የእንጀራ ወላጅ ያሉባቸው ቤተሰቦች የሚገጥሟቸው የተለዩ ችግሮች
የእንጀራ ወላጅ ያሉባቸው ቤተሰቦች ደስተኛ ሊሆኑ ይችላሉ! እንዴት?
የእንጀራ ወላጅ ያሉባቸው ቤተሰቦች ቁጥር በብዙ አገሮች እየጨመረ መጥቷል። ሆኖም የእንጀራ ወላጅ ያለበት ቤተሰብ ከሌላ ቤተሰብ ለየት ያሉ ችግሮች ይገጥሙታል። ከእነዚህ ችግሮች መካከል በጣም ተፈታታኝ የሆነው ልጅን የማሳደግ ጉዳይ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። ይሁን እንጂ ቀጥሎ የቀረቡት ሁለቱ ርዕሰ ትምህርቶች ለመግለጽ እንደሞከሩት የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ልጆችን በተሳካ ሁኔታ ማሳደግ ይቻላል።
ብዙውን ጊዜ ስለ እንጀራ አባት ወይም ስለ እንጀራ እናት መልካም አይወራም። መቼም አብዛኞቻችን ልጆች በነበርንበት ጊዜ በእንጀራ እናት ስለሚሠቃይ ልጅ የሚገልጹ የተለያዩ ተረቶች ሳንሰማ አልቀረንም። በአውሮፓ የሚኖሩ ልጆች ስኖው ዋይት ኤንድ ዘ ሰቭን ድዋርፍስ ተብሎ የሚጠራ ተረትም ያውቃሉ። ተረቱ የስኖው ዋይት እንጀራ እናት በጣም ክፉ ጠንቋይ እንደሆነች ይገልጻል!
እንደነዚህ ያሉ ተረቶች ስለ እንጀራ ወላጅ ትክክለኛ መልእክት ያስተላልፋሉን? እንጀራ ወላጆች ሁሉ ክፉዎች ናቸውን? በጭራሽ። አብዛኞቹ ለሚያሳድጓቸው የእንጀራ ልጆች ሁልጊዜ መልካም የሆነውን የሚመኙ ናቸው። ሆኖም የእንጀራ ወላጅ መሆን የሚያስከትላቸውን ለየት ያሉ ችግሮች መጋፈጥ ግድ ይሆንባቸዋል።
ልጅ በማሳደግ ረገድ የሚገጥም ችግር
ብዙውን ጊዜ የመጀመሪያ ትዳር የሚፈርሰው ባልና ሚስት በደንብ ካለመብሰላቸው የተነሳ ነው። ሁለተኛ ትዳር በሚመሠርቱበት ጊዜ ደግሞ ልጆችን በተመለከተ የሚኖረው ሁኔታ በመካከላቸው ውጥረት እንዲፈጠር ያደርጋል። የእንጀራ ወላጅ ካለባቸው አሥር ቤተሰቦች መካከል ከአራት የሚበልጡት በመጀመሪያዎቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በፍቺ እንደሚፈርሱ አንዳንድ ዘገባዎች ያሳያሉ።
የእንጀራ ወላጅ ከቤተሰቡ ጋር መቀላቀሉ በእንጀራ ልጆች ላይ የሚያስከትለውን የስሜት መረበሽ፣ ለማን ታማኝ እንሁን የሚለውን ጭንቀት እንዲሁም የቅንዓትና የቅሬታ ስሜት አዲሶቹ ተጋቢዎች ላይገነዘቡት ይችላሉ። ልጆች ሥጋዊ ወላጃቸው ለእነርሱ ያለውን ፍቅር የእንጀራ ወላጃቸው የሚቀማቸው ሊመስላቸው ይችላል። ከዚህም በላይ ልጆቹ ከቤት ከወጣው ወላጅ አባታቸው ወይም እናታቸው ጋር ያላቸው የጠበቀ ቅርርብ እንደሚቀጥል አሁን እቤት ያለ ወላጅ አባት ወይም እናት ላይገነዘብ ይችላል። አንድ ልጅ ከወላጅ አባቱ ጋር ስላለው ቅርርብ ሲናገር “እማማ፣ አባባ ለአንቺ ክፉ እንደነበር አውቃለሁ። ለእኔ ግን ጥሩ አባት ነበር!” በማለት ተናግሯል። እንዲህ ያለው አነጋገር በሃቅ ላይ የተመሠረተ ቢሆንም እንኳ እናትየው በልጁ አባት ላይ ከፍተኛ ጥላቻ እንዲያድርባት ሊያደርግ ይችላል።
አንድ የእንጀራ አባት እንዲህ በማለት ሳይሸሽግ ተናግሯል:- “የእንጀራ ልጆቼን በማሳድግበት ጊዜ ሊገጥሙኝ የሚችሉ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደምችል ቀደም ብዬ አላሰብኩበትም ነበር። እናታቸውን ካገባሁ ያው እንደ አባታቸው ያዩኛል ብዬ አስቤ ነበር። ይህን ጉዳይ እንደ ቀላል ነገር አድርጌ ነበር የተመለከትኩት። ልጆቹ ከወላጅ አባታቸው ጋር የነበራቸውን የጠበቀ ቅርርብ ፈጽሞ አልተረዳሁም ነበር። ከዚህም የተነሳ ብዙ ተሳሳትኩ።”
በተለይ ተግሣጽን በመስጠት ረገድ አለመግባባቶች ሊነሱ ይችላሉ። ልጆች ፍቅራዊ በሆነ መንገድ ተግሣጽ ሊሰጣቸው ይገባል። ሆኖም ብዙውን ጊዜ ልጆች የወላጃቸውን ተግሣጽ እንኳ አልቀበል ይላሉ። የእንጀራ አባታቸው ወይም እናታቸው የሚሰጧቸውን ተግሣጽማ ለመቀበል ምን ያክል እንደሚቸገሩ መገመት ይቻላል! ብዙውን ጊዜ አንድ የእንጀራ ልጅ ተግሣጽ ሲሰጠው “አንተ እኮ አባቴ አይደለህም!” የሚሉ የመሰሉ አነጋገሮችን ይሰነዝራል። እነዚህ ቃላት በጥሩ ልብ የተነሳሳውን የእንጀራ አባት ወይም እናት ቅስም ምንኛ የሚሰብሩ ናቸው!
የእንጀራ ወላጅ ባለባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ልጆችን በተሳካ ሁኔታ ማሳደግ ይቻላልን? እንዲህ ያለውን የተሳካ ቤተሰብ መገንባት ይቻል ዘንድ የእንጀራ ወላጅ አዎንታዊ ሚና ሊጫወት ይችላልን? ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፈው በአምላክ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሰፈሩትን ምክሮች ከተከተሉ ለሁለቱም ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ አዎንታዊ ይሆናል።
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“አንተ እኮ አባቴ አይደለህም!”