አፖካሊፕስ—የሚያስፈራ ወይስ በተስፋ የሚጠበቅ?
“ዛሬ አፖካሊፕስ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መግለጫ ብቻ መሆኑ ቀርቶ በገሃድ ሊታይ የሚችል ነገር ሆኗል።”—ሃቪየር ፔረዝ ዴኩዌር የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ
በዓለም መድረክ ከፍተኛ ቦታ ያላቸው እኒህ ሰው “አፖካሊፕስ” የሚለውን ቃል የተጠቀሙበት መንገድ አብዛኛው ሰው ቃሉን እንዴት እንደሚረዳው እንዲሁም በፊልሞች፣ በመጻሕፍት ሽፋን፣ በመጽሔቶች ውስጥና በጋዜጣ ዘገቦች ላይ በምን መልኩ እንደሚቀርብ የሚያስገነዝብ ነው። የሚያስተላልፉት መልእክት ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ እልቂት ይመጣል የሚል ነው። ይሁን እንጂ “አፖካሊፕስ” የሚለው ቃል ትክክለኛ ትርጉም ምንድን ነው? ከሁሉ ይበልጥ ደግሞ አፖካሊፕስ ወይም ራእይ እየተባለ በሚጠራው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ የሚገኘው መልእክት ምንድን ነው?
“አፖካሊፕስ” የሚለው ቃል “ማራቆት” ወይም “መግለጥ” የሚል ትርጉም ካለው የግሪክኛ ቃል የተገኘ ነው። በመጽሐፍ ቅዱሱ የራእይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጠው ነገር ምንድን ነው? አንድም ነፍስ የማይተርፍበት እልቂት እንደሚመጣ የሚገልጽ የጥፋት ነጋሪት ነውን? ኧስቲቱ ደ ፍራንስ የተባለው ተቋም አባል የሆኑት ታሪክ ጸሐፊው ዣ ደሉሞ ስለ አፖካሊፕስ ምን እንደሚያስቡ ተጠይቀው ሲመልሱ “መጽናኛና ተስፋ የያዘ መጽሐፍ ነው። ሰዎች ስለ ጥፋት በሚናገረው ክፍል ላይ ብቻ በማተኮር መልእክቱን አጋንነው ተመልክተውታል” ብለዋል።
የጥንቷ ቤተ ክርስቲያንና አፖካሊፕስ
የጥንቶቹ “ክርስቲያኖች” አፖካሊፕስንና በዚያ ውስጥ የሚገኘውን ክርስቶስ ምድርን ስለሚያስተዳድርበት የሺህ ዓመት ጊዜ የሚናገረውን ተስፋ የሚመለከቱት እንዴት ነበር? እኒሁ ታሪክ ጸሐፊ እንዲህ ብለዋል:- “እንደ እኔ አስተሳሰብ በመጀመሪያዎቹ ጥቂት መቶ ዓመታት የነበሩት ክርስቲያኖች በጥቅሉ ሲታይ የሺህ ዓመቱን ግዛት አምነው ተቀብለው ነበር። . . . በመጀመሪያዎቹ መቶ ዓመታት ውስጥ ከነበሩትና በሺው ዓመት ግዛት ከሚያምኑት ክርስቲያኖች መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሱት በትንሿ እስያ የምትገኘው የሄራፖሊስ ጳጳስ የነበረው ፓፒያስ፣ . . . በፍልስጤም ምድር የተወለደውና በ165 ገደማ በሮም ሰማዕት ሆኖ የሞተው ቅዱስ ጀስቲን፣ የላዮንስ ጳጳስ የነበረውና በ202 የሞተው ቅዱስ ኢራንየስ፣ በ222 የሞተው ተርቱሊያን እንዲሁም ታላቁ የሥነ ጽሑፍ ሰው ላክታንሺስ ይገኙበታል።”
