የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w92 2/1 ገጽ 25-28
  • ራስን የመሠዋት መንፈስ ይኑራችሁ!

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ራስን የመሠዋት መንፈስ ይኑራችሁ!
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የመጽሐፍ ቅዱስ ብቃት ነው
  • ራስን ከመሠዋት የሚመጡ በረከቶች
  • ራሳችንን መሥዋዕት የምናደርግባቸው መንገዶች
  • የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግን መንፈስ በመያዝ ይሖዋን ማገልገል
    መጠበቂያ ግንብ—1993
  • የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ ማሳየት አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
  • የራስን ጥቅም የመሠዋት መንፈስ አላችሁን?
    የመንግሥት አገልግሎታችን—2000
  • ይሖዋን የሚያስደስቱ የምሥጋና መሥዋዕቶች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—2000
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1992
w92 2/1 ገጽ 25-28

ራስን የመሠዋት መንፈስ ይኑራችሁ!

ሮልፍa ተወዳጅ ሠራተኛ ነበር። በክርስቲያናዊ አገልግሎቱ የሚያበረክተውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ ፈልጎ የትርፍ ሰዓት ሥራ እንዲሰጠው በጠየቀ ጊዜ አሠሪው በፍጥነት ተባበረው። በዚህም ምክንያት ሮልፍ ለበርካታ ዓመታት በአቅኚነት አገልግሎት ለመደሰት ችሏል። ይሁንና አንድ ቀን የሥራው ሁኔታ ተለወጠ። ሮልፍ በሥራው ከፍተኛ ብቃት እንዳለው ስላስመሰከረ በኩባንያው ውስጥ የሽያጭ ሥራ አስኪያጅ የመሆን ሹመት ተሰጠው። ሥራው የሚያጓጓ ደመወዝና ወደፊትም ተጨማሪ ዕድገቶች ሊያገኝ የሚያስችለውን አጋጣሚ ይዞለት ነበር። ይሁን እንጂ ይህን ሹመት ከተቀበለ የሚሠራው ሥራ በትርፍ ሰዓት ብቻ የተወሰነ አይሆንም።

ሮልፍ የሚያስተዳድራቸው ሚስትና ሁለት ልጆች ስላሉት የሚያገኘው ተጨማሪ ገንዘብ ሊጠቅመው ይችል ነበር። ይሁን እንጂ የቀረበለትን ዕድገት አልቀበልም ብሎ መንፈሳዊና ሥጋዊ ግዴታዎቹን ለማሟላት የሚያስችለው ሌላ ሥራ እንዲሰጠው ማመልከቻ አቀረበ። የሮልፍ አሠሪ በውሣኔው ተገረመ። አሠሪው ለሮልፍ ከፍተኛ ደመወዝ መስጠት እንኳን ሐሳቡን ሊያስቀይረው እንደማይችል ስለተገነዘበ “ከጽኑ እምነትህ ጋር መወዳደር እንዳልቻልኩ አውቄአለሁ” አለው።

አዎን ሮልፍ ጽኑ እምነት ነበረው። ነገር ግን ሌላም ባሕርይ ነበረው። እርሱም ራስን የመሠዋት መንፈስ ነው። እንዲህ ዓይነቱ መንፈስ ለራስ ጥቅም ተገዥ በሆነው ዓለማችን ውስጥ እንደ ብርቅ የሚታይ ነው። ቢሆንም ይህ መንፈስ ጠቃሚና አርኪ ወደሆነ ሕይወት ሊመራ የሚችል ነው። ራስን የመሠዋት መንፈስ ምንድን ነው? ምንስ ይጠይቃል? ይህን መንፈስ ይዘን ለመኖርስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?

