መላእክት ሊረዱህ የሚችሉት እንዴት ነው?
የመላእክትን መኖር የአምላክ ቃል ያረጋግጥልናል። እነዚህ መንፈሳዊ ፍጥረታት በሚልዮን የሚቆጠሩ እንደሆኑም ይነግረናል። የይሖዋ አምላክ አገልጋይ የሆነው ዳንኤል በሰማይ ስላሉ ነገሮች ራእይ ከተመለከተ በኋላ “ሺህ ጊዜ ሺህ [አምላክን] ያገለግሉት ነበር፣ እልፍ አእላፋትም በፊቱ ቆመው ነበር” በማለት ጽፏል።—ዳንኤል 7:10
ዳንኤል በርካታ ቁጥር ያላቸው መላእክት መኖራቸውን ብቻ እንዳልነገረን ልብ በል። አምላክን እንደሚያገለግሉ ጭምር አመልክቷል። መላእክት የአምላክ አገልጋዮች ናቸው። ከዚህ ጋር በመስማማት መዝሙራዊው “ቃሉን የምትፈጽሙ፣ ብርቱዎችና ኃያላን፣ የቃሉንም ድምፅ የምትሰሙ መላእክቱ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ። ፍጥረቶቹ ሁሉ በግዛቱ ስፍራ ሁሉ፣ እግዚአብሔርን ባርኩ” በማለት ዘምሯል።—መዝሙር 103:20, 21
በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ መላእክት በሕይወት መኖር የጀመሩት ልክ እንደ ሰዎች በምድር ላይ አለመሆኑን ይገልጻል። እንዲያውም ይሖዋ ሰማይ ላይ መላእክትን የፈጠረው ምድርን ከመፍጠሩ በፊት ነው። አምላክ ‘ምድርን ሲመሠርት መላው መላእክታዊ የአምላክ ልጆች እልል ብለዋል።’—ኢዮብ 38:4-7
መላእክት በዓይን የማይታዩ፣ ከፍተኛ ኃይልና የማሰብ ችሎታ ያላቸው መንፈሳዊ ፍጥረታት ናቸው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈሳዊ ፍጥረትን ለማመልከት የሚሠራባቸው ማልአክ የሚለው የዕብራይስጥ ቃልና አግጄሎስ የሚለው የግሪክኛ ቃል “መልአክ” ተብለው ተተርጉመዋል። እነዚህ ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 400 ያህል ጊዜ ይገኛሉ። ሁለቱም ቃላት “መልእክተኛ” የሚል አንድ ዓይነት ትርጉም አላቸው።
ከመላእክት ጋር መገናኘት
መላእክት በእርግጥም መልእክተኞች ናቸው። መልአኩ ገብርኤል ለማርያም እንደተገለጠላት የሚናገረውን የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ አንብበህ ይሆናል። ድንግል ብትሆንም እንኳ ኢየሱስ ተብሎ የሚጠራ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት። (ሉቃስ 1:26-33) እንዲሁም አንድ መልአክ በሜዳ ላይ ተሰማርተው ለነበሩ እረኞች ተገልጧል። እርሱም “ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና” በማለት አብስሯቸዋል። (ሉቃስ 2:8-11) በተመሳሳይም መላእክት ለአጋር፣ ለአብርሃም፣ ለሎጥ፣ ለያዕቆብ፣ ለሙሴ፣ ለጌዴዎን፣ ለኢየሱስና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ለሚገኙት ለሌሎች ሰዎች መልእክት አድርሰዋል።—ዘፍጥረት 16:7-12፤ 18:1-5, 10፤ 19:1-3፤ 32:24-30፤ ዘጸአት 3:1, 2፤ መሳፍንት 6:11-22፤ ሉቃስ 22:39-43፤ ዕብራውያን 13:2
መላእክት ያደረሷቸው እነዚህ ሁሉ መልእክቶች ከአምላክ ዓላማ አፈጻጸም ጋር የሚስማሙ እንጂ መልእክቱ የደረሳቸውን ሰዎች ዓላማ የሚያራምዱ እንዳልሆኑ ልብ ማለት ያስፈልጋል። መላእክት በአምላክ ፈቃድና እርሱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት አምላክን ወክለው ተገልጠዋል። ወደ ምድር የሚመጡት ሰዎች እየጠሯቸው አይደለም።
መላእክትን ለእርዳታ መጥራት ይኖርብናል?
