የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 12/15 ገጽ 21-25
  • መሣሪያ የታጠቁ ዘራፊዎች ጥቃት ሲሰነዝሩ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መሣሪያ የታጠቁ ዘራፊዎች ጥቃት ሲሰነዝሩ
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ከዝርፊያ ራስን መጠበቅና የአምላክ ቃል
  • የዝርፊያን አደጋ መቀነስ
  • የታጠቁ ዘራፊዎች ሲመጡ
  • መረጋጋት
  • በምዕራብ አፍሪካ ተካሂዶ የከሸፈ የዝርፊያ ሙከራ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ፍርሃት የሚያከትመው መቼ ይሆን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • ሌቦች የማይኖሩበት ዓለም
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • ቤተ መቅደሱ እንደገና ጸዳ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 12/15 ገጽ 21-25

መሣሪያ የታጠቁ ዘራፊዎች ጥቃት ሲሰነዝሩ

በምዕራብ አፍሪካ ከከተማ ዳር ለብቻዋ ተነጥላ በምትገኘው በኢኮዪ ትላልቅ ቤቶች በረዣዥም አጥሮች ታጥረዋል። ብዙዎቹ ቤቶች ሦስት ሜትር ከፍታ ባለው ግንብ የታጠሩ ሲሆን በግንቡ አናት ላይ ደግሞ የሾሉ ብረቶች፣ የተሰባበረ ጠርሙስ ወይም እሾሃማ ሽቦ ተደርጎባቸዋል። በብረት መቀርቀሪያ የሚዘጉ፣ በሰንሰለትና በሰረገላ ቁልፎች የሚቆለፉና በዘብ የሚጠበቁ ግዙፍ የግቢ በሮች አሏቸው። መስኮቶች በብረት ታጥረዋል። መኝታ ቤቶችን ከተቀረው የቤቱ ክፍል የሚለዩ የብረት መዝጊያዎች አሉ። ምሽት ላይ ኃይለኛ ውሾች ከታሰሩበት ይለቀቃሉ። ባውዛ መብራቶች ጨለማውን ቀን ሲያስመስሉት በኮምፒዩተር የሚሠሩ የጥበቃ መሣሪያዎች ደግሞ በአካባቢው ዝር የሚል መኖር አለመኖሩን ይቃኛሉ።

ሁሉም የቤታቸውን ደኅንነት ማስጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ያምኑበታል። የጋዜጣ ርዕሶች እንደሚከተለው ያሉ እሮሮዎችን ያሰማሉ:- “መሣሪያ የታጠቁ ቀማኞች ኅብረተሰቡን እየዘረፉ ነው፣” “ልጆችን የሚሰርቁ ወንበዴዎች ከቁጥጥር ውጪ ሆነዋል፣” እንዲሁም “ወሮበሎች [አንድን መንደር] በመቆጣጠራቸው ሽብር ተፈጥሯል።” በብዙ አገሮች ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አስቀድሞ እንደተናገረው የምንኖረው በጣም አስቸጋሪ በሆነ ጊዜ ውስጥ ነው።​—⁠2 ጢሞቴዎስ 3:​1

በመሣሪያ እያስፈራሩ መዝረፍን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚፈጸሙ ወንጀሎች ቁጥር ከዕለት ወደ ዕለት እያሻቀበ ሄዷል። ብዙ መንግሥታት የራሳቸውን ዜጎች ለመጠበቅ አልቻሉም ወይም ፈቃደኞች አይደሉም። በአንዳንድ አገሮች የሚገኘው የፖሊስ ኃይል በቁጥርም ሆነ በትጥቅ በመበለጡ ለሚደርሱት የድረሱልኝ ጥሪዎች ምላሽ ለመስጠት አይችልም። አብዛኞቹ ሰዎች ደግሞ ወንጀል ሲፈጸም ቢያዩም እርዳታ ለመስጠት ይፈራሉ።

