የእንጀራ ወላጅ ያሉባቸው ቤተሰቦች ስኬታማ ሊሆኑ ይችላሉ
የእንጀራ ወላጅ ያለበት ቤተሰብ ስኬታማ ሊሆን ይችላልን? ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሁሉ ‘ቅዱስ ጽሑፉ ሁሉ በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈና ለትምህርትና ለተግሣጽ ልብንም ለማቅናት በጽድቅም ላለው ምክር የሚጠቅም’ መሆኑን ካስታወሱ መልሱ አዎን፣ ይቻላል የሚል ይሆናል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16 NW) ሁሉም የቤተሰቡ አባላት የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሥራ ላይ ካዋሉ ጥሩ ውጤት ይገኛል ብሎ በእርግጠኝነት ለመጠበቅ ይቻላል።
መሠረታዊ ባሕርያት
መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ረገድ እንደ መመሪያ ሆነው እንዲያገለግሉ ያወጣቸው ሕግጋት በጣም ውስን ናቸው። ብዙውን ጊዜ በጥበብ እንድንመላለስ የሚረዱንን መልካም ባሕርያትና ዝንባሌዎች እንድናዳብር ያበረታታል። እነዚህ መልካም ዝንባሌዎችና ባሕርያት ደስተኛ የቤተሰብ ኑሮ ለመመሥረት የሚያስችሉ መሠረቶች ናቸው።
የትኛውም ቤተሰብ የተሳካለት እንዲሆን የሚረዳው መሠረታዊ ባሕርይ ፍቅር መሆኑ ምንም የሚያጠያይቅ አይደለም። ሐዋርያው ጳውሎስ “ፍቅራችሁ ያለግብዝነት ይሁን። . . . በወንድማማች መዋደድ እርስ በርሳችሁ [“አጥብቃችሁ፣” NW] ተዋደዱ” በማለት ተናግሯል። (ሮሜ 12:9, 10) ብዙዎች “ፍቅር” ለሚለው ቃል የተሳሳተ ትርጉም ሰጥተውታል። ይሁን እንጂ ጳውሎስ እዚህ ላይ የገለጸው የፍቅር ባሕርይ በዓይነቱ ለየት ያለ ነው። ይህ ፍቅር አምላካዊ ፍቅር ሲሆን “ለዘወትር አይወድቅም።” (1 ቆሮንቶስ 13:8) መጽሐፍ ቅዱስ ይህ ዓይነቱ ፍቅር ከራስ ወዳድነት ነፃና ሌሎችን ለማገልገል ዝግጁ እንደሆነ ይገልጻል። ለሌሎች ጥቅም ይሠራል። ታጋሽና ደግ፣ ፈጽሞ የማይቀና፣ የማይኮራ ወይም ጉራውን የማይነዛ ነው። የራሱን ጥቅም አይፈልግም። ሁልጊዜ ሌሎች የሚሠሩትን ስህተት ለማለፍ፣ ሌላውን ለማመን፣ ተስፋ ለማድረግና የሚመጡትን ነገሮች ሁሉ በጽናት ለማለፍ ዝግጁ ነው።—1 ቆሮንቶስ 13:4-7
ልባዊ የሆነ ፍቅር አለመግባባቶችን ለመቀነስና የተለያየ አስተዳደግና ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ተስማምተው እንዲኖሩ ለማድረግ ይረዳል። በትዳር መፍረስ ወይም በወላጅ ሞት ምክንያት የሚመጡ ጭንቀቶችን ለመቋቋም ይረዳል። ከጊዜ በኋላ የእንጀራ አባት የሆነ አንድ ሰው የነበሩበትን ችግሮች ሲገልጽ እንዲህ ብሏል:- “ከመጠን በላይ ስለ ራሴ ስሜቶች ብቻ አስብ ስለነበር የእንጀራ ልጆቼንም ሆነ የባለቤቴን ስሜቶች ችላ አልኩ። ቶሎ የመጎዳትን ስሜት ማሸነፍ እንዳለብኝ መማር ነበረብኝ። ከሁሉም ይበልጥ ደግሞ የትሕትናን ባሕርይ መማር ነበረብኝ።” አስፈላጊ የሆኑ ማስተካከያዎች እንዲያደርግ ፍቅር ረዳው።
ወላጅ አባት ወይም እናት
