የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 11/15 ገጽ 21-24
  • መቃብያን እነማን ነበሩ?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መቃብያን እነማን ነበሩ?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የሄለናዊነት ማዕበል
  • የካህናቱ ምግባረ ብልሹ መሆን
  • አንቲዮከስ እርምጃ ወሰደ
  • የመቃብያን ተቃውሞ
  • ቤተ መቅደሱን አስመለሱ
  • ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ሲይዝ
  • ሃስሞናውያንና ትተው ያለፉት ቅርስ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2001
  • ክፍል 10:- ከ537 ከዘአበ ጀምሮ አሁንም መሲሕን ይጠብቃሉ
    ንቁ!—1994
  • ሁለት ተቀናቃኝ ነገሥታት
    የዳንኤልን ትንቢት በትኩረት ተከታተል!
  • ብርሃን ሲመጣ የጨለማ ዘመን አከተመ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1996
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 11/15 ገጽ 21-24

መቃብያን እነማን ነበሩ?

ለብዙዎች መቃብያን የኖሩበት ዘመን የመጨረሻዎቹ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ተጽፈው በተጠናቀቁበትና በኢየሱስ ክርስቶስ መምጣት መካከል ስለነበረው ጊዜ መረጃ እንደያዘ ጥቁር ሣጥን ነው። የአውሮፕላን አደጋ ከደረሰ በኋላ አውሮፕላኑ በበረራ ላይ በነበረበት ጊዜ ስለተከናወነው ሁኔታ መረጃ ለመሰብሰብ የሚያገለግለውን ጥቁር ሣጥን የሚባለውን መሣሪያ በመመርመር የተወሰኑ ዝርዝር መረጃዎችን ማግኘት እንደሚቻል ሁሉ ለአይሁድ ብሔር የሽግግርና የለውጥ ጊዜ የነበረውን የመቃብያንን ዘመን በመመርመርም አንዳንድ ነገሮችን ማስተዋል ይቻላል።

መቃብያን እነማን ነበሩ? በትንቢት የተነገረው መሲሕ ከመምጣቱ በፊት በአይሁድ እምነት ላይ ተጽእኖ ያሳደሩት እንዴት ነበር?​—⁠ዳንኤል 9:​25, 26

የሄለናዊነት ማዕበል

ታላቁ እስክንድር ከግሪክ አንስቶ እስከ ሕንድ ድረስ የሚገኙ የግዛት ክልሎችን (336–323 ከዘአበ) ድል አድርጎ ያዘ። ሰፊ የግዛት ክልሉ ለሄለናዊነት ማለትም ለግሪክ ቋንቋና ባህል መስፋፋት ምክንያት ሆኖ ነበር። የእስክንድር መኮንኖችና ወታደሮች በአካባቢው የሚገኙ ሴቶችን አገቡ፤ ይህ ደግሞ የግሪክና የባዕድ አገር ባህሎች እንዲቀላቀሉ አደረገ። ከእስክንድር ሞት በኋላ የጦር መኮንኖቹ ግዛቱን ተከፋፈሉት። በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጀመሪያ ላይ በሶሪያ የሚገኘው የግሪኩ የሴሌውከስ ሥርወ መንግሥት ገዥ አንቲዮከስ 3ኛ በግብጽ ከሚገኙት የግሪክ ታልሚዎች (ነገሥታት) እስራኤልን ቀምቶ ያዘ። በእስራኤል የነበሩት አይሁዶች በሄለናውያን አገዛዝ ምን ተጽእኖ ደርሶባቸው ነበር?

አንድ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “አይሁዳውያን ወደዱም ጠሉ ውሎአቸው ሁሉ ከሄለናውያን ጎረቤቶቻቸው ጋር ከመሆኑም ሌላ የግሪክ ባህል ተጽእኖ ካሳደረባቸው በውጭ ካሉት ወንድሞቻቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማስቀረት የማይታሰብ ነገር በመሆኑ የግሪካውያኑን ባሕልና የአስተሳሰብ ዘይቤ መቅዳታቸው አይቀሬ ነበር። . . . በሄለናውያን ዘመን መኖሩ ብቻ የግሪክን ባህል መቀበልን የሚያጠቃልል ነበር!” አይሁዳውያን በግሪክ ስሞች መጠራት ጀመሩ። ደረጃው ይለያይ እንጂ የግሪክን ባህልና የአለባበስ ሥርዓት መከተል ጀመሩ። ተቀላቅለው እንዲኖሩ በረቀቀ ሁኔታ የሚደርስባቸው ግፊት እያየለ ነበር።