የተዘረፉ ሰዎች ከፖሊስም ሆነ ከሕዝብ እርዳታ ለማግኘት እንደማይችሉ ስለሚገነዘቡ ራሳቸውን ለመከላከል የራሳቸውን እርምጃ ይወስዳሉ። በታዳጊ አገር የሚገኝ አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ እንዲህ ብሏል:- “የማንቂያ ደወሎች እደውላለሁ ብትል ዘራፊዎቹ አካለ ጎደሎ ያደርጉሃል ወይም ይገድሉሃል። ከውጪ እርዳታ አገኛለሁ የሚለውን ሐሳብ እርሳው። እርዳታ ካገኘህ እሰየው ነው፤ ሆኖም እርዳታ አገኛለሁ ብለህ አትጠብቅ፤ ወይም እርዳታ ለማግኘት እጮሃለሁ ብለህ አታስብ፤ እርዳታ ለማግኘት መጮኹ የበለጠ ችግር መጋበዝ ነው።”

ከዝርፊያ ራስን መጠበቅና የአምላክ ቃል

ክርስቲያኖች የዚህ ዓለም ክፍል አይሁኑ እንጂ የሚኖሩት በዚህ ዓለም ውስጥ ነው። (ዮሐንስ 17:​11, 16) ስለዚህ እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ሲሉ ምክንያታዊ ዝግጅቶች ያደርጋሉ። ቢሆንም ይሖዋን የማያገለግሉ ሰዎች ከሚያደርጉት በተቃራኒ የአምላክ ሕዝቦች ጥበቃ ለማግኘት የሚፈልጉት ክርስቲያናዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሳይጥሱ ነው።

በአንጻሩ ግን በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የሚኖሩ ሰዎች ከዝርፊያ ራሳቸውን ለመጠበቅ በአስማታዊ ነገሮች ይጠቀማሉ። አንድ ጠንቋይ እርዳታ ማግኘት የሚፈልገውን ሰው ክንድ፣ ደረት ወይም ጀርባ ይበጣል። ከዚያም የተበጣው ሥፍራ በአስማታዊ መድኃኒት ከታሸና ከተደገመበት ሰውየው የዘራፊዎች ጥቃት አይደርስበትም ተብሎ ይታሰባል። ሌሎች ደግሞ ዘራፊዎች እንዳያጠቁን “ዋስትና” ይሆነናል ብለው በማሰብ የተደገመባቸው ክታቦችን ወይም አስማታዊ መድኃኒቶችን በቤታቸው ያስቀምጣሉ።

እውነተኛ ክርስቲያኖች ከማንኛውም ዓይነት የአስማት ድርጊት ይርቃሉ። መጽሐፍ ቅዱስ ማንኛውንም ዓይነት መናፍስታዊ ድርጊት ያወግዛል፤ ይህ ደግሞ ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ድርጊቶች ሰዎች በምድር ላይ ዓመፅ እንዲስፋፋ ከሚያደርጉ አጋንንት ጋር ግንኙነት እንዲኖራቸው ያደርጋሉ። (ዘፍጥረት 6:​2, 4, 11) መጽሐፍ ቅዱስ “አስማትም አታድርጉ” በማለት በግልጽ ይናገራል።​—⁠ዘሌዋውያን 19:​26

አንዳንድ ሰዎች መሣሪያ በመታጠቅ ደህንነታቸውን ለማስጠበቅ ይጥራሉ። ክርስቲያኖች ግን “ሰይፍ የሚያነሡ ሁሉ በሰይፍ ይጠፋሉና” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት በቁም ነገር ይመለከታሉ። (ማቴዎስ 26:​52) የአምላክ ሕዝቦች ‘ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ ስላደረጉ’ ራሳቸውን ከዘረፋ ወይም ከጥቃት ለመጠበቅ ሲሉ መሣሪያ አይገዙም።​—⁠ሚክያስ 4:​3

የታጠቁ ዘቦችን ስለ መቅጠርስ ምን ለማለት ይቻላል? ምንም እንኳ ይህ የግል ውሳኔ ቢሆንም እንዲህ ማድረግ ማለት መሣሪያውን ሌላ ሰው እንዲጠቀምበት መስማማት ማለት መሆኑን ማስታወስ ያስፈልጋል። አንድ ቀጣሪ ዘራፊዎች ቢመጡ ጠባቂዎቹ ምን እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል? ደኅንነቱን የሚጠብቁትን ሕዝብ ወይም ንብረት ለማዳን ሲሉ አስፈላጊ ሆኖ ካገኙት ሌባውን ተኩሰው እንዲገድሉ ይጠብቅባቸዋል?