በ161 ወይም 165 እዘአ ላይ በጴርጋሞን ሰማዕት ሆኖ የሞተውን ፓፒያስን በሚመለከት ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክለፒዲያ እንዲህ ይላል:- “የሄራፖሊሱ ጳጳስና የቅዱስ ዮሐንስ ደቀ መዝሙር የነበረው ፓፒያስ ስለ ሺህ ዓመት ግዛት የሚናገረውን ትምህርት አጥብቆ የሚደግፍ የነበረ ይመስላል። ይህን መሠረተ ትምህርት የተቀበለው ከሐዋርያት ጋር ከነበሩ ሰዎች እንደሆነ የሚናገር ሲሆን ኢራንየስም ደቀ መዝሙሩን ዮሐንስን ያዩትና ከእርሱ የሰሙ ‘መንፈሳዊ አባቶች’ የሺህ ዓመት እምነትን ከሌሎቹ የጌታ ትምህርቶች ጋር ከእርሱ እንደተቀበሉ ተርኳል። እንደ ዩሴቢየስ አባባል ከሆነ . . . ፓፒያስ ከሙታን ትንሣኤ በኋላ እውን የሆነና ክብራማ የክርስቶስ ምድራዊ መንግሥት እንደሚጀምር በመጽሐፉ ውስጥ አስፍሯል።”
የአፖካሊፕስ ወይም የራእይ መጽሐፍ በጥንቶቹ አማኞች ላይ የነበረውን ተጽዕኖ በተመለከተ ከዚህ ምን እንረዳለን? የሚያስፈራቸው ነበር ወይስ ተስፋ የሚሰጣቸው? የሚያስገርመው ታሪክ ጸሐፊዎች የመጀመሪያዎቹን ክርስቲያኖች በእንግሊዝኛ ቺሊያስትስ ብለው የሚጠሯቸው ሲሆን ቃሉ ሂሊዬቲ (ሺህ ዓመት) ከሚለው የግሪክኛ ቃል የተገኘ ነው። አዎን፣ ብዙዎቹ በምድር ላይ ገነታዊ ሁኔታ በሚያመጣው የክርስቶስ ሺህ ዓመት ግዛት ላይ በነበራቸው እምነት ተለይተው ይታወቁ ነበር። የሺው ዓመት ተስፋ በግልጽ የተቀመጠበት ብቸኛው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል አፖካሊፕስ ወይም ራእይ ብቻ ነው። (20:1-7) ስለዚህ አፖካሊፕስ ለአማኞች ድንቅ ተስፋ የሚሰጥ እንጂ የሚያስፈራራቸው አልነበረም። በኦክስፎርድ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ፕሮፌሰር የሆኑት ሴሰል ካዱ፣ ዚ ኧርሊ ቸርች ኤንድ ዘ ዎርልድ በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “የቺሊያስቶች አመለካከት የኋላ ኋላ ተቀባይነት ቢነፈገውም ረዘም ላለ ጊዜ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በሰፊው ተቀባይነት አግኝቶ የቆየና አክብሮት ያተረፉ ጸሐፊዎች ሳይቀሩ ሲያስተምሩት የነበረ ነገር ነው።”
የአፖካሊፕስ ተስፋ ተቀባይነት ያጣበት ምክንያት
ከጥንቶቹ ክርስቲያኖች መካከል ብዙዎቹ (እንዲያውም አብዛኞቹ ማለት ይቻላል) ክርስቶስ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ስለሚያስተዳድርበት የሺህ ዓመት ጊዜ የነበራቸው እምነት ሊታበል የማይችል ታሪካዊ ሐቅ ሆኖ ሳለ ይህንን የመሰለው “የቺሊያስቶች አመለካከት የኋላ ኋላ ተቀባይነት ሊያጣ የቻለው” እንዴት ነው? ምሁሩ ሮበርት ማውንስ እንደጠቆሙት “ብዙ ቺሊያስቶች ራሳቸው በፈጠሩት ሐሳብ መቃዠት በመጀመራቸውና በሺው ዓመት ግዛት ውስጥ ስለሚኖረው ቁሳዊና ስሜታዊ ነገር ወደሌላኛው ጽንፍ ሄደው መፈላሰፍ መጀመራቸው የሚያሳዝን ነበር።” ከዚህ የተነሣ መሠረት ያለው ነቀፋ መሠንዘር ጀመረ። ይሁን እንጂ እውነተኛውን ተስፋ ገሸሽ ማድረግ ሳያስፈልግ የእነዚህን ጽንፈኞች አስተሳሰብ ማረም ይቻል ነበር።
