የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 11/1 ገጽ 3-4
  • 2000 የተለየ ዓመት ነውን?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • 2000 የተለየ ዓመት ነውን?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ሦስተኛው ሺህ የሚጀምረው መቼ ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • በ2000 ኮምፒዩተሮች ከአገልግሎት ውጭ መሆናቸው አንተንም ይነካ ይሆን?
    ንቁ!—1999
  • አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?
    አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?
  • ከአንባቢዎቻችን
    ንቁ!—2009
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 11/1 ገጽ 3-4

2000 የተለየ ዓመት ነውን?

መጪውን 2000 ዓመት ልዩ የሚያደርገው ነገር አለ? በምዕራቡ ዓለም የሚኖሩ ሰዎች በጥቅሉ የሦስተኛው ሺህ የመጀመሪያ ዓመት አድርገው ይመለከቱታል። ዕለቱን አክብሮ ለመዋል ከፍተኛ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። የአዲሱ ሺህ ዓመት መዳረሻ የሆኑትን ሰከንዶች ለመቁጠር ግዙፍ ኤሌክትሮኒክ ሰዓቶች በመገጠም ላይ ናቸው። የአዲሱን ዓመት ዋዜማ ለማክበር የዳንስ ምሽቶች በመዘጋጀት ላይ ናቸው። ሁለተኛው ሺህ ማብቃቱን የሚገልጹ መፈክሮች የተጻፈባቸው ካኔተራዎች በትናንሽ ከተሞች በሚገኙ ሱቆችና በትላልቅ ከተሞች በሚገኙ የገበያ አዳራሾች እየተቸበቸቡ ነው።

ትላልቅም ሆኑ ትናንሽ አብያተ ክርስቲያናት ለአንድ ዓመት በሚዘልቀው ክብረ በዓል ተካፋዮች ይሆናሉ። በሚቀጥለው ዓመት መግቢያ ላይ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ፖል ዳግማዊ “የሮማ ካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት የሺህ ዓመት የኢዮቤልዩ ክብረ በዓል” ተብሎ የተጠራውን በዓል ለማክበር የሮማ ካቶሊኮችን በመምራት ወደ እስራኤል ይጓዛሉ ተብሎ ይጠበቃል። በሚቀጥለው ዓመት ከአጥባቂዎቹ ሃይማኖተኞች አንስቶ በጉጉት ተነሣስተው እስከሚሄዱት ድረስ ከሁለት ተኩል እስከ ስድስት ሚልዮን የሚሆኑ አገር ጎብኚዎች እስራኤልን ለመጎብኘት እቅድ እንዳወጡ ተገምቷል።

ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው ሰዎች እስራኤልን ለመጎብኘት እቅድ ያወጡት ለምንድን ነው? ሮጀር ካርዲናል ኤቸገራይ የተባሉት የቫቲካን ባለ ሥልጣን ጳጳሱን ወክለው ሲናገሩ እንዲህ ብለዋል:- “2000 ክርስቶስንና በዚህ አገር ያሳለፈውን ሕይወት የምናስብበት ዓመት ነው። ስለዚህ ጳጳሱ ወደዚህ መምጣታቸው ምንም አያስደንቅም።” ክርስቶስ ከ2000 ጋር የተዛመደው እንዴት ነው? በ2000 ክርስቶስ ከተወለደ ልክ 2,000 ዓመት ይሆነዋል የሚል የተለመደ አባባል አለ። ይሁንና እንደዚያ ነውን? ይህን ነጥብ እንመለስበታለን።

2000 ዓመት ለአንዳንድ የሃይማኖት ቡድኖች አባላት ከዚህም የበለጠ ትርጉም አለው። በቀጣዩ ዓመት ወይም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ እንደሚመለስና የራእይ መጽሐፍ የሚናገርለት የአርማጌዶን ጦርነት በመጊዶ ሸለቆ ውስጥ እንደሚካሄድ አጥብቀው ያምናሉ። (ራእይ 16:​14-16) እነዚህን ክንውኖች ለማየት በመጓጓት በመቶዎች የሚቆጠሩ የዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪዎች ቤታቸውንና ንብረታቸውን በመሸጥ ወደ እስራኤል እየተጓዙ ነው። ቤታቸውን ትተው መሄድ ለማይችሉ ሰዎች ጥቅም ሲባል ታዋቂው የዩናይትድ ስቴትሱ ወንጌላዊ የኢየሱስን መመለስ በቴሌቪዥን በባለ ቀለም ምስል ለማስተላለፍ ቃል መግባቱ ተዘግቧል!

በምዕራባውያኑ አገሮች ሦስተኛውን ሺህ ለመቀበል ሽር ጉዱ ተጧጡፏል። ይሁንና በሌሎች አገሮች የሚኖሩ ሰዎች መደበኛ የሆነውን የእለት ተለት እንቅስቃሴያቸውን በማከናወን ላይ ይገኛሉ። አብዛኛውን የዓለም ኅብረተሰብ ያቀፉት እነዚህ ሰዎች የናዝሬቱ ኢየሱስ መሲህ መሆኑን አያምኑም። ከክርስቶስ ልደት በፊትና ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሚለውን የዘመን ቀመር የሚቀበሉትም ሁሉም አይደሉም።a ለምሳሌ ያህል ብዙ ሙስሊሞች የራሳቸው የዘመን አቆጣጠር ያላቸው ሲሆን በዚህ አቆጣጠር መሠረትም የሚቀጥለው ዓመት 1420 እንጂ 2000 አይደለም። ሙስሊሞች መነሻ ያደረጉት መሐመድ ከመካ ወደ መዲና ሸሽቶ የሄደበትን ጊዜ ነው። በአጠቃላይ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች ወደ 40 የሚጠጉ የተለያዩ የዘመን አቆጣጠሮችን ይጠቀማሉ።

ሁለት ሺህ ለክርስቲያኖች ትርጉም ይኖረው ይሆን? ጥር 1, 2000 ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ዕለት ነውን? እነዚህ ጥያቄዎች በሚቀጥለው ርዕስ መልስ ያገኛሉ።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ከክርስቶስ ልደት በፊትና ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሚለው አቆጣጠር መሠረት ኢየሱስ ተወልዶበታል ተብሎ ከሚታሰበው ጊዜ በፊት የተከናወኑ ነገሮች “ከክርስቶስ ልደት በፊት” የሚል ስያሜ ሲሰጣቸው ከዚያ በኋላ የተከናወኑ ነገሮች ደግሞ “ከክርስቶስ ልደት በኋላ” ወይም (አኖ ዶሚኒ:- “በጌታ ዘመን”) ተብለው ይጠራሉ። ይሁን እንጂ አንዳንድ ምሁራን “ከዘአበ” (ከዘመናችን አቆጣጠር በፊት) እና “እዘአ” (እንደ ዘመናችን አቆጣጠር) በሚለው ሃይማኖታዊ ያልሆነ አቆጣጠር መጠቀም ይመርጣሉ።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