ክርስቲያኖች ራሳቸውን ለመከላከል በአስማትና በጦር መሣሪያዎች ላለመጠቀም የሚወስዱት አቋም አምላክን በማያውቁ ሰዎች ዘንድ ሞኝነት ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “በእግዚአብሔር የሚታመን ግን እርሱ ይጠበቃል” የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል። (ምሳሌ 29:​25) ይሖዋ ሕዝቡን በአጠቃላይ የሚጠብቅ ቢሆንም አገልጋዮቹን ከዝርፊያ ለመከላከል ሲል በእያንዳንዱ ጉዳይ ውስጥ እጁን አያስገባም። ኢዮብ የታመነ ሰው በመሆን ተወዳዳሪ የማይገኝለት ቢሆንም የቤት እንስሳቱ በዘራፊዎች ሲወሰዱበትና ጠባቂዎቹም ሲገደሉበት አምላክ ምንም እርምጃ አልወሰደም። (ኢዮብ 1:​14, 15, 17) በተጨማሪም ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ከወንበዴዎች’ አደጋ እንዲደርስበት አምላክ ፈቅዷል። (2 ቆሮንቶስ 11:​26) ሆኖም አምላክ የዝርፊያን አደጋ ለመቀነስ የሚያስችሉ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ጠብቀው እንዲኖሩ ሕዝቦቹን ያስተምራል። በተጨማሪም የዝርፊያ ሙከራዎች በሚከሰቱበት ጊዜ ዘራፊዎቹ የሚያደርሱባቸው ጉዳት በሚቀንስ መንገድ ምላሽ እንዲሰጡ በሚያስችላቸው እውቀት ያስታጥቃቸዋል።

የዝርፊያን አደጋ መቀነስ

ጠቢቡ ሰው ከብዙ ዘመን በፊት “የባለጠጋ ጥጋብ [“ሀብቱ፣” የ1980 ትርጉም] ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል” ሲል ተናግሯል። (መክብብ 5:​12) በሌላ አነጋገር ብዙ ነገሮች ያሏቸው ሰዎች ንብረታቸውን እንዳያጡ ስለሚጨነቁ እንቅልፍ አጥተው ያድራሉ።

ስለዚህ ጭንቀትን ብቻ ሳይሆን የዝርፊያ አደጋን ጭምር ለመቀነስ የሚያስችለው አንዱ መፍትሔ ውድ ንብረቶችን ከማካበት መራቅ ነው። ሐዋርያው በመንፈስ ተገፋፍቶ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፣ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።” (1 ዮሐንስ 2:​16) ሰዎች ውድ የሆኑ ነገሮችን እንዲገዙ የሚገፋፋቸው ያው ምኞት ሌሎችን ደግሞ እንዲሰርቁ ያነሳሳቸዋል። እንዲሁም ‘ኑሮዬ ይታይልኝ የሚል መንፈስ’ ለዝርፊያ የተሰማሩ ሰዎችን የሚጋብዝ ነው።

የሌሎችን ትኩረት ላለመሳብ ከመጠንቀቅ በተጨማሪ ሌላው የዝርፊያ መከላከያ ደግሞ እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናችሁን በተግባር ማሳየት ነው። ለሌሎች ያላችሁን ፍቅር የምታሳዩ ከሆነ፣ ሐቀኞች ከሆናችሁና በክርስቲያናዊ አገልግሎት በትጋት የምትሳተፉ ከሆነ በምትኖሩበት አካባቢ ባለው ኅብረተሰብ ዘንድ ጥሩና ሊከበር የሚገባው ሰው ነው የሚል ስም ልታተርፉ ትችላላችሁ። (ገላትያ 5:​19-23) እንዲህ ያለውን ክርስቲያናዊ ስም ማትረፍ ከመሣሪያ ይልቅ የተሻለ ጥበቃ ሊሆን ይችላል።

