አስተሳሰብህን የሚቀርጸው ማን ነው?
“ምን ማሰብ እንዳለብኝና ምን ማድረግ እንዳለብኝ ማንም እንዲነግረኝ አልፈልግም!” ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለው የአጽንዖት አነጋገር በራስህም ሆነ በማመዛዘን ችሎታህ ከልክ በላይ የምትተማመን መሆንህን የሚያሳይ ነው። አንተስ እንደዚህ ይሰማሃልን? እርግጥ ነው ማንም ሰው በአንተ ቦታ ሆኖ ሊወስንልህ አይገባም። ሆኖም የኋላ ኋላ ጥሩ ውጤት ሊያስገኝ የሚችለውንም ምክር ጭምር በችኮላ አልቀበልም ማለት ጥበብ ነውን? ከዚህ ቀደም በጥበብ ላይ የተመሠረቱ ውሳኔዎችን ማድረግ ትችል ዘንድ አንድም ሰው ረድቶህ አያውቅም? እየታወቀህም ሆነ ሳይታወቅህ በማንም እንዳልተቀረጽህ በእርግጠኝነት መናገር ትችላለህን?
ለምሳሌ ያህል ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከመፈንዳቱ በፊት የሂትለር የፕሮፓጋንዳ ሚንስትር የነበረው ዮዜፍ ጎብልስ የጀርመንን የፊልም ኢንዱስትሪ በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ነበር። ለምን? ምክንያቱም “በሰዎች አመለካከት ብሎም በባሕርያቸው ላይ ተጽእኖ ለማሳደር” ከዚህ የተሻለ መሣሪያ እንደሌለ ተገንዝቦ ስለነበር ነው። (ፕሮፓጋንዳ እና የጀርመን ሲኒማ 1933-1945) ጤነኛና ጥሩ የማመዛዘን ችሎታ የነበረው ተራው ሕዝብ የናዚን ፍልስፍና በጭፍን እንዲከተል ለማድረግ በዚህም ሆነ በሌሎች ዘዴዎች በመጠቀም ረገድ ምን ያህል እንደተሳካለት ታውቅ ይሆናል።
የምታዳምጣቸው ሰዎች ስሜትና አመለካከት በአስተሳሰብህ ብሎም በድርጊትህ ላይ ምንጊዜም የተወሰነ ተጽዕኖ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። እርግጥ ይህ ጨርሶ መጥፎ ነው ማለት አይደለም። እነዚህ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብህ ሰዎች እንደ አስተማሪዎችህ፣ ጓደኞችህ ወይም ወላጆችህ ያሉ ለአንተ በጎ የሚያስቡ ሰዎች ከሆኑ የሚሰጡህ ምክርና ሐሳብ በጣም ይጠቅምሃል። ይሁን እንጂ ለራሳቸው ጥቅም ብቻ የቆሙና ሐዋርያው ጳውሎስ “የሚያታልሉ” ብሎ እንደገለጻቸው ዓይነት ሰዎች የተዛባ ወይም የተበላሸ አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ከሆኑ መጠንቀቅ ይኖርብሃል!—ቲቶ 1:10፤ ዘዳግም 13:6-8