የካህናቱ ምግባረ ብልሹ መሆን

ከአይሁዳውያኑ መካከል ለሄለናዊ ተጽእኖ ይበልጥ የተጋለጡት ካህናቱ ነበሩ። በብዙዎቹ ካህናት ሄለናዊነትን መቀበል የአይሁድ እምነት ከጊዜው ጋር እንዲራመድ ማድረግ ነው የሚል አስተሳሰብ ነበራቸው። ይህን የመሰለ አስተሳሰብ ከነበራቸው አይሁዳውያን መካከል አንዱ የሊቀ ካህናቱ የኦኒየስ 3ኛ ወንድም የሆነው ጄሰን (በዕብራይስጥ ጀሹዋ) ነበር። ኦኒየስ ወደ አንጾኪያ ሄዶ በነበረበት ጊዜ ጄሰን ለግሪክ ባለ ሥልጣናት ጉቦ አቀረበላቸው። ለምን? በኦኒየስ ምትክ ሊቀ ካህናት አድርገው እንዲሾሙት ለማግባባት ነበር። የግሪኩ ሴሌውከስ ገዥ የሆነው አንቲዮከስ ኤፒፋነስ (175–164 ከዘአበ) የቀረበለትን ሐሳብ ያለ ምንም ማንገራገር ተቀበለ። ከዚህ ቀደም ግሪካውያን ገዥዎች በአይሁዳውያን ከፍተኛ የክህነት አገልግሎት ውስጥ እጃቸውን አስገብተው ባያውቁም አንቲዮከስ ለወታደራዊ ዘመቻው ማካሄጃ የሚሆን ገንዘብ ይፈልግ ነበር። በተጨማሪም ሄለናዊነትን ይበልጥ በንቃት የሚያስፋፋ አይሁዳዊ መሪ በማግኘቱ ተደስቶ ነበር። በጄሰን ጠያቂነት ኢየሩሳሌም እንደ አንድ የግሪክ ከተማ (ፓሊስ) ተደርጋ እንድትቆጠር አንቲዮከስ ፈቀደ። በተራው ደግሞ ጄሰን ካህናትን ጨምሮ ወጣት አይሁዳውያን በጨዋታዎች የሚወዳደሩበት የስፖርት ማዕከል ገነባ።

ክህደት ክህደትን እየወለደ ሄደ። ከሦስት ዓመት በኋላ ሜነለስ የሚባል (የክህንነት ዘር የሌለው ሰው ሳይሆን አይቀርም) ከፍተኛ ጉቦ በመስጠቱ ጄሰን ሸሸ። ሜነለስ ለአንቲዮከስ ለመክፈል ሲል በርካታ ገንዘብ ከቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ወሰደ። (በአንጾኪያ በግዞት የሚገኘው) ኦኒየስ 3ኛ ይህን ድርጊት በመቃወሙ ሜነለስ እሱ የሚገደልበትን መንገድ አቀነባበረ።

አንቲዮከስ ሞቷል የሚል ጭምጭምታ በሰማ ጊዜ ጄሰን የሊቀ ክህንነቱን ቦታ ከሜነለስ ለመውሰድ አንድ ሺህ ወንዶችን አስከትሎ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሰ። ሆኖም አንቲዮከስ አልሞተም ነበር። አንቲዮከስ የጄሰንን እንቅስቃሴና ሄለናዊነትን ለማስፋፋት ያወጣቸውን ፖሊሲዎች በመቃወም በአይሁዳውያን መካከል የተፈጠረውን ግርግር ሲሰማ የኃይል እርምጃ ወሰደ።

አንቲዮከስ እርምጃ ወሰደ

ሞሼ ፐርልማን ዘ ማካቢስ በተባለው መጽሐፋቸው ላይ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “የታሪክ መዝገቦች በግልጽ አይናገሩ እንጂ አንቲዮከስ ለአይሁዳውያን የሃይማኖት ነፃነት መስጠት ፖለቲካዊ ስህተት ነው ብሎ ሳይደመድም አልቀረም። በእሱ ግምት በቅርቡ በኢየሩሳሌም የተቀሰቀሰው ዓመፅ ከንጹሕ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ የመነጨ ሳይሆን በይሁዳ ሰፍኖ ከሚገኘው አፍቃሬ ግብጽ ከሆነው አስተሳሰብ የመነጨ ሲሆን እነዚህ ፖለቲካዊ አመለካከቶች አደገኛ እየሆኑ የመጡት ደግሞ ከሕዝቦቹ መካከል ሃይማኖታዊ ነፃነት እንዲኖራቸው የጠየቁትና ይህም የተፈቀደላቸው አይሁዳውያን ብቻ በመሆናቸው ነበር። . . . ይህ መቆም አለበት ሲል ወሰነ።”

