የእኩልነት አለመኖር የአምላክ ዓላማ ነበር?
በአጭር ቃል መልሱ አልነበረም የሚል ነው። እስቲ ይህ የሆነበትን ምክንያት እንመልከት።
የአምላክ ዓላማ ሁሉም ሰዎች ሕይወትና ደስታ በማግኘት ረገድ እኩል አጋጣሚ እንዲኖራቸው ነበር። የሰዎችን አፈጣጠር በተመለከተ እንዲህ እናነባለን:- “እግዚአብሔርም አለ:- ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር፤ የባሕር ዓሦችንና የሰማይ ወፎችን፣ እንስሳትንና ምድርን ሁሉ፣ በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ይግዙ።” ምድራዊ ፍጥረቱን ሲያበቃ “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፣ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ።”—ዘፍጥረት 1:26, 31
አምላክ ዛሬ ያለውን እኩልነት የጠፋበት አሳዛኝ ሁኔታ “እጅግ መልካም” ብሎ ሊገልጸው ይችላል? ‘እግዚአብሔር ፍቅር ስለሆነ’ በጭራሽ እንደዚያ ብሎ አይገልጸውም። (1 ዮሐንስ 4:8) እርሱን በተመለከተ “በፍርድ የማያዳላ” እንደሆነ፤ እንዲሁም “ሥራውም ፍጹም ነው፤ መንገዱም ሁሉ የቀና [“ፍትህ፣” NW] ነው፤ የታመነ አምላክ፣ ክፋትም የሌለበት፣ እርሱ እውነተኛና ቅን ነው” ተብሎ ተገልጿል። (ዘዳግም 10:17፤ 32:4፤ ከኢዮብ 34:19 ጋር አወዳድር።) ሐዋርያው ጴጥሮስ ደግሞ “እግዚአብሔር ለሰው ፊት እንዳያደላ ነገር ግን በአሕዛብ ሁሉ እርሱን የሚፈራና ጽድቅን የሚያደርግ በእርሱ የተወደደ እንደ ሆነ በእውነት አስተዋልሁ” ሲል አጠቃሏል።—ሥራ 10:34, 35
አምላክ አፍቃሪ፣ የማያዳላ፣ ፍጹም፣ ቅንና ጻድቅ ስለሆነ ደስታ የማግኘት መብታቸውን በተመለከተ ሰዎችን በባሕርያቸው እንዴት አበላልጦ ይፈጥራቸዋል? በሰዎች መካከል መድልዎ እንዲኖር መፍቀድና እኩልነት በሌለው ሥርዓት ውስጥ እንዲኖሩ ማድረግ በቀጥታ ከባሕርይው ጋር የሚቃረን ይሆናል። ሁሉም “ነፃ ሆነው እንዲወለዱና እኩል ክብርና መብት እንዲኖራቸው” ዓላማው ነበር። ሆኖም ዛሬ ነገሮች በዚያ መልክ እንደማይገኙ ግልጽ ነው። ለምን እንደዚህ ሆነ?