የታጠቁ ዘራፊዎች ሲመጡ

ይሁንና ዘራፊዎች ቤታችሁ ቢገቡና ቢተናኮሏችሁ ምን ማድረግ አለባችሁ? ሕይወታችሁ ካላችሁ ንብረት ይልቅ ይበልጥ ውድ መሆኑን አስታውሱ። ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲህ ብሏል:- “ክፉውን አትቃወሙ፤ ዳሩ ግን ቀኝ ጉንጭህን በጥፊ ለሚመታህ ሁሉ ሁለተኛውን ደግሞ አዙርለት፤ . . . እጀ ጠባብህንም እንዲወስድ ለሚወድ መጎናጸፊያህን ደግሞ ተውለት።”​—⁠ማቴዎስ 5:​39, 40

ይህ ጥበብ ያለበት ምክር ነው። ክርስቲያኖች ስላላቸው ንብረት ለወንጀለኞች መረጃ የመስጠት ግዴታ ባይኖርባቸውም ዘራፊዎች የተቃውሞና ለመተባበር ፈቃደኛ ያለመሆን መንፈስ ከተመለከቱ ወይም የተታለሉ ሆኖ ከተሰማቸው የኃይል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ። ብዙዎቹ “የሐፍረት ስሜታቸው ስለጠፋ” በቀላሉ ጨካኞችና ምሕረት የለሾች ሊሆኑ ይችላሉ።​—⁠ኤፌሶን 4:​19 የ1980 ትርጉም

ሳሙኤል የሚኖረው በአንድ ትልቅ አፓርታማ ውስጥ ነው። ዘራፊዎች የሕንፃውን መተላለፊያዎች በመዝጋት ከአፓርታማ ወደ አፓርታማ እየሄዱ ዘረፉ። ሳሙኤል የተኩስ ድምፅ እንዲሁም በሮች በኃይል ሲዘጉ፣ ሰዎች ሲጮኹና ሲያለቅሱ ይሰማል። አምልጦ መውጣት የማይቻል ነገር ነበር። ሳሙኤል ሚስቱንና ሦስት ወንዶች ልጆቹን በወለሉ ላይ እንዲምበረከኩ፣ እጃቸውን ወደ ላይ እንዲያነሱ፣ ዓይናቸውን እንዲጨፍኑና እንዲጠብቁ ነገራቸው። ዘራፊዎቹ በሩን በርግደው ሲገቡ ሳሙኤል መሬት መሬት እያየ አነጋገራቸው። ይህን ያደረገው ፊታቸውን ካየ ጠቁሞ ሊያስይዘን ይችላል ብለው እንደሚያስቡ ስላወቀ ነበር። “ግቡ” አላቸው። “የፈለጋችሁትን ልትወስዱ ትችላላችሁ። እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ነን፤ ምንም አንነካችሁም።” ዘራፊዎቹ በዚህ ነገር ተደነቁ። በሚቀጥለው አንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ በጠቅላላው 12 የሚሆኑ ታጣቂዎች በቡድን በቡድን ሆነው መጡ። ምንም እንኳ ጌጣ ጌጦች፣ ገንዘብና የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች ቢዘረፍም ቤተሰቡ በሕንፃው ውስጥ እንደነበሩት እንደሌሎቹ አልተደበደበም ወይም በቆንጨራ የመቆረጥ አደጋ አልደረሰበትም። ሳሙኤልና ቤተሰቡ ሕይወታቸው በመትረፉ ይሖዋን አመስግነዋል።

ይህ እንደሚያሳየው ገንዘብንና ቁሳዊ ነገሮችን በተመለከተ የዝርፊያ ሰለባ የሆኑ ሰዎች ዘራፊዎቹን ከመቃወም መቆጠባቸው የሚደርስባቸውን ጉዳት ሊቀንስ ይችላል።a

አንዳንድ ጊዜ አንድ ክርስቲያን የሚሰጠው ምሥክርነት ከጉዳት ሊከላከልለት ይችላል። ዘራፊዎች ወደ ኤዲ ቤት ሰብረው በገቡ ጊዜ እንዲህ አላቸው:- “ለእናንተ ሁኔታዎች አስቸጋሪ መሆናቸውን አውቃለሁ፤ በዚህ ሥራ ላይ የተሰማራችሁትም ለዚህ ነው። የይሖዋ ምሥክሮች እንደመሆናችን መጠን አንድ ቀን ሁሉም ሰው ራሱም ሆነ ቤተሰቡ የሚመገበው በቂ ምግብ እንደሚኖረው እናምናለን። ሁሉም ሰው በአምላክ መንግሥት ሥር በሰላምና በደስታ ይኖራል።” ይህ የዘራፊዎቹን ጭካኔ አረገበው። ከእነሱ ውስጥ አንዱ እንዲህ አለ:- “ወደ ቤታችሁ በመምጣታችን እናዝናለን፤ ሆኖም የተራብን መሆናችንን መገንዘብ አለባችሁ።” የኤዲን ንብረት ቢዘርፉም በእሱም ሆነ በቤተሰቡ ላይ ምንም ጉዳት አላደረሱም።