እስራኤላዊው የፖለቲካ ሰውና ምሁር አባ ኢበን እንደሚከተለው በማለት ፍሬ ነገሩን በአጭሩ አስቀምጠዋል:- “በ168 እና በ167 [ከዘአበ] ተከታታይ ዓመታት አይሁዳውያን ተጨፈጨፉ፤ ቤተ መቅደሱ ተዘረፈ፤ የአይሁድ ሃይማኖትን መከተል ተከለከለ። መገረዝና ሰንበትን መጠበቅ በሞት የሚያስቀጡ ወንጀሎች ሆኑ። ከፍተኛው የንቀት ተግባር የተፈጸመው በታኅሣሥ 167 ሲሆን በአንቲዮከስ ትእዛዝ ለዘዩስ መሠዊያ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ተሠራ፤ አይሁዳውያን ደግሞ በአይሁድ ሕግ ርኩስ የሆነውን የእሪያ ሥጋ ለግሪኮች አምላክ መሥዋዕት አድርጎ የማቅረብ ግዳጅ ተጣለባቸው።” በዚህ ወቅት ሜነለስና ሄለናዊነትን የተቀበሉ ሌሎች አይሁዶች በዚህ በረከሰ ቤተ መቅደስ ውስጥ በየፊናቸው ሃይማኖታዊ ሥርዓታቸውን ማከናወን ቀጠሉ።

ብዙ አይሁዶች ሄለናዊነትን ቢቀበሉም ራሱን ሀሲዲም ብሎ የሚጠራ አንድ አዲስ የሃይማኖተኞች ቡድን የሙሴን ሕግ በጥብቅ መከተልን ያበረታታ ነበር። ተራው ሕዝብ ሄለናዊነትን የተቀበሉትን ካህናት እየተጸየፈ ከጊዜ ወደ ጊዜ ከሀሲዲሞች ጎን እየወገነ መጣ። በመላው አገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አይሁዶች አረማዊ ወጎችን እንዲከተሉና መሥዋዕቶችን እንዲያቀርቡ ይገደዱ አሊያም ይገደሉ ስለነበረ ጊዜው የሰማዕትነት ወቅት ሆኖ ነበር። የመቃብያን አዋልድ መጻሕፍት አቋማቸውን ከመለወጥ ይልቅ ሞትን ስለመረጡ በርካታ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ታሪክ ይናገራሉ።

የመቃብያን ተቃውሞ

አንቲዮከስ የወሰደው ከፍተኛ የጥቃት እርምጃ ብዙ አይሁዶች ለሃይማኖታቸው እንዲዋጉ አነሳስቷል። በኢየሩሳሌም ሰሜን ምዕራብ በዘመናዊቷ የሎድ ከተማ አቅራቢያ በምትገኘው በሞዲን፣ ማታቲያስ ተብሎ የሚጠራ አንድ ካህን ወደ መንደሩ ማዕከል ተጠራ። ማታቲያስ በአካባቢው ሕዝብ የተከበረ በመሆኑ የንጉሡ ተወካይ የራሱን ሕይወት ለማዳንና ለተቀረው ሕዝብ ምሳሌ እንዲሆን ሲል አረማዊ መሥዋዕት በማቅረብ እንዲካፈል ሊያግባባው ሞከረ። ማታቲያስ ፈቃደኛ ሳይሆን ሲቀር አንድ ሌላ አይሁዳዊ አቋሙን ለመለወጥ ዝግጁ ሆኖ ወደፊት ቀረብ አለ። ማታቲያስ እጅግ ከመናደዱ የተነሣ መሣሪያ ቀምቶ ገደለው። ይህ አዛውንት በፈጸመው የኃይል ድርጊት በመደናገጥ የግሪክ ወታደሮች ፈዝዘው ቀሩ። በሴኮንዶች ውስጥ ማታቲያስ የግሪክ ባለ ሥልጣናቱን ጭምር ገደለ። የግሪክ ወታደሮች የመከላከል እርምጃ ከመውሰዳቸው በፊት የማታቲያስ አምስት ልጆችና የመንደሪቱ ነዋሪዎች በቁጥጥራቸው ሥር አደረጓቸው።

