ምን ያህል ዕድሜ መኖር እንችላለን?
በጥቅሉ ሲታይ የሰዎች ዕድሜ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በመምጣቱ ብዙዎች ‘ምን ያህል ዕድሜ መኖር እንችላለን?’ ብለው እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል።
ቀደም ባሉት ጊዜያት ፒየር ዡቤር ከሁሉም ሰው ይበልጥ ረዥም እድሜ ኖረዋል ተብሎ ይታመን እንደነበረ ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ (1995) ገልጿል። በ1814 ሲሞቱ ዕድሜያቸው 113 ነበር። ከዚህ የሚበልጥ ዕድሜ የኖሩ ሰዎች እንዳሉ ቢነገርም ዕድሜያቸው ግን ተዓማኒነት ባለው ማስረጃ የተደገፈ አይደለም። ይሁን እንጂ አንድ ትክክለኛ መዝገብ በርካታ ሰዎች ከፒየር ዡቤር የበለጠ ዕድሜ እንደኖሩ አረጋግጧል።
ዣን ልዊዝ ካልሞ የተባሉት ሴት በደቡብ ምሥራቅ ፈረንሳይ በምትገኘው በአርል ከተማ የካቲት 21, 1875 ተወለዱ። ከ122 ዓመታት በላይ ኖረው ነሐሴ 4, 1997 ሲሞቱ ስለ እሳቸው ብዙ ተዘግቦ ነበር። የጃፓኑ ሺጌቺዮ ኢዙሚ በ1986 ሲሞቱ ዕድሜያቸው 120 ዓመት ነበር። ጊነስ ቡክ ኦቭ ሪኮርድስ 1999 የ118 ዓመቷ ሴራ ናውስ በጊዜው ከነበሩት ሰዎች ሁሉ ረጅም ዕድሜ በመኖር የመጀመሪያዋ ሴት መሆናቸውን ገልጾ ነበር። የተወለዱት በፔንሲልቬኒያ፣ ዩ ኤስ ኤ መስከረም 24, 1880 ነበር። በካናዳ፣ ኬቤክ ይኖሩ የነበሩት ማሪ-ልዊዝ ፌብሮኒ ሜየር በ1998 ሲሞቱ ዕድሜያቸው 118 ሲሆን ሴራን በ26 ቀናት ይበልጧቸው ነበር።
በእርግጥም የዕድሜ ባለ ጸጋ የሆኑ ሰዎች ቁጥር በሚያስደንቅ ሁኔታ እየጨመረ መጥቷል። በሚቀጥለው ምዕተ ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ መቶና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ቁጥር በ2.2 ሚልዮን እንደሚጨምር ይገመታል! በተመሳሳይም በ1970 26.7 ሚልዮን የነበረው 80 እና ከዚያ በላይ ዕድሜ ያላቸው ሰዎች ቁጥር በ1998 ወደ 66 ሚልዮን ከፍ ብሏል። ይህ 60 በመቶ ጭማሪ ከነበረው ከአጠቃላዩ የዓለም ሕዝብ ብዛት ጋር ሲወዳደር 147 በመቶ ጭማሪ ነው።
ሰዎች ረዥም ዕድሜ መኖር ብቻ ሳይሆን ብዙዎች የ20 ዓመት ጎረምሳ ማድረግ የማይችለውን ነገር በማድረግ ላይ ናቸው። በ1990 የ82 ዓመቱ ጆን ኬሊ 42.195 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነውን የማራቶን ውድድር በአምስት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ አጠናቀዋል። በ1991 ቅድመ አያት የሆኑት የ84 ዓመቷ አረጋዊት ማቪስ ሊንድግረን ይህንኑ ርቀት በሰባት ሰዓት ከዘጠኝ ደቂቃ ሸፍነዋል። አሁን በቅርቡ ደግሞ አንድ የ91 ዓመት ሰው በኒው ዮርክ ከተማ የተካሄደውን ማራቶን አጠናቀዋል!
ይህን ስንል ግን በጥንት ዘመን የነበሩ የዕድሜ ባለ ጸጋዎች አስደናቂ ነገሮችን አላደረጉም ማለታችን አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱሱ ፓትርያርክ አብርሃም በ99 ዓመቱ እንግዶቹን ‘ለመቀበል ሮጧል።’ ካሌብ በ85ኛው ዓመቱ ላይ እንዲህ ብሎ ነበር:- “ጉልበቴም በዚያን ጊዜ (ከ45 ዓመት በፊት) እንደ ነበረ፣ እንዲሁ ዛሬ፣ ለመዋጋት ለመውጣትም ለመግባትም ጉልበቴ ያው ነው።” እንዲሁም ሙሴ ዕድሜው 120 ዓመት ሲሞላ “ዓይኑ አልፈዘዘም፣ ጉልበቱም አልደነገዘም” በማለት መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል።—ዘፍጥረት 18:2፤ ኢያሱ 14:10, 11፤ ዘዳግም 34:7
ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የመጀመሪያ ሰው አዳምና መርከብ የሠራው ኖኅ በታሪክ የነበሩ ሰዎች መሆናቸውን ገልጿል። (ማቴዎስ 19:4-6፤ 24:37-39) የዘፍጥረት መጽሐፍ አዳም 930፣ ኖኅ ደግሞ 950 ዓመት እንደኖሩ ይናገራል። (ዘፍጥረት 5:5፤ 9:29) ሰዎች በእርግጥ ይህንን ያህል ረዥም ዕድሜ ኖረው ያውቃሉ? ከዚህ ለሚበልጥ ዘመን ምናልባትም ለዘላለም መኖር እንችል ይሆን? በሚቀጥለው ርዕስ ላይ የሚገኘውን ማስረጃ እባክህ መርምር።