ጠባቂ መልአክ አለህን?
ጠባቂ መልአክ አለኝ ብለህ ታምናለህን? ብዙዎች አዎን፣ አለኝ በማለት ይመልሳሉ። ይህን በሚመለከት በምዕራብ ካናዳ የምትኖር አንዲት ሴት መላእክትን የማነጋገር ልዩ ተሰጥኦ እንዳላት ይነገርላታል። ከ200 የካናዳ ዶላር ጋር ሙሉ ስምህን ከሰጠሃት ጠባቂህ ከሆነው መልአክ ጋር እንደምታገናኝህ ትናገራለች። በመጀመሪያ እየበራ ባለ ሻማ ነበልባል ላይ ዓይኗን ትተክልና በሐሳብ ትመሰጣለች። ከዚያም ለአንተ የምታስተላልፈውን መልእክት የአንተ መልአክ በራእይ በመታየት ይነግራታል። ደስ ካላት ደግሞ መልአክህ ምን እንደሚመስል በወረቀት ላይ ትሥልና ታሳይሃለች።
ብዙ ሰዎች ይህን ሁኔታ ስለ ፈረንሳዩ ንጉሥ ሉዊ ዘጠነኛ ከሚነገረው አፈ ታሪክ ጋር አንድ እንደሆነ አድርገው ያስባሉ። ንጉሥ ሉዊስ ዘጠነኛ ከሊቀ መልአኩ ሚካኤል ክንፍ ላይ የረገፉ ናቸው የሚባልላቸውን በጣም ውድ የሆኑ ላባዎች ገዝቷል ተብሎ ይታመናል። ብዙዎች የዚህን አፈ ታሪክ እውነተኝነት ቢጠራጠሩም ካናዳዊቷ ሴት የምትናገረውን ቅንጣት ታክል አይጠራጠሩም።
መላእክት ያላቸው አስገራሚ ችሎታ
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለመላእክት የሚሰጠው ትኩረት እየተበራከተ መጥቷል። መላእክት በጠና የታመሙ ሰዎችን እንደጠየቁ፣ መሪር ሐዘን የደረሰባቸውን እንዳጽናኑ፣ ጥበብ እንደ ሰጡና ሰዎችን ከሞት አፋፍ ነጥቀው እንዳዳኑ በቴሌቪዥንና በሲኒማዎች፣ በመጻሕፍት፣ በመጽሔቶችና በጋዜጦች ይዘገባል። በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ 20 ሚልዮን የሚያክሉ ሰዎች መላእክት በሰዎች ሕይወት ውስጥ ስለሚጫወቱት ሚና የሚያሳዩ ሳምንታዊ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን ይመለከታሉ። አንድ የመጻሕፍት መደብር ስለ መላእክት የሚናገሩ ከ400 የሚበልጡ መጻሕፍት ዝርዝር አለው።
በቅርቡ የወጣ አንድ መጽሐፍ፣ ጠባቂ መላእክት በጦር ግንባር የተሰለፉ ወታደሮችን ሕይወት እንዴት እንደታደጉ የሚተርክ ዘገባ ይዞ ወጥቷል። በመኪና ላይ የሚለጠፉ ወረቀቶች ጠባቂ መላእክት የመኪና አሽከርካሪዎችን ከአደጋ እንደሚጠብቋቸው ይናገራሉ። ድርጅቶች፣ ትላልቅ ስብሰባዎችና ሴሚናሮች ስለ መላእክት ጥናት እንዲደረግ የሚያበረታቱ ከመሆናቸውም በላይ ሰዎች ከመላእክት ጋር እንዲገናኙ ይረዳሉ ይባላል።
ኢሌን ፍሪማን ስለ መላእክት የሚናገሩ ሦስት መጻሕፍት የደረሱና ስለ መላእክት ብቻ የሚናገር መጽሔት የሚያሳትሙ ሴት ናቸው። እንዲህ በማለት አስረግጠው ይናገራሉ:- “ብዛታቸው በሰማይ ካሉት መላእክት የማይተናነስ በርካታ ጠባቂ መላእክት በምድር ላይ አሉ፤ የእነዚህም መላእክት ሥራ በሰማይ አምላክን ማወደስ ሳይሆን ለሰዎችና በምድር ላይ ለሚኖሩ ሕይወት ላላቸው ለሌሎች ነገሮች ጥበቃ ማድረግ እንደሆነ አምናለሁ። ገና ስንጸነስ ጀምሮ ለእያንዳንዳችን አንድ ጠባቂ መልአክ ይመደብልንና ከዚህ ዓለም ክልል አሻግሮ ክብር ወደተጎናጸፈው ሰማይ እስኪያገባን ድረስ በማሕጸን ውስጥ እድገት ስናደርግ፣ ስንወለድ፣ በዚህ ዓለም ላይ በምናሳልፈው ሕይወት ሁሉ ጥበቃ ያደርግልናል።” ይህ ሐሳብ ብዙዎች ጠባቂ መላእክትን በሚመለከት ያላቸውን አመለካከት ጥሩ አድርጎ ይገልጻል።
ጭንቀትና መከራ በነገሠበት በዚህ ዘመን እኛን የመጠበቅ ሥራ የተሰጣቸው የየራሳችን ጠባቂ መላእክት አሉን ብሎ ማመኑ የሚያጽናና ነው። ይሁን እንጂ የአምላክ ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? ከመላእክት ጋር ለመገናኘት መሞከር ይኖርብናልን? መላእክት ስለ ሥነ ምግባር አቋማችንና ስለ ሃይማኖታዊ እምነታችን የሚገዳቸው ናቸው? ምን ዓይነት እርዳታስ ይሰጡናል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን? የሚቀጥለው ርዕስ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ይሰጣል።