ማታቲያስ ‘ለሕጉ ቀናተኛ የሆነ ሰው ሁሉ ይከተለኝ’ ሲል ጮኸ። ሊወሰድባቸው ከሚችለው የበቀል እርምጃ ለማምለጥ ሲሉ እሱና ልጆቹ ወደ ኮረብታማው አገር ሸሹ። የእንቅስቃሴያቸው ወሬ ሲሰማ (ብዙ ሀሲዲሞችን ጨምሮ) አይሁዶች ተባበሯቸው።

ማታቲያስ ልጁን ጁዳን በወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ኃላፊ አድርጎ ሾመው። ጁዳ በነበረው ወታደራዊ ችሎታ ሳይሆን አይቀርም መቃብ ተብሎ ተጠራ፤ ትርጉሙም “መዶሻ” ማለት ነው። ማታቲያስና ልጆቹ ሃስሞኔያውያን ተብለው ይጠሩ የነበረ ሲሆን ይህ ስም ሐሽሞን ከሚባለው መንደር ወይም በዚህ ስም ይጠራ ከነበረ አንድ ቅድመ አያት የተገኘ ነበር። (ኢያሱ 15:​27) ይሁን እንጂ ጁዳ መቃብ በዚህ የዓመፅ እንቅስቃሴ ታዋቂነትን በማግኘቱ ቤተሰቡ በሙሉ መቃብያን ተብለው መጠራት ጀመሩ።

ቤተ መቅደሱን አስመለሱ

ዓመፁ በጀመረበት ዓመት ማታቲያስና ልጆቹ አንድ አነስተኛ ሠራዊት ለማደራጀት ችለው ነበር። ከአንድ ጊዜ በላይ የግሪክ ወታደሮች በሀሲዲም ተዋጊ ቡድኖች ላይ በሰንበት ቀን ጥቃት ሰንዝረውባቸው ነበር። ሀሲዲሞች ራሳቸውን የመከላከል አቅም ቢኖራቸውም እንኳ ሰንበትን አይጥሱም ነበር። በዚህ ምክንያት ብዙ ሰዎች ተጨፈጨፉ። በወቅቱ እንደ ሃይማኖታዊ ባለ ሥልጣን ተደርጎ ይታይ የነበረው ማታቲያስ አይሁዳውያን በሰንበት ቀን ራሳቸውን ለመከላከል የሚያስችላቸውን ደንብ አወጣ። ይህ ደንብ ለዓመፁ አዲስ ሕይወት ከመስጠቱም በላይ ሃይማኖታዊ መሪዎች የአይሁድን ሕግ ከሁኔታዎች ጋር ለማስማማት ሲሉ ለውጥ እንዲያደርጉ የሚያስችል መሠረት ሆኗቸዋል። ታልሙድ ይህን አስመልክቶ እንዲህ ብሏል:- “ብዙ ሰንበቶችን መቀደስ ይችሉ ዘንድ አንድ ሰንበትን ይሻሩ።”​—⁠ዮማ 85ለ

ጁዳ መቃብ አረጋዊው አባቱ ከሞተ በኋላ የዓመፅ ንቅናቄው ተቀናቃኝ የሌለው መሪ ሆነ። ጠላቱን ፊት ለፊት ገጥሞ የማሸነፍ አቅም እንደሌለው በመገንዘብ በዘመናችን ከሚካሄዱት የደፈጣ ውጊያዎች ጋር የሚመሳሰሉ አዳዲስ የውጊያ ስልቶችን ቀየሰ። የአንቲዮከስን ኃይሎች በተለመደው የመከላከያ ዘዴዎቻቸው መጠቀም በማይችሉባቸው ቦታዎች ላይ ጥቃት አደረሰባቸው። በዚህ ሁኔታ ጁዳ በተከታታይ በተደረጉ ውጊያዎች ከእሱ ኃይል እጅግ የሚበልጡ ኃይሎችን ለማሸነፍ ቻለ።

የሴሌውከስ ግዛት ገዥዎች፣ የውስጥ ተቀናቃኝና ገናና እየሆነ የመጣው የሮም ኃይል ተነስቶባቸው ስለነበረ ፀረ-አይሁድ ድንጋጌዎች የማስፈጸሙን ጉዳይ ችላ ብለውት ነበር። ይህ ሁኔታ ጁዳ ጥቃቱን እስከ ኢየሩሳሌም በሮች ድረስ እንዲገፋበት አስችሎታል። በታኅሣሥ 165 ከዘአበ (ወይም 164 ከዘአበ አካባቢ) እሱና ሠራዊቱ ቤተ መቅደሱን ተቆጣጠሩ፤ እቃዎቹን አጸዱ፣ ከዚያም ቤተ መቅደሱ እንዲረክስ በተደረገ ልክ በሦስተኛ ዓመቱ ዳግመኛ ለአምላክ እንዲወሰን አደረጉ። አይሁዶች በየዓመቱ በሃኑካ ማለትም በመቅደስ መታደስ በዓል ላይ ይህን ክንውን አስበውት ይውላሉ።

