አፖካሊፕስ አስፈሪ የሆነው ለምንድን ነው?
“ክርስቲያን ነን የሚሉ ሃይማኖታዊ አክራሪዎች [በሆነ መልኩ] መላውን ኅብረተሰብ የሚነካ ውድቀት የሚከሰትበት ጊዜ ሩቅ አይደለም እያሉ መተንበይ ከጀመሩ አሥርተ ዓመታት አስቆጥረዋል” በማለት የታይም መጽሔት ሃይማኖታዊ ዓምድ አዘጋጅ የሆኑት ዳሚየን ቶምፕሰን ተናግረዋል። “ዛሬ እነዚህ ትንበያዎች ሰዎች በቁም ነገር የሚመለከቷቸው ነገሮች በመሆን ብቻ አልተወሰኑም። በአንድ ወቅት ያላግጡባቸው የነበሩት የኮምፒዩተር ፕሮግራም አዘጋጆች፣ የንግድ ሰዎችና ፖለቲከኞች ሳይቀሩ የእነዚህ ትንበያዎች አራጋቢ ሆነዋል።” በ2000 በዓለም ዙሪያ ያሉ ኮምፒዩተሮች ችግር ይገጥማቸዋል የሚለው ፍርሃት “ከአሁን በፊት የለየላቸው ዓለማውያን የነበሩት ሰዎች” ይመጣል የተባለውን “ማኅበራዊ ሁከት፣ የመንግሥታት መሽመድመድ፣ ምግብ ለማግኘት የሚደረግ መራኮት፣ የአውሮፕላኖች ከሰማይ ጠቀስ ሕንጻዎች ጋር መላተም” በመፍራት “የወጣላቸው የሺህ ዓመት አማኞች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል” ሲሉ ገልጸዋል።
ጭንቀቱን ይበልጥ ያባባሰው ደግሞ ብዙውን ጊዜ “አፖካሊፕሳዊ” በመባል የሚጠሩት የተለያዩ ትናንሽ ሃይማኖታዊ ቡድኖች የሚያደርጉት ኅብረተሰቡን የሚያውክ እንቅስቃሴ ነው። በጥር 1999 ለ ፊጋሮ የተባለው ዕለታዊ የፈረንሳይኛ ጋዜጣ ባወጣው “ኢየሩሳሌም እና የአፖካሊፕስ የማስጠንቀቂያ ድምፅ” በሚል ዓምድ ሥር “የእስራኤል የፀጥታ ሠራተኞች በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ወይም በዚያ አቅራቢያ ሆነው ፓሩሲያን ወይም አፖካሊፕስን የሚጠባበቁት ሰዎች ቁጥር ከአንድ መቶ እንደሚበልጥ ገምተዋል” ብሏል።
የ1998 ብሪታኒካ ቡክ ኦቭ ዘ ይር “መዓት ይመጣል የሚሉ ኑፋቄዎችን” በተመለከተ ልዩ ዘገባ አውጥቶ ነበር። ሰዎች የገዛ ሕይወታቸውን እንዲያጠፉ ከሚያበረታቱ ሌሎች ኑፋቄያዊ ቡድኖች ጋር አዳምሮ ሄቨንስ ጌት፣ ፒፕልስ ቴምፕል፣ ኦርደር ኦቭ ሶላር ቴምፕልን እንዲሁም በ1995 በቶኪዮ በአንድ የምድር ውስጥ የባቡር መተላለፊያ መርዘኛ ጋዝ በማስቀመጥ ለ12 ሰዎች መሞትና በሺህ ለሚቆጠሩ ሰዎች መጎዳት ምክንያት የሆነውን የኦም ሺንሪክዮ (ታላቅ እውነት) ቡድን ጠቅሷል። የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ማርቲን ኢ ማርቲ ስለዚህ ሪፖርት ጠቅለል አድርገው ሲገልጹ እንዲህ በማለት ጽፈዋል:- “የቀን መቁጠሪያችን ወደ 2000 መሸጋገሩ እጅግ ስሜት ቀስቃሽ ነገር ነው። ይህም ብዙ ዓይነት ትንቢቶችና እንቅስቃሴዎች ብቅ እንዲሉ እንደሚያደርግ ምንም ጥርጥር የለውም። አንዳንዶቹም አደገኛ ሊሆኑ ይችላሉ። እንዲሁ እንደዋዛ የሚታይ ጊዜ አይሆንም።”
በታሪክ ዘመናት ስለ አፖካሊፕስ የነበረው ፍርሃት
አፖካሊፕስ ወይም ራእይ በአንደኛው መቶ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ለተጻፈው የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ የተሰጠ ስያሜ ነው። ይህ መጽሐፍ ካለው ትንቢታዊ ባሕርይና ከሚጠቀምበት እጅግ ምሳሌያዊ የሆነ አገላለጽ የተነሣ “አፖካሊፕሳዊ” የሚለው መግለጫ የራእይ መጽሐፍ ከመጻፉ ከረጅም ጊዜ በፊት የተጀመረውን አንድ ዓይነት የአጻጻፍ ስልት የተከተሉ ሥራዎች ለመግለጽ አገልግሏል። አፈ ታሪካዊ ይዘት ያለውና በምሳሌያዊ መግለጫዎች የተቀመጠው ይህ የሥነ ጽሑፍ ሥራ የተጀመረው በጥንቷ ፋርስና ከዚያም ቀደም ብሎ ነው። በመሆኑም ዘ ጁዊሽ ኢንሳይክለፒዲያ እንደሚለው ከሆነ “ይህ [የአይሁድ አፖካሊፕሳዊ] የጽሑፍ ሥራ በአብዛኛዎቹ አፈ ታሪካዊ ሥራዎች ላይ የሚንጸባረቀውን የባቢሎናውያን የአጻጻፍ ዘይቤ ወርሷል።”
