የተስፋ መቁረጥን ስሜት ለመቋቋም ምን ማድረግ ይቻላል?
አንድ ሰው የተስፋ መቁረጥን ስሜት መዋጋት የሚችለው እንዴት ነው? የይሖዋ ምሥክሮችን ጉባኤ እየዞሩ ለሚጎበኙ በርካታ ተጓዥ የበላይ ተመልካቾች ይህ ጥያቄ ይቀርብላቸዋል። የሰጡት መልስ የተስፋ መቁረጥ ስሜት መንስዔው ምን እንደሆነና በማንኛውም ክርስቲያን ላይ ሊደርስ ለሚችለው ለዚህ ዓይነቱ ስሜት መፍትሔው ምን እንደሆነ እንድናውቅ ሊረዳን ይችላል።
የተስፋ መቁረጥን ስሜት ለመቋቋም መንስኤውንና መፍትሄውን ማጤን ብቻ አይበቃም። ሆኖም ምልክቶቹ ለጸሎት ወይም ለግል ጥናት ፍላጎት ማጣትን፣ በስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ አለመገኘትን፣ የቅንዓት መቀነስንና ሌላው ቀርቶ ለክርስቲያን ባልደረቦች ቀዝቃዛ ስሜት ማሳየትን ሊጨምሩ ይችላሉ። ይሁን እንጂ ለወንጌላዊነቱ ሥራ ያለን ቅንዓት መቀነስ ዋና ምልክት ነው። እስቲ ምልክቶቹን እንመርምርና አንዳንድ መፍትሔዎችን እንመልከት።
በወንጌላዊነት ሥራችን የሚያጋጥም የተስፋ መቁረጥ ስሜት
ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ተልዕኮ ጋር የሚመጡ ችግሮች እንደሚኖሩ ያውቅ ነበር። (ማቴዎስ 28:19, 20) የስብከት እንቅስቃሴያቸው ስደት ሊያስነሳባቸው እንደሚችል ያውቅ ስለነበረ ተከታዮቹን “እንደ በጎች በተኵላዎች መካከል” እንደላካቸው አድርጎ ተናግሯል። (ማቴዎስ 10:16-23) ሆኖም ይህ ተስፋ እንዲቆርጡ የሚያደርጋቸው አልነበረም። እንዲያውም፣ በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ የሚደገፉ የአምላክ አገልጋዮች ብዙውን ጊዜ ከሚደርስባቸው ስደት ጥንካሬ ያገኛሉ።—ሥራ 4:29-31፤ 5:41, 42
የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ከባድ ስደት ባይደርስባቸውም እንኳ ሰዎች ሁልጊዜ በጥሩ ሁኔታ ይቀበሏቸው ነበር ለማለት አይቻልም። (ማቴዎስ 10:11-15) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያከናውኑት የስብከት ሥራ ሁልጊዜ ያለ ችግር ሊከናወን አይችልም።a ብዙ ሰዎች በአምላክ ማመን አለማመን የግል ምርጫ እንደሆነ ስለሚሰማቸው ውይይት ለማድረግ ፈቃደኞች አይሆኑም። ሌሎች ደግሞ ለአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት መሠረተ ቢስ ጥላቻ ይኖራቸውና ከዚህ ድርጅት ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዲኖራቸው አይፈልጉ ይሆናል። የሰዎች ግድ የለሽነት፣ ፍሬ ማጣት ወይም ሌሎች የተለያዩ ችግሮች የተስፋ መቁረጥ ስሜት ዋነኛ መንስዔ ሊሆኑ ይችላሉ። እነዚህን እንቅፋቶች እንዴት መወጣት ይቻላል?