የመጽሐፍ ቅዱስ ብቃት ነው

መሠዋት ማለት አንድ ዋጋማ የሆነን ነገር መተው ወይም አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። መሥዋዕት “ከበጐቹ በኩራት” ለአምላክ መሥዋዕት ካቀረበው ከመጀመሪያው ታማኝ ምሥክር ከአቤል ጀምሮ የንጹሕ አምልኮ ክፍል ሆኖ ቆይቷል። (ዘፍጥረት 4:4) እንደ ኖህና ያዕቆብ የመሳሰሉት የእምነት ሰዎችም እንደዚሁ አድርገዋል። (ዘፍጥረት 8:20፤ 31:54) የእንስሳት መሥዋዕት የሙሴ ሕግ አንድ አስፈላጊ ገጽታ ነበር። (ዘሌዋውያን 1:2-4) በዚህ ሕግ ሥር የነበሩ አምላኪዎች ካላቸው ነገር ምርጥ ምርጡን እንዲያቀርቡ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸው ነበር። እንከን ያለበት እንስሳ መሥዋዕት አድርገው እንዲያቀርቡ አይፈቀድላቸውም ነበር። (ዘሌዋውያን 22:19, 20፤ ዘዳግም 15:21) ከሐዲዎቹ እሥራኤላውያን ይህን ሕግ በጣሱ ጊዜ አምላክ “ዕውር መስዋዕትንም ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? አንካሳውንና የታመመውን ስታቀርቡ ይህ ክፉ አይደለምን? ያንን ለአለቃህ አቅርብ በውኑ በአንተ ደስ ይለዋልን? ወይስ ፊትህን ይቀበላልን? . . . በውኑ ከእጃችሁ ይህን ልቀበለውን?” በማለት ገስጿቸዋል። ሚልክያስ 1:8, 13

መሥዋዕት የማቅረብ መሠረታዊ ሥርዓት ወደ ክርስቲያናዊው አምልኮም ተላልፏል። ይሁን እንጂ ክርስቶስ ሙሉ የቤዛ ዋጋ ስለከፈለ የእንስሳ መሥዋዕት ማቅረብ ከዚህ ጊዜ ወዲህ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ አክትሞአል። ታዲያ ክርስቲያኖች ተቀባይነት ባለው መንገድ መሠዋት የሚችሉት ምንድን ነው? ጳውሎስ በሮሜ 12:1 ላይ “እንግዲህ ወንድሞች ሆይ ሰውነታችሁን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝና ሕያው ቅዱስም መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ (በማሰብ ኃይላችሁ ቅዱስ አገልግሎት እንድታቀርቡ) በእግዚአብሔር ርኅራኄ እለምናችኋለሁ” በማለት ጽፏል። እንዴት የሚያስደንቅ ለውጥ ነው! ክርስቲያኖች በድን እንስሳትን በመሠዋት ፈንታ የገዛ ራሳቸውን የጉልበታቸውን፣ የንብረታቸውንና የችሎታቸውን ሕያው መሥዋዕት ማቅረብ ሊኖርባቸው ነው። ይሖዋ ከእሥራኤላውያን እጅ “አንካሳውን” እንዳልተቀበለ ሁሉ ዛሬም “አንካሳውን” ወይም የግማሽ ልብ መሥዋዕት አይቀበልም። አምላኪዎቹ ምርጥ የሆነውን እንዲሰጡት፣ ማለትም በሙሉ ልባቸው፣ ነፍሳቸው ሐሳባቸውና ኃይላቸው እንዲያገለግሉት ይጠይቃል።—ማርቆስ 12:30

በመሆኑም ራስን የመሠዋት መንፈስ ለስብሰባ ፕሮግራሞችና ለክርስቲያናዊ አገልግሎት ሥራ ራስን ከማስገዛት የበለጠ ነገርን የሚጠይቅ ነው። የመጣው ቢመጣ የአምላክን ፈቃድ ለመፈጸም መቁረጥ ማለት ነው። ችግርና መከራን ለመቀበል ዝግጁ መሆን ማለት ነው። ኢየሱስ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር ራሱን ይካድ፤ [የመከራውንም እንጨት (አዓት)] ተሸክሞ ይከተለኝ” ብሏል። (ማቴዎስ 16:24) አንድ ክርስቲያን ዋናው የሚያሳስበው ጉዳይ የግል ምቾት ወይም የሃብት ማካበት ግብ እንዲሆን አይፈቅድም። ሕይወቱ የሚያተኩረው የእግዚአብሔርን መንግሥትና ጽድቁን አስቀድሞ በመፈለግ ላይ ነው። (ማቴዎስ 6:33) አስፈላጊ ከሆነ የመከራውን እንጨት ለመሸከም ማለትም ስደት፣ ውርደት፣ ሞትም እንኳን ሳይቀር ለመቀበል የተዘጋጀ ነው!

