የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግን መንፈስ በመያዝ ይሖዋን ማገልገል
“እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ የመከራውንም እንጨት ተሸክሞ ያለማቋረጥ ይከተለኝ።” — ማቴዎስ 16:24 አዓት
1. ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ በቅርቡ እንደሚሞት የነገራቸው እንዴት ነበር?
ኢየሱስ ክርስቶስ በበረዶ በተሸፈነው የአርሞንዔም ተራራ አጠገብ በሕይወቱ ውስጥ አንድ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደረሰ። በሕይወት የሚቆይበት ጊዜ ከአንድ ዓመት ያነሰ ሆኗል። እሱ ይህን ያውቃል፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን አያውቁም። አሁን እነሱም የሚያውቁበት ጊዜ ደረሰ። እውነት ነው ኢየሱስ ቀደም ብሎ በቅርቡ እንደሚገደል በተዘዋዋሪ ተናግሮ ነበር። ሆኖም እንደሚሞት በግልጽ ሲናገር ይህ የመጀመሪያ ጊዜው ነው። (ማቴዎስ 9:15፤ 12:40) ማቴዎስ የመዘገበው ታሪክ እንዲህ ይነበባል:- “ከዚያን ቀን ጀምሮ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ይሄድ ዘንድ ከሽማግሎችና ከካህናት አለቆች ከጻፎችም ብዙ መከራ ይቀበልና ይገደል ዘንድ በሦስተኛውም ቀን ይነሣ ዘንድ እንዲገባው ለደቀ መዛሙርቱ ይገልጥላቸው ጀመር።” — ማቴዎስ 16:21፤ ማርቆስ 8:31, 32
2. ኢየሱስ ወደፊት ስለሚደርስበት ሥቃይ በነገራቸው ጊዜ ጴጥሮስ ምን አለ? ኢየሱስስ የመለሰለት እንዴት ነበር?
2 ኢየሱስ ሊገደል የቀሩት ቀኖች በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ሆኖም ጴጥሮስ መጥፎ በሚመስለው በዚህ ሐሳብ በጣም በመሰቀቅ ተቆጣ። መሲሑ ይገደላል የሚለውን ሐሳብ ሊቀበለው አልቻለም። ስለዚህ ጴጥሮስ ጌታውን ለመገሰጽ ደፈረ። ባለው መልካም አሳቢነት በመገፋፋት ቸኩሎ “አይሁንብህ ጌታ ሆይ፤ ይህ ከቶ አይደርስብህም” ሲል አጥብቆ ተናገረው። ሆኖም አንድ ሰው አንድን መርዛም እባብ አናቱን እንደሚጨፈልቀው ሁሉ ኢየሱስም ጴጥሮስ አለቦታው ያሳየውን ደግነት ወዲያውኑ ተቃወመው። “ወደ ኋላዬ ሂድ፣ አንተ ሰይጣን፤ የሰውን እንጂ የእግዚአብሔርን አታስብምና ዕንቅፋት ሆነህብኛል አለው።” — ማቴዎስ 16:22, 23
3. (ሀ) ጴጥሮስ ሳይታወቀው ራሱን የሰይጣን ወኪል ያደረገው እንዴት ነበር? (ለ) ጴጥሮስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረጉ እርምጃ እንቅፋት የሆነው እንዴት ነበር?