የተሻሉ ውጤቶች ማግኘት
ከአገልግሎታችን የምናገኘው ደስታ በከፊል የተመካው በምናገኘው ውጤት ላይ ነው። ታዲያ ውጤታማ የሆነ አገልግሎት ማከናወን የምንችለው እንዴት ነው? ‘ሰው አጥማጆች’ መሆናችንን አንርሳ። (ማርቆስ 1:16-18) በጥንቷ እስራኤል ዓሣ አጥማጆች ዓሣ ለማስገር የሚሠማሩት ብዙ ዓሣ መያዝ በሚችሉበት በሌሊት ነበር። እኛም ብዙ ሰዎች እቤታቸው በሚገኙበትና መልእክታችንን ይበልጥ ሊያዳምጡ በሚችሉበት ጊዜ ‘ማጥመድ’ እንችል ዘንድ የአገልግሎት ክልላችንን በሚገባ ማጥናት ይኖርብናል። ምናልባትም ምቹ የሆነው ጊዜ ምሽት ላይ፣ ቅዳሜና እሁድ ወይም በሌላ ወቅት ሊሆን ይችላል። ሙሉ ቀን ሥራ የሚውሉ ሰዎች በሚኖሩበት አካባቢ እንዲህ ማድረጉ ተግባራዊ እንደሆነ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ተናግሯል። የምሽት አገልግሎት ግሩም ውጤት እንደሚያስገኝ ገልጿል። የስልክ ወይም መደበኛ ያልሆነ ምሥክርነትም በርካታ ሰዎችን እንድናገኝ ያስችለናል።
በአገልግሎቱ ሳይታክቱ መካፈል ጥሩ ውጤት ያስገኛል። በምሥራቅ አውሮፓና በአንዳንድ የአፍሪካ አገሮች የመንግሥቱ ስብከት ሥራ ጥሩ እድገት እያሳየ ሲሆን ይህም ግሩም ጭማሪ እያስገኘ ነው። በተመሳሳይም ለረዥም ጊዜያት እንደ ጠፍ ተደርገው ይታዩ የነበሩ ወይም በተደጋጋሚ የተሸፈኑ የአገልግሎት ክልሎች ብዙ ጉባኤዎች እየተቋቋሙባቸው ነው። ይሁን እንጂ የእናንተ የአገልግሎት ክልል እንዲህ ያለ ውጤት የሚታይበት ባይሆንስ?
ጥሩ ዝንባሌ መያዝ
ኢየሱስ ያስቀመጠውን ግብ በአእምሯችን መያዛችን በአገልግሎት ላይ በሚያጋጥመን የግዴለሽነት ስሜት ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። የክርስቶስ ፍላጎት ደቀ መዛሙርቱ የሚገባቸውን ሰዎች ፈልገው እንዲያገኙ እንጂ ሰዎችን በጅምላ እንዲለውጡ አይደለም። አብዛኞቹ እስራኤላውያን የጥንት ነቢያትን እንዳልሰሙ ሁሉ በአሁኑ ጊዜም በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ምሥራቹን እንደማይቀበሉ በተደጋጋሚ ገልጿል።—ሕዝቅኤል 9:4፤ ማቴዎስ 10:11-15፤ ማርቆስ 4:14-20
“በመንፈሳዊ የጐደላቸው ነገር እንዳለ የሚታወቃቸው” ሰዎች ‘የመንግሥቱን ወንጌል’ በአመስጋኝነት መንፈስ ይቀበላሉ። (ማቴዎስ 5:3 NW፤ 24:14) እሱ በሚለው መሠረት አምላክን ማገልገል ይፈልጋሉ። ስለሆነም በስብከቱ እንቅስቃሴ የምናገኘው ውጤት በአብዛኛው የተመካው መልእክቱን በማድረስ ረገድ ባለን ችሎታ ላይ ሳይሆን በሰዎች የልብ ዝንባሌ ነው። እርግጥ ነው፣ ምሥራቹን ይበልጥ ማራኪ በሆነ መንገድ ለማቅረብ የበኩላችንን ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ሆኖም ኢየሱስ “የላከኝ አብ ከሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል የለም” በማለት እንደተናገረው የምናገኘው ውጤት የተመካው በአምላክ ላይ ነው።—ዮሐንስ 6:44
