የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w00 9/15 ገጽ 10-15
  • ‘ጊዜው ገና አልደረሰም’

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ‘ጊዜው ገና አልደረሰም’
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቆርጦ ነበር
  • ለይሖዋ ቤት ያሳየው ቅንዓት
  • በገሊላ የተካሄደ ሰፊ የማስተማር ዘመቻ
  • በይሁዳና በፍርግያ በድፍረት መመሥከር
  • የሰውን ሁሉ ትኩረት የሳበ ተአምር
  • ‘ሰዓቱ ደረሰ!’
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • ኢየሱስ ቶሎ ያልሄደው ለምን ነበር?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2010
  • ወደ ይሁዳ ሲጓዝ በፔሪያ አስተማረ
    ኢየሱስ—መንገድ፣ እውነት፣ ሕይወት
  • የምሕረት ተልዕኮ ለመፈጸም ወደ ይሁዳ መጓዝ
    እስከ ዛሬ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቅ ሰው
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
w00 9/15 ገጽ 10-15

‘ጊዜው ገና አልደረሰም’

“ጊዜው ገና ስላልደረሰ ማንም እጁን አልጫነበትም።” ​—⁠ዮሐንስ 7:​30

1. ኢየሱስ ማንኛውንም ነገር ያከናውን የነበረው ከምን ሁለት ነገሮች አኳያ ነበር?

ኢየሱስ ክርስቶስ “የሰው ልጅ ሊያገለግል ነፍሱንም ለብዙዎች ቤዛ ሊሰጥ እንጂ እንዲያገለግሉት አልመጣም” ሲል ለሐዋርያቱ ነግሯቸዋል። (ማቴዎስ 20:​28) ለሮማዊው ገዥ ለጴንጤናዊው ጲላጦስ “እኔ ለእውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ” ብሎታል። (ዮሐንስ 18:​37) ኢየሱስ ለምን እንደሚሞትና ከመሞቱ በፊት ምን ሥራ ማከናወን እንዳለበት በሚገባ ያውቃል። በተጨማሪም ተልዕኮውን ለማጠናቀቅ ምን ያህል ጊዜ እንዳለው ያውቅ ነበር። መሲሕ ሆኖ በምድር ላይ የሚያከናውነው አገልግሎት ለሦስት ዓመት ተኩል ብቻ የሚቆይ ነው። አገልግሎቱ የጀመረው በትንቢት በተነገረው 70ኛው ምሳሌያዊ ሳምንት መጀመሪያ ላይ በዮርዳኖስ ወንዝ በውኃ በተጠመቀበት ጊዜ (በ29 እዘአ) ሲሆን ያበቃው ደግሞ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ (በ33 እዘአ) በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ሲሞት ነው። (ዳንኤል 9:​24–27፤ ማቴዎስ 3:​16, 17፤ 20:​17-19) በመሆኑም ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ማንኛውንም ነገር ያከናውን የነበረው ከሁለት ነገሮች አኳያ ማለትም ከመጣበት ዓላማና ከጊዜ አንፃር ነበር።

2. ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌል ዘገባዎች ላይ የተገለጸው በምን መንገድ ነው? ተልዕኮውን ተገንዝቦ እንደነበር ያሳየውስ እንዴት ነው?

2 የወንጌል ዘገባዎች ኢየሱስ ክርስቶስ በመላው የፍልስጤም ምድር እየተጓዘ የአምላክን መንግሥት ምስራች ያወጀና በርካታ ተአምራትን ያከናወነ የተግባር ሰው መሆኑን ይገልጻሉ። ኢየሱስ አገልግሎቱን በከፍተኛ ቅንዓት ማከናወን በጀመረበት ወቅት ‘ጊዜው ገና አልደረሰም’ ተብሎ ተነግሮለታል። ኢየሱስ ራሱ ‘ጊዜዬ ገና አልተፈጸመም’ ሲል ተናግሯል። የአገልግሎቱ መደምደሚያ ሲቃረብ ደግሞ “ሰዓቱ ደርሶአል” የሚል መግለጫ ተጠቅሟል። (ዮሐንስ 7:⁠8, 30፤ 12:​23) ኢየሱስ ሰዓቱን በተመለከተ ወይም መሥዋዕታዊ ሞቱን ጨምሮ የተመደበለትን ሥራ ስለሚያከናውንበት ጊዜ ያለው እውቀት በንግግሩና በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ መሆን አለበት። ይህን ማወቃችን ባሕርይውንና አስተሳሰቡን በጥልቅ በመረዳት ‘ፍለጋውን በቅርብ እንድንከተል’ ያስችለናል።​—⁠1 ጴጥሮስ 2:​21

የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም ቆርጦ ነበር

3, 4. (ሀ) በቃና በተካሄደው የሠርግ ድግስ ላይ የተከናወነው ነገር ምንድን ነው? (ለ) የአምላክ ልጅ የወይን ጠጅ እጥረቱን በተመለከተ አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት ማርያም ያቀረበችለትን ሐሳብ የተቃወመው ለምንድን ነው? እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን?

3 ጊዜው 29 እዘአ ነው። ኢየሱስ የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርቱን ከመረጠ ገና ጥቂት ቀናት ማለፉ ነው። በገሊላ አውራጃ በምትገኘው መንደር በቃና በሚካሄድ የሠርግ ድግስ ላይ ለመገኘት ሁሉም ወደዚያ መጥተዋል። የኢየሱስ እናት ማርያምም በዚያ ተገኝታለች። ለሠርጉ የተዘጋጀው ወይን ጠጅ በማለቁ ማርያም አንድ ነገር ማድረግ እንዳለበት በማሳሰብ ልጅዋን “የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም” ብላ ነገረችው። ይሁን እንጂ ኢየሱስ “አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም” ሲል መለሰላት።​—⁠ዮሐንስ 1:​35-51፤ 2:​1-4

4 ኢየሱስ “አንቺ ሴት፣ ከአንቺ ጋር ምን አለኝ?” ሲል የሰጠው መልስ ለቀረበው ማሳሰቢያ ወይም ሐሳብ ተቃውሞ ለመግለጽ የሚያገለግል በድሮ ዘመን የሚሠራበት የአጠያየቅ ዘይቤ ነው። ኢየሱስ ማርያም ያቀረበችውን ሐሳብ የተቃወመው ለምንድን ነው? አሁን 30 ዓመቱ ነው። ከጥቂት ሳምንታት በፊት ተጠምቆ በመንፈስ ቅዱስ ከተቀባ በኋላ አጥማቂው ዮሐንስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” መሆኑን አሳውቋል። (ዮሐንስ 1:​29-34፤ ሉቃስ 3:​21-23) ከዚህ በኋላ መመሪያ ማግኘት ያለበት እሱን ከላከው የመጨረሻው ባለሥልጣን ነው። (1 ቆሮንቶስ 11:​3) የቅርብ የቤተሰቡን አባላት ጨምሮ ማንም ሰው ኢየሱስ ሊያከናውነው ወደ ምድር በመጣበት ሥራ ላይ ጣልቃ እንዲገባ ሊፈቀድለት አይችልም። ኢየሱስ ለማርያም የሰጣት መልስ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ምን ያህል እንደቆረጠ የሚገልጽ ነበር! እኛም በተመሳሳይ በአምላክ ዘንድ ያለብንን ‘ሁለንተናዊ ግዴታ’ ለመፈጸም ቆርጠን እንነሳ።​—⁠መክብብ 12:​13

5. ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ያከናወነው ተአምር ምንድን ነው? ይህስ ተአምር በሌሎች ላይ ምን ተጽእኖ አሳድሯል?

5 ማርያም የልጅዋ አነጋገር ስለገባት ወዲያው ሄዳ ለአገልጋዮቹ “የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ” የሚል መመሪያ ሰጠቻቸው። ኢየሱስም ለችግሩ መፍትሄ አስገኘ። አገልጋዮቹ ጋኖቹን ውኃ እንዲሞሉ ካደረገ በኋላ ውኃውን በጣም ጥሩ ወደሆነ ወይን ጠጅ ቀየረው። ይህም ኢየሱስ ተአምር ለመሥራት ኃይል እንዳለው ማለትም የአምላክ መንፈስ በእሱ ላይ እንዳረፈ የሚያሳይ ምልክት ሆኖ አገልግሏል። አዳዲሶቹ ደቀ መዛሙርት ይህን ተአምር ሲመለከቱ እምነታቸው ተጠናከረ።​—⁠ዮሐንስ 2:​5-11

ለይሖዋ ቤት ያሳየው ቅንዓት

6. ኢየሱስ በኢየሩሳሌም፣ ቤተ መቅደሱ ውስጥ በተመለከተው ነገር የተናደደው ለምንድን ነው? ምን እርምጃስ ወሰደ?

