ያለማቋረጥ ኢየሱስን ተከተሉ
1 በአንድ ወቅት ኢየሱስ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ የመከራውንም እንጨት ተሸክሞ ያለማቋረጥ ይከተለኝ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 16:24 NW ) ኢየሱስ ለተናገራቸው ቃላት አዎንታዊ ምላሽ መስጠት እንደምንፈልግ የተረጋገጠ ነው። ኢየሱስ ያቀረበው ግብዣ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ እንመርምር።
2 “ራሱን ይካድ”:- ሕይወታችንን ለይሖዋ በወሰንበት ጊዜ ራሳችንን ክደናል። “መካድ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክኛ ቃል “እምቢ ማለት” የሚል መሠረታዊ ትርጉም አለው። ይህም ማለት ለዘላለም ይሖዋን ለማስደሰት ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ ፍላጎታችንን፣ ምኞታችንን፣ ምቾታችንንና በራስ ወዳድነት ላይ የተመሠረቱ ደስታዎችን በፈቃደኝነት መተው ማለት ነው።— ሮሜ 14:8፤ 15:3
3 ‘የመከራውንም እንጨት ይሸከም’:- የክርስቲያኖች ሕይወት መሥዋዕትነት የሚጠይቀውን ለይሖዋ የሚቀርበው አገልግሎት የሚያስከትለውን የመከራ እንጨት መሸከምን የሚጨምር ነው። ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የሚንጸባረቅበት አንደኛው መንገድ ራስን ለአገልግሎቱ ለማዋል ጥረት ማድረግ ነው። በዚህ ዓመት እስከ አሁን ድረስ ብዙ አስፋፊዎች በረዳት አቅኚነት በማገልገል ላይ ናቸው። አንተም ከእነሱ አንዱ ልትሆን ስለምትችል የምታገኛቸው በረከቶች ከከፈልከው መሥዋዕትነት በእጅጉ እንደሚበልጡ ልታረጋግጥ ትችላለህ። ረዳት አቅኚ ሆነው ማገልገል የማይችሉ የጉባኤ አስፋፊዎች በስብከቱ ሥራ ላይ ረዘም ያለ ሰዓት ለማሳለፍ አዘውትረው ዝግጅት ያደርጋሉ። ይህን ግብ በአእምሯቸው በመያዝ አንዳንድ ጉባኤዎች የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባቸውን ከዚህ ቀደም ያደርጉት ከነበረው ሰዓት ጥቂት ደቂቃዎች ቀደም ብለው ለማድረግ ፕሮግራም ያወጣሉ። በተጨማሪም አንዳንዶች ‘ተጨማሪ አንድ ቤት’ ለማንኳኳት ወይም ‘ጥቂት ደቂቃዎች አክለው’ ለመሥራት በመወሰናቸው አስደናቂ ውጤት አግኝተዋል።
4 የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ የሚታይበት ሌላኛው መንገድ የግል ግቦችን ማውጣት ነው። አንዳንዶች ጥንቃቄ የተሞላበት እቅድ በማውጣትና ፕሮግራማቸውን በማስተካከል የዘወትር አቅኚ ለመሆን ችለዋል። ሌሎችም ለቤቴል አገልግሎት ወይም ለመንግሥት አዳራሽ ግንባታ ሥራ ራሳቸውን ለማቅረብ ሁኔታዎቻቸውን አስተካክለዋል። አንዳንዶችም የመንግሥቱ አስፋፊዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ ሄደዋል።
5 “ያለማቋረጥ ይከተለኝ”:- የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ብዙ መከራዎች ቢደርሱባቸውም እንኳ ኢየሱስ በአገልግሎቱ ወቅት ያሳየው ቅንዓትና ጽናት አበረታቷቸዋል። (ዮሐ. 4:34) እርሱ በመካከላቸው በመገኘቱና በመልእክቱ መንፈሳቸው ታድሷል። እርሱን የተከተሉት ሁሉ እውነተኛ ደስታ ይንጸባረቅባቸው የነበረው በዚህ የተነሳ ነው። (ማቴ. 11:29) እኛም በተመሳሳይ ተወዳዳሪ በሌለው በመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በጽናት ለመካፈል እርስ በርሳችን እንበረታታ።
6 የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ በማዳበር ኢየሱስ ያለማቋረጥ እንድንከተለው ላቀረበልን ጥሪ አዎንታዊ ምላሽ የምንሰጥ እንሁን። እንዲህ ስናደርግ በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ደስታ የምናገኝ ሲሆን ወደፊት ደግሞ የተትረፈረፉ በረከቶችን ለማግኘት በጉጉት ልንጠባበቅ እንችላለን።