ብርሃን ሲመጣ የጨለማ ዘመን አከተመ
ኢየሱስ ክርስቶስ እና ሐዋርያቱ የነበሩበት ዘመን ከዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ዘመን በጣም የተለየ ነበር። ይህን የማያውቁ የመጽሐፍ ቅዱስ አንባብያን በሚልክያስና በማቴዎስ መካከል የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ ጽሑፎች ያልተጻፉባቸው 400 ዓመታት ካለማወቃቸው የተነሣ ማኅበራዊና ሃይማኖታዊ ሁኔታዎች ከነቢዩ ሚልክያስ ዘመን ወደ ወንጌል ጸሐፊው ማቴዎስ ዘመን እንዳሉ የቀጠሉ ይመስላቸው ይሆናል።
በአሁኑ ጊዜ በሚገኙ በአብዛኞቹ መጽሐፍ ቅዱሶች ውስጥ የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች የመጨረሻ መጽሐፍ የሆነው ሚልክያስ እስራኤላውያን ቀሪዎች ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ከወጡ በኋላ ወደ ትውልድ አገራቸው ተመልሰው እንደ ሰፈሩ በመግለጽ ይደመድማል። (ኤርምያስ 23:3) ለአምላክ ያደሩ አይሁዳውያን ክፋት ከዓለም የሚወገድበትንና መሲሕ የሚመጣበትን ዘመን እንዲጠብቁ ማበረታቻ ተሰጣቸው። (ሚልክያስ 4:1, 2) በዚያ ወቅት የፋርስ መንግሥት ይገዛ ነበር። በይሁዳ የሠፈሩት የፋርሳውያን ወታደሮች ሰላም ከማስከበራቸውም በተጨማሪ በወታደራዊ ኃይል ተጠቅመው የንጉሡን ትእዛዞች ያስፈጽሙ ነበር።—ከዕዝራ 4:23 ጋር አወዳድር።
ሆኖም በቀጣዮቹ አራት መቶ ዘመናት የመጽሐፍ ቅዱስ አገሮች የተረጋጋ ሕይወት መምራት አልቻሉም። መንፈሳዊ ጨለማና ግራ መጋባት ጀምሮ ነበር። ቅርብ ምሥራቅ በዓመፅ፣ በሽብርተኝነት፣ በጭቆና፣ ሥር ነቀል በሆነ ሃይማኖታዊ አስተሳሰብ፣ በፍልስፍና እና ግራ በሚያጋባ እንግዳ ባሕል ተናውጣ ነበር።
የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የመጀመሪያው መጽሐፍ የሆነው ማቴዎስ የተጻፈው ለየት ባለ ዘመን ነበር። የሮም ክፍለ ጦሮች ፓክስ ሮማናን ወይም የሮም መንግሥትን ሰላም ያስከብሩ ነበር። የሃይማኖት ሰዎች መሲሕ ሥቃይን፣ የጭቆና አገዛዝንና ድህነትን ለማጥፋት እንዲሁም ስለ ሕይወት፣ ስለ ሰላምና ብልጽግና ብርሃን ለመፈንጠቅ የሚመጣበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር። (ከሉቃስ 1:67-79፤ 24:21፤ 2 ጢሞቴዎስ 1:10 ጋር አወዳድር።) ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ በፊት በነበሩት መቶ ዘመናት የአይሁድ ማኅበረሰብን ሕይወት አዲስ ቅርጽ ያስያዙትን ኃይለኛ ተጽዕኖዎች እስቲ ቀረብ ብለን እንመርምር።
በፋርሳውያን ዘመን የነበረው የአይሁዳውያን ሕይወት
ቂሮስ በ537 ከዘአበ አይሁዳውያን ከባቢሎናውያን ምርኮ ነፃ እንዲወጡ ካወጀ በኋላ አይሁዳውያንንና አይሁዳውያን ያልሆኑ ተባባሪዎቻቸውን ያቀፈ አንድ ቡድን ከባቢሎን ወጣ። እነዚህ ለቀረበላቸው መንፈሳዊ ጥሪ ምላሽ የሰጡ ቀሪዎች ወደ ጠፉት ከተሞችና ባድማ ወደሆነው ምድር ተመለሱ። ኤዶማውያን፣ ፊንቃውያን፣ ሳምራውያን፣ የአረብ ነገዶችና ሌሎች በአንድ ወቅት እስራኤል የነበራትን ሰፊ ክልል አሳንሰውት ነበር። የቀረው የይሁዳና የብንያም ክልል አባር ናሃራ ተብሎ የሚጠራው (ከወንዙ ማዶ) ፋርሳውያን የሚያስተዳድሩት የይሁዳ የግዛት ክልል ሆነ።—ዕዝራ 1:1-4፤ 2:64, 65
