እንድንታመም የሚያደርገን ዲያብሎስ ነውን?
አምላክ ፍጹም ጤንነት አግኝተን ለዘላለም እንድንኖር ስለፈጠረን በሽታ ጨርሶ መኖር አልነበረበትም። የመጀመሪያዎቹን ወላጆቻችንን ማለትም አዳምና ሔዋንን ወደ ኃጢአት በመምራት የሰው ዘር ቤተሰብ በበሽታ፣ ሥቃይና ሞት እንዲጠቃ ያደረገው ሰይጣን የተባለው መንፈሳዊ ፍጡር ነው።—ዘፍጥረት 3:1-5, 17-19፤ ሮሜ 5:12
እንደዚህ ሲባል ግን ሁሉም በሽታዎች የሚመጡት በመንፈሳዊው ዓለም ባሉ ኃይሎች ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ነው ማለት ነውን? ከዚህ በፊት ባለው ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ዛሬ ብዙ ሰዎች እንደዚህ ብለው ያስባሉ። ከእነዚህ መካከል የትንሿ ኦማጂ አያት አንዷ ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በሞቃታማ የሐሩር ክልል የሚኖሩ ትንንሽ ልጆችን የሚገድለው ኦማጂን የያዛት የተቅማጥ በሽታ በእርግጥ በማይታዩ መናፍስት አማካኝነት የሚመጣ ነው?
በሽታን በማምጣት ረገድ ሰይጣን የተጫወተው ሚና
መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ ግልጽ መልስ ይሰጣል። በመጀመሪያ ደረጃ የቀድሞ አባቶች መናፍስት በሕይወት ያሉ ሰዎችን ሊጎዱ እንደማይችሉ ያሳያል። ሰዎች ሲሞቱ ‘አንዳች አያውቁም።’ ከሞት በኋላ በሕይወት የሚቀጥል መንፈስ የላቸውም። ‘ሥራና አሳብ እውቀትና ጥበብ በማይገኙበት’ መቃብር አንቀላፍተዋል። (መክብብ 9:5, 10) ሙታን በምንም ዓይነት ሕያዋን እንዲታመሙ ሊያደርጉ አይችሉም!
ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ክፉ መናፍስት እንዳሉ ይገልጻል። በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ የመጀመሪያው ዓመፀኛ አሁን ሰይጣን በመባል የሚታወቀው መንፈሳዊ ፍጡር ነበር። ሌሎችም ተባበሩትና አጋንንት ተብለው መጠራት ጀመሩ። ሰይጣንና አጋንንት በሽታ ሊያመጡ ይችላሉን? አምጥተው ያውቃሉ። አንዳንዶቹ የኢየሱስ ተአምራዊ ፈውሶች አጋንንት ማውጣትን የሚጨምሩ ነበሩ። (ሉቃስ 9:37-43፤ 13:10-16) ይሁን እንጂ ኢየሱስ የፈወሳቸው አብዛኞቹ ሕመሞች በአጋንንት አማካኝነት የመጡ አልነበሩም። (ማቴዎስ 12:15፤ 14:14፤ 19:2) ዛሬም ባጠቃላይ ሲታይ የአብዛኛው በሽታ መንስኤ ተፈጥሯዊ ነገር እንጂ ከሰው በላይ የሆነ ኃይል አይደለም።