በጭንቅ ጊዜ መላእክትን ለእርዳታ መጥራት ተገቢ ነውን? ከሆነ ፈጥኖ የሚደርስልንን መልአክ ስም ብናውቅ ደስ ይለናል። ከዚህም የተነሳ አንዳንድ የንግድ መጻሕፍት ደረጃቸውን፣ ማዕረጋቸውንና የሥራ ኃላፊነታቸውን ጨምሮ የብዙ መላእክትን ስም ዝርዝር ያወጣሉ። አንድ መጽሐፍ “በሰማይ ግንባር ቀደም የሆኑ” እና “በምዕራቡ ዓለም በጣም የታወቁ መላእክት” ብሎ የጠራቸውን የመላእክት ስም በዝርዝር አስፍሯል። ከዝርዝሩም ጋር ዓይንህን እንድትጨፍን፣ የመልአኩን ስም በዝግታ ብዙ ጊዜ ደጋግመህ እንድትጠራ፣ ወደ ውስጥ ትንፋሽ እንድትስብ፣ ቀስ ብለህ ወደ ውጭ ትንፋሽ እንድታስወጣና በመጨረሻም “ዓይንህን ገልጠህ ከእነርሱ ጋር እንድትገናኝ” ምክር ለግሷል።
መጽሐፍ ቅዱስ ግን ከአምላክ ታማኝ መላእክት መካከል የሁለቱን ስም ብቻ ይገልጻል፤ እነርሱም ሚካኤልና ገብርኤል ናቸው። (ዳንኤል 12:1፤ ሉቃስ 1:26) የእነዚህ መላእክት ስሞች የተጠቀሱት እያንዳንዱ መልአክ መጠሪያ ስም ያለውና ራሱን የቻለ መንፈሳዊ አካል እንጂ ስብዕና የሌለው ኃይል አለመሆኑን ለማስገንዘብ ሊሆን ይችላል።
አንዳንድ መላእክት ስማቸውን ለሰዎች ለመግለጥ ፈቃደኞች አለመሆናቸው ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ነገር ነው። ያዕቆብ አንድን መልአክ ስምህን ንገረኝ ብሎ በጠየቀው ጊዜ መልአኩ ሊነግረው ፈቃደኛ አልሆነም። (ዘፍጥረት 32:29) ኢያሱ ወደ እርሱ ቀርቦ የነበረው መልአክ ማንነቱን እንዲገልጥለት በጠየቀው ጊዜ “የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ” በማለት ብቻ መልሶለታል። (ኢያሱ 5:14) የሳምሶን ወላጆች አንድ መልአክ ስሙን እንዲነግራቸው በጠየቁት ጊዜ መልአኩ “ስሜ ድንቅ ነውና ለምን ትጠይቃለህ?” ሲል መልሷል። (መሳፍንት 13:17, 18) መጽሐፍ ቅዱስ የመላእክትን ስም ዝርዝር አለማስፈሩ ለመላእክት ተገቢ ያልሆነ ክብርና አምልኮ እንዳንሰጥ ይጠብቀናል። ቀጥለን እንደምናየውም እነርሱን እንድንለማመን አያዘንም።
ወደ አምላክ መጮኽ
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ መንፈሳዊው ዓለም ማወቅ የሚያስፈልገንን ያክል ይነግረናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “የእግዚአብሔር ሰው ፍጹምና ለበጎ ሥራ ሁሉ የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለበት መጽሐፍ ሁሉ ለትምህርት . . . ይጠቅማል” በማለት ጽፏል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17) አምላክ የብዙ መላእክትን ስሞች እንድናውቅ የሚፈልግ ቢሆን ኖሮ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በዝርዝር ያሰፍርልን ነበር። እንዲሁም ከመላእክት ጋር እንዴት ልንገናኝ እንደምንችልና በጸሎት እንዴት ልናነጋግራቸው እንደምንችል እኛን ማስተማር ቢፈልግ ኖር በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ በቂ መረጃ ያሰፍር ነበር።
