የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w99 11/1 ገጽ 4-6
  • ሦስተኛው ሺህ የሚጀምረው መቼ ነው?

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሦስተኛው ሺህ የሚጀምረው መቼ ነው?
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነው?
  • የሺህ ዓመት ተስፋቸው ሳይፈጸም ይቀር ይሆን?
  • 2000 የተለየ ዓመት ነውን?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
  • አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?
    አዲሱ ሺህ ዓመት—የወደፊቱ ጊዜ ምን ተስፋ ይዞልሃል?
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ማውጣት የሚቻለው እንዴት ነው?
    ተጨማሪ ርዕሰ ጉዳዮች
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1999
w99 11/1 ገጽ 4-6

ሦስተኛው ሺህ የሚጀምረው መቼ ነው?

ሦስተኛው ሺህ የሚጀምረው በ2000 ሳይሆን በ2001 ነው ሲባል ሰምተሃል? ይህ አባባል በተወሰነ መጠን ትክክል ነው። አንዳንዶች እንደሚያስቡት ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው ዛሬ 1 ከዘአበ ተብሎ በሚታወቀው ጊዜ ነው ብንል ታኅሣሥ 31, 2000 (1999 ሳይሆን) ሁለተኛው ሺህ አብቅቶ ጥር 1, 2001 ሦስተኛው ሺህ የሚጀምርበት ጊዜ ይሆናል።a ይሁን እንጂ በዛሬው ጊዜ ሁሉም ምሁራን ለማለት ይቻላል ኢየሱስ ክርስቶስ የተወለደው በ1 ከዘአበ እንዳልሆነ ይስማማሉ። ታዲያ ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነው?

ኢየሱስ የተወለደው መቼ ነው?

መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ የተወለደበትን ትክክለኛ ጊዜ አይናገርም። ይሁንና “በንጉሡ በሄሮድስ ዘመን” ስለ መወለዱ ይናገራል። (ማቴዎስ 2:​1) ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን ሄሮድስ በ4 ከዘአበ እንደሞተና ኢየሱስ ከዚያ ቀደም ብሎ ምናልባትም በ5 ወይም በ6 ከዘአበ እንደተወለደ ያምናሉ። ሄሮድስ የሞተበትን ጊዜ በሚመለከት ወደዚህ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ የቻሉት በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖር የነበረው የአይሁድ ታሪክ ጸሐፊ ፍላቪየስ ጆሴፈስ ከተናገረው ነገር በመነሳት ነው።b

እንደ ጆሴፈስ አባባል ከሆነ ንጉሥ ሄሮድስ ከመሞቱ ትንሽ ቀደም ብሎ የጨረቃ ግርዶሽ ታይቶ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራኑ በ4 ከዘአበ መጋቢት 11 ዕለት የታየውን ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ ሄሮድስ የሞተው በዚህ ዓመት ነው ለማለት እንደ ማስረጃ ይጠቀሙበታል። ይሁን እንጂ በ1 ከዘአበ ጥር 8 ዕለት ሙሉ የጨረቃ ግርዶሽና ታኅሣሥ 27 ቀን ደግሞ ከፊል የጨረቃ ግርዶሽ ነበረ። ጆሴፈስ የተናገረው በ1 ከዘአበ ከነበሩት የጨረቃ ግርዶሾች ውስጥ ስለ አንዱ ይሁን በ4 ከዘአበ ስለታየው የጨረቃ ግርዶሽ ማንም በእርግጠኝነት ሊናገር አይችልም። በመሆኑም ሄሮድስ የሞተበትን ትክክለኛ ዓመት ለመጠቆም ጆሴፈስ የተናገረውን እንደ ማስረጃ መጠቀም አንችልም። የእሱን ሐሳብ እንደ ማስረጃ እንጠቀም ብንል እንኳ ኢየሱስ የተወለደበትን ጊዜ ለማወቅ እንድንችል ተጨማሪ መረጃ ማግኘት ያስፈልገናል።

