ስለ ጊዜና ስለ ዘላለማዊነት የምናውቀው ምን ያህል ነው?
አንድ ኢንሳይክለፒዲያ “የሰው ልጅ ካጋጠሙት እጅግ ምስጢራዊ የሆኑ ነገሮች መካከል አንዱ ጊዜ ሳይሆን አይቀርም” ብሏል። አዎን፣ የጊዜን ፍቺ በቀላል ቃላት መግለጽ እጅግ አዳጋች ነው። ጊዜ “ይነጉዳል፣” “ይሮጣል፣” “ይከንፋል” እንዲሁም እኛ ራሳችንም “በጊዜ ሂደት” ውስጥ እየተጓዝን ነው ብለን እንናገር ይሆናል። ይሁን እንጂ በእርግጥ ስለ ምን ነገር እየተናገርን እንዳለን አናውቅም።
ጊዜ “በሁለት ክንውኖች መካከል ያለ ርቀት” የሚል ፍቺ ሲሰጠው ቆይቷል። ሆኖም ከተሞክሯችን ለመገንዘብ እንደቻልነው ጊዜ በክንውኖች የሚወሰን አይመስልም፤ ምንም ይከሰት ምን ጊዜ መጓዙን ይቀጥላል። አንድ ፈላስፋ ጊዜ እንዲያው ምናባዊ እንጂ በእርግጥ ያለ ነገር አይደለም ብሏል። ታዲያ ታሪካችን ሁሉ የተገነባበት ነገር አእምሯችን የፈጠረው ተራ ግምታዊ አሳብ ሊሆን ይችላልን?
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጊዜ ያለው አመለካከት
መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ጊዜ ምንም ፍቺ አይሰጥም፤ ይህ ደግሞ ምናልባት የጊዜ ትርጉም ከሰው ልጅ የመረዳት አቅም በላይ በመሆኑ ሊሆን ይችላል። እኛ ሰዎች መጀመሪያና መጨረሻውን መረዳት አስቸጋሪ ከሆነብን ከጠፈር ጋር ተመሳሳይ ነው። አምላክ “ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ” የሚኖር በመሆኑ እርሱ ብቻ ሙሉ በሙሉ ሊረዳቸው ከሚችላቸው ነገሮች መካከል አንዱ ጊዜ ነው።—መዝሙር 90:2
መጽሐፍ ቅዱስ ምንም እንኳ የጊዜን ፍቺ ባይሰጥም ጊዜ በእርግጥ ያለ ነገር መሆኑን ይናገራል። ለምሳሌ ያህል “ብርሃናት” ማለትም ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት “ለዘመኖች ለዕለታት ለዓመታትም” የጊዜ ጠቋሚ ምልክት ሆነው እንዲያገለግሉ አምላክ እንደፈጠራቸው ይነግረናል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው የሚገኙ በርካታ ክንውኖች በጊዜ ሂደት ውስጥ ቦታ ቦታቸውን ጠብቀው የሚገኙ ናቸው። (ዘፍጥረት 1:14፤ 5:3-32፤ 7:11, 12፤ 11:10-32፤ ዘጸአት 12:40, 41) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ ማብቂያ ለሌለው ጊዜ ማለትም ለዘላለም የመኖር ተስፋ እንዲኖረን ከፈለግን ጊዜያችንን በጥበብ መጠቀም እንዳለብን ይናገራል።—ኤፌሶን 5:15, 16
የዘላለም ሕይወት—እውን ሊሆን የሚችል ነገር ነውን?
ጊዜ ምን እንደሆነ ለመረዳት መሞከር ተስፋ አስቆራጭ እንደሆነ ሁሉ የዘላለም ሕይወት ወይም ለዘላለም መኖር የሚለው ሐሳብም ለብዙ ሰዎች እጅግ ግራ የሚያጋባ ነው። ይህ የሆነበት አንዱ ምክንያት የሕይወት ተሞክሯችን ሁልጊዜም ከመወለድ፣ ከማደግ፣ ከማርጀትና ከመሞት ጋር በመቆራኘቱ ሊሆን ይችላል። ይህም በመሆኑ የጊዜን ፍሰት ከራሱ ከማርጀት ሂደት ጋር እናያይዘዋለን። ለብዙዎች ከዚህ በተለየ መንገድ ማሰቡ ራሱ የጊዜን ጽንሰ ሐሳብ አለመረዳት ይመስላቸዋል። ‘ሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ ጸጥ ለጥ ብለው ለሚገዙለት ነገር ሰዎች ለምን የተለዩ ይሆናሉ?’ ብለው ይጠይቁ ይሆናል።
በዚህ ረገድ አብዛኛውን ጊዜ ልብ ሊባል የሚገባው ሐቅ ቀድሞውንም ቢሆን የሰው ልጆች ከሌሎች ፍጡራን በብዙ ሁኔታዎች የሚለዩ መሆናቸው ነው። ለምሳሌ ያህል እንስሳት የሰዎችን የመሰለ አእምሯዊ ችሎታ የላቸውም። አእምሯዊ ችሎታ አላቸው ቢባልም በደመ ነፍስ ተመርተው ከሚሠሩት ውጪ ምንም ዓይነት የፈጠራ ችሎታ የላቸውም። የሰዎችን የመሰለ ተሰጥዎም ሆነ ፍቅርና አድናቆት የማሳየት ችሎታ የላቸውም። ሰዎች ሕይወትን ትርጉም ያለው የሚያደርጉ እነዚህን የመሳሰሉ ባህርያትና ችሎታዎች በብዛት ተሰጥተዋቸው ሳለ ሕይወታቸው ለረዥም ጊዜ እንዲቀጥል ያልተደረገው ለምንድን ነው?
በሌላ በኩል ደግሞ ማሰብ የማይችሉ ዛፎች አንዳንድ ጊዜ በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲኖሩ የማሰብ ችሎታ ያላቸው ሰዎች ግን በአማካይ ከ70 እስከ 80 ዓመት ብቻ ሊኖሩ የሚችሉ መሆናቸው ግራ የሚያጋባ አይደለም? የፈጠራ ችሎታም ሆነ ተፈጥሯዊ ተሰጥኦ የሌላቸው ኤሊዎች ከ200 ዓመታት በላይ ለመኖር ሲችሉ እነዚህ ባህርያት በብዛት ያሏቸው ሰዎች ግን ለመኖር የሚችሉት ከዚህ ጊዜ ከግማሽ ያነሰ መሆኑ የሚያስገርም አይደለም?
የሰው ልጅ የጊዜንና የዘላለማዊነትን ትርጉም ሙሉ በሙሉ ለመረዳት ባይችልም ዘላለማዊ ሕይወት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኝ እርግጠኛ ተስፋ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የዘላለም ሕይወት” የሚለው ሐረግ ወደ 40 ለሚጠጉ ጊዜያት ተጠቅሶ ይገኛል። ይሁን እንጂ የአምላክ ዓላማ ሰዎችን ለዘላለም ማኖር ከሆነ እስከ አሁን ድረስ ሰዎች ለዘላለም መኖር ያልቻሉት ለምንድን ነው? ይህ ጥያቄ በሚቀጥለው ርዕስ ላይ ይብራራል።