3 ጴጥሮስ ሳይታወቀው ራሱን የሰይጣን ወኪል አድርጎ ነበር። ኢየሱስ ለጴጥሮስ የሰጠው ቁርጥ ያለ መልስ በምድረበዳ ለሰይጣን እንደመለሰለት ዓይነት ነበር። በዚያም ኢየሱስ የተዝናና ሕይወት እንዲመራ ማለትም ምንም መከራ ሳይደርስበት ንጉሥ እንዲሆን ሰይጣን ሊፈትነው ሞክሯል። (ማቴዎስ 4:1–10) ጴጥሮስም ኢየሱስ በራሱ ላይ እንዳይጨክን እያበረታታው ነው። ኢየሱስ ይህ የአባቱ ፈቃድ እንዳልሆነ ያውቃል። ሕይወቱ የራስን ጥቅም በመሰዋት ላይ እንጂ ራስን በማስደሰት ላይ የተመሠረተ መሆን የለበትም። (ማቴዎስ 20:28) ጴጥሮስ ለእንዲህ ዓይነቱ እርምጃ እንቅፋት ሆነ፤ የእሱ ልባዊ አዛኝነት ወጥመድ የሚሆን ነበር።a ሆኖም ኢየሱስ መስዋዕት የማይከፈልበት ሕይወት ለመምራት ቢያስብ በሰይጣን የሞት ወጥመድ ውስጥ በመግባት የአምላክን ሞገስ እንደሚያጣ በግልጽ ያውቅ ነበር።
4. የተዝናና ኑሮ ለኢየሱስም ሆነ ለተከታዮቹ የማይሆነው ለምንድን ነው?
4 ስለዚህ የጴጥሮስ አስተሳሰብ ማስተካከያ አስፈልጎት ነበር። ለኢየሱስ የተናገራቸው ቃላት የሚወክሉት የሰውን እንጂ የአምላክን አስተሳሰብ አይደለም። የተዝናና ወይም ከችግር ነፃ የሆነ ኑሮ መኖር የኢየሱስም ሆነ የተከታዮቹ የሕይወት መንገድ አይደለም፤ ምክንያቱም ኢየሱስ ቀጥሎ ለጴጥሮስና ለቀሩት ደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸዋል:- “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ የመከራውንም እንጨት ተሸክሞ ያለማቋረጥ ይከተለኝ።” — ማቴዎስ 16:24 አዓት
5. (ሀ) ክርስቲያን ሆኖ መኖር የሚያስከትለው ፈታኝ ሁኔታ ምንድን ነው? (ለ) አንድ ክርስቲያን ዝግጁ መሆን ያለበት ለየትኞቹ ሦስት አስፈላጊ ነገሮች ነው?
5 ኢየሱስ ቁልፍ የሆነውን አጠቃላይ መልዕት ማለትም ክርስቲያን ሆኖ መኖር የሚስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ ደግሞ ደጋግሞ ጠቅሶታል። ክርስቲያኖች የኢየሱስ ተከታዮች ለመሆን እንደ መሪያቸው ሁሉ የራስን ጥቅም መስዋዕት የማድረግን መንፈስ በመያዝ ይሖዋን ማገልገል አለባቸው። (ማቴዎስ 10:37–39) በዚህ መንገድ አንድ ክርስቲያን የሚከተሉትን ሦስት አስፈላጊ ነገሮች ለማድረግ ዝግጁ መሆን እንዳለበት ዘርዝሯል። እነርሱም:- (1) ራስን መካድ (2) የመከራውን እንጨት መሸከም እንዲሁም (3) ያለማቋረጥ እሱን መከተል ናቸው።
“እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር”
6. (ሀ) አንድ ሰው ራሱን የሚክደው እንዴት ነው? (ለ) ከራሳችን ይልቅ ማስደሰት ያለብን ማንን ነው?