ራስን ከመሠዋት የሚመጡ በረከቶች

አንድ ሰው እንዲህ ዓይነት አሳሳቢ አጋጣሚዎች ሲደቀኑበት ራስን መሠዋት አስፈላጊ ስለመሆኑ ሊጠራጠር ይችላል። ራስን መሠዋት ይሖዋ አምላክን ለሚወዱና ስሙ ተከብሮ ለማየት ለሚመኙ ሁሉ በእርግጥ አስፈላጊ ነው። (ማቴዎስ 22:37) ኢየሱስ ክርስቶስ የተወልንን ፍጹም ምሳሌ አስብ። ወደ ምድር ከመምጣቱ አስቀድሞ በሰማይ መንፈሳዊ ፍጡር ስለነበረ ከፍ ያለ ቦታ ነበረው። ይሁን እንጂ ለደቀመዛሙርቱ እንደነገራቸው “የአባቱን ፈቃድ እንጂ የራሱን ፈቃድ አልፈለገም።” (ዮሐንስ 5:30) ስለዚህ በፈቃደኝነት “የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ። በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ። ለሞትም ይኸውም [በመከራ እንጨት ላይ ለመሞት እንኳን (አዓት)] የታዘዘ ሆነ።”—ፊልጵስዩስ 2:7, 8

እንዲህ ዓይነት መሥዋዕቶች ፍሬ ቢስ ሆነው አልቀሩም። ኢየሱስ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ለመስጠት” ፈቃደኛ በመሆኑ የቤዛውን ዋጋ ሊከፍል ስለቻለ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች በሰማይ ሕያው ሆኖ መኖርን ወይም በምድር ላይ ዘላለማዊ ሕይወትን ለማግኘት እንዲችሉ አድርጎአል። (ዮሐንስ 3:16፤ 15:13፤ 1 ዮሐንስ 2:2) የታማኝነት አቋሙን በተሟላ ሁኔታ በመጠበቁ የይሖዋ ስም እጅግ እንዲመሰገን አድርጓል። (ምሳሌ 27:11) እንግዲያውስ የኢየሱስን ራስን የመሠዋት አካሄድ ይሖዋ መባረኩ ምንም አያስደንቅም! “በዚህ ምክንያት ደግሞ እግዚአብሔር ያለልክ ከፍ ከፍ አደረገው። ከስምም ሁሉ በላይ ያለውን ስም ሰጠው።”—ፊልጵስዩስ 2:9

እርግጥ ኢየሱስ የአምላክ አንድያ ልጅ ነበር። ታዲያ አምላክ ለሱ ሲሉ መሥዋዕት ለሚያደርጉ ሌሎች ሰዎችስ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋልን? አዎን፣ ይሰጣቸዋል። ይህም ጥንታዊም ሆነ ዘመናዊ በሆኑ ብዙ ምሳሌዎች ተገልጿል። ስለ ሞአባዊቱ ሩት የሚገልጸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ አስብ። በግልጽ እንደሚታየው ሩት በእሥራኤላዊ ባሏ አማካኝነት ስለ ይሖዋ አውቃለች። እሱ ከሞተ በኋላ ውሳኔ ማድረግ ነበረባት። በተወለደችበት አረማዊ አገር ትቀር ይሆን ወይስ በዕድሜ ከገፋችው አማቷ ከናዖሚ ጋር ወደ ተስፋይቱ ምድር ትሄድ ይሆን? ሩት ከአማቷ ጋር ወደ ተስፋይቱ ምድር መሄዷ ከወላጆቿ ጋር አብራ የመሆንና ምናልባትም ወደፊት እንደገና የማግባት አጋጣሚዋን መሠዋት ማለት ቢሆንም እሱኑ መርጣለች። ይሁን እንጂ ሩት ይሖዋን አውቃለች። በምርጥ ሕዝቦቹ መሃል ሆና እሱን የማምለክ ፍላጎቷ ከናዖሚ እንዳትለያይ አነሳስቷታል።

ታዲያ ሩት ለእንዲህ ዓይነቱ ራስን የመሠዋት መንፈስ ዋጋ አግኝታበታለችን? በእርግጥ አግኝታበታለች። ከጊዜ በኋላ አንድ ቦኤዝ የሚባል ባለመሬት ሚስት አድርጎ ወሰዳትና ሩት ኢዮቤድ የሚባል ልጅ ወለደች። በሱም በኩል የኢየሱስ ክርስቶስ ቅድመ አያት ለመሆን በቅታለች።—ማቴዎስ 1:5, 16

