የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
ቢል የሕንፃ ቴክኖሎጂ መምህር ሲሆን በ50ዎቹ ዕድሜ ላይ የሚገኝና የቤተሰብ ኃላፊ ነው። የራሱን ወጪ በመሸፈን በየዓመቱ ለይሖዋ ምሥክሮች ጉባኤዎች የሚሆኑ የመንግሥት አዳራሾችን ንድፍ በማውጣትና በመገንባት በርካታ ሳምንታት ያሳልፋል። ኤማ የተማረችና ጥሩ ችሎታ ያላት የ22 ዓመት ነጠላ ወጣት ናት። ሙሉ በሙሉ የግል ግቦችን ብቻ ከመከታተልና ደስታን ከማሳደድ ይልቅ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያውቁ ለመርዳት በየወሩ ከ70 የሚበልጥ ሰዓት ታሳልፋለች። ሞረስ እና ቤቲ ጡረታ ወጥተዋል። በዚህ ጊዜያቸው እንረፍ ከማለት ይልቅ ሰዎች አምላክ ለዚህች ምድር ያለውን ዓላማ እንዲያውቁ ለመርዳት ወደ ሌላ አገር ሄዱ።
እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ከሌሎች የተለዩ እንደሆኑ አድርገው አይቆጥሩም። ትክክል መሆኑን ያመኑበትን ነገር የሚያደርጉ ሰዎች ናቸው። ጊዜያቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ችሎታቸውንና ሃብታቸውን ሌሎችን ለመጥቀም የሚያውሉት ለምንድን ነው? እንዲህ እንዲያደርጉ የገፋፋቸው ለአምላክና ለሰዎች ያላቸው ጥልቅ ፍቅር ነው። ይህ ፍቅር እያንዳንዳቸው ከልብ የመነጨ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ እንዲያሳዩ አደረጋቸው።
የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ስንል ምን ማለታችን ነው? የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ለማሳየት የመናኝ ዓይነት ሕይወት መኖር አያስፈልግም። ደስታ ወይም እርካታ እስክናጣ ድረስ ራሳችንን መጉዳት አስፈላጊ አይደለም። ዘ ሾርተር ኦክስፎርድ ኢንግሊሽ ዲክሽነሪ የተባለው መዝገበ ቃላት እንዳስቀመጠው የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ማለት “አንድን የሞራል ግዴታ ለመወጣት ወይም ለሌሎች መልካም ተግባር ለማከናወን ሲባል የራስን ጥቅም፣ ደስታ እንዲሁም ፍላጎት አሳልፎ መስጠት” ማለት ነው።
ኢየሱስ ክርስቶስ—ዋነኛው ምሳሌ
የአምላክ አንድያ ልጅ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ረገድ ዋነኛው ምሳሌ ነው። ሰው ሆኖ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት ያሳለፈው ሕይወት ከፍተኛ ደስታና እርካታ የሞላበት እንደነበር ጥርጥር የለውም። ከአባቱና ከሌሎች መንፈሳዊ ፍጥረታት ጋር የተቀራረበና የጠለቀ ወዳጅነት ነበረው። ከዚህም በላይ የአምላክ ልጅ “ዋና ሠራተኛ” በነበረበት ጊዜ ችሎታዎቹን አስደናቂና አስደሳች ሥራዎችን ለማከናወን ተጠቅሞበታል። (ምሳሌ 8:30, 31) እዚህች ምድር ላይ ያለ እጅግ ባለጸጋ ነው የሚባልለት ሰው እንኳ ሊያገኘው በማይችለው እጅግ የተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ይኖር ነበር። በሰማይ ከይሖዋ አምላክ ቀጥሎ ከፍተኛና ልዩ ስልጣን ነበረው።