ከዚያ ይልቅ ኢየሱስ ክርስቶስ “አንተ ግን ስትጸልይ፣ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ . . . እንግዲህ እናንተስ እንዲህ ጸልዩ:- በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ” በማለት አስተምሯል። (ማቴዎስ 6:6, 9) ቅዱሳን ጽሑፎች ያላቸው አመለካከት የሚከተለው ነው:- ወደ መላእክት መጮኽም ሆነ ጸሎት ማቅረብ አይኖርብንም፤ ከዚያ ይልቅ በጸሎት መቅረብ ያለብን የመላእክት ፈጣሪ ወደሆነው ወደራሱ ወደ አምላክ ነው። የአምላክ ስም ምስጢራዊ አይደለም፤ ስሙንም ለማወቅ ራእይ ማየት አያስፈልገንም። ምንም እንኳ መለኮታዊውን ስም ለማድበስበስ ሙከራ የተደረገ ቢሆንም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከ7,000 ጊዜ በላይ ሰፍሮ ይገኛል። ለምሳሌ ያህል መዝሙራዊው “ስምህ ይሖዋ የሆነው አንተ፣ በምድር ሁሉ ላይ አንተ ብቻ ልዑል እንደሆንክ ሰዎች ሁሉ ይወቁ” በማለት መዝሙርን የዘመረው ለሰማያዊው አባት ነው።—መዝሙር 83:18 NW
ይሖዋ ተገቢ በሆነ መንገድ በጸሎት ወደ እሱ እስከቀረብን ድረስ ጸሎታችሁን ለመስማት ጊዜ የለኝም አይልም። መጽሐፍ ቅዱስ “እግዚአብሔር ልቡ በእርሱ ዘንድ ፍጹም የሆነውን ያጸና ዘንድ ዓይኖቹ በምድር ሁሉ ይመለከታሉና” በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል።—2 ዜና መዋዕል 16:9
መላእክትና ስነ ምግባር
በዜና ማሰራጫዎች ዘወትር እንደሚነገረው መላእክት በሰዎች ላይ አይፈርዱም። ደግሞም በሰዎች ላይ እንዲፈርዱ ሥልጣን አልተሰጣቸውም። ምንም እንኳ “ፍርድን ሁሉ ለወልድ” ማለትም ለኢየሱስ ክርስቶስ ቢሰጠውም “የሁሉም ዳኛ” ይሖዋ ነው። (ዕብራውያን 12:23፤ ዮሐንስ 5:22) ሆኖም መላእክት ስለ እኛ ሕይወት ምንም ደንታ የላቸውም ብሎ ማሰብ ስህተት ነው። ኢየሱስ “እንዲሁ ንስሐ በሚገባ በአንድ ኃጢአተኛ በእግዚአብሔር መላእክት ፊት ደስታ ይሆናል” በማለት ተናግሯል።—ሉቃስ 15:10
መላእክት እንዲሁ ዳር ቆመው የሚመለከቱ አይደሉም። ባለፉት ጊዜያት መላእክት የአምላክን ፍርድ በማስፈጸም ረገድ የቅጣት እርምጃ በመውሰድ አገልግለዋል። ለምሳሌ ያህል አምላክ የጥንት ግብፃውያንን ለማጥፋት መላእክትን ተጠቅሟል። መዝሙር 78:49 እንደሚናገረው “የመዓቱን መቅሠፍት በላያቸው ሰደደ፤ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ” ይላል። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስ በአንድ ምሽት 185,000 የሦርያ ወታደሮችን ስለ ገደለ አንድ መልአክ ይናገራል።—2 ነገሥት 19:35
በተመሳሳይም ወደፊት መላእክት ከአምላክ የጽድቅ አቋም ጋር ተስማምተው ለመሄድ አሻፈረኝ በማለት በሌሎች ደህንነት ላይ አደጋ የሚያስከትሉ ሰዎችን ይደመስሳሉ። ኢየሱስ “ከሥልጣኑ መላእክት ጋር ከሰማይ በእሳት ነበልባል ሲገለጥ፣ . . . እግዚአብሔርን የማያውቁትን፣ ለጌታችንም ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል የማይታዘዙትን ይበቀላል።”—2 ተሰሎንቄ 1:6-8