የወንጌላዊነት ሥራችን የይሖዋ ስም በስፋት እንዲታወቅ ያደርጋል። ሰዎች ሰሙም አልሰሙ የስብከት ሥራችን የይሖዋን ቅዱስ ስም እንዲቀደስ አስተዋጽዖ ያደርጋል። ከዚህም በላይ የወንጌላዊነት ሥራችን የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችንን የሚያረጋግጥ ከመሆኑም በላይ በጊዜያችን እየተከናወነ ባለው እጅግ አስፈላጊ ተልእኮ የመካፈል አጋጣሚ ይከፍትልናል።—ማቴዎስ 6:9፤ ዮሐንስ 15:8
ተስፋ የመቁረጥ ስሜትና ከሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት
በቤተሰብ ወይም በጉባኤ ውስጥ ከአንዳንድ ሰዎች ጋር ያለን ግንኙነት ተስፋ የሚያስቆርጡ ሁኔታዎችን ሊፈጥርብን ይችላል። ለምሳሌ ያህል ስሜታችንን የሚረዳልን እንደሌለ ይሰማን ይሆናል። በተጨማሪም የእምነት ባልደረቦቻችን አለፍጽምና ተስፋ ሊያስቆርጠን ይችላል። በዚህ ጊዜም ቅዱሳን ጽሑፎች ከፍተኛ እርዳታ ሊያበረክቱልን ይችላሉ።
‘መላው የወንድማማች ማኅበር’ አንድ ትልቅ ዓለም አቀፋዊ መንፈሳዊ ቤተሰብ እንዲመሠረት አድርጓል። (1 ጴጥሮስ 2:17 NW) ይሁን እንጂ በጠባይ አለመጣጣም የተነሳ ችግሮች በሚነሱበት ጊዜ በአንድ የተሳሰረ ሕዝብ አካል እንደሆንን ይሰማን የነበረው ስሜት ሊደበዝዝ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ በአንድነት ተስማምቶ ስለመኖር ተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ስለሰጠ የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችም ለዚህ ዓይነቱ ችግር የተጋለጡ እንደነበሩ ከሁኔታው ለመረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ያህል በመካከላቸው የነበረውን አለመግባባት እንዲያስወግዱ ኤዎድያን እና ሲንጤኪን የተባሉ ሁለት ክርስቲያን እህቶችን በጥብቅ መክሯቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 1:10፤ ኤፌሶን 4:1-3፤ ፊልጵስዩስ 4:2, 3
ችግሩ ይህ ከሆነ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ልባዊ ፍቅር በድጋሚ ማቀጣጠል የምንችለው እንዴት ነው? ክርስቶስ እንደሞተላቸውና እነርሱም እንደኛው በቤዛዊ መሥዋዕቱ ላይ እምነት እንዳላቸው ራሳችንን በማሳሰብ ነው። ብዙዎቹ ወንድሞቻችን የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ በመኮረጅ ሕይወታቸውን ለእኛ አሳልፈው ለመስጠት የተዘጋጁ መሆናቸውንም ልናስብ እንችላለን።
ከተወሰኑ ዓመታት በፊት በፓሪስ ፈረንሳይ የሚኖር አንድ ወጣት ምሥክር በመንግሥት አዳራሹ አጠገብ ተቀምጦ የነበረውን በውስጡ ቦምብ የነበረበትን አንድ ቦርሳ ተሸክሞ ለመሮጥ ፈጽሞ አላመነታም ነበር። በርካታ ደረጃዎችን በፍጥነት ከወረደ በኋላ በአካባቢው በሚገኝ በአንድ ሰው ሠራሽ ፏፏቴ ውስጥ ሲወረውረው ቦምቡ ፈነዳ። ሕይወቱን እንዲህ አደጋ ላይ ለመጣል ያነሳሳው ምን እንደሆነ በተጠየቀ ጊዜ እንዲህ በማለት መልሷል:- “ሕይወታችን አደጋ ላይ መውደቁን አውቄ ነበር። ስለዚህ ሁላችንም አንድ ላይ ከምናልቅ እኔ ብቻ ብሞት የተሻለ እንደሚሆን ተሰማኝ።”b ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ በቅርብ ለመከተል ዝግጁ የሆኑ እንዲህ ያሉ ወዳጆችን ማግኘት እንዴት ያለ በረከት ነው!