ሆኖም የአምላክ ልጅ “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ።” (ፊልጵስዩስ 2:7) በሰይጣን ምክንያት የመጣውን ክፋት ለማስቀረት የግል ጥቅሙን ወደ ጎን በመተው በፈቃደኝነት ሰው ሆኖ ወደ ምድር በመምጣት ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (ዘፍጥረት 3:1-7፤ ማርቆስ 10:45) ይህም በሰይጣን ዲያብሎስ ቁጥጥር ስር ባለው ዓለም ውስጥ በኃጢአተኛ የሰው ዘር መካከል ለመኖር ወደ ምድር መምጣትን ይጠይቃል። (1 ዮሐንስ 5:19) በተጨማሪም የሚደርስበትን ጉስቁልናና እንግልት በጽናት መቋቋም ይጠይቅበታል። ምንም እንኳ ከፍተኛ ዋጋ የሚጠይቅበት ቢሆንም ኢየሱስ ክርስቶስ የአባቱን ፈቃድ ለማድረግ ቆርጦ ነበር። (ማቴዎስ 26:39፤ ዮሐንስ 5:30፤ 6:38) ይህ ሁኔታ የኢየሱስ ፍቅርና ታማኝነት እስከ መጨረሻ ደረጃ እንዲፈተን አድርጓል። እስከ ምን ድረስ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነበር? ሐዋርያው ጳውሎስ “ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ” በማለት ተናግሯል።—ፊልጵስዩስ 2:8
“ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን”
የኢየሱስን ምሳሌ እንድንኮርጅ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። ጳውሎስ “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን” የሚል ማበረታቻ ሰጥቷል። (ፊልጵስዩስ 2:5) ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? አንደኛው መንገድ ‘የራስን ሳይሆን የባልንጀራን ጥቅም በመመልከት ነው።’ (ፊልጵስዩስ 2:4) እውነተኛ ፍቅር “የራሱን ጥቅም ብቻ ፈላጊ አይደለም።”—1 ቆሮንቶስ 13:5 የ1980 ትርጉም
አሳቢ የሆኑ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ሌሎችን ለማገልገል ሲሉ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ባሕርይ ያንጸባርቃሉ። ሆኖም በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች የራስ ወዳድነት ዝንባሌ ይታይባቸዋል። ዓለም እኔ ልቅደም የሚል ዝንባሌ ተጠናውቶታል። የዓለም አስተሳሰብ እንዳይጋባብን ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም ዓለም አስተሳሰባችንንና ዝንባሌያችንን እንዲቀርጽ የምንፈቅድ ከሆነ ከምንም ነገር በላይ የራሳችንን ፍላጎት የምናስቀድም ሰዎች መሆናችን የማይቀር ነው። ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንንም ሆነ ጥሪታችንን ሁሉ የምናውለው ለራስ ወዳድነት ጥቅም ብቻ ይሆናል። ስለዚህ የራስ ወዳድነትን ዝንባሌ አጥብቀን መዋጋት ይኖርብናል።
አንዳንድ ጊዜ በቅን አስተሳሰብ የተሰጠ ምክር እንኳ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈሳችንን ሊያቀዘቅዝብን ይችላል። ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ጎዳና መከተሉ ምን ሊያስከትል እንደሚችል በመገንዘብ ሐዋርያው ጴጥሮስ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም” ሲል ተናግሯል። (ማቴዎስ 16:22) ኢየሱስ ለአባቱ ሉዓላዊነት መከበርና ለሰው ልጆች መዳን ሲል እስከ ሞት ድረስ መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ የመሆኑን ጉዳይ ለጴጥሮስ ሊዋጥለት እንዳልቻለ ግልጽ ነው። ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ ያለውን ጎዳና እንዳይከተል ለማሳመን ሞክሯል።