ልጆች አሁን እቤት ከሌለው ወላጃቸው ጋር መገናኘታቸውን በተመለከተ ተገቢ የሆነ አመለካከት ለመያዝ ፍቅር ሊረዳ ይችላል። አንድ የእንጀራ አባት እንደሚከተለው በማለት የሚሰማውን ተናግሯል:- “የእንጀራ ልጆቼ በአንደኛ ደረጃ እኔን እንዲወዱ እፈልግ ነበር። ወላጅ አባታቸውን ለመጠየቅ በሚሄዱበት ጊዜ እርሱን እነቅፍ ነበር። ከእርሱ ጋር ውለው ተደስተው ሲመለሱ እበሳጫለሁ። አዝነው ሲመለሱ ደግሞ ደስ ይለኛል። ለእኔ ያላቸውን ፍቅር አጣ ይሆን እያልኩ እፈራለሁ። ከሁሉም የከፋው ደግሞ ወላጅ አባታቸው በእንጀራ ልጆቼ ሕይወት ውስጥ የሚጫወተውን ሚና አምኜ ለመቀበል መቸገሬ ነበር።”
ይህ የእንጀራ አባት “ወዲያው” የእንጀራ ልጆችን ፍቅር ማትረፍ አለብኝ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አለመሆኑን እንዲገነዘብ የረዳው እውነተኛ ፍቅር ማዳበሩ ነው። የእንጀራ ልጆቹ ወዲያው ባይቀበሉት እንደተጠላ ሆኖ ሊሰማው አይገባም። ወላጅ አባታቸው በልጆቹ ልብ ውስጥ የነበረውን ቦታ ሙሉ በሙሉ መተካት እንደማይችል ይህ የእንጀራ አባት የኋላ ኋላ ተገነዘበ። ልጆቹ ወላጅ አባታቸውን የሚያውቁት ከልጅነታቸው ጀምሮ ሲሆን እንጀራ አባታቸው ግን በቅርቡ የመጣ በመሆኑ የልጆቹን ፍቅር ለማትረፍ ጠንክሮ መሥራት ይኖርበታል። ኤልዛቤት አነስታይን የተባሉ አንዲት ተመራማሪ “ወላጆች በሌላ በማንም ሊተኩ አይችሉም። ሌላው ቀርቶ በሞት የተለየ ወይም ልጆቹን ትቶ የሄደ ወላጅ እንኳ ሳይቀር በልጆቹ ልብ ውስጥ ሁሌ ሲታሰብ ይኖራል” ሲሉ የተናገሩት አነጋገር የብዙዎችን አመለካከት የሚያንጸባርቅ ነው።
ተግሣጽ—ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ጉዳይ
መጽሐፍ ቅዱስ በፍቅር ላይ የተመሠረተ ተግሣጽ ለልጆች መስጠት እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ይገልጻል። ይህ ደግሞ የእንጀራ ልጆችንም ይጨምራል። (ምሳሌ 8:33) መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ከሚሰጠው ሐሳብ ጋር የሚስማሙ በርካታ ባለሙያዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ፕሮፌሰር ሲርዝ አልቭስ ደ አራዙ ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “በተፈጥሮው እገዳ ሲጣልበት የሚወድ ማንም ሰው የለም። ይሁን እንጂ ይህ አስፈላጊ ነው። አንድ ነገር አንዳይደረግ ‘መከልከል’ ከአደጋ የሚጠብቅ ነው።”
ይሁን እንጂ ስለ ተግሣጽ የሚኖራቸው አመለካከትም የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ሰፊ ልዩነት እንዲፈጠር ምክንያት ሊሆን ይችላል። የእንጀራ ልጆቹ አሁን አብሯቸው በማይኖረው ሰው በከፊል ተቀርጸዋል። የእንጀራ ወላጅ ሊያናድድ የሚችል አንድ ዓይነት ጠባይ ወይም ልማድ ይኖረው ይሆናል። በተጨማሪም የእንጀራ ወላጃቸው በአንዳንድ ጉዳዮች ረገድ ለምን ጥብቅ እንደሆነ ላይገነዘቡ ይችላሉ። ታዲያ እንዲህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ ችግሩን መወጣት የሚቻለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ‘ፍቅርን፣ መጽናትን፣ የዋህነትን ተከታተሉ’ ሲል አጥብቆ መክሯል። (1 ጢሞቴዎስ 6:11) ክርስቲያናዊ ፍቅር የእንጀራ ወላጅና ልጆች ይበልጥ እንዲግባቡ የሚረዷቸውን የየዋህነትንና የታጋሽነትን ባሕርይ እንዲያዳብሩ ሊረዳቸው ይችላል። የእንጀራ ወላጅዬው ትዕግሥት የለሽ፣ ‘ንዴተኛ፣ ቁጡና ተሳዳቢ’ ከሆኑ ተመሥርቶ የነበረው ዝምድና ሙሉ በሙሉ ሊናድ ይችላል።—ኤፌሶን 4:31