6 ራስን መካድ ማለት ምን ማለት ነው? አንድ ሰው ለራስ የመሞትን ያህል ሙሉ በሙሉ ራሱን መካድ አለበት ማለት ነው። “መካድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “አይሆንም ማለት” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። ይኸውም “ፈጽሞ መንፈግ” ማለት ነው። ስለዚህ ክርስቲያን ሆኖ መኖር የሚያስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ ከተቀበልክ የራስህን ፍላጎት፣ ምቾት፣ ምኞት፣ ደስታ እንዲሁም ተድላ በፈቃደኝነት ትተዋለህ። ይህም ማለት መላ ሕይወትህንና ከሕይወትህ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ነገሮች ሁሉ ለይሖዋ አምላክ ለዘላለም ትሰጣለህ ማለት ነው። ራስን መካድ ማለት የራስን ተድላዎች አልፎ አልፎ መተው ብቻ አይደለም። ከዚህ ይልቅ አንድ ሰው በራሱ ላይ ያለውን የባለቤትነት መብት ለይሖዋ ይሰጣል ማለት ነው። (1 ቆሮንቶስ 6:19, 20) ራሱን የካደ ሰው የሚኖረው ራሱን ሳይሆን አምላክን ለማስደሰት ነው። (ሮሜ 14:8፤ 15:3) ይህም ማለት በማንኛውም ጊዜ ራስ ወዳድ የሆኑትን ፍላጎቶቹን እምቢ በማለት ይሖዋን ይታዘዛል።
7. የአንድ ክርስቲያን የመከራ እንጨት ምንድን ነው? እንዴትስ ይሸከመዋል?
7 ስለዚህ የመከራውን እንጨት መሸከም ከበድ ያሉ ነገሮችንም ይጨምራል። የመሰቀያ እንጨት መሸከም ከባድ ነው፤ እንዲሁም የሞት ምልክት ነው። አንድ ክርስቲያን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይ በመሆኑ አስፈላጊ ከሆነ መከራ ለመቀበል፣ ለመዋረድ፣ ለመሰቃየት ወይም ለመሞት እንኳን ፈቃደኛ ነው። ኢየሱስ “መስቀሉንም [የመከራውን እንጨት አዓት] የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም” ብሏል። (ማቴዎስ 10:38) መከራ የሚደርስባቸው ሁሉ የመከራውን እንጨት ተሸክመዋል ማለት አይደለም። ክፉዎች ብዙ “መከራ” አለባቸው፤ ነገር ግን የመከራ እንጨት አልተሸከሙም። (መዝሙር 32:10) የክርስቲያን ሕይወት ግን ለይሖዋ የሚቀርበው መሥዋዕታዊ አገልግሎት የሚያስከትለውን የመከራ እንጨት መሸከም ነው።
8. ኢየሱስ ለተከታዮቹ የተወላቸው የአኗኗር ዘይቤ ምንድን ነው?
8 ኢየሱስ በመጨረሻ ላይ የጠቀሰው ነገር ያለማቋረጥ እሱን እንድንከተለው ነው። ኢየሱስ ከእኛ የሚፈልገው ያስተማረውን እንድንቀበልና እንድናምን ብቻ ሳይሆን በሕይወታችን ሁሉ እሱ የተወልንን ምሳሌ ያለማቋረጥ እንድንከተል ነው። በእሱ የአኗኗር ዘይቤ ውስጥ የሚታዩ አንዳንድ ጎላ ያሉ ገጽታዎች ምንድን ናቸው? ለተከታዮቹ የመጨረሻ ትዕዛዝ በሰጣቸው ጊዜ እንዲህ አለ:- “እንግዲህ ሂዱና . . . ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።” (ማቴዎስ 28:19, 20) ኢየሱስ የመንግሥቱን ምሥራች ሰብኳል፤ እንዲሁም አስተምሯል። የመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርቱም ሆኑ ጠቅላላው የጥንት ክርስቲያን ጉባኤ እንዲሁ አድርገዋል። የዓለምን ጥላቻና ተቃውሞ ያስከተለባቸው ከዓለም የተለዩ ከመሆናቸው በተጨማሪ ይህ የቅንአት እንቅስቃሴያቸው ነው። ይህም የመከራቸውን እንጨት መሸከሙን ከባድ እንዲሆንባቸው አድርጓል። — ዮሐንስ 15:19, 20፤ ሥራ 8:4
9. ኢየሱስ ሌሎች ሰዎችን የያዘበት መንገድ እንዴት ዓይነት ነበር?