ይሁዳ በፋርስ አገዛዝ ሥር ሆና “መስፋፋትና የሕዝብ ቁጥር ዕድገት ማሳየት ጀመረች” ይላል ዘ ካምብሪጅ ሂስትሪ ኦቭ ጁዳይዝም። በተጨማሪም ይኸው መጽሐፍ ኢየሩሳሌምን በተመለከተ ሲናገር “ጭሰኞችና ለመሳለም ወደዚያ የሚመጡ ሰዎች ስጦታዎችን ሲያመጡ ቤተ መቅደሱና ከተማው በለጸገ፤ በዚህም ምክንያት ሀብታቸው የውጭ አገር ነጋዴዎችንና የእጅ ጥበብ ባለ ሙያዎችን ማረከ” ይላል። ምንም እንኳ ፋርሳውያን አገሩ የራሱ የሆነ መስተዳድርና ሃይማኖት እንዲኖረው ቢፈቅዱም በሕዝቡ ላይ የተጣለው ቀረጥ ከባድ ከመሆኑ የተነሣ ሊከፈል የሚችለው በውድ ማዕድኖች ብቻ ነበር።—ከነህምያ 5:1-5, 15፤ 9:36, 37፤ 13:15, 16, 20 ጋር አወዳድር።
የፋርስ መንግሥት የመጨረሻ ዓመታት በተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች ውስጥ በተሾሙ ገዢዎች ዓመፅ ተለይተው የሚታወቁ የሁከት ጊዜያት ነበሩ። አያሌ አይሁዳውያን በሜድትራኒያን ጠረፍ በተነሣው ዓመፅ ስለ ተካፈሉ በካስፒያን ባሕር በስተ ሰሜን ራቅ ብሎ ወደሚገኘው ሃይራካና ወደ ተባለ ቦታ ተወስደው ነበር። ሆኖም በፋርስ መንግሥት የቅጣት እርምጃ አብዛኞቹ የይሁዳ ነዋሪዎች የተነኩ አይመስልም።
የግሪካውያን ዘመን
ታላቁ እስክንድር በ332 ከዘአበ በመካከለኛው ምሥራቅ እንደ ነብር ሆኖ የተነሣ ቢሆንም ከእሱ በፊትም ቢሆን የግሪክ ባህል ተወዳጅነት አትርፎ ነበር። (ዳንኤል 7:6) እስክንድር የግሪክ ባህል ፖለቲካዊ ጠቀሜታ እንዳለው በመገንዘብ የሚያስፋፋውን ግዛት ሆን ብሎ ከግሪክ ባህል ጋር ማስተዋወቅ ጀመረ። ግሪክኛ ዓለም አቀፍ ቋንቋ ሆነ። የእስክንድር አጭር የግዛት ዘመን አጉል ፍልስፍና፣ የጋለ የስፖርትና የኪነ ጥበብ ስሜት እንዲስፋፋ አድርጎ ነበር። ቀስ በቀስ የግሪካውያን ባህል በአይሁዳውያን ባህል ላይ ሳይቀር ተጽዕኖ አሳድሮ ነበር።
ነቢዩ ዳንኤል “የሰሜኑ ንጉሥ” እና “የደቡቡ ንጉሥ” በማለት የጠራቸውን ነገሥታት ሚና ለመጀመሪያ ጊዜ የተጫወቱት እስክንድር በ323 ከዘአበ ከሞተ በኋላ በሶርያና በግብፅ ውስጥ የነገሡት ተተኪዎቹ ነበሩ። (ዳንኤል 11:1-19) በግብፃውያን “የደቡቡ ንጉሥ” በዳግማዊ ፒቶለሚ ፊላደልፈስ የግዛት ዘመን ወቅት (285-246 ከዘአበ) የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ኮይኔ በተባለው ተራ የግሪክኛ ቋንቋ መተርጎም ጀመሩ። ይህ ትርጉም ሴፕቱጀንት በመባል ተጠርቷል። ከሴፕቱጀንት ትርጉም ብዙ ጥቅሶች በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ተጠቅሰዋል። በመንፈሳዊ ግራ ለተጋባውና በጨለማ ለተዋጠው ዓለም እውቀት ሰጪውን ብርሃን በማስተላለፍ ረገድ ግሪክኛ እጅግ ግሩም የሆነ መሣሪያ ነበር።