ስለ ድግምት ምን ማለት ይቻላል? ምሳሌ 18:10 እንዲህ በማለት ማረጋገጫ ይሰጠናል:- “የእግዚአብሔር [የይሖዋ NW] ስም የጸና ግንብ ነው፤ ጻድቅ ወደ እርሱ ሮጦ ከፍ ከፍ ይላል።” ያዕቆብ 4:7 ደግሞ “ዲያብሎስን ግን ተቃወሙ ከእናንተም ይሸሻል” ይላል። አዎን፣ አምላክ የታመኑ አገልጋዮቹን ከድግምትና ከሌላ ከማንኛውም ከሰው በላይ የሆነ ኃይል ሊጠብቃቸው ይችላል። ኢየሱስ የተናገራቸው “እውነትም አርነት ያወጣችኋል” የሚሉት ቃላት ይህንንም የሚያመለክቱ ናቸው።—ዮሐንስ 8:32
‘ስለ ኢዮብ ሁኔታስ ምን ማለት ይቻላል? እንዲታመም ያደረጉት ክፉ መናፍስት አልነበሩምን?’ ብለው የሚጠይቁ ሰዎች ይኖራሉ። አዎን፣ መጽሐፍ ቅዱስም ኢዮብ እንዲታመም ያደረገው ሰይጣን መሆኑን ይናገራል። ይሁን እንጂ የኢዮብ ጉዳይ ለየት ያለ ነበር። ኢዮብ ቀጥተኛ የሆነ አጋንንታዊ ጥቃት እንዳይደርስበት ለረጅም ጊዜ መለኮታዊ ጥበቃ አልተለየውም ነበር። ከዚያም ሰይጣን ይሖዋ እጁን ዘርግቶ ኢዮብን እንዲመታው በመጠየቅ ይሖዋን ተገዳደረ። ይሖዋም ከፍተኛ ግምት የሚሰጣቸው አከራካሪ ጉዳዮች ተነስተው ስለነበር ለዚህ ጊዜ ብቻ ለአምላኪው የሚያደርገውን ጥበቃ በከፊል አንስቷል።
ይሁን እንጂ አምላክ ገደብ አበጅቶ ነበር። ሰይጣን ኢዮብን እንዲጎዳው ቢፈቀድለትም ኢዮብን ለተወሰነ ጊዜ በሽታ ላይ ሊጥለው እንጂ ሊገድለው አይችልም ነበር። (ኢዮብ 2:5, 6) ከጊዜ በኋላ የኢዮብ መከራ አበቃና ይሖዋ ስላሳየው የጸና አቋም አብዝቶ ባረከው። (ኢዮብ 42:10-17) ኢዮብ ባሳየው የጸና አቋም የተረጋገጡት መሠረታዊ ሥርዓቶች ከረጅም ጊዜ ጀምሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተመዝግበው ስለሚገኙ ለሁሉም ሰው ግልጽ ናቸው። ስለዚህ እንደዚህ ያለው ፈተና ዳግመኛ አያስፈልግም።
ሰይጣን የሚጠቀምበት ዘዴ ምንድን ነው?
በሁሉም አጋጣሚ ማለት ይቻላል ሰይጣንንና የሰውን ልጅ ሕመም የሚያዛምዳቸው ነገር እርሱ የመጀመሪያዎቹን ባልና ሚስት መፈተኑና እነርሱም በኃጢአት ሥር መውደቃቸው ነው። እያንዳንዱን የጤና ቀውስ በቀጥታ የሚያመጡት ሰይጣንና አጋንንቱ አይደሉም። ይሁን እንጂ ሰይጣን እምነታችንን በማላላት በጤንነታችን ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ ጥበብ የጎደላቸው ውሳኔዎችን እንድናደርግ ተጽእኖ ከማሳደር ወደ ኋላ አይልም። አዳምና ሔዋንን አልደገመባቸውም፣ አልገደላቸውም ወይም በበሽታ እንዲያዙ አላደረገም። ሔዋን አምላክን እንዳትታዘዝ አሳመናት፤ አዳምም የእርሷን ያለመታዘዝ መንገድ ተከተለ። በሽታና ሞት የዚህ ውጤት ከሆኑት ነገሮች መካከል ናቸው።—ሮሜ 5:19