ኢየሱስ የተወለደበትን ዘመን ለማወቅ የሚረዳንን ጠንካራ ማስረጃ የምናገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ ነው። በመንፈስ አነሣሽነት የተጻፈው ዘገባ የኢየሱስ ዘመድ የሆነው መጥምቁ ዮሐንስ የነቢይነት ሥራውን የጀመረው የሮማው ንጉሠ ነገሥት ጢባርዮስ ቄሣር በነገሠ በ15ኛው ዓመት መሆኑን ይናገራል። (ሉቃስ 3:​1, 2) ሌሎች ታሪካዊ ምንጮች እንደሚያረጋግጡት ጢባርዮስ ንጉሠ ነገሥት ተደርጎ የተሾመው መስከረም 15, 14 እዘአ ስለሆነ 15ኛ ዓመቱ ከ28 እዘአ መገባደጃ እስከ 29 እዘአ መገባደጃ ድረስ ይሆናል። ዮሐንስ አገልግሎቱን የጀመረው በዚያ ጊዜ ሲሆን ኢየሱስ ደግሞ ከስድስት ወራት በኋላ አገልግሎቱን እንደጀመረ የተረጋገጠ ነው። (ሉቃስ 1:​24-31) ይህ ከሌሎች ማስረጃዎች ጋር ተዳምሮ ኢየሱስ አገልግሎቱን የጀመረው በ29 እዘአ የበልግ ወቅት እንደሆነ ያረጋግጣል።c ኢየሱስ አገልግሎቱን በጀመረ ጊዜ “ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ያህል” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሉቃስ 3:​23) በ29 እዘአ በልግ ላይ 30 ዓመት ሆኖት ከነበረ የተወለደው በ2 ከዘአበ የበልግ ወቅት ላይ መሆን አለበት። ስለዚህ ከ2 ከዘአበ የበልግ ወቅት ተነሥተን ሁለት ሺህ ዓመት ወደፊት ስንቆጥር (ዜሮ የሚባል ዓመት ስለሌለ ከ2 ከዘአበ እስከ 1 እዘአ ድረስ ያለው ጊዜ ሁለት ዓመት ይሆናል) በ1999 የበልግ ወቅት ላይ ሁለተኛው ሺህ አልቆ ሦስተኛው ሺህ እንደጀመረ ለመገንዘብ እንችላለን!

ይህ ለውጥ ያመጣል? ለምሳሌ ያህል ሦስተኛው ሺህ በራእይ መጽሐፍ ላይ የተገለጸው የኢየሱስ ክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት የሚጀምርበት ጊዜ ይሆናልን? አይሆንም። መጽሐፍ ቅዱስ በሦስተኛው ሺህ እና በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መካከል ተዛምዶ እንዳለ የሚጠቁምበት አንድም ቦታ የለም።

ኢየሱስ ተከታዮቹ ዘመናትን እንዳያሰሉ አስጠንቅቋቸዋል። ደቀ መዛሙርቱን “አብ በገዛ ሥልጣኑ ያደረገውን ወራትንና ዘመናትን ታውቁ ዘንድ ለእናንተ አልተሰጣችሁም” ብሏቸዋል። (ሥራ 1:​7) ኢየሱስ ከዚያ ቀደም ብሎም አምላክ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ እርምጃ በመውሰድ ለክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መንገድ የሚጠርግበትን ጊዜ እሱ ራሱ እንኳን እንደማያውቀው ገልጾ ነበር። “ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም” ብሏል።​—⁠ማቴዎስ 24:​36

ክርስቶስ ሰው ሆኖ ከተወለደ ከ2,000 ዓመታት በኋላ ተመልሶ ይመጣል ብሎ መጠበቁ ምክንያታዊ ነውን? የለም፣ ምክንያታዊ አይደለም። ኢየሱስ የተወለደበትን ጊዜ አሳምሮ ያውቃል። እንዲሁም ከዚያ ቀን አንስቶ 2,000 ዓመታትን መቁጠር እንደሚችል የተረጋገጠ ነው። ይሁንና የሚመጣበትን ቀንና ሰዓት አያውቅም ነበር። ተመልሶ የሚመጣበትን ቀን ማወቅ ያን ያህል ቀላል እንደማይሆን እርግጥ ነው! ‘ወራትና ዘመናትን’ ማለትም የጊዜ ሠሌዳን መወሰኑ የአብ ሥልጣን ነው። ይህ እርሱ ብቻ የሚያውቀው ነገር ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ ተከታዮቹ በሙሉ በአንድ በተወሰነ ቦታ እንዲጠብቁት አላዘዘም። አንድ ላይ ተሰባስበው እንዲጠብቁት ሳይሆን ‘እስከ ምድር ዳር ድረስ’ ተሠራጭተው ከብሔራት ሁሉ ሰዎችን ደቀ መዛሙርት እንዲያደርጉ ነግሯቸው ነበር። ይህን ትእዛዙን አልሻረውም።​—⁠ሥራ 1:​8፤ ማቴዎስ 28:​19, 20

የሺህ ዓመት ተስፋቸው ሳይፈጸም ይቀር ይሆን?