በዚህ ረገድ ሊረዳ እንደሚችል ነቢዩ ሚክያስ ተጨማሪ ማስተዋል ይሰጣል። “እግዚአብሔር ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን [“ፍትሕን፣” NW] ታደርግ ዘንድ፣ ምሕረትንም [“ደግነትን፣” NW] ትወድድ ዘንድ፣ ከአምላክህም ጋር በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” በማለት ተናግሯል። (ሚክያስ 6:8) ተግሣጽ በሚሰጥበት ጊዜ ፍትሕን ማንጸባረቅ እጅግ አስፈላጊ ነው። ደግነትን ስለማሳየትስ ምን ለማለት ይቻላል? አንድ ክርስቲያን ሽማግሌ የእንጀራ ልጆቹ ጠዋት ተነስተው በጉባኤ አምልኮ እንዲካፈሉ ለማድረግ ብዙውን ጊዜ ችግር ይገጥመው እንደነበር ተናግሯል። እነርሱን ከመነዝነዝ ይልቅ በደግነት ጥረት ማድረጉን ቀጠለ። በማለዳ ተነስቶ ቁርስ ያዘጋጅና ለሁሉም የሚጠጣ ትኩስ ነገር ይሰጣቸዋል። በዚህም የተነሳ ጠዋት እንዲነሱ የሚያቀርብላቸውን ጥያቄ ለመቀበል ይበልጥ ቀላል ይሆንላቸው ጀመር።
ፕሮፌሰር አና ሉዊዛ ቭዬራ ደ ማቶስ የሚከተለውን ጥሩ አስተያየት ሰንዝረዋል:- “ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የቤተሰቡ ሁኔታ ሳይሆን ቤተሰቡ ምን ዓይነት ጥሩ ግንኙነት አለው የሚለው ነው። ብዙውን ጊዜ የጠባይ ችግር ያለባቸው ልጆች የሚወጡት የተዳከመ የወላጅ ቁጥጥር ካለባቸው፣ ጥሩ መመሪያና የሐሳብ ግንኙነት ከሌለባቸው ቤተሰቦች እንደሆነ ባደረግኩት ጥናት ለመረዳት ችዬአለሁ።” አክለውም “ልጆችን ማሳደግ አንዳንድ ነገሮችን እንዳይፈጽሙ መከልከልንም ይጨምራል ብሎ መናገሩ የተጋነነ አይደለም።” ከዚህም በተጨማሪ ዶክተር ኢምሊ እና ጆን ቪሽር እንዲህ በማለት ገልጸዋል:- “በመሠረቱ ተግሣጽ ግቡን ሊመታ የሚችለው ተግሣጽ ተቀባዩ ተግሣጽ የሚሰጠውን ሰው አስተያየት የሚቀበልና ከግለሰቡ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዳያጣ የሚፈልግ ከሆነ ብቻ ነው።”
ይህ አስተያየት የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ተግሣጽ መስጠት የሚኖርበት ማን ነው የሚለውን ጥያቄ ያስነሳል። አንድ ነገር መከልከል በሚያስፈልግበት ጊዜ መከልከል ያለበት ማን ነው? አንዳንድ ወላጆች ጉዳዩን ከተወያዩበት በኋላ የእንጀራ ወላጁ ከልጆቹ ጋር ጥሩ ቅርርብ ለመፍጠር የሚያስችለው ጊዜ እንዲያገኝ ለማድረግ ሲሉ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ወላጅ የሆነው ራሱ ተግሣጹን እንዲሰጥ ተስማምተዋል። የእንጀራ ወላጅየው ለልጆቹ ተግሣጽ መስጠት ከመጀመሩ በፊት የሚያፈቅራቸው መሆኑን እንዲያዩ አጋጣሚ ሊሰጣቸው ይገባል።
