የእኩልነት አለመኖር ያስከተለውን ችግር መግታት
በቅርቡ ፈጣሪ ሰዎች የሚጓጉለትን እኩልነት ያመጣል። እስከዚያ ድረስ ግን እኛንም ሆነ ቤተሰባችንን የሚነካውን የእኩልነት አለመኖር ያስከተለውን ችግር ለመግታት ቢያንስ አንዳንድ እርምጃዎች መውሰድ እንችላለን። የቀድሞው የደቡብ አፍሪካ ፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ “አንዳችንን ከሌላው የሚለየን የተሰጠን ነገር ሳይሆን ያለንን ነገር የምንጠቀምበት መንገድ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ታሪክ የእርሳቸውን አባባል ትክክለኛነት ያረጋግጣል። ሲወለዱ ምናምን ያልነበራቸው ነገር ግን ያለቻቸውን በአግባቡ በመጠቀም ለስኬት የበቁና ምናልባትም የተሻለ ዕድል ከነበራቸው እኩዮቻቸው ልቀው የተገኙ ወንዶችና ሴቶች ቁጥር ጥቂት አይደለም። በአንጻሩ ደግሞ ከተወለዱበት ጊዜ አንስቶ የነበሯቸውን በርካታ አጋጣሚዎች በአግባቡ ሳይጠቀሙባቸው በመቅረት እንደሚጠበቅባቸው መኖር የተሳናቸው ግለሰቦች አሉ።
ያለህን ነገር በጥሩ ሁኔታ ተጠቀምበት!
የይሖዋ ምሥክሮች፣ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካኝነት ስለ አምላክ ዓላማዎች እውቀት እንዲያገኙ የመርዳት ልባዊ ፍላጎት አላቸው። ሆኖም ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ከያዘው እውቀት የተሟላ ጥቅም እንዲያገኙ ከማይምነት መላቀቅ እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። ከዚህ የተነሳ የይሖዋ ምሥክሮች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማንበብና መጻፍ አስተምረዋል። በአንድ የምዕራብ አፍሪካ አገር ብቻ እንኳን 23,000 ሰዎች (ከ1990ዎቹ አንስቶ) የዚህ ተጠቃሚ ሆነዋል። የይሖዋ ምሥክሮች የሚሰጡትን ጉልህ ማኅበራዊ አገልግሎት አስመልክቶ ሳን ፍራንሲስኮ ኤግዛሚነር እንዲህ ብሏል:- “አርአያ የሚሆኑ ዜጎች አድርጋችሁ ልትመለከቷቸው ትችላላችሁ። ሳያሰልሱ ቀረጥ ይከፍላሉ፣ የታመሙትን ያስታምማሉ፣ ማይምነትን ይዋጋሉ።”
በተጨማሪም ቀጣይ በሆነ የሕዝብ ተናጋሪነት ሥልጠና አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮች በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በሕዝብ ፊት ሐሳባቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ መግለጽ የሚችሉ ብቃት ያላቸው ተናጋሪዎች እንዲሆኑ አሰልጥነዋል። ከእነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ከባድ የመናገር እክሎች የነበሩባቸው ናቸው። ከደቡብ አፍሪካ እንዲህ ሲል የጻፈውን ሰው ተመልከት:- “ከባድ የመንተባተብ ችግር ስለነበረብኝ አብዛኛውን ጊዜ ሌሎች በእኔ ቦታ ሆነው እንዲናገሩ የምጠብቅ አንደበተ ዝግ ሰው ነበርኩ። . . . በቲኦክራሲያዊ የአገልግሎት ትምህርት ቤት ተመዝግቤ በጥቂት አድማጮች ፊት የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ሳቀርብ . . . በጣም ከመንተባተቤ የተነሳ በተመደበው ጊዜ ውስጥ ክፍሉን አቅርቤ መጨረስ አቃተኝ። ከስብሰባው በኋላ [ምክር የሚሰጠው ወንድም] በደግነት ተግባራዊ ምክር ሰጠኝ። ለራሴ ጮክ ብዬ በማንበብ እንድለማመድ ሐሳብ አቀረበልኝ። በየቀኑ ለተወሰነ ጊዜ ከመጽሐፍ ቅዱስና ከመጠበቂያ ግንብ መጽሔት ጮክ ብዬ በማንበብ ምክሩን ሠራሁበት።” ይህ ሰው ከፍተኛ እድገት ከማድረጉ የተነሳ አሁን በመቶዎች አልፎ ተርፎም በሺዎች ለሚቆጠሩ አድማጮች ንግግሮች ይሰጣል።
በወንድሞች መካከል እኩልነት ማግኘት
ትምህርትን፣ ሕክምናን እንዲሁም ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ደረጃን በተመለከተ በይሖዋ ምሥክሮች መካከል ያለው ሁኔታ በጣም ይለያያል። እነዚህ ልዩነቶች የሚኖሩበት ዓለም ፍጽምና የጎደላቸው ሁኔታዎች እንዳሉት የሚያንጸባርቁ ናቸው። ሆኖም ከሌሎች ሃይማኖታዊ ቡድኖች አንጻር ሲታይ የዘር፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ልዩነቶችን ቃል በቃል ከመካከላቸው አስወግደዋል።
ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሩትን ነገር አቅማቸው በሚፈቅድላቸው መጠን በተግባር ለማዋል በመጣር ይህን ሊያደርጉ ችለዋል። እንደሚከተለው ያሉትን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በሙሉ ልብ ይቀበላሉ:- “ሰው እንዲያይ እግዚአብሔር አያይምና . . . ሰው ፊትን ያያል፣ እግዚአብሔር ግን ልብን ያያል።” (1 ሳሙኤል 16:7) “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ።” (ሥራ 10:34, 35) “ለማንም ስለ ክፉ ፈንታ ክፉን አትመልሱ፤ በሰው ሁሉ ፊት መልካም የሆነውን አስቡ። ቢቻላችሁስ በእናንተ በኩል ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ኑሩ።”—ሮሜ 12:17, 18፤ በተጨማሪ 1 ጢሞቴዎስ 6:17-19፤ ያዕቆብ 2:5, 9ን ተመልከት።
አንድነት የሚያጎለብቱትን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች በጥብቅ በመከተል የይሖዋ ምሥክሮች በመካከላቸው በዘር፣ በማኅበራዊ ወይም በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች ላይ የተመሠረቱ ልዩነቶች እንዲኖሩ አይፈቅዱም። ለምሳሌ ያህል እነዚህ ሁኔታዎች በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ ማን የአገልግሎት መብት ማግኘት እንዳለበት ለመወሰን ምንም ቦታ የላቸውም። እንደ ማስተማርና የበላይ ተመልካችነት የመሳሰሉ የኃላፊነት ቦታዎች የሚሰጡት ሙሉ በሙሉ መንፈሳዊ መመዘኛዎችን መሠረት በማድረግ ነው።—1 ጢሞቴዎስ 3:1-13፤ ቲቶ 1:5-9
በአድልዎ የተሞላው ዓለም በሚያስከትለው የእኩልነት አለመኖር ይሰቃዩ የነበሩ ግለሰቦች ሌሎች እነርሱን በፈጣሪያቸው ፊት እኩል ቦታ እንዳላቸው በመቁጠር እንደ ወንድሞችና እህቶች ሲይዟቸው ምንኛ ይጽናናሉ! ማርቲና ይህ እውነት መሆኑን ትመሰክራለች። አባቷ ቤተሰቡን ጥሎ ከሄደ በኋላ በነጠላ ወላጅ በሚተዳደር ድሃ ቤተሰብ ውስጥ አደገች። አብዛኛውን ጊዜ በኅብረተሰቡ ውስጥ ተፈላጊ እንዳልሆነች ትቆጠር ነበር፣ በራስዋ ላይ የነበራት ትምክህት ዝቅተኛ ነበር እንዲሁም ከሌሎች ጋር ተግባብቶ መኖር ይከብዳት ነበር። ከዚህ የተነሳ የግድየለሽነት ዝንባሌ ተጠናወታት። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ማጥናት ከጀመረችና የይሖዋ ምሥክር ከሆነች በኋላ ሁኔታዎች ተለወጡ። እንዲህ ትላለች:- “አሁንም ቢሆን በውስጤ ያለውን አፍራሽ አስተሳሰብ መዋጋት አለብኝ፤ ሆኖም አሁን ችግሩን ለመቋቋም የተሻለ አቅም አግኝቻለሁ። ለራሴ ያለኝ አክብሮት የጨመረ ሲሆን ከበፊቱ የበለጠ በመተማመን ስሜት መናገር ችያለው። እውነት የኃላፊነት ስሜት እንዲሰማኝ አድርጓል። አሁን ይሖዋ እንደሚወድደኝና በሕይወት መኖር ትርጉም እንዳለው ተረድቻለሁ።”
የይሖዋ ምሥክሮች ከ230 በሚበልጡ አገሮች የሚኖሩ ዓለም አቀፋዊ የክርስቲያኖች ቡድን እንደመሆናቸው መጠን በዛሬው ዓለም ታይቶ የማይታወቅ እኩልነት አግኝተዋል። የትኛው ሌላ ሃይማኖታዊ ድርጅት እንዲህ ብሎ ሊናገርና ለአባባሉ ማስረጃ ሊያቀርብ ይችላል?
እርግጥ፣ የይሖዋ ምሥክሮች ከእውነታው አይሸሹም። ፍጹም ያልሆነ ሥርዓት ውጤት እንደመሆናቸው መጠን ባለፉት መቶ ዓመታት ሌሎች የእኩልነት አለመኖርን ለማስወገድ ጥረት አድርገው ሳይሳካላቸው እንደቀረ ሁሉ እነርሱም የማስወገድ አቅም እንደሌላቸው አምነው ይቀበላሉ። የሆነ ሆኖ የእኩልነት አለመኖር የሚያስከትለውን አደገኛ ችግር ለመግታት ከፍተኛ ጥረት በማድረጋቸው እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ደስተኞች ናቸው። እንዲሁም አምላክ በሰጠው ተስፋ ላይ ጠንካራ እምነት በማሳደር የእኩልነት አለመኖር ለዘላለም ተረስቶ የሚቀርበትን ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም በጉጉት ይጠባበቃሉ።
አዎን፣ በቅርቡ ታዛዥ የሆኑ ሰዎች ሁሉ ፈጣሪያቸው ከመጀመሪያ አንስቶ ለእነርሱ አስቦት ወደነበረው “በክብርና በመብት” እኩል ወደመሆን ደረጃ ይመለሳሉ። ይህ አባባል እንዴት ደስ ይላል! በዚህ ጊዜ እኩልነት እውን ይሆናል!
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የይሖዋ ምሥክሮች በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ማንበብና መጻፍ በማስተማር ማይምነትን ይዋጋሉ
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የዘር፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ መድልዎችን ለማስወገድ ይረዳል