ስለዚህ ማንም ሰው ተጽዕኖ ሊያሳድርብኝ አይችልም ብለህ አታስብ። (ከ1 ቆሮንቶስ 10:12 ጋር አወዳድር።) እንዲያውም በአሁኑ ሰዓት ምናልባትም ለማመን ሊያስቸግርህ በሚችል መጠን ሳይታወቅህ ሌሎች ተጽዕኖ እያሳደሩብህ ሊሆን ይችላል። ገበያ ወጥተህ ለመግዛት የምትመርጠውን ዕቃ እንደ ቀላል ምሳሌ ልንወስድ እንችላለን። ያንን ዕቃ መግዛት የመረጥከው ያለማንም ግፊት በራስህ ፍላጎት ተነሳስተህ ነው? ወይስ ሌሎች ሰዎች ብዙውን ጊዜ በስውር፣ በረቀቀ ሆኖም ኃይል ባለው መንገድ በምርጫህ ላይ ተጽዕኖ አሳድረውብህ ይሆን? ይህን በተመለከተ ጥናት ያደረጉ ኤሪክ ክላርክ የተባሉ አንድ ጋዜጠኛ እንደዚያ ይሰማቸዋል። “ለንግድ ማስታወቂያዎች ውርጅብኝ ይበልጥ ስንጋለጥ የሚያሳድሩትን ተጽዕኖ እምብዛም አንገነዘበውም። ሆኖም የዚያኑ ያክል ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድሩብናል” ሲሉ ተናግረዋል። ሰዎች የንግድ ማስታወቂያ ተጽዕኖ እንዳለውና እንደሌለው ሲጠየቁ “ብዙዎች ተጽዕኖ እንዳለው ይስማማሉ፤ ግን በእነሱ ላይ አይደለም” በማለት ሪፖርት አድርገዋል። የተቀረው ሰው ሁሉ ለአደጋው የተጋለጠ እንደሆነ ቢሰማቸውም እነርሱን ግን ምንም እንደማይነካቸው አድርገው ያስባሉ። “እነሱ ጨርሶ እንደማይበገሩ ይሰማቸዋል።”—ዘ ዋንት ሜከርስ
ሰይጣን እርሱ በሚፈልገው መንገድ እየቀረጸህ ይሆን?
በየዕለቱ የሚቀርቡ የንግድ ማስታወቂያዎች የሚያሳድሩብህ ተጽእኖ ይሄን ያህል አደገኛ ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ በጣም አደገኛ የሆነ ሌላ ዓይነት ተጽዕኖ አለ። ሰይጣን የወጣለት ሸረኛ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል። (ራእይ 12:9) የእሱ ፍልስፍና ደንበኞችን በሁለት መንገዶች ማለትም “በማባበል ወይም አእምሮአቸውን በማለማመድ” በቁጥጥር ሥር ማስገባት ይቻላል የሚል አመለካከት ካለው ከአንድ የንግድ ማስታወቂያ ወኪል ጋር የሚመሳሰል ነው። ፕሮፓጋንዳ ነዢዎችና የንግድ ማስታወቂያ አዘጋጂዎች አስተሳሰብህን ለመቅረጽ በእነዚህ የረቀቁ ዘዴዎች የሚጠቀሙ ከሆነ ታዲያ ሰይጣን እነዚህኑ ዘዴዎች በመጠቀም ረገድ ምንኛ የተዋጣለት ይሆን!—ዮሐንስ 8:44
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ጉዳይ በሚገባ ያውቅ ነበር። ትጥቃቸውን ያላሉ አንዳንድ መሰል ክርስቲያኖች በሰይጣን የማታለያ ዘዴዎች ይወድቃሉ የሚል ፍራቻ ነበረው። “እባብ በተንኮሉ ሔዋንን እንዳሳታት፣ አሳባችሁ ተበላሽቶ ለክርስቶስ ከሚሆን ቅንነትና ንጽሕና ምናልባት እንዳይለወጥ ብዬ እፈራለሁ” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 11:3) ይህንን ማስጠንቀቂያ ልብ ልትለው ይገባል። አለበለዚያ ግን ፕሮፓጋንዳና ማባበያ መሥራት ይሠራል “ሆኖም በእኔ ላይ አይሠራም” እንደሚሉት ዓይነት ሰዎች ልትሆን ትችላለህ። ሰይጣናዊ ፕሮፓጋንዳ ምን ያህል እንደሚሠራ የዚህ ትውልድ መለያ ምልክት ከሆነው በዙሪያችን ከምናየው ጭካኔ፣ ወራዳ ምግባርና ግብዝነት በግልጽ መረዳት ይቻላል።