የእንጀራ ወላጅየው አባት ከሆነስ? አባት የቤት ራስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ ይናገር የለምን? አዎን፣ ይናገራል። (ኤፌሶን 5:22, 23፤ 6:1, 2) ይሁን እንጂ የእንጀራ አባትየው ተግሣጽ መስጠትን በተለይ ደግሞ መቅጣትን በሚመለከት ለተወሰነ ጊዜ ይህን ኃላፊነት ለእናትዬው መተው ይፈልግ ይሆናል። ልጆቹ ‘[የአዲሱ] አባታቸውን ምክር ለመስማት’ የሚያስችላቸውን መሠረት በሚጥልበት ጊዜ ልጆቹ ‘የእናታቸውን ሕግ’ እንዲታዘዙ ሊያደርግ ይችላል። (ምሳሌ 1:8፤ 6:20፤ 31:1) ማስረጃዎች እንዳሳዩት ይህ የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት የሚያስጥስ አይሆንም። ከዚህ በተጨማሪ አንድ የእንጀራ አባት ሲናገር:- “ተግሣጽ ወቀሳ፣ እርማትና ምክር መስጠትን የሚጨምር እንደሆነ አስታውሳለሁ። ይህ በትክክል፣ በፍቅርና በርህራሄ መንገድ ከተሰጠና ወላጃዊ ምሳሌነት ከታከለበት ብዙውን ጊዜ ይሠራል።”
ወላጆች መነጋገር ይኖርባቸዋል
ምሳሌ 15:22 እንዲህ ይላል:- “ምክር ከሌለች ዘንድ የታሰበው ሳይሳካ ይቀራል።” የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ያሉ ወላጆች በተረጋጋና ግልጽ በሆነ መንገድ መነጋገራቸው እጅግ አስፈላጊ ነው። ኦ ኢስታዶ ደ ኤስ ፓውሎ የተባለው ጋዜጣ አዘጋጅ “ልጆች ሁልጊዜ ወላጆች ያወጧቸውን ገደቦች ለመዳፈር ይሞክራሉ” በማለት ዘግበዋል። የእንጀራ ወላጅ ሲሆን ደግሞ እንዲህ ያለው ሁኔታ የባሰ ሊሆን ይችላል። ስለዚህም ወላጆች አንድ ዓይነት አቋም እንዳላቸው ልጆች ማየት ይችሉ ዘንድ የተለያዩ ጉዳዮች በሚነሱበት ጊዜ ወላጆች ስምም ሆነው መገኘት ይኖርባቸዋል። ይሁን እንጂ ወላጅየው፣ የእንጀራ ወላጅ የሆነው ግለሰብ ያደረገው ነገር ትክክል እንዳልሆነ ሲሰማውስ? እንደዚህ ያለ ሁኔታ በሚፈጠርበት ጊዜ በልጆቹ ፊት ሳይሆን ለብቻቸው ሆነው መነጋገር ይኖርባቸዋል።
ዳግመኛ ያገባች አንዲት እናት እንዲህ በማለት ተናግራለች:- “ለአንዲት እናት ከሁሉ የከፋው ከባድ ነገር የእንጀራ አባት ልጅዋን ሲቀጣ መመልከቷ ነው። በተለይ ደግሞ የእንጀራ አባትየው ልጅዋን እየቀጣ ያለው ሳያገናዝብ ወይም ያለ አግባብ እንደሆነ ከተሰማት ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነው። ድርጊቱ ስሜቷን ሊነካውና ለልጅዋ እንድትቆረቆር ሊያደርጋት ይችላል። እንዲህ ባለ ጊዜ ለባሏ ታዛዥና ደጋፊ መሆን ይከብዳታል።
“አንድ ጊዜ 12 ዓመትና 14 ዓመት የሆናቸው ወንድ ልጆቼ አንድ ነገር ማድረግ ፈልገው የእንጀራ አባታቸውን ፈቃድ ይጠይቃሉ። እርሱ ግን ለምን እንደጠየቁ ምክንያታቸውን ሳይሰማ አይቻልም ብሏቸው ክፍሉን ለቆ ወጣ። ልጆቹ እንባቸው በዓይናቸው ላይ ቅርር አለ፤ እኔም መናገር አቅቶኝ ዝም አልኩ። ታላቅየው ልጅ ወደ እኔ ዞር ብሎ ‘እማማ፣ ያደረገውን አየሽ?’ ብሎ ተናገረ። እኔም ‘አዎን፣ አይቻለሁ። ቢሆንም የቤቱ ራስ እርሱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞ የራስነት ስልጣን እንድናከብር ይነግረናል’ ብዬ መለስኩለት። ጥሩ ልጆች ስለነበሩ ባልኩት ነገር ተስማሙና ዝም አሉ። በዚያኑ ዕለት ምሽት ሁሉንም ነገር ለባለቤቴ ነገርኩት። እርሱም ሥልጣኑን በአምባገነንነት እንደተጠቀመበት ወዲያው ተገነዘበ። ከዚያም በቀጥታ ወደ ልጆቹ መኝታ ቤት ሄደና ይቅርታ ጠየቃቸው።