‘ራስህን ካድ’
ኢየሱስ ምን ምላሽ ሰጠ? ዘገባው እንዲህ ይላል:- “እርሱ ግን ዘወር አለ ደቀ መዛሙርቱንም አይቶ ጴጥሮስን ገሠጸውና:- ወደ ኋላዬ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን ነገር አታስብምና አለው።” ከዚያም ኢየሱስ ሕዝቡንና ደቀ መዛሙርቱን ወደ እርሱ ጠርቶ “በኋላዬ ሊመጣ የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” አላቸው።—ማርቆስ 8:33, 34
ጴጥሮስ ይህን ምክር ለኢየሱስ ከሰጠ 30 ከሚያክሉ ዓመታት በኋላ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ምን ትርጉም እንዳለው የገባው መሆኑን አሳይቷል። ክርስቲያን ወንድሞቹ ራሳቸውን ማስጨነቃቸውን ትተው ተዝናንተው እንዲኖሩ አላበረታታም። ከዚህ ይልቅ ቀጥሎ ለሚጠብቃቸው ሥራ አእምሯቸውን እንዲያዘጋጁና ዓለማዊ ፍላጎቶችን ብቻ ያሳድዱ የነበሩበትን የቀድሞ አኗኗራቸውን እንዲተዉ አጥብቆ አሳስቧቸዋል። የተለያዩ ፈተናዎች ቢደርሱባቸውም እንኳ በሕይወታቸው ውስጥ የአምላክን ፈቃድ ለማድረጉ ቅድሚያ መስጠት ነበረባቸው።—1 ጴጥሮስ 1:6, 13, 14፤ 4:1, 2
ማንኛችንም ብንሆን ተወዳዳሪ የሌለው በረከት የሚያስገኝ መንገድ ተከትለናል ልንል የምንችለው ኢየሱስ ክርስቶስን በታማኝነት በመከተል ራሳችንን ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ስንሰጥና እንቅስቃሴያችንን ሁሉ አምላክ እንዲመራልን ስንፈቅድ ነው። ጳውሎስ በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። የጥድፊያ ስሜቱና ለይሖዋ ያለው አመስጋኝነት የአምላክን ፈቃድ እንዳያደርግ ሊያዘናጉት የሚችሉትን ዓለማዊ ግቦች ወይም አጋጣሚዎች ወደ ጎን እንዲተው አንቀሳቅሶታል። ሌሎችን ለመጥቀም ስል ‘ራሴን ምንም ሳልቆጥብ በደስታ እከፍላለሁ’ በማለት ተናግሯል። (2 ቆሮንቶስ 12:15 NW ) ጳውሎስ ችሎታውን የራሱን ጥቅም ለማስጠበቅ ሳይሆን መለኮታዊውን ፈቃድ ለማስፋፋት ተጠቅሞበታል።—ሥራ 20:24፤ ፊልጵስዩስ 3:8
ሐዋርያው ጳውሎስ የነበረው ዓይነት አመለካከት እንዳለንና እንደሌለን ራሳችንን መመርመር የምንችለው እንዴት ነው? እንዲህ እያልን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን:- ጊዜዬን፣ ጉልበቴን፣ ችሎታዬንና ጥሪቴን የምጠቀምበት እንዴት ነው? እነዚህንና ሌሎች ውድ ስጦታዎችን የምጠቀምባቸው ለግል ጥቅሜ ብቻ ነው ወይስ ሌሎችን ለመርዳት? ምናልባትም የሙሉ ጊዜ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪ በመሆን ሕይወት አድን በሆነው ምሥራቹን የማወጅ ሥራ ሙሉ ተሳትፎ ለማድረግ አስቤአለሁ? የመንግሥት አዳራሾችን መገንባት ወይም ማደስ በመሳሰሉ እንቅስቃሴዎች ላይ ሙሉ ተሳትፎ ማድረግ እችላለሁ? ችግር ውስጥ የወደቁትን ለመርዳት አጋጣሚዎችን እጠቀማለሁ? ለይሖዋ ምርጤን እሰጠዋለሁ?—ምሳሌ 3:9
‘በመስጠት የሚገኝ የበለጠ ደስታ’