6 ብዙም ሳይቆይ በ30 እዘአ የፀደይ ወቅት ኢየሱስና ተከታዮቹ የማለፍን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም እየሄዱ ነው። እዚያ ሲደርሱ ደቀ መዛሙርቱ መሪያቸው ምናልባት ከዚህ ቀደም አይተውት በማያውቁት ሁኔታ እርምጃ ሲወስድ ተመለከቱ። ስግብግብ አይሁዳውያን ነጋዴዎች እዚያው ቤተ መቅደሱ ውስጥ ለመሥዋዕት የሚቀርቡ እንስሳትና ርግቦች ይሸጣሉ። እንዲሁም ታማኝ አይሁዳውያን አምላኪዎችን በጣም ውድ ዋጋ ያስከፍላሉ። ኢየሱስ በጣም ከመናደዱ የተነሳ እርምጃ መውሰድ ጀመረ። የገመድ ጅራፍ አበጅቶ ሻጮቹን አባረራቸው። የገንዘብ ለዋጮቹን ሳንቲም አፍስሶ ጠረጴዛዎቻቸውን ገለበጠባቸው። ርግብ ሻጮችን “ይህን ከዚህ ውሰዱ” ሲል አዘዛቸው። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲህ በኃይል እርምጃ ሲወስድ ሲመለከቱት “የቤትህ ቅናት ይበላኛል” ተብሎ ስለ አምላክ ልጅ የተነገረውን ትንቢት አስታወሱ። (ዮሐንስ 2:​13–17፤ መዝሙር 69:​9) እኛም ዓለማዊ ዝንባሌዎች አምልኮታችንን እንዳይበክሉ በቅንዓት መከላከል አለብን።

7. (ሀ) ኒቆዲሞስ ወደ መሲሑ እንዲሄድ ያነሳሳው ምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት ከሰጠው ምሥክርነት ምን እንማራለን?

7 ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ሳለ አስደናቂ ምልክቶች በመፈጸሙ ብዙ ሰዎች አመኑበት። ሌላው ቀርቶ የሳንሄድሪን ማለትም የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ሸንጎ አባል የሆነው ኒቆዲሞስ ለኢየሱስ ከነበረው አድናቆት የተነሳ ተጨማሪ ትምህርት ለማግኘት በማታ ወደ እሱ ሄዷል። ከዚያም ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ እየሰበኩና ደቀ መዛሙርት እያደረጉ ለስምንት ወር ያህል ‘በይሁዳ አገር’ ተቀመጡ። ይሁን እንጂ አጥማቂው ዮሐንስ ከታሰረ በኋላ ይሁዳን ለቅቀው ወደ ገሊላ ሄዱ። በሰማርያ አውራጃ ሲያልፉ ኢየሱስ በተከፈተለት አጋጣሚ ተጠቅሞ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት የተሟላ ምሥክርነት ሰጠ። ይህም ብዙ ሳምራውያን አማኞች እንዲሆኑ መንገድ ከፍቷል። እኛም ስለ መንግሥቱ ለመናገር የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ለመጠቀም ንቁ እንሁን።​—⁠ዮሐንስ 2:​23፤ 3:​1-22፤ 4:​1-42፤ ማርቆስ 1:​14

በገሊላ የተካሄደ ሰፊ የማስተማር ዘመቻ

8. ኢየሱስ በገሊላ ምን ሥራ ጀመረ?