9 ሌላው በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የታየው ትልቅ ምሳሌ ሌሎች ሰዎችን የያዘበት መንገድ ነው። እሱም ደግና ‘የዋህ በልቡም ትሑት’ ነበር። ስለሆነም አድማጮቹ እሱ አጠገባቸው ሲሆን መንፈሳቸው እንደታደሰ ይሰማቸውና ይበረታቱ ነበር። (ማቴዎስ 11:29) ኢየሱስ በማስፈራራት ወይም በሕግ ላይ ሕግ በመጫን እንዲከተሉት ለማድረግ አልሞከረም፤ ወይም ተከታዮቹ እንዲሆኑ ለማስገደድ ሲል የጥፋተኝነት ስሜት እንዲሰማቸው አላደረገም። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት እያደረጉ ቢኖሩም እውነተኛ ደስታ እንዳላቸው አሳይተዋል። ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ምልክት የሆነው ራስን የማስደሰት ዓለማዊ መንፈስ ካላቸው ሰዎች አስተሳሰብ እንዴት ፈጽሞ የተለየ ነው! — 2 ጢሞቴዎስ 3:1–4
ኢየሱስ ያሳየውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግን መንፈስ ማዳበርና መያዝ
10. (ሀ) በፊልጵስዩስ 2:5–8 መሠረት ክርስቶስ ራሱን የካደው እንዴት ነበር? (ለ) የክርስቶስ ተከታዮች ከሆንን ምን ዓይነት የአእምሮ ዝንባሌ መያዝ አለብን?
10 ኢየሱስ ራስን የመካድ ምሳሌ ትቶልናል። የመከራውን እንጨት አንስቶ የአባቱን ፈቃድ በማድረግ ያለማቋረጥ ተሸክሞታል። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎላቸዋል:- “በክርስቶስ ኢየሱስ የነበረ ይህ አሳብ በእናንተ ዘንድ ደግሞ ይሁን። እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቆጠረውም፣ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፣ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፣ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት [በመከራ እንጨት ላይ ለመሞት አዓት] እንኳ የታዘዘ ሆነ።” (ፊልጵስዩስ 2:5–8) ከዚህ የበለጠ ሙሉ በሙሉ ራሱን ለመካድ የሚችል ማን ነው? የክርስቶስ ኢየሱስ ከሆንክና ከእሱ ተከታዮች አንዱ ከሆንክ ይህን የመሰለ የአእምሮ ዝንባሌ ልትይዝ ይገባሃል።
11. የራስን ጥቅም መሥዋዕት እያደረጉ መኖር ማለት ለማን ፈቃድ መኖር ማለት ነው?
11 ሌላው ሐዋርያ ማለትም ጴጥሮስ ኢየሱስ ለእኛ ሲል መከራ ስለተቀበለና ስለሞተ ክርስቲያኖችም ክርስቶስ በነበረው ዓይነት መንፈስ በሚገባ እንደተዘጋጁ ወታደሮች በመሆን ራሳቸውን ማስታጠቅ አለባቸው በማለት ይነግረናል። እሱም እንዲህ ሲል ጻፈ:- “ክርስቶስም በሥጋ ስለ እኛ መከራን ስለ ተቀበለ፣ ከእንግዲህ ወዲህ በሥጋ ልትኖሩ በቀረላችሁ ዘመን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ እንደ ሰው ምኞት እንዳትኖሩ፣ እናንተ ደግሞ ያን አሳብ እንደ ዕቃ ጦር አድርጋችሁ ያዙት፣ በሥጋ መከራን የተቀበለ ኃጢአትን ትቶአልና።” (1 ጴጥሮስ 3:18፤ 4:1, 2) የኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ መመላለሱ ስለ አምላክ ፈቃድ እንዴት እንደሚሰማው በግልጽ አሳይቷል። ኢየሱስ የውርደት ሞት እስከ መሞት ድረስ ከራሱ ፈቃድ ይልቅ ዘወትር የአባቱን ፈቃድ በማስቀደም ለቆመለት ዓላማ ምንም አላወላወለም። — ማቴዎስ 6:10፤ ሉቃስ 22:42
12. የራስን ጥቅም መሥዋዕት እያደረጉ መኖር ለኢየሱስ የሚያንገሸግሽ ሆኖበት ነበርን? አብራራ።
