በምዕራብ አፍሪካ ተካሂዶ የከሸፈ የዝርፊያ ሙከራ
ዩኒስ ኤቡ እንደተናገረችው
“የታጠቁ ዘራፊዎች ጥቃታቸውን ሊሰነዝሩ ያቀዱት በቤታችን የጉባኤ መጽሐፍ ጥናት በምናደርግበት ቀን ነበር። ወንድሞች፣ እህቶችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንዲገቡ ስንል በራችንን በሰፊው እንከፍት ነበር። ዘራፊዎቹ ልማዳችንንና የስብሰባ ሰዓታችንን ሳያውቁ አይቀሩም። ከሌላ ቦታ መኪና ሰርቀው እንደመጡና መጽሐፍ ጥናት በምናደርግበት ቀንና ሰዓት በራችን ላይ ቆመው ይጠብቁን እንደነበረ በሚገባ አውቀናል።
“እንደ አጋጣሚ ሆኖ የመጡበት ሳምንት የወረዳ የበላይ ተመልካች ጉብኝት የነበረበት ሳምንት ነበር። የተሰበሰብነው በቤታችን ሳይሆን በመንግሥት አዳራሹ ነበር። ስብሰባው ከተጠናቀቀ በኋላ የሽማግሌዎች ስብሰባ ነበር። የሽማግሌዎች ስብሰባ በሚኖርበት ጊዜ እኔና ልጆቹ ወደ ቤታችን እንሄድ የነበረ ቢሆንም ሽማግሌ የሆነው ባለቤቴ እንድንጠብቀው ጠየቀን። ስብሰባው ረዥም ጊዜ እንደማይወስድ ነገረን። ስለዚህ ቆየን።
“ቀጥሎ የመኪናው ሞተር አልነሳም አለን። የወረዳ የበላይ ተመልካቹና ባለቤቴ መኪናውን ሊያስነሱት አልቻሉም። እንዲሠራልን ያመጣነው መካኒክም መኪናውን ሊያሠራው አልቻለም።
“ልጆቹ ወደ ቤት በእግራቸው መሄድ ነበረባቸው። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እኔም ወደ ቤት ሄድኩ። አራት ሰዓት ገደማ ላይ ቤት ደረስኩ። እኔም ሆንኩ ልጆቹ ወደ ግቢያችን የገባነው በመኪና ስላልሆነ ትልቁን በር መክፈት አላስፈለገንም።
“ወደ መኝታ ቤቴ ስገባ ከፍተኛ የተኩስ ድምፅ ሰማሁ። ምን ተከስቶ ይሆን ስል አሰብኩ። ወደ ፖሊስ ስልክ ለመደወል ብፈልግም ስልኩ አይሠራም። ወደ ታች ሮጬ የመግቢያውን ብረት በር ከዚያም የመካከለኛውን በር ቆለፍኩ። መብራቶቹን አጠፋሁ። ልጆቼ በፍርሃት ተውጠው ነበር፤ ስለዚህ እንዲረጋጉ ነገርኳቸው። ይሖዋ እንዲጠብቀን አንድ ላይ ጸለይን። በዚህ ጊዜ ባለቤቴ መኪናው እንዲነሳ እየታገለ በመንግሥት አዳራሹ ይገኝ ነበር።
“በመስኮት በኩል ስመለከት ከበሩ ውጪ አንድ ሰው በመንገዱ ላይ ተዘርሯል። ዘራፊዎቹ ሳይሄዱ ስለማይቀሩ የተጎዳውን ሰው በመኪናዬ ጭኜ ወደ ሆስፒታል በፍጥነት ወሰድኩት። አደገኛ ቢሆንም አንድ ነገር ማድረግ ነበረብኝ። የሚያሳዝነው ግን ሰውየው በሚቀጥለው ቀን ሞተ።
“ምንም እንኳ የሰውየው መሞት የሚያሳዝን ቢሆንም ያን ቀን ሌላም የከፋ ነገር ሊከሰት ይችል ነበር። የወረዳ የበላይ ተመልካች ሊጎበኘን ሲመጣ የመጽሐፍ ጥናት በቤታችን ውስጥ አይደረግም። የመኪናው መበላሸት ቤተሰቡ በአንድ ላይ ሆኖ በመኪና እንዳይጓዝ አድርጓል። ዘራፊዎቹ ቢያገኙት ኖሮ ይይዙት የነበረው ባለቤቴ ወደ ቤት የመጣው በጣም ከመሸ በኋላ ነበር። እነዚህና ሌሎች ነገሮችም በዚያ ምሽት ጠቅመውናል።
“ይሖዋ አምባችንና መሸሸጊያችን ነው። ቅዱስ ጽሑፉ እንደሚለው ‘እግዚአብሔር ከተማን ካልጠበቀ፣ ጠባቂ በከንቱ ይተጋል።’”—መዝሙር 127:1