8 ኢየሱስ የሚሞትበት ‘ሰዓት’ ከመድረሱ በፊት ሰማያዊ አባቱ በሰጠው አገልግሎት ብዙ የሚያከናውነው ነገር አለ። ኢየሱስ በይሁዳም ሆነ በኢየሩሳሌም ካከናወነው እጅግ የላቀ አገልግሎት በገሊላ ማከናወን ጀመረ። “በምኵራቦቻቸው እያስተማረ የመንግሥትንም ወንጌል እየሰበከ በሕዝብም ያለውን ደዌና ሕማም ሁሉ እየፈወሰ በገሊላ ሁሉ” ዞረ። (ማቴዎስ 4:​23) “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ” የሚለው አሳሳቢ መልእክት በመላው የገሊላ አውራጃ ተዳረሰ። (ማቴዎስ 4:​17) ከጥቂት ወራት በኋላ የአጥማቂው ዮሐንስ ሁለት ደቀ መዛሙርት ስለ ኢየሱስ በቀጥታ ከራሱ ለመስማት በመጡ ጊዜ “ሄዳችሁ ያያችሁትን የሰማችሁትንም ለዮሐንስ አውሩለት፤ ዕውሮች ያያሉ፣ አንካሶችም ይሄዳሉ፣ ለምጻሞችም ይነጻሉ፣ ደንቆሮዎችም ይሰማሉ፣ ሙታንም ይነሣሉ፣ ለድሆችም ወንጌል ይሰበካል፤ በእኔም የማይሰናከለው ሁሉ ብፁዕ ነው” ሲል ነገራቸው።​—⁠ሉቃስ 7:​22, 23

9. በርካታ ሰዎች ወደ ክርስቶስ ኢየሱስ የጎረፉት ለምንድን ነው? ከዚህስ ምን ትምህርት ማግኘት እንችላለን?

9 ‘በዙሪያው ባለችው አገር ሁሉ ስለ ኢየሱስ ዝና በመውጣቱ’ ከገሊላ፣ ከዲካፖሊስ፣ ከኢየሩሳሌም፣ ከይሁዳና ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ብዙ ሰዎች ወደ እሱ ጎረፉ። (ሉቃስ 4:​14, 15፤ ማቴዎስ 4:​24, 25) ወደ እሱ የመጡት ተአምራዊ ፈውስ በማከናወኑ ምክንያት ብቻ ሳይሆን አስደናቂ በሆኑት ትምህርቶቹም ጭምር ነው። መልእክቱ ማራኪና አበረታች ነበር። (ማቴዎስ 5:​1–7:​27) የኢየሱስ ቃላት ጸጋ የተሞሉና አስደሳች ናቸው። (ሉቃስ 4:​22) ከቅዱሳን ጽሑፎች እየጠቀሰ የሚናገረው እንደ ባለሥልጣን ስለነበር ሕዝቡ “በትምህርቱ ተገረሙ።” (ማቴዎስ 7:​28, 29፤ ሉቃስ 4:​32) እንዲህ በመሰለው ሰው የማይሳብ ማን አለ? እኛም ቅን ልብ ያላቸው ግለሰቦች ወደ እውነት ተስበው እንዲመጡ የማስተማር ችሎታችንን እናዳብር።

10. የናዝሬት ከተማ ሰዎች ኢየሱስን ለመግደል የሞከሩት ለምንድን ነው? ሳይሳካላቸው የቀረውስ ለምንድን ነው?

10 ሆኖም ኢየሱስን ያዳመጡ ሰዎች በሙሉ መልእክቱን ተቀብለዋል ማለት አይደለም። በአገልግሎቱ መጀመሪያ ላይ እንኳ ባደገበት ከተማ በናዝሬት በሚገኝ ምኩራብ ሲያስተምር ሊገድሉት ሞክረዋል። ምንም እንኳ የከተማው ነዋሪዎች ‘በጸጋው ቃል’ ቢደነቁም ፍላጎታቸው ተአምር ማየት ነበር። ሆኖም ኢየሱስ በዚያ ብዙ ተአምራትን ከመፈጸም ይልቅ ሰዎቹ ራስ ወዳድና እምነት የለሽ መሆናቸውን አጋለጠ። በምኩራብ የነበሩት ሰዎች በቁጣ ተሞልተው ኢየሱስን ይዘው ወደ ተራራ አፋፍ በመውሰድ በአፍጢሙ ሊወረውሩት ፈለጉ። ሆኖም ከእጃቸው አምልጦ ምንም ጉዳት ሳያገኘው ሄደ። የሚሞትበት ‘ሰዓት’ ገና አልደረሰም ነበር።​—⁠ሉቃስ 4:​16-30

11. (ሀ) አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ኢየሱስን ለመስማት የመጡት ለምንድን ነው? (ለ) ኢየሱስ የሰንበትን ሕግ ጥሰሃል ተብሎ የተከሰሰው ለምንድን ነው?

