አዲስ የአስተዳደር አካል አባላት
ቅዳሜ ጥቅምት 2, 1999 በፔንሲልቫኒያው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ዓመታዊ ስብሰባ መደምደሚያ ላይ አንድ ያልተጠበቀ ማስታወቂያ ተነገረ። በዚያ የነበሩትና በስልክ መስመር የተገናኙት 10, 594 ተሰብሳቢዎች በሙሉ አራት አዲስ የይሖዋ ምሥክሮች የአስተዳደር አካል አባላት መጨመራቸውን ሲሰሙ በጣም ተደስተዋል። አዲሶቹ አባላት በሙሉ የተቀቡ ክርስቲያኖች ሲሆኑ እነርሱም ሳሙኤል ኤፍ ኸርድ፣ ኤም ስቲቨን ሌት፣ ጋይ ኤች ፒርስ እንዲሁም ዴቨድ ኤች ስፕሌን ናቸው።
• ሳሙኤል ኸርድ የአቅኚነት አገልግሎት የጀመረው በ1958 ሲሆን ከ1965 እስከ 1997 ድረስ የወረዳና የአውራጃ የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። ከዚያ በኋላ ባለው ጊዜ ደግሞ እርሱና ባለቤቱ ግሎሪያ በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነው ያገለገሉ ሲሆን ወንድም ኸርድ በአገልግሎት ክፍል ውስጥ ሲሠራ ቆይቷል። ከዚህም በላይ የአገልግሎት ኮሚቴው ረዳት ሆኖም ሠርቷል።
• ስቲቨን ሌት አቅኚ ሆኖ ማገልገል የጀመረው በታኅሣስ 1966 ወር ሲሆን ከ1967 እስከ 1971 ድረስ ዩናይትድ ስቴትስ በሚገኘው ቤቴል አገልግሏል። በጥቅምት 1971 ባለቤቱን ሱዛንን ካገባ በኋላ የልዩ አቅኚነትን አገልግሎት ጀመረ። ከ1979 እስከ 1998 የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ አገልግሏል። ከሚያዝያ 1998 ጀምሮ እርሱና ሱዛን ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው የቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነዋል። በዚያም በአገልግሎት ክፍል ውስጥ ሲሠራና የትምህርት ኮሚቴን ሲረዳ ቆይቷል።
• ጋይ ፒርስ የራሱ ቤተሰብ የነበረው ሲሆን ከሚስቱ ጋር አቅኚነት የጀመረው በሚያዝያ 1982 ነው። ከ1986 እስከ 1997 ባለው ጊዜ የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ያገለገለ ሲሆን ከዚያ በኋላ እርሱና ባለቤቱ ፔኒ ብሩክሊን የሚገኘው ቤቴል ቤተሰብ አባል ሆነዋል። ወንድም ፒርስ የፐርሶኔል ኮሚቴውን ሲረዳ ቆይቷል።
• ዴቪድ ስፕሌን አቅኚነት የጀመረው በመስከረም 1963 ነው። የ42ኛው ክፍል የጊልያድ ተመራቂ ሲሆን አፍሪካ ውስጥ በምትገኘው በሴኔጋል ሚስዮናዊ ሆኖ አገልግሏል። በኋላም በካናዳ ለ19 ዓመታት የወረዳ የበላይ ተመልካች ሆኖ ሠርቷል። እርሱና ባለቤቱ ሊንዳ ከ1990 አንስቶ ዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘው ቤቴል ቤተሰብ አባል የሆኑ ሲሆን ወንድም ስፕሌን በአገልግሎትና በጽሑፍ ዝግጅት ክፍል ውስጥ አገልግሏል። ከ1998 ጀምሮም የጽሑፍ ዝግጅት ኮሚቴውን ሲረዳ ቆይቷል።
ከአራቱ አዲስ አባላት በተጨማሪ በአሁኑ ጊዜ የአስተዳደር አካሉ ወንድም ሲ ደብልዩ ባርበር፣ ጄ ኢ ባር፣ ኤም ጂ ሄንሼል፣ ጂ ሎሽ፣ ቲ ጃራዝ፣ ኬ ኤፍ ክላይን፣ ኤ ዲ ሽሮደር፣ ኤል ኤ ስዊንግል እንዲሁም ዲ ሲድሊክን ያቀፈ ነው። በቁጥር የጨመረው የአስተዳደር አካል በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን ሥራ በበላይነት መከታተሉንና የሰዎችን መንፈሳዊ ፍላጎት ማሟላቱን በቀጠለ መጠን ይሖዋ የአስተዳደር አካሉን መባረኩንና ኃይል መስጠቱን ይቀጥል ዘንድ የሁላችንም ጸሎት ነው።