ያም ሆኖ ግን አንዳንድ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች 2000 ዓመትን የሚጠባበቁት በከፍተኛ ጉጉት ነው። በሚቀጥሉት ጥቂት ወራት ውስጥ የራእይ መጽሐፍ የተወሰኑ ክፍሎች ቃል በቃል ተፈጻሚነት እንደሚኖራቸው ያምናሉ። እንዲያውም እነርሱም ጭምር በዚያ ፍጻሜ ውስጥ ተካፋዮች እንደሚሆኑ አድርገው ያስባሉ። ለምሳሌ ያህል ‘በመንፈሳዊ ምሳሌ ሰዶምና ግብጽ በተባለች ደግሞ ጌታቸው በተሰቀለባት’ “በታላቂቱ ከተማ” ስለሚተነብዩት ሁለት ምስክሮች የሚናገረውን በራእይ 11:​3, 7, 8 ላይ ተመዝግቦ የሚገኘውን ትንቢት ይጠቅሳሉ። ምሥክራቸውን ሲፈጽሙ እነዚህ ሁለት ምሥክሮች ከጥልቁ በሚወጣው አስፈሪ አውሬ ይገደላሉ።

ታኅሣሥ 27, 1998 የታተመው ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ መጋዚን እንደዘገበው ከሆነ የአንድ ሃይማኖታዊ ቡድን መሪ “የምድርን መጥፋትና የጌታን መምጣት ከሚያውጁት ሁለት ምስክሮች መካከል አንዱ እሱ መሆኑንና ከዚያም በኢየሩሳሌም አደባባዮች ላይ በሰይጣን እንደሚገደል ለተከታዮቹ ተናግሯል።” የእስራኤል ባለ ሥልጣናት ይህ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው የታወቀ ነው። በጦር መሣሪያ የታገዘ ግጭት ሊያስነሳ የሚችል ቢሆንም አንዳንድ ጽንፈኞች ትንቢቱን ራሳቸው “ለመፈጸም” ይሞክሩ ይሆናል የሚል ስጋት አለባቸው! ይሁን እንጂ አምላክ ዓላማውን ከዳር ለማድረስ የሰውን “እርዳታ” አይሻም። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች በሙሉ አምላክ በወሰነው ጊዜና በራሱ መንገድ ተፈጻሚነታቸውን ያገኛሉ።

የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው “በምልክቶች [NW]” ነው። በራእይ 1:​1 አባባል መሠረት ኢየሱስ በቅርቡ የሚሆነውን ነገር “ለባሪያዎቹ” (ለጠቅላላው ዓለም ሳይሆን) ለማሳየት ፈልጎ ነበር። የክርስቶስ ባሪያዎች ወይም ተከታዮች የራእይን መጽሐፍ ለመረዳት ከፈለጉ ይሖዋ እሱን ለሚታዘዙት ሰዎች የሚሰጠው የአምላክ ቅዱስ መንፈስ ያስፈልጋቸዋል። የራእይን መጽሐፍ ቃል በቃል ለመረዳት የሚቻል ቢሆን ኖሮ እምነት የለሽ የሆኑ ሰዎች እንኳን ሳይቀሩ ሊያነቡትና ሊያስተውሉት በቻሉ ነበር። ክርስቲያኖችም ራእዩን ለመረዳት የሚያስችላቸውን መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት መጸለይ አያስፈልጋቸውም ነበር።​—⁠ማቴዎስ 13:​10-15

በቅዱስ ጽሑፋዊው ማረጋገጫ መሠረት ከኢየሱስ ልደት ተነሥተን ስንቆጥር ሦስተኛው ሺህ የሚጀምረው በ1999 የበልግ ወራት መሆኑንና ጥር 1, 2000ም ሆነ ጥር 1, 2001 ልዩ የሚያደርጋቸው ነገር አለመኖሩን ተመልክተናል። ይሁንና የክርስቲያኖችን ትኩረት የሚስብ ሌላ ሺህ ዓመት አለ። ይህ ሦስተኛው ሺህ ካልሆነ ታዲያ የትኛው ነው? የእነዚህ ተከታታይ ርዕሶች የመጨረሻው ክፍል ለዚህ ጥያቄ መልሱን ይሰጠናል።

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a በገጽ 5 ላይ የሚገኘውን “2000 ወይስ 2001?” የሚለውን ሣጥን ተመልከት።

b በእነዚህ ምሁራን የዘመን ስሌት መሠረት ከሆነ ሦስተኛው ሺህ የጀመረው በ1995 ወይም 1996 መሆን ነበረበት።

c ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) የተባለውን መጽሐፍ ጥራዝ 1 ገጽ 1094-5 ተመልከት።

[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

2000 ወይስ 2001?