11 ጻፎች፣ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያንና ሌሎች የሃይማኖት መሪዎችም አብዛኛውን ጊዜ ኢየሱስ በሚሰብክበት ቦታ ይገኙ ነበር። አብዛኞቹ በዚያ የሚገኙት ለማዳመጥና ለመማር ሳይሆን በእሱ ላይ ስህተት ፈላልገው ለማጥመድ ነው። (ማቴዎስ 12:​38፤ 16:​1፤ ሉቃስ 5:​17፤ 6:​1, 2) ለምሳሌ ያህል ኢየሱስ በ31 እዘአ የማለፍን በዓል ለማክበር በኢየሩሳሌም በነበረበት ወቅት ለ38 ዓመታት ተምሞ የነበረን ሰው ፈወሰ። የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሰንበትን ጥሰሃል ብለው ወነጀሉት። እሱም “አባቴ እስከ ዛሬ ይሠራል እኔም ደግሞ እሠራለሁ” ሲል መለሰላቸው። በዚህ ጊዜ አይሁዳውያኑ ራሱን የአምላክ ልጅ በማድረግ አባቴ ብሎ በመጥራቱ አምላክን ሰድቧል ብለው ከሰሱት። ኢየሱስን ለመግደል መንገድ ይፈልጋሉ፤ ሆኖም እሱና ደቀ መዛሙርቱ ኢየሩሳሌምን ለቅቀው ወደ ገሊላ ሄዱ። እኛም በተመሳሳይ ጉልበታችንን በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዝሙር በማድረጉ ሥራ ላይ ስናውል ከተቃዋሚዎች ጋር አላስፈላጊ ግጭት ከመፍጠር መራቃችን ጥበብ ነው።​—⁠ዮሐንስ 5:​1-18፤ 6:​1

12. ኢየሱስ የገሊላን ክልል በሰፊው የሸፈነው እንዴት ነው?

12 በቀጣዩ አንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም የሄደው አይሁዳውያን በሚያከብሯቸው በሦስቱ ዓመታዊ በዓሎች ላይ ለመገኘት ብቻ ሲሆን በአብዛኛው አገልግሎቱን ያከናወነው በገሊላ ነበር። በገሊላ በድምሩ ሦስት የስብከት ዙሮች አካሂዷል:- የመጀመሪያው ከ4 አዳዲስ ደቀ መዛሙርቱ ጋር፣ ሁለተኛው ከ12 ሐዋርያቱ ጋር እንዲሁም ሥልጠና ያገኙ ሐዋርያቱን በመላክ ረዘም ላለ ጊዜ የሰበከበትም ወቅት አለ። ገሊላ ውስጥ እውነት ምንኛ በሰፊው ተሰብኳል!​—⁠ማቴዎስ 4:​18-25፤ ሉቃስ 8:​1-3፤ 9:​1-6

በይሁዳና በፍርግያ በድፍረት መመሥከር

13, 14. (ሀ) አይሁዳውያን ኢየሱስን ለመያዝ የሞከሩት በምን አጋጣሚ ነው? (ለ) ሎሌዎቹ ኢየሱስን ሳይዙት የቀሩት ለምንድን ነው?