መረጋጋት

በአደገኛ ሁኔታዎች በተለይም ደግሞ የዘራፊዎቹ ተቀዳሚ ዓላማ የሚዘርፏቸውን ሰዎች በማሸበር በቁጥጥራቸው ሥር ማድረግ በሚሆንበት ጊዜ ተረጋግቶ መቀመጥ ቀላል አይደለም። ጸሎት ይረዳናል። ለእርዳታ የምናሰማው ልመና አጭርና በዝምታ የቀረበ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ይሰማዋል። መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “የእግዚአብሔር ዓይኖች ወደ ጻድቃን ጆሮቹም ወደ ጩኸታቸው ናቸውና።” (መዝሙር 34:​15) ይሖዋ ይሰማናል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ሁኔታ በተረጋጋ መንገድ ለመያዝ የሚያስችለንን ጥበብ ይሰጠናል።​—⁠ያዕቆብ 1:​5

ከጸሎት በተጨማሪ ለመረጋጋት የሚረዳው ሌላው ነገር ብትዘረፍ ምን ማድረግ እንዳለብህና ምን ማድረግ እንደሌለብህ አስቀድሞ መወሰን ነው። እርግጥ ነው በዚያ ወቅት በምን ሁኔታ ውስጥ እንደምትሆን አስቀድሞ ማወቅ አይቻልም። እንደዚያም ሆኖ ግን እሳት በተያያዘ ሕንፃ ውስጥ ብትሆን ምን ማድረግ እንዳለብህ በአእምሮህ መያዙ ጥበብ እንደሆነ ሁሉ አንዳንድ መመሪያዎችን በአእምሯችን ማስቀመጡ የተሻለ ነው። አስቀድሞ ማሰብ እንድትረጋጋ፣ እንዳትደናገጥና ከጉዳት እንድታመልጥ ያስችልሃል።

አምላክ ስለ ዝርፊያ ያለው አመለካከት በግልጽ ተቀምጧል:- “እኔ እግዚአብሔር ፍርድን የምወድድ ስርቆትንና በደልን የምጠላ ነኝ።” (ኢሳይያስ 61:​8) ይሖዋ ዝርፊያን ከባድ ከሚባሉ ኃጢአቶች መካከል መድቦ እንዲጽፈው ነቢዩ ሕዝቅኤልን በመንፈስ አነሳስቶታል። (ሕዝቅኤል 18:​18) ሆኖም ይኸው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ንስሐ የሚገባንና የዘረፈውን የሚመልስን ሰው አምላክ በምሕረት ይቅር እንደሚለው ይናገራል።​—⁠ሕዝቅኤል 33:​14–16

ክርስቲያኖች ወንጀል በተስፋፋበት ዓለም ውስጥ ቢኖሩም ዝርፊያ በማይኖርበት በአምላክ መንግሥት ሥር ለመኖር ባላቸው ተስፋ ይደሰታሉ። ያንን ጊዜ በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ የሚከተለውን ተስፋ ይሰጣል:- “የሠራዊት ጌታ የእግዚአብሔር አፍም ተናግሮአልና [የአምላክ ሕዝብ የሆነ] እያንዳንዱ ከወይኑና ከበለሱ በታች ይቀመጣል፣ የሚያስፈራውም የለም።”​—⁠ሚክያስ 4:​4

[የግርጌ ማስታወሻ]

a የምናሳየው የትብብር መንፈስ ገደብ እንዳለው የተረጋገጠ ነው። የይሖዋ አገልጋዮች የአምላክን ሕግ በሚያስጥስ በማንኛውም መንገድ አይተባበሩም። ለምሳሌ ያህል አንድ ክርስቲያን በፆታ ለመደፈር ፈቃደኛ አይሆንም።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