በእርግጥም ደግሞ ተቃዋሚዎች የሺውን ዓመት ተስፋ ለማፈን የተጠቀሙበት ዘዴ የሚያስገርም ነበር። ዲክሲዮኔር ደ ቴኦሎዢ ካቶሊክ የሮማውን የቤተ ክርስቲያን ሰው ካየስን (ከሁለተኛው መቶ ዘመን መጨረሻ እስከ ሦስተኛው መቶ ዘመን መጀመሪያ ድረስ የኖረ) በተመለከተ “የሺህ ዓመቱን ተስፋ ለማዳፈን ሲል ያላንዳች ማቅማማት የአፖካሊፕስን [የራእይን] እንዲሁም የቅዱስ ዮሐንስን ወንጌል ትክክለኛነት ሙሉ በሙሉ አልቀበልም ብሏል።” ይኸው ዲክሲዮኔር አክሎ ሲገልጽ በሦስተኛው መቶ ዘመን የእስክንድርያ ጳጳስ የነበረው ዲዮኒሲየስ “በቅዱስ ዮሐንስ አፖካሊፕስ ላይ ተመሥርተው ይህንን እምነት አጥብቀው የሚከተሉትን ሰዎች ለመቃወም ሲል” የሺህ ዓመቱን ግዛት ተስፋ የሚነቅፍ ጽሑፍ በማዘጋጀት “የአፖካሊፕስን ትክክለኝነት ሽምጥጥ አድርጎ ክዷል።” የሺህ ዓመቱ ግዛት የሚያመጣቸውን በረከቶች በተመለከተ የተሰጠው ተስፋ ይህን ያህል ጠንካራ ተቃውሞ የገጠመው መሆኑ በወቅቱ የነበሩት ሃይማኖታዊ ምሁራን ምን ዓይነት መሠሪ ተጽእኖ እንደነበራቸው የሚያመላክት ነው።
ፕሮፌሰር ኖርማን ኮህን ዘ ፐርሱት ኦቭ ዘ ሚሊኒየም በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ ብለዋል:- “የሺህ ዓመት ግዛትን ተስፋ ማጣጣል የተጀመረው በሦስተኛው መቶ ዘመን ሲሆን በዚህ ጊዜ በጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ከነበሩት የሃይማኖት ምሁራን ሁሉ የላቀ ተሰሚነት ሳይኖረው እንዳልቀረ የሚገመተው ኦሪጀን የአምላክ መንግሥት በአማኞች ነፍስ ውስጥ ያለ ነገር እንጂ እውን አይደለም ብሎ ያስተምር ነበር።” ኦሪጀን ከመጽሐፍ ቅዱስ ይልቅ በግሪክ ፍልስፍና ላይ በመደገፍ በመሲሐዊው መንግሥት አማካኝነት ስለሚመጣ ምድራዊ በረከት የሚገልጸውን አስደናቂ ተስፋ ‘በአማኞች ልብ ውስጥ የሚከናወን’ ለመረዳት የሚያስቸግር ነገር እንደሆነ አድርጎ በማቅረብ በርዞታል። ተክቶ አቅርቦታል። ካቶሊካዊው ጸሐፊ ሌዮ ገሪ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “በጉልህ ይታይ የነበረው የግሪካውያን ፍልስፍና ያሳደረው ተጽዕኖ . . . ቀስ በቀስ የቺሊያስቶች ሐሳብ እንዲዳከም ምክንያት ሆኗል።”
“ቤተ ክርስቲያን የምትናገረው የተስፋ መልእክት አጥታለች”
በዘመኑ ከነበረው የይስሙላ ክርስትና ጋር የግሪካውያንን ፍልስፍና በመቀላቀል ረገድ ትልቅ ሚና የተጫወተው የቤተ ክርስቲያን አባት አውጉስቲን እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም። መጀመሪያ ላይ ስለ ሺህ ዓመቱ ግዛት የሚገልጸውን ትምህርት አጥብቆ ይደግፍ የነበረ ቢሆንም የኋላ ኋላ ክርስቶስ ወደፊት በምድር ላይ ለአንድ ሺህ ዓመት ይገዛል የሚል ምንም ዓይነት ሐሳብ አልቀበልም ብሏል። ራእይ ምዕራፍ 20ንም ሌላ መንፈሳዊ ትርጉም እንዳለው በማድረግ አጣምሞ አቅርቦታል።