13 ጊዜው 32 እዘአ የበልግ ወቅት ሲሆን የኢየሱስ ‘ሰዓት’ ገና አልደረሰም። የዳስ በዓል ተቃርቧል። በዚህ ጊዜ የኢየሱስ ግማሽ ወንድሞች “ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ” ብለው ገፋፉት። ኢየሱስ በዓሉን ለማክበር በኢየሩሳሌም ተሰብስበው ለነበሩት ሰዎች ሁሉ ተአምር የመሥራት ኃይሉን እንዲያሳይ ፈልገዋል። ይሁን እንጂ ኢየሱስ አደጋ ሊፈጠር እንደሚችል ተገንዝቧል። ስለዚህ ወንድሞቹን “እኔስ ጊዜዬ ገና ስላልተፈጸመ ወደዚህ በዓል ገና አልወጣም” አላቸው።​—⁠ዮሐንስ 7:​1-8

14 ኢየሱስ ለተወሰነ ጊዜ በገሊላ ከቆየ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም “በግልጥ ሳይሆን ተሰውሮ” ሄደ። በእርግጥም አይሁዳውያኑ “እርሱ ወዴት ነው?” ብለው በመጠየቅ ኢየሱስን በበዓሉ ላይ ለማግኘት ፈልገዋል። ኢየሱስ በበዓሉ ሥርዓት አጋማሽ ላይ ወደ ቤተ መቅደሱ ሄዶ በድፍረት ማስተማር ጀመረ። ምናልባት እስር ቤት ሊያስገቡት ወይም ሊያስገድሉት ሳይሆን አይቀርም ሊይዙት ፈልገዋል። ሆኖም ‘ጊዜው ገና ስላልደረሰ’ ሊሳካላቸው አልቻለም። በዚህ ጊዜ ብዙዎች በኢየሱስ አመኑ። ይዘው እንዲያመጡት ፈሪሳውያን የላኳቸው ሎሌዎች እንኳ ሳይቀር ባዶ እጃቸውን ተመልሰው “እንደዚህ ሰው ማንም ከቶ አልተናገረም” አሉ።​—⁠ዮሐንስ 7:​9-14, 30-46

15. አይሁዳውያን ኢየሱስን በድንጋይ ሊወግሩት የነበረው ለምንድን ነው? ከዚህ በኋላስ ምን የስብከት ዘመቻ አካሄደ?

15 ኢየሱስ በበዓሉ ወቅት ቤተ መቅደሱ ውስጥ ስለ አባቱ በማስተማሩ በእሱና በአይሁዳውያን ተቃዋሚዎቹ መካከል ያለው ግጭት ቀጠለ። በበዓሉ የመጨረሻ ቀን ላይ ኢየሱስ ሰው ከመሆኑ በፊት ስለነበረው ሕይወት ሲናገር አይሁዶች ሊወግሩት ድንጋይ አነሱ። ሆኖም ተሰወረባቸውና ምንም ጉዳት ሳያገኘው አምልጧቸው ሄደ። (ዮሐንስ 8:​12-59) ኢየሱስ ከኢየሩሳሌም ውጭ በመቀመጥ በይሁዳ ከፍተኛ የስብከት ዘመቻ አካሄደ። ሰባ ደቀ መዛሙርት መረጠና መመሪያ ከሰጣቸው በኋላ በክልሉ እንዲሰብኩ ሁለት ሁለት አድርጎ ላካቸው። ኢየሱስ ከሐዋርያቱ ጋር ሆኖ ሊሄድበት ወዳቀደው ቦታና ከተማ ሁሉ ከእሱ በፊት ይሄዱ ነበር።​—⁠ሉቃስ 10:​1-24

16. ኢየሱስ በመቅደስ መታደስ በዓል ወቅት ያመለጠው ከምን ዓይነት አደጋ ነው? እንዲሁም በድጋሚ በምን ዓይነት ሥራ ተጠምዷል?

16 በ32 እዘአ የክረምት ወቅት የኢየሱስ ‘ሰዓት’ ይበልጥ እየተቃረበ መጣ። ኢየሱስ የመቅደስ መታደስን በዓል ለማክበር ወደ ኢየሩሳሌም መጥቷል። አይሁዳውያኑ አሁንም እሱን ለመግደል ይፈልጋሉ። ኢየሱስ በቤተ መቅደሱ መተላለፊያ እየሄደ ሳለ ዙሪያውን ከበቡት። አምላክን ተሳድበሃል ብለው በድጋሚ በመክሰስ ሊገድሉት ድንጋይ አነሱ። ሆኖም ኢየሱስ ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት እንዳደረገው ሁሉ አምልጧቸው ሄደ። በዚህ ጊዜ ደግሞ ከይሁዳ ዮርዳኖስን ተሻግሮ በፍርግያ አውራጃ ከከተማ ወደ ከተማና ከመንደር ወደ መንደር እየሄደ ወዲያው ማስተማሩን ቀጠለ። ደግሞም ብዙዎች በእሱ አመኑ። ሆኖም ወዳጁ አልዓዛርን በተመለከተ የደረሰው አስቸኳይ መልእክት ወደ ይሁዳ እንዲመለስ አደረገው።​—⁠ሉቃስ 13:​33፤ ዮሐንስ 10:​20-42