በአንድ ወቅት የእስራኤል ብሔር በሞዓብ ድንበር ሰፍሮ ነበር። የሞዓብ ንጉሥ ለእነርሱ ስጋት ይፈጥር የነበረውን ይህን ሕዝብ እንዲረግምለት ለከሃዲው ነቢይ ለበለዓም ገንዘብ ሰጠው። በለዓም የእስራኤልን ብሔር ለመርገም ቢሞክርም በይሖዋ ጥበቃ ሥር ስለነበሩ አልተሳካለትም። በዚህን ጊዜ ሞዓባውያን የእስራኤል ሕዝብ የጣዖት አምልኮና የጾታ ብልግና እንዲፈጽም ማባበሉን ተያያዙት። ይህ ሙከራ ተሳካና እስራኤላውያን የይሖዋን ጥበቃ አጡ።—ዘኁልቁ 22:5, 6, 12, 35፤ 24:10፤ 25:1-9፤ ራእይ 2:14
ከዚህ ጥንታዊ ታሪክ አንድ ጠቃሚ ትምህርት ልናገኝ እንችላለን። መለኮታዊ እርዳታ ታማኝ አምላኪዎችን ከክፉ መናፍስት ቀጥተኛ ጥቃት ይጠብቃቸዋል። ይሁን እንጂ ሰይጣን ግለሰቦች እምነታቸውን እንዲያላሉ ለማድረግ ሊሞክር ይችላል። የሥነ ምግባር ብልግና እንዲፈጽሙ ለማባበል ይሞክር ይሆናል። ወይም ደግሞ የአምላክን ጥበቃ ሊያሳጣቸው የሚችል ድርጊት እንዲፈጽሙ ልክ እንደሚያገሳ አንበሳ ሊያስፈራራቸው ይችላል። (1 ጴጥሮስ 5:8) ሐዋርያው ጳውሎስ ሰይጣንን ‘በሞት ላይ ሥልጣን ያለው’ በማለት የጠራው ለዚህ ነው።—ዕብራውያን 2:14
የኦማጂ አያት ከበሽታ ይጠብቃሉ የሚባሉትን ክታቦችና የአስማት ኃይል እንዳላቸው የሚታመንባቸውን ነገሮች ሐዋ እንድትጠቀም ለማሳመን ሞክረዋል። ሐዋ እሺ ብላ ቢሆን ኖሮ ውጤቱ ምን ይሆን ነበር? በይሖዋ ላይ ሙሉ ትምክህት እንደሌላት ማሳየቷ ስለሚሆን ከዚያ በኋላ በእርሱ ጥበቃ ልትተማመን አትችልም ነበር።—ዘጸአት 20:5፤ ማቴዎስ 4:10፤ 1 ቆሮንቶስ 10:21
ሰይጣን ኢዮብንም ለማሳመን ሞክሯል። ቤተሰቡን፣ ሀብቱንና ጤንነቱን ማሳጣቱ ብቻ አልበቃውም። ሚስቱ ጭምር “እግዚአብሔርን ስደብና ሙት” በማለት መጥፎ ምክር ሰጥታው ነበር። (ኢዮብ 2:9) ከዚያም ሦስት “ጓደኖቹ” መጥተው ይህ በሽታ የያዘው በገዛ ሥራው እንደሆነ ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። (ኢዮብ 19:1-3) በዚህ መንገድ ሰይጣን ኢዮብ የነበረበትን የተዳከመ ሁኔታ በመጠቀም ተስፋ ሊያስቆርጠውና በይሖዋ ጽድቅ ላይ ያለውን ትምክህት ሊያናጋበት ሞክሯል። ሆኖም ኢዮብ ይሖዋን ብቸኛ ተስፋው አድርጎ በመመልከት በእርሱ ላይ ከመደገፍ ወደኋላ አላለም።—ከመዝሙር 55:22 ጋር አወዳድር።
እኛም በምንታመምበት ጊዜ እንተክዝ ይሆናል። እንደዚህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር ሰይጣን አጋጣሚውን ተጠቅሞ እምነታችንን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ እርምጃ እንድንወስድ ለማድረግ ፈጣን ነው። በመሆኑም በሽታ ሲይዘን ለሥቃይ የዳረገን መሠረታዊ መንስኤ ከሰው በላይ የሆነ ተጽዕኖ ሳይሆን የወረስነው አለፍጽምና እንደሚሆን ማስታወሱ ጠቃሚ ነው። ታማኙ ይስሐቅ ከመሞቱ ከበርካታ ዓመታት ቀደም ብሎ ዓይነ ስውር ሆኖ እንደነበር አትዘንጋ። (ዘፍጥረት 27:1) ምክንያቱ ክፉ መናፍስት ሳይሆኑ የዕድሜ መግፋት ነበር። ራሔል ልጅ ስትወልድ የሞተችው በሰይጣን ምክንያት ሳይሆን በሰብዓዊ ድካም ነበር። (ዘፍጥረት 35:17-19) ከዚያ በኋላ የነበሩት የጥንቶቹ ታማኝ አገልጋዮች ሁሉ የሞቱት በድግምት ወይም በእርግማን ሳይሆን በወረሱት አለፍጽምና ምክንያት ነበር።