በተመሳሳይም በዘመናችን ያሉ ራሳቸውን የሚሠዉ የአምላክ አገልጋዮችም በረከቶችን አግኝተዋል። ለምሳሌ ያህል በ1923 ይበልጥ “ባይብል” ብራውን በመባል ይታወቅ የነበረው ዊሊያም አር ብራውን በምዕራብ አፍሪካ የስብከቱን ሥራ በግንባር ቀደምትነት ለማከናወን በዌስት ኢንዲስ የሚገኘውን ቤቱን ትቶ ሄደ። ከእርሱ ጋር የሄዱት ሚስቱና ሴት ልጁ ነበሩ። በኋላም የስብከቱ ሥራ ገና ፍሬ ማፍራት ወደጀመረበት ወደ ናይጄሪያ ሄደ። “ባይብል” ብራውን ቪንሴንት ሳሙኤል ከተባለ አንድ ጥቁር አሜሪካዊና ክላውድ ብራውን ከተባለ የዌስት ኢንዲስ ተወላጅ የሆነ ምስክር ጋር ሆኖ በምዕራብ አፍሪካ በሥራው የመጀመሪያ ደረጃ ወቅት ጠቃሚ ሚና ተጫውቷል።

ዛሬ “ባይብል” ብራውንና ተባባሪዎቹ ባቀኑአቸው በሴራሊዮን በላይቤሪያ፣ በጋናና በናይጄሪያ ክልሎች ከ187,000 በላይ አስፋፊዎች በማገልገል ላይ ናቸው። “ባይብል” ብራውን በ1967 ከመሞቱ በፊት “ወንዶችና ሴቶች ለአምላክ መንግሥት የምሥራች ታዛዦች ሲሆኑ ማየት እንዴት ደስ ይላል!” ብሎ ነበር። አዎ፣ ራስን መሥዋዕት የማድረግን አካሄድ ስለተከተለ እጅግ ተባርኮ ነበር።

ራሳችንን መሥዋዕት የምናደርግባቸው መንገዶች

በዛሬው ጊዜ ይህንን መንፈስ ልናሳይ የምንችልባቸው አንዳንድ መንገዶች ምንድን ናቸው? አንዱ መንገድ በየሳምንቱ ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት መካፈል ነው። (ሥራ 20:20) በዚህ ሥራ መካፈል በተለይም በዓለማዊ ሥራ ሲደክሙ ከሰነበቱ በኋላ ቀላል ላይሆን ይችላል። ራስን መገሰጽንና ጥሩ ፕሮግራም ማውጣትን ይጠይቅ ይሆናል። ነገር ግን ሊያጋጥመን ከሚችለው ከማንኛውም ችግር ይልቅ የሚገኘው ደስታ ያመዝናል። አንተም አንድ ሰው “በሕያው እግዚአብሔር መንፈስ እንጂ በቀለም ሳይሆን፣ ሥጋ በሆነ ልብ ጽላት እንጂ በድንጋይ ጽላት ያልተጻፈ . . . የክርስቶስ መልእክት (ደብዳቤ) እንዲሆን” የመርዳት መብት ይኖርሃል።—2 ቆሮንቶስ 3:3

አንዳንዶች በዓለማዊ ሥራ ወይም በመዝናኛዎች የሚያሳልፉትን ጊዜ በጥንቃቄ “በመዋጀት” በስብከቱ ሥራ ያላቸውን ድርሻ ከፍ አድርገዋል። (ኤፌሶን 5:16) ብዙዎች ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ በረዳት አቅኚነት አገልግሎት ለመካፈል እንዲችሉ ፕሮግራማቸውን አስተካክለዋል። ሌሎችም በተከታታይ በረዳት አቅኚነት ወይም በዘወትር አቅኚነት ለማገልገል ይችላሉ። ሊታሰብበት የሚገባው ሌላው ተጨማሪ መሥዋዕት የመንግሥት አስፋፊዎች ወደሚያስፈልጉበት አካባቢ መዛወር ነው። ይህም አብዛኛውን ጊዜ በአኗኗር ላይ ከፍተኛ ለውጥ ማድረግን፣ ከአዲስ ልማድና ባሕል ጋር መለማመድን ይጠይቃል። ይሁንና ሌሎች ሕይወት እንዲያገኙ በመርዳት ሥራ ሙሉ ድርሻ ማበርከት የሚያስገኛቸው በረከቶች እንዲህ ዓይነቶቹ መሥዋዕቶች ዋጋ ያላቸው እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