ሃይማኖታዊ እንቅስቃሴ ፖለቲካዊ አቅጣጫ ሲይዝ

ዓመፁ የተቀሰቀሰበት ዓላማ ግቡን መትቷል። በአይሁድ ሃይማኖት ላይ ተጥለው የነበሩ ማዕቀቦች ተነሱ። በቤተ መቅደሱ ውስጥ አምልኮ ማከናወንና መሥዋዕት ማቅረብ እንደገና ተጀመረ። ሀሲዲሞች በዚህ በመርካታቸው የጁዳ መቃብን ሠራዊት ትተው ወደ ቤታቸው ተመለሱ። ሆኖም ጁዳ ሌሎች ውጥኖች ነበሩት። በሚገባ የሰለጠነ ሠራዊት አለው፤ ታዲያ ለምን ራሱን የቻለ የአይሁድ መንግሥት ለማቋቋም አይጠቀምበትም? ዓመፁ እንዲቀሰቀስ ያደረጉት ሃይማኖታዊ ምክንያቶች አሁን በፖለቲካዊ ትልሞች ተተኩ። ስለዚህ ትግሉ ቀጠለ።

ጁዳ መቃብ የሴሌውከስን የበላይነት በመቃወም ለሚያደርገው ውጊያ ድጋፍ ለማግኘት ሲል ከሮም ጋር ስምምነት ተፈራረመ። በ160 ከዘአበ በውጊያ ላይ እንዳለ ቢገደልም ወንድሞቹ ትግሉን ቀጠሉ። የጁዳ ወንድም ጆናታን በዘዴ ነገሮችን በእጁ ውስጥ በማስገባት የይሁዳ ሊቀ ካህናትና ገዥ መሆኑን የሴሌውከስ ገዥዎች እንዲቀበሉ አደረገ፤ ሆኖም አሁንም ቢሆን በእነሱ የበላይነት ሥር ነበር። ጆናታን በሶሪያ ሴራ ተታልሎ በተያዘና በተገደለ ጊዜ ከመቃብያን ወንድሞች የመጨረሻ የሆነው ወንድሙ ስምዖን ቦታውን ወሰደ። በስምዖን አገዛዝ ሥር የሴሌውከስ የበላይነት (በ141 ከዘአበ) ሙሉ በሙሉ ተወገደ። ስምዖን ከሮም ጋር የነበረውን ትብብር አደሰ፤ የአይሁድ አመራርም ገዥና ሊቀ ካህናት አድርጎ ተቀበለው። በዚህ መንገድ ራሱን የቻለ የሃስሞናውያን ሥርወ መንግሥት በመቃብያን እጅ ተቋቋመ።

መቃብያን መሲሑ ከመምጣቱ በፊት በቤተ መቅደሱ የሚከናወነው አምልኮ እንደገና እንዲጀመር አድርገዋል። (ከዮሐንስ 1:​42, 43፤ 2:​13–17 ጋር አወዳድር።) ሆኖም ሄለናዊነትን በተቀበሉ ካህናት ድርጊት ምክንያት ሰዎች በክህንነቱ ላይ የነበራቸው ትምክህት ተዳክሞ እንደነበረ ሁሉ በሀስሞናውያን ጊዜ ደግሞ ከዚያ የከፋ ሆኗል። በእርግጥም በታመነው ንጉሥ በዳዊት መስመር በመጣ ሰው ሳይሆን ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ባላቸው ካህናት መመራት ለአይሁድ ብሔር እውነተኛ በረከቶች አላስገኘለትም።​—⁠2 ሳሙኤል 7:​16፤ መዝሙር 89:​3, 4, 35, 36

[በገጽ 21 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

የጁዳ መቃብ አባት ማታቲያስ ‘ለሕጉ ቀናተኛ የሆነ ሰው ሁሉ ይከተለኝ’ ሲል ጮኸ

[ምንጭ]

ማታቲያስ አይሁዳውያን ስደተኞች እንዲከተሉት ሲማጸን/The Doré Bible Illustrations/Dover Publications

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