12 ምንም እንኳን ኢየሱስ የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ያሳለፈው ሕይወት በጣም ከባድና ፈታኝ ቢሆንበትም የሚያንገሸግሽ ሆኖ አላገኘውም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ራሱን ለመለኮታዊው ፈቃድ በማስገዛቱ ደስታ አግኝቷል። የአባቱን ሥራ መሥራት ለእሱ እንደ መብል ሆኖለት ነበር። አንድ ሰው ጥሩ ምግብ ሲበላ እርካታ እንደሚያገኝ ሁሉ እሱም የአባቱን ፈቃድ በማድረግ እርካታ አግኝቷል። (ማቴዎስ 4:4፤ ዮሐንስ 4:34) እንግዲያው በሕይወትህ ውስጥ እውነተኛ እርካታ ለማግኘት ከፈለግህ የኢየሱስን ዓይነት አስተሳሰብ በመኮትኮት የእሱን ምሳሌ ከመከተል የተሻለ ሌላ ምንም ነገር ልታደርግ አትችልም።
13. ፍቅር የራስን ጥቅም መሥዋዕት ከማድረግ መንፈስ በስተጀርባ ያለ የሚገፋፋ ኃይል የሆነው እንዴት ነው?
13 የራስን ጥቅም መሥዋዕት ከማድረግ መንፈስ በስተጀርባ ያለው የሚገፋፋ ኃይል ምንድን ነው? በአጭሩ ፍቅር ነው። ኢየሱስ እንዲህ ብሏል:- “ጌታ [ይሖዋ አዓት] አምላክህን በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ። ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት። ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፣ እርስዋም:- ባልንጀራህን [ጎረቤትህን አዓት] እንደ ነፍስህ ውደድ የምትለው ናት።” (ማቴዎስ 22:37–39) አንድ ክርስቲያን ራሱን ብቻ እየወደደ ይህን ትዕዛዝ አከብራለሁ ሊል አይችልም። የእሱ ደስታና ፍላጎት በመጀመሪያ ደረጃ ለይሖዋ ከዚያም ለጎረቤቱ ባለው ፍቅር የሚመራ መሆን አለበት። ኢየሱስ ሕይወቱን ያሳለፈው በዚህ መንገድ ነው፤ ተከታዮቹም እንዲሁ እንዲያደርጉ ይጠብቅባቸዋል።
14. (ሀ) በዕብራውያን 13:15, 16 ላይ የተገለጹት ኃላፊነቶች ምንድን ናችው? (ለ) ምሥራቹን በቅንዓት እንድንሰብክ የሚገፋፋን ምንድን ነው?
14 ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን የፍቅር ሕግ ተገንዝቦት ነበር። እንዲህ ሲል ጽፏል:- “እንግዲህ ዘወትር ለእግዚአብሔር የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ፣ በእርሱ እናቅርብለት። ነገር ግን መልካም ማድረግን ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና።” (ዕብራውያን 13:15, 16) ክርስቲያኖች እንስሳትን ወይም ሌሎች ነገሮችን ለይሖዋ መሥዋዕት አያቀርቡም፤ ስለዚህ ለአምልኮታቸው በምድራዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ የሚያገለግሉ ሰብአዊ ካህናት አይፈልጉም። የምስጋና መሥዋዕታችን የሚቀርበው በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ነው። ለአምላክ ያለንን ፍቅር የምናሳየው በዚህ የምስጋና መሥዋዕት ማለት ስሙን ለሰዎች ሁሉ በየቦታው በማሳወቅ ነው። በተለይ በፍቅር ላይ የመሠረተ ራስ ወዳድነት የሌለበት መንፈስ ምሥራቹን በቅንአት እንድንሰብክ ይገፋፋናል፤ የከንፈሮቻችንን ፍሬ ለአምላክ መሥዋዕት ለማቅረብ ሁልጊዜ ዝግጁዎች ለመሆን እንጥራለን። በዚህ መንገድ ለጎረቤቶቻችንም ጭምር ያለንን ፍቅር እናሳያለን።
የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ ብዙ በረከቶችን ያስገኛል
15. የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግን በተመለከተ ራሳችንን እንድንመረምር የሚያደርጉ ምን ጥያቄዎችን ልንጠይቅ እንችላለን?
