪ ነገርም አለ። መጽሐፍ ቅዱስ “ለምድርና ለባሕር ወዮላቸው፣ ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን እንዳለው አውቆ በታላቅ ቊጣ ወደ እናንተ ወርዶአልና” በማለት ይናገራል። (ራእይ 12:12) ሰይጣንና የእርሱ አጋንንታዊ ጭፍራ ከሰማይ ስለተጣሉ ባሁኑ ጊዜ የክፋት ተግባራቸው በሰው ዘር ላይ አነጣጥሯል። ዲያብሎስ ‘በአየር ላይ ሥልጣን ያለው አለቃ’ እንደመሆኑ መጠን ‘በማይታዘዙት ልጆች ላይ አሁን እየሠራ ያለውን መንፈስ’ ስለሚቆጣጠር ምድርን ከቀን ወደ ቀን ይባስ የዓመፅ ቦታ አድርጓታል።—ኤፌሶን 2:2
ታዲያ ዛሬ በዓለም ላይ ያለውን ዓመፀኛ “አየር” መቋቋም የምንችለው እንዴት ነው? እንዲሁም የኃይል እርምጃ ሳንወስድ አለመግባባትን መፍታት የምንችለው እንዴት ነው?
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
ቁጥር ስፍር የሌላቸው ልጆች በምድር ላይ ካሉት ከፍተኛ የጠበኝነት ባሕርይ ከሚታይባቸው ቦታዎች በአንዱ ማለትም በቤታቸው ውስጥ ጥቃት ይፈጸምባቸዋል፣ ይደበደባሉ ወይም ይገደላሉ!