የሚያጋጥመን በሽታ ሁሉ የማይታዩ መናፍስት ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት አለበት ብሎ ማሰብ ወጥመድ ነው። ይህ መናፍስትን በጣም እንድንፈራ ሊያደርገን ይችላል። ከዚያም በምንታመምበት ጊዜ ከአጋንንት ከመራቅ ይልቅ እነርሱን ለመለማመን ልንፈተን እንችላለን። ሰይጣን በመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንታመን እስከማድረግ ድረስ ካስፈራራን በእውነተኛው አምላክ በይሖዋ ላይ ያለን ትምክህት ጠፍቷል ማለት ነው። (2 ቆሮንቶስ 6:15) ለአምላክ ባለን አክብሮታዊ ፍርሃት እንጂ ለባላጋራው ባለን ከአጉል እምነት የመነጨ ፍርሃት መመራት የለብንም።—ራእይ 14:7
ትንሿ ኦማጂ ከክፉ መናፍስት ሊጠብቃት የሚችለውን ከሁሉ የሚበልጥ ጥበቃ አግኝታለች። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው የምታምን እናት ስላለቻት አምላክ ‘ቅዱስ’ አድርጎ የሚቆጥራት ሲሆን እናቷም አምላክ በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ከልጅዋ ጋር ይሆን ዘንድ ልትጸልይ ትችላለች። (1 ቆሮንቶስ 7:14) ሐዋ እንደዚህ ያለ ትክክለኛ እውቀት በማግኘት ስለተባረከች በክታቦች ከመታመን ይልቅ ለኦማጂ ውጤታማ የሆነ የሕክምና ዘዴ ልትፈልግላት ችላ ነበር።
በሽታ የሚያመጡ የተለያዩ ምክንያቶች
ብዙ ሰዎች በመናፍስት አያምኑም። በሚታመሙበት ወቅት አቅማቸው የሚፈቅድ ከሆነ ሐኪም ዘንድ ይሄዳሉ። እርግጥ አንድ የታመመ ሰው ሐኪም ዘንድ ቢሄድም እንኳን ላይድን ይችላል። ሐኪሞች ተአምር ሊሠሩ አይችሉም። ይሁን እንጂ በአጉል እምነት የተተበተቡ ብዙ ሰዎች ሊድኑ ሲችሉ ሐኪም ዘንድ የሚሄዱት ምንም ማድረግ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ከደረሱ በኋላ ነው። መጀመሪያ በመናፍስታዊ ኃይሎች እርዳታ ለመፈወስ ይሞክራሉ። ከዚያም እነዚህ ዘዴዎች ሳይሠሩ ሲቀሩ እንደ መጨረሻ አማራጭ በመውሰድ ሐኪም ዘንድ ለእርዳታ ይሄዳሉ። ብዙዎች ሊድኑ ሲችሉ ሕይወታቸውን ያጣሉ።
ሌሎች ደግሞ ባጭሩ የሚቀጩት ባለማወቅ ምክንያት ነው። የበሽታ ምልክቶች ምን እንደሆኑና ለመከላከል ደግሞ ምን ተግባራዊ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት አያውቁም። እውቀት ሳያስፈልግ ለሥቃይ ከመዳረግ ሊጠብቀን ይችላል። ያልተማሩ እናቶች ከተማሩት ይልቅ ብዙ ልጆችን በበሽታ ምክንያት እንደሚያጡ ማወቁ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ነው። አዎን አለማወቅ ሕይወትን ሊያሳጣ ይችላል።