የአይሁዳውያን አፖካሊፕሳዊ የጽሑፍ ሥራ ገንኖ የነበረው ከሁለተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ መጀመሪያ አንስቶ እስከ ሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ መጨረሻ ድረስ ነበር። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር እነዚህ ጽሑፎች እንዲጻፉ ምክንያት የሆነውን ነገር ሲያስረዱ እንዲህ ብለዋል:- “አይሁዳውያን ዘመናትን ሁሉ በሁለት ይከፍሏቸዋል። ሙሉ በሙሉ ክፉ የሆነው ይህ የአሁኑ ዘመን አንዱ ነበር። . . . በመሆኑም አይሁዳውያኑ የነገሮች መጨረሻ እንዲመጣ ተጠባብቀዋል። መጪው ዘመን ደግሞ ሰላም፣ ብልጽግናና ጽድቅ የሚሰፍንበት ሙሉ በሙሉ መልካም የሆነ፣ ወርቃማ የአምላክ ዘመን ነው። . . . ይህ የአሁኑ ዘመን ወደ መጪው ዘመን ሊለወጥ የሚችለው እንዴት ነው? አይሁዳውያን ይህ ለውጥ በሰብዓዊ ወኪል ፈጽሞ ሊመጣ እንደማይችል ያምኑ ስለነበር የአምላክን ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት በተስፋ ይጠባበቁ ነበር። . . . የአምላክ መምጫ ቀን የጌታ ቀን ተብሎ ተጠርቷል። ለአዲሱ ዘመን እንደ ምጥ የሆነና ሽብርና ጥፋት እንዲሁም ፍርድ የሚኖርበት ከባድ ጊዜ እንደሚሆን ያምኑ ነበር። አፖካሊፕሳዊ ጽሑፎቹ በሙሉ እነዚሁኑ ክንውኖች የሚዳስሱ ናቸው።”
አፖካሊፕስን መፍራት ምክንያታዊ ነውን?
የመጽሐፍ ቅዱሱ የራእይ መጽሐፍ ‘ሁሉን ስለሚችለው አምላክ ታላቅ የጦርነት ቀን’ ወይም አርማጌዶን የሚናገር ሲሆን በዚህ ጊዜ ክፉዎች እንደሚጠፉ ከዚያ በኋላም ሰይጣን ወደ ጥልቁ የሚጣልበትና ክርስቶስ በሰው ዘር ላይ የሚገዛበት የአንድ ሺህ ዓመት ጊዜ (አንዳንድ ጊዜ በእንግሊዝኛ ሚሊኒየም ይባላል) እንደሚጀምር ይገልጻል። (ራእይ 16:14, 16፤ 20:1-4) ካቶሊኩ “ቅዱስ” አውጉስቲን (354-430 እዘአ) የሺው ዓመት ግዛት በኢየሱስ ልደት እንደጀመረና የመጨረሻውም ፍርድ ተከትሎ እንደሚመጣ ስለተናገረ በመካከለኛው ዘመን አንዳንዶች እነዚህን ትንቢቶች በተሳሳተ መንገድ ተረድተዋቸው ነበር። አውጉስቲን ስለ ጊዜው እምብዛም አላሰበበትም ነበር። ይሁንና 1000 ዓመት እየተጠጋ ሲመጣ ፍርሃቱ ጨመረ። በመካከለኛው ዘመን የነበረው የአፖካሊፕስ ፍርሃት ምን ያህል ነበር በሚለው ጉዳይ ላይ ታሪክ ጸሐፊዎች ያላቸው ሐሳብ የተለያየ ነው። ይሁንና ፍርሃቱ ምንም ያህል ይሁን ምን መሠረተ ቢስ እንደነበር ግልጽ ሆኗል።
ዛሬም በተመሳሳይ ሃይማኖታዊ ወገኖችና ሌሎችም 2000 ወይም 2001 ዓመት በፍርሃት የሚያርድ አፖካሊፕስ የሚፈጸምባቸው ጊዜያት ይሆናሉ የሚል ፍርሃት አላቸው። ይሁን እንጂ ይህ ዓይነቱ ፍርሃት ምክንያታዊ ነውን? ደግሞስ በመጽሐፍ ቅዱሱ የራእይ ወይም አፖካሊፕስ መጽሐፍ ውስጥ የሰፈረው ነገር የሚያስፈራ ነው ወይስ ተስፋ የምናደርግበት? እባክህ የሚቀጥለውን ርዕስ ማንበብህን ቀጥል።
[በገጽ 4 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በመካከለኛው ዘመን የነበሩት ሰዎች አፖካሊፕስን መፍራታቸው ምክንያታዊ እንዳልነበር ታይቷል
[ምንጭ]
© Cliché Bibliothèque Nationale de France, Paris
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Maya/Sipa Press