ዘ ካቶሊክ ኢንሳይክለፒዲያ እንዲህ ይላል:- “በመጨረሻ አውጉስቲን የሺህ ዓመት ግዛት የሚባል ነገር የለም የሚል ጽኑ እምነት ይዞ ነበር። . . . ይህ ምዕራፍ የሚናገርለት ፊተኛ ትንሣኤ የሚገልጸው በጥምቀት አማካኝነት ዳግም በመንፈሳዊ ስለ መወለድ ነው፤ የዘላለም ሕይወት ማለትም ከሰው ልጅ የስድስት ሺህ ዓመት ታሪክ በኋላ የሚኖረው የአንድ ሺህ ዓመት ሰንበት ነው ይለናል።” ዘ ኒው ኢንሳይክለፒዲያ ብሪታኒካ እንዲህ ይላል:- “አውጉስቲን ሌላ መንፈሳዊ ትርጉም የሰጠው የሺህ ዓመት እምነት የቤተ ክርስቲያን ኦፊሴላዊ ትምህርት ሆነ። . . . በሉተራን፣ በካልቪኒስቶችና በአንግሊካን ወጎች ላይ የተሃድሶ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ፕሮቴስታንቶች . . . የአውጉስቲንን አመለካከት በጥብቅ መከተላቸውን ቀጥለዋል።” በዚህ መልኩ የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት አባል የሆኑ ሰዎች የክርስቶስን የሺህ ዓመት ግዛት ተስፋ ተነፍገዋል።
ከዚህም በላይ እንደ የስዊስ ተወላጅ የሆኑት የሃይማኖት ምሁር እንደ ፍሬዴሪክ ደ ሩዥሞ አባባል ከሆነ “[አውጉስቲን] መጀመሪያ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ላይ የነበረውን እምነት መካዱ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያስከተለው ኪሳራ ይህ ነው ተብሎ ሊሰላ አይችልም። የነበረውን ከፍተኛ ተሰሚነት ተጠቅሞ [ቤተ ክርስቲያን] ምድራዊ ግብዋን እንድትስት ያደረጋትን ስህተት ፈጽሟል።” ጀርመናዊው የሃይማኖት ምሁር አዶልፍ ሆርኖክ የሺው ዓመት እምነት ገሸሽ መደረጉ “ጥንታዊውን እምነትና ጥንታዊውን ተስፋ” ወደ ጎን ትቶ ‘ሊረዱት በማይችሉት እምነት’ በመተካት ሰዎችን “ከሚዋጥላቸው እምነታቸው” አለያይቷቸዋል በሚለው ሐሳብ ይስማማሉ። ዛሬ በብዙ አገሮች ውስጥ ኦና የቀሩት አብያተ ክርስቲያናት ሰዎች ሊረዱት የሚችሉት እምነትና ተስፋ እንደሚያስፈልጋቸው የሚያሳዩ በቂ ማስረጃዎች ናቸው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር የሆኑት ጆርጅ ቢስሊ መሪ ሃይላይትስ ኦቭ ዘ ቡክ ኦቭ ሪቨሌሽን በተባለው መጽሐፋቸው ውስጥ እንዲህ በማለት አስፍረዋል:- “በአንድ ወገን የአውጉስቲን ከፍተኛ ተጽዕኖ በሌላ ወገን ደግሞ በሺህ ዓመት ግዛቱ ላይ እምነት የጣሉ ቡድኖች ተጽእኖ ቢኖርም ካቶሊኮችና ፕሮቴስታንቶች ትምህርቱን አንቀበልም ብለው ቀጥለዋል። በዚህ ዓለም ላለው የሰው ልጅ ሌላ ምን ተስፋ እንዳላቸው ሲጠየቁ በይፋ የሚሰጡት መልስ ምንም ዓይነት ተስፋ የለም የሚል ነው። ክርስቶስ ሲመጣ መላው ዓለም ጠፍቶ ዘላለማዊ ለሆነ ሰማያዊ ሕይወትና ለሲኦል ቦታውን ይለቅቃል። ከዚህ በኋላ ታሪክ የተረሳ ነገር ይሆናል። . . . ቤተ ክርስቲያን የምትናገረው የተስፋ መልእክት አጥታለች።”
ድንቅ የሆነው የአፖካሊፕስ ተስፋ ዛሬም ሕያው ነው!