17. (ሀ) ኢየሱስ በፍርግያ እየሰበከ በነበረበት ወቅት ምን አስቸኳይ መልእክት ደረሰው? (ለ) ኢየሱስ እርምጃ መውሰድ ያለበት በምን ዓላማ እንደሆነና ሁኔታዎች በየትኛው ጊዜ መፈጸም እንዳለባቸው እንደሚያውቅ የሚያሳየው ምንድን ነው?

17 ይህ አስቸኳይ መልእክት በይሁዳ ቢታንያ ከሚኖሩት የአልዓዛር እህቶች ከማርታና ከማርያም የመጣ ነው። መልእክተኛው “ጌታ ሆይ፣ እነሆ፣ የምትወደው ታሞአል” ብሎ ነገረው። ኢየሱስ “ይህ እመም የእግዚአብሔር ልጅ በእርሱ ይከብር ዘንድ ስለ እግዚአብሔር ክብር ነው እንጂ ለሞት አይደለም” ሲል መለሰለት። ኢየሱስ ይህ ዓላማ ግቡን እንዲመታ ለማድረግ ሆነ ብሎ እዚያው ባለበት ለሁለት ቀናት ቆየ። ከዚያም ለደቀ መዛሙርቱ “ወደ ይሁዳ ደግሞ እንሂድ” አላቸው። ደቀ መዛሙርቱ በጥርጣሬ ስሜት “መምህር ሆይ፣ አይሁድ ከጥቂት ጊዜ በፊት ሊወግሩህ ይፈልጉ ነበር፣ ደግሞም ወደዚያ ትሄዳለህን?” አሉት። ሆኖም ኢየሱስ የቀረው ‘በቀን የሚመላለስበት ጊዜ’ ማለትም አምላክ ለምድራዊ አገልግሎቱ የመደበለት ጊዜ አጭር መሆኑን ተገንዝቧል። ማድረግ ያለበትንና ለምን ማድረግ እንዳለበት በሚገባ ያውቃል።​—⁠ዮሐንስ 11:​1-10

የሰውን ሁሉ ትኩረት የሳበ ተአምር

18. ኢየሱስ ቢታንያ ሲደርስ ሁኔታው ምን ይመስል ነበር? እዚያ ከደረሰስ በኋላ ምን ተከናወነ?

18 ቢታንያ እንደደረሰ ከኢየሱስ ጋር መጀመሪያ የተገናኘችው ማርታ ስትሆን “ጌታ ሆይ፣ አንተ በዚህ ኖረህ ብትሆን ወንድሜ ባልሞተም ነበር” አለችው። ማርያምና ወደ ቤታቸው የመጡት ሰዎችም ተከትለዋት መጡ። ሁሉም ያለቅሳሉ። ኢየሱስ “ወዴት አኖራችሁት?” ሲል ጠየቃቸው። “ጌታ ሆይ፣ መጥተህ እይ” ብለው መለሱለት። መግቢያው በድንጋይ ወደተዘጋ ዋሻ ማለትም ወደ መታሰቢያው መቃብር ሲደርሱ ኢየሱስ “ድንጋዩን አንሡ” አላቸው። ማርታ፣ ኢየሱስ ምን ለማድረግ እንዳሰበ ባለመረዳቷ “ጌታ ሆይ፣ ከሞተ አራት ቀን ሆኖታልና አሁን ይሸታል” ስትል ተቃወመች። ሆኖም ኢየሱስ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር እንድታዪ አልነገርሁሽምን?” ሲል ጠየቃት።​—⁠ዮሐንስ 11:​17-40

19. ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ከማስነሣቱ በፊት በሕዝብ ፊት የጸለየው ለምንድን ነው?