በዚህም የተነሳ ጳውሎስ እንደ እርሱ ያሉ ክርስቲያኖችን ‘ይህን ዓለም አትምሰሉ’ ሲል ተማጽኗቸዋል። (ሮሜ 12:2) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚ እነዚህን የጳውሎስ ቃላት “በዙሪያችሁ ያለው ዓለም በራሱ መልክ እንዳይቀርጻችሁ ተጠንቀቁ” በማለት ቀለል ባለ አገላለጽ ተርጉመውታል። (ሮሜ 12:2 ፊሊፕስ) በጥንት ጊዜ የነበረ አንድ ሸክላ ሠሪ የሸክላ ጭቃውን በቅርጽ ማውጫው ላይ በማስቀመጥ እርሱ የፈለገውን መልክና ቅርጽ ይዞ እንዲወጣ እንደሚያደርግ ሁሉ ሰይጣንም እርሱ በፈለገው መንገድ አንተን ለመቅረጽ የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። ሰይጣን ይህን ዓላማውን ለማሳካት የዓለምን ፖለቲካ፣ ሃይማኖትና መዝናኛ እንደ መሣሪያ አድርጎ ይጠቀማል። ለመሆኑ የሰይጣን ተጽዕኖ ምን ያክል ተስፋፍቷል? በሐዋርያው ዮሐንስ ዘመን የነበረውን ያክል አሁንም ተስፋፍቶ ይገኛል። ዮሐንስ ‘ዓለም በሞላው በክፉው ተይዟል’ በማለት ተናግሯል። (1 ዮሐንስ 5:19፤ በተጨማሪም 2 ቆሮንቶስ 4:4ን ተመልከት።) ሰይጣን ሰዎችን ለማታለልና አስተሳሰባቸውን ለመበከል ያለውን ችሎታ የምትጠራጠር ከሆነ አምላክን ለማገልገል ወስኖ የነበረውን መላውን የእስራኤል ብሔር ለማታለልና አስተሳሰባቸውን ለመበከል ያደረገው ጥረት ምን ያክል ተሳክቶለት እንደነበር አስታውስ። (1 ቆሮንቶስ 10:6-12) በአንተም ላይ ተመሳሳይ ነገር ሊደርስ ይችላል? አታላይ ለሆኑ የሰይጣን ተጽዕኖዎች አእምሮህን ክፍት ካደረግህ ተመሳሳይ ነገር ሊደርስብህ ይችላል።
ምን እየተካሄደ እንዳለ ማወቅ
አብዛኛውን ጊዜ እነዚህ ስውር ተጽዕኖዎች አስተሳሰብህን የሚቀርጹት ከፈቀድክላቸው ብቻ ነው። ቫንስ ፓካርድ ዘ ሂድን ፐርሱዌደርስ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ የሚከተለውን ቁም ነገር አስፍረዋል:- “እነዚህን የመሰሉ [ስውር] ተጽዕኖዎች የምንቋቋምበት ጠንካራ መከላከያ አለን። በተጽዕኖዎቹ ላለመሸነፍ መምረጥ እንችላለን። በዚያም ሆነ በዚህ ምርጫ አለን፤ ምን እየተካሄደ እንዳለ ካወቅን በቀላሉ አንታለልም።” ፕሮፓጋንዳና ማታለያዎችን በተመለከተም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው።