15 እስቲ ለጥቂት ጊዜ ቆም በልና የሚከተሉትን ጥያቄዎች አሰላስልባቸው:- ያለኝ የአኗኗር ዘይቤ የራስን ጥቅም መስዋዕት የማድረግ ጎዳና እንደምከተል ያሳያልን? ግቦቼ እንዲህ ዓይነቱን ሕይወት ያመለክታሉን? የቤተሰቤ አባሎች ከእኔ ምሳሌ መንፈሳዊ ጥቅም እያገኙ ናቸውን? (ከ1 ጢሞቴዎስ 5:8 ጋር አወዳድር።) ወላጆች የሌላቸው ልጆችና መበለቶችስ? ከእኔ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ይጠቀማሉን? (ያዕቆብ 1:27) በሕዝብ ፊት የምስጋና መሥዋዕት በማቅረብ የማሳልፈውን ጊዜ ከፍ ለማድረግ እችላለሁን? ለአቅኚነት፣ ለቤቴል ወይም ለሚሲዮናዊነት የአገልግሎት መብቶች ብቁ ለመሆን እችላለሁን? ወይም ደግሞ የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄጄ ለማገልገል እችላለሁን?
16. ብልህነት የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግን ሕይወት ለመምራት ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
16 አንዳንድ ጊዜ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በመያዝ ይሖዋን በሙሉ ኃይላችን ለማገልገል የሚጠይቀው ጥቂት ብልሃት ብቻ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል በኢኳዶር የዘወትር አቅኚ ሆና የምታገለግለው ጃኔት የሙሉ ጊዜ ሰብአዊ ሥራ ትሠራ ነበር። ብዙም ሳይቆይ የሥራ ፕሮግራሟ በዘወትር አቅኚነቷ የሚፈለግባትን ሰዓት በደስታ ለማምጣት አዳጋች አድርጎባት ነበር። ችግሩን ለአሠሪዋ ለመንገርና ከሥራ ሰዓቷ ላይ እንዲቀነስላት ለመጠየቅ ወሰነች። አሠሪዋ የሥራ ሰዓቷን ለመቀነስ ፈቃደኛ ስላልሆነ በሚቀጥለው ጊዜ ስትሄድ አቅኚ ለመሆን የግማሽ ቀን ሥራ ትፈልግ የነበረችውን ማሪያን ወሰደቻት። የሙሉውን ቀን ሥራ ለሁለት ተካፍለው እያንዳንዳቸው ግማሽ ግማሽ ቀን ለመሥራት አመለከቱ። አሠሪውም ባቀረቡት ሐሳብ ተስማማ። አሁን ሁለቱም እኅቶች የዘወትር አቅኚዎች ናቸው። ለዚሁ ኩባንያ ሙሉ ቀን በመሥራት ጉልበቷ ተሟጦ የነበረችውና የአቅኚነት ሰዓቷን ለማሟላት ስትታገል የነበረችው ካፋ ይህን ግሩም ውጤት በመመልከት ማጋሊንን ይዛ በመሄድ ተመሳሳይ ጥያቄ አቀረበች። የእነሱም ጥያቄ ተቀባይነት አገኘ። የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ሊተዉ ጥቂት ቀርቷቸው ከነበሩት ሁለት እኅቶች ይልቅ በዚህ መንገድ አራት እኅቶች አቅኚ ለመሆን ቻሉ። ብልሃተኝነትና ጥሩ ሐሳብ የማመንጨት ችሎታ ጠቃሚ ውጤት አላቸው።
17–21. አንድ ባልና ሚስት በሕይወታቸው ውስጥ ያላቸውን ዓላማ እንደገና የመረመሩት እንዴት ነው? ከምንስ ውጤት ጋር?