አንቲዮከስ አራተኛ ኢፒፋንስ የሶርያ ንጉሥና የጳለስጢና ገዢ ከሆነ በኋላ (175-164 ከዘአበ) የአይሁድ እምነት በመንግሥት በተጠነሰሰ ስደት ሊጠፋ ተቃርቦ ነበር። ግሪካውያን እንገድላችኋለን እያሉ በማስፈራራት ይሖዋ አምላክን እንዲክዱና ለግሪክ አማልክት ብቻ እንዲሠዉ አይሁዳውያንን ያስገድዷቸው ነበር። በታኅሣሥ 168 ከዘአበ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውስጥ ለይሖዋ በተሠራው ታላቅ መሠዊያ ላይ አንድ አረማዊ መሠዊያ ተገንብቶ ለኦሎምፒያው ዚየስ መሥዋዕቶች ይቀርብበት ጀመር። በዚህ ሁኔታ የተረበሹ ደፋር የገጠር ሰዎች በጁዳስ ማክቤዝ መሪነት ሕብረት ከፈጠሩ በኋላ ከባድ ጦርነት አድርገው ኢየሩሳሌምን በእጃቸው አስገቡ። ቤተ መቅደሱ ለአምላክ እንደገና ተመረቀ። ከዚያም ቤተ መቅደሱ ከረከሰ ከሦስት ዓመታት በኋላ የዕለት ተለት መሥዋዕቶች መቅረባቸውን ቀጠሉ።
በቀሪው የግሪካውያን ዘመን ውስጥ የአይሁድ ማኅበረሰብ አባላት በጠብ ጫሪነት ክልላቸውን ወደ ጥንት ወሰኑ ለማስፋት ፈለጉ። አዲስ ያገኙትን ጀግንነት ለአምላክ አክብሮት በጎደለው መንገድ አረማዊ ጎረቤቶቻቸውን በሰይፍ አስገድደው ለመለወጥ ተጠቀሙበት። ሆኖም የግሪክ የፖለቲካ ንድፈ ሐሳብ በትላልቅና በትናንሽ ከተሞች ላይ ከባድ ተጽዕኖ ማሳደሩን ቀጠለ።
በዚያ ወቅት ከፍተኛ የክህነት ሥልጣን ለማግኘት የሚጥሩ ሰዎች በአብዛኛው ጊዜ በጣም ብልሹ የሆነ ሥነ ምግባር ነበራቸው። ተንኮል፣ ሰውን በምሥጢር መግደልና ፖለቲካዊ ሤራ የያዙትን ቦታ አርክሶባቸው ነበር። በአይሁዳውያን መካከል የነበረው መንፈስ አምላካዊ አክብሮት እየጎደለው በሄደ መጠን የግሪክ ስፖርቶች በይበልጥ ተወዳጅነት እያተረፉ መጡ። ወጣት ካህናት በጨዋታዎቹ ለመሳተፍ ሲሉ ሥራቸውን በቸልታ መመልከታቸው እንዴት የሚያስገርም ነው! ሌላው ቀርቶ አይሁዳውያን አትሌቶች ራቁታቸውን ሆነው ከአሕዛብ ጋር ውድድር ሲያካሂዱ ከእፍረት ለመዳን ሲሉ “ወደ አለመገረዝ” ለመመለስ ብለው የሚሰቀጥጥ ቀዶ ሕክምና ያደርጉ ነበር።—ከ1 ቆሮንቶስ 7:18 ጋር አወዳድር።
ሃይማኖታዊ ለውጦች
የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ከምርኮ በኋላ ባሉት የመጀመሪያ ዓመታት ታማኝ አይሁዳውያን አረማዊ ጽንሰ ሐሳቦችንና ፍልስፍናዎችን ከእውነተኛ ሃይማኖት ጋር እንዲቀላቅሉ የቀረበላቸውን ፈተና እንደተቋቋሙ ያሳያሉ። አይሁዳውያን ከፋርሳውያን ጋር ከ60 ዓመት በላይ የቅርብ ግንኙነት ካደረጉ በኋላ የተጻፈው የአስቴር መጽሐፍ አንድም የዞርስትራ እምነት ሐሳብ አይገኝበትም። ከዚህም በላይ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል በሆኑት በዕዝራ፣ በነህምያ ወይም በሚልክያስ ላይ የፋርሳውያን ሃይማኖት ተጽዕኖ አላደረገባቸውም። እነዚህ ሁሉ መጻሕፍት የተጻፉት በፋርሳውያን ዘመን (537-443 ከዘአበ) መጀመሪያ ላይ ነበር።