አንዳንዶች ከኢየሱስ ልደት ተነሥተን ስንቆጥር ሦስተኛ ሺህ የሚጀምረው ጥር 1, 2001 ላይ ነው የሚሉበትን ምክንያት ለመረዳት የሚከተለውን ምሳሌ ተመልከት። ሁለት መቶ ገጾች ያሉት መጽሐፍ እያነበብክ ነው እንበል። ገጽ 200 አናት ላይ ስትደርስ 199 ገጾችን አንብበህ አንድ ገጽ ብቻ ይቀርሃል። ገጽ 200 መጨረሻ ላይ እስካልደረስክ ድረስ መጽሐፉን አንብበህ አጠናቅቀሃል አይባልም። በተመሳሳይም በታኅሣሥ 31, 1999 ላይ አብዛኛው ሰው እንደሚያስበው የዚህ ሺህ ዓመት 999 ዓመታት ያለፉ ሲሆን ይህ ሺህ ዓመት ሊያበቃ አንድ ዓመት ይቀረዋል። በዚህ አቆጣጠር መሠረት ሦስተኛው ሺህ የሚጀምረው ጥር 1, 2001 ላይ ይሆናል። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል እንደተገለጸው በዚህ ጊዜ ከኢየሱስ ልደት አንስቶ በትክክል 2,000 ዓመታት አልፈዋል ማለት አይደለም።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሣጥን]

ከክርስቶስ ልደት በፊትና ከክርስቶስ ልደት በኋላ የሚለው የዘመናት ቀመር የጀመረው እንዴት ነው?

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጆን ቀዳማዊ በስድስተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጀመሪያ ላይ አብያተ ክርስቲያናት በዓለ ትንሣኤን የሚያከብሩበትን ኦፊሴላዊ ቀን ለመቁረጥ የሚያስችል የዘመን ቀመር እንዲያዘጋጅ ዲዮናስዮስ ኤክሲጁስ ለተባለ መነኩሴ ኃላፊነቱን ሰጡ።

ዲዮናስዮስ ሥራውን ተያያዘው። ወደ ኋላ በመቁጠር ክርስቶስ የሞተበትን ጊዜ አልፎ በመሄድ ኢየሱስ የተወለደበት ነው ብሎ ያሰበው ጊዜ ላይ ደረሰ። ከዚያም እያንዳንዱን ዓመት ከዚያ ነጥብ በመነሳት ቁጥር ሰጠው። ዲዮናስዮስ ኢየሱስ ከተወለደበት ጊዜ አንስቶ ያለውን ወቅት “ከክርስቶስ ልደት በኋላ” (በእንግሊዝኛ “A.D.” ማለትም አኖ ዶሚኒ:- “በጌታችን ዓመት”) ብሎ ሰየመው። ዲዮናስዮስ ይዞት የተነሣው ዓላማ በዓለ ትንሣኤ የሚከበርበትን ቀን ለመወሰን የሚያስችል የማያሻማ ዘዴ መቀየስ ቢሆንም እግረ መንገዱንም ከክርስቶስ ልደት አንስቶ ዓመታትን የመቁጠር ንድፈ ሐሳብ እንዲጸነስ ምክንያት ሆኗል።

አብዛኞቹ ምሁራን ዲዮናስዮስ ለስሌቱ መሠረት አድርጎ በተጠቀመበት ዓመት ኢየሱስ እንዳልተወለደ የሚስማሙ ቢሆንም የእርሱ የዘመን አቆጣጠር ዘዴ ግን በጊዜ ሂደት ውስጥ የተለያዩ ነገሮች መቼ እንደተከናወኑ ለማወቅና አንዳቸው ከሌላው ጋር ስላላቸው ዝምድና እንድናስተውል ይረዳናል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