ቁጣ እንዳያሰናክልህ ተጠንቀቅ
“ተረጋጋ!” “ለመናገር አትቸኩል!” “አንደበትህን ግታ!” እነዚህን አባባሎች ሰምተሃቸዋል? ምናልባት ያደረብህን የቁጣ ስሜት ለማብረድ እነዚህን ቃላት በልብህ ደግመሃቸው ታውቅ ይሆናል። አንዳንድ ሰዎች በቁጣ ገንፍለው ላለመናገር ሲሉ ለመናፈስ ወጣ ይላሉ። እነዚህ ቁጣን ለመቆጣጠርና ከሌሎች ጋር ያለንን ዝምድና ላለማበላሸት የሚረዱ ቀላል ዘዴዎች ናቸው።
ሆኖም ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ብዙዎች ቁጣን መቆጣጠር ወይም ማመቅ ተገቢ መሆን አለመሆኑን በተመለከተ ባለሙያዎች በሚሰጡት ምክር ግራ ተጋብተዋል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ የሥነ ልቦና ጠበብት “የሚበርድልህ ከሆነ” ተናገርና ይውጣልህ የሚል ፍልስፍና አስፋፍተዋል። ሌሎች ደግሞ በተደጋጋሚ በቁጣ ስሜት መገንፈል “እንደ ማጨስ፣ ከፍተኛ የደም ግፊትና ኮሌስትሮል ከመሳሰሉ ለአደጋ የሚያጋልጡ ነገሮች የከፋ፣ በአጭሩ መቀጨትን የሚጠቁም አደገኛ ምልክት” እንደሆነ ያስጠነቅቃሉ። የአምላክ ቃል እንዲህ ሲል በግልጽ ይናገራል:- “ከቍጣ ራቅ መዓትንም ተው፤ እንዳትበድል አትቅና።” (መዝሙር 37:8) መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ዓይነት ቀጥተኛ ምክር የሚሰጠው ለምንድን ነው?
ስሜታችንን ካልተቆጣጠርነው ድርጊታችንን መቆጣጠር እንዲሳነን ስለሚያደርግ ነው። ገና የሰው ልጅ ታሪክ በጀመረበት ጊዜ ይህ ነገር እውነት መሆኑ በግልጽ ታይቷል። “ቃየንም እጅግ ተናደደ ፊቱም ጠቆረ” የሚል እናነባለን። ይህ ወዴት አመራው? ያደረበት ቁጣ አንቆ ስለያዘውና ስለተቆጣጠረው ይሖዋ መልካም ነገር እንዲያደርግ የሰጠውን ምክር እንዳይቀበል ልቡን አደነደነበት። ቃየን ያደረበት ከፍተኛ ቁጣ የከፋ ኃጢአት እንዲፈጽም ማለትም ወንድሙን እንዲገድል አነሳሳው።—ዘፍጥረት 4:3-8
በተመሳሳይም የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ ሳኦል፣ ዳዊት ከእርሱ የላቀ ምስጋና በማግኘቱ የቁጣ ስሜት አድሮበታል። “ሴቶችም:- ሳኦል ሺህ፣ ዳዊትም እልፍ ገደለ እያሉ እየተቀባበሉ ይዘፍኑ ነበር። ሳኦልም እጅግ ተቆጣ፣ ይህም ነገር አስከፋው።” ሳኦል ያደረበት የቁጣ ስሜት አስተሳሰቡን ተቆጣጥሮት ስለነበር በዳዊት ላይ ተደጋጋሚ የግድያ ሙከራ እንዲያደርግ ገፋፋው። ምንም እንኳ ዳዊት በመካከላቸው ያለው ዝምድና እንዲሻሻል ቀዳሚ ሆኖ ቢገኝም ሳኦል ሰላምና ዕርቅ እንዲሰፍን ፈቃደኛ ሳይሆን ቀረ። በመጨረሻ ሙሉ በሙሉ የይሖዋን ሞገስ አጣ።—1 ሳሙኤል 18:6-11፤ 19:9, 10፤ 24:1-21፤ ምሳሌ 6:34, 35
አንድ ሰው ቁጣውን መቆጣጠር ሲያቅተው እርሱ ወይም እርሷ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ሰዎች ሁሉ የሚጎዳ ነገር መናገራቸው ወይም ማድረጋቸው የማይቀር ነው። (ምሳሌ 29:22) ቃየንና ሳኦል የተናደዱት ሁለቱም በተለያየ ምክንያት ቅናትና ምቀኝነት ስላደረባቸው ነው። ይሁን እንጂ በቁጣ ተነሳስቶ እርምጃ መውሰድ በተለያዩ ምክንያቶች ሊከሰት ይችላል። አግባብ ያልሆነ ትችት፣ ስድብ፣ አለመግባባት ወይም በደል ቁጣን ሊቀሰቅሱ የሚችሉ ነገሮች ናቸው።
የቃየንና የሳኦል ሁኔታ ሁለቱም በጋራ የነበራቸውን አንድ ጉልህ ድክመት ያሳያል። ቃየን መሥዋዕቱን ያቀረበው በእምነት ተነሳስቶ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። (ዕብራውያን 11:4) ሳኦል ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ ሳይታዘዝ መቅረቱና ከዚያም ጥፋቱን አምኖ ላለመቀበል ያደረገው ሙከራ የይሖዋን ሞገስና መንፈስ እንዲያጣ አድርጎታል። በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ሁለቱም ከይሖዋ ጋር የነበራቸውን ዝምድና አበላሽተዋል።
እነርሱ የነበራቸውን ባሕርይ ዳዊት ከነበረው ባሕርይ ጋር አነጻጽር። ዳዊት፣ ሳኦል ባደረሰበት በደል የተነሳ የሚናደድበት ምክንያት ቢኖረውም መንፈሱን ተቆጣጥሯል። ለምን? “እግዚአብሔር በቀባው በጌታዬ ላይ እንዲህ ያለውን ነገር አደርግ ዘንድ . . . እግዚአብሔር ከእኔ ያርቀው” ሲል ተናግሯል። ዳዊት ከይሖዋ ጋር የነበረውን ዝምድና ከፍ አድርጎ ይመለከት ስለነበር በሳኦል ላይ መጥፎ ነገር ከማድረግ ተቆጥቧል። ጉዳዩን በትሕትና በይሖዋ እጅ ትቷል።—1 ሳሙኤል 24:6, 15
በእርግጥም ከቁጥጥር ውጭ የሆነ ቁጣ የከፋ መዘዝ ያስከትላል። ሐዋርያው ጳውሎስ “ተቈጡ ኃጢአትንም አታድርጉ” ሲል አስጠንቅቋል። (ኤፌሶን 4:26) የጽድቅ ቁጣ የራሱ ቦታ ቢኖረውም እንኳ ቁጣ የመሰናከያ ዓለት የመሆኑ አደጋ ምንጊዜም አለ። ስለዚህ የቁጣ ስሜታችንን የመቆጣጠር ፈተና የተደቀነብን መሆኑ ምንም አያስደንቅም። ሆኖም ስሜታችንን መቆጣጠር የምንችለው እንዴት ነው?