ሆኖም በፋርሳውያን ዘመን የኋለኞቹ ዓመታት ብዙ አይሁዳውያን የፋርሳውያን ዋንኛ አምላክ የሆነውን የኡራ ማዝዳ አምላኪዎችን አንዳንድ አመለካከቶች መቀበል እንደ ጀመሩ ምሁራን ያምናሉ። ይህ ሁኔታ ኤሴናውያን ባሏቸው የታወቁ አጉል ልማዶችና እምነቶች ታይቷል። አይሁዳውያን ቀበሮዎችን፣ ሌሎች የበረሃ ፍጥረታትንና የሌሊት ወፎችን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸውን የተለመዱ ግሪክኛ ቃላት ከክፉ መናፍስትና በባቢሎናውያንና በፋርሳውያን ከሚገለጹት የአፈ ታሪክ የሌሊት ጭራቆች ጋር ያገናኟቸዋል።
አይሁዳውያን አረማዊ ሐሳቦችን በተለየ አቅጣጫ መመልከት ጀመሩ። ስለ ሰማይ፣ ስለ ሲኦል፣ ስለ ነፍስ፣ ስለ ቃል (ሎጎስ) እና ስለ ጥበብ የሚናገሩት ጽንሰ ሐሳቦች አዲስ ትርጉም እየያዙ መጡ። በተጨማሪም በዚያ ወቅት አምላክ ከሰው በጣም የራቀ ስለ ሆነ ከሰው ጋር የሐሳብ ግንኙነት ማድረጉን አቁሟል፤ ከእርሱ ጋር ለመነጋገር አማላጆች ያስፈልጋሉ በማለት ያስተምሩ ነበር። ግሪኮች እነዚህን አማላጅና ጠባቂ መናፍስት ዳይሞንስ ይሏቸው ነበር። አይሁዳውያን ዳይሞንስ (አጋንንት) ጥሩ ወይም መጥፎ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለውን ሐሳብ ስለ ተቀበሉ በአጋንንት ቁጥጥር ሥር ለመሆን በቀላሉ የተጋለጡ ሆኑ።
የአካባቢውን አምልኮ በተመለከተ አንድ ገንቢ ለውጥ ተደርጎ ነበር። በአንድ አካባቢ የሚገኙ አይሁዳውያን ሃይማኖታዊ ትምህርት የሚያገኙባቸውና ለአገልግሎት የሚሰበሰቡባቸው ምኩራቦች በፍጥነት ብቅ ማለት ጀመሩ። የአይሁዳውያን ምኩራቦች መቼ፣ የትና እንዴት እንደ ተቋቋሙ በትክክል አይታወቅም። ምኩራቦች በሩቅ አገሮች ውስጥ የሚገኙ አይሁዳውያን ወደ ቤተ መቅደሱ መሄድ በማይችሉበት ወቅት የሚያስፈልጋቸውን ነገር ለማሟላት ይጠቅሟቸው ስለ ነበር በአጠቃላይ ሲታይ በምርኮ ወቅት ወይም ከምርኮ በኋላ እንደ ተቋቋሙ ይታመናል። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ‘ሰዎችን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራቸውን የእርሱን በጎነት ሲናገሩ’ ምኩራቦች ጥሩ የሕዝብ መሰብሰቢያ ስፍራ በመሆን ከፍተኛ ጠቀሜታ አበርክተዋል።—1 ጴጥሮስ 2:9
የአይሁድ እምነት የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች ነበሩት
በሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተለያየ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች ብቅ ማለት ጀመሩ። እነዚህ ቡድኖች የተለያዩ ሃይማኖታዊ ድርጅቶች አልነበሩም። ከዚህ ይልቅ በአይሁድ እምነት ተጠቅመው በሕዝቡ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደርና አገሪቱን ለመቆጣጠር የሚፈልጉ አይሁዳውያን ካህናትን፣ ፈላስፎችንና የፖለቲካ ቅጥረኞችን ያቀፉ አነስተኛ ቡድኖች ነበሩ።