በዚህም የተነሳ የአምላክ ታማኝ መላእክት የአምላክን መመሪያዎች በማስፈጸምና የጽድቅ የአቋም ደረጃዎቹን በማስከበር ሁልጊዜ ፈቃዱን እንደሚፈጽሙ ቅዱሳን ጽሑፎች ያሳያሉ። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው የአምላክ መላእክት እንዲረዱን የምንፈልግ ከሆነ የአምላክ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማወቅና በተግባር ለመተርጎም ከልብ መጣጣር ይኖርብናል።
ጠባቂ መላእክት
መላእክት ለሰዎች እንክብካቤና ጥበቃ ያደርጉላቸዋልን? ሐዋርያው ጳውሎስ “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” በማለት ጠይቋል። (ዕብራውያን 1:14) ጳውሎስ ላቀረበው ጥያቄ መልሱ አዎን የሚል እንደሚሆን የታወቀ ነው።
ባቢሎናዊው ንጉሥ ናቡከደነፆር ላቆመው የወርቅ ምስል ለመስገድ እምቢ በማለታቸው ምክንያት ሲድራቅ፣ ሚሳቅ እና አብደናጎ የተባሉት ሦስት ዕብራውያን በእቶን እሳት ውስጥ ተጥለው ነበር። ይሁን እንጂ እሳቱ በእነዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች ላይ ምንም ዓይነት ጉዳት አላስከተለባቸውም። ንጉሡ ወደ ምድጃው ሲያይ “አራት ሰዎች” ተመለከተ። ከዚያም “የአራተኛውም መልክ የአማልክትን ልጅ ይመስላል” በማለት ተናገረ። (ዳንኤል 3:25) ከጥቂት ዓመታት በኋላ ዳንኤል በታማኝነት አቋሙ ምክንያት አንበሶች ያሉበት ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ነበር። እርሱም ቢሆን ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስበት ድኗል። “አምላኬ መልአኩን ልኮ የአንበሶችን አፍ ዘጋ” በማለት ተናግሯል።—ዳንኤል 6:22
በመጀመሪያው መቶ ዘመን እዘአ የክርስቶስ ተከታዮች ጉባኤ በተመሠረተ ጊዜ መላእክት ዳግመኛ ተገልጠው ሐዋርያትን ከእስር ቤት አስፈትተዋል። (ሥራ 5:17-24፤ 12:6-12) እንዲሁም ጳውሎስ በባሕር ላይ እየተጓዘ ሳለ ሕይወቱ አደጋ ላይ ወድቆ በነበረ ጊዜ ምንም ሳይሆን ሮም እንደሚደርስ አንድ መልአክ ማረጋገጫ ሰጥቶት ነበር።—ሥራ 27:13-24
በዛሬው ጊዜም የሚኖሩ የይሖዋ አምላክ አገልጋዮች በዓይን የማይታዩት የአምላክ መላእክታዊ ኃይሎች እውን እንደሆኑና ለኤልሳዕና ለሎሌው እንዳደረጉት ሁሉ ጥበቃ እንደሚያደርጉላቸው ሙሉ እምነት አላቸው። (2 ነገሥት 6:15-17) በእርግጥም “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎቸ ዙሪያ ይሰፍራል፣ ያድናቸውማል።”—መዝሙር 34:7፤ 91:11
መላእክት የሚያሰራጩት መልእክት
መላእክት የይሖዋ አምላክን አገልጋዮች ደህንነት ከመጠበቃቸውም ባሻገር ሰዎች ስለ ይሖዋና ስለ ዓላማው በመማር ላይ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ይፈልጋሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ፤ በታላቅ ድምፅም:- የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት” በማለት ጽፏል።—ራእይ 14:6, 7
ይህ “የዘላለም ወንጌል” ምን ነገሮችን እንደያዘ ለማወቅ ትፈልጋለህ? ከሆነ የይሖዋ ምሥክሮችን ጠይቃቸው። በደስታ ይነግሩሃል።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
በሰማይ መካከል ያለ አንድ መልአክ የዘላለሙን ምሥራች እያወጀ ነው። ስለዚህ ምሥራች ለማወቅ ትፈልጋለህ?