“በዚያን ጊዜ ከደረሰው ነገር ብዙ ነገር ተማርን። ባለቤቴ አንድ ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት ማዳመጥ እንዳለበት ተማረ። እኔም ለመቀበል የሚከብድ ቢሆንብኝም እንኳ የራስነትን መሠረታዊ ሥርዓት ከፍ አድርጌ መመልከት እንዳለብኝ ተገነዘብኩ። ልጆቹም ታዛዥ የመሆንን አስፈላጊነት ተማሩ። (ቆላስይስ 3:18, 19) እንዲሁም ባለቤቴ ከልቡ ይቅርታ መጠየቁ ትሕትናን በማሳየት በኩል ከፍተኛ ትምህርት አስተማረን። (ምሳሌ 29:23) ዛሬ ሁለቱም ወንዶች ልጆች ክርስቲያን ሽማግሌዎች ናቸው።”
ስህተት ሊሠራ ይችላል። ልጆች የሚጎዱ ቃላትን ሊሰነዝሩ ወይም የሚጎዱ ነገሮችን ሊያደርጉ ይችላሉ። ነገሮች ልክ እንደተፈጸሙ የሚፈጥሩት ጭንቀት የእንጀራ ወላጆች ምክንያታዊ ያልሆነ እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል። ይሁን እንጂ “እባክህ ይቅርታ አድርግልኝ” የሚሉት ቃላት የተፈጠረው ቁስል እንዲፈወስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ።
የቤተሰብን አንድነት ማጠናከር
የእንጀራ ወላጅ ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ሞቅ ያለ ወዳጅነት መመሥረት ጊዜ ይጠይቃል። የእንጀራ ወላጅ ከሆናችሁ ርኅራኄ ማሳየት ይኖርባችኋል። ማስተዋል ይኑራችሁ፣ ከልጆቹ ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ጥረት አድርጉ። ከትንንሾቹ ጋር አብራችሁ ተጫወቱ። በዕድሜ ትላልቅ ከሆኑት ጋር ለመጨዋወት ዝግጁዎች ሁኑ። አብራችሁ ጊዜ ማሳለፍ የምትችሉባቸውን አጋጣሚዎች ፈልጉ፤ ለምሳሌ ምግብ ማዘጋጀትን ወይም መኪና ማጠብን የመሰሉ የቤት ውስጥ ሥራዎችን አብረዋችሁ እንዲሠሩ ጋብዟቸው። ገበያ ስትወጡ አብረዋችሁ እንዲሄዱ ጋብዟቸው። በተጨማሪም የምትወዷቸው መሆናችሁን በተግባር በመግለጽ ለእነርሱ ያላችሁን ፍቅር ማሳየት ትችላላችሁ። (እርግጥ የእንጀራ አባቶች የእንጀራ ሴት ልጆቻቸውን ወሰን እንዳያልፉና እነርሱን የሚያሳፍር ድርጊት እንዳይፈጽሙ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። እንዲሁም የእንጀራ እናቶች ወንድ ልጆቻቸው ወሰን እንዳላቸው ማወቅ ይኖርባቸዋል።)
የእንጀራ ወላጅ ያለበት ቤተሰብ ስኬታማ ሊሆን ይችላል። ብዙዎችም ተሳክቶላቸዋል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው በተለይ ደግሞ ወላጆች ትክክለኛ ዝንባሌ ማዳበራቸውና ምክንያታዊ የሆኑ ነገሮችን መጠበቃቸው ከሌሎች በተሻለ መንገድ ስኬታማ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ “ወዳጆች ሆይ፣ ፍቅር ከእግዚአብሔር ስለ ሆነ፣ . . . እርስ በርሳችን እንዋደድ” በማለት ጽፏል። (1 ዮሐንስ 4:7) አዎን፣ የእንጀራ ወላጅ ያለበት ቤተሰብ ደስተኛ እንዲሆን የሚያስችለው ብቸኛ ቁልፍ ልባዊ የሆነ ፍቅር ነው።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኙ ሥዕሎች]
የእንጀራ ወላጅ ያለበት ደስተኛ ቤተሰብ:-
የአምላክን ቃል አብሮ ያጠናል . . .
አብሮ ጊዜ ያሳልፋል . . .
ይነጋገራል . . .
አብሮ ይሠራል . . .