በጊዜያችን የተንሰራፋው የእኩልነት አለመኖር መቅሰፍት
“ሁሉም ሰው እኩል ሆኖ ተፈጥሯል፤ ፈጣሪያቸው አንዳንድ የማይገሰሱ መብቶችን፣ ከእነዚህም ውስጥ በሕይወት የመኖር፣ የነፃነትና ደስታን የመፈለግ መብት እንደሰጣቸው የሚያሳዩት እነዚህ ተጨባጭ ሐቆች ማስረጃ እንደማያስፈልጋቸው እናምናለን።”—በ1776 በዩናይትድ ስቴትስ የጸደቀው የነፃነት ድንጋጌ።
“ሁሉም ሰዎች ነፃ ሆነውና እኩል መብቶች ይዘው ይወለዳሉ።”—በ1789 በፈረንሳይ ብሔራዊ ጉባኤ የጸደቀው የሰዎችና የዜግነት መብቶች ድንጋጌ።
“ሁሉም ሰብዓዊ ፍጥረታት ነፃ ሆነው የተወለዱ ሲሆን በክብርና በመብት እኩል ናቸው።”—በ1948 በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ የጸደቀው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌ።
ይህ አሌ የማይባል ሐቅ ነው። የሰው ልጆች እኩልነት እንዲሰፍን ያላቸው ፍላጎት ዓለም አቀፋዊ ይዘት አለው። የሚያሳዝነው ግን ሰዎች እኩል ናቸው የሚለው ሐሳብ ይህን ያህል ተደጋግሞ መጠቀሱ ራሱ እስካሁን ድረስ የሰው ልጅ እኩልነትን መጨበጥ እንዳልቻለ ያሳያል።
በዚህ በ20ኛው ምዕተ ዓመት ማብቂያ ላይ ሁኔታዎች የተሻለ መልክ እየያዙ መጥተዋል ብሎ ሊከራከር የሚደፍር ሰው ይኖራልን? የዩናይትድ ስቴትስም ሆነ የፈረንሳይ ወይም ከ185ቱ የተባበሩት መንግሥታት አባል አገሮች መካከል አንዳቸውም ቢሆኑ ዜጎቻቸው ባጠቃላይ በውልድ ያገኙታል ተብሎ የሚታመነው እኩል መብት በእርግጥ አላቸው?
ምንም እንኳ ሁሉም ሰዎች እኩል ናቸው የሚለው ሐሳብ ‘ማስረጃ የማያስፈልገው’ ጉዳይ ቢሆንም ሰዎች ሁሉ ‘በሕይወት ለመኖር፣ ነፃነት ለማግኘትና ደስታን ለመፈለግ’ ያላቸው መብት ፈጽሞ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ አይደለም። ለምሳሌ ያህል በአፍሪካ የሚኖር ሕፃን አንድ ዶክተር የሚደርሰው ከሌሎች 2,569 ሰዎች ጋር በመጋራት ሲሆን በአንጻሩ ደግሞ በአውሮፓ የሚኖር ሕፃን ከ289 ሰዎች ጋር ብቻ ይደርሰዋል። ታዲያ እነዚህ ሕፃናት በሕይወት ለመኖር ባላቸው መብት ረገድ እንዴት እኩል ናቸው ብለን መናገር እንችላለን? ወይም በሕንድ ከሚኖሩ ወንዶች ልጆች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑትና ከልጃገረዶቹ መካከል ደግሞ ሁለት ሦስተኛ የሚሆኑት የመማር ዕድል ሳያገኙ ሲያድጉ በአንጻሩ ደግሞ እንደ ጃፓን፣ ጀርመንና ታላቋ ብሪታንያ በመሳሰሉ አገሮች ቃል በቃል እያንዳንዱ ልጅ የመማር ዕድል ዋስትና ሲኖረው በነፃነትና ደስታን በመፈለግ ረገድ እንዴት እኩል መብት አለ ሊባል ይችላል?
አማካኝ ዓመታዊ ገቢያቸው 1,380 የአሜሪካ ዶላር የሆነው በማዕከላዊ አሜሪካ አገሮች የሚኖሩ ሕዝቦች፣ ዓመታዊ ገቢያቸው 24,990 የአሜሪካ ዶላር እንደሆነው የፈረንሳይ ነዋሪዎች በኑሮ ረገድ ተመሳሳይ “ክብርና መብት” አላቸውን? በአማካኝ 56 ዓመት የመኖር ዕድል ይዛ የምትወለድ አንዲት አፍሪካዊት ሕፃን በሰሜን አሜሪካ ከተወለደችው 79 ዓመት የመኖር ዕድል ካላት ሕፃን ጋር ስትነጻጸር ምን ዓይነት እኩልነት አላት?
የእኩልነት አለመኖር አስቀያሚ የሆኑ ብዙ ገጽታዎች አሉት። የኑሮ ደረጃ፣ ሕክምናና የትምህርት ዕድል የእኩልነት አለመኖር ከሚንጸባረቅባቸው ገጽታዎች መካከል ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው። አንዳንድ ጊዜ የፖለቲካ፣ የዘር ወይም የሃይማኖት ልዩነቶች የሰውን ክብርና ነፃነት በመንፈግ ረገድ ጉልህ ሚና ይጫወታሉ። እኩልነትን በተመለከተ ብዙ ቢለፈፍም፣ የምንኖረው እኩልነት በጠፋበት ዓለም ውስጥ ነው። ዛሬ እንደ መቅሰፍት የሆነው የእኩልነት መጥፋት ያልዳሰሰው የሰው ልጅ ኅብረተሰብ የለም። መቅሰፍት የሚለው ቃል ደግሞ “በእጅጉ የተስፋፋና ከባድ መከራ የሚያስከትል ችግር” ማለት ነው። በድህነት፣ በበሽታ፣ በማይምነት፣ በሥራ አጥነትና በመድልዎ መልክ የሚያስከትለው ስቃይ በጥልቅ ይጎዳል።
“ሁሉም ሰው እኩል ሆኖ ተፈጥሯል።” ይህ አባባል እንዴት ደስ ይላል! የሚያሳዝነው ግን እውነታው ፍጹም የዚህ ተቃራኒ ነው!
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
UN PHOTO 152113/SHELLEY ROTNER