የመጀመሪያው እርምጃ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መመሥረት ነው። ይሖዋ ልብህንና አእምሮህን እንድትከፍትለት ያበረታታሃል። የሚያስጨንቁህንና የሚያሳስቡህን ነገሮች ንገረው፤ እንዲሁም የቁጣ ስሜትን ለመቆጣጠር የሚያስችል የረጋ ልብ እንዲሰጥህ ጠይቀው። (ምሳሌ 14:30) ‘የጌታ ዓይኖች ወደ ጻድቃን እንደሆኑና ጆሮዎቹም ለጸሎታቸው እንደተከፈቱ’ እርግጠኛ ሁን።—1 ጴጥሮስ 3:12
ጸሎት አስተሳሰብህን ሊቀርጽና ሊመራህ ይችላል። በምን መንገድ? ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ የጎላ ተጽእኖ ሊያሳድር ይችላል። ይሖዋ ምን ዓይነት አያያዝ እንዳደረገልህ አትዘንጋ። ቅዱሳን ጽሑፎች እንደሚናገሩት ይሖዋ “እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም።” (መዝሙር 103:10) ‘በሰይጣን እንዳትታለል’ የይቅር ባይነት መንፈስ መያዝህ ወሳኝ ነው። (2 ቆሮንቶስ 2:10, 11) ከዚህ በተጨማሪ ጸሎት መንፈስ ቅዱስ ለሚሰጠው አመራር ልብህን እንድትከፍት ይረዳሃል። ይህ ደግሞ በሕይወትህ የምትከተላቸውን ሥር የሰደዱ ልማዶች ሊያስወግድልህ ይችላል። ይሖዋ፣ አንቆ ከሚይዘው የቁጣ ኃይል መላቀቅ የሚያስችልህን ‘አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ ሰላም’ በደስታ ይሰጥሃል።—ፊልጵስዩስ 4:7
ሆኖም ‘የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ ማስተዋል’ እንዲቻለን ከጸሎት በተጨማሪ ቋሚ የሆነ የቅዱሳን ጽሑፎች ጥናት ማድረግ አለብን። (ኤፌሶን 5:17፤ ያዕቆብ 3:17) ቁጣህን መቆጣጠር የሚያስቸግርህ ከሆነ በዚህ ረገድ የይሖዋን አመለካከት ለማወቅ ብርቱ ጥረት አድርግ። በተለይ ቁጣን ስለ መቆጣጠር የሚናገሩትን ጥቅሶች መርምር።
ሐዋርያው ጳውሎስ የሚከተለውን ጠቃሚ ምክር ይሰጣል:- “ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተ ሰዎች መልካም እናድርግ።” (ገላትያ 6:10) አስተሳሰብህና ድርጊትህ ለሌሎች መልካም በማድረግ ላይ እንዲያተኩር አድርግ። እንዲህ ዓይነት ጤናማና አዎንታዊ ድርጊት የሌሎችን ስሜት እንድንረዳና እንድናምናቸው ከማድረጉም በላይ በቀላሉ ወደ ቁጣ ሊያመሩ የሚችሉ አለመግባባቶችን ሊያበርድ ይችላል።
መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል:- “አካሄዴን እንደ ቃልህ አቅና፤ ኃጢአትም ሁሉ አይግዛኝ። ሕግህን ለሚወድዱ ብዙ ሰላም ነው፣ ዕንቅፋትም የለባቸውም።” (መዝሙር 119:133, 165) ይህ ባንተም ላይ ሊፈጸም ይችላል።
[በገጽ 9 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ቁጣን ለመቆጣጠር የሚረዱ እርምጃዎች
□ ወደ ይሖዋ ጸልይ።—መዝሙር 145:18
□ በየዕለቱ ቅዱሳን ጽሑፎችን መርምር። —መዝሙር 119:133,165
□ ጠቃሚ በሆኑ እንቅስቃሴዎች ተሳተፍ። —ገላትያ 6:9, 10