ከዚህም በተጨማሪ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ማጎሪያ ካምፕ ውስጥ የነበሩት የይሖዋ ምሥክሮች እርስ በርሳቸው እንዴት ይረዳዱ እንደነበር ልናሰላስል እንችላለን።c በቅርቡም በማላዊ የሚኖሩ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከአቋማቸው ፍንክች ባለማለት የታመኑ እውነተኛ ክርስቲያኖች መሆናቸውን አስመስክረዋል። በጉባኤያችን የሚገኙ ወንድሞቻችንም አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሟቸው ተመሳሳይ እርምጃ እንደሚወስዱ ማሰባችን በየዕለቱ የሚገጥሙንን አለመግባባቶችና ግጭቶች ችላ ብለን እንድናልፋቸው ወይም ቢያንስ አሳንሰን እንድንመለከታቸው አይገፋፋንምን? የክርስቶስ ዓይነት አስተሳሰብ ከኮተኮትን ከእምነት ባልደረቦቻችን ጋር የሚኖረን የዕለት ተዕለት ግንኙነት የተስፋ መቁረጥ ሳይሆን የማነቃቂያ ምንጭ ይሆንልናል።
ተስፋ የሚያስቆርጡ የግል ስሜቶች
“የምትዘገይ ተስፋ ልብን ታሳዝናለች፤ የተገኘች ፈቃድ ግን የሕይወት ዛፍ ናት።” (ምሳሌ 13:12) አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች የዚህ የነገሮች ሥርዓት ፍጻሜ የሚዘገይ ይመስላቸዋል። አሁን ያለንበት ጊዜ አማኝ ላልሆኑ ሰዎች ብቻ ሳይሆን ለክርስቲያኖችም ‘አስጨናቂ ዘመን’ ነው።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5
ሆኖም ክርስቲያኖች ከማያምኑ ሰዎች በተለየ መንገድ የአምላክ መንግሥት በቅርቡ በዚህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ላይ ጥፋት እንደሚያመጣ የሚያመለክተውን የኢየሱስን መገኘት ‘ምልክት’ በማየታቸው መደሰት ይኖርባቸዋል። (ማቴዎስ 24:3-14) ሁኔታዎቹ እየተባባሱ በሚሄዱበት ወቅት (‘በታላቁ መከራ ወቅት’ መሆኑ አይቀርም) የአምላክ አዲስ ዓለም መቃረቡን የሚያበስሩ በመሆናቸው ደስታችንን ይበልጥ ከፍ ያደርጉታል።—ማቴዎስ 24:21፤ 2 ጴጥሮስ 3:13
መንግሥቱ በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት ጊዜ ገና እንደሆነ አድርጎ ማሰቡ አንድ ክርስቲያን የበለጠውን ጊዜ ለቁሳዊ ነገሮች እንዲያውል ሊያደርገው ይችላል። ዓለማዊ ሥራንና መዝናኛን የመሳሰሉ ነገሮች ጊዜውንና ጉልበቱን እንዲያሟጥጡበት የሚፈቅድ ከሆነ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶቹን ተገቢ በሆነ መንገድ መፈጸም ይበልጥ አዳጋች እየሆነበት ይሄዳል። (ማቴዎስ 6:24, 33, 34) እንደዚህ ያለው ዝንባሌ ለብስጭት ከመዳረጉም በላይ ተስፋ የመቁረጥ ስሜት ሊያስከትል ይችላል። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች “በአዲሱ ሥርዓት ልናገኛቸው የምንችላቸውን ነገሮች በዚህ የነገሮች ሥርዓት ውስጥ ለማግኘት መጣር የማይሆን ነገር ነው” ሲል ተናግሯል።
ሁለት ፍቱን መድኃኒቶች
አንድ ሰው በሽታው በሕክምና ምርመራ አንዴ ከታወቀለት ፈውስ የሚሰጥ መድኃኒት ሊያገኝ የሚችለው እንዴት ነው? የግል ጥናት አንደኛው ፈዋሽ መድኃኒት ነው። ለምን? “የምናደርገውን ነገር ለምን ማድረግ እንዳለብን ያስታውሰናል” በማለት አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች አስተያየቱን ሰጥቷል። በተጨማሪም አንድ ሌላ ተጓዥ የበላይ ተመልካች “እንደ ግዴታ በመቁጠር በስብከቱ ሥራ መካፈል ሸክም እንዲሆንብን ያደርጋል” ብሏል። ይሁን እንጂ ጥሩ የግል ጥናት ወደ መጨረሻው ይበልጥ እየተጠጋን ስንሄድ በትክክል ምን ማድረግ እንዳለብን እንድናውቅ ይረዳናል። በተመሳሳይም የአምላክን ፈቃድ በማድረግ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት በመንፈሳዊ በደንብ መመገብ እንዳለብን ቅዱሳን ጽሑፎች በተደጋጋሚ ያሳስቡናል።—መዝሙር 1:1-3፤ 19:7-10፤ 119:1, 2