17 በተጨማሪም ባለፉት አሥር ዓመታት ኢቮን የተከተለችውን የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንገድ ተመልከት። በግንቦት 1991 ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሚከተለውን ጽፋለች:-
18 “በጥቅምት 1982 እኔና ቤተሰቤ የብሩክሊን ቤቴልን ጎብኝተን ነበር። ቤቴልን ማየቴ በፈቃደኝነት እዚያ ለመሥራት ፍላጎት አሳደረብኝ። አንድ ማመልከቻ አነበብኩ፤ በውስጡም ‘ባለፉት ስድስት ወራት በመስክ አገልግሎት ያሳለፍከው አማካይ ሰዓትህ ምን ያህል ነው? አማካይ ሰዓትህ ከአሥር ሰዓት በታች ከሆነ ምክንያቱን ግለጽ’ የሚል አንድ ልብ የሚነካ ጥያቄ አለ። አነስተኛ ሰዓት ለመመለስ ምንም በቂ ምክንያት አልነበረኝም፤ ስለዚህ ግብ አወጣሁና ለአምስት ወር ግቤን አሟላሁ።
19 “ምንም እንኳን አቅኚ ላለመሆን ጥቂት ሰበቦችን ለመደርደር ብችልም የ1983 የይሖዋ ምስክሮች የዓመት መጽሐፍ ሳነብ ሌሎች አቅኚ ለመሆን ሲሉ ከእኔ የበለጡ እንቅፋቶችን እንዳሸነፉ ተረዳሁ። ስለዚህ በሚያዝያ 1, 1983 ትርፍ የሚያስገኝ የሙሉ ጊዜ ሥራዬን ተውኩና ረዳት አቅኚ ሆንኩ፤ ከዚያም በመስከረም 1, 1983 የዘወትር አቅኚ ሆንኩ።
20 “በሚያዝያ 1985 አንድ ጎበዝ ዲያቆን አገባሁ። ከሦስት ዓመት በኋላ በወረዳ ስብሰባ ላይ አቅኚነትን በተመለከተ የቀረበ ንግግር ባለቤቴ ‘በመስከረም 1 አቅኚነትን እንዳልጀምር የሚከለክለኝ ምንም ምክንያት እንደሌለ ታውቂያለሽ?’ ብሎ በሹክሹክታ እንዲጠይቀኝ አነሳሳው። በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታት በአቅኚነት አብረን ሠራን።
21 “በተጨማሪም ባለቤቴ ለሁለት ሳምንት በብሩክሊን ቤቴል በሚካሄደው የግንባታ ሥራ ለመካፈል ፈቃደኛ ሆነ፤ እንዲሁም በዓለም አቀፉ የግንባታ ሥራ ለመሳተፍ ጥያቄ አቀረበ። ስለዚህ በግንቦት 1989 በቅርንጫፍ ቢሮ ግንባታ ለመርዳት ለአንድ ወር ያህል ወደ ናይጄሪያ ሄድን። ነገ ደግሞ ፖላንድ የምንገባበት ቪዛ ወደሚዘጋጅበት ወደ ጀርመን እንሄዳለን። በዚህ ዓይነቱ ታሪካዊ የግንባታ ፕሮጀክት ውስጥ በመግባታችንና በዚህ አዲስ ዓይነት የሙሉ ጊዜ አገልግሎት ተካፋይ በመሆናችን በጣም ደስተኞች ነን።”
22. (ሀ) እንደ ጴጥሮስ ሳይታወቀን እንቅፋት ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በመያዝ ይሖዋን ማገልገል በምን ላይ የተመካ አይደለም?