ሌላው ለበሽታ ምክንያት የሚሆነው ነገር ቸልተኝነት ነው። ለምሳሌ ያህል ብዙዎች የሚታመሙት ምግቡ ከመበላቱ በፊት ነፍሳት እንዲወሩት በመፍቀዳቸው ወይም ደግሞ ምግቡን የሚያዘጋጁት ሰዎች አስቀድመው እጃቸውን ባለመታጠባቸው ነው። በወባ በሚጠቃ ክልል ውስጥ የወባ ትንኝ መከላከያ አጎበር ሳይዘረጉ መተኛትም በጣም አደገኛ ነው።a ጤንነትን በተመለከተ “ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ” የሚለው አባባል ብዙውን ጊዜ ይሠራል።
ጥበብ የጎደለው የአኗኗር ዘይቤ በሚልዮን ለሚቆጠሩ ሰዎች መታመምና በአጭር መቀጨት ምክንያት ሆኗል። ስካር፣ የጾታ ብልግና፣ አደገኛ መድኃኒቶችን አለአግባብ መጠቀምና ትምባሆ ማጨስ የብዙዎችን ጤና አቃውሷል። አንድ ሰው በእነዚህ መጥፎ ድርጊቶች ውስጥ ተዘፍቆ በሽታ ላይ ቢወድቅ ሰው ስለደገመበት ወይም አንድ መንፈስ ስላጠቃው ነው ማለት ይቻላል? አይቻልም። ለያዘው በሽታ ተጠያቂው ራሱ ነው። በመናፍስት ማሳበብ ጥበብ ለጎደለው የአኗኗር ዘይቤው ከተጠያቂነት ለማምለጥ ቀዳዳ መፈለግ ይሆናል።
እርግጥ አንዳንዶቹን ነገሮች ልንቆጣጠራቸው አንችልም። ለምሳሌ ያህል በሽታን ለሚያመጡ ረቂቅ ሕዋሳት ወይም ብክለት ልንጋለጥ እንችላለን። ኦማጂንም ያጋጠማት ይኸው ነው። ተቅማጥ እንዲይዛት ምክንያት የሆነው ነገር ምን እንደሆነ እናቷ አላወቀችም ነበር። ቤቷንና አጥር ግቢዋን በንጽሕና ስለምትይዝ እንዲሁም ምግብ ከማዘጋጀቷ በፊት ሁልጊዜ እጆቿን ስለምትታጠብ ልጆቿ እንደ ሌሎቹ ልጆች ቶሎ ቶሎ አይታመሙም። ይሁን እንጂ ልጆች አልፎ አልፎ መታመማቸው አይቀርም። ተቅማጥን የሚያመጡ 25 የሚያህሉ የተለያዩ ኢንፌክሽኖች አሉ። ምናልባት ለኦማጂ ችግር ምክንያት የሆነው የትኛው እንደሆነ ማንም ላያውቅ ይችላል።
ዘላቂ መፍትሔ
በሽታ መኖሩ የአምላክ ጥፋት አይደለም። “እግዚአብሔር በክፉ አይፈተንምና፤ እርሱ ራሱስ ማንንም አይፈትንም።” (ያዕቆብ 1:13) ከአምላኪዎቹ አንዱ ቢታመም ይሖዋ በመንፈሳዊ ነገሮች ይደግፈዋል። “እግዚአብሔር በደዌው አልጋ ሳለ ይረዳዋል፤ መኝታውን ሁሉ በበሽታው ጊዜ ያነጥፍለታል።” (መዝሙር 41:3) አዎን፣ አምላክ ሩኅሩኅ ነው። እኛን ለመርዳት እንጂ ለመጉዳት አያስብም።