የካናዳ ተወላጅ የሆነው ጆን ካትፎርዝ በግል ተሞክሮው የዚህን እውነትነት ተገንዝቦአል። ከጊሊያድ የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ቤት ከተመረቀ በኋላ ሚስዮናዊ ሆኖ አውስትራሊያ ተመደበ። “ይህ አገር ከአገሬ በጣም የራቀ ነበር!” በማለት ካትፎርዝ ያስታውሳል። “ወላጆቼንና ወዳጆቼን ለማየት ከአርማጌዶን በፊት ወደ ካናዳ መመለስ እችል ይሆን? መልሱን ለማግኘት የሚቻለው እዚያ በመሄድ ብቻ ነበር።” ወንድም ካትፎርዝ ሄደ። ባደረጋቸው መሥዋዕቶች አልተጸጸተም። እስከ አሁን በቅንዓት እያገለገለ ባለበት በፓፑዋ ኒው ጊኒ የስብከቱን ሥራ በግምባር ቀደምትነት አካሂዷል። አሁን በሙሉ ጊዜ አገልግሎት 50 ዓመት ያህል አሳልፎአል። አንድ ወቅት “ሁልጊዜ የይሖዋን መሪነት ለመከተል መፈለግ፣ እሱ ይስማማሃል ብሎ የሰጠውን ማንኛውንም ዓይነት የሥራ ምድብ መቀበል ደስታ፣ እርካታና ቁጥር ስፍር የሌላቸው ወዳጆችን ያስገኛል” ብሎ ነበር።

በእርግጥ እንደ ጤና፣ ገንዘብና የቤተሰብ ግዴታዎች የመሳሰሉት ሁኔታዎች ልታደርገው የምትችለውን ነገር ሊወስኑብህ ይችሉ ይሆናል። ሁሉም ሰዎች አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ሆነው ማገልገል አይችሉም። ይሁን እንጂ መጥፎ ያየር ጠባይን የመሳሰሉ ጥቃቅን ችግሮች ከስብሰባና ከመስክ አገልግሎት እንዲያስቀሩህ ባለመፍቀድ የሚቻልህን ያህል ሙሉ ተሳትፎ እንዲኖርህ ቁረጥ። (ዕብራውያን 10:24, 25) የአምላክን ቃል ለማጥናት የበለጠ ጊዜ መሥዋዕት ለማድረግ ትችል ይሆናል። አንዳንድ ቤተሰቦች የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን በመመልከት የሚጠፋውን ጊዜ በመቀነስ ምናልባትም በየሳምንቱ ቴሌቪዥን የማይመለከቱበት ምሽት እንዲኖር በመወሰን ወይም ጭራሹኑ ቴሌቪዥን እንዲኖራቸው ባለማድረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ያደርጋሉ። ለግል ጥናት ጊዜ መመደብህ በስብሰባና በመስክ አገልግሎት “ለስሙ የምትመሠክርበትን የከንፈር መሥዋዕት” ይበልጥ ከፍ ያለ ጥራት ያለው መሥዋዕት እንዲሆን ሊያደርግልህ ይችላል።—ዕብራውያን 13:15

በአሁኑ ጊዜ የስብከቱ ሥራ በመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውስ። አምላክ በቅርቡ በዚህ ስስታምና ለራሱ ጥቅም ተገዥ በሆነ ዓለም ላይ ፍርዱን ያመጣል። (ሶፎንያስ 2:3) የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ከፈለግን ጉልበታችንን ቆጣቢዎች ልንሆን አንችልም። “ሰውነታችንን ሕያው ቅዱስና በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሥዋዕት አድርገን ማቅረብ” አለብን። (ሮሜ 12:1) እንዲህ ዓይነቱ መንፈስ ከፍተኛ ደስታና እርካታ ያስገኛል። በአገልግሎታችን ከፍተኛ ደስታ እንድናገኝ ይረዳናል። የይሖዋንም ልብ ያስደስታል!—ምሳሌ 27:11

ስለዚህ ራስን የመሠዋት መንፈስ ይኑራችሁ! ራሳችሁን ለሌሎችና ለመንግሥቱ ፍላጎቶች ድጋፍ ለመስጠት ከማቅረብ አታመንቱ። ጳውሎስ “መልካም ማድረግንና ለሌሎችም ማካፈልን አትርሱ። እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና” በማለት በጥብቅ አሳስቧል።—ዕብራውያን 13:16

[የግርጌ ማስታወሻዎች]

a ስሙ ተለውጧል።

[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ለግል ጥናትና ለመስክ አገልግሎት ጊዜ መመደብ መሥዋዕትን ይጠይቅ ይሆናል፤ ነገር ግን ከፍተኛ ሽልማት ያስገኛል።

[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ደብልዩ አር ብራውንና ጆን ካትፎርዝ ራሳቸውን መሥዋዕት በማድረጋቸው በብዙ ተባርከዋል።

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