22 አንተ ራስህ አቅኚ ለመሆን ካልቻልክ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ያሉት ይህን መብታቸውን አጥብቀው እንዲይዙት ልታበረታታቸውና የሙሉ ጊዜ አገልግሎታችውን እንዲፈጽሙ ልትረዳቸው ትችላለህን? ወይስ አንዳንድ የቤተሰብ አባሎች ወይም ጓደኞች እንደ ጴጥሮስ እንቅፋት እንደሆኑ ሳይገነዘቡ በቅን ልብ እንደሚናገሩት አንድ የሙሉ ጊዜ አገልጋይ መዝናናት አለበት፤ ራሱን ማስጨነቅ የለበትም ብለህ ትናገራለህን? እውነት ነው፣ አንድ አቅኚ ጤንነቱ በጣም ከተጎዳ ወይም ክርስቲያናዊ ግዴታዎቹን ቸል የሚል ከሆነ ለተወሰነ ጊዜ የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን መተው ሊኖርበት ይችል ይሆናል። የራስን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ መንፈስ ይሖዋን ማገልገል ማለት አቅኚ፣ ቤቴላዊ ወይም ሌላ ስም በማግኘት ብቻ የተመካ አይደለም። ከዚህ ይልቅ ምን ዓይነት ግለሰቦች በመሆናችን ማለትም እንዴት እንደምናስብ፣ ምን እንደምናደርግ፣ ሌሎችን እንዴት አድርገን እንደምንይዝና ሕይወታችንን እንዴት አድርገን እንደምንመራ በምናሳይበት መንገድ ላይ የተመካ ነው።
23. (ሀ) ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ በመሆን የምናገኘውን ደስታ እንደያዝን ለመቀጠል የምንችለው እንዴት ነው? (ለ) በዕብራውያን 6:10–12 ምን ዋስትና እናገኛለን?
23 ከልብ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ ካለን ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ በመሆናችን ደስታ እናገኛለን። (1 ቆሮንቶስ 3:9) የይሖዋን ልብ ደስ እያሰኘን መሆናችንን በማወቃችን እርካታ እናገኛለን። (ምሳሌ 27:11) እንዲሁም ታማኞች ሆነን እስከቀጠልን ድረስ ይሖዋ በፍጹም እንደማይረሳን ወይም እንደማይተወን ዋስትና ይኖረናል። — ዕብራውያን 6:10–12
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በግሪክኛ “እንቅፋት” የሚለው ቃል (ስካንዳሎን) መሠረታዊ ትርጉሙ “ማጥመጃው ምግብ የሚቀመጥበትን የአንድን ወጥመድ ክፍል ስለሚያመለክት መጥለፊያውን ወይም ማጥመጃውን ራሱን ያመለክታል።” — ቫይንስ ኤክፖሲተርስ ኦቭ ኦልድ ኤንድ ኒው ቴስታመንት ዎርድስ
ምን ሐሳብ ትሰጣለህ?
◻ ጴጥሮስ ሳይታወቀው የራስን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረጉ መንገድ እንቅፋት የሆነው እንዴት ነበር?
◻ ራስን መካድ ማለት ምን ማለት ነው?
◻ አንድ ክርስቲያን የራሱን የመከራ እንጨት የሚሸከመው እንዴት ነው?
◻ የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግን መንፈስ ልናዳብርና ልንይዝ የምንችለው እንዴት ነው?
◻ የራስን ጥቅም መሥዋዕት ከማድረግ መንፈስ በስተጀርባ ያለው የሚገፋፋ ኃይል ምንድን ነው?
[በገጽ 10 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ራስህን ለመካድ፣ የመከራህን እንጨት ለመሸከምና ያለማቋረጥ ኢየሱስን ለመከተል ፈቃደኛ ነህን?