የፖለቲካ ተሳትፎ የሚያደርጉት ሰዱቃውያን በአብዛኛው ሀብታም ባላባቶች የነበሩ ሲሆን በሁለተኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ከዘአበ መቃባውያን ከተነሡበት ጊዜ ጀምሮ በዘዴኛነታቸው የታወቁ ነበሩ። ምንም እንኳ አንዳንዶቹ ነጋዴዎችና የመሬት ከበርቴዎች የነበሩ ቢሆንም አብዛኞቹ ካህናት ነበሩ። ኢየሱስ በተወለደበት ወቅት አብዛኞቹ ሰዱቃውያን የሮም መንግሥት የጳለስጢናን ምድር መግዛቱን ይደግፉ ነበር። ይህም የሆነበት ምክንያት የሮም መንግሥት ይበልጥ የተረጋጋ ስለሆነ በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ ለመጠበቅ ይችላል ብለው ያስቡ ስለነበር ነው። (ከዮሐንስ 11:47, 48 ጋር አወዳድር።) ጥቂቶች (የሄሮድስ ደጋፊዎች) ሕዝቡ የሄሮድስ ቤተሰብ እንዲገዛ ይፈልጋል የሚል እምነት ነበራቸው። በዚህም ሆነ በዚያ ሰዱቃውያን አገሪቱ በአይሁዳውያን አክራሪዎች እጅ እንድትወድቅም ሆነ ቤተ መቅደሱን ከካህናት በስተቀር ማንም ሰው እንዳይቆጣጠረው ይፈልጉ ነበር። የሰዱቃውያን እምነቶች በተለይ በሙሴ ጽሑፎች ትርጓሜ ላይ የተመሠረቱ የቆዩ ወጎችን ያቀፉ ነበሩ። ይህ አቋማቸው ኃይለኛ ለሆነው ለፈሪሳውያን ቡድን በነበራቸው ተቃውሞ ተንጸባርቋል። (ሥራ 23:6-8) ሰዱቃውያን በዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኙትን ትንቢቶች ግምታዊ አስተሳሰብ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ አይቀበሏቸውም ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካዊ መጻሕፍት፣ በግጥም መልክ የተጻፉ መጻሕፍትና ምሳሌያዊ መጻሕፍት በመንፈስ አነሣሽነት እንዳልተጻፉና አስፈላጊ እንዳልሆኑ ያስተምሩ ነበር።
ፈሪሳውያን የተነሡት በግሪካውያን ዘመን በዘመኑ የነበሩትን ፀረ አይሁዳውያን የሆኑ የግሪክ ባህሎች በመጻረር ነበር። ሆኖም በኢየሱስ ዘመን ግትር፣ ወግ አጥባቂ፣ በሕግ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ፣ ኩራተኞች፣ ራሳቸውን የሚያመጻድቁ ሰባኪዎችና አስተማሪዎች ነበሩ፤ በምኩራብ በሚሰጡት ትምህርት አማካኝነት ሕዝቡን ለመቆጣጠር ይፈልጉ ነበር። በአብዛኛው መካከለኛ ኑሮ ካላቸው ሰዎች የመጡ ሲሆን ተራውን ሕዝብ በንቀት ይመለከቱ ነበር። ኢየሱስ አብዛኞቹን ፈሪሳውያን ራሳቸውን እንደሚያመጻድቁ፣ በጣም ግብዞች፣ ጨካኞችና ገንዘብ ወዳዶች እንደሆኑ አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (ማቴዎስ ምዕራፍ 23) የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችን የሚቀበሉት እንደ ራሳቸው ትርጓሜ ቢሆንም ለቃል ሕጎቻቸው እኩል ወይም ከዚያ የበለጠ ዋጋ ይሰጧቸዋል። ወጋችን “በሕጉ ዙሪያ ያለ አጥር ነው” ይሉ ነበር። ሆኖም ወጎቻቸው አጥር ከመሆን ይልቅ የአምላክን ቃል የሚሽሩና ሕዝቡን ግራ የሚያጋቡ ነበሩ።—ማቴዎስ 23:2-4፤ ማርቆስ 7:1, 9-13
ኤሴናውያን ገለል ብለው በሚገኙ ጥቂት ማኅበረሰቦች ውስጥ ከሕዝብ ተሰውረው ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ሳይሆኑ አይቀርም። ራሳቸውን መሲሕን ለመቀበል ንጹሕ ሆነው የሚጠብቁ እውነተኛ የእስራኤል ቀሪዎች አድርገው ይመለከቱ ነበር። ኤሴናውያን ራሳቸውን እያጎሳቆሉና እየጸለዩ ይኖሩ ነበር፤ በተጨማሪም ብዙዎቹ እምነቶቻቸው የፋርሳውያንንና የግሪካውያንን ጽንሰ ሐሳብ የሚያንጸባርቁ ነበሩ።