ሆኖም የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ማሳየት በእርግጥ ጥበብ ነውን? እንዴታ! እንደዚህ ያለ መንፈስ ማሳየት የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያስገኝ ጳውሎስ በራሱ አይቶታል። ታላቅ ደስታና ይህ ነው የማይባል እርካታ አስገኝቶለታል። በሚሊጢን ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ጋር በተገናኘ ጊዜ ይህን ሁኔታ ገልጾላቸው ነበር። ጳውሎስ “እንዲሁ እየደከማችሁ [የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ መንፈስ] ድውዮችን ልትረዱና እርሱ ራሱ:- ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው እንዳለ የጌታን የኢየሱስን ቃል ልታስቡ ይገባችሁ ዘንድ በሁሉ አሳየኋችሁ” ብሏቸው ነበር። (ሥራ 20:35) በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲህ ያለውን መንፈስ ማንጸባረቅ አሁንም እንኳ ከፍ ያለ ደስታ እንደሚያስገኝ ተረድተዋል። እንዲሁም ይሖዋ ከራሳቸው ፍላጎት ይልቅ የእርሱንና የሌሎችን ፍላጎት ለሚያስቀድሙ ሰዎች ወደፊት ወሮታቸውን በሚከፍልበት ጊዜ ደስታ ያስገኝላቸዋል።—1 ጢሞቴዎስ 4:8-10
ቢል የመንግሥት አዳራሾችን በመገንባት ሌሎችን ለመርዳት ምን እንዳነሳሳው ተጠይቆ ሲመልስ “ትንንሽ ጉባኤዎችን በዚህ መንገድ መርዳት እርካታ ይሰጠኛል። ያለኝን ችሎታ ወይም ሙያ ሌሎችን ለመጥቀም ማዋል በጣም ያስደስተኛል” በማለት ተናግሯል። ኤማ ቅዱስ ጽሑፋዊውን እውነት ሌሎች እንዲማሩ ለመርዳት ጉልበቷንና ችሎታዋን ሁሉ መሥዋዕት ያደረገችው ለምንድን ነው? “ከዚህ የተለየ ሌላ ሥራ መሥራት ፈጽሞ ላስበውም አልችልም። ገና ወጣት እስከሆንኩና አቅሜ እስከፈቀደ ድረስ ይሖዋን ለማስደሰትና ሌሎችን ለመርዳት እጥራለሁ። አንዳንድ ቁሳዊ ጥቅሞችን መሥዋዕት ማድረጉ ከቁጥር የሚገባ አይደለም። ይሖዋ ካደረገልኝ አንጻር ሲታይ እያደረግኩ ያለሁት ማድረግ ያለብኝን ነው።”
ሞሪስ እና ቤቲ ልጆቻቸውን ለማሳደግና ቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ለማሟላት ለብዙ ዓመታት ሲደክሙ ከቆዩ በኋላ ዘና ያለ ሕይወት ለመምራት አለመምረጣቸው ምንም አያስቆጫቸውም። አሁን ጡረታ ወጥተዋል፤ በቀሪው ሕይወታቸው ጠቃሚና ትርጉም ያለው ነገር ማከናወናቸውን መቀጠል ይፈልጋሉ። እንዲህ ይላሉ:- “ብዙ ስንደክም ኖረናል በሚል እጃችንን አጣጥፈን መቀመጥ አንፈልግም። በባዕድ አገር ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ መርዳት በሕይወታችን ውስጥ ትርጉም ያለው ነገር መሥራታችንን እንድንቀጥል አጋጣሚውን ይበልጥ ክፍት ያደርግልናል።”
አንተስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ አድርገሃል? እንዲህ ማድረጉ ቀላል አይደለም። ፍጹም ባልሆነው ሰብዓዊ ፍላጎታችን እና ይሖዋን ለማስደሰት ባለን ከፍተኛ ምኞት መካከል የማያቋርጥ ትግል አለ። (ሮሜ 7:21-23) ይሖዋ ሕይወታችንን እንዲመራልን የምንፈቅድ ከሆነ በትግሉ አሸናፊ መሆን እንችላለን። (ገላትያ 5:16, 17) እሱን ለማገልገል ስንል የምንከፍለውን መሥዋዕትነት ፈጽሞ ስለማይረሳ አብዝቶ ይባርከናል። በእርግጥም ይሖዋ አምላክ ‘የሰማይን መስኮት በመክፈት በረከትን አትረፍርፎ ያፈስስልናል።’—ሚልክያስ 3:10፤ ዕብራውያን 6:10
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ኢየሱስ የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ነበረው። አንተስ?
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ ትኩረቱን በመንግሥቱ የስብከት ሥራ ላይ አድርጓል