ሽማግሌዎች የሚያበረታቱ የእረኝነት ጉብኝቶችን በማድረግ ሌሎች የሚሰማቸውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲያሸንፉ ሊረዷቸው ይችላሉ። ሽማግሌዎች እንዲህ ያለውን የግል ጉብኝት ሲያደርጉ ሁላችንም ዋጋ እንዳለንና በይሖዋ ሕዝቦች መካከል ጠቃሚ ድርሻ እንደምናበረክት ሊጠቁሙ ይችላሉ። (1 ቆሮንቶስ 12:20-26) አንድ ሽማግሌ ክርስቲያን ባልደረቦቹን በሚመለከት ሲናገር እንዲህ ብሏል:- “ከፍተኛ ዋጋ እንዳላቸው እንዲገነዘቡ ለማድረግ ባለፉት ጊዜያት ያከናወኗቸውን ነገሮች አስታውሳቸዋለሁ። በይሖዋ ፊት ውድ እንደሆኑና የልጁ ደም እንደፈሰሰላቸው እገልጽላቸዋለሁ። ይህ ብዙውን ጊዜ ያጽናናቸዋል። እንዲህ ያለው አቀራረብ ጠንካራ በሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅስ ሲደገፍ ተስፋ ቆርጠው የነበሩት በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው መጸለይንና መጽሐፍ ቅዱስ ማንበብን የመሰሉ አዳዲስ ግቦችን ማውጣት ይጀምራሉ።”—ዕብራውያን 6:10
ሽማግሌዎች የእረኝነት ጉብኝት በሚያደርጉበት ወቅት አምላክን ማስደሰት አስቸጋሪ እንደሆነ በሚያስመስል መንገድ እንዳይናገሩ መጠንቀቅ ይኖርባቸዋል። ከዚያ ይልቅ የኢየሱስ ተከታዮች የተሸከሙት ሸክም ቀላል መሆኑን እንዲገነዘቡ በማድረግ በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተደቆሱ የእምነት ባልደረቦቻቸውን ሊረዷቸው ይችላሉ። ይህም ከምናከናውነው የክርስትና አገልግሎት ደስታ እንድናገኝ ያስችለናል።—ማቴዎስ 11:28-30
የተስፋ መቁረጥን ስሜት ማሸነፍ
መነሾው ምንም ይሁን ምን የተስፋ መቁረጥ ስሜት ተዋግተን ልናሸንፈው የሚገባ ችግር ነው። ሆኖም በዚህ ውጊያ ብቻችንን እንዳልሆንን አስታውስ። የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከተሰማን ክርስቲያን ወዳጆቻችን በተለይ ሽማግሌዎች የሚሰጡንን እርዳታ እንቀበል። እንዲህ በማድረግ የተስፋ መቁረጥን ስሜት መቀነስ እንችላለን።
ከሁሉም በላይ ደግሞ የተስፋ መቁረጥን ስሜት ታግለን ለማሸነፍ እንድንችል የአምላክን እርዳታ መጠየቅ አለብን። በጸሎት አማካኝነት በይሖዋ ላይ ከተደገፍን የተስፋ መቁረጥን ስሜት ፈጽመን እንድናሸንፍ ሊረዳን ይችላል። (መዝሙር 55:22፤ ፊልጵስዩስ 4:6, 7) የእርሱ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን በማንኛውም ወቅት እንደሚከተለው ብሎ የዘመረውን መዝሙራዊ ስሜት እኛም ልንካፈል እንችላለን:- “እልልታ የሚያውቅ ሕዝብ ምስጉን ነው፤ አቤቱ፣ በፊትህ ብርሃን ይሄዳሉ። በስምህ ቀኑን ሁሉ ደስ ይላቸዋል፣ በጽድቅህም ከፍ ከፍ ይላሉ፤ የኃይላቸው ትምክሕት አንተ ነህና፣ በሞገስህም ቀንዳችን ከፍ ከፍ ይላልና።”—መዝሙር 89:15-17
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ግንቦት 15, 1981 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ከቤት ወደ ቤት የሚደረገው አገልግሎት ተፈታታኝነት” የሚለውን ርዕስ ተመልከት።
b ኒው ዮርክ በሚገኘው በመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስ እና ትራክት ማኅበር የታተመውን የየካቲት 22, 1985 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ገጽ 12 እና 13ን ተመልከት።
c ነሐሴ 15, 1980 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “ከሞት ጉዞ ተረፍኩ” የሚለውንና ሰኔ 22, 1985 ንቁ! (እንግሊዝኛ) ላይ የወጣውን “በናዚ ጀርመን የጸና አቋም መያዝ” የሚሉትን ርዕሶች ተመልከት።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አፍቃሪ እረኞች የሚያደርጉት ገንቢ የእረኝነት ጉብኝት ክርስቲያኖች የሚሰማቸውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት እንዲያሸንፉ ሊረዳቸው ይችላል