በሃይማኖትና በአርበኝነት ስሜት የሚነዱት እነዚህ የተለያዩ የአክራሪነት መንፈስ ያላቸው ቡድኖች ነፃ በሆነው በአይሁድ መንግሥታቸው ላይ ጣልቃ የሚገባውን ሰው ሁሉ በክፉ ዓይን ይመለከቱት ነበር። ከመቃባውያን ጋር የሚመሳሰሉ ሲሆን እምነታቸው በተለይ የሚማርከው በሐሳብ የሚመሩ፣ ጀብደኛ የሆኑ ወጣቶችን ነበር። የሽምቅ ውጊያዎች ስለሚያደርጉ የገጠር መንገዶችንና በከተማ ውስጥ ሕዝብ የሚሰበሰብባቸውን አደባባዮች አደገኛ ቦታዎች በማድረግ በዘመኑ ለነበረው ውጥረት አስተዋጽኦ አድርገው ነበር።
በግብፅ ውስጥ የግሪክን ባህል በሚከተሉ አይሁዳውያን መካከል የግሪክ ፍልስፍና ተስፋፍቶ ነበር። ፍልስፍናው ከዚያ ተነሥቶ ወደ ጳለስጢና እና ከጳለስጢና ምድር ውጪ ተበታትነው በሚገኙ አይሁዳውያን መካከል ተሰራጨ። ልዩ ልዩ አዋልዶችን የጻፉት አይሁዳውያን የንድፈ ሐሳብ አውጪዎች የሙሴ ጽሑፎችን ግልጽ ያልሆኑ፣ ጣዕም የሌላቸው ምሳሌዎች ናቸው ይሏቸው ነበር።
የሮም ዘመን በተቃረበበት ወቅት የግሪክ ባህል በማኅበራዊ ኑሮ፣ በፖለቲካና በፍልስፍና ረገድ በጳለስጢና ላይ ዘላቂ ለውጥ አምጥቶ ነበር። የአይሁዳውያን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሃይማኖት ጥቂት ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነቶችን ከባበሎናውያን፣ ከፋርሳውያንና ከግሪካውያን ጽንሰ ሐሳቦች ጋር ቀላቅሎ በያዘው የአይሁድ እምነት ተተክቶ ነበር። ሆኖም ሰዱቃውያን፣ ፈሪሳውያንና ኤሴናውያን አንድ ላይ ሲዳመሩ ከሕዝቡ ውስጥ ከ7 በመቶ ያነሱ ነበሩ። በእነዚህ እርስ በርሳቸው በሚጋጩ ግራ የሚያጋቡ ኃይሎች መካከል የነበሩት የአይሁድ ሕዝቦች “እረኛ እንደ ሌላቸው በጎች ተጨንቀው ተጥለውም ነበር።”—ማቴዎስ 9:36
በዚያ በጨለማ በተዋጠ ዓለም ውስጥ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቅ አለ። “እናንተ ደካሞች ሸክማችሁ የከበደ ሁሉ፣ ወደ እኔ ኑ፣ እኔም አሳርፋችኋለሁ” በማለት ያቀረበው ግብዣ የሚያጽናና ነበር። (ማቴዎስ 11:28) “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ብሎ ሲናገር መስማት ምንኛ ያስደስት ነበር! (ዮሐንስ 8:12) በተጨማሪም “የሚከተለኝ የሕይወት ብርሃን ይሆንለታል እንጂ በጨለማ አይመላለስም” ሲል የሰጠው ልብን በደስታ የሚያስፈነድቅ ተስፋ በእርግጥም አስደሳች ነበር።—ዮሐንስ 8:12
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች በመንፈሳዊ ጨለማ ውስጥ እንዳሉ ገልጿል
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአንቲዮከስ አራተኛን (ኢፒፋንስ) ምስል የያዘ ሳንቲም
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.