ደግሞም ይሖዋ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አማካኝነት ለበሽታ ዘላቂ መፍትሔ አዘጋጅቷል። ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከኃጢአት የተቤዡ ሲሆን በመጨረሻ ፍጹም ጤንነት አግኝተው ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም ለመኖር ይበቃሉ። (ማቴዎስ 5:5፤ ዮሐንስ 3:16) የኢየሱስ ተአምራት የአምላክ መንግሥት የሚያመጣው እውነተኛ ፈውስ ምን ሊመስል እንደሚችል በጥቂቱ ያመላከቱ ነበሩ። አምላክ ሰይጣንን እና አጋንንቱንም ያስወግዳቸዋል። (ሮሜ 16:20) በእርግጥም ይሖዋ በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ አስደናቂ ነገሮችን አዘጋጅቷል። ከእኛ የሚፈለገው ትዕግሥትና ጽናት ብቻ ነው።
እስከዚያው ድረስ ግን አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስና በታማኝ አምላኪዎች ዓለም አቀፍ የወንድማማች ማኅበር አማካኝነት ተግባራዊ ጥበብና መንፈሳዊ መመሪያ ያቀርብልናል። የጤና ችግር ሊያስከትሉ የሚችሉ መጥፎ ድርጊቶችን እንዴት መራቅ እንደምንችል ይጠቁመናል። እንዲሁም ችግሮች ሲነሱ ሊረዱን የሚችሉ እውነተኛ ጓደኞች ይሰጠናል።
እስቲ እንደገና ስለ ኢዮብ አስብ። ኢዮብ ወደ ጠንቋይ ሄዶ ቢሆን ኖሮ የከፋ ስህተት ይሆን ነበር! የአምላክን ጥበቃና ካጋጠመው ከባድ መከራ በኋላ ያገኘውን በረከት ሁሉ ያጣ ነበር። አምላክ ኢዮብን አልረሳውም፤ እኛንም ቢሆን አይረሳንም። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ “ኢዮብ እንደ ታገሠ ሰምታችኋል፣ ጌታም እንደ ፈጸመለት አይታችኋል” ብሏል። (ያዕቆብ 5:11) እኛም ተስፋ ካልቆረጥን አምላክ በወሰነው ጊዜ አስደናቂ በረከቶችን እናገኛለን።
ትንሿ ኦማጂስ ምን ሆነች? እናቷ የመጠበቂያ ግንብ ተጓዳኝ በሆነው ንቁ! መጽሔት ላይ የወጣውን የሰውነትን ፈሳሽ ለመተካት የሚጠጣ ፈሳሽ በመስጠት ስለሚከናወነው ሕክምና (oral rehydration therapy) የሚገልጸውን ርዕስ አስታወሰች።b እዚያ ላይ ያለውን መመሪያ በመከተል ለኦማጂ የምትጠጣው ፈሳሽ አዘጋጀችላት። ከዚያ በኋላ ትንሿ ልጅ ደህና ሆነች።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በየዓመቱ ወደ ግማሽ ቢልዮን የሚጠጉ ሰዎች በወባ በሽታ ይለከፋሉ። በየዓመቱ ሁለት ሚልዮን የሚሆኑ ሰዎች በዚህ በሽታ የሚሞቱ ሲሆን አብዛኛዎቹ የሚገኙት አፍሪካ ውስጥ ነው።
b የመስከረም 22, 1985 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 24-5 ላይ “ሕይወትን የሚያድን ጨዋማ የሆነ ፈሳሽ!” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ይሖዋ በሽታን ለማስወገድ ዘላቂ መፍትሔ አዘጋጅቷል