እርግጥ ነው “ምን እየተካሄደ እንዳለ ማወቅ” እንዲቻል ጥሩ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ነገሮችን ለመቀበል አእምሮህን ክፍት ማድረግ ይኖርብሃል። ጤነኛ አእምሮ በትክክል እንዲሠራ ከተፈለገ ልክ እንደ ጤነኛ አካል በደንብ መመገብ ይኖርበታል። (ምሳሌ 5:1, 2) የተሳሳተ መረጃ አጥፊ እንደሆነ ሁሉ በቂ መረጃ ሳያገኙ መቅረትም የዚያኑ ያክል አጥፊ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አሳሳች የሆኑ ሐሳቦችና ፕሮፓጋንዳዎች ወደ አእምሮህ እንዳይገቡ መከላከልህ ተገቢ ቢሆንም የሚቀርቡልህን ምክሮች ወይም መረጃዎች በሙሉ አፍራሽ በሆነና ጥርጣሬ ባዘለ መንገድ እንዳትመለከት መጠንቀቅ ይኖርብሃል።—1 ዮሐንስ 4:1
በሐቅ ላይ የተመሠረተ አሳማኝ ማስረጃ ከሐሰት ወሬ ፈጽሞ የተለየ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያሳቱና እየሳቱ፣ በክፋት እየባሱ” ከሚሄዱ ‘ክፉ ሰዎች’ እንዲጠነቀቅ ወጣቱን ጢሞቴዎስን አሳስቦታል። ከዚያም ጳውሎስ “አንተ ግን በተማርህበትና በተረዳህበት [“እንድታምን በተደረግህበት፣” NW] ነገር ጸንተህ ኑር፣ ከማን እንደ ተማርኸው ታውቃለህና” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (2 ጢሞቴዎስ 3:13, 14) ወደ አእምሮህ የምታስገባው ማንኛውም ነገር በተወሰነ መጠን በአንተ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩ ስለማይቀር ነገሩ ትክክል መሆኑንና አለመሆኑን ለማረጋገጥ የሚረዳህ ቁልፍ ‘የተማርከው ከእነማን እንደሆነ’ ማለትም የራሳቸውን ሳይሆን ስለ አንተ ደህንነት ከልብ ከሚያስቡ ሰዎች መሆኑን ማረጋገጥ ይኖርብሃል።
ምርጫው የአንተ ነው። የዚህ ዓለም ፍልስፍናና የሥነ ምግባር አቋም አስተሳሰብህን እንዲቆጣጠረው በመፍቀድ ‘ይህን ዓለም ለመምሰል’ ልትመርጥ ትችላለህ። (ሮሜ 12:2) ይሁን እንጂ ይህ ዓለም ለአንተ ደህንነት የሚጨነቅ አይደለም። በዚህም የተነሳ ሐዋርያው ጳውሎስ “እንደ ሰው ወግና እንደ ዓለማዊ እንደ መጀመሪያ ትምህርት ባለ በፍልስፍና በከንቱም መታለል ማንም እንዳይማርካችሁ ተጠበቁ” በማለት ያስጠነቅቃል። (ቆላስይስ 2:8) ሰይጣን በሚፈልገው መንገድ ለመቀረጽ ወይም ‘በከንቱ መታለል ለመወሰድ’ ምንም ልፋት አይጠይቅም። ሲጋራ በሚያጨስ ሰው አጠገብ የመቀመጥ ያክል ነው። የተበከለውን አየር በመተንፈስ ብቻ ጉዳት ላይ ልትወድቅ ትችላለህ።
በሌላው በኩል ደግሞ ያንን ‘አየር’ ላለመተንፈስ ትችላለህ። (ኤፌሶን 2:2) የጳውሎስን ምክር ተከተል:- “የእግዚአብሔር ፈቃድ እርሱም በጎና ደስ የሚያሰኝ ፍጹምም የሆነው ነገር ምን እንደ ሆነ ፈትናችሁ ታውቁ ዘንድ በልባችሁ መታደስ ተለወጡ።” (ሮሜ 12:2) እንዲህ ማድረጉ ጥረት ይጠይቃል። (ምሳሌ 2:1-5) ይሖዋ ማንንም በተንኮል እንደማያታልል አስታውስ። አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎችን በሙሉ አቅርቧል። ይሁን እንጂ ከዚህ ጥቅም ለማግኘት ማዳመጥና አስተሳሰብህን እንዲቀርጸው መፍቀድ አለብህ። (ኢሳይያስ 30:20, 21፤ 1 ተሰሎንቄ 2:13) አእምሮህን ‘በቅዱሳን መጻሕፍት’ ማለትም አምላክ ባስጻፈው በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በሚገኘው እውነት ለመሙላት ፈቃደኛ መሆን አለብህ።—2 ጢሞቴዎስ 3:15-17