19 በአልዓዛር መቃብር መግቢያ ላይ ያለው ድንጋይ በሚነሳበት ጊዜ ኢየሱስ ሊፈጽመው ያለው ነገር ከአምላክ ባገኘው ኃይል የሚከናወን መሆኑን ሰዎቹ ማወቅ እንዲችሉ ድምፁን ከፍ አድርጎ ጸለየ። ከዚያም “አልዓዛር ሆይ፣ ወደ ውጭ ና” ብሎ በከፍተኛ ድምፅ ተጣራ። አልዓዛር እጅና እግሩ በመገነዣ እንደተገነዘ፣ ፊቱም በጨርቅ እንደተጠመጠመ ወጣ። ኢየሱስ “ፍቱትና ይሂድ ተዉት” አላቸው።​—⁠ዮሐንስ 11:​41-44

20. ኢየሱስ አልዓዛርን ከሞት ሲያስነሣው የተመለከቱ ሰዎች ምን ምላሽ ሰጡ?

20 ይህን ተአምር በሚያዩበት ጊዜ ማርታና ማርያምን ለማጽናናት የመጡት አብዛኞቹ አይሁዳውያን በኢየሱስ አመኑ። ሌሎች ደግሞ የተፈጸመውን ነገር ለፈሪሳውያን ለመንገር ሄዱ። የፈሪሳውያን ምላሽ ምን ነበር? ወዲያው ፈሪሳውያንና የካህናት አለቆች ሳንሄድሪን በአስቸኳይ እንዲሰበሰብ አደረጉ። በሁኔታው ተሸብረው “ምን እናድርግ? ይህ ሰው ብዙ ምልክቶች ያደርጋልና። እንዲሁ ብንተወው ሁሉ በእርሱ ያምናሉ፤ የሮሜም ሰዎች መጥተው አገራችንን ወገናችንንም ይወስዳሉ” ሲሉ ምሬታቸውን ገለጹ። ሆኖም ሊቀ ካህኑ ቀያፋ እንዲህ አላቸው:- “ሕዝቡም ሁሉ ከሚጠፋ አንድ ሰው ስለ ሕዝቡ ይሞት ዘንድ እንዲሻለን አታስቡም።” ስለዚህ ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስን ለመግደል ተማከሩ።​—⁠ዮሐንስ 11:​45-53

21. በተአምር የተፈጸመው የአልዓዛር ትንሣኤ ለምን ነገር መቅድም ነው?

21 በመሆኑም ኢየሱስ ወደ ቢታንያ ዘግይቶ በመምጣት የሰውን ሁሉ ትኩረት የሳበ ተአምር መፈጸም ችሏል። ኢየሱስ ከአምላክ ባገኘው ኃይል ለአራት ቀናት ሞቶ የነበረን ሰው አስነሳ። ሌላው ቀርቶ የታወቀው የሳንሄድሪን ሸንጎ እንኳ ሁኔታውን ለመቀበልና ተአምር በሠራው ሰው ላይ የሞት ፍርድ ለማስተላለፍ ተገድዷል! በመሆኑም ይህ ተአምር ‘ጊዜው ገና ያልደረሰበት’ ወቅት አልፎ ‘ሰዓቱ ወደደረሰበት’ ጊዜ ለተሸጋገረበት በኢየሱስ አገልግሎት ወሳኝ ለሆነ ለውጥ ዋዜማ ሆኖ አገልግሏል።

ምን ብለህ ትመልሳለህ?

• ኢየሱስ አምላክ የሰጠውን ሥራ ያውቅ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው?

• ኢየሱስ ወይን ጠጅን በተመለከተ እናቱ ያቀረበችለትን ሐሳብ የተቃወመው ለምንድን ነው?

• ኢየሱስ አብዛኛውን ጊዜ ተቃዋሚዎቹን በተመለከተ ካደረገው ነገር ምን መማር እንችላለን?

• ኢየሱስ የአልዓዛርን መታመም ሲሰማ ወዲያው እርምጃ ያልወሰደው ለምንድን ነው?

[በገጽ 12 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ ጉልበቱን ሁሉ ያዋለው አምላክ ለሰጠው ሥራ ነው

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