የይሖዋ ምሥክሮች ግን ከክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ጋር ዝምድና ያላቸው ግሩም ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ ያምናሉ። “2000 እና የአፖካሊፕስ ፍርሃት” በሚል ርዕስ በተካሄደ የፈረንሳይ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ላይ ፈረንሳዊው ታሪክ ጸሐፊ ዣ ደሉሞ እንዲህ ብለዋል:- “የሺህ ዓመት ግዛትን እምነት በትክክል የሚከተሉት የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው። ምክንያቱም እነርሱ በቅርብ ጊዜ ውስጥ . . . ከአንድ መጠነ ሰፊ ጥፋት አልፈን ደስታ ወደ ሰፈነበት የ1,000 ዓመት ጊዜ እንገባለን ይላሉ።”
ሐዋርያው ዮሐንስም በራእይ ያየውና በአፖካሊፕስ ወይም በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የጠቀሰው ነገር ይኸው ነው። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “አዲስ ሰማይንና አዲስ ምድርንም አየሁ፣ . . . ታላቅም ድምፅ ከሰማይ:- እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል፤ እንባዎችንም ሁሉ ከዓይኖቻቸው ያብሳል፣ ሞትም ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ ኀዘንም ቢሆን ወይም ጩኸት ወይም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይሆንም፣ የቀደመው ሥርዓት አልፎአልና ብሎ ሲናገር ሰማሁ።”—ራእይ 21:1, 3, 4
የይሖዋ ምሥክሮች የተቻለውን ያህል ብዙ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ይህንን ተስፋ መጨበጥ ይችሉ ዘንድ ዓለም አቀፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ዘመቻ በማካሄድ ላይ ናቸው። አንተም ስለዚህ ተስፋ ተጨማሪ ነገር መማር ትችል ዘንድ ሊረዱህ ፈቃደኞች ናቸው።
[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ፓፒያስ ስለ ክርስቶስ ሺህ ዓመት የሚገልጸውን መሠረተ ትምህርት ከሐዋርያት ጋር ከነበሩ ሰዎች በቀጥታ እንደተቀበለ ገልጿል
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ተርቱሊያን በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ያምን ነበር
[ምንጭ]
© Cliché Bibliothèque Nationale de France, Paris
[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“[አውጉስቲን] መጀመሪያ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ላይ የነበረውን እምነት መካዱ በቤተ ክርስቲያን ላይ ያስከተለው ኪሳራ ይህ ነው ተብሎ ሊሰላ አይችልም”
[በገጽ 8 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምድር ገነት እንደምትሆን የሚናገረው የአፖካሊፕስ ተስፋ በጉጉት የምንጠባበቀው ነገር ነው