በይሖዋ እጅ ለመቀረጽ ፈቃደኛ መሆን
ይሖዋ ከሚያከናውነው ቅርጽ የማውጣት ሥራ ጥቅም ለማግኘት እንድትችል በአንተ በኩል ፈቃደኝነትና ታዛዥነት የማሳየቱን አስፈላጊነት ነቢዩ ኤርምያስ አንድ ሸክላ ሠሪ ሥራውን ወደሚያከናውንበት ቤት እንዲሄድ ይሖዋ ከነገረው ከባድ መልእክት ከሚያስተላልፈው ምሳሌያዊ አገላለጽ ለመመልከት ይቻላል። ኤርምያስ ሸክላ ሠሪው ሊሠራ ያሰበው ዕቃ “በሸክላ ሠሪው እጅ” በተበላሸ ጊዜ ሌላ ዕቃ ለመሥራት ሐሳቡን እንደቀየረ ተመልክቷል። ከዚያም ይሖዋ “የእስራኤል ቤት ሆይ፣ ይህ ሸክላ ሠሪ እንደሚሠራ በውኑ እኔ በእናንተ ዘንድ መሥራት አይቻለኝምን? እነሆ፣ ጭቃው በሸክላ ሠሪ እጅ እንዳለ፣ እንዲሁ እናንተ በእኔ እጅ አላችሁ” በማለት ተናገረ። (ኤርምያስ 18:1-6) ታዲያ ይህ ማለት የእስራኤል ብሔር በይሖዋ እጅ ያሉ ሕይወት አልባ ጭቃ እንደሆኑና እርሱም በማን አለብኝነት የፈለገውን ዓይነት ቅርጽ ሊሰጣቸው እንደሚችል ያሳያልን?
ይሖዋ ሁሉን ማድረግ የሚችለውን ኃይሉን በመጠቀም ሰዎች ከፈቃዳቸው ውጪ የሆኑ ነገሮችን እንዲያከናውኑ አያስገድድም። አንድ ሸክላ ሠሪ እንከን ኖሯቸው ለሚሠሩ ዕቃዎች ተጠያቂ ሊሆን ይችላል፤ ይሖዋ ግን በዚህ መንገድ ተጠያቂ አይሆንም። (ዘዳግም 32:4) እንከን መታየት የሚጀምረው ይሖዋ ጥሩ በሆነ መንገድ ሊቀርጻቸው ሲል መመሪያውን ለመከተል በማይፈልጉ ሰዎች ላይ ነው። በአንተና ሕይወት አልባ በሆነ በአንድ የሸክላ ዕቃ መካከል ያለው ትልቅ ልዩነት ይህ ነው። አንተ የመምረጥ ነፃነት አለህ። ይህን ነፃነትህን በመጠቀም ይሖዋ የሚያከናውነውን ቅርጽ የማውጣት ሥራ ለመቀበል ልትመርጥ ወይም ሆነ ብለህ ላለመቀበል ልትመርጥ ትችላለህ።
ምንኛ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ትምህርት ነው! “ምን ማድረግ እንዳለብኝ ማንም እንዲነግረኝ አልፈልግም” ብሎ በትዕቢት ከመናገር ይልቅ የይሖዋን ድምፅ መስማት ምንኛ የተሻለ ነው! ሁላችንም የይሖዋ አመራር ያስፈልገናል። (ዮሐንስ 17:3) “አቤቱ፣ መንገድህን አመልክተኝ፣ ፍለጋህንም አስተምረኝ” ብሎ እንደጸለየው መዝሙራዊ ዳዊት ሁን። (መዝሙር 25:4) ንጉሥ ሰሎሞን “ጠቢብ እነዚህን ከመስማት ጥበብን ይጨምራል” ብሎ የተናገረውን አስታውስ። (ምሳሌ 1:5) አንተስ ትሰማለህ? የምትሰማ ከሆነ “ጥንቃቄ [“የማሰብ ችሎታ፣” NW] ይጠብቅሃል፣ ማስተዋልም ይጋርድሃል።”—ምሳሌ 2:11