የእኩልነት አለመኖር መንስዔ
አምላክ ሰዎችን እኩል አድርጎ ፈጥሯቸዋል ሲባል ዓላማው ሁሉም ሰዎች በማንኛውም ረገድ እኩል እንዲሆኑ ነበር ማለት አይደለም። የተለያየ ተሰጥዎ፣ ፍላጎትና ባሕርይ ሊኖራቸው ይችላል። ባላቸው ቦታ ወይም ሥልጣን ሊለያዩም ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል ወንድና ሴት በሁሉም ነገር እኩል አይደሉም። አምላክ ሴቲቱን የፈጠራት የወንዱ “ማሟያ” እንድትሆን አድርጎ ነው። (ዘፍጥረት 2:18 NW) ወላጆችና ልጆች በሥልጣን እንደሚበላለጡ ግልጽ ነው። እነዚህ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳ ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ባጠቃላይ ደስታ ለማግኘት የሚያስፈልጉትን መሠረታዊ ነገሮች ለማሟላት የሚያስችሏቸውን ተመሳሳይ አጋጣሚዎች ከአምላክ እንደተሰጣቸው መብት በመቁጠር ሊጠቀሙባቸው ይችሉ ነበር። በአምላክ ፊት ሁሉም እኩል ክብርና ደረጃ ማግኘት ይችላሉ።
በተመሳሳይ ከሰዎች በፊት የተፈጠሩት የአምላክ መንፈሳውያን ልጆች የተለያየ ዓይነት የሥራ ምድብና ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘፍጥረት 3:24፤ 16:7-11፤ ኢሳይያስ 6:6፤ ይሁዳ 9) የሆነ ሆኖ ከተሰጣቸው ገደብ ሳያልፉ ሁሉም ለሕይወትና ለደስታ የተደረጉትን መለኮታዊ ዝግጅቶች በእኩል ደረጃ መጠቀም ይችሉ ነበር። በዚህ መንገድ ከአድልዎ ነፃ የሆነውን የአምላክን ባሕርይ አስደናቂ በሆነ መንገድ አንጸባርቀዋል።
ዳሩ ምን ያደርጋል አንድ መንፈሳዊ ፍጡር ከአድልዎ ነፃ በሆነው የአምላክ ዝግጅት ሳይደሰት ቀረ። ከፍ ያለና ከበፊቱ የላቀ ደረጃ ለመያዝ በመጓጓት አምላክ ከሰጠው በላይ ለማግኘት ፈለገ። ይህን የተሳሳተ ምኞት በውስጡ በማሳደግ፣ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን የመጨረሻውን ደረጃ የመያዝ መብት ያለውን ይሖዋን መቀናቀን ጀመረ። ይህ ዓመፀኛ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ከጊዜ በኋላ ሰዎች አምላክ ከሰጣቸው በላይ ማግኘት አለብን እንዲሉ አነሳሳቸው። (ዘፍጥረት 3:1-6፤ ከኢሳይያስ 14:12-14 ጋር አወዳድር።) በመሆኑም ይሖዋ ሰዎች ሕይወትና ደስታ እንዲያገኙ ያደረገው ዝግጅት ከጥቅም ውጪ የሆነ መሰለ። በራእይ 20:2 ላይ “ዲያብሎስና ሰይጣን” ተብሎ የተገለጸው ይህ ዓመፀኛ መንፈሳዊ ፍጡር ለሰው ልጅ እኩልነት ማጣት መንስዔ ሆኗል።
ይህ ሁኔታ የሚለወጥበት ጊዜ ይመጣ ይሆን?
መልሱ በአንድ ቃል አዎን የሚል ነው!
ሆኖም አስፈላጊ የሆኑትን ለውጦች ማምጣት የሚችለው ማን ነው? ሰብዓዊ መሪዎች ይህን ለውጥ ለማምጣት ለብዙ መቶ ዓመታት ሲታገሉ መኖራቸው እሙን ነው። አንዳንዶቹም ልባዊ ጥረት አድርገዋል። ያገኙት ስኬት ውስን በመሆኑ ብዙዎች የሰው ልጅ የገጠመው የእኩልነት አለመኖር የሚወገድበት ጊዜ ይመጣል ብሎ መጠበቅ የማይመስል ነገር ነው የሚል መደምደሚያ ላይ እንዲደርሱ አድርጓቸዋል። ይሁን እንጂ አምላክ ያለው አመለካከት በኢሳይያስ 55:10, 11 ላይ እንደሚከተለው ተመዝግቦ ይገኛል:- “ዝናብና በረዶ ከሰማይ እንደሚወርድ፣ ምድርን እንደሚያረካት፣ ታበቅልና ታፈራም ዘንድ እንደሚያደርጋት፣ ዘርንም ለሚዘራ እንጀራንም ለሚበላ እንደሚሰጥ እንጂ ወደ ሰማይ እንደማይመለስ፣ ከአፌ የሚወጣ ቃሌ እንዲሁ ይሆናል፤ የምሻውን ያደርጋል የላክሁትንም ይፈጽማል እንጂ ወደ እኔ በከንቱ አይመለስም።”
ይሖዋ አምላክ ሰዎች ሁሉ ሕይወትና ደስታ ለማግኘት እኩል አጋጣሚ እንዲኖራቸው የነበረውን የመጀመሪያ ዓላማ እንደሚፈጽም መናገሩን ማወቅ ምንኛ ያጽናናል! የእውነት አምላክ እንደመሆኑ መጠን ቃል የገባውን ነገር ለመፈጸም ራሱን ግዴታ ውስጥ አስገብቷል። የሚያስደስተው ይህን ለማድረግ ፍላጎትም ሆነ ኃይል ያለው መሆኑ ነው። ይህን የሚያሳካው በምን መንገድ ነው?
ኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮቹ ሁሉ እንዲጸልዩለት ያስተማረው መንግሥት መልሱን ይዟል:- “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ . . . መንግሥትህ ትምጣ፤ ፈቃድህ በሰማይ እንደ ሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን።” (ማቴዎስ 6:9, 10) አዎን፣ ይሖዋ ‘እነዚያንም መንግሥታት ሁሉ [አሁን ያሉትን] ለመፍጨትና ለማጥፋት ለዘላለም በምትቆመው’ የአምላክ መንግሥት ይጠቀማል።—ዳንኤል 2:44
በሰማያዊው መንግሥት አገዛዝ ስር አዲስ ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ይቋቋማል። በዚህ ረገድ ሐዋርያው ዮሐንስ የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ በሆነው በዮሐንስ ራእይ ላይ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ ፊተኛው ሰማይና ፊተኛይቱ ምድር አልፈዋልና።” (ራእይ 21:1) የእኩልነት መዛባት አስከፊ ገጽታ የሆኑት ድህነት፣ በሽታ፣ ድንቁርና፣ መድልዎና ሰዎች የገጠሟቸው ሌሎች ችግሮች ባጠቃላይ ጊዜ ያለፈባቸው ነገሮች ይሆናሉ።a
ከአንድ መቶ ዓመት በላይ የይሖዋ ምሥክሮች ሰዎች ለዚህች መንግሥት ትኩረት እንዲሰጡ ሲያደርጉ ቆይተዋል። (ማቴዎስ 24:14) በታተሙ ጽሑፎችና በግል በሚሰጡት ድጋፍ አማካኝነት የይሖዋ ምሥክሮች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በሰፈረው መሠረት ሰዎች አምላክ ስላለው ዓላማ እውቀት እንዲያገኙ በመርዳት ረገድ የአቅማቸውን ያህል ጥረት አድርገዋል። ዓለም አቀፋዊው የማስተማር ሥራቸው ሰዎች ወደፊት በእኩልነትና በደስታ እንደሚኖሩ ተስፋ ከመስጠቱም በላይ የእኩልነት መዛባትን ወረርሽኝ በመግታት ረገድ አሁንም ቢሆን ጥቅም አስገኝቷል። እስቲ ይህ የሆነበትን መንገድ እንመልከት።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በቅርቡ የአምላክ መንግሥት ለሰዎች ሁሉ እኩልነት ስለሚያመጣበት መንገድ የተሟላ ማብራሪያ ለማግኘት እባክህ ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመው ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ እውቀት ከተባለው መጽሐፍ ምዕራፍ 10 እና 11ን ተመልከት።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ የተቀነጨበ ሐሳብ]
አምላክ ሁሉም ሰዎች ሕይወትና ደስታ በማግኘት ረገድ እኩል አጋጣሚ እንዲኖራቸው ዓላማው ነበር